መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ (1 Samuel)

እሱ ተከታታይ ጅማሬዎችን ያሳያል – የዓለም መጀመሪያ ፣ የሰው ልጅ እና እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የገባውን ቃል ኪዳን። የመጀመሪያው መጽሐፍ ዘፍጥረት በእግዚአብሔር ዓለም ፍጥረት ተከፈተ። የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ባለመታዘዙ የሰው ልጅ ብዛት ወደ ተለያዩ ብሔሮች እና ቋንቋዎች ሲከፋፈል ፍጹምው ዓለም በክፋት ውስጥ ይወድቃል።

መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ያንብቡ

መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ (1 Samuel)

1 ፤ በተራራማው በኤፍሬም አገር ከአርማቴም መሴፋ የሆነ ስሙ ሕልቃና የተባለ ኤፍሬማዊ ሰው ነበረ፤ እርሱም የኢያሬምኤል ልጅ የኢሊዮ ልጅ የቶሑ ልጅ የናሲብ ልጅ ነበረ።
2 ፤ ሁለትም ሚስቶች ነበሩት፤ የአንዲቱ ስም ሐና የሁለተኛይቱም ስም ፍናና ነበረ፤ ለፍናናም ልጆች ነበሩአት፥ ለሐና ግን ልጅ አልነበራትም።
3 ፤ ያም ሰው በሴሎ ይሰግድ ዘንድ ለሠራዊት ጌታም ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ከከተማው በየዓመቱ ይወጣ ነበር። የእግዚአብሔርም ካህናት ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በዚያ ነበሩ።
4 ፤ ሕልቃና የሚሠዋበት ቀን በደረሰ ጊዜም ለሚስቱ ለፍናና ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋ ሁሉ እድል ፈንታቸውን ሰጣቸው።
5 ፤ ሐናንም ይወድድ ነበርና ለሐና ሁለት እጥፍ እድል ፈንታ ሰጣት። እግዚአብሔር ግን ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበር።
6 ፤ እግዚአብሔርም ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበርና ጣውንትዋ ታስቆጣት ታበሳጫትም ነበር።
7 ፤ በየዓመቱም እንዲህ ባደረገ ጊዜ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር በምትወጣበት ጊዜ ታበሳጫት ነበር፤ ሐናም ታለቅስ ነበር፥ አንዳችም አትቀምስም ነበር።
8 ፤ ባልዋም ሕልቃና። ሐና ሆይ፥ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትቀምሺም? ለምንስ ልብሽ ያዝንብሻል? እኔስ ከአሥር ልጆች አልሻልልሽምን? አላት።
9 ፤ በሴሎ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሣች። ካህኑም ዔሊ በእግዚአብሔር መቅደስ መቃን አጠገብ በመንበሩ ላይ ተቀምጦ ነበር።
10 ፤ እርስዋም በልብዋ ትመረር ነበር፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸለየች፥ ጽኑ ልቅሶም አለቀሰች።
11 ፤ እርስዋም። አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ የባሪያህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፥ እኔንም ባትረሳ፥ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፥ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም ብላ ስእለት ተሳለች።
12 ፤ ጸሎትዋንም በእግዚአብሔር ፊት ባበዛች ጊዜ ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር።
13 ፤ ሐናም በልብዋ ትናገር ነበር፤ ድምፅዋም ሳይሰማ ከንፈርዋን ታንቀሳቅስ ነበር፤ ዔሊም እንደ ሰከረች ቈጠራት።
14 ፤ ዔሊም። ስካርሽ እስከ መቼ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አርቂው አላት።
15 ፤ ሐናም። ጌታዬ ሆይ፥ አይደለም፥ እኔስ ልብዋ ያዘነባት ሴት ነኝ፤ ጠጅና ሌላ የሚያሰክር ነገር አልጠጣሁም፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ነፍሴን አፈሰስሁ፤
16 ፤ ኀዘኔና ጭንቀቴ ስለ በዛ እስከ አሁን ድረስ ተናግሬአለሁና ባሪያህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቍጠረኝ ብላ መለሰችለት።
17 ፤ ዔሊም። በደኅና ሂጂ፥ የእስራኤልም አምላክ የለመንሽውን ልመና ይስጥሽ ብሎ መለሰላት።
18 ፤ እርስዋም። ባሪያህ በዓይንህ ፊት ሞገስ ላግኝ አለች። ሴቲቱም መንገድዋን ሄደች በላችም፥ ፊትዋም ከእንግዲህ ወዲያ አዘንተኛ መስሎ አልታየም።
19 ፤ ማልደው ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፥ ተመልሰውም ወደ አርማቴም ወደ ቤታቸው መጡ። ሕልቃናም ሚስቱን ሐናን አወቃት፤ እግዚአብሔርም አሰባት፤
20 ፤ የመፅነስዋም ወራት ካለፈ በኋላ ሐና ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርስዋም። ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ ስትል ስሙን ሳሙኤል ብላ ጠራችው።
21 ፤ ሰውዮውም ሕልቃና ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር የዓመቱን መሥዋዕትና ስእለቱን ለእግዚአብሔር ያቀርብ ዘንድ ወጣ።
22 ፤ ሐና ግን አልወጣችም፥ ባልዋንም። ሕፃኑ ጡት እስኪተው ድረስ እቀመጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ፥ በዚያም ለዘላለም ይሆን ዘንድ አመጣዋለሁ አለችው።
23 ፤ ባልዋም ሕልቃና። በዓይንሽ ደስ ያሰኘሽን አድርጊ፥ ጡትም እስኪተው ድረስ ተቀመጪ፤ ብቻ እግዚአብሔር ቃሉን ያጽና አላት። ሴቲቱም ልጅዋን እያጠባች ጡት እስኪተው ድረስ በቤትዋ ተቀመጠች።
24 ፤ ጡትም በተወ ጊዜ ከእርስዋ ጋር እርሱንና አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን፥ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት፥ አንድ አቁማዳ የወይን ጠጅ ይዛ ወደ ሴሎ ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጣችው፤ ሕፃኑም ገና ታናሽ ነበረ።
25 ፤ ወይፈኑንም አረዱ፥ ሕፃኑንም ወደ ዔሊ አመጡት።
26 ፤ እርስዋም አለች። ጌታዬ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ጌታ ሆይ፥ ወደ እግዚአብሔር ለመጸለይ በዚህ በአንተ ዘንድ ቆማ የነበረች ሴት እኔ ነኝ።
27 ፤ ሰለዚህ ሕፃን ጸለይሁ፤
28 ፤ እግዚአብሔርም የለመንሁትን ልመናዬን ሰጥቶኛል፤ እኔም ደግሞ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል።

1 ፤ ሐናም ስትጸልይ እንዲህ አለች። ልቤ በእግዚአብሔር ጸና፥ ቀንዴ በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ፤ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ፤ በማዳንህ ደስ ብሎኛል።
2 ፤ እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና፥ እንደ አምላካችንም ጻድቅ የለምና፤ ከአንተ በቀር ቅዱስ የለም።
3 ፤ አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ።
4 ፤ የኃያላንን ቀስት ሰብሮአል፥ ደካሞችንም በኃይል ታጥቀዋል።
5 ፤ ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ፤ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋል፤ መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው ደክማለች።
6 ፤ እግዚአብሔር ይገድላል ያድናልም፤ ወደ ሲኦል ያወርዳል፥ ያወጣል።
7 ፤ እግዚአብሔር ድሀ ያደርጋል፥ ባለጠጋም ያደርጋል፤ ያዋርዳል፥ ደግሞም ከፍ ከፍ ያደርጋል።
8 ፤ ከሕዝቡ መኳንንት ጋር ያስቀምጣቸው ዘንድ፥ የክብርንም ዙፋን ያወርሳቸው ዘንድ፥ ችግረኛውን ከመሬት ያስነሣል፥ ምስኪኑንም ከጉድፍ ያስነሣል፤ የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፥ በእነርሱ ላይም ዓለምን አደረገ።
9 ፤ እርሱ የቅዱሳኑን እግር ይጠብቃል ኃጥኣን ግን ዝም ብለው በጨለማ ይቀመጣሉ፤ ሰው በኃይሉ አይበረታምና።
10 ፤ ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ፤ በሰማይም ያንጐደጕድባቸዋል፤ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፤ ለንጉሡም ኃይል ይሰጣል፤ የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።
11 ፤ ሕልቃናም ወደ ቤቱ ወደ አርማቴም ሄደ፤ ብላቴናውም በካሁኑ በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር።
12 ፤ የዔሊም ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አያውቁም ነበር።
13 ፤ የካህናትም ልማድ በሕዝቡ ዘንድ እንዲህ ነበረ፤ ሰው ሁሉ መሥዋዕት ሲያቀርብ ሥጋው በተቀቀለ ጊዜ የካህኑ ሎሌ ይመጣ ነበር፥ በእጁም ሦስት ጣት ያለው ሜንጦ ነበረ፤
14 ፤ ወደ ድስቱም ወይም ወደ ምንቸቱ ወይም ወደ አፍላሉ ወይም ወደ ቶፋው ይሰድድው ነበር፤ ሜንጦውም ያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለእርሱ ይወስደው ነበር። ወደዚያም በመጡት በእስራኤላውያን ላይ በሴሎ እንዲህ ያደርጉ ነበር።
15 ፤ ደግሞም ስቡን ሳያቃጥሉ የካህኑ ሎሌ መጥቶ የሚሠዋውን ሰው። ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ አይወስድምና እጠብስለት ዘንድ ለካህኑ ሥጋ ስጠኝ ይለው ነበር።
16 ፤ ሰውዮውም። አስቀድሞ ስቡን ያቃጥሉት ኋላም ሰውነትህ ደስ የሚያሰኛትን ትወስዳለህ ቢለው፥ እርሱ። አይሆንም፥ ነገር ግን አሁን ስጠኝ፤ እንቢም ብትል በግድ እወስደዋለሁ ይለው ነበር።
17 ፤ ሰዎቹም የእግዚአብሔርን ቍርባን ይንቁ ነበርና የጎበዛዝቱ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረች።
18 ፤ ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ የበፍታ ኤፉድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር።
19 ፤ እናቱም ታናሽ መደረቢያ ሠራችለት፥ በየዓመቱም መሥዋዕት ለመሠዋት ከባልዋ ጋር ስትወጣ ታመጣለት ነበር።
20 ፤ ዔሊም ሕልቃናንና ሚስቱን። ለእግዚአብሔር ስለ ተሳለችው ስጦታ ፋንታ ከዚህች ሴት እግዚአብሔር ዘር ይስጥህ ብሎ ባረካቸው፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ሄዱ።
21 ፤ እግዚአብሔርም ሐናን አሰበ፥ ፀነሰችም፥ ሦስት ወንዶችና ሁለትም ሴቶች ልጆች ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ።
22 ፤ ዔሊም እጅግ አረጀ፤ ልጆቹም በእስራኤል ሁሉ ላይ ያደረጉትን ሁሉ፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደ ተኙ ሰማ።
23 ፤ እርሱም አላቸው። ስለ ክፉ ሥራችሁ ከዚህ ሕዝብ ሁሉ ሰምቻለሁና ስለምን እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ?
24 ፤ ልጆቼ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለ እናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይሆንም።
25 ፤ ሰውስ ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድበታል፤ ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለ እርሱ የሚለምን ማን ነው? እነርሱ ግን እግዚአብሔር ሊገድላቸው ወድዶአልና የአባታቸውን ቃል አልሰሙም።
26 ፤ ብላቴናውም ሳሙኤል እያደገ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት ሞገስ እያገኘ ሄደ።
27 ፤ የእግዚአብሔርም ሰው ወደ ዔሊ መጥቶ አለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በግብጽ በፈርዖን ቤት ባሪያ ሳለ ለአባትህ ቤት ተገለጥሁ፤
28 ፤ ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ ካህን ይሆነኝ ዘንድ፥ በመሠዊያዬ ላይ ይሠዋ ዘንድ፥ ዕጣንንም ያጥን ዘንድ ኤፉድንም በፊቴ ይለብስ ዘንድ ለእኔ መረጥሁት፤ የእስራኤልንም ልጆች የእሳት ቍርባን ሁሉ ስለ ምግብ ለአባትህ ቤት ሰጠሁ።
29 ፤ በማደሪያዬ ያቀርቡት ዘንድ ያዘዝሁትን መሥዋዕቴንና ቍርባኔን ስለ ምን ረገጣችሁ? እንድትወፍሩም የሕዝቤን የእስራኤልን ቍርባን ሁሉ መጀመሪያ በመብላታችሁ ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ለምን አከበርህ?
30 ፤ ስለዚህም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእውነት ቤትህ የአባትህም ቤት ለዘላለም በፊቴ እንዲኖር ተናግሬአለሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያከበሩኝን አከብራለሁና፥ የናቁኝም ይናቃሉና ይህ አይሆንልኝም።
31 ፤ እነሆ፥ ለቤትህ ሽማግሌ እንዳይገኝ፥ ክንድህን የአባትህንም ቤት ክንድ የምሰብርበት ዘመን ይመጣል።
32 ፤ በእስራኤል በረከት ሁሉ፥ በማደሪያዬ ጠላትህን ታያለህ በቤትህም ለዘላለም ሽማግሌ አይገኝም።
33 ፤ ከመሠዊያዬ ያልተቈረጠ ልጅህ ቢገኝ ዓይንህን ያፈዝዘዋል፥ ነፍስህንም ያሳዝናል ከቤትህም የሚወለዱ ሰዎች ሁሉ በጐልማስነት ይሞታሉ።
34 ፤ ይህ በሁለቱ ልጆችህ በአፍኒንና በፊንሐስ ላይ የሚመጣ ለአንተ ምልክት ነው፤ ሁለቱ በአንድ ቀን ይሞታሉ።
35 ፤ የታመነም ካህን ለእኔ አስነሣለሁ፥ በልቤም በነፍሴም እንዳለ እንዲሁ ያደርጋል፤ እኔም የታመነ ቤት እሠራለታለሁ፥ ዘመኑን ሁሉ እኔ በቀባሁት ሰው ፊት ይሄዳል።
36 ፤ ከቤትህም የቀረው ሁሉ ይመጣል፥ በፊቱም ሰግዶ፥ ቍራሽ እንጀራ እበላ ዘንድ ከካህናት ወደ አንዲቱ ዕጣ፥ እባክህ፥ ስደደኝ ብሎ አንድ ብር አንድ እንጀራም ይለምናል።

1 ፤ ብላቴናውም ሳሙኤል በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር፤ በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ፤ ራእይም አይገለጥም ነበር።
2 ፤ በዚያም ዘመን እንዲህ ሆነ፤ የዔሊ ዓይኖች ማየት እስኪሳናቸው ድረስ መፍዘዝ ጀምረው ነበር።
3 ፤ ዔሊም በስፍራው ተኝቶ ሳለ፥ የእግዚአብሔር መብራት ገና ሳይጠፋ፥ ሳሙኤልም የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት በእግዚአብሔር መቅደስ ተኝቶ ሳለ፥
4 ፤ እግዚአብሔር ሳሙኤልን ጠራው፤ እርሱም። እነሆኝ አለ።
5 ፤ ወደ ዔሊም ሮጠ። እነሆኝ የጠራኸኝ አለው። እርሱም። አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ አለው። ሄዶም ተኛ።
6 ፤ እግዚአብሔርም ደግሞ። ሳሙኤል ሆይ ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና። እነሆኝ የጠራኸኝ አለው። እርሱም። ልጄ ሆይ፥ አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ ብሎ መለሰ።
7 ፤ ሳሙኤል ግን ገና እግዚአብሔርን አላወቀም ነበር፥ የእግዚአብሔርም ቃል ገና አልተገለጠለትም ነበር።
8 ፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ ጠራው። እርሱም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና። እነሆኝ የጠራኸኝ አለ። ዔሊም እግዚአብሔር ብላቴናውን እንደ ጠራው አስተዋለ።
9 ፤ ዔሊም ሳሙኤልን። ሄደህ ተኛ ቢጠራህም። አቤቱ፥ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር በለው አለው። ሳሙኤልም ሄዶ በስፍራው ተኛ።
10 ፤ እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፥ እንደ ቀድሞውም። ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም። ባሪያህ ይሰማልና ተናገር አለው።
11 ፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው። እነሆ፥ የሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ አንድ ነገርን በእስራኤል አደርጋለሁ።
12 ፤ በዚያም ቀን በቤቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ በዔሊ አወርዳለሁ፤ እኔም ጀምሬ እፈጽምበታለሁ።
13 ፤ ልጆቹ የእርግማን ነገር እንዳደረጉ አውቆ አልከለከላቸውምና ስለ ኃጢአቱ በቤት ለዘላለም እንድፈርድ አስታውቄዋለሁ።
14 ፤ ስለዚህም የዔሊ ቤት ኃጢአት በመሥዋዕትና በቍርባን ለዘላለም እንዳይሰረይለት ለዔሊ ቤት ምያለሁ።
15 ፤ ሳሙኤልም እስኪነጋ ተኛ፥ ማልዶም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት ደጅ ከፈተ። ሳሙኤልም ራእዩን ለዔሊ መንገር ፈራ።
16 ፤ ዔሊም ሳሙኤልን ጠርቶ። ልጄ ሳሙኤል ሆይ፥ አለ፤ እርሱም። እነሆኝ አለ።
17 ፤ እርሱም። እግዚአብሔር የነገረህ ነገር ምንድር ነው? ከእኔ አትሸሽግ፤ ከነገረህ ነገር ሁሉ የሸሸግኸኝ እንደ ሆነ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብህ፥ እንዲህም ይጨምርብህ አለው።
18 ፤ ሳሙኤልም ነገሩን ሁሉ ነገረው፥ አንዳችም አልሸሸገውም። ዔሊም። እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ።
19 ፤ ሳሙኤልም አደገ፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ከቃሉም አንዳች በምድር ላይ አይወድቀም ነበር።
20 ፤ እስራኤልም ሁሉ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሳሙኤል ለእግዚአብሔር ነቢይ ይሆን ዘንድ የታመነ እንደ ሆነ አወቀ።
21 ፤ እግዚአብሔርም ደግሞ በሴሎ ተገለጠ፤ እግዚአብሔርም በእግዚአብሔር ቃል ለሳሙኤል በሴሎ ይገለጥ ነበር። የሳሙኤልም ቃል ለእስራኤል ሁሉ ደረሰ።

1 ፤ እስራኤልም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሊዋጋ ወጡ፥ በአቤንኤዘር አጠገብ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያን በአፌቅ ሰፈሩ።
2 ፤ ፍልስጥኤማውያንም በእስራኤል ላይ ተሰለፉ፤ ሰልፉም በተመደበ ጊዜ እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ፊት ተመቱ፤ ጦርነት በተደረገበትም ስፍራ ከእስራኤል አራት ሺህ የሚያህሉ ሰዎችን ገደሉ።
3 ፤ ሕዝቡም ወደ ሰፈር በመጡ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎች። ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ፊት ስለ ምን መታን? በመካከላችን እንዲሄዱ፥ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ አሉ።
4 ፤ ሕዝቡም ወደ ሴሎ ላኩ፥ በኪሩቤልም ላይ የሚቀመጠውን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከዚያ አመጡ፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ።
5 ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አደረጉ፥ ምድሪቱም አስተጋባች።
6 ፤ ፍልስጥኤማውያንም የእልልታውን ድምፅ በሰሙ ጊዜ። በዕብራውያን ሰፈር ያለው ይህ ታላቅ የእልልታ ድምፅ ምንድር ነው? አሉ። የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ሰፈሩ እንደገባ አስተዋሉ።
7 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው። እግዚአብሔር ወደ ሰፈር መጥቶአል አሉ። ደግሞም እንዲህ አሉ። ወዮልን፤ ከዚህ አስቀድሞ እንዲህ ያለ ነገር አልሆነም።
8 ፤ ወዮልን፤ ከእነዚህ ከኃያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነዚህ አማልክት ግብጻውያንን በምድረ በዳ በልዩ በልዩ መቅሠፍት የመቱ ናቸው።
9 ፤ እናንተ ፍልስጥኤማውያን ሆይ፥ አይዞአችሁ፥ ጎብዙ፤ እናንተ ባሪያዎች እንዳደረጋችኋቸው ዕብራውያን ባሪያዎች እንዳያደርጉአችሁ ጎብዙ፥ ተዋጉ።
10 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ተዋጉ፤ እስራኤልም ተመቱ፥ ሁሉም እያንዳንዱ ወደ ድንኳናቸው ሸሹ፤ እጅግም ታላቅ ግድያ ሆነ፥ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኞች ወደቁ።
11 ፤ የእግዚአብሔርም ታቦት ተማረከች፥ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ።
12 ፤ በዚያም ቀን አንድ የብንያም ሰው ከሰልፍ እየበረረ ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ ወደ ሴሎ መጣ።
13 ፤ በመጣም ጊዜ ዔሊ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ልቡ ተናውጦ ነበርና በመንገድ ዳር በወንበሩ ላይ ተቀምጦ ይጠባበቅ ነበር፤ ሰውዮውም ወደ ከተማይቱ ገብቶ ባወራ ጊዜ ከተማይቱ ሁሉ ተጭዋጭዋኸች።
14 ፤ ዔሊም የጩኸቱን ድምፅ በሰማ ጊዜ። ይህ ጫጫታ ምንድር ነው? አለ። ሰውዮውም ፈጥኖ መጣና ለዔሊ ነገረው።
15 ፤ ዔሊም የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ነበረ፤ ዓይኖቹም ማየት እስኪሳናቸው ድረስ ፈዝዘው ነበር።
16 ፤ ሰውዮውም ዔሊን። ከሰልፍ የመጣሁ እኔ ነኝ፥ ዛሬም ከሰልፍ ኮበለልሁ አለ። እርሱም። ልጄ ሆይ፥ ነገሩሳ እንዴት ሆነ? አለው።
17 ፤ ወሬኛውም መልሶ። እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ ታላቅ ግድያ ሆኖአል፥ ሁለቱም ልጆችህ አፍኒንና ፊንሐስ ሞተዋል፤ የእግዚአብሔርም ታቦት ተማርካለች አለ።
18 ፤ ሰውዮውም ስለ እግዚአብሔር ታቦት በተናገረ ጊዜ ዔሊ በበሩ አጠገብ ካለው ከወንበሩ ወደቀ፤ እርሱ ሸምግሎ ደንግዞም ነበርና አንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እርሱም በእስራኤል ላይ አርባ ዓመት ፈራጅ ነበረ።
19 ፤ ምራቱም የፊንሐስ ሚስት አርግዛ ልትወልድ ተቃርባ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ታቦት እንደ ተማረከች፥ አማትዋና ባልዋም እንደ ሞቱ በሰማች ጊዜ ምጥ ደርሶባት ነበርና ተንበርክካ ወለደች።
20 ፤ ወደሞትም በቀረበች ጊዜ በዙሪያዋ ያሉት ሴቶች። ወንድ ልጅ ወልደሻልና አትፍሪ አሉአት። እርስዋ ግን አልመለሰችላቸውም፥ በልብዋም አላኖረችውም።
21 ፤ እርስዋም የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከች ስለአማትዋና ስለ ባልዋም። ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል የሕፃኑን ስም። ኢካቦድ ብላ ጠራችው።
22 ፤ እርስዋም። የእግዚአብሔር ታቦት ተማርካለችና ክብር ከእስራኤል ለቀቀ አለች።

1 ፤ ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ወሰዱ፤ ከአቤንኤዘርም ወደ አዛጦን ይዘውት መጡ።
2 ፤ ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ወስደው ወደ ዳጎን ቤት አገቡት፥ በዳጎንም አጠገብ አኖሩት።
3 ፤ በነጋውም የአዛጦን ሰዎች ማለዱ፥ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ ነበር፤ ዳጎንንም አንሥተው ወደ ስፍራው መለሱት።
4 ፤ በነጋውም ማለዱ፥ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ ነበር፤ የዳጎንም ራስ እጆቹም ተቈርጠው በመድረኩ ላይ ወድቀው ነበር፤ የዳጎንም ደረት ብቻውን ቀርቶ ነበር።
5 ፤ ስለዚህም የዳጎን ካህናት ወደ ዳጎንም ቤት የሚገቡት ሁሉ በአዛጦን ያለውን የዳጎንን መድረክ እስከ ዛሬ ድረስ አይረግጡም።
6 ፤ የእግዚአብሔርም እጅ በአዛጦን ሰዎች ላይ ከበደች፥ አጠፋቸውም፥ አዛጦንንና ድንበራቸውንም በእባጭ መታቸው።
7 ፤ የአዛጦንም ሰዎች እንዲህ እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ። እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጠንክራለችና የእስራኤል አምላክ ታቦት ከእኛ ዘንድ አይቀመጥ አሉ።
8 ፤ ልከውም የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ወደ እነርሱ ሰበሰቡና። በእስራኤል አምላክ ታቦት ምን እናድርግ? አሉ፤ እነርሱም። የእስራኤል አምላክ ታቦት ወደ ጌት ይዙር ብለው መለሱ። የእስራኤልንም አምላክ ታቦት ወደዚያ ተሸከሙት።
9 ፤ ከተሸከሙትም በኋላ የእግዚአብሔር እጅ በታላቅ ድንጋጤ በከተማይቱ ላይ ሆነች፤ ከታናሹም እስከ ታላቁ ድረስ የከተማይቱን ሰዎች መታ፥ እባጭም መጣባቸው።
10 ፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት ወደ አስቀሎና ሰደዱት። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ አስቀሎና በመጣ ጊዜ አስቀሎናውያን። እኛንና ሕዝባችንን ሊገድሉ የእስራኤልን አምላክ ታቦት አመጡብን ብለው ጮኹ።
11 ፤ በከተማይቱ ሁሉ የሞት ድንጋጤ ነበርና፥ የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ እጅግ ከብዳ ነበረችና ልከው የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ሰብስበው። የእስራኤልን አምላክ ታቦት ስደዱ፥ እኛንና ሕዝባችንን እንዳይገድል ወደ ስፍራው ይመለስ አሉ።
12 ፤ ያልሞቱትም ሰዎች በእባጭ ተመቱ፤ የከተማይቱም ዋይታ እስከ ሰማይ ወጣ።

1 ፤ የእግዚአብሔር ታቦት በፍልስጥኤማውያን አገር ሰባት ወር ተቀመጠ።
2 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ካህናትንና ምዋርተኞችን ጠርተው። በእግዚአብሔር ታቦት ላይ ምን እናድርግ? ወደ ስፍራውስ በምን እንስደደው? አስታውቁን አሉ።
3 ፤ እነርሱም። የእስራኤልን አምላክ ታቦት ብትሰድዱ የበደል መሥዋዕት መልሱለት እንጂ ባዶውን አትስደዱት፥ የዚያን ጊዜም ትፈወሳላችሁ፤ እጁም ከእናንተ አለመራቁ ስለ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ አሉ።
4 ፤ እነርሱም። ስለ በደል መሥዋዕት የምንመልስለት ምንድር ነው? አሉ። እነርሱም እንዲህ አሉ። እናንተንና አለቆቻችሁን ያገኘች መቅሠፍት አንዲት ናትና እንደ ፍልስጥኤማውያን አለቆች ቍጥር አምስት የወርቅ እባጮች አምስትም የወርቅ አይጦች አቅርቡ።
5 ፤ የእባጫችሁንም ምሳሌ፥ ምድራችሁንም የሚያጠፋአትን የአይጦችን ምሳሌ አድርጋችሁ ለእስራኤል አምላክ ክብርን ስጡ፤ እጁን ከእናንተና ከአማልክቶቻችሁ ከምድራችሁም ምናልባት ያቀልል ይሆናል።
6 ፤ ግብጻውያንና ፈርዖንም ልባቸውን እንዳጸኑ ልባችሁን ለምን ታጸናላችሁ? እግዚአብሔር ኃይሉን ካደረገባቸው በኋላ ያወጡአቸው አይደሉምን?
7 ፤ እነርሱም አልሄዱምን? አሁንም ወስዳችሁ አንዲት ሰረገላ ሥሩ፤ የሚያጠቡም፥ ቀንበር ያልተጫነባቸውን ሁለት ላሞች በሰረገላ ጥመዱአቸው፥ እንቦሶቻቸውንም ለይታችሁ ወደ ቤት መልሱአቸው።
8 ፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት ወስዳችሁ በሰረገላው ላይ አኑሩት፤ ስለ በደልም መሥዋዕት ያቀረባችሁትን የወርቁን ዕቃ በሣጥን ውስጥ አድርጋችሁ በታቦቱ አጠገብ አኑሩት፤ ይሄድም ዘንድ ስደዱት።
9 ፤ ተመልከቱም በድንበሩም መንገድ ወደ ቤትሳሚስ ቢወጣ ይህን እጅግ ክፉ ነገር ያደረገብን እግዚአብሔር ነው፤ አለዚያም እንዲያው መጥቶብናል እንጂ የመታን የእርሱ እጅ እንዳልሆነ እናውቃለን።
10 ፤ ሰዎቹም እንዲሁ አደረጉ፤ የሚያጠቡትን ሁለቱን ላሞች ወሰዱ፥ በሰረገላም ጠመዱአቸው፥ እንቦሶቻቸውንም በቤት ዘጉባቸው፤
11 ፤ የእግዚአብሔርም ታቦት፥ የወርቁ አይጦችና የእባጮቻቸው ምሳሌ ያሉበትንም ሣጥን በሰረገላው ላይ ጫኑ።
12 ፤ ላሞችም ወደ ቤትሳሚስ ወደሚወስደው መንገድ አቅንተው እምቧ እያሉ በጎዳናው ላይ ሄዱ፥ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላሉም፤ የፍልስጥኤማውያንም አለቆች እስከ ቤትሳሚስ ዳርቻ ድረስ በኋላ በኋላቸው ይሄዱ ነበር።
13 ፤ የቤትሳሚስ ሰዎችም በሸለቆው ውስጥ ስንዴ ያጭዱ ነበር፤ ዓይናቸውንም ከፍ አድርገው ታቦቱን አዩ፥ በማየታቸውም ደስ አላቸው።
14 ፤ ሰረገላውም ወደ ቤትሳሚሳዊው ወደ ኢያሱ እርሻ መጣ፥ ታላቅም ድንጋይ በነበረበት በዚያ ቆመ፤ የሰረገላውንም እንጨት ፈልጠው ላሞቹን ለእግዚአብሔር ለሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ።
15 ፤ ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት፥ ከእርሱ ጋር የነበረውንም የወርቅ ዕቃ ያለበትን ሣጥን አወረዱ፥ በታላቁም ድንጋይ ላይ አኖሩት፤ በዚያም ቀን የቤትሳሚስ ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረቡ፥ መሥዋዕትንም ሠዉ።
16 ፤ ፍልስጥኤማውያንም አምስቱ አለቆች ባዩት ጊዜ በዚያው ቀን ወደ አስቀሎና ተመለሱ።
17 ፤ ፍልስጥኤማውያን ስለ በደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀረቡአቸው የወርቅ እባጮች እነዚህ ናቸው፤ አንዲቱ ለአዛጦን፥ አንዲቱም ለጋዛ፥ አንዲቱም ለአስቀሎና፥ አንዲቱ ለጌት፥
18 ፤ አንዲቱ ለአቃሮን የወርቁም አይጦች ቍጥር ለአምስቱ የፍልስጥኤማውያን አለቆች እንደ ነበሩት ከተሞች ሁሉ ቍጥር እንዲሁ ነበረ፤ እነርሱም እስከ ታላቁ ድንጋይ የሚደርሱ ከተሞችና መንደሮች ናቸው። በዚህም ድንጋይ ላይ የእግዚአብሔርን ታቦት አስቀመጡ፥ ድንጋዩም እስከ ዛሬ ድረስ በቤትሳሚሳዊው በኢያሱ እርሻ አለ።
19 ፤ ወደ እግዚአብሔርም ታቦት ውስጥ ተመልክተዋልና የቤትሳሚስን ሰዎች መታ፤ በሕዝቡም ከአምስት ሺህ ሰው ሰባ ሰዎችን መታ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ ግዳይ ስለ መታ ሕዝቡ አለቀሰ።
20 ፤ የቤትሳሚስም ሰዎች። በዚህ በቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት መቆም ማን ይችላል? ከእኛስ ወጥቶ ወደ ማን ይሄዳል? አሉ።
21 ፤ በቂርያትይዓሪምም ወደ ተቀመጡት ሰዎች መልክተኞች ልከው። ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት መልሰዋል፤ ወርዳችሁም ወደ እናንተ አውጡት አሉ።

1 ፤ የቂርያትይዓሪም ሰዎችም መጥተው የእግዚአብሔርን ታቦት አወጡ፥ በኮረብታውም ላይ ወዳለው ወደ አሚናዳብ ቤት አገቡት፤ የእግዚአብሔርም ታቦት እንዲጠብቅ ልጁን አልዓዛርን ቀደሱት።
2 ፤ ታቦቱም በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠበት ቀን ጀምሮ ወራቱ ረዘመ፥ ሀያ ዓመትም ሆነ፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ አዝኖ እግዚአብሔርን ተከተለ።
3 ፤ ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ። በሙሉ ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሳችሁ እንግዶችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እግዚአብሔር አቅኑ፥ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ያድናችኋል ብሎ ተናገራቸው።
4 ፤ የእስራኤልም ልጆች በኣሊምንና አስታሮትን አራቁ፥ እግዚአብሔርንም ብቻ አመለኩ።
5 ፤ ሳሙኤልም። እስራኤልን ሁሉ ወደ ምጽጳ ሰብስቡ፥ ስለ እናንተም ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ አለ።
6 ፤ ወደ ምጽጳም ተሰበሰቡ፤ ውኃም ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሱ፥ በዚያም ቀን ጾሙ፥ በዚያም። እግዚአብሔርን በድለናል አሉ። ሳሙኤልም በእስራኤል ልጆች ላይ በምጽጳ ፈረደ።
7 ፤ ፍልስጥኤማውያንም የእስራኤል ልጆች ወደ ምጽጳ እንደ ተሰበሰቡ በሰሙ ጊዜ የፍልስጥኤማውያን አለቆች በእስራኤል ላይ ወጡ፤ የእስራኤልም ልጆች ሰምተው ፍልስጥኤማውያንን ፈሩ።
8 ፤ የእስራኤልም ልጆች ሳሙኤልን። ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድነን ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ትጸልይልን ዘንድ አትታክት አሉት።
9 ፤ ሳሙኤልም አንድ የሚጠባ የበግ ጠቦት ወስዶ ለእግዚአብሔር ፈጽሞ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው፤ ሳሙኤልም ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው።
10 ፤ ሳሙኤልም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሲያሳርግ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በዚያች ቀን በፍልስጥኤማውያን ላይ ታላቅ ነጐድጓድ አንጐደጐደ፥ አስደነገጣቸውም በእስራኤልም ፊት ድል ተመቱ።
11 ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከምጽጳ ወጡ፥ ፍልስጥኤማውያንንም አሳደዱ፤ በቤትካር ታችም እስኪደርሱ ድረስ መቱአቸው።
12 ፤ ሳሙኤልም አንድ ድንጋይ ወስዶ በምጽጳና በሼን መካከል አኖረው፤ ስሙንም። እስከ አሁን ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል ሲል አቤንኤዘር ብሎ ጠራው።
13 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ተዋረዱ፥ ዳግመኛም ከዚያ ወዲያ ወደ እስራኤል ድንበር አልወጡም፤ በሳሙኤል ዕድሜ ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ በፍልስጥኤማውያን ላይ ነበረች።
14 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ከአስቀሎና ጀምሮ እስከ ጌት ድረስ ከእስራኤል የወሰዱአቸው ከተሞች ለእስራኤል ተመለሱ፤ እስራኤልም ድንበሩን ከፍልስጥኤማውያን እጅ አዳነ። በእስራኤልና በአሞራውያንም መካከል ዕርቅ ነበረ።
15 ፤ ሳሙኤልም በዕድሜው ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር።
16 ፤ በየዓመቱም ወደ ቤቴል ወደ ጌልገላ ወደ ምጽጳም ይዞር ነበር፤ በእነዚያም ስፍራዎች ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር።
17 ፤ ቤቱም በዚያ ነበረና ወደ አርማቴም ይመለስ ነበር፤ በዚያም በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር፥ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።

1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ልጆቹን በእስራኤል ላይ ፈራጆች አደረጋቸው።
2 ፤ የበኵር ልጁም ስም ኢዮኤል፥ የሁለተኛውም ስም አብያ ነበረ። እነርሱም በቤርሳቤህ ይፈርዱ ነበር።
3 ፤ ልጆቹም በመንገዱ አልሄዱም፥ ነገር ግን ረብ ለማግኘት ፈቀቅ አሉ፥ ጉቦም እየተቀበሉ ፍርድን ያጣምሙ ነበር።
4 ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ተሰብስበው ወደ ሳሙኤል ወደ አርማቴም መጡና።
5 ፤ እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፥ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም፤ አሁንም እንደ አሕዛብ ሁሉ የሚፈርድልን ንጉሥ አድርግልን አሉት።
6 ፤ የሚፈርድልንም ንጉሥ ስጠን ባሉት ጊዜ ነገሩ ሳሙኤልን አስከፋው፤ ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።
7 ፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው። በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ።
8 ፤ ከግብጽ ካወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው እንግዶች አማልክት በማምለካቸው እንደ ሠሩት ሥራ ሁሉ እንዲሁ በአንተ ደግሞ ያደርጉብሃል።
9 ፤ አሁንም ቃላቸውን ስማ፤ ነገር ግን ጽኑ ምስክር መስክርባቸው፥ በእነርሱም ላይ የሚነግሠውን የንጉሡን ወግ ንገራቸው።
10 ፤ ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ንጉሥን ለፈለጉ ሕዝብ ነገራቸው።
11 ፤ እንዲህም አለ። በእናንተ ላይ የሚነግሠው የንጉሡ ወግ ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሰረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፥ በሰረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ፤
12 ፤ ለራሱም የሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋቸዋል፤ እርሻውንም የሚያርሱ እህሉንም የሚያጭዱ የጦር መሣሪያውንና የሰረገሎቹንም ዕቃ የሚሠሩ ይሆናሉ።
13 ፤ ሴቶች ልጆቻችሁንም ወስዶ ሽቶ ቀማሚዎችና ወጥቤቶች አበዛዎችም ያደርጋቸዋል።
14 ፤ ከእርሻችሁና ከወይናችሁም መልካም መልካሙን ወስዶ ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል።
15 ፤ ከዘራችሁና ከወይናችሁም አሥራት ወስዶ ለጃንደረቦቹና ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል።
16 ፤ ሎሌዎቻችሁንና ገረዶቻችሁን፥ ከከብቶቻችሁና ከአህዮቻችሁም መልካም መልካሞቹን ወስዶ ያሠራቸዋል።
17 ፤ ከበጎቻችሁና ከፍየሎቻችሁ አሥራት ይወስዳል፤ እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ።
18 ፤ በዚያም ቀን ለእናንተ ከመረጣችሁት ከንጉሣችሁ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር አልሰማችሁም።
19 ፤ ሕዝቡ ግን የሳሙኤልን ነገር ይሰማ ዘንድ እንቢ አለ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይሁንልን፥
20 ፤ እኛም ደግሞ እንደ አሕዛብ ሁሉ እንሆናለን፤ ንጉሣችንም ይፈርድልናል፥ በፊታችንም ወጥቶ ስለ እኛ ይዋጋል አሉት።
21 ፤ ሳሙኤልም የሕዝቡን ቃል ሁሉ ሰማ፥ ለእግዚአብሔርም ተናገረ።
22 ፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን። ቃላቸውን ስማ፥ ንጉሥም አንግሥላቸው አለው። ሳሙኤልም የእስራኤልን ሰዎች። እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ሂዱ አላቸው።

1 ፤ ስሙ ቂስ የተባለ አንድ ብንያማዊ ሰው ነበረ፤ እርሱም የአቢኤል ልጅ፥ የጽሮር ልጅ፥ የብኮራት ልጅ፥ የብንያማዊው የአፌቅ ልጅ፥ ጽኑዕ ኃያል ሰው ነበረ።
2 ፤ ለእርሱም ሳኦል የሚባል የተመረጠ መልካም ልጅ ነበረው፤ ከእስራኤልም ልጆች ከእርሱ ይልቅ መልካም የሆነ ሰው አልነበረም፤ ከሕዝቡም ሁሉ ይልቅ ከትከሻውና ከዚያም በላይ ቁመቱ ዘለግ ያለ ነበረ።
3 ፤ የሳኦልም አባት የቂስ አህዮች ጠፍተው ነበር፤ ቂስም ልጁን ሳኦልን። ከብላቴኖቹ አንዱን ወስደህ ተነሣ፥ አህዮችንም ለመሻት ሂድ አለው።
4 ፤ በተራራማው በኤፍሬም አገርና በሻሊሻ አለፉ፥ አላገኙአቸውምም በሻዕሊም ምድርም አለፉ፥ በዚያም አልነበሩም፤ በብንያም ምድርም አለፉ፥ አላገኙአቸውምም።
5 ፤ ወደ ጹፍ ምድር በመጡ ጊዜም ሳኦል ከእርሱ ጋር የነበረውን ብላቴና። አባቴ ስለ አህዮች ማሰብ ትቶ ስለ እኛ እንዳይጨነቅ፥ ና፥ እንመለስ አለው።
6 ፤ እርሱም። እነሆ፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በዚህች ከተማ አለ፤ እርሱም የተከበረ ሰው ነው፥ የሚናገረውም ሁሉ በእውነት ይፈጸማል፤ አሁን ወደዚያ እንሂድ፤ ምናልባት የምንሄድበትን መንገድ ይነግረናል አለው።
7 ፤ ሳኦልም ብላቴናውን። እነሆ፥ እንሄዳለን፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ሰው ምን እናመጣለታለን? እንጀራ ከከረጢታችን አልቆአልና፥ እጅ መንሻም የለንምና ለእግዚአብሔር ሰው የምናመጣለት ምን አለን? አለው።
8 ፤ ብላቴናው ደግሞ ለሳኦል መልሶ። እነሆ፥ በእጄ የሰቅል ብር ሩቡ አለኝ፤ እርሱንም መንገዳችንን እንዲነግረን ለእግዚአብሔር ሰው እሰጣለሁ አለ።
9 ፤ ዛሬ ነቢይ የሚባለው ቀድሞ ባለ ራእይ ይባል ነበርና አስቀድሞ በእስራኤል ዘንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሲሄድ። ኑ፥ ወደ ባለ ራእይ እንሂድ ይል ነበር።
10 ፤ ሳኦልም ብላቴናውን። የተናገረኸው ነገር መልካም ነው፤ ና፥ እንሂድ አለውና የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ከተማ ሄዱ።
11 ፤ በከተማይቱም ዳገት በወጡ ጊዜ ቆነጃጅት ውኃውን ሊቀዱ ሲወጡ አገኙና። ባለ ራእይ በዚህ አለ ወይ? አሉአቸው።
12 ፤ እነርሱም። አዎን፤ እነሆ፥ በፊታችሁ ነው፤ ዛሬ ወደ ከተማይቱ መጥቶአልና፥ ዛሬም ሕዝቡ በኮረብታው ላይ ባለው መስገጃ መሥዋዕት ማቅረብ አለባቸውና ፈጥናችሁ ውጡ።
13 ፤ ወደ ከተማይቱም በገባችሁ ጊዜ መሥዋዕቱን እርሱ የሚባርክ ስለ ሆነ እርሱ ሳይወጣ ሕዝቡ ምንም አይቀምሱምና፥ ከዚያም በኋላ የተጠሩት ይበላሉና ለመብላት ወደ ኮረብታው መስገጃ ሳይወጣ ታገኙታላችሁ፤ በዚህም ጊዜ ታገኙታላችሁና አሁን ውጡ አሉአቸው።
14 ፤ ወደ ከተማይቱም ወጡ፤ በከተማይቱም ውስጥ በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ሳሙኤል ወደ ኮረብታው መስገጃ ለመውጣት ወደ እነርሱ መጣ።
15 ፤ ገናም ሳኦል ሳይመጣ ከአንድ ቀን በፊት እግዚአብሔር ሳሙኤልን እንዲህ ብሎ ገልጦለት ነበር።
16 ፤ ነገ በዚህች ሰዓት ከብንያም አገር አንድ ሰው እሰድድልሃለሁ፤ ልቅሶአቸው ወደ እኔ የደረስ ሕዝቤን ተመልክቻለሁና ለሕዝቤ ለእስራኤል አለቃ ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ሕዝቤን ያድናል።
17 ፤ ሳሙኤልም ሳኦልን ባየ ጊዜ እግዚአብሔር። ያ የነገርሁህ ሰው እነሆ፤ እርሱም በሕዝቤ ላይ ይሠለጥናል አለው።
18 ፤ ሳኦልም በበሩ ወደ ሳሙኤል ቀርቦ። የባለ ራእዩ ቤት ወዴት እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለው።
19 ፤ ሳሙኤልም መልሶ ሳኦልን። ባለ ራእዩ እኔ ነኝ፤ ዛሬም ከእኔ ጋር ትበላላችሁና በፊቴ ወደ ኮረብታው መስገጃ ውጡ፤ ነገም አሰናብትሃለሁ፥ በልብህም ያለውን ሁሉ እነግርሃለሁ፤
20 ፤ ከሦስት ቀንም በፊት የጠፉ አህዮችህ ተገኝተዋልና ልብህን አትጣልባቸው። የእስራኤል ምኞት ለማን ነው? ለአንተና ለአባትህ ቤት አይደለምን? አለው።
21 ፤ ሳኦልም መልሶ። እኔ ከእስራኤል ነገዶች ከሚያንስ ወገን የሆንሁ ብንያማዊ አይደለሁምን? ወገኔስ ከብንያም ነገድ ወገኖች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? እንዲህስ ያለውን ነገር ለምን ነገርኸኝ? አለው።
22 ፤ ሳሙኤልም ሳኦልንና ብላቴናውን ወስዶ ወደ አዳራሽ አገባቸው፥ በመርፈቂያውም ራስ አስቀመጣቸው፤ የተጠሩትም ሠላሳ ሰዎች ያህል ነበሩ።
23 ፤ ሳሙኤልም ወጥቤቱን። በአንተ ዘንድ አኑረው ብዬ የሰጠሁህን እድል ፈንታ አምጣ አለው።
24 ፤ ወጥቤቱም ጭኑንና በእርሱ ላይ የነበረውን አምጥቶ በሳኦል ፊት አኖረው። ሳሙኤልም። ሕዝቡን ከጠራሁ ጀምሮ እስከ ተወሰነው ጊዜ ድረስ ለአንተ ተጠብቆአልና እነሆ፥ የተቀመጠልህን በፊትህ አኑረህ ብላው አለ። በዚያም ቀን ሳኦል ከሳሙኤል ጋር በላ።
25 ፤ ከኮረብታውም መስገጃ ወደ ከተማይቱ ወረዱ፤ ሳሙኤልም ለሳኦል በሰገነቱ ላይ መኝታ አዘጋጀለት፥ እርሱም ተኛ።
26 ፤ ማልዶም ተነሡ፤ በነጋም ጊዜ ሳሙኤል ሳኦልን ከሰገነቱ ላይ ጠርቶ። ተነሣና ላሰናብትህ አለው። ሳኦልም ተነሣ፥ እርሱና ሳሙኤልም ሁለቱ ወደ ሜዳ ወጡ።
27 ፤ እነርሱም በከተማይቱ ዳር ሲወርዱ ሳሙኤል ሳኦልን። ብላቴናውን ወደ ፊታችን እንዲያልፍ እዘዘው፤ አንተ ግን የእግዚአብሔርን ቃል አሰማህ ዘንድ በዚህ ቁም አለው። ብላቴናውም አለፈ።

1 ፤ ሳሙኤልም የዘይቱን ብርሌ ወስዶ በራሱ ላይ አፈሰሰው፥ ሳመውም፥ እንዲህም አለው። በርስቱ ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶሃል፤ የእግዚአብሔርንም ሕዝብ ትገዛለህ፥ በዙሪያውም ካሉ ጠላቶቻቸው እጅ ታድናቸዋለህ።
2 ፤ ዛሬ ከእኔ በተለየህ ጊዜ በብንያም ዳርቻ በጼልጻህ አገር ባለው በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ፤ እነርሱም። ልትሻቸው ሄደህ የነበርህላቸ አህዮች ተገኝተዋል፤ እነሆም፥ አባትህ ስለ አህዮች ማሰብ ትቶ። የልጄን ነገር እንዴት አደርጋለሁ? እያለ ስለ እናንተ ይጨነቃል ይሉሃል።
3 ፤ ከዚያም ደግሞ ወደ ፊት ትሄዳለህ፤ ወደ ታቦር ወደ ትልቁ ዛፍ ትደርሳለህ፤ በዚያም ሦስት ሰዎች፥ አንዱ ሦስት ሰዎች፥ አንዱ ሦስት የፍየል ጠቦቶች፥ ሁለተኛው ሦስት ዳቦ፥ ሦስተኛውም የወይን ጠጅ አቁማዳ ይዘው ወደ እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ሲወጡ ያገኙሃል፤
4 ፤ ሰላምታም ይሰጡሃል፥ ሁለትም ዳቦ ይሰጡሃል፥ ከእጃቸውም ትቀበላለህ።
5 ፤ ከዚያም በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ፤ ወደዚያም ወደ ከተማይቱ በደረስህ ጊዜ፥ በገናና ከበሮ እምቢልታና መሰንቆ ይዘው ትንቢት እየተናገሩ ከኮረብታው መስገጃ የሚወርዱ የነቢያት ጉባኤ ያገኙሃል።
6 ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ይወርድብሃል፥ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ትናገራለህ፥ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ።
7 ፤ እነዚህም ምልክቶች በደረሱህ ጊዜ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና እጅህ የምታገኘውን ሁሉ አድርግ።
8 ፤ በፊቴም ወደ ጌልገላ ትወርዳለህ፤ እኔም፥ እነሆ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀርብ ዘንድ፥ የደኅንነትም መሥዋዕት እሠዋ ዘንድ ወደ አንተ እወርዳለሁ፤ እኔ ወደ አንተ እስክመጣና የምታደርገውን እስክነግርህ ድረስ ሰባት ቀን ትቆያለህ።
9 ፤ ከሳሙኤልም ዘንድ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ እግዚአብሔር ሌላ ልብ ለወጠለት፤ በዚያም ቀን እነዚህ ምልክቶች ሁሉ ደረሱለት።
10 ፤ ወደዚያም ኮረብታ በደረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ የነቢያት ጉባኤ አገኙት፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ወረደበት፥ በመካከላቸውም ትንቢት ተናገረ።
11 ፤ ቀድሞም የሚያውቁት ሁሉ ከነቢያት ጋር ትንቢት ሲናገር ባዩት ጊዜ ሕዝቡ እርስ በርሳቸው። የቂስን ልጅ ያገኘው ምንድር ነው? በውኑ ሳኦል ከነቢያት ወገን ነውን? ተባባሉ።
12 ፤ ከዚያም ስፍራ ያለ አንድ ሰው። አባታቸውስ ማን ነው? ብሎ መለሰ። ስለዚህም። ሳኦል ደግሞ ከነቢያት ወገን ነውን? የሚል ምሳሌ ሆነ።
13 ፤ ትንቢት መናገሩንም በፈጸመ ጊዜ ወደ ኮረብታው መስገጃ መጣ።
14 ፤ አጎቱም ሳኦልንና ብላቴናውን፥ ወዴት ሄዳችሁ ኖሮአል? አላቸው። እርሱም። አህዮችን ልንሻ ሄደን ነበር፤ ባጣናቸውም ጊዜ ወደ ሳሙኤል መጣን አለ።
15 ፤ የሳኦልም አጎት። ሳሙኤል የነገረህን፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለው።
16 ፤ ሳኦልም አጎቱን። አህዮች እንደ ተገኙ ገለጠልን አለው፤ ነገር ግን ሳሙኤል የነገረውን የመንግሥትን ነገር አላወራለትም።
17 ፤ ሳሙኤልም ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ጠራ።
18 ፤ የእስራኤልንም ልጆች። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስራኤልን ከግብጽ አወጣሁ፥ ከግብጻውያንም እጅ ከሚያስጨንቁአችሁም ነገሥታት ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ።
19 ፤ ዛሬ ግን ከመከራችሁና ከጭንቃችሁ ሁሉ ያዳናችሁን አምላካችሁን ንቃችሁ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ አታንግሥልን አላችሁት። አሁንም በየነገዳችሁና በየወገናችሁ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ አላቸው።
20 ፤ ሳሙኤልም የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ አቀረበ፥ ዕጣውም በብንያም ነገድ ላይ ወደቀ።
21 ፤ የብንያምንም ነገድ በየወገናቸው አቀረበ፥ ዕጣውም በማጥሪ ወገን ላይ ወደቀ። የማጥሪንም ወገን በየሰዉ አቀረበ፥ ዕጣውም በቂስ ልጅ በሳኦል ላይ ወደቀ፤ ፈለጉትም፥ አላገኙትምም።
22 ፤ ከእግዚአብሔርም። ገና ወደዚህ የሚመጣ ሰው አለን? ብለው ደግሞ ጠየቁት፤ እግዚአብሔርም። እነሆ፥ በዕቃ መካከል ተሸሽጎአል ብሎ መለሰ።
23 ፤ እነርሱም ሮጠው ከዚያ አመጡት፤ እርሱም በሕዝቡ መካከል ቆመ፥ ከሕዝቡም ሁሉ ይልቅ ከትከሻው ወደ ላይ ከፍ ያለ ቁመተ ረጅም ነበረ።
24 ፤ ሳሙኤልም ለሕዝቡ ሁሉ። ከሕዝቡ ሁሉ እርሱን የሚመስል እንደሌለ እግዚአብሔር የመረጠውን ታያላችሁን? አላቸው፤ ሕዝቡም ሁሉ። ንጉሥ ሕያው ይሁን እያሉ እልልታ አደረጉ።
25 ፤ ሳሙኤልም የመንግሥቱን ወግ ነገረ፥ በመጽሐፍም ጻፈው በእግዚአብሔርም ፊት አኖረው። ሳሙኤልም ሕዝቡን ሁሉ ወደ እየቤታቸው አሰናበታቸው።
26 ፤ ሳኦልም ወደ ቤቱ ወደ ጊብዓ ሄደ፤ እግዚአብሔር ልባቸውን የነካ ኃያላንም ከእርሱ ጋር ሄዱ።
27 ፤ ምናምንቴዎች ሰዎች ግን። ይህ ሰው እንዴት ያድነናል? ብለው ናቁት፥ እጅ መንሻም አላመጡለትም።

1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ከአንድ ወር በኋላ አሞናዊው ናዖስ ወጣ፥ በኢያቢስ ገለዓድም ሰፈረ፤ የኢያቢስም ሰዎች ሁሉ። ቃል ኪዳን አድርግልን፥ እኛም እንገዛልሃለን አሉት።
2 ፤ አሞናዊውም ናዖስ። ቀኝ ዓይናችሁን ሁሉ በማውጣት ቃል ኪዳን አደርግላችኋለሁ፤ በእስራኤልም ሁሉ ላይ ስድብ አደረጋለሁ አላቸው።
3 ፤ የኢያቢስም ሽማግሌዎች። ወደ እስራኤል አገር ሁሉ መልክተኞችን እንድንልክ ሰባት ቀን ቆይልን፤ ከዚያም በኋላ የሚያድነን ባይኖር ወደ አንተ እንመጣለን አሉት።
4 ፤ መልክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው ይህን ነገር በሕዝቡ ጆሮ ተናገሩ፤ ሕዝቡም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ።
5 ፤ እነሆም፥ ሳኦል በሬዎቹን ተከትሎ ከእርሻው መጣ፤ ሳኦልም። ሕዝቡ የሚያለቅስ ምን ሆኖ ነው? አለ። የኢያቢስንም ሰዎች ነገር ነገሩት።
6 ፤ ይህንም ነገር በሰማው ጊዜ በሳኦል ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ወረደ፥ ቍጣውም እጅግ ነደደ።
7 ፤ ጥምዱንም በሬዎች ወስዶ ቈራረጣቸው፥ ወደ እስራኤልም ዳርቻ ሁሉ በመልክተኞቹ እጅ ሰደደና። ሳኦልንና ሳሙኤልን ተከትሎ የማይወጣ ሁሉ፥ በበሬዎቹ እንዲሁ ይደረግ አለ። ድንጋጤም በሕዝቡ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደቀ፥ እንደ አንድ ሰውም ሆነው ወጡ።
8 ፤ በቤዜቅም ቈጠራቸው፤ የእስራኤልም ልጆች ሦስት መቶ ሺህ፥ የይሁዳም ሰዎች ሠላሳ ሺህ ነበሩ።
9 ፤ የመጡትንም መልክተኞች። የኢያቢስ ገለዓድን ሰዎች። ነገ ፀሐይ በተኮሰ ጊዜ ማዳን ይሆንላችኋል በሉአቸው አሉአቸው። መልክተኞችም መጥተው ለኢያቢስ ሰዎች ነገሩ፤ ደስም አላቸው።
10 ፤ የአያቢስም ሰዎች። ነገ እንወጣላችኋለን፥ ደስ የሚያሰኛችሁንም አድርጉብን አሉ።
11 ፤ በነጋውም ሳኦል ሕዝቡን በሦስት ወገን አደረጋቸው፤ ወገግም ባለ ጊዜ ወደ ሰፈሩ መካከል ገቡ፥ ቀትርም እስኪሆን ድረስ አሞናውያንን መቱ፤ የቀሩትም ተበተኑ፥ ሁለትም በአንድ ላይ ሆነው አልቀሩላቸውም።
12 ፤ ሕዝቡም ሳሙኤልን። ሳኦል አይንገሥብን ያሉ እነማናቸው? አውጡአቸውና እንግደላቸው አሉት።
13 ፤ ሳኦልም። ዛሬ እግዚአብሔር ለእስራኤል ማዳን አድርጎአልና ዛሬ አንድ ሰው አይሞትም አለ።
14 ፤ ሳሙኤልም ሕዝቡን። ኑ፥ ወደ ጌልገላ እንሂድ፥ በዚያም መንግሥቱን እናድስ አላቸው።
15 ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ጌልገላ ሄዱ፥ በዚያም ሳኦልን በእግዚአብሔር ፊት በጌልገላ አነገሡት፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት የደኅንነት መሥዋዕት አቀረቡ፤ በዚያም ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ታላቅ ደስታ አደረጉ።

1 ፤ ሳሙኤልም እስራኤልን ሁሉ አለ። የነገራችሁኝን ሁሉ ሰምቼ አንግሼላችኋለሁ።
2 ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ ንጉሡ በፊታችሁ ይሄዳል፤ እኔም አርጅቻለሁ ሸምግያለሁም፤ እነሆም፥ ልጆቼ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔም ከሕፃንነቴ ጀምሬ እስከ ዛሬ ድረስ በፊታችሁ ሄድሁ።
3 ፤ እነሆኝ፤ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ፤ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንንስ አህያ ወሰድሁ? ማንንስ ሸነገልሁ? በማንስ ላይ ግፍ አደረግሁ? ዓይኖቼንስ ለማሳወር ከማን ጋር እጅ ጉቦ ተቀበልሁ? እኔም እመልስላችኋለሁ።
4 ፤ እነርሱም። አልሸነገልኸንም፥ ግፍም አላደረግህብንም፥ ከሰውም እጅ ምንም አልወሰድህም አሉ።
5 ፤ እርሱም። በእጄ ምንም እንዳላገኛችሁ እግዚአብሔርና እርሱ የቀባው ዛሬ በእናንተ ላይ ምስክሮች ናቸው አላቸው፤ እነርሱም። ምስክር ነው አሉ።
6 ፤ ሳሙኤልም ሕዝቡን አለ። ሙሴንና አሮንን ያላቀ፥ አባቶቻችሁንም ከግብጽ ምድር ያወጣ እግዚአብሔር ነው።
7 ፤ አሁንም እግዚአብሔር ለእናንተና ለአባቶቻችሁ ስላደረገው ጽድቅ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እምዋገታችሁ ዘንድ በዚህ ቁሙ።
8 ፤ ያዕቆብና ልጆቹ ወደ ግብጽ በገቡ ጊዜ ግብጻውያን አስጨነቁአቸው፤ አባቶቻችሁም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን ላከ፥ አባቶቻችሁንም ከግብጽ አውጥተው በዚህ ቦታ አኖሩአቸው።
9 ፤ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ፥ ለአሶር ሠራዊትም አለቃ ለሲሣራ እጅ፥ ለፍልስጥኤማውያንም እጅ፥ ለሞዓብም ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ ከእነርሱም ጋር ተዋጉ።
10 ፤ እነርሱም። እግዚአብሔርን ትተን በኣሊምንና አስታሮትን በማምለካችን በድለናል፤ አሁንም ከጠላቶቻችን እጅ አድነን፥ እናመልክህማለን ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
11 ፤ እግዚአብሔርም ይሩበአልም፥ ባርቅንም፥ ዮፍታሔንም፥ ሳሙኤልንም ላከ፥ በዙሪያችሁም ካሉት ከጠላቶቻችሁ እጅ አዳናችሁ፤ ተዘልላችሁም ተቀመጣችሁ።
12 ፤ የአሞንም ልጆች ንጉሥ ናዖስ እንደ መጣባችሁ ባያችሁ ጊዜ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ንጉሣችሁ ሳለ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይንገሥልን አላችሁኝ።
13 ፤ አሁንም የመረጣችሁትንና የፈለጋችሁትን ንጉሥ እዩ፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ንጉሥ አደረገላችሁ።
14 ፤ እግዚአብሔርን ብትፈሩ ብታመልኩትም፥ ቃሉንም ብትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ባታምፁ፥ እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ብትከተሉ፥ መልካም ይሆንላችኋል።
15 ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ብታምፁ፥ በእናንተና በንጉሣችሁ ላይ የእግዚአብሔር እጅ ትሆናለች።
16 ፤ አሁንም ቁሙ፥ እግዚአብሔርም በዓይናችሁ ፊት ወደሚያደርገው ወደዚህ ታላቅ ነገር ተመልከቱ።
17 ፤ የስንዴ መከር ዛሬ አይደለምን? ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ፥ እርሱም ነጎድጓድና ዝናብ ይልካል፤ እናንተም ንጉሥ በመለመናችሁ በእግዚአብሔር ፊት ያደረጋችሁት ክፋት ታላቅ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ ታያላችሁም።
18 ፤ ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፥ እግዚአብሔርም በዚያን ቀን ነጐድጓድና ዝናብ ላከ፤ ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርንና ሳሙኤልን እጅግ ፈሩአቸው።
19 ፤ ሕዝቡም ሁሉ ሳሙኤልን። ንጉሥ በመለመናችን በኃጢአታችን ሁሉ ላይ ይህን ክፋት ጨምረናልና እንዳንሞት ስለ ባሪያዎችህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ አሉት።
20 ፤ ሳሙኤልም ሕዝቡን አለ። አትፍሩ፤ በእውነት ይህን ክፋት ሁሉ አደረጋችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ አምልኩት እንጂ እግዚአብሔርን ከመከተል ፈቀቅ አትበሉ።
21 ፤ ምናምንቴ ነውና የማይረባንና የማያድን ከንቱን ነገር ለመከተል ፈቀቅ አትበሉ።
22 ፤ እግዚአብሔር ለእርሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ወድዶአልና እግዚአብሔር ስለ ታላቅ ስሙ ሕዝቡን አይተውም።
23 ፤ ደግሞ መልካሙንና ቅኑን መንገድ አስተምራችኋለሁ እንጂ ስለ እናንተ መጸለይን በመተው እግዚአብሔርን እበድል ዘንድ ይህ ከእኔ ይራቅ።
24 ፤ ብቻ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ያደረገላችሁንም ታላቅ ነገር አይታችኋልና በፍጹም ልባችሁ በእውነት አምልኩት።
25 ፤ ነገር ግን ክፉ ብትሠሩ እናንተም ንጉሣችሁም ትጠፋላችሁ።

1 ፤ ሳኦልም በእስራኤል ላይ ሁለት ዓመት ከነገሠ በኋላ፥
2 ፤ ሳኦል ሦስት ሺህ ሰዎች ከእስራኤል መረጠ፤ ሁለቱም ሺህ በማክማስና በቤቴል ተራራ ከሳኦል ጋር ነበሩ፥ አንዱም ሺህ በብንያም ጊብዓ ከዮናታን ጋር ነበሩ፤ የቀረውንም ሕዝብ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ አሰናበተ።
3 ፤ ዮናታንም በናሲብ ውስጥ የነበረውን የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መታ፥ ፍልስጥኤማውያንም ያን ሰሙ፤ ሳኦልም። ዕብራውያን ይስሙ ብሎ በአገሩ ሁሉ ቀንደ መለከት ነፋ።
4 ፤ እስራኤልም ሁሉ ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ እንደ መታ፥ ደግሞም እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ ተጸየፉ ሰሙ፤ ሕዝቡም ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ።
5 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ተሰበሰቡ፤ ሠላሳ ሺህ ሰረገሎች ስድስትም ሺህ ፈረሰኞች በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበሩ፤ ወጥተውም ከቤትአዌን በምሥራቅ በኩል በማክማስ ሰፈሩ።
6 ፤ ሕዝቡም ተጨንቀው ነበርና የእስራኤል ሰዎች በጭንቀት እንዳሉ ባዩ ጊዜ ሕዝቡ በዋሻና በእሾህ ቍጥቋጦ በገደልና በግንብ በጕድጓድም ውስጥ ተሸሸጉ።
7 ፤ ከዕብራውያንም ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ፤ ሳኦል ግን ገና በጌልገላ ነበረ፥ ሕዝቡም ሁሉ ተንቀጥቅጠው ተከተሉት።
8 ፤ ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ቀጠረው ጊዜ ሰባት ቀን ቆየ፤ ሳሙኤል ግን ወደ ጌልገላ አልመጣም፥ ሕዝቡም ከእርሱ ተለይተው ተበታተኑ።
9 ፤ ሳኦልም። የሚቃጠል መሥዋዕትና የደኅንነት መሥዋዕት አምጡልኝ አለ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ።
10 ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማሳረግ በፈጸመ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም እንዲመርቀው ሊገናኘው ወጣ።
11 ፤ ሳሙኤልም። ያደረግኸው ምንድር ነው? አለ። ሳኦልም። ሕዝቡ ከእኔ ተለይተው እንደ ተበታተኑ፥ አንተም በቀጠሮው እንዳልመጣህ፥ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ማክማስ እንደ ተሰበሰቡ አየሁ፤
12 ፤ ሰለዚህ። ፍልስጥኤማውያን አሁን ወደ ጌልገላ ይወርዱብኛል፥ እኔም የእግዚአብሔርን ሞገስ አልለመንሁም አልሁ፤ ስለዚህም ሳልታገሥ የሚቃጠልን መሥዋዕት አሳረግሁ አለ።
13 ፤ ሳሙኤልም ሳኦልን። አላበጀህም፤ አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ዛሬ እግዚአብሔር መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጽንቶልህ ነበረ።
14 ፤ አሁንም መንግሥትህ አይጸናም፤ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል፤ እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበቅህምና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዞታል አለው።
15 ፤ ሳሙኤልም ከጌልገላ ተነሥቶ መንገዱን ሄደ፤ የቀሩትም ሕዝብ ሳኦልን ተከተለው ሰልፈኞቹን ሊገናኙ ሄዱ። ከጌልገላም ተነሥተው ወደ ብንያም ጊብዓ መጡ፤ ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቈጠረ፥ ስድስት መቶም የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ።
16 ፤ ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ከእነርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ በብንያም ጊብዓ ተቀመጡ፤ ፍልስጥኤማውያንም በማክማስ ሰፈሩ።
17 ፤ ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር ማራኪዎች በሦስት ክፍል ሆነው ወጡ፤ አንዱም ክፍል በዖፍራ መንገድ ወደ ሦጋል ምድር ሄደ።
18 ፤ ሁለተኛው ክፍል ወደ ቤት ሖሮን መንገድ ዞረ፤ ሦስተኛውም ክፍል በበረሃው አጠገብ ባለው ወደ ስቦይም ሸለቆ በሚመለከተው በዳርቻ መንገድ ዞረ።
19 ፤ ፍልስጥኤማውያንም። ዕብራውያን ሰይፍና ጦር እንዳይሠሩ ብለው ነበርና በእስራኤል ምድር ሁሉ ብረተ ሠሪ አልተገኘም።
20 ፤ እስራኤልም ሁሉ የማረሻውን ጫፍና ማጭዱን መጥረቢያውንና መቆፈሪያውን ይስል ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን ይወርድ ነበር።
21 ፤ ለማረሻው ጫፍና ለመቆፈሪያው ዋጋው የሰቅል ከ3 እጅ 2ቱ እጅ ነበረ። መጥረቢያውንም ለማሳል መውጊያውንም ለማበጀት ዋጋው የሰቅል ከ3 እጅ 1ዱ እጅ ነበረ።
22 ፤ ስለዚህም በሰልፍ ቀን ሰይፍና ጦር ከሳኦልና ከዮናታን ጋር በነበሩ ሕዝብ ሁሉ እጅ አልተገኘም፤ ብቻ በሳኦልና በልጁ በዮናታን ዘንድ ተገኘ። የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ ወደ ማክማስ መተላለፊያ ወጡ።

1 ፤ አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ የሳኦል ልጅ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን። ና፥ በዚያ በኩል ወዳለው ወደ ፍልስጥኤማውያን ጭፍራ እንለፍ አለው፤ ለአባቱም አልነገረውም።
2 ፤ ሳኦልም በመጌዶን ባለው በሮማኑ ዛፍ በታች በጊብዓ ዳርቻ ተቀምጦ ነበረ፤ ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ስድስት መቶ የሚያህል ሰው ነበረ።
3 ፤ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ የፊንሐስ ልጅ የዔሊ ልጅ በሴሎ ለእግዚአብሔር ካህን የሆነ ኤፉድም የለበሰ አኪያ አብሮ ነበር፤ ሕዝቡ ዮናታን እንደ ሄደ አላወቁም።
4 ፤ ዮናታንም ወደ ፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ሊሻገርበት በወደደው መተላለፊያ መካከል በወዲህ አንድ ሾጣጣ በወዲህ አንድ ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፤ የአንዱም ስም ቦጼጽ የሁለተኛውም ስም ሴኔ ነበረ።
5 ፤ አንዱም ሾጣጣ በማክማስ አንጻር በሰሜን በኩል፥ ሁለተኛውም በጊብዓ አንጻር በደቡብ በኩል የቆሙ ነበሩ።
6 ፤ ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን። ና፥ ወደ እነዚህ ቈላፋን ጭፍራ እንለፍ፤ በብዙ ወይም በጥቂት ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና ምናልባት እግዚአብሔር ይሠራልን ይሆናል አለው።
7 ፤ ጋሻ ጃግሬውም። ልብህ ያሰኘህን ሁሉ አድርግ፤ እነሆ፥ ከአንተ ጋር ነኝ፤ እንደ አንተ ልብ ሁሉ የእኔም ልብ እንዲሁ ነው አለው።
8 ፤ ዮናታንም አለ። እነሆ፥ ወደ ሰዎቹ እናልፋለን እንገለጥላቸውማለን፤
9 ፤ እነርሱም። ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ ቆዩ ቢሉን በስፍራችን እንቆማለን፥ ወደ እነርሱም አንወጣም።
10 ፤ ነገር ግን። ወደ እኛ ውጡ ቢሉን እግዚአብሔር በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና እንወጣለን፤ ምልክታችንም ይህ ይሆናል።
11 ፤ ሁለታቸውም ለፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ተገለጡ፤ ፍልስጥኤማውያንም። እነሆ፥ ዕብራውያን ከተሸሸጉበት ጕድጓድ ይወጣሉ አሉ።
12 ፤ የጭፍራው ሰዎችም ዮናታንንና ጋሻ ጃግሬውን። ወደ እኛ ውጡ፥ አንድ ነገርም እናሳያችኋለን አሉ። ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን። እግዚአብሔር በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና ተከተለኝ አለው።
13 ፤ ዮናታንም በእጁና በእግሩ ወጣ፥ ጋሻ ጃግሬውም ተከተለው፤ ፍልስጥኤማውያንም በዮናታን እጅ ወደቁ፥ ጋሻ ጃግሬውም ተከትሎ ገደላቸው።
14 ፤ የዮናታንና የጋሻ ጃግሬውም የመጀመሪያ ግዳያቸው በአንድ ትልም እርሻ መካከል ሀያ ያህል ሰው ነበረ።
15 ፤ በሰፈሩም በእርሻውና በሕዝቡም ሁሉ መካከል ሽብር ነበረ፤ በሰፈሩ የተቀመጡና ለምርኮ የወጡት ተሸበሩ፤ ምድሪቱም ተናወጠች፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ሽብር ሆነ።
16 ፤ በብንያም ጊብዓ ያሉ የሳኦል ዘበኞችም ተመለከቱ፤ እነሆም፥ ሠራዊቱ ወዲህና ወዲያ እየተራወጡ ተበታተኑ።
17 ፤ ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ። እስኪ ተቋጠሩ፥ ከእኛ ዘንድ የሄደ ማን እንደሆነ ተመልከቱ አላቸው። በተቋጠሩም ጊዜ እነሆ፥ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም።
18 ፤ በዚያም ቀን አኪያ በእስራኤል ልጆች ፊት ኤፉድ ለብሶ ነበርና ሳኦል። ኤፉድን አምጣ አለው።
19 ፤ ሳኦል ከካህኑ ጋር ሲነጋገር በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ግርግርታ እየበዛና እየጠነከረ ሄደ፤ ሳኦልም ካህኑን። እጅህን መልስ አለው።
20 ፤ ሳኦልና ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተሰብስበው ወደ ውጊያው መጡ፤ እነሆም፥ የእያንዳንዱ ሰው ሰይፍ በባልንጀራው ላይ ነበረ፥ እጅግም ታላቅ ድንጋጤ ሆነ።
21 ፤ ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጋር የነበሩት ከእነርሱም ጋር ከሰፈሩ ዙሪያ የወጡት ዕብራውያን ደግሞ ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደ ነበሩት አስራኤላውያን ለመሆን ዞሩ።
22 ፤ ከእስራኤልም ሰዎች በተራራማው በኤፍሬም አገር የተሸሸጉት ሁሉ ፍልስጥኤማውያን እንደ ኰበለሉ በሰሙ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ሊዋጉአቸው ተከትለው ገሠገሡ።
23 ፤ እግዚአብሔርም በዚያ ቀን እስራኤልን አዳነ፤ ውጊያውም በቤትአዌን በኩል አለፈ። ከሳኦልም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ አሥር ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ፤ ውጊያውም በተራራማው በኤፍሬም አገር ሁሉ ተበታትኖ ነበር።
24 ፤ የእስራኤልም ሰዎች በዚያ ቀን ተጨነቁ፤ ሳኦል። ጠላቶቼን እስክበቀል እስከ ማታ ድረስ መብል የሚበላ ሰው ርጉም ይሁን ብሎ ሕዝቡን አምሎአቸው ነበርና። ሕዝቡም ሁሉ መብል አልቀመሱም።
25 ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ዱር ገባ፤ ማርም በምድር ላይ ነበረ።
26 ፤ ሕዝቡም ወደ ዱር በገባ ጊዜ እነሆ፥ የሚፈስስ ማር ነበረ፤ ሕዝቡ መሐላውን ፈርቶ ነበርና ማንም እጁን ወደ አፉ አላደረገም።
27 ፤ ዮናታን ግን አባቱ ሕዝቡን ባማለ ጊዜ አልሰማም ነበር፤ እርሱም በእጁ ያለችውን በትር ጫፍዋን ወደ ወለላው ነከረ፥ እጁንም ወደ አፉ አደረገ፤ ዓይኑም በራ።
28 ፤ ከሕዝቡም አንድ ሰው መልሶ። አባትህ። ዛሬ መብል የሚበላ ሰው ርጉም ይሁን ብሎ ሕዝቡን መሐላ አምሎአቸዋል አለው፤ ሕዝቡም ደከሙ።
29 ፤ ዮናታንም። አባቴ ምድሪቱን አስቸገረ፤ ከዚህ ማር ጥቂት ብቀምስ ዓይኔ እንደ በራ እዩ።
30 ፤ ይልቅስ ሕዝቡ ካገኙት ከጠላቶቻቸው ምርኮ በልተው ቢሆኑ የፍልስጥኤማውያን መመታት ይበልጥ አልነበረምን? አለ።
31 ፤ በዚያም ቀን ፍልስጥኤማውያንን ከማክማስ እስከ ኤሎን ድረስ መቱአቸው፤ ሕዝቡም እጅግ ደከሙ።
32 ፤ ሕዝቡም ለምርኮ ሳሱ፤ በጎችን በሬዎችንም ጥጆችንም ወስደው በምድር ላይ አረዱ፤ ሕዝቡም ከደሙ ጋር በሉ።
33 ፤ ለሳኦልም። እነሆ፥ ሕዝቡ ከደሙ ጋር በመብላታቸው እግዚአብሔርን በደሉ ብለው ነገሩት። ሳኦልም። እጅግ ተላለፋችሁ፤ አሁንም ትልቅ ድንጋይ አንከባልላችሁ አቅርቡልኝ አላቸው።
34 ፤ ሳኦልም። በሕዝቡ መካከል እየዞራችሁ። እያንዳንዱ ሰው በሬውንና በጉን ወደ እኔ ያቅርብ፥ በዚህም እረዱና ብሉ፤ ከደሙም ጋር በመብላታችሁ እግዚአብሔርን አትበድሉ በሉአቸው አለው። እያንዳንዱም ሰው ሁሉ በእጁ ያለውን በሬውን በዚያች ሌሊት አቀረበ፥ በዚያም አረደው።
35 ፤ ሳኦልም ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ፤ ይኸውም ለእግዚአብሔር የሠራው መጀመሪያ መሠዊያ ነው።
36 ፤ ሳኦልም። ፍልስጥኤማውያንን በሌሊት ተከትለን እስኪነጋ ድረስ እንበዝብዛቸው፤ አንድ ሰው እንኳ አናስቀርላቸው አለ። እነርሱም። ደስ የሚያሰኝህን ሁሉ አድርግ አሉት። ካህኑም። ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ አለ።
37 ፤ ሳኦልም። ፍልስጥኤማውያንን ልከተልን? በእስራኤልስ እጅ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀው። በዚያ ቀን ግን አልመለሰለትም።
38 ፤ ሳኦልም። እናንተ የሕዝቡ አለቆች ሁሉ፥ ወደዚህ ቅረቡ፤ ዛሬ ይህ ኃጢአት በምን እንደ ሆነ እወቁ፥ ተመልከቱም፤
39 ፤ እስራኤልን የሚያድን ሕያው እግዚአብሔርን! ኃጢአቱ በልጄ በዮናታን ቢሆን ፈጽሞ ይሞታል አለ። ከሕዝቡም ሁሉ አንድ የመለሰለት ሰው አልነበረም።
40 ፤ እስራኤልንም ሁሉ። እናንተ በአንድ ወገን ሁኑ፥ እኔና ልጄ ዮናታንም በሌላ ወገን እንሆናለን አለ። ሕዝቡም ሳኦልን ደስ የሚያሰኝህን አድርግ አሉት።
41 ፤ ሳኦልም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን። እውነትን ግለጥ አለው። ሳኦልና ዮናታንም ተያዙ፤ ሕዝቡም ነጻ ሆነ።
42 ፤ ሳኦልም። በእኔና በልጄ በዮናታን መካከል ዕጣ ጣሉ አለ። ዮናታንም ተያዘ።
43 ፤ ሳኦልም ዮናታንን። ያደረግኸውን ንገረኝ አለው፤ ዮናታንም። በእጄ ባለው በበትሬ ጫፍ ጥቂት ማር በእርግጥ ቀምሻለሁ፤ እነሆኝ፥ እሞታለሁ ብሎ ነገረው።
44 ፤ ሳኦልም። እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብኝ እንዲህም ይጨምርብኝ፤ ዮናታን ሆይ፥ ፈጽመህ ትሞታለህ አለ።
45 ፤ ሕዝቡም ሳኦልን። በውኑ በእስራኤል ዘንድ ታላቅ መድኃኒት ያደረገ ዮናታን ይሞታልን? ይህ አይሁን፤ ዛሬ ከእግዚአብሔር ጋር አድርጎአልና ሕያው እግዚአብሔርን! ከራሱ ጠጕር አንዲት በምድር ላይ አትወድቅም አሉት። ሕዝቡም እንዳይሞት ዮናታንን አዳነው።
46 ፤ ሳኦልም ፍልስጥኤማውያንን ከመከተል ተመለሰ፤ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ስፍራቸው ሄዱ።
47 ፤ ሳኦልም መንግሥቱን በእስራኤል ላይ አጸና፤ በዙሪያውም ካሉት ከጠላቶቹ ሁሉ ጋር፥ ከሞዓብም፥ ከአሞንም ልጆች፥ ከኤዶምያስም፥ ከሱባም ነገሥታት፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ይዋጋ ነበር፤ በየሄደበትም ሁሉ ድል ይነሣ ነበር።
48 ፤ እርሱም ጀግና ነበረ፥ አማሌቃውያንንም መታ፥ እስራኤልንም ከዘራፊዎቹ እጅ አዳነ።
49 ፤ የሳኦልም ወንዶች ልጆች ዮናታን፥ የሱዊ፥ ሜልኪሳ ነበሩ፤ የሁለቱም ሴቶች ልጆቹ ስም ይህ ነበረ፤ የታላቂቱ ስም ሜሮብ፥ የታናሺቱም ስም ሜልኮል ነበረ።
50 ፤ የሳኦልም ሚስት ስም የአኪማአስ ልጅ አኪናሆም ነበረ፤ የሠራዊቱም አለቃ ስም የሳኦል አጎት የኔር ልጅ አበኔር ነበረ።
51 ፤ የሳኦልም አባት ቂስ ነበረ፤ የአበኔርም አባት ኔር የአቢኤል ልጅ ነበረ።
52 ፤ በሳኦልም ዕድሜ ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጽኑ ውጊያ ነበረ፤ ሳኦልም ጽኑ ወይም ኃያል ሰው ባየ ጊዜ ወደ እርሱ ይሰበስብ ነበር።

1 ፤ ሳሙኤልም ሳኦልን አለው። በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንድትሆን እቀባህ ዘንድ እግዚአብሔር ላከኝ፥ አሁንም የእግዚአብሔርን ድምፅ ስማ።
2 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ አማሌቅ በመንገድ እየተቃወመ ያደረገበትን እበቀላለሁ።
3 ፤ አሁንም ሄደህ አማሌቅን ምታ፥ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፥ አትማራቸውም፤ ወንዱንና ሴቱን ብላቴናውንና ሕፃኑን በሬውንና በጉን ግመሉንና አህያውን ግደል።
4 ፤ ሳኦልም ሕዝቡን ጠርቶ በጌልገላ ቈጠራቸው፤ ሁለት መቶ ሺህ እግረኞች፥ ከይሁዳም አሥር ሺህ ሰዎች ነበሩ።
5 ፤ ሳኦልም ወደ አማሌቅ ከተማ ወጣ፥ በሸለቆውም ውስጥ ተደበቀ።
6 ፤ ሳኦል ቄናውያንን። ተነሥታችሁ ሂዱ፤ ከግብጽ በወጡ ጊዜ ለእስራኤል ልጆች ቸርነት አድርጋችኋልና ከአማሌቅ ጋር እንዳላጠፋችሁ ከመካከላቸው ውረዱ አላቸው፤ ቄናውያንም ከአማሌቃውያን መካከል ሄዱ።
7 ፤ ሳኦልም አማሌቃውያንን ከኤውላጥ ጀምሮ በግብጽ ፊት እስካለችው እስከ ሱር ድረስ መታቸው።
8 ፤ የአማሌቅንም ንጉሥ አጋግን በሕይወቱ ማረከው፥ ሕዝቡንም ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋቸው።
9 ፤ ነገር ግን ሳኦልና ሕዝቡ ለአጋግ፥ ለተመረጡትም በጎችና በሬዎች ለሰቡትም ጥጆችና ጠቦቶች፥ ለመልካሞቹም ሁሉ ራሩላቸው፥ ፈጽሞ ሊያጠፉአቸውም አልወደዱም፤ ነገር ግን ምናምንቴንና የተናቀውን ሁሉ ፈጽመው አጠፉት።
10፤11 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል። ሳኦል እኔ ከመከተል ተመልሶአልና፥ ትእዛዜንም አልፈጸመምና ስላነገሥሁት ተጸጸትሁ ብሎ ወደ ሳሙኤል መጣ። ሳሙኤልም ተቈጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
12 ፤ ሳሙኤልም በነጋው ሳኦልን ለመገናኘት ማለደ። ሳኦልም ወደ ቀርሜሎስ መጣ፤ እነሆም፥ የመታሰቢያ ዓምድ ባቆመ ጊዜ ዞሮ አለፈ፥ ወደ ጌልገላም ወረደ የሚል ወሬ ለሳሙኤል ደረሰለት።
13 ፤ ሳሙኤልም ወደ ሳኦል መጣ፤ ሳኦልም። አንተ ለእግዚአብሔር የተባረክህ ሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ አለው።
14 ፤ ሳሙኤልም። ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድር ነው? አለ።
15 ፤ ሳኦልም። ሕዝቡ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ይሠዉአቸው ዘንድ መልካሞቹን በጎችና በሬዎች አድነዋቸዋልና ከአማሌቃውያን አምጥተዋቸዋል፤ የቀሩትንም ፈጽመን አጠፋን አለው።
16 ፤ ሳሙኤልም ሳኦልን። ቆይ፥ እግዚአብሔር ዛሬ ሌሊት የነገረኝን ልንገርህ አለው፤ እርሱም። ተናገር አለው።
17 ፤ ሳሙኤልም አለ። በዓይንህ ምንም ታናሽ ብትሆን ለእስራኤል ነገዶች አለቃ አልሆንህምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባህ።
18 ፤ እግዚአብሔርም። ሄደህ ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፥ እስኪጠፉም ድረስ ውጋቸው ብሎ በመንገድ ላከህ።
19 ፤ ለምርኮ ሳስተህ ለምን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህም? ለምንስ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረግህ?
20 ፤ ሳኦልም ሳሙኤልን። የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቻለሁ፥ እግዚአብሔርም በላከኝ መንገድ ሄጃለሁ፤ የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጥቻለሁ፥ አማሌቃውያንንም ፈጽሜ አጥፍቻለሁ።
21 ፤ ሕዝቡ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በጌልገላ ይሠዉ ዘንድ ከእርሙ የተመረጡትን በጎችንና በሬዎችን ከምርኮው ወሰዱ አለው።
22 ፤ ሳሙኤልም። በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል።
23 ፤ ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ ኃጢአት፥ እልከኝነትም ጣዖትንና ተራፊምን እንደ ማምለክ ነው፤ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ አለ።
24 ፤ ሳኦልም ሳሙኤልን። ሕዝቡን ስለ ፈራሁ፥ ቃላቸውንም ስለ ሰማሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና የአንተን ቃል በመተላለፍ በድያለሁ።
25 ፤ አሁንም፥ እባክህ፥ ኃጢአቴን ይቅር በለኝ፥ ለእግዚአብሔርም እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ አለው።
26 ፤ ሳሙኤልም ሳኦልን። የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና፥ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃልና ከአንተ ጋር አልመለስም አለው።
27 ፤ ሳሙኤልም ሊሄድ ዘወር ባለ ጊዜ ሳኦል የልብሱን ጫፍ ያዘ፥ ተቀደደም።
28 ፤ ሳሙኤልም። እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀደዳት፥ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጣት፤
29 ፤ የእስራኤል ኃይል እንደ ሰው የሚጸጸት አይደለምና አይዋሽም አይጸጸትምም አለው።
30 ፤ እርሱም። በድያለሁ፤ አሁን ግን በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊትና በእስራኤል ፊት፥ እባክህ፥ አክብረኝ፤ ለአምላክህም ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ አለው።
31 ፤ ሳሙኤልም ከሳኦል በኋላ ተመለሰ፤ ሳኦልም ለእግዚአብሔር ሰገደ።
32 ፤ ሳሙኤልም። የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጡልኝ አለ። አጋግም እየተንቀጠቀጠ ወደ እርሱ መጣ። አጋግም። በውኑ ሞት እንደዚህ መራራ ነውን? አለ።
33 ፤ ሳሙኤልም። ሰይፍህ ሴቶችን ልጆች አልባ እንዳደረገቻቸው እንዲሁ እናትህ በሴቶች መካከል ልጅ አልባ ትሆናለች አለ፤ ሳሙኤልም አጋግን በእግዚአብሔር ፊት በጌልገላ ቈራረጠው።
34 ፤ ሳሙኤልም ወደ አርማቴም ሄደ፤
35 ፤ ሳኦልም ወደ ቤቱ ወደ ጊብዓ ወጣ። ሳሙኤልም እስከ ሞተበት ቀን ድረስ ሳኦልን ለማየት ዳግመኛ አልሄደም፥ ሳሙኤልም ለሳኦል አለቀሰ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ሳኦልን ስላነገሠ ተጸጸተ።

1 ፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን። በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? በቀንድህ ዘይቱን ሞልተህ ሂድ፤ በልጆቹ መካከል ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ አለው።
2 ፤ ሳሙኤልም። እንዴት እሄዳለሁ? ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል አለ። እግዚአብሔርም። አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፥ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ በል።
3 ፤ እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፥ የምታደርገውንም አስታውቅሃለሁ፤ የምነግርህንም ቅባልኝ አለው።
4 ፤ ሳሙኤልም እግዚአብሔር የተናገረውን አደረገ፥ ወደ ቤተ ልሔምም መጣ። የአገሩም ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡና። የመጣኸው ለደኅንነት ነውን? አሉት።
5 ፤ እርሱም። ለደኅንነት ነው፤ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ፤ ቅዱሳን ሁኑ፥ ከእኔም ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ አለ። እሴይንና ልጆቹንም ቀደሳቸው፥ ወደ መሥዋዕቱም ጠራቸው።
6 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በመጡ ጊዜ ወደ ኤልያብ ተመልክቶ። በእውነት እግዚአብሔር የሚቀባው በፊቱ ነው አለ።
7 ፤ እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን። ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው።
8 ፤ እሴይም አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት አሳለፈው፤ እርሱም። ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም አለ።
9 ፤ እሴይም ሣማን አሳለፈው፤ እርሱም። ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም አለ።
10 ፤ እሴይም ከልጆቹ ሰባቱን በሳሙኤል ፊት አሳለፋቸው። ሳሙኤልም እሴይን። እግዚአብሔር እነዚህን አልመረጠም አለው።
11 ፤ ሳሙኤልም እሴይን። የቀረ ሌላ ልጅ አለህን? አለው። እርሱም። ታናሹ ገና ቀርቶአል፤ እነሆም፥ በጎችን ይጠብቃል አለ። ሳሙኤልም እሴይን። እርሱ እስኪመጣ ድረስ አንረፍቅምና ልከህ አስመጣው አለው።
12 ፤ ልኮም አስመጣው፤ እርሱም ቀይ፥ ዓይኑም የተዋበ፥ መልኩም ያማረ ነበረ። እግዚአብሔርም። ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው አለ።
13 ፤ ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ አርማቴም ሄደ።
14 ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፥ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አሠቃየው።
15 ፤ የሳኦልም ባሪያዎች። እነሆ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሠቃይሃል፤
16 ፤ በገና መልካም አድርጎ የሚመታ ሰው ይሹ ዘንድ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን ባሪያዎቹን ይዘዝ፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ክፉ መንፈስ በሆነብህ ጊዜ በእጁ ሲመታ አንተ ደኅና ትሆናለህ አሉት።
17 ፤ ሳኦልም ባሪያዎቹን። መልካም አድርጎ በገና መምታት የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ አላቸው።
18 ፤ ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ። እነሆ፥ መልካም አድርጎ በገና የሚመታ የቤተ ልሔማዊውን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፤ እርሱም ጽኑዕ ኃያል ነው፥ በነገርም ብልህ፥ መልኩም ያማረ ነው፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው አለ።
19 ፤ ሳኦልም ወደ እሴይ መልክተኞች ልኮ። ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ አለ።
20 ፤ እሴይም እንጀራና የወይን ጠጅ አቁማዳ የተጫነ አህያ የፍየልም ጠቦት ወስዶ በልጁ በዳዋት እጅ ወደ ሳኦል ላከ።
21 ፤ ዳዊትም ወደ ሳኦል መጣ፥ በፊቱም ቆመ፤ እጅግም ወደደው፥ ለእርሱም ጋሻ ጃግሬው ሆነ።
22 ፤ ሳኦልም ወደ እሴይ። በዓይኔ ሞገስ አግኝቶአልና ዳዊት በፊቴ፥ እባክህ፥ ይቁም ብሎ ላከ።
23 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፤ ሳኦልንም ደስ ያሰኘው ያሳርፈውም ነበር፥ ክፉ መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር።

1 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ጭፍሮቻቸውን በይሁዳ ባለው በሰኮት አከማቹ፤ በሰኮትና በዓዜቃ መካከል በኤፌስደሚም ሰፈሩ።
2 ፤ ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ተከማቹ፥ በዔላ ሸለቆም ሰፈሩ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ሊዋጉ ተሰለፉ።
3 ፤ ፍልስጥኤማውያንም በአንድ ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፥ እስራኤልም በሌላው ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፤ በመካከላቸውም ሸለቆ ነበረ።
4 ፤ ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር የጌት ሰው ጎልያድ፥ ቁመቱም ስድስት ክንድ ከስንዝር የሆነ፥ ዋነኛ ጀግና መጣ።
5 ፤ በራሱም የናስ ቍር ደፍቶ ነበር፥ ጥሩርም ለብሶ ነበር፤ የጥሩሩም ሚዛን አምስት ሺህ ሰቅል ናስ ነበረ።
6 ፤ በእግሮቹም ላይ የናስ ገምባሌ ነበረ፥ የናስም ጭሬ በትከሻው ላይ ነበረ።
7 ፤ የጦሩም የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅልያ ነበረ፤ የጦሩም ሚዛን ስድስት መቶ ሰቅል ብረት ነበረ፤ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር።
8 ፤ እርሱም ቆሞ ወደ እስራኤል ጭፍሮች ጮኸ። ለሰልፍ ትሠሩ ዘንድ ለምን ወጣችሁ? እኔ ፍልስጥኤማዊ፥ እናንተም የሳኦል ባሪያዎች አይደላችሁምን? ለእናንተ አንድ ሰው ምረጡ፥ ወደ እኔም ይውረድ፤
9 ፤ ከእኔም ጋር ሊዋጋ ቢችል ቢገድለኝም፥ ባሪያዎች እንሆናችኋለን፤ እኔ ግን ባሸንፈው ብገድለውም፥ እናንተ ባሪያዎች ትሆኑናላችሁ፥ ለእኛም ትገዛላችሁ አለ።
10 ፤ ፍልስጥኤማዊውም። ዛሬ የእስራኤልን ጭፎሮች ተገዳደርኋቸው፤ እንዋጋ ዘንድ አንድ ሰው ስጡኝ አለ።
11 ፤ ሳኦልና እስራኤልም ሁሉ እንዲህ የሚላቸውን የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፥ ደነገጡም።
12 ፤ ዳዊትም የዚያ የኤፍራታዊው ሰው ልጅ ነበረ፤ ያም ሰው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ስሙም እሴይ ነበረ፤ ስምንትም ልጆች ነበሩት፤ በሳኦልም ዘመን በዕድሜ አርጅቶ ሸምግሎም ነበር።
13 ፤ የእሴይም ሦስቱ ታላላቆች ልጆቹ ሳኦልን ተከትለው ወደ ሰልፉ ሄደው ነበር፤ ወደ ሰልፉም የሄዱት የሦስቱ ልጆቹ ስም ይህ ነበረ፤ ታላቁ ኤልያብ ሁለተኛውም አሚናዳብ ሦስተኛውም ሣማ ነበረ።
14 ፤ ዳዊት የሁሉ ታናሽ ነበረ፤ ሦስቱም ታላላቆች ሳኦልን ተከትለው ነበር።
15 ፤ ዳዊትም የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም ይመላለስ ነበር።
16 ፤ ፍልስጥኤማዊውም ጥዋትና ማታ ይቀርብ፥ አርባ ቀንም ይታይ ነበር።
17 ፤ እሴይም ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው። ከዚህ ከተጠበሰው እሸት አንድ የኢፍ መስፈሪያ እነዚህንም አሥር እንጀራዎች ለወንድሞችህ ውሰድ፥ ወደ ሰፈሩም ወደ ወንድሞችህ ፈጥነህ አድርሳቸው፤
18 ፤ ይህንም አሥሩን አይብ ወደ ሻለቃው ውሰደው፤ የወንድሞችህንም ደኅንነት ጠይቅ፥ ወሬአቸውንም አምጣልኝ።
19 ፤ ሳኦልና እነርሱ የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ በዔላ ሸለቆ ነበሩ።
20 ፤ ዳዊትም ማልዶ ተነሣ፥ በጎቹንም ለጠባቂ ተወ፥ እሴይም ያዘዘውን ይዞ ሄደ፤ ጭፍራውም ተሰልፎ ሲወጣ ለሰልፍም ሲጮኽ በሰረገሎች ወደ ተከበበው ሰፈር መጣ።
21 ፤ እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ፊት ለፊት ተሰላልፈው ነበር።
22 ፤ ዳዊትም ዕቃውን በዕቃ ጠባቂው እጅ አኖረው፥ ወደ ሠራዊቱም ሮጠ፥ የወንድሞቹንም ደኅንነት ጠየቀ።
23 ፤ እርሱም ሲነጋገራቸው፥ እነሆ፥ ጎልያድ የተባለው ያ ዋነኛ ጀግና ፍልስጥኤማዊ የጌት ሰው ከፍልስጥኤማውያን ጭፍራ መካከል ወጣ፥ የተናገረውንም ቃል ተናገረ፤ ዳዊትም ሰማ።
24 ፤ የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ሰውዮውን ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው ከእርሱ ሸሹ።
25 ፤ የእስራኤልም ሰዎች። ይህን የወጣውን ሰው አያችሁትን? በእውነት እስራኤልን ሊገዳደር ወጣ፤ የሚገድለውንም ሰው ንጉሡ እጅግ ባለጠጋ ያደርገዋል፥ ልጁንም ይድርለታል፤ ያባቱንም ቤተ ሰብ በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያወጣቸዋል አሉ።
26 ፤ ዳዊትም በአጠገቡ ለቆሙት ሰዎች። ይህን ፍልስጥኤማዊ ለሚገድል፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን ለሚያርቅ ሰው ምን ይደረግለታል? የሕያውን አምላክ ጭፍሮች የሚገዳደር ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው።
27 ፤ ሕዝቡም። ለሚገድለው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ብለው እንደ ቀድሞው መለሱለት።
28 ፤ ታላቅ ወንድሙም ኤልያብ ከሰዎች ጋር ሲነጋገር ሰማ፤ የኤልያብም ቍጣ በዳዊት ላይ ነድዶ። ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂቶች በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? እኔ ኵራትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁና ሰልፉን ለማየት መጥተሃል አለው።
29 ፤ ዳዊትም። እኔ ምን አደርግሁ? ይህ ታላቅ ነገር አይደለምን? አለ።
30 ፤ ዳዊትም ከእርሱ ወደ ሌላ ሰው ዘወር አለ፥ እንደዚህም ያለ ነገር ተናገረ፤ ሕዝቡም እንደ ቀድሞው ያለ ነገር መለሱለት።
31 ፤ ዳዊትም የተናገረው ቃል ተሰማ፥ ለሳኦልም ነገሩት፤ ወደ እርሱም አስጠራው።
32 ፤ ዳዊትም ሳኦልን። ስለ እርሱ የማንም ልብ አይውደቅ፤ እኔ ባሪያህ ሄጄ ያንን ፍልስጥኤማዊ እወጋዋለሁ አለው።
33 ፤ ሳኦልም ዳዊትን። አንተ ገና ብላቴና ነህና፥ እርሱም ከብላቴንነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነውና ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም አለው።
34 ፤ ዳዊትም ሳኦልን አለው። እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፥ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር።
35 ፤ በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፥ ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሣብኝም ጊዜ ጕሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር።
36 ፤ እኔ ባሪያህ አንበሳና ድብ መታሁ፤ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ የሕያውን አምላክ ጭፍሮች ተገዳድሮአልና ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል።
37 ፤ ዳዊትም። ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል አለ። ሳኦልም ዳዊትን። ሂድ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል አለው።
38 ፤ ሳኦልም ዳዊትን የገዛ ራሱን ልብስ አለበሰው፥ በራሱም ላይ የናስ ቍር ደፋለት፥ ጥሩርም አለበሰው።
39 ፤ ዳዊትም ሰይፉን በልብሱ ላይ ታጠቀ፥ ገናም አልፈተነውምና መሄድ ሞከረ። ዳዊትም ሳኦልን። አልፈተንሁትምና እንዲህ ብዬ መሄድ አልችልም አለው።
40 ፤ ዳዊትም አወለቀ። በትሩንም በእጁ ወሰደ፥ ከወንዝም አምስት ድብልብል ድንጋዮችን መረጠ፥ በእረኛ ኮረጆውም በኪሱ ከተታቸው፤ ወንጭፍም በእጁ ነበረ፤ ወደ ፍልስጥኤማዊውም ቀረበ።
41 ፤ ፍልስጥኤማዊውም መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ፤ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር።
42 ፤ ጎልያድም ዳዊትን ትኵር ብሎ አየው፤ ቀይ ብላቴና መልኩም ያማረ ነበረና ናቀው።
43 ፤ ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን። በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን? አለው። ፍልስጥኤማዊውም በአምላኮቹ ስም ዳዊትን ረገመው።
44 ፤ ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን። ወደ እኔ ና፥ ሥጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ አለው።
45 ፤ ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን አለው። አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።
46 ፤ እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እመታህማለሁ፥ ራስህንም ከአንተ አነሣዋለሁ፤ የፍልስጥኤማውያንንም ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለሁ። ይኸውም ምድር ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ፤
47 ፤ ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደል ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፤ እናንተንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።
48 ፤ ፍልስጥኤማዊውም ተነሥቶ ዳዊትን ሊገናኘው በቀረበ ጊዜ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ሊገናኘው ወደ ሰልፉ ሮጠ።
49 ፤ ዳዊትም እጁን ወደ ኮረጆው አግብቶ አንድ ድንጋይ ወሰደ፥ ወነጨፈውም፥ ፍልስጥኤማዊውንም ግምባሩን መታ፤ ድንጋዩም በግምባሩ ተቀረቀረ፥ እርሱም በምድር ላይ በፊቱ ተደፋ።
50 ፤ ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው፥ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለ፤ በዳዊትም እጅ ሰይፍ አልነበረም።
51 ፤ ዳዊትም ሮጦ በፍልስጥኤማዊው ላይ ቆመ፤ ሰይፉንም ይዞ ከሰገባው መዘዘው፥ ገደለውም፥ ራሱንም ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ዋናቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ሸሹ።
52 ፤ የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ተነሥተው እልል አሉ፥ ፍልስጥኤማውያንንም እስከ ጌትና እስከ አስቀሎና በርድረስ አሳደዱአቸው። ፍልስጥኤማውያንም ከሸዓራይም ጀምሮ እስከ ጌትና እስከ አቃሮን ድረስ በመንገድ ላይ የተመቱት ወደቁ።
53 ፤ የእስራኤልም ልጆች ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመልሰው ሰፈራቸውን በዘበዙ።
54 ፤ ዳዊትም የፍልስጥኤማዊውን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ጋሻ ጦሩን ግን በድንኳኑ ውስጥ አኖረው።
55 ፤ ሳኦልም ዳዊትን ወደ ፍልስጥኤማዊው ሲወጣ ባየው ጊዜ ለሠራዊቱ አለቃ ለአበኔር። አበኔር ሆይ፥ ይህ ብላቴና የማን ልጅ ነው? አለው። አበኔርም። ንጉሥ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! አላውቅም አለ።
56 ፤ ንጉሡም። ይህ ብላቴና የማን ልጅ እንደ ሆነ አንተ ጠይቅ አለ።
57 ፤ ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ አበኔር ወሰደው፥ ወደ ሳኦልም ፊት አመጣው፤ የፍልስጥኤማዊውንም ራስ በእጁ ይዞ ነበር።
58 ፤ ሳኦልም። አንተ ብላቴና፥ የማን ልጅ ነህ? አለው። ዳዊትም። እኔ የቤተ ልሔሙ የባሪያህ የእሴይ ልጅ ነኝ ብሎ መለሰ።

 

1 ፤ ዳዊትም ለሳኦል መናገሩን በፈጸመ ጊዜ የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፥ ዮናታንም እንደ ነፍሱ ወደደው።
2 ፤ በዚያም ቀን ሳኦል ወሰደው፥ ወደ አባቱም ቤት ይመልሰው ዘንድ አልተወውም።
3 ፤ ዮናታንም እንደ ነፍሱ ስለ ወደደው ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ።
4 ፤ ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን ሰይፉንም ሸለመው። ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን ሰይፉንም ቀስቱንም መታጠቂያውንም ለዳዊት ሸለመው።
5 ፤ ዳዊትም ሳኦል ወደ ሰደደው ሁሉ ይሄድ ነበር፥ አስተውሎም ያደርግ ነበር፤ ሳኦልም በጦረኞች ላይ ሾመው፤ ይህም በሕዝብ ሁሉ ዓይን እና በሳኦል ባሪያዎች ዓይን መልካም ነበረ።
6 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ፥ እየዘመሩና እየዘፈኑ እልልም እያሉ ከበሮና አታሞ ይዘው ንጉሡን ሳኦልን ሊቀበሉ ሴቶች ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ወጡ።
7 ፤ ሴቶችም። ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር።
8 ፤ ሳኦልም እጅግ ተቈጣ፥ ይህም ነገር አስከፋው፤ እርሱም። ለዳዊት እልፍ ሰጡት፥ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ ሰጡኝ፤ ከመንግሥት በቀር ምን ቀረበት? አለ።
9 ፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ተመቅኝቶ ተመለከተው።
10 ፤ በነጋውም ሳኦልን ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው፥ በቤቱም ውስጥ ትንቢት ተናገረ።ዳዊትም በየቀኑ ያደርግ እንደ ነበረ በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር።
11 ፤ ሳኦልም። ዳዊትን ከግንቡ ጋር አጣብቄ እመታዋለሁ ብሎ ጦሩን ወረወረ። ዳዊትም ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ።
12 ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ ከሳኦልም ስለ ተለየ ሳኦል ዳዊትን ፈራው።
13 ፤ ስለዚህም ሳኦል ከእርሱ አራቀው፥ የሺህ አለቃም አደረገው፤ በሕዝቡም ፊት ይወጣና ይገባ ነበር።
14 ፤ ዳዊትም በአካሄዱ ሁሉ አስተውሎ ያደርግ ነበር፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ።
15 ፤ ሳኦልም እጅግ ብልህ እንደ ሆነ አይቶ እጅግ ፈራው።
16 ፤ ነገር ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለ ነበረ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱ።
17 ፤ ሳኦልም ዳዊትን። ታላቂቱ ልጄ ሜሮብ እነኋት፤ እርስዋን እድርልሃለሁ፤ ብቻ ቀልጣፋ ልጅ ሁንልኝ፥ ስለ እግዚአብሔርም ጦርነት ተጋደል አለው። ሳኦልም። የፍልስጥኤማውያን እጅ በእርሱ ላይ ትሁን እንጂ የእኔ እጅ በእርሱ ላይ አትሁን ይል ነበር።
18 ፤ ዳዊትም ሳኦልን። ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ሰውነቴስ ምንድር ናት? የአባቴስ ወገን በእስራኤል ዘንድ ምንድር ነው? አለው።
19 ፤ ነገር ግን የሳኦል ልጅ ሜሮብ ዳዊትን የምታገባበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤስድሪኤል ተዳረች።
20 ፤ የሳኦልም ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደች፤ ይህም ወሬ ለሳኦል ደረሰለት፥ ነገሩም ደስ አሰኘው።
21 ፤ ሳኦልም። ወጥመድ ትሆነው ዘንድ፥ የፍልስጥኤማውያንም እጅ በእርሱ ላይ ትሆን ዘንድ እርስዋን እድርለታለሁ አለ፤ ሳኦልም ዳዊትን። ዛሬ ሁለተኛ አማች ትሆነኛለህ አለው።
22 ፤ ሳኦልም ባሪያዎቹን። እነሆ፥ ንጉሥ እጅግ ወድዶሃል፥ ባሪያዎቹም ሁሉ ወድደውሃል፥ አሁንም ለንጉሥ አማች ሁን ብላችሁ በስውር ለዳዊት ንገሩት ብሎ አዘዛቸው።
23 ፤ የሳኦልም ባሪያዎች ይህን ቃል በዳዊት ጆሮ ተናገሩ፤ ዳዊትም። እኔ ድሀ የተጠቃሁም ሰው ስሆን ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ ለእናንተ ትንሽ ነገር ይመስላችኋልን? አለ።
24 ፤ የሳኦልም ባሪያዎች። ዳዊት እንዲህ ብሎ ተናገረ ብለው ነገሩት።
25 ፤ ሳኦልም ዳዊትን በፍልስጥኤማውያን እጅ ይጥለው ዘንድ አስቦ። የንጉሥን ጠላቶች ይበቀል ዘንድ ከመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት በቀር ንጉሥ ማጫ አይሻም ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት አላቸው።
26 ፤ የሳኦልም ባሪያዎች ይህን ቃል ለዳዊት ነገሩት፥ ለንጉሥም አማች ይሆን ዘንድ ዳዊትን ደስ አሰኘው።
27 ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ተነሥተው ሄዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም መቶ ሰዎች ገደሉ፤ ዳዊትም ለንጉሥ አማች ይሆን ዘንድ ሰለባቸውን አምጥቶ በቍጥራቸው ልክ ለንጉሡ ሰጠ። ሳኦልም ልጁን ሜልኮልን ዳረለት።
28 ፤ ሳኦልም እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደ ሆነ አየ፤ እስራኤልም ሁሉ ወደዱት።
29 ፤ ሳኦልም ዳዊትን አጥብቆ ፈራው፤ ሳኦልም ዕድሜውን ሁሉ ለዳዊት ጠላት ሆነ።
30 ፤ የፍልስጥኤማውያንም አለቆች ይወጡ ነበር፤ በወጡም ጊዜ ሁሉ ከሳኦል ባሪያዎች ሁሉ ይልቅ ዳዊት አስተውሎ ያደርግ ነበርና ስሙ እጅግ ተጠርቶ ነበር።

1 ፤ ሳኦልም ለልጁ ለዮናታንና ለባሪያዎቹ ሁሉ ዳዊትን ይገድሉ ዘንድ ነገራቸው። የሳኦል ልጅ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድድ ነበር።
2 ፤ ዮናታንም። አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ፈልጎአል፤ አሁን እንግዲህ ለነገው ተጠንቅቀህ ተሸሸግ፥ በስውርም ተቀመጥ፤
3 ፤ እኔም እወጣለሁ አንተም ባለህበት እርሻ በአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፥ ስለ አንተም ከአባቴ ጋር እነጋገራለሁ፤ የሆነውንም አይቼ እነግርሃለሁ ብሎ ለዳዊት ነገረው።
4 ፤ ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል። እርሱ አልበደለህምና። ሥራውም ለአንተ እጅግ መልካም ሆኖአልና ንጉሡ ባሪያውን ዳዊትን አይበድለው፤
5 ፤ ነፍሱንም በእጁ ጥሎ ፍልስጥኤማዊውን ገደለ፥ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ሁሉ ታላቅ መድኃኒት አደረገ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ፤ በከንቱ ዳዊትን በመግደልህ ስለምን በንጹሕ ደም ላይ ትበድላለህ? ብሎ ስለ ዳዊት መልካም ተናገረ።
6 ፤ ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፤ ሳኦልም። ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም ብሎ ማለ።
7 ፤ ዮናታንም ዳዊትን ጠርቶ ይህን ነገር ሁሉ ነገረው፤ ዮናታንም ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፥ እንደ ቀድሞውም በፊቱ ነበረ።
8 ፤ ደግሞም ጦርነት ሆነ፤ ዳዊትም ወጥቶ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፥ ታላቅ ግዳይም ገደላቸው፥ ከፊቱም ሸሹ።
9 ፤ ሳኦልም ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው። ዳዊትም በእጁ በገና ይመታ ነበር።
10 ፤ ሳኦልም ዳዊትን ከግንብ ጋር ያጣብቀው ዘንድ ጦሩን ወረወረ፤ ዳዊትም ከሳኦል ፊት ዘወር አለ፥ ጦሩም በግንቡ ውስጥ ተተከለ፤ በዚያም ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ።
11 ፤ ሳኦልም ዳዊትን ጠብቀው በነጋው እንዲገድሉት መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ቤት ላከ፤ ሚስቱም ሜልኮል። በዚህች ሌሊት ነፍስህን ካላዳንህ ነገ ትገደላለህ ብላ ነገረችው።
12 ፤ ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አወረደችው፤ ሄደም፥ ሸሽቶም አመለጠ።
13 ፤ ሜልኮልም ተራፊምን ወስዳ በአልጋ ላይ አኖረችው፥ በራስጌውም ጕንጕን የፍየል ጠጉር አደረገች፥ በልብስም ከደነችው።
14 ፤ ሳኦልም ዳዊትን እንዲያመጡት መልእክተኞችን ላከ፥ እርስዋም። ታምሞአል አለቻቸው።
15 ፤ ሳኦልም። እገድለው ዘንድ ዳዊትን ከነ አልጋው አምጡልኝ ብሎ መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ሰደደ።
16 ፤ መልእክተኞቹም በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ተራፊሙን በአልጋው ላይ አገኙ፥ በራስጌውም ጕንጕን የፍየል ጠጉር ነበረ።
17 ፤ ሳኦልም ሜልኮልን። ስለ ምን እንዲህ አድርገሽ አታለልሽኝ? ጠላቴን አስኰበለልሽው አላት። ሜልኮልም ለሳኦል። እርሱ። አውጥተሽ ስደጂኝ፥ አለዚያም እገድልሻለሁ አለኝ ብላ መለሰችለት።
18 ፤ ዳዊትም ሸሽቶ አመለጠ፥ ወደ አርማቴምም ወደ ሳሙኤል መጣ፥ ሳኦልም ያደረገበትን ሁሉ ነገረው፤ እርሱና ሳሙኤልም ሄዱ በነዋትዘራማም ተቀመጡ።
19 ፤ ሳኦልም። ዳዊት፥ እነሆ፥ በአርማቴም አገር በነዋትዘራማ ተቀምጦአል የሚል ወሬ ሰማ።
20 ፤ ሳኦልም ዳዊትን ያመጡት ዘንድ መልእክተኞችን ሰደደ፤ የነቢያት ጉባኤ ትንቢት ሲናገሩ፥ ሳሙኤልም አለቃቸው ሆኖ ሲቆም ባዩ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል መልእክተኞች ላይ ወረደ፥ እነርሱም ትንቢት ይናገሩ ጀምር።
21 ፤ ሳኦልም ያንን በሰማ ጊዜ ሌሎች መልእክተኞችን ሰደደ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። ሳኦልም እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ መልእክተኞችን ሰደደ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ።
22 ፤ የሳኦልም ቍጣ ነደደ፥ እርሱም ደግሞ ወደ አርማቴም መጣ፥ በሤኩም ወዳለው ወደ ታላቁ የውኃ ጕድጓድ ደረሰ። ሳሙኤልና ዳዊት የት ናቸው? ብሎ ጠየቀ፤ አንድ ሰውም። እነሆ፥ በአርማቴም አገር በነዋትዘራማ ናቸው አለው።
23 ፤ ወደ አርማቴምም አገር ወደ ነዋትዘራማ ሄደ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ደግሞ ወረደ፥ እርሱም ሄደ፥ ወደ አርማቴምም አገር ወደ ነዋትዘራማ እስኪመጣ ድረስ ትንቢት ይናገር ነበር።<br id=”20″>
24 ፤ ልብሱንም አወለቀ፥ በሳሙኤልም ፊት ትንቢት ተናገረ፥ ራቁቱንም ወድቆ በዚያ ቀን ሁሉ በዚያም ሌሊት ሁሉ ተጋደመ። ስለዚህ። ሳኦል ደግሞ ከነቢያት መካከል ነውን? ይባባሉ ነበር።

1 ፤ ዳዊትም ከአርማቴም አገር ከነዋትዘራማ ሸሸ፥ ወደ ዮናታንም መጥቶ። ምን አደረግሁ? እኔንስ ለመግደል የሚፈልግ በአባትህ ፊት ጠማምነቴና ኃጢአቴ ምንድር ነው? ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ዮናታንም። ይህንስ ያርቀው፥ አትሞትም፤ እነሆ፥ አባቴ አስቀድሞ ለእኔ ሳይገልጥ ትልቅም ትንሽም ነገር ቢሆን አያደርግም፤ አባቴስ ይህን ነገር ለምን ይሰውረኛል? እንዲህ አይደለም አለው።
3 ፤ ዳዊትም። እኔ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘሁ አባትህ በእውነት ያውቃል፤ እርሱም። ዮናታን እንዳይከፋው አይወቅ ይላል፤ ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ያህል ቀርቶአል ብሎ ማለ።
4 ፤ ዮናታንም ዳዊትን። ነፍስህ የወደደችውን ሁሉ አደርግልሃለሁ አለው።
5 ፤ ዳዊትም ዮናታንን አለው። እነሆ፥ ነገ መባቻ ነው፤ በንጉሥም አጠገብ ለምሳ አልቀመጥም፤ እስከ ሦስተኛው ቀን ማታ ድረስ በውጭ በሜዳ እንድሸሸግ አሰናብተኝ።
6 ፤ አባትህም ቢፈልገኝ። ለዘመዶቹ ሁሉ በዚያ በቤተ ልሔም የዓመት መሥዋዕት አላቸውና ዳዊት ወደ ከተማው ፈጥኖ ይሄድ ዘንድ አጽንቶ ለምኖኛል በለው።
7 ፤ እርሱም። መልካም ነው ቢል ለእኔ ለባሪያህ ደኅንነት ይሆናል፤ ቢቈጣ ግን ክፋት ከእርሱ ዘንድ በእኔ ላይ እንደ ተቈረጠች እወቅ።
8 ፤ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ከባሪያህ ጋር አድርገሃልና ለባሪያህ ቸርነት አድርግ፤ በደል ግን ቢገኝብኝ አንተ ግደለኝ፤ ለምን ወደ አባትህ ታደርሰኛለህ?
9 ፤ ዮናታንም። ይህ ከአንተ ይራቅ፤ ከአባቴ ዘንድ ክፋት በላይህ እንደ ተቈጠረች ያወቅሁ እንደ ሆነ አልነግርህምን? አለ።
10 ፤ ዳዊትም ዮናታንን። አባትህ ስለ እኔ ክፉ ነገር የነገረህ እንደ ሆን ማን ይነግረኛል? አለው።
11 ፤ ዮናታንም ዳዊትን። ና ወደ ሜዳ እንውጣ አለው። ሁለቱም ወደ ሜዳ ወጡ።
12 ፤ ዮናታንም ዳዊትን አለው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁን፤ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በዚህ ጊዜ አባቴን መርምሬ፥ እነሆ፥ በዳዊት ላይ መልካም ቢያስብ ልኬ እገልጥልሃለሁ፤
13 ፤ አባቴም በአንተ ላይ ክፋት ማድረግ ቢወድድ እኔም ባላስታውቅህ በደህና ትሄድ ዘንድ ባላሰናብትህ፥ እግዚአብሔር በዮናታን ይህን ያድርግ ይህንም ይጨምር፤ እግዚአብሔርም ከአባቴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን።
14 ፤ እኔም እንዳልሞት በሕይወቴ ዘመን የእግዚአብሔርን ቸርነት አድርግልኝ፤
15 ፤ ደግሞም እግዚአብሔር የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ እያንዳንዱ ከምድር ባጠፋቸው ጊዜ ለዘላለም ቸርነትህን ከቤቴ አታርቀው።
16 ፤ ዮናታንም። እግዚአብሔር ከዳዊት ጠላቶች እጅ ይፈልገው ብሎ ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ።
17 ፤ ዮናታንም ዳዊትን እንደ ነፍሱ ይወድድ ነበርና እንደ ገና ማለለት።
18 ፤ ዮናታንም አለው። ነገ መባቻ ነው፥ መቀመጫህም ባዶ ሆኖ ይገኛልና ትታሰባለህ።
19 ፤ ሦስት ቀንም ያህል ቆይ፤ ከዚህም በኋላ ፈጥነህ ውረድ፥ ነገሩም በተደረገበት ቀን ወደ ተሸሸግህበት ስፍራ ሂድ፥ በኤዜል ድንጋይም አጠገብ ቆይ።
20 ፤ እኔም በዓላማ ላይ እወረውራለሁ ብዬ ሦስት ፍላጻዎችን ወደ አጠገቡ እወረውራለሁ።
21 ፤ እነሆም። ሂድ ፍላጻዎችን ፈልግ ብዬ ብላቴናውን እልከዋለሁ፤ ብላቴናውንም። እነሆ፥ ፍላጻው ከአንተ ወደዚህ ነው፤ ይዘኸው ወደ እኔ ና ያልሁት እንደ ሆነ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! ለአንተ ደኅንነት ነውና ምንም የለብህም።
22 ፤ ብላቴናውን ግን። እነሆ፥ ፍላጻው ከአንተ ወዲያ ነው ያልሁት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔር አሰናብቶሃልና መንገድህን ሂድ።
23 ፤ አንተና እኔም ስለ ተነጋገርነው፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለዘላለም በመካከላችን ምስክር ነው።
24 ፤ ዳዊትም በሜዳው ተሸሸገ፤ መባቻም በሆነ ጊዜ ንጉሡ ግብር ለመብላት ተቀመጠ።
25 ፤ ንጉሡም እንደ ቀድሞው በግንቡ አጠገብ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮናታንም ቆሞ ነበር፥ አበኔርም በሳኦል አጠገብ ተቀመጠ፤ የዳዊትም ስፍራ ባዶውን ነበረ።
26 ፤ ሳኦልም። አንድ ነገር ሆኖአል፥ ንጹሕም አይደለም፤ በእውነት ንጹሕ አይደለም ብሎ አስቦአልና በዚያን ቀን ምንም አልተናገረም።
27 ፤ ከመባቻም በኋላ በማግሥቱ በሁለተኛው ቀን የዳዊት ስፍራ ባዶውን ነበረ፤ ሳኦልም ልጁን ዮናታንን። የእሴይ ልጅ ትናንትና ወይም ዛሬ ግብር ሊበላ ያልመጣ ስለ ምን ነው? አለው።
28 ፤ ዮናታንም ለሳኦል። ዳዊት ወደ ቤተ ልሔም ይሄድ ዘንድ አጽንቶ ለመነኝ፤
29 ፤ እርሱም። ዘመዶቼ በከተማ ውስጥ መሥዋዕት አላቸውና፥ ወንድሜም ጠርቶኛልና እባክህ፥ አሰናብተኝ፤ አሁንም በዓይኖችህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ልሂድና ወንድሞቼን ልይ አለ፤ ስለዚህ ወደ ንጉሥ ሰደቃ አልመጣም ብሎ መለሰለት።
30 ፤ የሳኦልም ቍጣ በዮናታን ላይ ነደደና። አንተ የጠማማ ሴት ልጅ፥ የእሴይን ልጅ ለአንተ ማፈርያ ለእናትህም ኀፍረተ ሥጋ ማፈርያ እንደ መረጥህ እኔ አላውቅምን?
31 ፤ የእሴይም ልጅ በምድር ላይ በሕይወት በሚኖርበት ዘመን ሁሉ አንተና መንግሥትህ አትጸኑም፤ አሁንም የሞት ልጅ ነውና ልከህ አስመጣልኝ አለው።
32 ፤ ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል። ስለ ምን ይሞታል? ያደረገውስ ምንድር ነው? ብሎ መለሰለት።
33 ፤ ሳኦልም ሊወጋው ጦሩን ወረወረበት፤ ዮናታንም አባቱ ዳዊትን ፈጽሞ ሊገድለው እንደ ፈቀደ አወቀ።
34 ፤ አባቱ ዳዊትን ስላሳፈረው ዮናታን ስለ ዳዊት አዝኖአልና እጅግ ተቈጥቶ ከሰደቃው ተነሣ፥ በመባቻውም በሁለተኛ ቀን ግብር አልበላም።
35 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ዮናታን ከዳዊት ጋር ወደ ተቃጠረበት ቦታ ወደ ሜዳ ወጣ፥ ከእርሱም ጋር ታናሽ ብላቴና ነበረ።
36 ፤ ብላቴናውንም። ሮጠህ የምወረውራቸውን ፍላጻዎች ፈልግልኝ አለው። ብላቴናውም በሮጠ ጊዜ ፍላጻውን ወደ ማዶ ወረወረው።
37 ፤ ብላቴናውም ዮናታን ፍላጻውን ወደ ወረወረበት ስፍራ በመጣ ጊዜ ዮናታን። ፍላጻው ከአንተ ወዲያ ነው ብሎ ወደ ብላቴናው ጮኸ።
38 ፤ ዮናታንም ደግሞ። ቶሎ ፍጠን፥ አትቆይ ብሎ ወደ ብላቴናው ጮኸ፤ የዮናታንም ብላቴና ፍላጻዎቹን ሰብስቦ ወደ ጌታው መጣ።
39 ፤ ዮናታንና ዳዊት ብቻ ነገሩን ያውቁ ነበር እንጂ ብላቴናው ምንም አያውቅም ነበር።
40 ፤ ዮናታንም መሣርያውን ለብላቴናው ሰጥቶ። ወደ ከተማ ውሰድ አለው።
41 ፤ ብላቴናውም በሄደ ጊዜ ዳዊት ከስፍራው በደቡብ አጠገብ ተነሣ፥ በምድርም ላይ በግምባሩ ተደፋ፥ ሦስት ጊዜም ለሰላምታ ሰገደ፤ እየተላቀሱም እርስ በእርሳቸው ተሳሳሙ፥ ይልቁንም ዳዊት እጅግ አለቀሰ።
42 ፤ ዮናታንም ዳዊትን። በደኅና ሂድ፤ እነሆ፥ እኛ ሁለታችን በእኔና በአንተ፥ በዘሬና በዘርህ መካከል ለዘላለም እግዚአብሔር ይሁን ብለን በእግዚአብሔር ስም ተማምለናል አለው። ዳዊትም ተነሥቶ ሄደ፤ ዮናታንም ወደ ከተማ ገባ።

1 ፤ ዳዊትም ወደ ካህኑ ወደ አቢሜሌክ ወደ ኖብ መጣ፤ አቢሜሌክም እየተንቀጠቀጠ ዳዊትን ሊገናኘው መጣና። ስለ ምን አንተ ብቻህን ነህ? ከአንተስ ጋር ስለ ምን ማንም የለም? አለው።
2 ፤ ዳዊትም ካህኑን አቢሜሌክን። የተላክህበትን ነገርና የሰጠሁህን ትእዛዝ ማንም አይወቅ ብሎ ንጉሡ አንድ ነገር አዝዞኛል፤ ስለዚህም ብላቴኖቹን እንዲህ ባለ ስፍራ ተውኋቸው።
3 ፤ አሁንስ በእጅህ ምን አለ? አምስት እንጀራ ወይም የተገኘውን በእጄ ስጠኝ አለው።
4 ፤ ካህኑም ለዳዊት መልሶ። ሁሉ የሚበላው እንጀራ የለኝም፥ ነገር ግን የተቀደስ እንጀራ አለ፤ ብላቴኖቹ ከሴቶቹ ንጹሐን እንደ ሆኑ መብላት ይቻላል አለው።
5 ፤ ዳዊትም ለካህኑ መልሶ። በእውነት ከወጣን ጀምረን እኛ ሰውነታችንን ከሴቶች ሦስት ቀን ጠብቀናል፤ የብላቴኖችም ዕቃ የተቀደሰች ናት፤ ስለዚህ ዛሬ ዕቃቸው የተቀደሰች በመሆንዋ እንጀራው እንደሚበላ እንጀራ ይሆናል አለው።
6 ፤ ካህኑም በእርሱ ፋንታ ትኩስ እንጀራ ይደረግ ዘንድ ከእግዚአብሔር ፊት ከተነሣው ከገጹ ኅብስት በቀር ሌላ እንጀራ አልነበረምና የተቀደሰውን እንጀራ ሰጠው።
7 ፤ በዚያም ቀን ከሳኦል ባሪያዎች አንድ ሰው በዚያ በእግዚአብሔር ፊት ተገኝቶ ነበር፤ ስሙም ኤዶማዊው ዶይቅ ነበረ፥ ለሳኦልም የእረኞቹ አለቃ ነበረ።
8 ፤ ዳዊትም አቢሜሌክን። የንጉሥ ጉዳይ ስላስቸኰለኝ ሰይፌንና መሣሪያዬን አላመጣሁምና በአንተ ዘንድ ጦር ወይም ሰይፍ አለ ወይ? አለው።
9 ፤ ካህኑም። በኤላ ሸለቆ የገደልኸው የፍልስጥኤማዊው የጎልያድ ሰይፍ፥ እነሆ፥ በመጎናጸፊያ ተጠቅልሎ ከዚህ ከኤፉዱ በኋላ አለ፤ ትወድደውም እንደ ሆነ ውሰደው፤ ሌላ ከዚህ የለም አለ። ዳዊትም። እንደ እርሱ ያለ የለምና እርሱን ስጠኝ አለው።
10 ፤ ዳዊትም ተነሣ በዚያም ቀን ሳኦልን ፈርቶ ሸሸ፥ ወደ ጌትም ንጉሥ ወደ አንኩስ ሄደ።
11 ፤ የአንኩስ ባሪያዎችም። ይህ ዳዊት የአገሩ ንጉሥ አይደለምን? ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ ብለው ሴቶች በዘፈን የዘመሩለት እርሱ አይደለምን? አሉት።
12 ፤ ዳዊትም ይህን ቃል በልቡ አኖረ፥ የጌትንም ንጉሥ አንኩስን እጅግ ፈራ።
13 ፤ በፊታቸውም አእምሮውን ለወጠ፥ በያዙትም ጊዜ እንደ እብድ ሆነ፥ በበሩም መድረክ ላይ ተንፈራፈረ፥ ልጋጉም በጢሙ ላይ ይወርድ ነበር።
14 ፤ አንኩስም ባሪያዎቹን። እነሆ፥ ይህ ሰው እብድ እንደ ሆነ አይታችኋል፤ ለምን ወደ እኔ አመጣችሁት? በፊቴ ያብድ ዘንድ ይህን ያመጣችሁት እብድ ጠፍቶብኝ ነውን? እንዲህ ያለውስ ወደ ቤቴ ይገባልን? አላቸው።

 

1 ፤ ዳዊትም ከዚያ ተነሣ ወደ ዓዶላም ዋሻ ኮበለለ፤ ወንድሞቹና የአባቱም ቤተ ሰብ ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ እርሱ ወደዚያ ወረዱ።
2 ፤ የተጨነቀውም ሁሉ፥ ብድርም ያለበት ሁሉ፥ የተከፋም ሁሉ ወደ እርሱ ተከማቸ፤ እርሱም በላያቸው አለቃ ሆነ፤ ከእርሱም ጋር አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ።
3 ፤ ዳዊትም ከዚያ በሞዓብ ምድር ወዳለችው ወደ ምጽጳ ሄደ፤ የሞዓብንም ንጉሥ። እግዚአብሔር የሚያደርግልኝን እስካውቅ ድረስ አባቴና እናቴ ከአንተ ጋር ይቀመጡ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው።
4 ፤ በሞዓብም ንጉሥ ፊት አመጣቸው፤ ዳዊትም በአምባ ውስጥ በነበረበት ወራት ሁሉ በእርሱ ዘንድ ተቀመጡ።
5 ፤ ነቢዩ ጋድም ዳዊትን። ተነሥተህ ወደ ይሁዳ ምድር ሂድ እንጂ በአምባው ውስጥ አትቀመጥ አለው፤ ዳዊትም ተነሥቶ ወደ ሔሬት ዱር መጣ።
6 ፤ ሳኦልም ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንደ ተገለጡ ሰማ። ሳኦልም በጊብዓ በአጣጥ ዛፍ በታች በኮረብታው ላይ ተቀምጦ በእጁም ጦር ይዞ ነበር፤ ባሪያዎቹም ሁሉ በአጠገቡ ቆመው ነበር።
7 ፤ ሳኦልም በአጠገቡ የቆሙትን ባሪያዎቹን። ብንያማውያን ሆይ፥ እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ የእሴይ ልጅ እርሻና የወይን ቦታ ለሁላችሁ ይሰጣችኋልን? ሁላችሁንስ ሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋችኋልን?
8 ፤ ሁላችሁ በላዬ ዶልታችሁ ተነሣችሁብኝ፤ ልጄ ከእሴይ ልጅ ጋር ሲማማል ምንም አይገልጥልኝም፤ ከእናንተም አንድ ለእኔ የሚያዝን የለም፥ ዛሬም እንደ ሆነው ሁሉ ልጄ ባሪያዬን እንዲዶልት ሲያስነሣብኝ ማንም አላስታወቀኝም አላቸው።
9 ፤ በሳኦልም ባሪያዎች አጠገብ የቆመው ኤዶማዊው ዶይቅ መልሶ። የእሴይ ልጅ ወደ ኖብ ወደ አኪጦብ ልጅ ወደ አቢሜሌክ ሲመጣ አይቼዋለሁ።
10 ፤ እግዚአብሔርንም ጠየቀለት፥ ስንቅንም ሰጠው፥ የፍልስጥኤማዊውንም የጎልያድን ሰይፍ ሰጠው አለ።
11 ፤ ንጉሡም የአኪጦብን ልጅ ካህኑን አቢሜሌክን በኖብም ያሉትን ካህናት የአባቱን ቤት ሁሉ ልኮ አስጠራቸው፤ ሁላቸውም ወደ ንጉሡ መጡ።
12 ፤ ሳኦልም። የአኪጦብ ልጅ ሆይ፥ እንግዲህ ስማ አለ፤ እርሱም። እነሆኝ፥ ጌታዬ ሆይ ብሎ መለሰ።
13 ፤ ሳኦልም። አንተና የእሴይ ልጅ ለምን ዶለታችሁብኝ? እንጀራና ሰይፍ ሰጠኸው፥ ዛሬም እንደ ተደረገው ጠላት ሆኖ ይነሣብኝ ዘንድ እግዚአብሔርን ስለ እርሱ ጠየቅህለት አለው።
14 ፤ አቢሜሌክም መልሶ ንጉሡን። ከባሪያዎችህ ሁሉ የታመነ፥ ለንጉሥም አማች የሆነ፥ በትእዛዝህ የሚሄድ፥ በቤትህም የከበረ እንደ ዳዊት ያለ ማን ነው?
15 ፤ በውኑ ስለ እርሱ እግዚአብሔርን እጠይቅ ዘንድ ዛሬ ጀመርሁን? ይህ ከእኔ ይራቅ፤ እኔ ባሪያህ ይህን ሁሉ እጅግ ወይም ጥቂት ቢሆን አላውቅምና ንጉሡ እንደዚህ ያለውን ነገር በእኔ በባሪያውና በአባቴ ቤት ሁሉ ላይ አያኑር አለ።
16 ፤ ንጉሡም። አቢሜሌክ ሆይ። አንተና የአባትህ ቤት ሁሉ ፈጽማችሁ ትሞታላችሁ አለ።
17 ፤ ንጉሡም በዙሪያው የቆሙትን እግረኞች። የእግዚአብሔር ካህናት እጅ ከዳዊት ጋር ነውና፥ ኵብለላውንም ሲያውቁ በጆሮዬ አልገለጡምና ዞራችሁ ግደሉአቸው አላቸው። የንጉሡ ባሪያዎች ግን እጃቸውን በእግዚአብሔር ካህናት ላይ ይዘረጉ ዘንድ እንቢ አሉ።
18 ፤ ንጉሡም ዶይቅን። አንተ ዞረህ በካህናቱ ላይ ውደቅባቸው አለው። ኤዶማዊውም ዶይቅ ዞሮ በካህናቱ ላይ ወደቀ፥ በዚያም ቀን የበፍታ ኤፉድ የለበሱትን ሰማንያ አምስት ሰዎች ገደለ።
19 ፤ የካህናቱም ከተማ ኖብን በሰይፍ ስለት መታ፤ ወንዶችንና ሴቶችንም፥ ብላቴኖችንና ጡት የሚጠቡትን፥ በሬዎችንና አህዮችንም በጎችንም በሰይፍ ስለት ገደለ።
20 ፤ ከአኪጦብም ልጅ ከአቢሜሌክ ልጆች ስሙ አብያታር የሚባል አንዱ ልጅ አምልጦ ወደ ዳዊት ሸሸ።
21 ፤ አብያታርም ሳኦል የእግዚአብሔርን ካህናት እንደ ፈጀ ለዳዊት ነገረው።
22 ፤ ዳዊት አብያታርን። ኤዶማዊው ዶይቅ በዚያ መኖሩን ባየሁ ጊዜ። ለሳኦል በእርግጥ ይነግራል ብዬ በዚያው ቀን አውቄዋለሁ፤ ለአባትህ ቤት ነፍስ ሁሉ የጥፋታቸው ምክንያት እኔ ነኝ።
23 ፤ ነፍሴን የሚፈልግ የአንተን ነፍስ ይፈልጋልና፥ ከእኔም ጋር ተጠብቀህ ትኖራለህና በእኔ ዘንድ ተቀመጥ፥ አትፍራ አለው።

1 ፤ ለዳዊትም። እነሆ፥ ፍልስጥኤማውያን ቅዒላን ይወጋሉ፥ አውድማውንም ይዘርፋሉ የሚል ወሬ ደረሰው።
2 ፤ ዳዊትም። ልሂድን? እነዚህንስ ፍልስጥኤማውያን ልምታን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም ዳዊትን። ሂድ፥ ፍልስጥኤማውያንን ምታ ቅዒላንም አድን አለው።
3 ፤ የዳዊትም ሰዎች። እነሆ፥ በዚህ በይሁዳ መቀመጥ እንፈራለን፥ ይልቁንስ በፍልስጥኤማውያን ጭፍሮች ላይ ወደ ቅዒላ ብንሄድ እንዴት ነው? አሉት።
4 ፤ ዳዊትም ደግሞ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም መልሶ። ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጣለሁና ተነሥተህ ወደ ቅዒላ ውረድ አለው።
5 ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ወደ ቅዒላ ሄዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ተዋጉ፤ እንስሶቻቸውንም ማረኩ፥ በታላቅም አገዳደል ገደሉአቸው። ዳዊትም በቅዒላ የሚኖሩትን አዳነ።
6 ፤ እንዲህም ሆነ፤ የአቢሜሌክ ልጅ አብያታር ወደ ዳዊት ወደ ቅዒላ በኰበለለ ጊዜ ኤፉዱን ይዞ ወርዶ ነበር።
7 ፤ ሳኦልም ዳዊት ወደ ቅዒላ እንደ መጣ ሰማ፤ ሳኦልም። መዝጊያና መወርወሪያ ወዳለባት ከተማ ገብቶ ተገኝቶአልና እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ሰጥቶታል አለ።
8 ፤ ሳኦልም ወደ ቅዒላ ወርደው ይዋጉ ዘንድ፥ ዳዊትንና ሰዎቹንም ይከብቡ ዘንድ ሕዝቡን ሁሉ አዘዘ።
9 ፤ ዳዊትም ሳኦል ክፉን እንዳሰበበት አወቀ፤ ካሁኑን አብያታርንም። ኤፉዱን ወደዚህ አምጣ አለው።
10 ፤ ዳዊትም። የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ በእኔ ምክንያት ከተማይቱን ያጠፋ ዘንድ ሳኦል ወደ ቅዒላ ሊመጣ እንደሚፈልግ እኔ ባሪያህ ፈጽሜ ሰምቻለሁ።
11 ፤ የቅዒላ ሰዎች በእጁ አሳልፈው ይሰጡኛልን? ባሪያህስ እንደ ሰማ ሳኦል በውኑ ይወርዳልን? የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ እንድትነግረኝ እለምንሃለሁ አለ። እግዚአብሔርም። ይወርዳል አለ።
12 ፤ ዳዊትም። የቅዒላ ሰዎች እኔንና ሰዎቼን በሳኦል እጅ አሳልፈው ይሰጡናልን? አለ። እግዚአብሔርም። አሳልፈው ይሰጡአችኋል ብሎ ተናገረ።
13 ፤ ዳዊትና ስድስት መቶ የሚሆኑ ሰዎችም ተነሥተው ከቅዒላ ወጡ፥ መሄድም ወደሚችሉበት ሄዱ። ሳኦልም ዳዊት ከቅዒላ እንደ ሸሸ ሰማ፤ ስለዚህም ከመውጣት ቀረ።
14 ፤ ዳዊትም በምድረ በዳ በአምባ ውስጥ ይኖር ነበር፥ ከዚፍ ምድረ በዳም ባለው በተራራማው አገር ተቀመጠ፤ ሳኦልም ሁልጊዜ ይፈልገው ነበር፥ እግዚአብሔር ግን በእጁ አሳልፎ አልሰጠውም።
15 ፤ ዳዊትም ሳኦል ነፍሱን ሊፈልግ እንደ ወጣ አየ፤ ዳዊትም በዚፍ ምድረ በዳ በጥሻው ውስጥ ይኖር ነበር።
16 ፤ የሳኦልም ልጅ ዮናታን ተነሥቶ ወደ ዳዊት ወደ ጥሻው ስጥ ሄደ፤ እጁንም በእግዚአብሔር አጽንቶ።
17 ፤ የአባቴ የሳኦል እጅ አታገኝህምና አትፍራ፤ አንተም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ፥ እኔም ከአንተ በታች ሁለተኛ እሆናለሁ፤ ይህን ደግሞ አባቴ ሳኦል ያውቃል አለው።
18 ፤ ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረጉ፤ ዳዊትም በጥሻው ውስጥ ተቀመጠ፥ ዮናታንም ወደ ቤቱ ሄደ።
19 ፤ የዚፍ ሰዎችም ወደ ሳኦል ወደ ጊብዓ መጥተው። እነሆ፥ ዳዊት በየሴሞን ደቡብ በኩል በኤኬላ ኮረብታ ላይ በጥሻ ውስጥ ባሉት አምባዎች በእኛ ዘንድ ተሸሽጎ የለምን?
20 ፤ አሁንም፥ ንጉሥ ሆይ፥ ትወርድ ዘንድ ነፍስህ እንደ ወደደች ውረድ፤ በንጉሡም እጅ እርሱን አሳልፎ ለመስጠት እኛ አለን አሉት።
21 ፤ ሳኦልም አለ። እናንተ ስለ እኔ አዝናችኋልና ከእግዚአብሔር ዘንድ የተባረካችሁ ሁኑ፤
22 ፤ አሁንም ደግሞ ሂዱ፤ እርሱም እጅግ ተንኰለኛ እንደ ሆነ ሰምቻለሁና አጥብቃችሁ ፈልጉት፥ እግሩም የሚሄድበትን ስፍራ እዩና እወቁ፥ በዚያ ያየውንም ሰው አግኙ።
23 ፤ እርሱ የሚደበቅበትንና የሚሸሸግበትን ስፍራ እዩና እወቁ፥ በእርግጥም ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ከእናንተ ጋር እሄዳለሁ፤ በምድርም ውስጥ ቢሸሸግ በይሁዳ አእላፋት ሁሉ መካከል እፈልገዋለሁ።
24 ፤ እነዚያም ተነሥተው ከሳኦል በፊት ወደዚፍ ሄዱ፤ ዳዊትና ሰዎቹ ግን በየሴሞን ደቡብ በኩል በዓረባ በማዖን ምድረ በዳ ነበሩ።
25 ፤ ሳኦልና ሰዎቹም ሊፈልጉት ሄዱ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ወደ ዓለቱ ወርዶ በማዖን ምድረ በዳ ተቀመጠ፤ ሳኦልም ያንን በሰማ ጊዜ ዳዊትን በማዖን ምድረ በዳ አሳደደው።
26 ፤ ሳኦልም በተራራው በአንድ ወገን ሄደ፥ ዳዊትና ሰዎቹም በተራራው በሌላው ወገን ሄዱ። ሳኦልና ሰዎቹም ዳዊትንና ሰዎቹን ለመያዝ ከብበዋቸው ነበርና ዳዊት ከሳኦል ፊት ያመልጥ ዘንድ ፈጠነ።
27 ፤ ወደ ሳኦልም መልእክተኛ መጥቶ። ፍልስጥኤማውያን አገሩን ወርረውታልና ፈጥነህ ና አለው።
28 ፤ ሳኦልም ዳዊትን ማሳደድ ትቶ ተመለሰ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ሊዋጋ ሄደ። ስለዚህ የዚህ ስፍራ ስም የማምለጥ ዓለት ተባለ።
29 ፤ ዳዊትም ከዚያ ወጥቶ በዓይንጋዲ አምባዎች ተቀመጠ።

1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ከተመለሰ በኋላ። እነሆ፥ ዳዊት በዓይንጋዲ ምድረ በዳ አለ የሚል ወሬ ደረሰለት።
2 ፤ ሳኦልም ከእስራኤል ሁሉ የተመረጡትን ሦስት ሺህ ሰዎች ወሰደ፥ ዳዊትንና ሰዎቹንም ለመፈለግ የበረሀ ፍየሎች ወደ ነበሩባቸው ዓለቶች ሄደ።
3 ፤ በመንገድም አጠገብ ወዳሉት የበጎች ማደሪያዎች መጣ፥ በዚያም ዋሻ ነበረ፤ ሳኦልም ወገቡን ይሞክር ዘንድ ከዚያ ገባ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ከዋሻው በውስጠኛው ቦታ ተቀምጠው ነበር።
4 ፤ የዳዊትም ሰዎች። እነሆ፥ ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ በዓይንህም ደስ የሚያሰኝህን ታደርግበታለህ ብሎ እግዚአብሔር የነገረህ ቀን፥ እነሆ፥ ዛሬ ነው አሉት። ዳዊትም ተነሥቶ የሳኦልን መጎናጸፊያ ዘርፍ በቀስታ ቈረጠ።
5 ፤ ከዚያም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የሳኦልን የልብሱን ዘርፍ ስለቈረጠ የዳዊት ልብ በኀዘን ተመታ።
6 ፤ ሰዎቹንም። እግዚአብሔር የቀባው ነውና እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር አደርግ ዘንድ እጄንም እጥልበት ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው አላቸው።
7 ፤ ዳዊትም በዚህ ቃል ሰዎቹን ከለከላቸው፥ በሳኦልም ላይ ይነሡ ዘንድ አልተዋቸውም፤ ሳኦልም ከዋሻው ተነሥቶ መንገዱን ሄደ።
8 ፤ ከእርሱም በኋላ ዳዊት ደግሞ ተነሣ፥ ከዋሻውም ወጣ፥ ከሳኦልም በኋላ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ብሎ ጮኸ፤ ሳኦልም ወደ ኋላው ተመለከተ፥ ዳዊትም ወደ ምድር ተጐንብሶ እጅ ነሣ።
9 ፤ ዳዊትም ሳኦልን አለው። እነሆ፥ ዳዊት ክፉ ነገር ይሻብሃል የሚሉህን ሰዎች ቃል ለምን ትሰማለህ?
10 ፤ እነሆ፥ ዛሬ በዋሻው ውስጥ እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ እንደ ሰጠህ ዓይንህ አይታለች፤ አንተንም እንድገድልህ ሰዎች ተናገሩኝ፤ እኔ ግን። በእግዚአብሔር የተቀባ ነውና እጄን በጌታዬ ላይ አልዘረጋም ብዬ ራራሁልህ።
11 ፤ ደግሞም፥ አባቴ ሆይ፥ የልብስህ ዘርፍ በእጄ እንዳለ ተመልክተህ እወቅ፤ የልብስህንም ዘርፍ በቈረጥሁ ጊዜ አልገደልሁህም፤ ስለዚህም በእጄ ክፋትና በደል እንደሌለ፥ አንተም ነፍሴን ልትወስድ ምንም ብታሳድደኝ እንዳልበደልሁህ ተመልክተህ እወቅ።
12 ፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ፥ እግዚአብሔርም አንተን ይበቀልልኝ፤ እጄ ግን በአንተ ላይ አትሆንም።
13 ፤ በጥንት ምሳሌ። ከኃጢአተኞች ኀጢአት ይወጣል እንደ ተባለ፤ እጄ ግን በአንተ ላይ አትሆንም።
14 ፤ የእስራኤል ንጉሥ ማንን ለማሳደድ መጥቶአል? አንተስ ማንን ታሳድዳለህ? የሞተ ውሻን ወይስ ቁንጫን ታሳድዳለህን?
15 ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር ዳኛ ይሁን፥ በእኔና በአንተም መካከል ይፍረድ፥ አይቶም ይምዋገትልኝ፥ ከእጅህም ያድነኝ።
16 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት ይህን ቃል ለሳኦል መናገር በፈጸመ ጊዜ፥ ሳኦል። ልጄ ሆይ ዳዊት፥ ይህ ድምፅህ ነውን? አለ፤ ሳኦልም ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ።
17 ፤ ዳዊትን አለው። እኔ ክፉ በመለስሁልህ ፋንታ በጎ መልሰህልኛልና አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ።
18 ፤ እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶኝ ሳለ አልገደልኸኝምና ለእኔ መልካም እንዳደረግህልኝ አንተ ዛሬ አሳየኸኝ።
19 ፤ ጠላቱን አግኝቶ በመልካም መንገድ ሸኝቶ የሚሰድድ ማን ነው? ስለዚህ ለእኔ ስላደረግኸው ቸርነት እግዚአብሔር ይመልስልህ።
20 ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ አንተ በእርግጥ ንጉሥ እንድትሆን የእስራኤልም መንግሥት በእጅህ እንድትጸና እኔ አውቃለሁ።
21 ፤ አሁን እንግዲህ ከእኔ በኋላ ዘሬን እንዳትቈርጥ ከአባቴም ቤት ስሜን እንዳታጠፋው በእግዚአብሔር ማልልኝ።
22 ፤ ዳዊትም ለሳኦል ማለለት፤ ሳኦልም ወደ ቤቱ ሄደ፥ ዳዊትና ሰዎቹም ወደ አምባው ወጡ።

1 ፤ ሳሙኤልም ሞተ፤ እስራኤልም ሁሉ ተሰብስበው አለቀሱለት፥ በአርማቴምም በቤቱ ቀበሩት። ዳዊትም ተነሥቶ ወደ ፋራን ምድረ በዳ ወረደ።
2 ፤ በማዖንም የተቀመጠ አንድ ሰው ነበረ፥ ከብቱም በቀርሜሎስ ነበረ፤ እጅግም ታላቅ ሰው ነበረ፥ ለእርሱም ሦስት ሺህ በጎችና አንድ ሺህ ፍየሎች ነበሩት፤ በቀርሜሎስም በጎቹን ይሸልት ነበር።
3 ፤ የሰውዮውም ስም ናባል፥ የሚስቱም ስም አቢግያ ነበረ፤ የሴቲቱም አእምሮ ታላቅ፥ መልክዋም የተዋበ ነበረ፤ ሰውዮው ግን ባለጌ ነበረ፥ ግብሩም ክፉ ነበረ፤ ከካሌብም ወገን ነበረ።
4 ፤ ዳዊትም በምድረ በዳ ሳለ። ናባል በጎቹን ይሸልታል የሚል ወሬ ሰማ።
5 ፤ ዳዊትም አሥር ጕልማሶች ላከ ለጕልማሶችም አለ። ወደ ቀርሜሎስ ወጥታችሁ ወደ ናባል ሂዱ፥ በስሜም ስለ ሰላም ጠይቁት፤
6 ፤ እንዲህም በሉት። በደኅንነት ኑር፥ ለአንተና ለቤትህም ለአንተም ላሉት ሁሉ ሰላም ይሁን።
7 ፤ አሁንም በጎችህን እንድትሸልት ሰምቻለሁ፤ እረኞችህም ከእኛ ጋር ነበሩ፥ ከቶ አልበደልናቸውም፤ በቀርሜሎስም በተቀመጡበት ዘመን ሁሉ ከመንጋው አንዳች አልጎደለባቸውም።
8 ፤ ጕልማሶችህን ጠይቃቸው፥ እነርሱም ይነግሩሃል፤ አሁንም እንግዲህ በመልካም ቀን መጥተንብሃልና ጕልማሶች በፊትህ ሞገስ ያግኙ፤ በእጅህም ከተገኘው ለባሪያዎችህና ለልጅህ ለዳዊት፥ እባክህ፥ ስጥ።
9 ፤ የዳዊትም ጕልማሶች መጡ፥ ይህንም ቃል ሁሉ በዳዊት ስም ለናባል ነግረው ዝም አሉ።
10 ፤ ናባልም ለዳዊት ባሪያዎች። ዳዊት ማን ነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? እያንዳንዳቸው ከጌቶቻቸው የኰበለሉ ባሪያዎች ዛሬ ብዙዎች ናቸው።
11 ፤ እንጀራዬንና የወይን ጠጄን ለሸላቾቼም ያረድሁትን ሥጋ ወስጄ ከወዴት እንደ ሆኑ ለማላውቃቸው ሰዎች እሰጣለሁን? ብሎ መለሰላቸው።
12 ፤ የዳዊትም ጕልማሶች ዞረው በመጡበት መንገድ ተመለሱ፥ መጥተውም ይህን ነገር ሁሉ ለዳዊት ነገሩት።
13 ፤ ዳዊትም ሰዎቹን። ሁላችሁ ሰይፋችሁን ታጠቁ አላቸው። ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፥ ዳዊትም ሰይፉን ታጠቀ፤ አራት መቶ ሰዎችም ዳዊትን ተከትለው ወጡ፥ ሁለት መቶውም በዕቃው ዘንድ ተቀመጡ።
14 ፤ ከብላቴኖቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢግያ እንዲህ ብሎ ነገራት። እነሆ፥ ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ጌታችንን ሊባርኩ መልእክተኞች ላከ፤ እርሱ ግን ሰደባቸው።
15 ፤ እነዚህ ሰዎች ግን በእኛ ዘንድ እጅግ መልካም ነበሩ፤ አልበደሉንምም፥ ከእነርሱም በሄድንበት ዘመን ሁሉ በምድረ በዳ ሳለን አንዳች አልጠፋብንም፤
16 ፤ ከእነርሱ ጋር ሆነን መንጋውን በጠበቅንበት ዘመን ሁሉ ሌሊትና ቀን አጥር ሆነውን ነበር።
17 ፤ ስለዚህም በጌታችንና በቤቱ ሁሉ ላይ ክፉ ነገር እንዲመጣ ተቈርጦአልና፥ እርሱ ምናምንቴ ሰው ስለ ሆነ ማንም ሊናገረው አይችልምና የምታደርጊውን ተመልከቺና እወቂ።
18 ፤ አቢግያም ፈጥና ሁለት መቶ እንጀራ፥ ሁለት አቁማዳ የወይን ጠጅ፥ አምስትም የተዘጋጁ በጎች፥ አምስትም መስፈሪያ ጥብስ እሸት፥ አንድ መቶ ዘለላ ዘቢብ፥ ሁለት መቶም የበለስ ጥፍጥፍ ወሰደች፥ በአህዮችም ላይ አስጫነች።
19 ፤ ለብላቴኖችዋም። አስቀድማችሁ በፊቴ ሂዱ፥ እነሆም፥ እከተላችኋለሁ አለች። ይህንም ለባልዋ ለናባል አልነገረችውም።
20 ፤ እርስዋም በአህያው ላይ ተቀምጣ በተራራው ላይ በተሰወረ ስፍራ በወረደች ጊዜ፥ እነሆ፥ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እርስዋ ወረዱ፤ እርስዋም ተገናኘቻቸው።
21 ፤ ዳዊትም። ለዚህ ሰው ከሆነው ሁሉ አንድ ነገር እንዳይጠፋበት በእውነት ከብቱን ሁሉ በምድረ በዳ በከንቱ ጠበቅሁ፥ እርሱም ስለ በጎነቴ ክፋት መለሰልኝ።
22 ፤ ለእርሱም ከሆነው ሁሉ እስከ ነገ ጥዋት ድረስ አንድ ወንድ ስንኳ ብተው፥ እግዚአብሔር በዳዊት ላይ እንዲህ ያድርግ እንዲህም ይጨምር ብሎ ነበር።
23 ፤ አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ከአህያዋ ላይ ፈጥና ወረደች፥ በዳዊትም ፊት በግምባርዋ ወደቀች፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣች።
24 ፤ በእግሩም ላይ ወደቀች፥ እንዲህም አለች። ጌታዬ ሆይ፥ ይህ ኃጢአት በእኔ ላይ ይሁን፤ እኔ ባሪያህ በጆሮህ ልናገር፥ የባሪያህንም ቃል አድምጥ።
25 ፤ በዚህ ምናምንቴ ሰው በናባል ላይ ጌታዬ ልቡን እንዳይጣል እለምናለሁ፤ እንደ ስሙ እንዲሁ እርሱ ነው፤ ስሙ ናባል ነው፥ ስንፍናም አድሮበታል፤ እኔ ባሪያህ ግን ከአንተ የተላኩትን የጌታዬን ጕልማሶች አላየሁም።
26 ፤ አሁንም፥ ጌታዬ ሆይ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! ወደ ደም እንዳትገባ፥ እጅህም ራስህን እንዳታድን የከለከለህ እግዚአብሔር ነው፤ አሁንም ጠላቶችህና በጌታዬ ላይ ክፉ የሚሹ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ።
27 ፤ አሁንም ባሪያህ ወደ ጌታዬ ያመጣችው ይህ መተያያ ጌታዬን ለሚከተሉ ጕልማሶች ይሰጥ።
28 ፤ የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለምትዋጋ እግዚአብሔር በእውነት ለጌታዬ የታመነ ቤት ይሠራልና የእኔን የባሪያህን ኃጢአት፥ እባክህ፥ ይቅር በል፤ በዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህም።
29 ፤ ያሳድድህ ዘንድ ነፍስህንም ይሻ ዘንድ ሰው ቢነሣ፥ የጌታዬ ነፍስ በሕያዋን ወገን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የታሰረች ትሆናለች፤ የጠላቶችህንም ነፋስ ከወንጭፍ እንደሚጣል እንዲሁ ይጥላታል።
30 ፤ እግዚአብሔርም ለጌታዬ የተናገረውን ቸርነት ሁሉ ባደረገልህ ጊዜ፥ በእስራኤልም ላይ አለቃ አድርጎ ባስነሣህ ጊዜ፥
31 ፤ አንተ በከንቱ ደም እንዳላፈሰስህ፥ በገዛ እጅህም እንዳልተካስህ ይህ ዕንቅፋትና የሕሊና ጸጸት በጌታዬ አይሆንልህም፤ እግዚአብሔርም ለጌታዬ በጎ ባደረገልህ ጊዜ፥ ባሪያህን አስብ።
32 ፤ ዳዊትም አቢግያን አላት። ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የሰደደ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን።
33 ፤ ወደ ደም እንዳልሄድ፥ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፥ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ።
34 ፤ ነገር ግን ክፉ እንዳላደርግብሽ የከለከለኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔን ለመገናኘት ፈጥነሽ ባልመጣሽ ኖሮ እስኪነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ ስንኳ ባልቀረውም ነበር።
35 ፤ ዳዊትም ያመጣችውን ከእጅዋ ተቀብሎ። በደኅና ወደቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፥ ቃልሽን ሰማሁ፥ ፊትሽንም አከበርሁ አላት።
36 ፤ አቢግያም ወደ ናባል መጣች፤ እነሆም፥ በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ግብዣ ያደርግ ነበር፤ ናባልም እጅግ ሰክሮ ነበርና ልቡ ደስ ብሎት ነበር፤ ስለዚህም እስኪነጋ ድረስ ታናሽ ነገር ወይም ታላቅ ነገር አልነገረችውም ነበር።
37 ፤ በነጋውም የጠጁ ስካር ከናባል ባለፈ ጊዜ ሚስቱ ይህን ነገር ነገረችው፤ ልቡም በውስጡ ሞተ፥
38 ፤ እንደ ድንጋይም ሆነ፤ ከአሥር ቀንም በኋላ እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፥ እርሱም ሞተ።
39 ፤ ዳዊትም ናባል እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ። ከናባል እጅ የስድቤን ፍርድ የፈረደልኝ፥ ባሪያውንም ከክፋት የጠበቀ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እግዚአብሔርም የናባልን ክፋት በራሱ ላይ መለሰ አለ። ዳዊትም ልኮ ያገባት ዘንድ አቢግያን ተነጋገራት።
40 ፤ የዳዊትም ባሪያዎች ወደ ቀርሜሎስ ወደ አቢግያ በመጡ ጊዜ። ዳዊት ያገባሽ ዘንድ ወደ አንቺ ልኮናል ብለው ነገሩአት።
41 ፤ ተነሥታም በግምባርዋ ወድቃ እጅ ነሣችና። እነሆ፥ እኔ ገረድህ የጌታዬን ሎሌዎች እግር አጥብ ዘንድ አገልጋይ ነኝ አለች።
42 ፤ አቢግያም ፈጥና ተነሣች፤ በአህያም ላይ ተቀመጠች፥ አምስቱም ገረዶችዋ ተከተሉአት፤ የዳዊትንም መልእክተኞች ተከትላ ሄደች፥ ሚስትም ሆነችው።
43 ፤ ዳዊትም ደግሞ ኢይዝራኤላዊቱን አኪናሆምን ወሰደ፤ ሁለቱም ሚስቶች ሆኑለት።
44 ፤ ሳኦል ግን የዳዊትን ሚስት ልጁን ሜልኮልን አገሩ ጋሊም ለነበረው ለሌሳ ልጅ ለፈልጢ ሰጥቶ ነበር።

1 ፤ የዚፍ ሰዎችም ወደ ጊብዓ ወደ ሳኦል መጥተው። እነሆ፥ ዳዊት በየሴሞን ፊት ለፊት ባለው በኤኬላ ኮረብታ ላይ ተሸሽጎአል አሉት።
2 ፤ ሳኦልም ተነሥቶ ዳዊትን በዚፍ ምድረ በዳ ይሻ ዘንድ ከእስራኤል የተመረጡ ሦስት ሺህ ሰዎች ይዞ ወደ ዚፍ ምድረ በዳ ወረደ።
3 ፤ ሳኦልም በየሴሞን ፊት ለፊት ባለው በኤኬላ ኮረብታ ላይ በመንገዱ አጠገብ ሰፈረ። ዳዊትም በምድረ በዳ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፥ ሳኦልም በስተ ኋላው ወደ ምድረ በዳ እንደ መጣ አየ።
4 ፤ ዳዊትም ሰላዮች ሰደደ፥ ሳኦልም ወደዚህ እንደ መጣ በእርግጥ አወቀ።
5 ፤ ዳዊትም ተነሥቶ ሳኦል ወደ ሰፈረበት ቦታ መጣ፤ ሳኦልና የሠራዊቱ አለቃ የኔር ልጅ አበኔርም የተኙበትን ስፍራ አየ፤ ሳኦልም በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ነበር፤ ሕዝቡም በዙሪያው ሰፍሮ ነበር።
6 ፤ ዳዊትም ኬጢያዊውን አቢሜሌክንና የጽሩያን ልጅ የኢዮአብን ወንድም አቢሳን። ወደ ሳኦል ወደ ሰፈሩ ከእኔ ጋር የሚወርድ ማን ነው? ብሎ ጠየቃቸው፤ አቢሳም። እኔ ከአንተ ጋር እወርዳለሁ አለ።
7 ፤ ዳዊትና አቢሳም ወደ ሕዝቡ በሌሊት መጡ፤ እነሆም፥ ሳኦል ጦሩ በራሱ አጠገብ በምድር ተተክሎ በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ነበር፤ አበኔርና ሕዝቡም በዙርያው ተኝተው ነበር።
8 ፤ አቢሳም ዳዊትን። ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አሁንም እኔ በጦር አንድ ጊዜ ከምድር ጋር ላጣብቀው፥ ሁለተኛም አያዳግምም አለው።
9 ፤ ዳዊትም አቢሳን። እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን የሚዘረጋ ንጹሕ አይሆንምና አትግደለው አለው።
10 ፤ ደግሞም ዳዊት። ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ይመታዋል፥ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፥ ወይም ወደ ሰልፍ ወርዶ ይገደላል፤
11 ፤ እኔ ግን እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው፤ አሁንም በራሱ አጠገብ ያለውን ጦርና የውኃውን መንቀል ይዘህ እንሂድ አለ።
12 ፤ ዳዊትም በሳኦል ራስ አጠገብ የነበረውን ጦርና የውኃውን መንቀል ወሰደ፤ ማንም ሳያይ ሳያውቅም ሄዱ፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ከባድ እንቅልፍ ወድቆባቸው ነበርና ሁሉ ተኝተው ነበር እንጂ የነቃ አልነበረም።
13 ፤ ዳዊትም ወደዚያ ተሻገረ፤ በተራራውም ራስ ላይ ርቆ ቆመ፤ በመካከላቸውም ሰፊ ስፍራ ነበረ።
14 ፤ ዳዊትም ለሕዝቡና ለኔር ልጅ ለአበኔር። አበኔር ሆይ፥ አትመልስምን? ብሎ ጮኸ። አበኔርም መልሶ። ለንጉሡ የምትጮኸው አንተ ማን ነህ? አለ።
15 ፤ ዳዊትም አበኔርን። አንተ ጕልማሳ አይደለህምን? በእስራኤል ዘንድ አንተን የሚመስል ማን ነው? ጌታህን ንጉሡን ለመግደል አንድ ሰው ገብቶ ነበርና ጌታህን ንጉሡን የማትጠብቅ ስለ ምን ነው?
16 ፤ ይህ ያደረግኸው ነገር መልካም አይደለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! እናንተ እግዚአብሔር የቀባውን ጌታችሁን አልጠበቃችሁምና ሞት ይገባችኋል፤ አሁንም የንጉሡ ጦርና በራሱ አጠገብ የነበረው የውኃው መንቀል የት እንደ ሆነ ተመልከት አለው።
17 ፤ ሳኦልም የዳዊት ድምፅ እንደ ሆነ አውቆ። ልጄ ዳዊት ሆይ፥ ይህ ድምፅህ ነውን? አለው። ዳዊትም። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ድምፄ ነው አለው።
18 ፤ ደግሞ አለ። ጌታዬ ባሪያውን ስለ ምን ያሳድዳል? ምን አደረግሁ? ምንስ ክፋት በእጄ ላይ ተገኘብኝ?
19 ፤ አሁንም ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የእኔን የባሪያህን ቃል ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ እግዚአብሔር በእኔ ላይ አስነሥቶህ እንደ ሆነ፥ ቁርባንን ይቀበል፤ የሰው ልጆች ግን ቢሆኑ። ሂድ ሌሎችን አማልክት አምልክ ብለው በእግዚአብሔር ርስት ላይ እንዳልቀመጥ ዛሬ ጥለውኛልና በእግዚአብሔር ፊት ርጉማን ይሁኑ።
20 ፤ አሁንም በተራራው ላይ ሰው ቆቅን እንደሚሻ የእስራኤል ንጉሥ ነፍሴን ለመሻት ወጥቶአልና ደሜ ከእግዚአብሔር ፊት ርቆ በምድር ላይ አይፍሰስ።
21 ፤ ሳኦልም። በድያለሁ፤ ልጄ ሆይ ዳዊት፥ ተመለስ፤ ዛሬ ነፍሴ በዓይንህ ፊት ከብራለችና ከዚህ በኋላ ክፉ አላደርግብህም እነሆ፥ ስንፍና አድርጌአለሁ፥ እጅግ ብዙም ስቻለሁ አለ።
22 ፤ ዳዊትም መልሶ አለ። የንጉሥ ጦር እነሆ፥ ከብላቴኖችም አንድ ይምጣና ይውሰዳት።
23 ፤ ዛሬም እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ሰጥቶህ ሳለ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ አልወደድሁምና ለሁሉ እያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ጽድቁና እንደ እምነቱ ፍዳውን ይክፈለው።
24 ፤ ነፍስህም ዛሬ በዓይኔ ፊት እንደ ከበረች እንዲሁ ነፍሴ በእግዚአብሔር ዓይን ፊት ትክበር፥ ከመከራም ሁሉ ያድነኝ።
25 ፤ ሳኦል ዳዊትን። ልጄ ዳዊት ሆይ፥ ቡሩክ ሁን፤ ማድረግን ታደርጋለህ፥ መቻልንም ትችላለህ አለው። ዳዊትም መንገዱን ሄደ፥ ሳኦልም ወደ ስፍራው ተመለሰ።

 

1 ፤ ዳዊትም በልቡ። አንድ ቀን በሳኦል እጅ እጠፋለሁ፤ ወደ ፍልስጥኤማውያንም ምድር ከመሸሽ በቀር የሚሻለኝ የለም፤ ሳኦልም በእስራኤል አውራጃ ሁሉ እኔን መሻት ይተዋል፥ እንዲሁም ከእጁ እድናለሁ አለ።
2 ፤ ዳዊትም ከእርሱም ጋር የነበሩት ስድስቱ መቶ ሰዎች ተነሥተው ወደ ጌት ንጉሥ ወደ አሜህ ልጅ ወደ አንኩስ አለፉ።
3 ፤ ዳዊትና ሰዎቹም እያንዳንዳቸው ከነ ቤተ ሰቡ ከአንኩስ ጋር በጌት ውስጥ ተቀመጡ፤ ከዳዊትም ጋር ኢይዝራኤላዊቱ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት አቢግያ ሁለቱ ሚስቶቹ ነበሩ።
4 ፤ ሳኦልም ዳዊት ወደ ጌት እንደ ኰበለለ ሰማ፤ ከዚያም በኋላ ደግሞ አልፈለገውም።
5 ፤ ዳዊትም አንኩስን። በዓይንህ ፊት ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ በዚህ አገር በአንዲቱ ከተማ የምቀመጥበት ስፍራ ስጠኝ፤ ስለ ምን እኔ ባሪያህ ከአንተ ጋር በንጉሥ ከተማ እቀመጣለሁ? አለው።
6 ፤ በዚያም ቀን አንኩስ ጺቅላግን ሰጠው፤ ስለዚህም ጺቅላግ እስከ ዛሬ ድረስ ለይሁዳ ነገሥታት ሆነች።
7 ፤ ዳዊትም በፍልስጥኤማውያን አገር የተቀመጠበት የዘመን ቍጥር አንድ ዓመት ከአራት ወር ነበረ።
8 ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ወጥተው በጌሹራውያንና በጌርዛውያን በአማሌቃውያንም ላይ ዘመቱ፤ እነዚህም እስከ ሱር እስከ ግብጽ ምድር ድረስ ባለው አገር ድሮውኑ ተቀምጠው ነበር።
9 ፤ ዳዊትም ምድሪቱን መታ፤ ወንድ ሆነ ሴትም ሆነ ማንንም በሕይወት አልተወም፤ በጎችንና ላሞችን አህያዎችንና ግመሎችን ልብስንም ማረከ፥ ተመልሶም ወደ አንኩስ መጣ።
10 ፤ አንኩስም። ዛሬ በማን ላይ ዘመታችሁ? አለ፤ ዳዊትም። በይሁዳ ደቡብ፥ በይረሕምኤላውያንም ደቡብ፥ በቄናውያንም ደቡብ ላይ ዘመትን አለ።
11 ፤ ዳዊት እንዲህ አደረገ በፍልስጥኤማውያንም አገር በሚቀመጥበት ዘመን ሁሉ ልማዱ ይህ ነበረ ብለው እንዳይናገሩብን ብሎ ዳዊት ወደ ጌት ያመጣቸው ዘንድ ወንድም ሆነ ሴትም ሆነ ማንንም በሕይወት አልተወም።
12 ፤ አንኩስም። በሕዝቡ በእስራኤል ዘንድ እጅግ የተጠላ ሆኖአል፤ ስለዚህም ለዘላለም ባሪያ ይሆነኛል ብሎ ዳዊትን አመነው።

1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በዚያ ወራት ከእስራኤል ጋር ይዋጉ ዘንድ ፍልስጥኤማውያን ጭፍሮቻቸውን ለሰልፍ ሰበሰቡ፤ አንኩስም ዳዊትን። አንተና ሰዎችህ ከእኔ ጋር ወደ ሰልፍ እንድትወጡ በእርግጥ እወቅ አለው።
2 ፤ ዳዊትም አንኩስን። አሁን ባሪያህ የሚያደርገውን ታያለህ አለው። አንኩስም ዳዊትን። እንግዲህ በዘመኑ ሁሉ ራሴን ጠባቂ አደርግሃለሁ አለው።
3 ፤ ሳሙኤል ግን ሞቶ ነበር፥ እስራኤልም ሁሉ አልቅሰውለት ነበር፥ በከተማውም በአርማቴም ቀብረውት ነበር። ሳኦልም መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር አጥፍቶ ነበር።
4 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ተሰብስበው መጡ በሱነምም ሰፈሩ፤ ሳኦልም እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ በጊልቦዓም ሰፈሩ።
5 ፤ ሳኦልም የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ባየ ጊዜ ፈራ፥ ልቡም እጅግ ተንቀጠቀጠ።
6 ፤ ሳኦልም እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም በሕልም ወይም በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም።
7 ፤ ሳኦልም ባሪያዎቹን። ወደ እርስዋ ሄጄ እጠይቅ ዘንድ መናፍስትን የምትጠራ ሴት ፈልጉልኝ አላቸው፤ ባሪያዎቹም። እነሆ፥ መናፍስትን የምትጠራ አንዲት ሴት በዓይንዶር አለች አሉት።
8 ፤ ሳኦልም መልኩን ለውጦ ሌላ ልብስም ለብሶ ሄደ፥ ሁለትም ሰዎች ከእርሱ ጋር ነበሩ፥ በሌሊትም ወደ ሴቲቱ መጡ። እርሱም። እባክሽ፥ በመናፍስት አምዋርቺልኝ፥ የምልሽንም አስነሽልኝ አላት።
9 ፤ ሴቲቱም። እነሆ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር እንዳጠፋ ሳኦል ያደረገውን ታውቃለህ፤ ስለ ምን እኔን ለማስገደል ወጥመድ ለነፍሴ ታደርጋለህ? አለችው።
10 ፤ ሳኦልም። ሕያው እግዚአብሔርን! በዚህ ነገር ቅጣት አያገኝሽም ብሎ በእግዚአብሔር ማለላት።
11 ፤ ሴቲቱም። ማንን ላስነሣልህ? አለች፤ እርሱም። ሳሙኤልን አስነሽልኝ አለ።
12 ፤ ሴቲቱም ሳሙኤልን ባየች ጊዜ በታላቅ ድምፅ ጮኸች፤ ሴቲቱም ሳኦልን። አንተ ሳኦል ስትሆን ለምን አታለልኸኝ? ብላ ተናገረችው።
13 ፤ ንጉሡም። አትፍሪ፤ ያየሽው ምንድር ነው? አላት። ሴቲቱም ሳኦልን። አማልክት ከምድር ሲወጡ አየሁ አለችው።
14 ፤ እርሱም። መልኩ ምን ዓይነት ነው? አላት። እርስዋም። ሽማግሌ ሰው ወጣ፤ መጐናጸፊያም ተጐናጽፎአል አለች። ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ሆነ አወቀ፥ በፊቱም ተጐነበሰ፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣ።
15 ፤ ሳሙኤልም ሳኦልን። ለምን አወክኸኝ? ለምንስ አስነሣኸኝ? አለው። ሳኦልም መልሶ። ፍልስጥኤማውያን ይወጉኛልና እጅግ ተጨንቄአለሁ፥ እግዚአብሔርም ከእኔ ርቆአል፤ በነቢያት ወይም በሕልም አልመለሰልኝም፤ ስለዚህም የማደርገውን ታስታውቀኝ ዘንድ ጠራሁህ አለው።
16 ፤ ሳሙኤልም አለ። እግዚአብሔር ከራቀህ ጠላትም ከሆነህ ለምን ትጠይቀኛለህ?
17 ፤ እግዚአብሔርም በቃሌ እንደ ተናገረ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም መንግሥትህን ከእጅህ ነጥቆ ለጎረቤትህ ለዳዊት ሰጥቶታል።
18 ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህምና፥ በአማሌቅም ላይ ታላቅ የሆነ ቍጣውን አላደረግህምና ስለዚህ ዛሬ እግዚአብሔር ይህን ነገር አድርጎብሃል።
19 ፤ እግዚአብሔርም እስራኤልን ከአንተ ጋር በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል፤ ነገም አንተና ልጆችህ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ጭፍራ ደግሞ በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል።
20 ፤ ሳኦልም በዚያን ጊዜ በቁመቱ ሙሉ በምድር ላይ ወደቀ፥ ከሳሙኤልም ቃል የተነሣ እጅግ ፈራ። በዚያም ቀን ሁሉ በዚያም ሌሊት ሁሉ እንጀራ አልበላምና ኃይል አልቀረለትም።
21 ፤ ሴቲቱም ወደ ሳኦል መጣች፥ እጅግም ደንግጦ እንደ ነበረ አይታ። እነሆ፥ እኔ ባሪያህ ቃልህን ሰማሁ፥ ነፍሴንም በእጄ ጣልሁ፥ የነገርኸኝንም ቃል ሰማሁ።
22 ፤ አሁን እንግዲህ አንተ ደግሞ የባሪያህን ቃል እንድትሰማ እለምንሃለሁ፥ በፊትህም ቍራሽ እንጀራ ላኑርልህ፤ በመንገድም ስትሄድ ትበረታ ዘንድ ብላ አለችው።
23 ፤ እርሱ ግን። አልበላም ብሎ እንቢ አለ፤ ነገር ግን ባሪያዎቹና ሴቲቱ አስገደዱት፥ ቃላቸውንም ሰማ፤ ከምድርም ተነሥቶ በአልጋ ላይ ተቀመጠ።
24 ፤ ለሴቲቱም ማለፊያ እንቦሳ ነበራት፤ ፈጥና አረደችው፤ ዱቄቱንም ወስዳ ለወሰችው፥ ቂጣም እንጀራ አድርጋ ጋገረችው።
25 ፤ በሳኦልና በባሪያዎቹም ፊት አቀረበችው፤ በልተውም ተነሡ፥ በዚያም ሌሊት ሄዱ።

1 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ጭፍሮቻቸውን ሁሉ ወደ አፌቅ ሰበሰቡ፤ እስራኤላውያንም በኢይዝራኤል ባለው ውኃ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ።
2 ፤ የፍልስጥኤማውያንም አለቆች በመቶ በመቶ በሺህ በሺህ እየሆኑ ያልፉ ነበር፤ ዳዊትና ሰዎቹም ከአንኩስ ጋር በኋለኛው ጭፍራ በኩል ያልፉ ነበር።
3 ፤ የፍልስጥኤማውያንም አለቆች። እነዚህ ዕብራውያን በዚህ ምን ያደርጋሉ? አሉ፤ አንኩስም የፍልስጥኤማውያንን አለቆች። ይህ የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል ባሪያ ዳዊት አይደለምን? እርሱም በእነዚህ ቀኖች በእነዚህ ዓመታት ከእኔ ጋር ነበረ፥ ወደ እኔም ከተጠጋበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ምንም አላገኘሁበትም አላቸው።
4 ፤ የፍልስጥኤማውያን አለቆች ግን ተቆጥተው። ይህ ሰው ባስቀመጥኸው ስፍራ ይቀመጥ ዘንድ ይመለስ፤ በሰልፉ ውስጥ ጠላት እንዳይሆነን ከእኛ ጋር ወደ ሰልፍ አይውረድ፤ ከጌታው ጋር በምን ይታረቃል? የእነዚህን ሰዎች ራስ በመቍረጥ አይደለምን?
5 ፤ ወይስ ሴቶች። ሳኦል ሺህ ገደለ፥ ዳዊት እልፍ ገደለ ብለው በዘፈን የዘመሩለት ይህ ዳዊት አይደለምን? አሉት።
6 ፤ አንኩስም ዳዊትን ጠርቶ። ሕያው እግዚአብሔርን! አንተ ቅን ነህ፥ ከእኔም ጋር በጭፍራው በኩል መውጣትህና መግባትህ በፊቴ መልካም ነው፤ ወደ እኔም ከመጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ አንዳች ክፋት አላገኘሁብህም፤ ነገር ግን በአለቆች ዘንድ አልተወደድህም።
7 ፤ አሁንም ተመልሰህ በደኅና ሂድ፥ በፍልስጥኤማውያንም አለቆች ዓይን ክፋት አታድርግ አለው።
8 ፤ ዳዊትም አንኩስን። ምን አድርጌአለሁ? ሄጄስ ከጌታዬ ከንጉሡ ጠላቶች ጋር እንዳልዋጋ፥ በፊትህ ከተቀመጥሁ ጀምሬ እስከ ዛሬ ድረስ በእኔ በባሪያህ ምን አግኝተህብኛል? አለው።
9 ፤ አንኩስም መልሶ ዳዊትን። እንደ አምላክ መልእክተኛ በዓይኔ ፊት መልካም እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ነገር ግን የፍልስጥኤማውያን አለቆች። ከእኛ ጋር ወደ ሰልፍ አይወጣም አሉ።
10 ፤ አሁንም አንተ ከአንተም ጋር የመጡ የጌታህ ባሪያዎች ማልዳችሁ ተነሡ፤ ሲነጋም ተነሥታችሁ ሂዱ አለው።
11 ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ማልደው ይሄዱ ዘንድ፥ ወደ ፍልስጥኤማውያንም አገር ይመለሱ ዘንድ ተነሡ። ፍልስጥኤማውያንም ወደ ኢይዝራኤል ወጡ።

1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ዳዊትና ሰዎቹ በሦስተኛው ቀን ወደ ጺቅላግ በመጡ ጊዜ፥ አማሌቃውያን በደቡብ አገርና በጺቅላግ ላይ ዘምተው ነበር፥ ጺቅላግንም መትተው በእሳት አቃጥለዋት ነበር፤
2 ፤ ሴቶቹንና በውስጥዋም የነበሩትን ሁሉ ከታናሽ እስከ ታላቅ ድረስ ማርከው ነበር፤ ሁሉንም ወስደው መንገዳቸውን ሄዱ እንጂ አንድስ እንኳ አልገደሉም ነበር።
3 ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ወደ ከተማ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ በእሳት ተቃጥላ፥ ሚስቶቻቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም ተማርከው አገኙ።
4 ፤ ዳዊት ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለማልቀስ ኃይል እስኪያጡ ድረስ አለቀሱ።
5 ፤ የዳዊትም ሁለቱ ሚስቶቹ ኢይዝራኤላዊቱ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢግያ ተማርከው ነበር።
6 ፤ ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻቸው የሕዝቡ ሁሉ ልብ ተቈጥቶ ነበርና ሕዝቡ ሊወግሩት ስለ ተናገሩ ዳዊት እጅግ ተጨነቀ፤ ዳዊት ግን በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን አበረታ።
7 ፤ ዳዊትም የአቢሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን። ኤፉዱን አቅርብልኝ አለው፤ አብያታርም ኤፉዱን ለዳዊት አቀረበለት።
8 ፤ ዳዊትም። የእነዚህን ሠራዊት ፍለጋ ልከተልን? አገኛቸዋለሁን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እርሱም። ታገኛቸዋለህና፥ ፈጽመህም ምርኮውን ትመልሳለህና ፍለጋቸውን ተከተል ብሎ መለሰለት።
9 ፤ ዳዊትም ከእርሱም ጋር የነበሩት ስድስት መቶ ሰዎች ሄዱ፥ እስከ ቦሦር ወንዝ ድረስም መጡ፤ ከእነርሱም የቀሩት በዚያ ተቀመጡ።
10 ፤ ዳዊትም ከእርሱም ጋር ያሉት አራት መቶ ሰዎች አሳደዱ፤ ሁለቱ መቶ ሰዎች ግን የቦሦር ወንዝን መሻገር ደክመዋልና በኋላ ቀሩ።
11 ፤ በበረሀውም ውስጥ አንድ ግብጻዊ አግኝተው ወደ ዳዊት ይዘውት መጡ፤ እንጀራም ሰጡትና በላ፥ ውኃም አጠጡት፤
12 ፤ ከበለሱም ጥፍጥፍ ቁራጭና ሁለት የወይን ዘለላ ሰጡት፤ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንጀራ አልበላም ውኃም አልጠጣም ነበርና በበላ ጊዜ ነፍሱ ወደ እርሱ ተመለሰች።
13 ፤ ዳዊትም። አንተ የማን ነህ? ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም። እኔ የአማሌቃዊ ባሪያ ግብጻዊ ብላቴና ነኝ፤ ከሦስት ቀንም በፊት ታምሜ ነበርና ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ።
14 ፤ እኛም በከሊታውያን ደቡብ፥ በይሁዳም ምድር፥ በካሌብም ደቡብ ላይ ዘመትን፤ ጺቅላግንም በእሳት አቃጠልናት አለ።
15 ፤ ዳዊትም። ወደ እነዚያ ሠራዊት ዘንድ ልትመራኝ ትወድዳለህን? አለው፤ እርሱም። እንዳትገድለኝ፥ ለጌታዬም እጅ አሳልፈህ እንዳትሰጠኝ በአምላክ ማልልኝ እንጂ ወደ እነዚያ ሠራዊት እመራሃለሁ አለ።
16 ፤ ወደ ታችም እንዲወርድ ባደረገው ጊዜ፥ እነሆ፥ ከፍልስጥኤማውያንና ከይሁዳ ምድር ከወሰዱት ከብዙ ምርኮ ሁሉ የተነሣ በልተው ጠጥተውም የበዓልም ቀን አድርገው በምድር ሁሉ ላይ ተበትነው ነበር።
17 ፤ ዳዊትም ከማታ ጀምሮ እስከ ማግሥቱ ማታ ድረስ መታቸው፤ ከእነርሱም በግመል ተቀምጠው ከሸሹ ከአራት መቶ ጕልማሶች በቀር አንድ ያመለጠ የለም።
18 ፤ ዳዊትም አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣላቸው፥ ሁለቱንም ሚስቶቹን አዳነ።
19 ፤ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች፥ ከወሰዱትም ምርኮ ሁሉ፥ ታላቅም ሆነ ታናሽም ሆነ፥ ምንም የጐደለባቸው የለም፤ ዳዊትም ሁሉን አስጣለ።
20 ፤ ዳዊትም የበጉንና የላሙን መንጋ ሁሉ ወሰደ፥ ከራሱም ከብት ፊት እየነዳ። ይህ የዳዊት ምርኮ ነው አለ።
21 ፤ ዳዊትም ደክመው ዳዊትን ይከተሉት ዘንድ ወዳልቻሉ፥ በቦሦር ወንዝ ወዳስቀራቸው ወደ ሁለቱ መቶ ሰዎች መጣ፤ እነርሱም ዳዊትን ከእርሱም ጋር የነበሩትን ሕዝብ ሊቀበሉ ወጡ፤ ዳዊትም ወደ ሕዝቡ በቀረበ ጊዜ ደኅንነታቸውን ጠየቀ።
22 ፤ ከዳዊትም ጋር ከሄዱ ሰዎች ክፉዎቹና ምናምንቴዎቹ ሁሉ። እነዚህ ከእኛ ጋር አልመጡምና እየራሳቸው ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ይዘው ይሂዱ እንጂ ካስጣልነው ምርኮ ምንም አንሰጣቸውም አሉ።
23 ፤ ዳዊትም። ወንድሞቼ ሆይ፥ የጠበቀን በእኛም ላይ የመጣውን ጭፍራ በእጃችን አሳልፎ የሰጠን እግዚአብሔር በሰጠን ነገር እንዲህ አታድርጉ፤
24 ፤ ይህንስ ነገ ማን ይሰማችኋል? ነገር ግን የተዋጉትና ዕቃውን የጠበቁት እድል ፈንታ እኩል ይሆናል፥ አንድነት ይካፈላሉ አለ።
25 ፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይህን ለእስራኤል ሥርዓትና ፍርድ አደረገው።
26 ፤ ዳዊትም ወደ ጺቅላግ በመጣ ጊዜ ለዘመዶቹ ለይሁዳ ሽማግሌዎች። እነሆ ከእግዚአብሔር ጠላቶች ምርኮ በረከትን ተቀበሉ ብሎ ከምርኮው ሰደደላቸው።
27 ፤ በቤቴል ለነበሩ፥ በራሞት በደቡብ ለነበሩ
28 ፤ በየቲር ለነበሩ፥ በአሮዔር ለነበሩ፥ በሢፍሞት ለነበሩ፥ በኤሽትሞዓ ለነበሩ፥
29 ፤ በቀርሜሎስ ለነበሩ፥ በይረሕምኤላውያንና በቄናውያን ከተሞችም ለነበሩ፥
30 ፤ በሔርማ ለነበሩ፥ በቦራሣን ለነበሩ፥ በዓታክ ለነበሩ፥ በኬብሮን ለነበሩ፥
31 ፤ ዳዊትና ሰዎቹም በተመላለሱበት ስፍራ ለነበሩ ሰዎች ሁሉ ላከ።

1 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወደቁ።
2 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ።
3 ፤ ሰልፍም በሳኦል ላይ ጠነከረ፥ ቀስተኞችም አገኙት፤ እርሱም ከቀስተኞቹ የተነሣ እጅግ ተጨነቀ።
4 ፤ ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን። እነዚህ ቈላፋን መጥተው እንዳይወጉኝና እንዳይሳለቁብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና እንቢ አለ። ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ።
5 ፤ ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱ ደግሞ በሰይፉ ላይ ወደቀ፥ ከእርሱም ጋር ሞተ።
6 ፤ በዚያም ቀን ሳኦል ሦስቱም ልጆቹ ጋሻ ጃግሬውም ሰዎቹም ሁሉ በአንድ ላይ ሞቱ።
7 ፤ በሸለቆውም ማዶና በዮርዳኖስ ማዶ የነበሩ እስራኤላውያን የእስራኤል ሰዎች እንደ ሸሹ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቹን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው።
8 ፤ በማግሥቱም ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ በመጡ ጊዜ ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው።
9 ፤ የሳኦልንም ራስ ቈረጠው የጦር ዕቃውን ገፍፈው ለጣዖታቱ መቅደስ ለሕዝቡም የምስራች ይሰጥ ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ሁሉ ሰደዱ።
10 ፤ የጦር ዕቃውንም በአስታሮት መቅደስ ውስጥ አኖሩት፤ ሬሳውንም በቤትሳን ቅጥር ላይ አንጠለጠሉት።
11 ፤ ፍልስጥኤማውያንም በሳኦል ላይ ያደረጉትን የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች በሰሙ ጊዜ፥
12 ፤ ጀግኖች ሰዎች ሁሉ ተነሥተው ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ፥ የሳኦልንም ሬሳ የልጆቹንም ሬሳ ከቤትሳን ቅጥር ላይ አወረዱ፤ ወደ ኢያቢስም መጡ፥ በዚያም አቃጠሉት።
13 ፤ አጥንታቸውንም ወሰዱ በኢያቢስም ባለው በአጣጡ ዛፍ በታች ቀበሩት፥ ሰባት ቀንም ጾሙ።

Latest News

ilovejesus1.com

My name is Eden Fessehaye and i build ilovejesus1.com website for everyone to have access to the bible and audio bible as well.  There is Amharic, Tigrigna and English bible.  Also, the English bible can be translated to any languages for everyone to have access to...

Trust in Christ and receive Him as your Savior.

Christ is ready. “Here I am! I stand at the door and knock. If anyone hears my voice and opens the door, I will go in” (Revelation 3:20). Receive him now. “Yet to all who received him, to those who believed in his name, he gave the right to become children of God”...

You must repent and ask God for forgiveness.

“He who conceals his sins does not prosper, but whoever confesses and renounces them finds mercy” (Proverbs 28:13).  Forgiveness is promised. “If we confess our sins, he is faithful and just and will forgive us our sins and purify us from all unrighteousness” (1 John...

Jesus Christ died and rose again for our sins.

Jesus Christ died in our place. “But God demonstrates his own love for us in this: While we were still sinners, Christ died for us” (Romans 5:8). He is the way to new life. “Therefore, if anyone is in Christ, he is a new creation; the old has gone, the new has come!”...

Sin separates you from God

Everyone has sinned. “For all have sinned and fall short of the glory of God” (Romans 3:23). Sin brings death. “For the wages of sin is death” (Romans 6:23). “For it is by grace you have been saved, through faith and this not from yourselves, it is the gift of God-not...

Recognize that God loves you

“For God so loved the world that he gave his one and only Son, that whoever believes in him shall not perish but have eternal life” (John 3:16). He has new life for you. “I have come that they may have life, and have it to the full” (John 10:10).

The light of Jesus

Then Jesus again spoke to them, saying, “I am the Light of the world; he who follows Me will not walk in the darkness, but will have the Light of life.” (John 8:12, NASB) While I am in the world, I am the Light of the world.”...

Second Coming of Christ

Revelation 7:14 - “...they are the people who are coming out safely through the terrible tribulation. The blood of the Lamb has washed and made white their robes.” Revelation 19:7 - “They will be Christ's bride and will have...

ilovejesus1.com

My name is Eden Fessehaye and i build ilovejesus1.com website for everyone to have access to the bible and audio bible as well.  There is Amharic, Tigrigna and English bible.  Also, the English bible can be translated to any languages for everyone to have access to...

Trust in Christ and receive Him as your Savior.

Christ is ready. “Here I am! I stand at the door and knock. If anyone hears my voice and opens the door, I will go in” (Revelation 3:20). Receive him now. “Yet to all who received him, to those who believed in his name, he gave the right to become children of God”...

You must repent and ask God for forgiveness.

“He who conceals his sins does not prosper, but whoever confesses and renounces them finds mercy” (Proverbs 28:13).  Forgiveness is promised. “If we confess our sins, he is faithful and just and will forgive us our sins and purify us from all unrighteousness” (1 John...