መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን (Song of Solomon)
እሱ ተከታታይ ጅማሬዎችን ያሳያል – የዓለም መጀመሪያ ፣ የሰው ልጅ እና እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የገባውን ቃል ኪዳን። የመጀመሪያው መጽሐፍ ዘፍጥረት በእግዚአብሔር ዓለም ፍጥረት ተከፈተ። የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ባለመታዘዙ የሰው ልጅ ብዛት ወደ ተለያዩ ብሔሮች እና ቋንቋዎች ሲከፋፈል ፍጹምው ዓለም በክፋት ውስጥ ይወድቃል።
መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን (Song of Solomon)
1 ፤ ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር።
2 ፤ በአፉ መሳም ይሳመኝ፥ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና።
3 ፤ ዘይትህ መልካም መዓዛ አለው፤ ስምህ እንደሚፈስስ ዘይት ነው፤ ስለዚህ ደናግል ወደዱህ።
4 ፤ ሳበኝ፥ ከአንተም በኋላ እንሮጣለን፤ ንጉሡ ወደ ቤቱ አገባኝ በአንተ ደስ ይለናል፥ ሐሤትም እናደርጋለን፤ ከወይን ጠጅ ይልቅ ፍቅርህን እናስባለን፤ በቅንነት ይወድዱሃል።
5 ፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እኔ ጥቁር ነኝ፤ ነገር ግን ውብ ነኝ፥ እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞንም መጋረጃዎች።
6 ፤ ፀሐይ መልኬን አክስሎታልና፤ ጥቁር ስለ ሆንሁ አትዩኝ፤ የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ፥ የወይን ቦታዎችንም ጠባቂ አደረጉኝ፤ ነገር ግን የእኔን ወይን ቦታ አልጠበቅሁም።
7 ፤ ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ፤ ወዴት ታሰማራለህ? በቅትርስ ጊዜ ወዴት ትመስጋለህ? ስለ ምንስ ከባልንጀሮችህ መንጎች በኋላ እቅበዘበዛለሁ?
8 ፤ አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ያላወቅሽ እንደ ሆነ የመንጎችን ፍለጋ ተከትለሽ ውጪ፥ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞች ድንኳኖች አጠገብ አሰማሪ።
9 ፤ ወዳጄ ሆይ፥ በፈርዖን ሰረገሎች እንዳለ ፈረስ መሰልሁሽ።
10 ፤ የጕንጭሽ ውበት በከበረ ሉል፥ አንገትሽም በዕንቍ ድሪ ያማረ ነው።
11 ፤ ባለ ብር ጕብጕብ የሆነ የወርቅ ጠልሰም እናደርግልሻለን።
12 ፤ ንጉሡ በማዕዱ ሳለ፥ የእኔ ናርዶስ መዓዛውን ሰጠ።
13 ፤ ውዴ ለእኔ በጡቶቼ መካከል እንደሚያርፍ እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው።
14 ፤ ውዴ ለእኔ በዓይንጋዲ ወይን ቦታ እንዳለ እንደ አበባ እቅፍ ነው።
15 ፤ ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፤ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፤ ዓይኖችሽም እንደ ርግቦች ናቸው።
16 ፤ ውዴ ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ውብ ነህ፥ መልከ መልካምም ነህ፤ አልጋችንም ለምለም ነው።
17 ፤ የቤታችን ሰረገላ የዝግባ ዛፍ ነው፥ የጣሪያችንም ማዋቀሪያ የጥድ ዛፍ ነው።
1 ፤ እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ።
2 ፤ በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥ እንዲሁ ወዳጄ በቈነጃጅት መካከል ናት።
3 ፤ በዱር እንዳለ እንኮይ፥ እንዲሁ ውዴ በልጆች መካከል ነው። ከጥላው በታች እጅግ ወድጄ ተቀመጥሁ፥ ፍሬውም በጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው።
4 ፤ ወደ ወይን ጠጁም ቤት አገባኝ፥ በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው።
5 ፤ በዘቢብም አጽናኑኝ፥ በእንኮይ አበረታቱኝ፥ በፍቅሩ ተነድፌ ታምሜያለሁና።
6 ፤ ግራው ከራሴ በታች ናት፥ ቀኙም ታቅፈኛለች።
7 ፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ፥ ፍቅርን እንዳታስነሱትና እንዳታነሣሡት በሚዳቋ በምድረ በዳም ዋላ አምላችኋለሁ።
8 ፤ እነሆ፥ የውዴ ቃል! በተራሮች ላይ ሲዘልል፥ በኮረብቶችም ላይ ሲወረወር ይመጣል።
9 ፤ ውዴ ሚዳቋን ወይም የዋላን እምቦሳ ይመስላል፤ እነሆ፥ በመስኮቶች ሲጐበኝ፥ በዓይነ ርግብም ሲመለከት፥ እርሱ ከቅጥራችን በኋላ ቆሞአል።
10 ፤ ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ። ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ።
11 ፤ እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ።
12 ፤ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ፥ የቊርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ።
13 ፤ በለሱ ጐመራ፥ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፤ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ።
14 ፤ በዓለት ንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግብ ሆይ፥ ቃልሽ መልካም ፊትሽም ያማረ ነውና መልክሽን አሳዪኝ፥ ድምፅሽንም አሰሚኝ።
15 ፤ ወይናችን አብቦአልና የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ቀበሮች፥ ጥቃቅኑን ቀበሮች አጥምዳችሁ ያዙልን።
16 ፤ ውዴ የእኔ ነው፥ እኔም የእርሱ ነኝ፤ በሱፍ አበባዎች መካከልም መንጋውን ያሰማራል።
17 ፤ ውዴ ሆይ፥ ቀኑ እስኪነፍስ፥ ጥላውም እስኪሸሽ ድረስ ተመለስ፤ በቅመም ተራራ ላይ ሚዳቋውን ወይም የዋላውን እምቦሳ ምሰል።
1 ፤ ሌሊት በምንጣፌ ላይ ነፍሴ የወደደችውን ፈለግሁት፤ ፈለግሁት አላገኘሁትም።
2 ፤ እነሣለሁ በከተማይቱም እዞራለሁ፥ ነፍሴ የወደደችውን በጎዳናና በአደባባይ እፈልጋለሁ፤ ፈለግሁት አላገኘሁትም።
3 ፤ ከተማይቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፤ ነፍሴ የወደደችውን አያችሁትን? አልኋቸውም።
4 ፤ ከእነርሱም ጥቂት እልፍ ብዬ ነፍሴ የወደደችውን አገኘሁት፥ ያዝሁትም ወደ እናቴም ቤት ወደ ወላጅ እናቴም እልፍኝ እስካገባው ድረስ አልተውሁትም።
5 ፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ፥ ፍቅርን እንዳታስነሡትና እንዳታነሣሡት በሚዳቋ በምድረ በዳም ዋላ አምላችኋለሁ።
6 ፤ መዓዛም እንደ ከርቤና እንደ ዕጣን የሆነችው፥ ከልዩ ከነጋዴ ቅመም ሁሉ የሆነችው፥ ይህች ከምድረ በዳ እንደ ጢስ ምስሶ የወጣችው ማን ናት?
7 ፤ እነሆ፥ የሰሎሞን አልጋ ናት፤ ከእስራኤል ኃያላን ስድሳ ኃያላን በዙሪያው ናቸው።
8 ፤ ሁሉም ሰይፍ የያዙ ሰልፈኞች ናቸው፤ በሌሊት ከሚወድቀው ፍርሃት የተነሣ ሰው ሁሉ ሰይፉ በወገቡ አለ።
9 ፤ ንጉሡ ሰሎሞን መሸከሚያን ከሊባኖስ እንጨት ለራሱ አሠራ።
10 ፤ ምሰሶቹን የብር፥ መደገፊያውንም የወርቅ፥ መቀመጫውንም ሐምራዊ ግምጃ አደረገ፤ ውስጡ በኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ፍቅር የተለበጠ ነው።
11 ፤ እናንተ የጽዮን ቈነጃጅት፥ ውጡ፤ እናቱ በሠርጉ ቀንና በልቡ ደስታ ቀን ያደረገችለትን አክሊል ደፍቶ ንጉሥ ሰሎሞንን እዩ።
1 ፤ ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፤ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፤ በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ዓይኖችሽ እንደ ርግቦች ናቸው፤ ጠጕርሽ በገለዓድ ተራራ እንደሚወርድ እንደ ፍየል መንጋ ነው።
2 ፤ ጥርሶችሽ ታጥበው እንደ ተሸለቱ ሁሉም መንታ እንደ ወለዱ ከእነርሱም መካን እንደሌለባቸው መንጎች ናቸው።
3 ፤ ከንፈሮችሽ እንደ ቀይ ሐር ፈትል ናቸው፥ አፍሽም ያማረ ነው፤ በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ጕንጭና ጕንጭሽ እንደ ተከፈለ ሮማን ናቸው።
4 ፤ አንገትሽ ለሰልፍ ዕቃ መስቀያ እንደ ተሠራው እንደ ዳዊት ግንብ ነው፤ ሺህ ጋሻ የኃያላንም መሣሪያ ሁሉ ተንጠልጥሎበታል።
5 ፤ ሁለቱ ጡቶችሽ መንታ እንደ ተወለዱ፥ በሱፍ አበባ መካከል እንደሚሰማሩ እንደ ሚዳቋ ግልገሎች ናቸው።
6 ፤ ቀኑ እስኪነፍስ ጥላውም እስኪያልፍ ድረስ፥ ወደ ከርቤው ተራራ ወደ ዕጣኑም ኮረብታ እሄዳለሁ።
7 ፤ ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ ነውርም የለብሽም።
8 ፤ ሙሽራዬ ሆይ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከአማና ራስ ከሳኔርና ከኤርሞን ራስ፥ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች።
9 ፤ እኅቴ ሙሽራ ሆይ፥ ልቤን በደስታ አሳበድሽው፤ አንድ ጊዜ በዓይኖችሽ፥ ከአንገትሽ ድሪ በአንዱ ልቤን በደስታ አሳበድሽው።
10 ፤ እኅቴ ሙሽራ ሆይ፥ ፍቅርሽ እንዴት መልካም ነው! ፍቅርሽ ከወይን ጠጅ ይልቅ እንዴት ይሻላል! የዘይትሽም መዓዛ ከሽቱ ሁሉ!
11 ፤ ሙሽራዬ ሆይ፥ ከከንፈሮችሽ ማር ይንጠበጠባል፤ ከምላስሽ በታች ማርና ወተት አለ፥ የልብስሽም መዓዛ እንደ ሊባኖስ ሽታ ነው።
12 ፤ እኅቴ ሙሽራ የተቈለፈ ገነት፥ የተዘጋ ምንጭ የታተመም ፈሳሽ ናት።
13 ፤ ቡቃያሽ ሮማንና የተመረጠ ፍሬ፥ ቆዕ ከናርዶስ ጋር ያለበት ገነት ነው፥
14 ፤ ናርዶስ ከቀጋ ጋር፥ የሽቱ ሣርና ቀረፋ፥ ከልዩ ልዩ ዕጣን ጋር፥ ከርቤና እሬት ከክቡር ሽቱ ሁሉ ጋር።
15 ፤ አንቺ የገነት ምንጭ፥ የሕይወት ውኃ ጕድጓድ፥ ከሊባኖስም የሚፈስስ ወንዝ ነሽ።
16 ፤ የሰሜን ነፋስ ሆይ፥ ተነሥ፥ የደቡብም ነፋስ ና፤ በገነቴ ላይ ንፈስ፥ ሽቱውም ይፍሰስ፤ ውዴ ወደ ገነቱ ይግባ፥ መልካሙንም ፍሬ ይብላ።
1 ፤ እኅቴ ሙሽራዬ ሆይ፥ ወደ ገነቴ ገባሁ፥ ከርቤዬን ከሽቱዬ ጋር ለቀምሁ፥ እንጀራዬን ከማሬ ጋር በላሁ፥ የወይን ጠጄን ከወተቴ ጋር ጠጣሁ። ባልንጀሮቼ ሆይ፥ ብሉ፤ ወዳጄ ሆይ፥ ጠጪ፤ እስክትረኪ ድረስ ጠጪ።
2 ፤ እኔ ተኝቻለሁ፥ ልቤ ግን ነቅቶአል፤ የውዴ ቃል ነው፥ እርሱም ደጁን ይመታል፤ እኅቴ፥ ወዳጄ፥ ርግቤ፥ መደምደሚያዬ ሆይ፥ በራሴ ጠል፥ በቈንዳላዬም የሌሊት ነጠብጣብ ሞልቶበታልና ክፈችልኝ።
3 ፤ ቀሚሴን አወለቅሁ፤ እንዴት እለብሰዋለሁ? እግሬን ታጠብሁ፤ እንዴት አሳድፈዋለሁ?
4 ፤ ውዴ እጁን በቀዳዳ ሰደደ፥ አንጀቴም ስለ እርሱ ታወከ።
5 ፤ ለውዴ እከፍትለት ዘንድ ተነሣሁ፤ እጆቼ በደጅ መወርወሪያ ላይ ከርቤን አፈሰሱ፥ ጣቶቼ ፈሳሹን ከርቤ አንጠበጠቡ።
6 ፤ ለውዴ ከፈትሁለት፥ ውዴ ግን ፈቀቅ ብሎ አልፎ ነበር። ነፍሴ ከቃሉ የተነሣ ደነገጠች፤ ፈለግሁት፥ አላገኘሁትም፤ ጠራሁት፥ አልመለሰልኝም።
7 ፤ ከተማይቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፤ መቱኝ፥ አቈሰሉኝም፤ ቅጥር ጠባቂዎችም የዓይነ ርግብ መሸፈኛዬን ወሰዱት።
8 ፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ አምላችኋለሁ፤ ውዴን ያገኛችሁት እንደ ሆነ፥ እኔ ከፍቅር የተነሣ መታመሜን ንገሩት።
9 ፤ አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ውድሽ ማን ነው? ይህን የሚያህል አምለሽናልና ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ውድሽ ማን ነው?
10 ፤ ውዴ ነጭና ቀይ ነው፥ ከእልፍ የተመረጠ ነው።
11 ፤ ራሱ ምዝምዝ ወርቅ ነው፤ ቈንዳላው የተዝረፈረፈ ነው፥ እንደ ቁራ ጥቁረትም ጥቁር ነው።
12 ፤ ዓይኖቹ በሙሉ ፈሳሽ አጠገብ እንዳሉ በወተት እንደ ታጠቡ በፈሳሽ ውኃ አጠገብ እንደ ተቀመጡ እንደ ርግቦች ናቸው።
13 ፤ ጕንጩና ጕንጩ የሽቱ መደብ እርከን እንዳለበት እንደ ሽቱ አትክልት ናቸው፤ ከንፈሮቹ እንደ አበቦች ናቸው፥ የሚፈስስ ከርቤንም ያንጠበጥባሉ።
14 ፤ እጆቹ የቢረሌ ፈርጥ እንዳለበት እንደ ወርቅ ቀለበት ናቸው፤ አካሉ ብልሃተኛ እንደ ሠራው በሰንፔር እንዳጌጠ እንደ ዝሆን ጥርስ ነው።
15 ፤ እግሮቹ በምዝምዝ ወርቅ እንደ ተመሠረቱ እንደ ዕብነ በረድ ምሰሶች ናቸው፤ መልኩ እንደ ሊባኖስና እንደ ዝግባ ዛፍ መልካም ነው።
16 ፤ አፉ እጅግ ጣፋጭ ነው፥ እርሱም ፈጽሞ ያማረ ነው፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ ውዴ ይህ ነው፥ ባልንጀራዬም ይህ ነው።
1 ፤ አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ከአንቺ ጋር እንፈልገው ዘንድ ውድሽ ወዴት ሄደ? ውድሽስ ወዴት ፈቀቅ አለ?
2 ፤ ውዴ በገነቱ መንጋውን ያሰማራ ዘንድ አበባውንም ይሰበስብ ዘንድ ወደ ሽቱ መደብ ወደ ገነቱ ወረደ።
3 ፤ እኔ የወዴ ነኝ ውዴም የእኔ ነው፤ በሱፉ አበባ መካከል መንጋውን ያሰማራል።
4 ፤ ወዳጄ ሆይ፥ እንደ ቴርሳ ውብ ነሽ፥ እንደ ኢየሩሳሌምም ያማርሽ ነሽ፤ ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት ታስፈሪያለሽ።
5 ፤ አውከውኛልና ዓይኖችሽን ከፊቴ መልሺ፤ ጠጕርሽ ከገለዓድ እንደ ወረደ እንደ ፍየል መንጋ ነው።
6 ፤ ጥርሶችሽ ታጥበው እንደ ወጡ ሁሉ መንታ እንደ ወለዱ ከእነርሱም መካን እንደሌለባቸው መንጎች ናቸው።
7 ፤ በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ጕንጭና ጕንጭሽ እንደ ተከፈለ ሮማን ናቸው።
8 ፤ ስድሳ ንግሥታት ሰማንያም ቍባቶች ቍጥር የሌላቸውም ቈነጃጅት አሉ።
9 ፤ ርግቤ መደምደሚያዬም አንዲት ናት፤ ለእናትዋ አንዲት ናት ለወለደቻትም የተመረጠች ናት። ቈነጃጅትም አይተው አሞገሱአት፥ ንግሥታትና ቍባቶችም አመሰገኑአት።
10 ፤ ይህች እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጐበኝ፥ እንደ ጨረቃ የተዋበች እንደ ፀሐይም የጠራች፥ ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ማን ናት?
11 ፤ የወንዙን ዳር ልምላሜ አይ ዘንድ፥ ወይኑ አብቦ ሮማኑም አፍርቶ እንደ ሆነ እመለከት ዘንድ ወደ ገውዝ ገነት ወረድሁ።
12 ፤ ሳላውቅ ነፍሴ በከበረው ሰረገላ ላይ አስቀመጠችኝ።
1 ፤ አንቺ ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሽ፥ ተመለሽ፤ እናይሽ ዘንድ ተመለሽ፥ ተመለሽ። በሱላማጢስ ምን ታያላችሁ? እርስዋ እንደ መሃናይም ዘፈን ናት።
2 ፤ አንቺ የመኰንን ልጅ ሆይ፥ እግሮችሽ በጫማ ውስጥ እንዴት ውቦች ናቸው! ዳሌዎችሽስ በአንጥረኛ እጅ እንደ ተሠሩ እንደ ዕንቍዎች ይመስላሉ።
3 ፤ እንብርትሽ የወይን ጠጅ እንደማይጐድልበት እንደ ተነጠጠ ጽዋ ነው፤ ሆድሽ እንደ ስንዴ ክምር፥ በአበባም እንደ ታጠረ ነው።
4 ፤ ሁለቱ ጡቶችሽ እንደ ሁለቱ መንታ እንደ ሚዳቋ ግለገሎች ናቸው።
5 ፤ አንገትሽ እንደ ዝሆን ጥርስ ግንብ ነው፤ ዓይኖችሽ በሐሴቦን ውስጥ በባትረቢ በር አጠገብ እንደ ውኃ ኵሬዎች ናቸው፤ አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ አፋዛዥ እንደሚመለከት እንደ ሊባኖስ ግንብ ነው።
6 ፤ ራስሽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ በላይሽ ነው፤ የራስሽም ጠጕር እንደ ሐምራዊ ሐር ነው፤ ንጉሡ በሹርባው ታስሮአል።
7 ፤ ወዳጄ ሆይ፥ እንዴት የተዋብሽ ነሽ! እንዴትስ ደስ ታሰኛለሽ!
8 ፤ ይህ ቁመትሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፥ ጡቶችሽም የወይን ዘለላ ይመስላሉ።
9 ፤ ወደ ዘንባባው ዛፍ እወጣለሁ ጫፎችዋንም እይዛለሁ አልሁ፤ ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ የአፍንጫሽም ሽቱ እንደ እንኮይ ናቸው።
10 ፤ ጕሮሮሽ ለወዳጄ እየጣፈጠ እንደሚገባ፥ የተኙትን ከንፈሮች ይናገሩ ዘንድ እንደሚያደርግ፥ እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ነው።
11 ፤ እኔ የውዴ ነኝ፥ የእርሱም ምኞት ወደ እኔ ነው።
12 ፤ ውዴ ሆይ፥ ና፥ ወደ መስክ እንውጣ በመንደሮችም እንደር።
13 ፤ ወደ ወይኑ ቦታ ማልደን እንሂድ፤ ወይኑ አብቦ አበባውም ፍሬ አንዠርግጎ ሮማኑም አፍርቶ እንደ ሆነ እንይ፤ በዚያ ውዴን እሰጥሃለሁ።
[14]፤ ትርንጎዎች መዓዛን ሰጡ፤ መልካሞች ፍሬዎች ሁሉ፥ አሮጌው ከአዲሱ ጋር፥ በደጃችን አሉ፤ ውዴ ሆይ፥ ሁሉን ለአንተ ጠበቅሁልህ።
1 ፤ አንተ የእናቴን ጡት እንደ ጠባ እንደ ወንድሜ ምነው በሆንህ! በሜዳ ባገኘሁህ ጊዜ በሳምሁህ፥ ማንም ባልናቀኝም ነበር።
2 ፤ መርቼ ወደ እናቴ ቤት ባገባሁህ፥ በዚያም አንተ ባስተማርከኝ፤ እኔም ከመልካሙ ወይን ጠጅ ከሮማኔም ውኃ ባጠጣሁህ ነበር።
3 ፤ ግራው ከራሴ በታች በሆነች ቀኙም ባቀፈችኝ ነበር።
4 ፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ ፍቅርን እንዳታስነሡት እንዳታነሣሡትም አምላችኋለሁ።
5 ፤ በውድዋ ላይ ተደግፋ ከምድረ በዳ የምትወጣ ይህች ማን ናት? ከእንኮይ በታች አስነሣሁህ፤ በዚያ እናትህ ወለደችህ፥ በዚያም ወላጅ እናትህ አማጠችህ።
6 ፤ እንደ ማኅተም በልብህ፥ እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ፤ ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናትና፥ ቅንዓትም እንደ ሲኦል የጨከነች ናትና። ፍንጣሪዋ እንደ እሳት ፍንጣሪ፥ እንደ እግዚአብሔር ነበልባል ነው።
7 ፤ ብዙ ውኃ ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልም፥ ፈሳሾችም አያሰጥሙአትም፤ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ ይንቁታል።
8 ፤ እኛ ጡት የሌላት ታናሽ እኅት አለችን፤ ስለ እርስዋ በሚናገሩባት ቀን ለእኅታችን ምን እናድርግላት?
9 ፤ እርስዋ ቅጥር ብትሆን የብር ግንብ በላይዋ እንሠራለን፤ ደጅም ብትሆን በዝግባ ሳንቃ እንከብባታለን።
10 ፤ እኔ ቅጥር ነኝ ጡቶቼም እንደ ግንብ ናቸው፤ በዚያን ጊዜ በፊቱ ሰላምን እንደምታገኝ ሆንሁ።
11 ፤ ለሰሎሞን በብኤላሞን የወይን ቦታ ነበረው፤ የወይኑን ቦታ ለጠባቂዎች አከራየው፤ ሰው ሁሉ ለፍሬው ሺህ ብር ያመጣለት ነበር።
12 ፤ ለእኔ ያለኝ የወይን ቦታ በፊቴ ነው፤ ሰሎሞን ሆይ፥ ሺሁ ለአንተ፥ ሁለት መቶውም ፍሬውን ለሚጠብቁ ይሆናል።
13 ፤ በገነቱ የምትቀመጪ ሆይ፥ ባልንጀሮች የአንቺን ቃል ያደምጣሉ፤ ቃልሽን አሰሚኝ።
14 ፤ ውዴ ሆይ፥ ፍጠን፤ በቅመም ተራራ ላይ ሚዳቋን ወይም የዋላን እምቦሳ ምሰል።
Latest News
ilovejesus1.com
My name is Eden Fessehaye and i build ilovejesus1.com website for everyone to have access to the bible and audio bible as well. There is Amharic, Tigrigna and English bible. Also, the English bible can be translated to any languages for everyone to have access to...
Trust in Christ and receive Him as your Savior.
Christ is ready. “Here I am! I stand at the door and knock. If anyone hears my voice and opens the door, I will go in” (Revelation 3:20). Receive him now. “Yet to all who received him, to those who believed in his name, he gave the right to become children of God”...
You must repent and ask God for forgiveness.
“He who conceals his sins does not prosper, but whoever confesses and renounces them finds mercy” (Proverbs 28:13). Forgiveness is promised. “If we confess our sins, he is faithful and just and will forgive us our sins and purify us from all unrighteousness” (1 John...