ትንቢተ ሕዝቅኤል (Ezekiel)

እሱ ተከታታይ ጅማሬዎችን ያሳያል – የዓለም መጀመሪያ ፣ የሰው ልጅ እና እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የገባውን ቃል ኪዳን። የመጀመሪያው መጽሐፍ ዘፍጥረት በእግዚአብሔር ዓለም ፍጥረት ተከፈተ። የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ባለመታዘዙ የሰው ልጅ ብዛት ወደ ተለያዩ ብሔሮች እና ቋንቋዎች ሲከፋፈል ፍጹምው ዓለም በክፋት ውስጥ ይወድቃል።

መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ያንብቡ

ትንቢተ ሕዝቅኤል (Ezekiel)

1 ፤ በሠላሳኛው ዓመት በአራተኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን በኮቦር ወንዝ በምርኮኞች መካከል ሳለሁ ሰማያት ተከፈቱ፥ የእግዚአብሔርንም ራእይ አየሁ።
2 ፤ ንጉሡ ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት
3 ፤ ከወሩም በአምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በከለዳውያን አገር በኮቦር ወንዝ ወደ ቡዝ ልጅ ወደ ካህኑ ወደ ሕዝቅኤል መጣ። የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ በእኔ ላይ ሆነች፥
4 ፤ እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስና ታላቅ ደመና የሚበርቅም እሳት መጣ፥ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ፥ በመካከልም በእሳቱ ውስጥ እንደሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ ነበረ።
5 ፤ ከመካከልም የአራት እንስሶች አምሳያ ወጣ። መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፥ ሰውም ይመስሉ ነበር።
6 ፤ ለእያዳንዱም አራት አራት ፊት፥ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት።
7 ፤ እግሮቻቸውም ቀጥ ያሉ እግሮች ነበሩ፤ የእግራቸውም ኮቴ እንደ ጥጃ እግር ኮቴ ነበረ፤ እንደ ተወለወለ ናስም ይብለጨለጭ ነበር።
8 ፤ በክንፎቻቸውም በታች በእያራቱ ጐድናቸው እንደ ሰው እጅ ነበረ፤ ለአራቱም እንደዚህ ያሉ ፊትና ክንፍ ነበሩአቸው።
9 ፤ ክንፎቻቸው እርስ በእርሱ የተያያዘ ነበረ፤ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር፥ እያንዳንዱም ፊቱን አቅንቶ ይሄድ ነበር።
10 ፤ የፊታቸው አምሳያ እንደ ሰው ፊት ነበረ፥ ለአራቱም በስተ ቀኛቸው እንደ አንበሳ ፊት፥ በስተ ግራቸውም እንደ ላም ፊት ነበራቸው፥ ለአራቱም ደግሞ የንስር ፊት ነበራቸው።
11 ፤ ክንፋቸውም በላይ ተዘርግቶ ነበር፥ የእያንዳንዱም ሁለት ሁለት ክንፋቸው የተያያዙ ነበሩ፥ ሁለት ሁለቱም ገላቸውን ይከድኑ ነበር።
12 ፤ እያንዳንዱም ወደ ፊት ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር፤ መንፈስም ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር።
13 ፤ በእንስሶቹ መካከል እንደሚነድድ የእሳት ፍም ያለ ምስያ ነበረ፤ በእንስሶች መካከል ወዲህና ወዲያ የሚሄድ እንደ ፋና ያለ ምስያ ነበረ፤ ለእሳቱም ፀዳል ነበረው፥ ከእሳቱም መብረቅ ይወጣ ነበር።
14 ፤ እንስሶቹም እንደ መብረቅ ምስያ ይሮጡና ይመለሱ ነበር።
15 ፤ እንስሶችንም ስመለከት፥ እነሆ፥ በአራቱ እንስሶች አጠገብ በምድር ላይ አንድ አንድ መንኰራኵር አየሁ።
16 ፤ የመንኰራኵሩም መልክ እንደ ቢረሌ ነበረ፤ አራቱም አንድ አምሳያ ነበሩ፤ ሥራቸውም በመንኰራኵር ውስጥ እንዳለ መንኰራኵር ነበረ።
17 ፤ በእያራቱ ጐድናቸው ይሄዱ ነበር፤ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር።
18 ፤ ቁመታቸውም የረዘመና የሚያስፈራ ነበረ፤ የአራቱም ክበብ ዙሪያው በዓይን ተሞልቶ ነበር።
19 ፤ እንስሶቹም በሄዱ ጊዜ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ሄዱ። እንስሶቹም ከምድር ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ መንኰራኵሮቹ ከፍ ከፍ አሉ።
20 ፤ መንፈሱ ወደሚሄድበት ሁሉ እነርሱ ሄዱ፤ የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮቹ ውስጥ ነበረና መንኰራኵሮቹ በእነርሱ አጠገብ ከፍ ከፍ አሉ።
21 ፤ የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮቹ ውስጥ ነበረና እነዚያ ሲሄዱ እነዚህ ይሄዱ ነበር፤ እነዚያም ሲቆሙ እነዚህ ይቆሙ ነበር፤ እነዚያም ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር።
22 ፤ ከእንስሶች ራስ በላይ የሚያስፈራ በረዶ የሚመስል የጠፈር አምሳያ በራሳቸው ላይ ተዘርግቶ ነበር።
23 ፤ ከጠፈሩም በታች ክንፎቻቸው እርስ በርሳቸው ተቃንተው ነበር፤ ለእያንዳንዱም ገላውን የሚከድኑ ሁለት ሁለት ክንፎች ነበሩት።
24 ፤ ሲሄዱም የክንፎቻቸው ድምፅ እንደ ብዙ ውኃ ድምፅ፥ እንደ ሁሉን የሚችል የአምላክም ድምፅ፥ እንደ ታላቅም ሠራዊት ድምፅ ሆኖ ሰማሁ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።
25 ፤ በራሳቸውም ላይ ካለው ጠፈር በላይ ድምፅ ተሰማ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።
26 ፤ በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ።
27 ፤ ከወገቡም አምሳያ ወደ ላይ የሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ አየሁ፤ ከወገቡም አምሳያ ወደ ታች እንደ እሳት ምስያ አየሁ፤ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ።
28 ፤ በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ።

1 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ በእግርህ ቁም እኔም እናገርሃለሁ አለኝ።
2 ፤ በተናገረኝም ጊዜ መንፈስ ገባብኝ በእግሬም አቆመኝ፥ የሚናገረኝንም ሰማሁ።
3 ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ በእኔ ላይ ወደ ዐመፁ ወደ ዓመፀኞች ሰዎች ወደ እስራኤል ልጆች እልክሃለሁ። እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ ዐመፁብኝ።
4 ፤ እነርሱ ፊታቸው የተጨማተረ ልባቸውም የደነደነ ልጆች ናቸው። እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፤ አንተም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው።
5 ፤ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ነቢይ በመካከላቸው እንዳለ ያውቃሉ።
6 ፤ አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ኵርንችትና እሾህ ከአንተ ጋር ቢኖሩም፥ አንተም በጊንጦች መካከል ብትቀመጥም፥ አትፍራቸው፥ ቃላቸውንም አትፍራ፤ አንተ ቃላቸውን አትፍራ፥ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና።
7 ፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ቃሌን ትነግራቸዋለህ።
8 ፤ አንተ ግን፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የምነግርህን ስማ፤ እንደዚያ እንደ ዓመፀኛው ቤት ዓመፀኛ አትሁን፤ አፍህን ክፈት የምሰጥህንም ብላ።
9 ፤ ባየሁም ጊዜ፥ እነሆ፥ እጅ ወደ እኔ ተዘርግታ ነበር፤ እነሆም፥ የመጽሐፍ ጥቅልል ነበረባት።
10 ፤ በፊቴም ዘረጋው፥ በውስጥና በውጭም ተጽፎበት ነበር፤ ልቅሶና ኀዘን ዋይታም ተጽፎበት ነበር።

1 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ያገኘኸውን ብላ፤ ይህን መጽሐፍ ብላ፥ ሄደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር አለኝ።
2 ፤ አፌንም ከፈትሁ መጽሐፉንም አጐረሰኝ።
3 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ አፍህ ይብላ፥ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ። እኔም በላሁት፥ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ።
4 ፤ እንዲህም አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፥ ቃሌንም ተናገራቸው።
5 ፤ ወደ እስራኤል ቤት እንጂ ንግግራቸው ወደ ጠለቀው ቋንቋቸውም ወደማይታወቅ ሕዝብ አልተላክህምና፤
6 ፤ ንግግራቸው ወደ ጠለቀው ቋንቋቸውም ወደማይታወቅ ቃላቸውንም ታውቅ ዘንድ ወደማይቻልህ ሕዝብ አልላክሁህም። ወደ እነዚያስ ልኬህ ቢሆን ኖሮ በሰሙህ ነበር።
7 ፤ ነገር ግን የእስራኤል ቤት ሁሉ የጠነከረ ግምባርና የደነደነ ልብ አላቸውና፥ እኔንም መስማት እንቢ ብለዋልና የእስራኤል ቤት አንተን አይሰሙም።
8 ፤ እነሆ፥ ፊትህን በፊታቸው ግምባርህንም በግምባራቸው አጠንክሬአለሁ።
9 ፤ ከቡላድ ድንጋይ ይልቅ እንዳለ አልማዝ ግምባርህን አጠንክሬአለሁ፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ቢሆኑ አትፍራቸው፤ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ።
10 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ የነገርሁህን ቃሌን ሁሉ በልብህ ተቀበል በጆሮህም ስማ።
11 ፤ ተነሥተህም ወደ ተማረኩ ወደ ወገንህ ልጆች ሂድ፤ እነርሱም ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው አለኝ።
12 ፤ መንፈስም አነሣኝ፥ በኋላዬም። የእግዚአብሔር ክብር ከቦታው ይባረክ የሚል የጽኑ ንውጥውጥታ ድምፅ ሰማሁ።
13 ፤ የአራቱም እንስሳ ክንፎች እርስ በርሳቸው ሲማቱ፥ በአጠገባቸውም የመንኰራኵሮችን ድምፅ፥ የጽኑውንም ንውጥውጥታ ድምፅ ሰማሁ።
14 ፤ መንፈስ አንሥቶ አስወገደኝ፥ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ሙቀት ሄድሁ፥ የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ በርትታ ነበር።
15 ፤ በቴልአቢብም ወዳሉ በኮቦርም ወንዝ አጠገብ ወደ ተቀመጡ ምርኮኞች መጣሁ፥ በተቀመጡበትም ቦታ ተቀመጥሁ፤ በዚያም ሰባት ቀን በድንጋጤ በመካከላቸው ተቀመጥሁ።
16 ፤ ከሰባቱም ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
17 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ የአፌን ቃል ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው።
18 ፤ እኔ ኃጢአተኛውን። በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ አንተም ባታስጠነቅቀው ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኃጢአተኛው አስጠንቅቀህ ባትነግረው፥ ያ ኃጢአተኛ በኃጢአት ይሞታል፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።
19 ፤ ነገር ግን አንተ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቅ እርሱም ከኃጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል፥ አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል።
20 ፤ ደግሞ ጻድቁ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአት በሠራ ጊዜ እኔ በፊቱም ዕንቅፋትን ሳደርግ፥ እርሱ ይሞታል፤ አንተም አላስጠነቀቅኸውምና በኃጢአቱ ይሞታል ያደረጋትም ጽድቅ ነገር አትታሰብለትም፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።
21 ፤ ነገር ግን ኃጢአት እንዳይሠራ ጻድቁን ብታስጠነቅቅ እርሱም ኃጢአት ባይሠራ፥ ተጠንቅቆአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፤ አንተም ነፍስህን አድነሃል።
22 ፤ በዚያም የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ እርሱም። ተነሥተህ ወደ ቈላው ሂድ በዚያም እናገርሃለሁ አለኝ።
23 ፤ እኔም ተነሥቼ ወደ ቈላው ሄድሁ፤ እነሆም፥ በኮቦር ወንዝ እንዳየሁት ክብር ያለ የእግዚአብሔር ክብር በዚያ ቆሞ ነበር፥ በግምባሬም ተደፋሁ።
24 ፤ መንፈስም ገባብኝ በእግሬም አቆመኝ፥ ተናገረኝም እንዲህም አለኝ። ሂድ፥ ገብተህ ቤትህን ዝጋ።
25 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ ገመድ ያደርጉብሃል ያስሩህማል፥ አንተም በመካከላቸው አትወጣም፤
26 ፤ እኔም ምላስህን ከትናጋህ ጋር አጣብቃታለሁ አንተም ዲዳ ትሆናለህ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና የሚዘልፍ ሰው አትሆንባቸውም።
27 ፤ ነገር ግን በተናገርሁህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና አንተ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሚሰማ ይስማ፥ የማይሰማም አይስማ ትላቸዋለህ።

1 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጡብን ወስደህ በፊትህ አኑራት የኢየሩሳሌምንም ከተማ ስዕል ሳልባት ክበባት፥
2 ፤ ምሽግም ሥራባት፥ አፈርም ደልድልባት፥ ሰፈርም አቁምባት፥ በዙሪያዋም የሚያፈርስ ግንድ አድርግባት።
3 ፤ የብረት ምጣድም ወስደህ በአንተና በከተማይቱ መካከል ለብረት ቅጥር አድርገው፥ ፊትህንም ወደ እርስዋ አቅና፥ የተከበበችም ትሆናለች አንተም ትከብባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል።
4 ፤ አንተም በግራ ጐድንህ ተኛ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት አኑርባት፤ በምትተኛበትም ቀን ቍጥር ኃጢአታቸውን ትሸከማለህ።
5 ፤ እኔም የኃጢአታቸውን ዓመታት ለአንተ የቀን ቍጥር እንዲሆንልህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ሰጥቼሃለሁ፤ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ።
6 ፤ እነዚህንም በፈጸምህ ጊዜ በቀኝ ጐድንህ ትተኛለህ፥ የይሁዳንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ፤ አንድን ዓመት አንድ ቀን አድርጌ አርባ ቀን ሰጥቼሃለሁ።
7 ፤ ክንድህን ዕራቁቱን አድርገህ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም ክቡ ታቀናለህ፥ ትንቢትም ትናገርባታለህ።
8 ፤ እነሆም፥ ገመድ አደርግብሃለሁ፥ የምትከበብበትንም ወራት እስክትፈጽም ድረስ ከጐድን ጐድንህ አትገላበጥም።
9 ፤ አንተም ስንዴንና ገብስን ባቄላንና ምስርን ጤፍንና አጃን ወደ አንተ ውሰድ፥ በአንድ ዕቃም ውስጥ አድርገህ እንጀራ ጋግር፤ በጐድንህ እንደ ተኛህበት ቀን ቍጥር ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ትበላዋለህ።
10 ፤ የምትበላውም በሚዛን በየቀኑ ሀያ ሀያ ሰቅል ይሁን፥ በየጊዜው ትበላዋለህ።
11 ፤ ውኃውንም በልክ የኢን መስፈሪያ ከስድስት እጅ አንድን እጅ ትጠጣለህ፥ በየጊዜው ትጠጣዋለህ።
12 ፤ እንደ ገብስ እንጐቻም አድርገህ ትበላዋለህ፥ ከሰውም በሚወጣ ፋንድያ በፊታቸው ትጋግረዋለሁ።
13 ፤ እግዚአብሔርም። እንዲሁ የእስራኤል ልጆች እነርሱን በምበትንባቸው በአሕዛብ መካከል ርኩስ እንጀራቸውን ይበላሉ አለ።
14 ፤ እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነሆ፥ ሰውነቴ አልረከሰችም፤ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ጥንብና አውሬ የሰበረውን ከቶ አልበላሁም፥ ርኩስም ሥጋ በአፌ ውስጥ አልገባም አልሁ።
15 ፤ እርሱም። እነሆ፥ በሰው ፋንድያ ፋንታ ኩበት ሰጥቼሃለሁ በእርሱም እንጀራህን ትጋግራለህ አለኝ።
16 ፤ ደግሞም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ የኢየሩሳሌምን እንጀራ በትር እሰብራለሁ፥ እየፈሩም እንጀራን በሚዛን ይበላሉ፥ እየደነገጡም ውኃን በልክ ይጠጣሉ፤
17 ፤ ይህም እንጀራንና ውኃን እንዲያጡ፥ እርስ በርሳቸውም እንዲደነቁ፥ በኃጢአታቸውም እንዲሰለስሉ ነው።

1 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የተሳለን ጐራዴ ውሰድ፥ እንደ ጢም መላጫ ወደ አንተ ትወስደዋለህ፥ ራስህንና ጢምህንም ትላጭበታለህ፤ ሚዛንንም ውሰድ ጠጕሩንም ትከፋፍላለህ።
2 ፤ የመከበብም ወራት በተፈጸመ ጊዜ በከተማይቱ መካከል ሢሶውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ሢሶውንም ወስደህ ዙሪያውን በጐራዴ ትመታለህ፥ ሢሶውንም ወደ ነፋስ ትበትናለህ እኔም በኋላቸው ጐራዴ እመዝዛለሁ።
3 ፤ ከዚያም በጥቂቱ ውሰድ በመጐናጸፊያህም ጫፍ ቋጥራቸው።
4 ፤ ከእነርሱም ደግሞ ወስደህ በእሳት ውስጥ ትጥላለህ በእሳትም ታቃጥላቸዋለህ፤ ከዚያም በእስራኤል ቤት ሁሉ ላይ እሳት ትወጣለች።
5 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህች ኢየሩሳሌም ናት፤ በአሕዛብም መካከል አድርጌአታለሁ፥ አገሮችም በዙሪያዋ አሉ።
6 ፤ እርስዋም ከአሕዛብ ይልቅ ፍርዴን በኃጢአት ለወጠች በዙሪያዋም ካሉ አገሮች ሁሉ ይልቅ ትእዛዜን ተላለፈች፤ ፍርዴን ጥለዋልና፥ በትእዛዜም አልሄዱምና።
7 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዙሪያችሁ ላሉት አሕዛብ ሰበብ ሆናችኋልና፥ በትእዛዜም አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አልጠበቃችሁምና፥ በዙሪያችሁም እንዳሉ እንደ አሕዛብ ፍርድ እንኳ አላደረጋችሁምና
8 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እኔ ራሴ በአንቺ ላይ ነኝ፥ አሕዛብም እያዩ ፍርድን በመካከልሽ አደርጋለሁ።
9 ፤ ስለ ርኵሰትሽም ሁሉ ያልሠራሁትን እርሱንም የሚመስል ደግሞ የማልሠራውን ነገር እሠራብሻለሁ።
10 ፤ ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን ይበላሉ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፤ ፍርድንም አደርግብሻለሁ ከአንቺም የቀረውን ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ።
11 ፤ ስለዚህ፥ እኔ ሕያው ነኝና በእድፍሽና በርኵሰትሽ መቅደሴን ስላረከስሽ፥ ስለዚህ በእውነት እኔ አሳንስሻለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ዓይኔም አይራራም እኔም አላዝንም።
12 ፤ ከአንቺም ሢሶው በቸነፈር ይሞታል፥ በመካከልሽም በራብ ያልቃል፤ ሢሶውም በዙሪያሽ በሰይፍ ይወድቃል፤ ሢሶውንም ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ በኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ።
13 ፤ ቍጣዬም ይፈጸማል መዓቴንም እጨርሳለሁ እጽናናማለሁ፥ መዓቴንም በፈጸምሁባቸው ጊዜ እኔ እግዚአብሔር በቅንዓቴ እንደ ተናገርሁ ያውቃሉ።
14 ፤ በዙሪያሽም ባሉ በአሕዛብ መካከል በሚያልፉም ሁሉ ፊት ባድማና መሰደቢያ አደርግሻለሁ።
15 ፤ በቍጣና በመዓት፥ በመዓትም ዘለፋ ፍርድን ባደረግሁብሽ ጊዜ በዙሪያሽ ላሉ አሕዛብ መሰደቢያና መተረቻ፥ ተግሣጽና መደነቂያ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።
16 ፤ ለማጥፋትም የሆነውን፥ አጠፋችሁም ዘንድ የምሰድደውን የራብ ፍላጻ በላያችሁ በሰደድሁ ጊዜ፥ ራብን እጨምርባችኋለሁ፥ የእንጀራችሁንም በትር እሰብራለሁ።
17 ፤ ራብንና ክፉዎችን አራዊት እሰድድባችኋለሁ፥ ልጆቻችሁንም ያጠፋሉ፤ ቸነፈርና ደምም በአንቺ ዘንድ ያልፋሉ፤ ሰይፍንም አመጣብሻለሁ። እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አቅና ትንቢትም ተናገርባቸው።
3 ፤ እንዲህም በል። የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኮረብቶች ለምንጮችና ለሸለቆች እንዲህ ይላል። እኔ፥ እነሆ፥ እኔ ሰይፍን አመጣባችኋለሁ የኮረብታው መስገጃዎቻችሁንም አጠፋለሁ።
4 ፤ መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ፥ የፀሐይም ምስሎቻችሁ ይሰበራሉ፤ ተወግተውም የሞቱትን ሰዎቻችሁን በጣዖቶቻችሁ ፊት እጥላለሁ።
5 ፤ የእስራኤልንም ልጆች ሬሳዎች በጣዖቶቻቸው ፊት አኖራለሁ፥ አጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ።
6 ፤ በምትኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ከተሞቹ ይፈርሳሉ፥ የኮረብታው መስገጃዎችም ሁሉ ውድማ ይሆናሉ፥ መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ ባድማም ይሆናሉ፥ ጣዖቶቻችሁም ይሰበራሉ ያልቃሉም፥ የፀሐይም ምስሎቻችሁ ይቈረጣሉ፥ ሥራችሁም ይሻራል።
7 ፤ ተወግተውም የሞቱት በመካከላችሁ ይወድቃሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
8 ፤ ነገር ግን በአገሮች በተበተናችሁ ጊዜ ከሰይፍ ያመለጡትን ቅሬታ በአሕዛብ መካከል አስቀርላችኋለሁ።
9 ፤ ከእናንተም የዳኑት ከእኔ በራቀው በአመንዝራ ልባቸውና ጣዖቶቻቸውን በተከተሉ በአመንዝራ ዓይኖቻቸው የተሰበርሁትን እኔን ወደ እነርሱ በተማረኩት አሕዛብ መካከል ሆነው ያስቡኛል፤ በርኵሰታቸውም ሁሉ ስላደረጉት ክፋት ራሳቸውን ይጸየፋሉ።
10 ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ይህን ክፉ ነገር አደርግባቸው ዘንድ መናገሬ በከንቱ አይደለም።
11 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእጅህ አጨብጭብ በእግርህም አሸብሽብ እንዲህም በል። በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይወድቃሉና ስለ እስራኤል ቤት ስለ አስጸያፊ ሥራዎቻቸው ሁሉ ወዮ!
12 ፤ በሩቅ ያለው በቸነፈር ይሞታል፥ በቅርብም ያለው በሰይፍ ይወድቃል፥ የቀረውና የዳነውም በራብ ይሞታል፤ እንዲሁ መዓቴን እፈጽምባቸዋለሁ።
13 ፤ ተወግተውም የሞቱ ሰዎቻቸው በጣዖቶቻቸው መካከልና በመሠዊያዎቻቸው ዙሪያ፥ ለጣዖቶቻቸው ጣፋጭ ሽታ ባቀረቡበት ስፍራ፥ ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ በተራሮችም ራስ ሁሉ ላይ፥ ከለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ቅጠሉም ከበዛ ከአድባር ዛፍ ሁሉ በታች በሆኑ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
14 ፤ እጄንም እዘረጋባቸዋለሁ፥ በሚኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ምድሪቱን ከዴብላታ ምድረ በዳ ይልቅ ውድማና በረሃ አደርጋታለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል። ፍጻሜ፥ በምድሪቱ በአራቱ ማዕዘን ላይ ፍጻሜ ደርሶአል።
3 ፤ አሁን ፍጻሜ በአንቺ ላይ ነው፥ ቍጣዬንም እሰድድብሻለሁ፥ እንደ መንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፥ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ።
4 ፤ ዓይኔም አይራራልሽም እኔም አላዝንም፤ መንገድሽንም አመጣብሻለሁ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ይሆናል፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
5 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ክፉ ነገር፥ አንድ ክፉ ነገር፥ እነሆ፥ ይመጣል።
6 ፤ ፍጻሜ መጥቶአል፥ ፍጻሜ መጥቶአል፥ ነቅቶብሻል፤ እነሆ፥ ደርሶአል።
7 ፤ በምድር የምትቀመጥ ሆይ፥ ተራህ ደርሶአል፥ ጊዜ መጥቶአል፥ ቀን ቀርቦአል፤ የሽብር ቀን ነው እንጂ በተራራ ላይ ያለ እልልታ አይደለም።
8 ፤ አሁን በቅርብ መዓቴን አፈስስብሻለሁ፥ ቍጣዬንም እፈጽምብሻለሁ፥ እንደ መንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፥ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ።
9 ፤ ዓይኔም አይራራም እኔም አላዝንም፤ እንደ መንገድሽም መጠን አመጣብሻለሁ፥ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ይሆናል፥ እኔም እግዚአብሔር የምቀሥፍ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
10 ፤ እነሆ ቀኑ፥ እነሆ፥ መጥቶአል፤ ተራህ ወጥቶአል፤ ብትር አብቦአል፥ ትዕቢትም አጅብጅፎአል።
11 ፤ ግፍ ወደ ክፋት ብትር ተነስቶአል፤ ከእነርሱና ከብዛታቸው ከሀብታቸውም ምንም አይቀርም፥ የሚያለቅስላቸውም የለም።
12 ፤ ጊዜው መጥቶአል፥ ቀኑ ቀርቦአል፤ መዓት በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና የሚገዛ ደስ አይበለው የሚሸጥም አያልቅስ።
13 ፤ የሚሸጥ ወደሸጠው ነገር አይመለስም፥ ሰውም በነፍሱ ኃጢአት አይጸናም።
14 ፤ መለከቱን ነፍተዋል ሁሉንም አዘጋጅተዋል፤ ነገር ግን መዓቴ በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና ወደ ሰልፍ የሚሄድ የለም።
15 ፤ ሰይፍ በውጭ ቸነፈርና ራብ በውስጥ አለ፤ በሜዳ ያለው በሰይፍ ይሞታል፥ በከተማም ያለውን ቸነፈርና ራብ ይፈጁታል።
16 ፤ ከእነርሱም የሚሸሹ ይድናሉ በተራራም ላይ ይሆናሉ፤ እኔም በኃጢአታቸው ሁሉን እገድላለሁ።
17 ፤ እጅ ሁሉ ትደክማለች ጕልበትም ሁሉ እንደ ውኃ ትቀልጣለች።
18 ፤ ማቅም ይለብሳሉ ድንጋጤም ይሸፍናቸዋል፤ በፊትም ሁሉ ላይ እፈረት ይሆናል፥ ራሳቸውንም ሁሉ ይነጩታል።
19 ፤ ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ ወርቃቸውም እንደ ጕድፍ ይሆናል፤ በእግዚአብሔር መዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ያድናቸው ዘንድ አይችልም። እርሱ የኃጢአታቸው ዕንቅፋት ሆኖአልና ሰውነታቸውን አያጠግቡም ሆዳቸውንም አይሞሉም።
20 ፤ የክብሩንም ጌጥ ወደ ትዕቢት ለወጡ፥ የርኵስነታቸውንም ምስሎች አደረጉባት፤ ስለዚህ እኔ በእነርሱ ዘንድ ርኩስ አድርጌአታለሁ።
21 ፤ በባዕድም እጅ ለንጥቂያ፥ በምድር ኃጢአተኞችም እጅ ለብዝበዛ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እነርሱም ያረክሱአታል።
22 ፤ ፊቴን ከእነርሱ ዘንድ እመልሳለሁ፥ ምሥጢሬንም ያረክሳሉ፤ ወንበዴዎችም ይገቡባታል ያረክሱአትማል።
23 ፤ ምድር ደም ባመጣው በደል፥ ከተማም በግፍ ተሞልታለችና ሰንሰለት ሥራ።
24 ፤ ከአሕዛብ ዘንድ ከሁሉ የሚከፉትን አመጣለሁ ቤቶቻቸውንም ይወርሳሉ፤ የኃያላንንም ትዕቢት አጠፋለሁ፥ መቅደሶቻቸውም ይረክሳሉ።
25 ፤ ጥፋት መጥቶአል፤ ሰላምም ይሻሉ እርሱም አይገኝም።
26 ፤ ድንጋጤ በድንጋጤ ላይ ይመጣል፥ ወሬም ወሬውን ይከተላል፥ ከነቢዩም ዘንድ ራዕይን ይሻሉ፤ ከካህኑም ዘንድ ትምህርት፥ ከሽማግሌዎችም ዘንድ ምክር ይጠፋል።
27 ፤ ንጉሡም ያለቅሳል፥ አለቃም ውርደትን ይለብሳል፥ የምድርም ሕዝብ እጅ ትንቀጠቀጣለች፤ እንደ መንገዳቸውም መጠን አደርግባቸዋለሁ፥ በፍርዳቸውም መጠን እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

1 ፤ በስድስተኛውም ዓመት በስድስተኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን በቤቴ ተቀምጬ ሳለሁ የይሁዳም ሽማግሌዎች በፊቴ ተቀምጠው ሳሉ፥ በዚያ የጌታ የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ወደቀች።
2 ፤ እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ እንደ እሳት የሚመስል አምሳያ ነበረ፤ ከወገቡም ምሳሌ ወደ ታች እሳት ነበረ፥ ከወገቡም ወደ ላይ እንደ ፀዳል ምሳሌ፥ እንደሚብለጨለጭም የወርቅ ምሳሌ ነበረ።
3 ፤ እጅ መሳይንም ዘረጋ በራስ ጠጕሬም ያዘኝ፤ መንፈስም በምድርና በሰማይ መካከል አነሣኝ፥ በእግዚአብሔርም ራእይ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ሰሜን ወደሚመለከተው ወደ ውስጠኛው አደባባይ በር መግቢያ አመጣኝ፤ በዚያም ቅንዓት የሚያነሣሣ የቅንዓት ጣዖት ተተክሎ ነበር።
4 ፤ እነሆም፥ በቈላው እንዳየሁት ራእይ የእስራኤል አምላክ ክብር በዚያ ነበረ።
5 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ዓይንህን ወደ ሰሜን መንገድ አንሣ አለኝ። ዓይኔንም ወደ ሰሜን መንገድ አነሣሁ፤ እነሆም፥ በመሠዊያው በር በሰሜን በኩል በመግቢያው ይህ የቅንዓት ጣዖት ነበረ።
6 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ የሚያደርጉትን፥ ከመቅደሴ ያርቁኝ ዘንድ የእስራኤል ቤት በዚህ የሚያደርጉትን ታላቁን ርኵሰት ታያለህን? ደግሞም ተመልሰህ ከዚህ የበለጠ ታላቅ ርኵሰት ታያለህ አለኝ።
7 ፤ ወደ አደባባዩም መግቢያ አመጣኝ፤ ባየሁም ጊዜ፥ እነሆ፥ በግንቡ ውስጥ ፉካ ነበረ።
8 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ግንቡን ንደለው አለኝ፤ ግንቡንም በነደልሁት ጊዜ መዝጊያ አገኘሁ።
9 ፤ እርሱም። ግባ፥ በዚህም የሚያደርጉትን ክፉውን ርኵሰት እይ አለኝ።
10 ፤ እኔም ገባሁና እነሆ፥ በግንቡ ዙሪያ ላይ የተንቀሳቃሾችና የርኩሳን አራዊት ምሳሌ የእስራኤልንም ቤት ጣዖታት ሁሉ ተስለው አየሁ።
11 ፤ በፊታቸውም ከእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች ሰባ ሰዎች ቆመው ነበር፥ በመካከላቸውም የሳፋን ልጅ ያእዛንያ ቆሞ ነበር፥ ሰውም ሁሉ እያንዳንዱ በእጁ ጥናውን ይዞ ነበር፥ የዕጣኑም ጢስ ሽቱ ይወጣ ነበር።
12 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች በጨለማ እያንዳንዱ በስዕሉ ቤት የሚያደርጉትን አይተሃልን? እነርሱ። እግዚአብሔር አያየንም፤ እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአታል ይላሉና አለኝ።
13 ፤ እርሱም። ደግሞ ተመልሰህ ከዚህ የበለጠውን የሚያደርጉትን ታላቅ ርኵሰት ታያለህ አለኝ።
14 ፤ ወደ ሰሜንም ወደሚመለከተው ወደ እግዚአብሔር ቤት በር መግቢያ አመጣኝ፤ እነሆም፥ ሴቶች ለተሙዝ እያለቀሱ በዚያ ተቀምጠው ነበር።
15 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ይህን አይተሃልን? ደግሞ ተመልሰህ ከዚህ የበለጠ ርኵሰት ታያለህ አለኝ።
16 ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፥ እነሆም፥ በእግዚአብሔር መቅደስ መግቢያ ፊት በወለሉና በመሠዊያው መካከል ሀያ አምስት የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ ጀርባቸውም ወደ እግዚአብሔር መቅደስ ፊታቸውም ወደ ምሥራቅ ነበረ፤ እነርሱም ወደ ምሥራቅ ለፀሐይ ይሰግዱ ነበር።
17 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ይህን አይተሃልን? በዚህ የሚያደርጉትን ይህን ርኵሰት ያደርጉ ዘንድ ለይሁዳ ቤት ጥቂት ነገር ነውን? ምድሪቱን በግፍ ሞልተዋታል ያስቈጡኝም ዘንድ ተመልሰዋል፤ እነሆም፥ ቅርንጫፉን ወደ አፍንጫው አቅርበዋል።
18 ፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ በመዓት እሠራለሁ፤ ዓይኔ አይራራም እኔም አላዝንም፤ ወደ ጆሮዬም በታላቅ ድምፅ ቢጮኹ አልሰማቸውም አለኝ።

1 ፤ እርሱም። እያንዳንዳቸው የሚያጠፋ መሣሪያን በእጃቸው ይዘው ከተማይቱን የሚቀሥፉ ይቅረቡ ብሎ በታላቅ ድምፅ በጆሮዬ ጮኸ።
2 ፤ እነሆም፥ እያንዳንዳቸው አጥፊውን መሣሪያ በእጃቸው ይዘው ስድስት ሰዎች ወደ ሰሜን ከሚመለከተው ከላይኛው በር መንገድ መጡ፤ በመካከላቸውም የበፍታ ልብስ የለበሰ የጸሐፊም ቀለም ቀንድ በወገቡ የያዘ አንድ ሰው ነበረ። እነርሱም ገብተው በናሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ።
3 ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር በበላዩ ከነበረበት ኪሩብ ተነሥቶ ወደ ቤቱ መድረክ ሄዶ ነበር፤ በፍታም የለበሰውን የጸሐፊውንም ቀለም ቀንድ በወገቡ የያዘውን ሰው ጠራ።
4 ፤ እግዚአብሔርም። በከተማይቱ በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ፥ በመካከልዋም ስለ ተሠራው ርኵሰት ሁሉ በሚያለቅሱና በሚተክዙ ሰዎች ግምባር ላይ ምልክት ጻፍ አለው።
5 ፤ እኔም እየሰማሁ ለሌሎቹ። እርሱን ተከትላችሁ በከተማይቱ መካከል እለፉ ግደሉም፤ ዓይናችሁ አይራራ አትዘኑም፤
6 ፤ ሽማግሌውንና ጐበዙን ቈንጆይቱንም ሕፃናቶቹንና ሴቶቹን ፈጽማችሁ ግደሉ፤ ነገር ግን ምልክቱ ወዳለበት ሰው ሁሉ አትቅረቡ፤ በመቅደሴም ጀምሩ አላቸው። በቤቱም አንጻር ባሉ ሽማግሌዎች ጀመሩ።
7 ፤ እርሱም። ቤቱን አርክሱ፥ በተገደሉትም ሰዎች አደባባዮችን ሙሉ፤ ውጡ አላቸው። እነርሱም ወጥተው በከተማይቱ ገደሉ።
8 ፤ ሲገድሉም እኔ ብቻዬን ቀርቼ ሳለሁ በግምባሬ ተደፍቼ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! መዓትህን በኢየሩሳሌም ላይ ስታፈስስ የእስራኤልን ቅሬታ ሁሉ ታጠፋለህን? ብዬ ጮኽሁ።
9 ፤ እርሱም። የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ኃጢአት እጅግ በዝቶአል ምድሪቱም ደም፥ ከተማይቱም ዓመፅን ተሞልታለች፤ እነርሱም። እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአታል እግዚአብሔርም አያይም ብለዋል።
10 ፤ እኔም ደግሞ በዓይኔ አልራራም አላዝንምም፥ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ አለኝ።
11 ፤ እነሆም፥ በፍታ የለበሰው የቀለም ቀንድም በወገቡ የያዘው ሰው። ያዘዝኸኝን አድርጌአለሁ ብሎ በቃሉ መለሰ።

1 ፤ እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ በኪሩቤል ራስ ላይ ባለው ጠፈር በላያቸው እንደ ሰንፔር ድንጋይ ያለ እንደ ዙፋን የሚመስል መልክ ተገለጠ።
2 ፤ በፍታም የለበሰውን ሰው። በመንኰራኵሮች መካከል ከኪሩብ በታች ግባ፥ ከኪሩቤልም መካከል ካለው እሳት ፍም እጆችህን ሙላ በከተማይቱም ላይ በትናት ብሎ ተናገረው። እኔም እያየሁ ገባ።
3 ፤ ሰውዬውም ሲገባ ኪሩቤል በቤቱ ቀኝ በኩል ቆመው ነበር፥ ደመናውም ውስጠኛውን አደባባይ ሞላ።
4 ፤ የእግዚአብሔር ክብርም ከኪሩቤል ወጥቶ በቤቱ መድረክ ላይ ቆመ፤ ቤቱም በደመናው ተሞላ፥ አደባባዩም በእግዚአብሔር ክብር ፀዳል ተሞላ።
5 ፤ ሁሉንም የሚችል አምላክ እንደሚናገረው ያለ ጽምፅ እንዲሁ የኪሩቤል ክንፎች ድምፅ እስከ ውጭው አደባባይ ድረስ ተሰማ።
6 ፤ በፍታም የለበሰውን ሰው። ከመንኰራኵሮች ከኪሩቤል መካከል እሳት ውሰድ ብሎ ባዘዘው ጊዜ እርሱ ገብቶ በአንድ መንኰራኵር አጠገብ ቆመ።
7 ፤ ኪሩብም ከኪሩቤል መካከል እጁን በኪሩቤል መካከል ወዳለው እሳት ዘርግቶ ከዚያ ወሰደ፥ በፍታም በለበሰው ሰው እጅ አኖረው፤ እርሱም ይዞ ወጣ።
8 ፤ በኪሩቤልም ከክንፎቻቸው በታች የሰው እጅን መሳይ ታየ።
9 ፤ እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ በኪሩቤል አጠገብ አራት መንኰራኵሮች ነበሩ፤ አንዱ መንኰራኵር በአንዱ ኪሩብ፥ አንዱ መንኰራኵር በአንዱ ኪሩብ አጠገብ ነበረ። የመንኰራኵሮቹም መልክ እንደ ቢረሌ ድንጋይ ነበረ።
10 የአራቱም መልክ አንድ ይመስል ነበር፥ መልካቸውም በመንኰራኵር ውስጥ እንዳለ መንኰራኵር ነበረ።
11 ፤ ሲሄዱም በአራቱ ጐድናቸው ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር፥ ራሱ ወደምታመለክትበት ስፍራ ወደዚያ ይከተሉ ነበር፤ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር።
12 ፤ ገላቸውም ሁሉ ጀርባቸውም እጃቸውም ክንፋቸውም መንኰራኵሮቹም፥ ለአራቱ የነበሩ መንኰራኵሮች፥ በዙሪያቸው ዓይኖች ተሞልተው ነበር።
13 ፤ መንኰራኵሮችም እኔ እየሰማሁ ጌልጌል ተብለው ተጠሩ።
14 ፤ ለእያንዳንዱም አራት አራት ፊት ነበሩት፤ አንደኛው ፊት የኪሩብ ፊት፥ ሁለተኛውም የሰው ፊት፥ ሦስተኛው የአንበሳ ፊት፥ አራተኛውም የንስር ፊት ነበረ።
15 ፤ ኪሩቤልም ከፍ ከፍ አሉ፤ ይህ በኮቦር ወንዝ ያየሁት እንስሳ ነው።
16 ፤ ኪሩቤልም ሲሄዱ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ይሄዱ ነበር፤ ኪሩቤልም ከምድር ከፍ ከፍ ይሉ ዘንድ ክንፎቻቸውን ሲዘረጉ መንኰራኵሮች ደግሞ ከአጠገባቸው ፈቀቅ አይሉም ነበር።
17 ፤ ሕይወት ያላቸው የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮች ውስጥ ነበረና እነዚህ ሲቆሙ እነዚያ ይቆሙ ነበር፥ እነዚህም ከፍ ከፍ ሲሉ እነዚያ ከእነርሱ ጋር ከፍ ከፍ ይሉ ነበር።
18 ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ከቤቱ መድረክ ላይ ወጥቶ በኪሩቤል ላይ ቆመ።
19 ፤ ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ እኔም እያየሁ ከምድር ከፍ ከፍ አሉ፤ በወጡም ጊዜ መንኰራኵሮች በአጠገባቸው ነበሩ፤ በእግዚአብሔርም ቤት በምሥራቁ በር መግቢያ ቆሙ፥ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበረ።
20 ፤ ይህ በኮበር ወንዝ ከእስራኤል አምላክ በታች ያየሁት እንስሳ ነው፥ ኪሩቤልም እንደ ነበሩ አስተዋልሁ።
21 ፤ ለእያንዳንዱ አራት አራት ፊት፥ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት፥ የሰውም እጅ አምሳያ ከክንፎቻቸው በታች ነበረ። 
22 ፤ ፊቶቻቸውም በኮቦር ወንዝ ያየኋቸውን ፊቶች ይመስሉ ነበር፤ እነርሱና መልካቸውም እንዲሁ ነበረ፤ እያንዳንዱም አቅንቶ ወደ ፊት ይሄድ ነበር።

1 ፤ መንፈስም አነሣኝ፤ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደሚመለከት ወደ እግዚአብሔር ቤትም ወደ ምሥራቁ በር አመጣኝ። እነሆም፥ በበሩ መግቢያ ሀያ አምስት ሰዎች ነበሩ፥ በመካከላቸውም የሕዝቡን አለቆች የዓዙርን ልጅ ያእዛንያንና የበናያስ ልጅ ፈላጥያን አየሁ።
2 ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ክፋትን የሚያስቡ በዚህችም ከተማ ክፉን ምክር የሚመክሩ ሰዎች ናቸው።
3 ፤ እነርሱም። በውኑ ቤቶችን የምንሠራበት ዘመን የቀረበ አይደለምን? ይህች ከተማ ድስት እኛም ሥጋ ነን ብለዋል።
4 ፤ ስለዚህ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገርባቸው፤ ትንቢት ተናገር።
5 ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ ወደቀብኝ እንዲህም አለኝ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ተናገር። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ይህን ነገር ተናግራችኋል፥ እኔም የልባችሁን አሳብ አውቃለሁ።
6 ፤ በዚህች ከተማ ውስጥ ግዳዮቻችሁን አብዝታችኋል በጎዳናዎችዋም ግዳዮችን ሞልታችኋል።
7 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመካከልዋ ያኖራችኋቸው ግዳዮቻችሁ እነርሱ ሥጋው ናቸው፥ ይህችም ከተማ ድስቱ ናት፤ እናንተን ግን ከመካከልዋ አወጣችኋለሁ።
8 ፤ ሰይፍን ፈርታችኋል እኔም ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
9 ፤ ከመካከልዋም አወጣችኋለሁ፥ በእንግዶችም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፥ በላያችሁም ፍርድ አደርጋለሁ።
10 ፤ በሰይፍ ትወድቃላችሁ በእስራኤልም ድንበር እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
11 ፤ ይህች ከተማ ድስት አትሆንላችሁም እናንተም በመካከልዋ ሥጋ አትሆኑም፥ እኔም በእስራኤል ድንበር እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
12 ፤ በትእዛዜ አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አላደረጋችሁምና፤ በዙሪያችሁም እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ሕግ አድርጋችኋል።
13 ፤ ትንቢትም በተናገርሁ ጊዜ የበናያስ ልጅ ፈላጥያ ሞተ፤ እኔም በግምባሬ ተደፍቼ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! በውኑ የእስራኤልን ቅሬታ ፈጽመህ ታጠፋለህን? ብዬ በታላቅ ድምፅ ጮኽሁ።
14 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
15 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ። ከእግዚአብሔር ዘንድ ራቁ፤ ይህች ምድር ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች የሚሉአቸው ወንድሞችህና ዘመዶችህ የወገኖችህም ሰዎች ሁሉ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ናቸው።
16 ፤ ስለዚህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ወደ አሕዛብ አርቄአቸዋለሁ፥ ወደ አገሮችም በትኛቸዋለሁ፤ ይሁን እንጂ፥ በመጡባቸው አገሮች በእነዚያ ትንሽ መቅደስ እሆናቸዋለሁ በል።
17 ፤ ስለዚህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከአሕዛብ ዘንድ አከማቻችኋለሁ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች እሰበስባችኋለሁ፥ የእስራኤልንም ምድር እሰጣችኋለሁ።
18 ፤ ወደዚያም ይመጣሉ፥ ጸያፉንና ርኩሱንም ነገር ሁሉ ከእርስዋ ያወጣሉ።
19፤20 ፤ በትእዛዜም ይሄዱ ዘንድ ፍርዴንም ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፥ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ እሰጣለሁ፥ ከሥጋቸውም ውስጥ የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
21 ፤ ልባቸውም ጸያፍንና ርኩስን ነገር በሚከተል በእነርሱ ራስ ላይ መንገዳቸውን እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
22 ፤ ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፥ መንኰራኵሮችም በአጠገባቸው ነበሩ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበረ።
23 ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ከከተማይቱ ውስጥ ተነሥቶ በከተማይቱ ምሥራቅ በኩል ባለው ተራራ ላይ ቆመ።
24 ፤ መንፈስም አነሣኝ፥ በእግዚአብሔርም መንፈስ በራእይ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ ምርኮኞቹ አመጣኝ። ያየሁትም ራእይ ከእኔ ወጥቶ ተለየ። 
25 ፤ እግዚአብሔርም ያሳየኝን ነገር ሁሉ ለምርኮኞች ተናገርሁ።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በዓመፀኛ ቤት መካከል ተቀምጠሃል፤ ያዩ ዘንድ ዓይን አላቸው እነርሱም አያዩም፥ ይሰሙም ዘንድ ጆሮ አላቸው እነርሱም አይሰሙም፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና።
3 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የስደተኛ እክት አዘጋጅ በፊታቸውም ቀን ለቀን ተማረክ፥ በፊታቸውም ከስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ተማርከህ ሂድ፤ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት እንደ ሆኑ ምናልባት ያስተውሉ ይሆናል።
4 ፤ ቀን ለቀንም በፊታቸው እክትህን እንደ ስደተኛ እክት አውጣው፥ በማታም ጊዜ በፊታቸው ስደተኞች እንደሚወጡ እንዲሁ ውጣ።
5 ፤ በፊታቸውም ግንቡን ንደል በእርሱም አውጣ።
6 ፤ ለእስራኤልም ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና በፊታቸው በጫንቃህ ላይ አንግተው፥ በጨለማም ተሸክመህ ውጣ፤ ምድሪቱንም እንዳታይ ፊትህን ሸፍን።
7 ፤ እንዳዘዘኝም አደረግሁ፤ ቀን ለቀንም እክቱን እንደ ስደተኛ እክት አወጣሁ፥ በማታም ጊዜ ግንቡን በእጄ ነደልሁ፥ በጨለማም አወጣሁት በፊታቸውም በጫንቃዬ ላይ አንግቼ ተሸከምሁት።
8 ፤ በነጋውም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
9 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ዓመፀኛ ቤት የእስራኤል ቤት። የምታደርገው ምንድር ነው? አላሉህምን?
10 ፤ አንተም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህ ሸክም በኢየሩሳሌም በሚኖረው አለቃ ላይ በመካከላቸውም በሚኖሩት በእስራኤል ቤት ሁሉ ላይ ነው በላቸው።
11 ፤ ደግሞም። እኔ ምልክታችሁ ነኝ፤ እኔ እንዳደረግሁ እንዲሁ ይደረግባቸዋል፥ እነርሱም በስደት ወደ ምርኮ ይሄዳሉ በል።
12 ፤ በመካከላቸውም የሚኖረው አለቃ በጫንቃው ላይ አንግቶ በጨለማ ይወጣል፤ በዚያ ያወጡ ዘንድ ግንቡን ይነድላሉ፥ በዓይኑም ምድርን እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል።
13 ፤ መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ በወጥመዴም ይያዛል፥ ወደ ከለዳውያንም ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፤ ሆኖም አያያትም በዚያም ይሞታል።
14 ፤ ሊረዱትም በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ጭፍሮቹንም ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ በኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ።
15 ፤ በአሕዛብም መካከል በበተንኋቸው ጊዜ፥ በአገሮችም በዘራኋቸው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
16 ፤ በሚሄዱባቸውም አሕዛብ መካከል ርኵሰታቸውን ሁሉ ይናገሩ ዘንድ ከሰይፍና ከራብ ከቸነፈርም ጥቂቶች ሰዎችን ከእነርሱ አስቀራለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
17 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
18 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ እንጀራህን በድንጋጤ ብላ ውኃህንም በመንቀጥቀጥና በኀዘን ጠጣ፤
19 ፤ ለምድሪቱም ሕዝብ። ጌታ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ስለሚኖሩ ስለ እስራኤልም ምድር እንዲህ ይላል። ስለሚኖሩባት ሁሉ ግፍ ምድሪቱ ከነሞላዋ ትጠፋ ዘንድ እንጀራቸውን በችግር ይበላሉ ወኃቸውንም በድንጋጤ ይጠጣሉ።
20 ፤ ሰዎች የሚኖሩባቸው ከተሞች ባድማ ይሆናሉ ምድሪቱም ውድማ ትሆናለች፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው።
21 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
22 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር። ዘመኑ ረዝሞአል ራእዩም ሁሉ ጠፍቶአል የምትሉት ምሳሌ ምንድር ነው?
23 ፤ ስለዚህ እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህን ምሳሌ አስቀረዋለሁ በእስራኤልም ዘንድ ደግሞ ምሳሌ አድርገው አይናገሩትም፤ አንተ ግን። ዘመኑና የራእዩ ሁሉ ነገር ቀርቦአል በላቸው።
24 ፤ ከዚህም በኋላ በእስራኤል ቤት መካከል ከንቱ ራእይና ውሸተኛ ምዋርት አይሆንም።
25 ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እናገራለሁ የምናገረውም ቃል ይፈጸማል፥ ደግሞም አይዘገይም፤ እናንተ ዓመፀኛ ቤት ሆይ፥ በዘመናችሁ ቃሌን እናገራለሁ እፈጽመውማለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
26 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
27 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ የእስራኤል ቤት። ይህች የሚያያት ራእይ ለብዙ ዘመን ናት፥ እርሱም ለሩቅ ወራት ትንቢት ይናገራል ይላሉ። 
28 ፤ ስለዚህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የምናገረው ቃል ይፈጸማል እንጂ ከቃሌ ሁሉ ደግሞ የሚዘገይ የለም፥ ይላል እግዚአብሔር።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት በሚናገሩ በእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፥ ከገዛ ልባቸውም ትንቢት የሚናገሩትን። የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በላቸው፤
3 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ምንምን ሳያዩ የገዛ መንፈሳቸውን ለሚከተሉ ለሰነፎች ነቢያት ወዮላቸው!
4 ፤ እስራኤል ሆይ፥ ነቢያትህ በምድረ በዳ እንደሚኖሩ ቀበሮች ናቸው።
5 ፤ ወደ ተሰበረው ቅጥር አልወጣችሁም፥ በእግዚአብሔርም ቀን በሰልፍ ትቆሙ ዘንድ ለእስራኤል ቤት ቅጥር አልሠራችሁም።
6 ፤ እግዚአብሔር ሳይልካቸው። እግዚአብሔር ይላል የሚሉ ሰዎች ከንቱ ነገርንና ውሸተኛ ምዋርትን አይተዋል፤ ቃሉም ይጠና ዘንድ ተስፋ አስደርገዋል።
7 ፤ እኔም ሳልናገር። እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአል ስትሉ፥ ከንቱ ራእይን ያያችሁ ውሸተኛንም ምዋርት የተናገራችሁ አይደላችሁምን?
8 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከንቱ ነገርን ስለ ተናገራችሁ ውሸተኛ ራእይንም ስላያችሁ፥ ስለዚህ፥ እነሆ፥ እኔ በእናንተ ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
9 ፤ እጄም ከንቱ ራእይን በሚያዩ፥ በውሸትም በሚያምዋርቱ ነቢያት ላይ ትሆናለች፤ እነርሱም በሕዝቤ ማኅበር ውስጥ አይገኙም፥ በእስራኤልም ቤት መጽሐፍ አይጻፉም፥ ወደ እስራኤልም ምድር አይገቡም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
10 ፤ ሰላም ሳይኖር። ሰላም እያሉ ሕዝቤን አታልለዋልና፤ አንዱም ሰው ቅጥር ሲሠራ፥ እነሆ፥ ገለባ በሌለበት ጭቃ ይመርጉታልና
11 ፤ ገለባ በሌለበት ጭቃ ለሚመርጉት ሰዎች። ይወድቃል በላቸው። የሚያሰጥም ዝናብ ይዘንባል፥ ታላቅም የበረዶ ድንጋይ ይወድቃል፥ ዐውሎ ነፋስም ይሰነጣጥቀዋል።
12 ፤ እነሆ፥ ግንቡ በወደቀ ጊዜ። የመረጋችሁት ጭቃ ወዴት አለ? አይሉአችሁምን?
13 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመዓቴ በዐውሎ ነፋስ እሰነጣጥቀዋለሁ፥ ያጠፋውም ዘንድ በቍጣዬ የሚያሰጥም ዝናብ፥ በመዓቴም ታላቅ የበረዶ ድንጋይ ይወርዳል።
14 ፤ ገለባም በሌለበት ጭቃ የመረጋችሁትን ቅጥር አፈርሳለሁ ወደ ምድርም እጥለዋለሁ፥ መሠረቱም ይታያል። እርሱም ይናዳል በመካከሉም ትጠፋላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
15 ፤ መዓቴንም በግንቡ ላይ ገለባም በሌለበት ጭቃ በመረጉት ላይ እፈጽማለሁ፤ እኔም። ግንቡና መራጊዎቹ የሉም እላችኋለሁ።
16 ፤ እነርሱም ስለ ኢየሩሳሌም ትንቢት የሚናገሩ የሰላምን ራእይ የሚያዩላት የእስራኤል ነቢያት ናቸው፥ ሰላምም የለም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
17 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ከገዛ ልባቸው ትንቢት በሚናገሩ በሕዝብህ ሴቶች ልጆች ላይ ፊትህን አድርግ፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፥
18 ፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነፍስን ለማጥመድ ለእጅ ድጋፍ ሁሉ መከዳ ለሚሰፉ ለሰውም ሁሉ ራስ እንደ እየቁመቱ ሽፋን ለሚሠሩ ሴቶች ወዮላቸው! የሕዝቤንም ነፍስ ብታጠምዱ በውኑ ነፍሳችሁን ታድናላችሁን?
19 ፤ ውሸታችሁን ለሚሰሙት ሕዝቤ እየዋሻችሁ ሞት የማይገባቸውን ነፍሳት ትገድሉ ዘንድ በሕይወትም መኖር የማይገባቸውን ነፍሳት በሕይወት ታኖሩ ዘንድ ስለ ጭብጥ ገብስና ስለ ቍራሽ እንጀራ በሕዝቤ ዘንድ አርክሳችሁኛል።
20 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እኔ ነፍሳትን እንደ ወፍ በምታጠምዱባት በመከዳችሁ ላይ ነኝ፥ ከክንዳችሁም ወስጄ እቀድዳታለሁ፥ እንደ ወፍም የምታጠምዱአቸውን ነፍሳት እለቅቃለሁ።
21 ፤ ሽፋኖቻችሁን ደግሞ እቀድዳለሁ ሕዝቤንም ከእጃችሁ አድናለሁ፥ ከዚያም ወዲያ በእጃችሁ ለመታደን አይሆኑም፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
22 ፤ እኔም ያላሳዘንሁትን የጻድቁን ልብ በውሸት አሳዝናችኋልና፥ በሕይወትም ይኖር ዘንድ ከክፉ መንገድ እንዳይመለስ የኃጢአተኛውን እጅ አበርትታችኋልና 
23 ፤ ስለዚህ ከንቱን ራእይ እንግዲህ አታዩም ምዋርትንም አታምዋርቱም፥ ሕዝቤንም ከእጃችሁ አድናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

1 ፤ ከእስራኤልም ሽማግሌዎች አያሌ ሰዎች ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ።
2 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
3 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል የበደላቸውንም መቅሠፍት በፊታቸው አቁመዋል፤ እኔስ ከእነርሱ ልጠየቅን?
4፤5 ፤ ስለዚህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሁሉም በጣዖቶቻቸው ከእኔ ተለይተዋልና የእስራኤልን ቤት በልባቸው እይዝ ዘንድ ከእስራኤል ቤት ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖታቱ ብዛት እመልስለታለሁ ብለህ ንገራቸው።
6 ፤ ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ንስሐ ግቡ ከጣዖቶቻችሁም ተመለሱ፥ ፊታችሁንም ከርኵሰታችሁ ሁሉ መልሱ።
7 ፤ ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም ዘንድ ከሚቀመጡ መጻተኞች የሚሆን፥ ከእኔ ተለይቶ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ፥ ስለ እኔ ይጠይቅ ዘንድ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር በራሴ እመልስለታለሁ፤
8 ፤ ፊቴንም በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ ምልክትና ምሳሌም አደርገዋለሁ ከሕዝቤም መካከል አጠፋዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
9 ፤ ነቢዩም ቢታለል ቃልንም ቢናገር፥ ያንን ነቢይ ያታለልሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ እጄንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ ከሕዝቤም ከእስራኤል መካከል አጠፋዋለሁ።
10 ፤ ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ እንደሚጠይቀውም ሰው ኃጢአት እንዲሁ የነቢዩ ኃጢአት ይሆናል።
11 ፤ ይኸውም የእስራኤል ቤት ደግሞ ከእኔ ርቀው እንዳይስቱ በኃጢአታቸውም ሁሉ እንዳይረክሱ ነው። እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
12 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
13 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ምድር በማመፅ በእኔ ላይ ኃጢአት ስትሠራ፥ እኔም እጄን ስዘረጋባት የእንጀራዋንም በትር ስሰብር ራብን ስሰድድባት ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ ሳጠፋ፥
14 ፤ እነዚህ ሦስት ሰዎች፥ ኖኅና ዳንኤል ኢዮብም፥ ቢኖሩባት በጽድቃቸው የገዛ ነፍሳቸውን ብቻ ያድናሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15 ፤ ክፉዎቹን አራዊት በምድር ባሳልፍ እነርሱም ልጆችዋን ቢያጠፉ ስለ አራዊትም ማንም እንዳያልፍባት ባድማ ብትሆን፥
16 ፤ እነዚህ ሦስት ሰዎች ቢኖሩባት፥ እኔ ሕያው ነኝና እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ምድሪቱም ባድማ ትሆናለች፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
17 ፤ ወይም በዚያች ምድር ላይ ሰይፍ አምጥቼ። ሰይፍ ሆይ፥ በምድሪቱ ላይ እለፊ ብል፥ ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ ባጠፋ፥
18 ፤ እነዚህ ሦስት ሰዎች ቢኖሩባት፥ እኔ ሕያው ነኝና እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
19 ፤ ወይም በዚያች ምድር ላይ ቸነፈር ብሰድድ ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ አጠፋ ዘንድ መዓቴን በደም ባፈስስባት፥
20 ፤ ኖኅና ዳንኤል ኢዮብም ቢኖሩባት፥ እኔ ሕያው ነኝና በጽድቃቸው ነፍሳቸውን ብቻ ያድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
21 ፤ ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ይልቁንስ ሰውንና እንስሳን ከእርስዋ አጠፋ ዘንድ በኢየሩሳሌም ላይ አራቱን ክፉ ፍርዶቼን፥ ሰይፍንና ራብን ክፉዎችንም አውሬዎች ቸነፈርንም፥ ስሰድድባት!
22 ፤ ነገር ግን፥ እነሆ፥ የሚያመልጡና ወንዶችና ሴቶች ልጆችን የሚያመጡ ይቀሩላታል፤ እነሆ፥ ወደ እናንተ ይወጣሉ እናንተም መንገዳቸውንና ሥራቸውን ታያላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም ላይ ስላመጣሁት ክፉ ነገር ሁሉ ስላመጣሁባትም ነገር ሁሉ ትጽናናላችሁ። 
23 ፤ መንገዳቸውንና ሥራቸውን ባያችሁ ጊዜ ያጽናኑአችኋል፤ ያደረግሁባትንም ሁሉ በከንቱ እንዳላደረግሁባት ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የወይን ግንድ፥ በዱር ዛፎች መካከል ያለ የወይን አረግ፥ ከዛፍ ሁሉ ይልቅ ብልጫው ምንድር ነው?
3 ፤ በውኑ ሥራ የሚሠራበትን እንጨት ከእርሱ ይወስዳሉን? ወይስ ሰዎች ዕቃ የሚንጠለጠልበትን ኵላብ ከእርሱ ይወስዳሉን?
4 ፤ እነሆ፥ ለመቃጠል በእሳት ላይ ተጥሎአል፥ እሳቱም ሁለቱን ጫፎቹን በልቶአል፥ መካከሉም ተቃጥሎአል፤ በውኑ ለሥራ ይጠቅማልን?
5 ፤ እነሆ፥ ደህና ሳለ ለሥራ ካልጠቀመ፥ ይልቁንስ እሳት ከበላው እርሱም ከተቃጠለ በኋላ እንዴት ሥራ ይሠራበታል?
6 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዱር ዛፎች መካከል ያለውን የወይን ግንድ እሳት ይበላው ዘንድ እንደ ሰጠሁት፥ እንዲሁ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አሳልፌ እሰጣለሁ።
7 ፤ ፊቴንም በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ከእሳትም ይወጣሉ፥ እሳት ግን ይበላቸዋል፤ ፊቴንም በእነርሱ ላይ ባደረግሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 
8 ፤ ዓመፅን አድርገዋልና ምድሪቱን ባድማ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለኢየሩሳሌም ርኵሰትዋን አስታውቃት፥
3 ፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይላል። ዘርሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፤ አባትሽ አሞራዊ ነበረ እናትሽም ኬጢያዊት ነበረች።
4 ፤ በተወለድሽ ጊዜ በዚያው ቀን እትብትሽ አልተቈረጠም ንጹሕም ትሆኚ ዘንድ በውኃ አልታጠብሽም፥ በጨውም አልተቀባሽም በጨርቅም አልተጠቀለልሽም።
5 ፤ በተወለድሽበት ቀን ከሰውነትሽ ጕስቍልና የተነሣ በሜዳ ላይ ተጣልሽ እንጂ ከዚህ አንዳች ይደረግልሽ ዘንድ ዓይን አልራራልሽም፥ ማንም አላዘነልሽም።
6 ፤ በአንቺም ዘንድ ባለፍሁ ጊዜ በደምሽም ውስጥ ተለውሰሽ ባየሁሽ ጊዜ። በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ፤ አዎን። በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ።
7 ፤ በእርሻ ላይ እንዳለ ቡቃያ አበዛሁሽ፥ አንቺም አደግሽ ታላቅም ሆንሽ፥ በእጅጉም አጌጥሽ፤ ጡቶችሽም አጐጠጐጡ ጠጕርሽም አደገ፥ ነገር ግን ዕርቃንሽን ሆንሽ፥ ተራቍተሽም ነበርሽ።
8 ፤ በአንቺ ዘንድ ባለፍሁና ባየሁሽ ጊዜ፥ እነሆ፥ ጊዜሽ የፍቅር ጊዜ ነበረ፤ እኔም መጐናጸፊያዬን በላይሽ ዘረጋሁ ኀፍረተ ሥጋሽንም ከደንሁ፤ ማልሁልሽም ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ አንቺም ለእኔ ሆንሽ።
9 ፤ በውኃም አጠብሁሽ ከደምሽም አጠራሁሽ በዘይትም ቀባሁሽ።
10 ፤ ወርቀ ዘቦም አለበስሁሽ በአቆስጣ ቁርበትም ጫማ አደረግሁልሽ፤ በጥሩ በፍታ አስታጠቅሁሽ በሐርም ከደንሁሽ።
11 ፤ በጌጥም አስጌጥሁሽ በእጅሽም ላይ አንባር በአንገትሽም ላይ ድሪ አደረግሁልሽ።
12 ፤ በአፍንጫሽም ቀለበት በጆሮሽም ጕትቻ በራስሽም ላይ የክብር አክሊል አደረግሁ።
13 ፤ በወርቅና በብር አጌጥሽ፥ ልብስሽም ጥሩ በፍታና ሐር ወርቀ ዘቦም ነበረ፤ አንቺም መልካምን ዱቄትና ማርን ዘይትንም በላሽ፤ እጅግ በጣም ውብ ሆንሽ ለመንግሥትም ደረስሽ።
14 ፤ ባንቺ ላይ ካኖርኋት ከክብሬ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም ነበረና ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ወጣ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15 ፤ ነገር ግን በውበትሽ ታምነሻል ስለ ዝናሽም አመንዝረሻል ምንዝርናሽንም ከመንገድ አላፊ ሁሉ ጋር አበዛሽ።
16 ፤ ከልብስሽም ወስደሽ በኮረብቶች ላይ በዝንጕርጕር ልብስ ያስጌጥሻቸውን መስገጆች ለራስሽ ሠራሽ በዚያም ገለሞትሽ፤ እንዲህም ያለ ነገር ከአሁን በፊት አልነበረም፥ ከእንግዲህም ወዲያ አይሆንም።
17 ፤ ከሰጠሁሽም ከወርቄና ከብሬ የተሠራውን የክብርሽን ዕቃ ወስደሽ የወንድ ምስሎች ለራስሽ አድርገሻል አመንዝረሽባቸውማል።
18 ፤ ወርቀዘቦውን ልብስሽንም ወስደሽ ደረብሽላቸው፥ ዘይቴንና ዕጣኔንም በፊታቸው አኖርሽ።
19 ፤ የሰጠሁሽንም እንጀራዬን ያበላሁሽንም መልካሙን ዱቄትና ዘይቱን ማሩንም ጣፋጭ ሽታ አድርገሽ በፊታቸው አኖርሽ፥ እንዲሁም ሆኖአል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
20 ፤ ለእኔም የወለድሻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ወስደሽ መብል ይሆኑ ዘንድ ሠዋሽላቸው።
21 ፤ ልጆቼን አረድሽ፤ ለእነርሱም በእሳት በኩል አሳልፈሽ ሰጠሽ፤ በውኑ ግልሙትናሽ ጥቂት ነውን?
22 ፤ በርኵስነትሽና በግልሙትናሽ ሁሉ ዕርቃንሽን ሆነሽ ተራቍተሽም ሳለሽ በደምሽም ተለውሰሽ ሳለሽ የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽም።
23 ፤ ወዮ! ወዮልሽ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤
24 ፤ ከክፋትሽም ሁሉ በኋላ የምንዝርናን ስፍራ፥ በየአደባባዩም ከፍ ያለ ቦታን ለራስሽ ሠራሽ።
25 ፤ በየመንገዱ ራስ ከፍ ያለውን ቦታሽን ሠራሽ፥ ውበትሽንም አረከስሽ፥ ለመንገድ አላፊም ሁሉ እግርሽን ገለጥሽ ግልሙትናሽንም አበዛሽ።
26 ፤ ሥጋቸውም ከወፈረ ከጐረቤቶችሽ ከግብጻውያን ጋር አመነዘርሽ፥ እኔንም ታስቈጭ ዘንድ ግልሙትናሽን አበዛሽ።
27 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቻለሁ ድርጐሽንም አጕድያለሁ፤ ለሚጠሉሽም ከክፉ መንገድሽ የተነሣ ለሚያፍሩ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች ፈቃድ አሳልፌ ሰጥቼሻለሁ።
28 ፤ አልጠገብሽምና ከአሦራውያን ጋር ደግሞ ገለሞትሽ ከዚህም ጋር ገና አልጠገብሽም።
29 ፤ እስከ ነጋዴዎች ምድር እስከ ከላውዴዎን ድረስ ግልሙትናሽን አበዛሽ። ከዚህም ጋር ገና አልጠገብሽም።
30 ፤ የማታፍረውን የጋለሞታን ሥራ ሁሉ ሠርተሻልና ልብሽ ምንኛ ደካማ ነው? ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
31 ፤ በየመንገዱ ራስ የምንዝርናሽን ስፍራ ሠርተሻል በየአደባባዩም ከፍ ያለውን ቦታሽን አድርገሻል። ዋጋዋን እንደምትንቅ እንደ ጋለሞታ አልሆንሽም።
32 ፤ በባልዋ ፋንታ ሌሎችን ተቀብላ የምታመነዝር ሴትን ትመስያለሽ።
33 ፤ ለጋለሞቶች ሁሉ ዋጋ ይሰጡአቸዋል፤ አንቺ ግን ለውሽሞችሽ ሁሉ ዋጋ ትሰጫለሽ፥ ከአንቺም ጋር ለማመንዘር በዙሪያሽ ይገቡብሽ ዘንድ መማለጃ ትሰጫቸዋለሽ።
34 ፤ ግልሙትናሽ ከሌሎች ሴቶች ግልብጥ ነው፤ ማንም ለግልሙትና የሚከተልሽ የለም፤ ዋጋ ሳይሰጥሽ አንቺ ዋጋ በመስጠትሽ በዚህ ነገር ልዩ ሆነሻል።
35 ፤ ስለዚህ፥ ጋለሞታ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ።
36 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከውሽሞችሽ ጋር ባደረግሽው በግልሙትናሽ ርኵሰትሽ ስለ ፈሰሰ ኀፍረተ ሥጋሽም ስለ ተገለጠ፥ ስለ ርኵሰትሽም ጣዖታት ሁሉ ስለ ሰጠሻቸውም ስለ ልጆች ደም፥
37 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ ከእነርሱ ጋር ደስ ያለሽን የወደድሻቸውንም ውሽሞችሽ ሁሉ ከጠላሻቸው ሁሉ ጋር እሰበስባቸዋለሁ፤ በአንቺ ላይ በዙሪያሽ እሰበስባቸዋለሁ፥ ኀፍረተ ሥጋሽንም ሁሉ እንዲያዩ በፊታቸው ኀፍረተ ሥጋሽን እገልጣለሁ።
38 ፤ በአመንዝሮችና በደም አፍሳሾች ላይ የሚፈረደውን ፍርድ እፈርድብሻለሁ፥ የመዓትንና የቅንዓትን ደምም አመጣብሻለሁ።
39 ፤ በእጃቸውም አሳልፌ እሰጥሻለሁ፥ የምንዝርናሽንም ስፍራ ያፈርሳሉ ከፍ ያለውንም ቦታሽን ይገለብጣሉ፤ ልብስሽንም ይገፉሻል የክብርሽንም ጌጥ ይወስዳሉ፥ ዕርቃንሽን አድርገው ዕራቁትሽን ይተዉሻል።
40 ፤ ጉባኤን ያመጡብሻል በድንጋይም ይወግሩሻል፥ በሰይፋቸውም ይወጉሻል።
41 ፤ ቤቶችሽንም በእሳት ያቃጥላሉ በብዙም ሴቶች ፊት በላይሽ ፍርድን ያደርጉብሻል፤ ግልሙትናሽንም አስተውሻለሁ፥ እንግዲህስ ዋጋ አትሰጭም።
42 ፤ መዓቴንም በአንቺ ላይ እጨርሳለሁ ቅንዓቴም ከአንቺ ይርቃል፥ እኔም ዝም እላለሁ ደግሞም አልቈጣም።
43 ፤ የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽምና፥ በዚህም ነገር ሁሉ አስቈጥተሽኛልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ እኔ ደግሞ መንገድሽን በራስሽ ላይ አመጣለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ሌላንም ነውር በርኵሰትሽ ሁሉ ላይ አትጨምሪም።
44 ፤ እነሆ፥ በምሳሌ የሚናገር ሁሉ። እንደ እናቲቱ እንዲሁ ሴት ልጂቱ ናት እያለ ምሳሌ ይመስልብሻል።
45 ፤ አንቺ ባልዋንና ልጆችዋን የጠላሽ የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ አንቺም ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የጠሉ የእኅቶችሽ እኅት ነሽ፤ እናታችሁ ኬጢያዊት ነበረች አባታችሁም አሞራዊ ነበረ።
46 ፤ ታላቂቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በስተ ግራሽ የምትቀመጥ ሰማርያ ናት፤ ታናሺቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በስተ ቀኝሽ የምትቀመጥ ሰዶም ናት።
47 ፤ አንቺ ግን በመንገዳቸው አልሄድሽም እንደ ርኵሰታቸውም አላደረግሽም ያው ለአንቺ ጥቂት ነበረና በመንገድሽ ሁሉ ከእነርሱ የሚከፋ ርኵሰት አደረግሽ።
48 ፤ እኔ ሕያው ነኝና አንቺና ሴቶች ልጆችሽ እንዳደረጋችሁት እንዲሁ ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ አላደረጉም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
49 ፤ እነሆ፥ የእኅትሽ የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበረ፤ ትዕቢት እንጀራን መጥገብ መዝለልና ሥራ መፍታት በእርስዋና በሴቶች ልጆችዋ ነበረ፥ የችግረኛውንና የድሀውንም እጅ አላጸናችም።
50 ፤ ኰርተው ነበር በፊቴም ርኩስ ነገር አደረጉ፤ ስለዚህ ባየሁ ጊዜ አጠፋኋቸው።
51 ፤ ሰማርያም የኃጢአትሽን እኵሌታ አልሠራችም፤ አንቺ ግን ከእኅቶችሽ ይልቅ ርኵሰትሽን አበዛሽ፥ በሥራሽም ርኵሰት ሁሉ አጸደቅሻቸው።
52 ፤ አሁንም ለእኅቶችሽ ስለ ፈረድሽ እፍረትሽን ተሸከሚ፤ ከእነርሱ የባሰ ኃጢአት ሠርተሻልና ከአንቺ ይልቅ ጻድቃን ናቸው፤ እኅቶችሽንም ስለ አጸደቅሻቸው እፈሪ እፍረትሽንም ተሸከሚ።
53 ፤ ምርኮአቸውን፥ የሰዶምና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ የሰማርያንና የሴቶች ልጆችዋንም ምርኮ፥ በመካከላቸውም ያሉትን የምርኮኞችሽን ምርኮ እመልሳለሁ፤
54 ፤ ስለ አጽናናሻቸው፥ እፍረትን ትሸከሚ ዘንድ ስለ አደረግሽውም ሁሉ ታፍሪ ዘንድ።
55 ፤ እኅቶችሽም ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ ሰማርያና ሴቶች ልጆችዋም ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ አንቺና ሴቶች ልጆችሽም ወደ ቀድሞ ሁኔታችሁ ትመለሳላችሁ።
56 ፤ ክፋትሽ ሳይገለጥ በትዕቢትሽ ቀን እኅትሽ ሰዶም በአፍሽ መተረቻ አልነበረችምን?
57 ፤ አሁን ለሶርያ ሴቶች ልጆችና ለጎረቤቶችዋ ሁሉ፥ በዙሪያሽም ለሚንቁሽ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች እንደ እርስዋ መሰደቢያ ሆነሻል።
58 ፤ ምንዝርነትሽንና ርኵስነትሽን ተሸክመሻል፥ ይላል እግዚአብሔር።
59 ፤ ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። አንቺ ቃል ኪዳንን በማፍረስ መሐላን የናቅሽ ሆይ፥ አንቺ እንዳደረግሽ እኔ ደግሞ አደርግብሻለሁ።
60 ፤ ነገር ግን በሕፃንነትሽ ወራት ከአንቺ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ የዘላለምንም ቃል ኪዳን አጸናልሻለሁ።
61 ፤ እኅቶችሽንም ታላቂቱንና ታናሺቱን በተቀበልሽ ጊዜ መንገድሽን ታስቢያለሽ ታፍሪማለሽ፤ ለአንቺም ልጆች ይሆኑ ዘንድ እሰጣቸዋለሁ፥ ስለ ቃል ኪዳንሽ ግን አይደለም። 
62፤63 ፤ ስላደረግሽውም ሁሉ ይቅር ባልሁሽ ጊዜ፥ ታስቢ ዘንድ ታፍሪም ዘንድ ስለ እፍረትሽም ደግሞ አፍሽን እንዳትከፍቺ፥ ቃል ኪዳኔን ከአንቺ ጋር አጸናለሁ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

1 ፤ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእንቈቅልሽ አጫውት ለእስራኤልም ቤት ምሳሌ ንገር፥ እንዲህም በል።
3 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ታላቅ ክንፍ ረጅምም ማርገብገቢያ ያለው ላባም የተሞላ፥ መልከ ዝንጕርጕር ታላቅ ንስር ወደ ሊባኖስ መጣ፥ የዝግባንም ጫፍ ወሰደ።
4 ፤ ቀንበጡንም ቀነጠበ ወደ ከነዓንም ምድር ወሰደው በነጋዶችም ከተማ አኖረው።
5 ፤ ከምድርም ዘር ወሰደ በፍሬያማ እርሻ ተከለው በብዙም ውኃ አጠገብ እንደ አኻያ ዛፍ አኖረው።
6 ፤ በበቀለም ጊዜ ቁመቱ ያጠረ አረጉም ወደ እርሱ የሚመለስ ሥሩም በበታቹ የነበረ ሰፊ ወይን ሆነ፥ እንዲሁ ወይን ሆነ አረግም ሰደደ ቀንበጥም አወጣ።
7 ፤ ታላቅ ክንፍና ብዙ ላባም ያለው ሌላ ታላቅ ንስር ነበረ፤ እነሆም፥ ያጠጣው ዘንድ ይህ ወይን ሥሩን ወደ እርሱ አዘነበለ አረጉንም ከተተከለበት ከመደቡ ወደ እርሱ ሰደደ።
8 ፤ አረግም ያወጣ ፍሬም ያፈራ የከበረም ወይን ይሆን ዘንድ በመልካም መሬት ውስጥ በብዙም ውኃ አጠገብ ተተክሎ ነበር።
9 ፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በውኑ ይከናወንለት ይሆንን? ይደርቅስ ዘንድ፥ አዲስ የበቀለውስ ቅጠሉ ይጠወልግ ዘንድ ሥሩን አይነቅለውምን? ፍሬውንስ አይለቅመውምን? ሥሩም የተነቀለው በብርቱ ክንድና በብዙ ሕዝብ አይደለም።
10 ፤ ተተክሎስ፥ እነሆ፥ ይከናወንለት ይሆንን? የምሥራቅ ነፋስ ባገኘው ጊዜ ፈጽሞ አይደርቅምን? በተተከለበት መደብ ላይ ይደርቃል።
11 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
12 ፤ ለዓመፀኛ ቤት። ይህ ትርጓሜ ምን እንደ ሆነ አታውቁምን? በላቸው። እንዲህም ብለህ ንገራቸው። እነሆ፥ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ ንጉሥዋንና መኳንንቶችዋንም ማረከ፥ ወደ እርሱም ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው።
13 ፤ ከመንግሥትም ዘር ወስዶ ቃል ኪዳን ከእርሱ ጋር አደረገ፤ አማለውም፥ የምድሪቱንም ኃያላን ወሰደ፤
14 ፤ ይኸውም ቃል ኪዳኑን በመጠበቅ እንድትጸና እንጂ መንግሥቱ እንድትዋረድና ከፍ እንዳትል ነው።
15 ፤ እርሱ ግን በእርሱ ላይ ሸፈተ ፈረሶችንና ብዙንም ሕዝብ ይሰጡት ዘንድ መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ላከ። በውኑ ይከናወንለት ይሆንን? ይህንስ ያደረገ ያመልጣልን? ቃል ኪዳንንስ አፍርሶ ያመልጣልን?
16 ፤ እኔ ሕያው ነኝና ያነገሠውና መሐላውን የናቀበቱ፥ ቃል ኪዳኑንም ያፈረሰበቱ ንጉሥ በሚኖርበት ስፍራ ከእርሱ ጋር በባቢሎን መካከል በእርግጥ ይሞታል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
17 ፤ ብዙዎችን ነፍሳት ለማስወገድ አፈርን በደለደሉ ምሽግም በሠሩ ጊዜ፥ ፈርዖን ከብዙ ሠራዊቱና ከታላቁ ጉባኤው ጋር በሰልፍ አይረዳውም።
18 ፤ ቃል ኪዳኑንም በማፍረስ መሐላውን ንቆአል፤ እነሆም፥ እጁን ሰጠ፥ ይህንም ሁሉ አድርጎአል፤ ስለዚህ አያመልጥም።
19 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና የናቀውን መሐላዬን ያፈረሰውንም ቃል ኪዳኔን በራሱ ላይ አመጣለሁ።
20 ፤ መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ በወጥመድም ይያዛል፥ ወደ ባቢሎንም አመጣዋለሁ በእኔም ላይ ስላደረገው ዓመፅ በዚያ ከእርሱ ጋር እፋረዳለሁ።
21 ፤ ጭፍሮቹም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ የቀሩትም ሁሉ ወደ እየነፋሳቱ ይበተናሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ ታውቃላችሁ።
22 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከረጅሙ ዝግባ ጫፍ ላይ ቀንበጥን ወስጄ አኖረዋለሁ፤ ከጫፎቹ አንዱን ቀንበጥ እቀነጥበዋለሁ፤ በረጅምና በታላቅ ተራራም ላይ እተክለዋለሁ።
23 ፤ ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ እተክለዋለሁ፥ ቅርንጫፎችም ያወጣል ፍሬም ያፈራል የከበረም ዝግባ ይሆናል፤ በበታቹም ወፎች ሁሉ ያርፋሉ፥ በቅርንጫፎቹም ጥላ በክንፍ የሚበርር ሁሉ ይጠጋል። 
24 ፤ የዱር ዛፎች ሁሉ ረጅሙን ዛፍ ዝቅ ያደረግሁ፥ አጭሩንም ዛፍ ከፍ ያደረግሁ፥ የለመለመውንም ዛፍ ያደረቅሁ፥ የደረቀውንም ዛፍ ያለመለምሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ እኔም አድርጌአለሁ።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ ስለ እስራኤል ምድር። አባቶች ጨርቋ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ ብላችሁ የምትመስሉት ምሳሌ ምንድር ነው?
3 ፤ እኔ ሕያው ነኝና እንግዲህ ወዲህ ይህን ምሳሌ በእስራኤል ዘንድ አትመስሉትም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
4 ፤ እነሆ፥ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፤ የአባት ነፍስ የእኔ እንደ ሆነች ደግሞ የልጅ ነፍስ የእኔ ናት፤ ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።
5 ፤ ሰውም ጻድቅ ቢሆን ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥
6 ፤ በተራራም ላይ ባይበላ ዓይኞቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ አደፍም ወዳለባት ሴት ባይቀርብ፤
7 ፤ ሰውንም ባያስጨንቅ ለባለ ዕዳም መያዣውን ቢመልስ ፈጽሞም ባይቀማ ከእንጀራውም ለተራበ ቢሰጥ የተራቈተውንም በልብስ ቢያለብስ፤
8 ፤ በአራጣ ባያበድር፥ ትርፎቻም ባይወስድ፥ እጁንም ከኃጢአት ቢመልስ፥ በሰውና በሰው መካከልም የእውነትን ፍርድ ቢፈርድ፤
9 ፤ በትእዛዜም ቢሄድ፥ እውነትንም ለማድረግ ፍርዴን ቢጠብቅ፥ እርሱ ጻድቅ ነው፥ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
10 ፤ እርሱም ቀማኛና ደም አፍሳሽ ልጅ ከዚህም ሁሉ አንዳቸውን የሚያደርገውን ቢወልድ፥
11 ፤ እርሱም ጻድቅ አባቱ የሠራውን ሁሉ ባይሠራ በተራራም ላይ ቢበላ የባልንጀራውንም ሚስት ቢያረክስ፥
12 ፤ ድሀውንና ችግረኛውንም ቢያስጨንቅ ቢቀማም መያዣውንም ባይመልስ ዓይኖቹንም ወደ ጣዖታት ቢያነሣ ርኩስን ነገር ቢያደርግ፥
13 ፤ በአራጣ ቢያበድር፥ ትርፎቻም ቢወስድ፥ በውኑ እርሱ በሕይወት ይኖራልን? በሕይወት አይኖርም፤ ይህን ርኵሰት ሁሉ አድርጎአልና ፈጽሞ ይሞታል፤ ደሙ በላዩ ላይ ይሆናል።
14 ፤ እነሆም፥ ልጅ ቢወልድ፥ እርሱም አባቱ የሠራውን ኃጢአት አይቶ ቢፈራ እንዲህም ባይሠራ፥
15 ፤ በተራራ ላይ ባይበላ ዓይኖቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ፥
16 ፤ ሰውንም ባያስጨንቅ መያዣውን ባይወስድ ባይቀማም ከእንጀራውም ለተራበ ቢሰጥ ለተራቈተውም ልብስን ቢያለብስ፥
17 ፤ እጁንም ድሀን ከመበደል ቢመልስ አራጣን ትርፎቻንም ባይወስድ ፍርዴንም ቢያደርግ በትእዛዜም ቢሄድ፥ እርሱ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ በአባቱ ኃጢአት አይሞትም።
18 ፤ አባቱ ግን ፈጽሞ በድሎአልና፥ ወንድሙንም ቀምቶአልና፥ በሕዝቡም መካከል ክፉን ነገር አድርጎአልና እነሆ፥ እርሱ በበደሉ ይሞታል።
19 ፤ እናንተ ግን። ልጅ የአባቱን ኃጢአት ስለ ምን አይሸከምም? ትላላችሁ። ልጅ ፍርድንና ቅን ነገርን ባደረገ ትእዛዜንም ሁሉ በጠበቀና ባደረገ ጊዜ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል።
20 ፤ ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች፤ ልጅ የአባቱን ኃጢአት አይሸከምም፥ አባትም የልጁን ኃጢአት አይሸከምም፤ የጻድቁ ጽድቅ በራሱ ላይ ይሆናል፥ የኃጢአተኛውም ኃጢአት በራሱ ላይ ይሆናል።
21 ፤ ኃጢአተኛውም ካደረጋት ኃጢአት ሁሉ ቢመለስ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቅ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።
22 ፤ የበደለው በደል ሁሉ አይታሰብበትም፤ በሠራው ጽድቅ በሕይወት ይኖራል።
23 ፤ በውኑ ኃጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን?
24 ፤ ጻድቁ ግን ከጽድቁ ቢመለስ ኃጢአትንም ቢሠራ ኃጢአተኛውም እንደሚያደርገው ርኵሰት ሁሉ ቢያደርግ፥ በሕይወት ይኖራልን? የሠራት ጽድቅ ሁሉ አትታሰብለትም፤ ባደረገው ዓመፅና በሠራት ኃጢአት በዚያች ይሞታል።
25 ፤ እናንተ ግን። የጌታ መንገድ የቀናች አይደለችም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ መንገዴ የቀናች አይደለችምን? ይልቅስ የእናንተ መንገድ ያልቀናች አይደለችምን?
26 ፤ ጻድቁ ከጽድቁ ቢመለስ፥ ኃጢአትንም በሠራ ጊዜ፥ በዚያም ቢሞት፥ እርሱ ባደረገው በደል ይሞታል።
27 ፤ ኃጢአተኛውም ከሠራው ኃጢአት ቢመለስ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ነፍሱን ይጠብቃል።
28 ፤ አስቦ ከሠራው በደል ሁሉ ተመልሶአልና ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።
29 ፤ ነገር ግን የእስራኤል ቤት። የጌታ መንገድ የቀናች አይደለችም ይላል። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በውኑ መንገዴ የቀናች አይደለችምን? ይልቅስ የእናንተ መንገድ ያልቀናች አይደለችምን?
30 ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለዚህ እንደ መንገዱ በየሰዉ ሁሉ እፈርድባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ንስሐ ግቡ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ።
31 ፤ የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ ምን ትሞታላችሁ? 
32 ፤ የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።

1 ፤ አንተም በእስራኤል አለቆች ላይ ይህን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በል።
2 ፤ እናትህ ምን ነበረች? አንበሳ ነበረች፤ በአንበሶች መካከል ተጋደመች፤ በደቦል አንበሶች መካከል ግልገሎችዋን አሳደገች።
3 ፤ ከግልገሎችዋም አንዱን አወጣች እርሱም ደቦል አንበሳ ሆነ፤ ንጥቂያንም ተማረ፥ ሰዎችንም በላ።
4 ፤ አሕዛብም ወሬውን ሰሙ እርሱም በጕድጓዳቸው ተያዘ፥ በሰንሰለትም አድርገው ወደ ግብጽ ምድር ወሰዱት።
5 ፤ እርስዋም እንደ ደከመችና ተስፋዋ እንደ ጠፋ ባየች ጊዜ፥ ከግልገሎችዋ ሌላን ወስዳ ደቦል አንበሳ አደረገችው።
6 ፤ እርሱም በአንበሶች መካከል ተመላለሰ ደቦል አንበሳም ሆነ፤ ንጥቂያም ተማረ፥ ሰዎችንም በላ።
7 ፤ ግንቦቻቸውንም አወቀ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረሰ፤ ከግሣቱም ድምፅ የተነሣ ምድሪቱና ሞላዋ ጠፋች።
8 ፤ አሕዛብም በዙሪያው ከየአገሩ ሁሉ ተሰበሰቡበት፤ መረባቸውንም በእርሱ ላይ ዘረጉ በጕድጓዳቸውም ተያዘ።
9 ፤ በሰንሰለትም አድርገው በቀፎ ውስጥ አኖሩት ወደ ባቢሎንም ንጉሥ አመጡት፤ ድምፁም በእስራኤል ተራሮች ላይ ከዚያ ወዲያ እንዳይሰማ ወደ አምባ አገቡት።
10 ፤ እናትህ በመልክህ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለች እንደ ወይን ግንድ ነበረች፤ ከውኃም ብዛት የተነሣ የምታፈራና የምትሰፋ ሆነች።
11 ፤ ለእርስዋም ብርቱዎች በትሮች ነበሩአት እነርሱም ለነገሥታት በትሮች ነበሩ። ቁመታቸውም በዛፎች ቅርንጫፎች መካከል ረዘመ፥ በጫፎቻቸውም ብዛትና በርዝመታቸው ታዩ።
12 ፤ ነገር ግን በመዓት ተነቀለች ወደ መሬትም ተጣለች የምሥራቅም ነፋስ ፍሬዋን አደረቀ፤ ብርቱዎች በትሮችዋም ተሰበሩና ደረቁ፥ እሳትም በላቻቸው።
13 ፤ አሁንም በምድረ በዳ፥ በደረቅና በተጠማች መሬት ተተከለች። 
14 ፤ ከጫፎችዋም በትሮች እሳት ወጣች ፍሬዋንም በላች፥ የነገሥታትም በትር ይሆን ዘንድ የበረታ በትር የለባትም። ይህ ሙሾ ነው፥ ለልቅሶም ይሆናል።

1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን እግዚአብሔርን ይጠይቁ ዘንድ ከእስራኤል ሽማግሌዎች አያሌ ሰዎች መጡ፥ በፊቴም ተቀመጡ።
2 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
3 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ሽማግሌዎች ተናገር፥ እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔን ትጠይቁ ዘንድ መጥታችኋልን? እኔ ሕያው ነኝና በእናንተ ዘንድ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
4 ፤ ትፈርድባቸዋለህን? የሰው ልጅ ሆይ፥ በውኑ ትፈርድባቸዋለህን? የአባቶቻቸውን ርኵሰት አስታውቃቸው።
5 ፤ እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስራኤልን በመረጥሁበት ለያዕቆብም ቤት ዘር በማልሁበት ቀን በግብጽም ምድር በተገለጥሁላቸውና። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ ብዬ በማልሁላቸው ጊዜ፥
6 ፤ በዚያ ቀን ከግብጽ ምድር ወዳዘጋጀሁላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው፥ የምድርም ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ምድር አወጣቸው ዘንድ ማልሁላቸው፤
7 ፤ እኔም። ከእናንተ እያንዳንዱ የዓይኑን ርኵሰት ይጣል፥ በግብጽም ጣዖታት አትርከሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ አልኋቸው።
8 ፤ እነርሱ ግን ዐመፁብኝ ይሰሙኝም ዘንድ አልወደዱም፥ ሁሉም እያንዳንዱ የዓይኑን ርኵሰት አልጣለም የግብጽንም ጣዖታት አልተወም፤ በዚህም ጊዜ። በግብጽ ምድር መካከል ቍጣዬን እፈጽምባቸው ዘንድ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ አልሁ።
9 ፤ ነገር ግን በመካከላቸው ባሉ ከግብጽም ምድር አወጣቸው ዘንድ በፊታቸው በተገለጥሁላቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ።
10 ፤ ከግብጽም ምድር አወጣኋቸው ወደ ምድረ በዳም አመጣኋቸው።
11 ፤ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዓቴንም ሰጠኋቸው፥ ፍርዴንም አስታወቅኋቸው።
12 ፤ የምቀድሳቸውም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእኔና በእነርሱ መካከል ምልክት ይሆኑ ዘንድ ሰንበታቴን ሰጠኋቸው።
13 ፤ ነገር ግን የእስራኤል ቤት በምድረ በዳ ዐመፁብኝ፤ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትንም ፍርዴን ጣሱ፥ በትእዛዜም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም ፈጽመው አረከሱ። በዚህም ጊዜ። አጠፋቸው ዘንድ ቍጣዬን በምድረ በዳ አፈስስባቸዋለሁ አልሁ።
14 ፤ ነገር ግን በፊታቸው ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ።
15 ፤ ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው የምድር ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ወደ ሰጠኋቸው ምድር አላመጣቸውም ብዬ በምድረ በዳ ማልሁባቸው።
16 ፤ ልባቸው ጣዖቶቻቸውን ተከትሎአልና፤ ፍርዴንም ጥሰዋልና፥ በሥርዓቴም አልሄዱምና፥ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና።
17 ፤ ነገር ግን ዓይኔ ራራችላቸው እኔም አላጠፋኋቸውም፥ በምድረ በዳም ፈጽሜ አልፈጀኋቸውም።
18 ፤ ለልጆቻቸውም በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው። በአባቶቻችሁ ሥርዓት አትሂዱ ወጋቸውንም አትጠብቁ በጣዖቶቻቸውም አትርከሱ።
19 ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ በትእዛዜ ሂዱ ፍርዴንም ጠብቁ አድርጓትም።
20 ፤ ሰንበታቴንም ቀድሱ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆናሉ።
21 ፤ ልጆች ግን ዐመፁብኝ፥ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርባትን ፍርዴን ጠብቀው አላደረጓትም በሥርዓቴም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም አረከሱ፤ በዚህም ጊዜ። መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ ቍጣዬንም በምድረ በዳ እፈጽምባቸዋለሁ አልሁ።
22 ፤ ነገር ግን እጄን መለስሁ፥ በፊታቸውም ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ።
23 ፤ ደግሞም ወደ አሕዛብ እበትናቸው ዘንድ፥ በአገሮችም እበትናቸው ዘንድ በምድረ በዳ ማልሁባቸው፤ ፍርዴን አላደረጉምና፤
24 ፤ ሥርዓቴንም ጥሰዋልና፤ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና፤ ዓይናቸውም የአባቶቻቸውን ጣዖታቶች ተከትለዋልና።
25 ፤ ደግሞም መልካም ያልሆነውን ሥርዓት በሕይወት የማይኖሩበትንም ፍርድ ሰጠኋቸው።
26 ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንዲያውቁ አጠፋቸው ዘንድ፥ ማኅፀን የሚከፍተውን ሁሉ በእሳት ባሳለፉ ጊዜ፥ በመባቸው አረከስኋቸው።
27 ፤ ስለዚህ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ተናገር እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህም ደግሞ አባቶቻችሁ ባደረጉት ዓመፅ አስቈጡኝ።
28 ፤ እሰጣቸውም ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ባገባኋቸው ጊዜ፥ ከፍ ያለውን ኮረብታ ሁሉ ቅጠልማውንም ዛፍ ሁሉ አዩ፥ በዚያም መሥዋዕታቸውን ሠዉ በዚያም የሚያስቈጣኝን ቍርባናቸውን አቀረቡ በዚያም ደግሞ ጣፋጩን ሽታቸውን አደረጉ በዚያም የመጠጥ ቍርባናቸውን አፈሰሱ።
29 ፤ እኔም። እናንተ ወደ እርሱ የምትሄዱበት ከፍታ ምንድር ነው? አልኋቸው። እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ተጠርቶአል።
30 ፤ ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንደ አባቶቻችሁ ልማድ ትረክሳላችሁን? ርኵሰታቸውንም ተከትላችሁ ታመነዝራላችሁን?
31 ፤ ቍርባናችሁን ባቀረባችሁ ጊዜ፥ ልጆቻችሁንም በእሳት ባሳለፋችሁ ጊዜ፥ እስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ትረክሳላችሁን የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ከእናንተስ ዘንድ እጠየቃለሁን? እኔ ሕያው ነኛና ከእናንተ ዘንድ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤
32 ፤ ለእናንተም። እንደ አሕዛብና እንደ ምድር ወገኖች እንሆናለን፥ እንጨትና ድንጋይም እናመልካለን የሚል ከልባችሁ የወጣ አሳብ አይፈጸምላችሁም።
33 ፤ እኔ ሕያው ነኝና በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እነግሥባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
34 ፤ ከአሕዛብም ዘንድ አወጣችኋለሁ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እሰበስባችኋለሁ።
35 ፤ ወደ አሕዛብም ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ።
36 ፤ በግብጽ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ እንዲሁ ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
37 ፤ ከበትርም በታች አሳልፋችኋለሁ ወደ ቃል ኪዳንም እስራት አገባችኋለሁ፤
38 ፤ ከእናንተም ዘንድ ዓመፀኞችንና የበደሉኝን እለያለሁ፤ ከኖሩባትም ምድር አወጣቸዋለሁ፥ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
39 ፤ ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ሂዱ፥ ከዚህም በኋላ ትሰሙኝ ዘንድ ባትወድዱ ሁላችሁ ጣዖቶቻችሁን አምልኩ። ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ በቍርባናችሁና በጣዖቶቻችሁ ቅዱሱን ስሜን አታረክሱም።
40 ፤ በቅዱሱ ተራራዬ፥ ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ በዚያ የእስራኤል ቤት ሁሉ ሁላቸው በምድሩ ላይ ያመልኩኛል፤ በዚያም እቀበላቸዋለሁ፥ በዚያም ቍርባናችሁን በኵራታችሁንም የቀደሳችሁትንም ነገር ሁሉ እፈልጋለሁ።
41 ፤ ከአሕዛብም ዘንድ ባወጣኋችሁ ጊዜ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በሰበሰብኋችሁ ጊዜ እንደ ጣፋጭ ሽታ እቀበላችኋለሁ፥ በአሕዛብም ፊት እቀደስባችኋለሁ።
42 ፤ ለአባቶቻችሁም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር ባገባኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
43 ፤ በዚያም የረከሳችሁባትን መንገዳችሁንና ሥራችሁን ሁሉ ታስባላችሁ፤ ስለ ሠራችሁትም ክፋታችሁ ሁሉ ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ።
44 ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እንደ ክፉ መንገዳችሁና እንደ ርኩስ ሥራችሁ ሳይሆን ስለ ስሜ ስል በሠራሁላችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
45 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
46 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ደቡብ አቅና ወደ ደቡብም ተናገር በደቡብም ባለው ዱር ላይ ትንቢት ተናገር፤
47 ፤ ለደቡብም ዱር። የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በአንተ ውስጥ እሳት አነድዳለሁ፤ በውስጥህም ያለውን የለመለመውንና የደረቀውን ዛፍ ሁሉ ይበላል፤ የሚቃጠል ነበልባል አይጠፋም፤ ከደቡብም ጀምሮ እስከ ሰሜን ድረስ ፊት ሁሉ ይቃጠልበታል።
48 ፤ እኔም እግዚአብሔር እንዳነደድሁት ሥጋ ለባሽ ሁሉ ያያል፥ እርሱም አይጠፋም በለው። 
49 ፤ እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነርሱ ስለ እኔ። ይህ ምሳሌን የሚመስል አይደለምን? ብለዋል አልሁ።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም አቅና ወደ መቅደሶችም ተናገር በእስራኤልም ምድር ላይ ትንቢት ተናገር።
3 ፤ ለእስራኤልም ምድር እንዲህ በል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ ሰይፌንም ከሰገባው እመዝዘዋለሁ፥ ጻድቁንና ክፉውንም ከአንተ ዘንድ አጠፋለሁ።
4 ፤ እኔም ጻድቁንና ክፉውን ከአንተ ዘንድ ስለማጠፋ፥ ስለዚህ ሰይፌ ከደቡብ ጀምሮ እስከ ሰሜን ድረስ ባለ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ከሰገባው ይመዘዛል።
5 ፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ እኔ እግዚአብሔር ሰይፌን ከሰገባው እንደ መዘዝሁ ያውቃል፥ እርሱም ደግሞ አይመለስም።
6 ፤ ስለዚህም፥ አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ አልቅስ፤ ወገብህን በማጕበጥ በፊታቸው ምርር ብለህ አልቅስ።
7 ፤ እነርሱም። ስለ ምን ታለቅሳለህ? ቢሉህ፥ አንተ እንዲህ በላቸው። ወሬ ስለሚመጣ ነው፤ ልብም ሁሉ ይቀልጣል፥ እጆችም ሁሉ ይዝላሉ፥ ነፍስም ሁሉ ትደክማለች፥ ጉልበትም እንደ ውኃ ይፈስሳል፤ እነሆ፥ ይመጣል ይፈጸምማል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
8 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
9 ፤ የሰው ልጅ ሆይ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ትንቢት ተናገር፤ ሰይፍ ሰይፍ የተሳለ የተሰነገለም ነው በል።
10 ፤ ይገድል ዘንድ ተስሎአል ያብረቀርቅም ዘንድ ተሰንግሎአል፤ እኛስ ደስ ይለናልን? የልጄን በትር እንደ ዛፍ ሁሉ ንቆታል።
11 ፤ በእጁም እንዲያዝ ለመሰንገል ተሰጠ፤ ሰይፍ በገዳይ እጅ እንዲሰጥ ተሳለና ተሰነገለ።
12 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በሕዝቤ ላይ ነውና፥ በእስራኤል አለቆች ሁሉ ላይ ነውና ጩኽ ዋይም በል፤ እነርሱ ከሕዝቤ ጋር ለሰይፍ ተሰጥተዋል፤ ስለዚህ ጭንህን ጽፋ።
13 ፤ ፈተና ደርሶአል፤ የተናቀ በትርስ ደግሞ ባይኖር ምንድር ነው? ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
14 ፤ ስለዚህ፥ አንተ የሰው ልጅ፥ ትንቢት ተናገር፥ እጅህን አጨብጭብ፤ የተገደሉ ሰዎች ሰይፍ ሦስት ጊዜ ይደጋግም የሚከብባቸው የተገደለ የታላቅ ሰው ሰይፍ ነው።
15 ፤ ልባቸው እንዲቀልጥ መሰናክላቸውም እንዲበዛ የሚገድለውን ሰይፍ በበሮቻቸው ሁሉ ላይ አድርጌአለሁ፤ ወዮ! ያብረቀርቅ ዘንድ ተሰንግሎአል ይገድልም ዘንድ ተስሎአል።
16 ፤ ተዘጋጅተህ ፊትህ ወደ ወደደው ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሂድ።
17 ፤ እኔ ደግሞ በእጄ አጨበጭባለሁ መዓቴንም እጨርሳለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።
18 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
19 ፤ አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ ይመጣ ዘንድ ሁለት መንገዶችን አድርግ፤ ሁለቱም ከአንዲት ምድር ይውጡ፤ ምልክትም አድርግ፥ በከተማይቱ መንገድ ራስ ላይ አድርገው።
20 ፤ ሰይፍ ወደ አሞን ልጆች አገር ወደ ረባት ወደ ይሁዳም ወደ ተመሸገች ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣ ዘንድ መንገድን አድርግ።
21 ፤ የባቢሎን ንጉሥ ምዋርቱን ያምዋርት ዘንድ በመንታ መንገድ ላይ በሁለቱ መንገዶች ራስ ላይ ቆሞ ነበር፤ ፍላጾችን ወዘወዘ፥ ከተራፊምም ጠየቀ፥ ጉበትም ተመለከተ።
22 ፤ የቅጥሩን ማፍረሻ ያደርግ ዘንድ፥ አፍንም በጩኸት ይከፍት ዘንድ፥ በውካታም ድምፅን ከፍ ያደርግ ዘንድ፥ የቅጥሩን ማፍረሻ በበሮች ላይ ያደርግ ዘንድ፥ አፈርን ይደለድል ዘንድ፥ ምሽግም ይሠራ ዘንድ የኢየሩሳሌም ዕጣ በቀኝ እጁ ውስጥ ነበረ።
23 ፤ መሐላውንም በማሉ በዓይናቸው ዘንድ የሐሰት ምዋርት ይመስላል፥ ነገር ግን እነርሱ ይያዙ ዘንድ እርሱ ኃጢአትን ያሳስባል።
24 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ኃጢአታችሁን ስለ አሰባችሁ መተላለፋችሁም ስለ ተገለጠ ኃጢአታችሁም በሥራችሁ ሁሉ ስለ ታየ እናንተም ስለ ታሰባችሁ፥ በእጅ ትያዛላችሁ።
25 ፤ አንተም ቀንህ የደረሰብህ፥ የኃጢአትህ ቀጠሮ ጊዜ የደረሰብህ፥ ርኩስ ኃጢአተኛ የእስራኤል አለቃ ሆይ፥
26 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። መጠምጠሚያውን አውልቅ፥ ዘውዱንም አርቅ፤ ይህ እንዲህ አይሆንም፤ የተዋረደውን ከፍ አድርግ፥ ከፍ ያለውንም አዋርድ።
27 ፤ ባድማ፥ ባድማ፥ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ፍርድ ያለው እስኪመጣ ድረስ ይህች ደግሞ አትሆንም፥ ለእርሱም እሰጣታለሁ።
28፤29 ፤ አንተም የሰው ልጅ ሆይ። ጌታ እግዚአብሔር ስለ አሞን ልጆችና ስለ ስድባቸው እንዲህ ይላል ብለህ ትንቢት ተናገር፤ ቀናቸው በደረሰ፥ የኃጢአታቸው ቀጠሮ ጊዜ በደረሰ፥ በተገደሉት ኃጢአተኞች አንገት ላይ ያኖሩህ ዘንድ ከንቱን ራእይ ነገር ሲያዩልህ በሐሰትም ምዋርት ሲናገሩልህ። ሰይፍ፥ ሰይፍ ተመዝዞአል፥ ይገድልም ዘንድ ያብረቀርቅም ዘንድ ተሰንግሎአል በል።
30 ፤ ወደ ሰገባውም መልሰው። በተፈጠርህበት ስፍራ በተወለድህባትም ምድር እፈርድብሃለሁ።
31 ፤ ቍጣዬንም አፈስስብሃለሁ፥ በመዓቴም እሳት አናፋብሃለሁ፥ ማጥፋትንም ለሚያውቁ ለጨካኞች ሰዎች እጅ አሳልፌ እሰጥሃለሁ። 
32 ፤ ለእሳት ማገዶ ትሆናለህ፥ ደምህም በምድር መካከል ይሆናል፥ ደግሞም አትታሰብም፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ትፈርዳለህን? ደም በምታፈስስ ከተማ ላይ ትፈርዳለህን? ርኵሰትዋን ሁሉ አስታውቃት።
3 ፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጊዜሽ እንዲደርስ በመካከልሽ ደምን የምታፈስሺ እንድትረክሺም በራስሽ ላይ ጣዖታትን የምታደርጊ ከተማ ሆይ!
4 ፤ ባፈሰስሽው ደም በድለሻል ባደረግሽውም ጣዖታት ረክሰሻል፤ ቀንሽን አቀረብሽ ዘመንሽንም አሳጠርሽ፤ ስለዚህ ለአሕዛብ መሰደቢያ ለአገሮችም ሁሉ መሳለቂያ አደረግሁሽ።
5 ፤ አንቺ ስምሽ የረከሰ ሽብርም የሞላብሽ ሆይ፥ ወደ አንቺ የቀረቡና ከአንቺ የራቁ ይሳለቁብሻል።
6 ፤ እነሆ፥ የእስራኤል አለቆች እያንዳንዱ እንደ ችሎቱ ደም ያፈስሱ ዘንድ በአንቺ ውስጥ ነበሩ።
7 ፤ በአንቺ ውስጥ አባትንና እናትን አቃለሉ፤ በመካከልሽ በመጻተኛው ላይ በደልን አደረጉ፤ በአንቺ ውስጥ ድሀ አደጉንና መበለቲቱን አስጨነቁ።
8 ፤ ቅድሳቴንም ናቅሽ ሰንበታቴንም አረከስሽ።
9 ፤ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ቀማኞች ሰዎች በአንቺ ውስጥ ነበሩ፤ በአንቺ ውስጥ በተራሮች ላይ በሉ፤ በመካከልሽ ሴሰኝነትን አደረጉ።
10 ፤ በአንቺ ውስጥ የአባቶቻቸውን ኀፍረተ ሥጋ ገለጡ፤ በአንቺም ውስጥ አደፍ ያለባትን አዋረዱ።
11 ፤ ሰውም በባልንጀራው ሚስት ርኵሰትን አደረገ፥ አባትም የልጁን ሚስት አረከሰ፥ በአንቺም ዘንድ ወንድም የአባቱን ልጅ እኅቱን አሳፈረ።
12 ፤ በአንቺ ውስጥ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ጉቦን ተቀበሉ፤ አንቺም አራጣና ትርፍ ወስደሻል፥ ከባልንጀሮችሽም በቅሚያ የስስትን ትርፍ አገኘሽ፥ እኔንም ረሳሽኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
13 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ አንቺ ባደረግሽው ስስት በመካከልሽም በነበረው ደም ላይ እጄን አጨበጨብሁ።
14 ፤ በውኑ እኔ በማደርግብሽ ወራት ልብሽ ይታገሣልን? ወይስ እጅሽ ትጸናለችን? እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ አደርገውማለሁ።
15 ፤ ወደ አሕዛብም እበትንሻለሁ ወደ አገሮችም እዘራሻለሁ፥ ርኵሰትሽንም ከአንቺ ዘንድ አጠፋለሁ።
16 ፤ በአሕዛብም ፊት አንቺ ትረክሻለሽ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂአለሽ።
17 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
18 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት ለእኔ እንደ አተላ ሆኑብኝ፤ እነርሱ ሁሉ በከውር ውስጥ መዳብና ቈርቈሮ ብረትና እርሳስ ናቸው፤ የብር አተላ ናቸው።
19 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሁላችሁ አተላ ሆናችኋልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ በኢየሩሳሌም ውስጥ እሰበስባችኋለሁ።
20 ፤ እንዲያቀልጡት እሳት ያናፉበት ዘንድ ብርንና መዳብን ብረትንና እርሳስን ቈርቈሮንም በከውር እንደሚሰበስቡ፥ እንዲሁ በቍጣዬና በመዓቴ እሰበስባችኋለሁ፥ በዚያም ውስጥ እጨምራችኋለሁ አቀልጣችሁማለሁ።
21 ፤ አሰበስባችሁማለሁ የመዓቴንም እሳት አናፋባችኋለሁ በውስጡም ትቀልጣላችሁ።
22 ፤ ብርም በከውር ውስጥ እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ በውስጡዋ ትቀልጣላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር መዓቴን እንዳፈሰስሁባችሁ ታውቃላችሁ።
23 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
24 ፤ የሰው ልጅ ሆይ። አንቺ ያልነጻሽ በቍጣም ቀን ያልዘነበብሽ ምድር ነሽ በላት።
25 ፤ በውስጥዋ ያሉ ነቢያት እንደሚጮኽና እንደሚናጠቅ አንበሳ አንድ ሆነው ተማማሉ፤ ነፍሶችን በልተዋል፥ ብልጥግናና ሀብትን ወስደዋል፥ በውስጥዋም መበለቶችን አብዝተዋል።
26 ፤ ካህናቶችዋም ሕጌን በድለዋል ቅድሳቴንም አርክሰዋል፤ ቅዱስ በሆነና ቅዱስ ባልሆነ መካከልም አልለዩም፥ በንጹሕና በርኩስ መካከል ያለውን ልዩነት አላስታወቁም፤ ዓይናቸውንም ከሰንበታቴ ሰወሩ እኔም በመካከላቸው ረከስሁ።
27 ፤ በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ የስስትን ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ነፍሶችንም ያጠፉ ዘንድ እንደሚናጠቁ ተኵላዎች ናቸው።
28 ፤ እግዚአብሔርም ሳይናገር ነቢያቶችዋ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እያሉ ከንቱን ራእይ በማየት የሐሰትንም ምዋርት ለእነርሱ በማምዋረት ያለ ገለባ በጭቃ ይመርጓቸዋል።
29 ፤ የምድርን ሕዝብ ግፍ አደረጉ ቅሚያም ሠሩ፤ ድሆችንና ችግረኞችን አስጨነቁ፥ መጻተኛውንም በደሉ።
30 ፤ ቅጥርን የሚጠግንን፥ ምድሪቱንም እንዳላጠፋት በፈረሰበት በኩል በፊቴ የሚቆምላትን ሰው በመካከላቸው ፈለግሁ፥ ነገር ግን አላገኘሁም። 
31 ፤ ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፥ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

1 ፤ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የአንዲት እናት ልጆች የሆኑ ሁለት ሴቶች ነበሩ።
3 ፤ በግብጽም አመነዘሩ፥ በኰረዳነታቸው አመነዘሩ፤ በዚያ ጡቶቻቸው ምዋሸሹ በዚያም የድንግልናቸውን ጡቶች ዳበሱ።
4 ፤ ስማቸውም የታላቂቱ ኦሖላ የእኅትዋም ኦሖሊባ ነበረ፥ ለእኔም ሆኑ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለዱ። ስማቸውም ኦሖላ ሰማርያ ናት፤ ኦሖሊባ ደግሞ ኢየሩሳሌም ናት።
5 ፤ ኦሖላም ገለሞተችብኝ፥ ውሽሞችዋንም ጎረቤቶችዋን አሦራውያንን በፍቅር ተከተለቻቸው።
6 ፤ እነርሱም ሰማያዊ ሐር የለበሱ አለቆችና ሹማምቶች፥ መልከ መልካሞች ጐበዛዝት፥ በፈረስ ላይ የሚቀመጡ ፈረሰኞች ነበሩ።
7 ፤ ግልሙትናዋንም ከተመረጡ ከአሦር ሰዎች ሁሉ ጋር አደረገች፥ በፍቅር በተከተለቻቸውም ጣዖቶቻቸው ሁሉ ረከሰች።
8 ፤ በግብጽም የነበረውን ግልሙትናዋን አልተወችም፤ በዚያ በኰረዳነትዋ ጊዜ ከእርስዋ ጋር ተኝተው ነበር፥ የድንግልናዋንም ጡቶች ዳብሰው ነበር፥ ግልሙትናቸውንም አፍስሰውባት ነበር።
9 ፤ ስለዚህ በፍቅር በተከተለቻቸው በውሽሞችዋ በአሦራውያን እጅ አሳልፌ ሰጠኋት።
10 ፤ እነርሱም ኅፍረተ ሥጋዋን ገለጡ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችዋንም ማርከው ወሰዱ፥ እርስዋንም በሰይፍ ገደሉ፤ ፍርድንም ስላደረጉባት በሴቶች መካከል መተረቻ ሆነች።
11 ፤ እኅትዋም ኦሖሊባ ይህን አየች፤ ሆኖም ከእርስዋ ይልቅ በፍቅር በመከተልዋ ረከሰች፥ ግልሙትናዋም ከእኅትዋ ግልሙትና ይልቅ በዛ።
12 ፤ አለቆችንና ሹማምቶችን ጎረቤቶችዋን ጌጠኛ ልብስ የለበሱትን በፈረሶች ላይ የሚቀመጡትን ፈረሰኞች፥ ሁሉም መልከ መልካሞችን ጐበዛዝት አሦራውያንን በፍቅር ተከተለቻቸው።
13 ፤ የረከሰችም እንደ ሆነች አየሁ፥ ሁለቱም አንድ መንገድ ሄደዋል።
14 ፤ ግልሙትናዋንም አበዛች፤ በቀይ ቀለምም የተሳለችውን የከለዳውያንን ስዕል፥ በናስ ላይ የተሳሉትን ሰዎች አየች።
15 ፤ በወገባቸው ዝናር የታጠቁ ራሳቸውንም በቀለማዊ መጠምጠሚያ የጠመጠሙ ነበሩ፤ ሁሉም ከተወለዱባት አገር የሆኑትን የከለዳውያንን ልጆች መስለው መሳፍንትን ይመስሉ ነበር።
16 ፤ ባየቻቸውም ጊዜ በፍቅር ተከተለቻቸው፥ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ እነርሱ መልእክተኞችን ላከች።
17 ፤ የባቢሎንም ሰዎች ወደ እርስዋ ፍቅር ወዳለበት መኝታ መጡ በግልሙትናቸውም አረከሱአት፤ እርስዋም ከእነርሱ ጋር ረከሰች ነፍስዋም ከእነርሱ ተለየች።
18 ፤ ግልሙትናዋንም ገለጠች ኅፍረተ ሥጋዋንም አሳየች፤ ነፍሴም ከእኅትዋ እንደ ተለየች እንዲሁ ነፍሴ ከእርስዋ ተለየች።
19 ፤ ነገር ግን በግብጽ ምድር የገለሞተችበትን የኰረዳነትዋን ዘመን አስባ ግልሙትናዋን አበዛች።
20 ፤ ሥጋቸውም እንደ አህዮች ሥጋ ዘራቸውም እንደ ፈረሶች ዘር የሆነውን እነዚያን ምልምሎች በፍቅር ተከተለቻቸው።
21 ፤ ስለ ኰረዳነትሽ ምክንያት ግብጻውያን ጡቶችሽን በዳበሱ ጊዜ የኰረዳነትሽን ሴሰኝነት አሰብሽ።
22 ፤ ስለዚህ፥ ኦሖሊባ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነፍስሽ ከእነርሱ የተለየች ውሽሞችሽን አስነሣብሻለሁ፥ በዙሪያሽም በአንቺ ላይ አመጣቸዋለሁ።
23 ፤ እነርሱም የባቢሎን ሰዎች ከለዳውያንም ሁሉ፥ ፋቁድ፥ ሱሔ፥ ቆዓ፥ ከእነርሱም ጋር አሦራውያን ሁሉ፥ መልከ መልካሞች ጐበዛዝት፥ አለቆችና ሹማምቶች ሁሉ፥ መሳፍንቶችና አማካሪዎች ሁሉ፥ በፈረስ ላይ የተቀመጡ ናቸው።
24 ፤ በመሣሪያና በሰረገላ በመንኰራኵርም በአሕዛብም ጉባኤ ይመጡብሻል፤ ጋሻና አላባሽ ጋሻ ራስ ቍርም ይዘው በዙሪያሽ ይዘጋጁብሻል፤ ፍርድንም እሰጣቸዋለሁ፥ እንደ ፍርዳቸውም ይፈርዱብሻል።
25 ፤ ቅንዓቴንም በአንቺ ላይ አደርጋለሁ በመዓትም ያደርጉብሻል፤ አፍንጫሽንና ጆሮሽንም ከአንቺ ይቈርጣሉ፥ ከአንቺም የቀረ በሰይፍ ይወድቃል፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽንም ማርከው ይወስዳሉ፥ ከአንቺም የቀረውን እሳት ትበላቸዋለች።
26 ፤ ልብስሽንም ይገፍፉሻል የክብርሽንም ጌጥ ይወስዳሉ።
27 ፤ ሴሰኝነትሽንም፥ ከግብጽ ምድር ያወጣሽውን ግልሙትናሽንም ከአንቺ አስቀራለሁ፤ ዓይንሽንም ወደ እነርሱ አታነሺም ግብጽንም ከዚያ ወዲያ አታስቢም።
28 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ በጠላሻቸው እጅ፥ ነፍስሽ በተለየቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤
29 ፤ እነርሱም በጥል ያደርጉብሻል፥ የደከምሽበትንም ሁሉ ይወስዳሉ፥ ዕራቁትሽንና ዕርቃንሽን አድርገውም ይተዉሻል፤ የግልሙትናሽም ነውር፥ ሴሰኝነትሽና ግልሙትናሽም ሁሉ ይገለጣል።
30 ፤ ከአሕዛብ ጋር ስላመነዘርሽ በጣዖቶቻቸውም ስለ ረከስሽ ይህን ያደረጉብሻል።
31 ፤ በእኅትሽ መንገድ ሄደሻል፤ ስለዚህ ጽዋዋን በእጅሽ እሰጥሻለሁ።
32 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የጠለቀውንና የሰፋውን ብዙም የሚይዘውን የእኅትሽን ጽዋ ትጠጪአለሽ፤ መሳቂያና መሳለቂያም ትሆኛለሽ።
33 ፤ በእኅትሽ በሰማርያ ጽዋ፥ በድንጋጤና በጥፋት ጽዋ፥ በስካርና በውርደት ትሞልያለሽ።
34 ፤ ትጠጪዋለሽ ትጨልጪውማለሽ ገሉንም ታኝኪዋለሽ ጡትሽንም ትሸነትሪዋለሽ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
35 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዘንግተሽኛልና፥ ወደ ኋላሽም ጥለሽኛልና አንቺ ደግሞ ሴሰኝነትሽንና ግልሙትናሽን ተሸከሚ።
36 ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ በኦሖላና በኦሖሊባ ትፈርዳለህን? ኃጢአታቸውንም ታስታውቃቸዋለህ?
37 ፤ አመንዝረዋልና፥ ደምም በእጃቸው አለና፥ ከጣዖቶቻቸውም ጋር አመንዝረዋልና፥ ለእኔም የወለዱአቸውን ልጆቻቸውን መብል እንዲሆኑላቸው በእሳት አሳልፈዋቸዋልና።
38 ፤ ይህን ደግሞ አድርገውብኛል፤ በዚያ ቀን መቅደሴን አርክሰዋል ሰንበታቴንም ሽረዋል።
39 ፤ ልጆቻቸውንም ለጣዖቶቻቸው በሠዉ ጊዜ፥ በዚያው ቀን ያረክሱት ዘንድ ወደ መቅደሴ ገቡ፤ እነሆም፥ በቤቴ ውስጥ እንደዚህ አደረጉ።
40 ፤ ደግሞ መልእክተኛ ወደ ተላከባቸው ከሩቅም ወደሚመጡ ሰዎች ልካችኋል፤ እነሆም መጡ፥ አንቺም ታጠብሽላቸው ዓይኖችሽንም ተኳልሽ ጌጥም አጌጥሽ፤
41 ፤ በክብር አልጋ ላይ ተቀመጥሽ፥ በፊት ለፊትዋም ማዕድ ተዘጋጅታ ነበር፥ ዕጣኔንና ዘይቴንም አኖርሽባት።
42 ፤ የደስተኞችም ድምፅ በእርስዋ ዘንድ ነበረ፤ ከብዙም ሰዎች ጉባኤ ጋር ሰካራሞቹ ከምድረ በዳ መጡ፤ በእጃቸው አንበር በራሳቸውም የተዋበ አክሊል አደረጉ።
43 ፤ እኔም በምንዝር ላረጀችው። አሁን ከእርስዋ ጋር ያመነዝራሉ እርስዋም ከእነርሱ ጋር ታመነዝራለች አልሁ።
44 ፤ ወደ ጋለሞታም እንደሚገቡ ወደ እርስዋ ገቡ፤ እንዲሁ ይሰስኑ ዘንድ ወደ ኦሖላና ወደ ኦሖሊባ ገቡ።
45 ፤ ሴቶቹ አመንዝሮች ናቸውና፥ በእጃቸውም ደም አለና ጻጽቃን ሰዎች በአመንዝሮቹና በደም አፍሳሾቹ ሴቶች ላይ በሚፈረደው ፍርድ ይፈርዱባቸዋል።
46 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጉባኤን አመጣባቸዋለሁ፥ ለመበተንና ለመበዝበዝም አሳልፌ አሰጣቸዋለሁ።
47 ፤ ጉባኤውም በድንጋይ ይወግሩአቸዋል በሰይፋቸውም ይቈርጡአቸዋል፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም ይገድላሉ፥ ቤቶቻቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ።
48 ፤ ሴቶችም ሁሉ እንደ ሴሰኝነታችሁ እንዳይሠሩ ይማሩ ዘንድ ሴሰኝነትን ከምድር ላይ አጠፋለሁ። 
49 ፤ ሴሰኝነታችሁንም በላያችሁ ላይ ይመልሳሉ፥ እናንተም የጣዖቶቻችሁን ኃጢአት ትሸከማላችሁ፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

1 ፤ በዘጠነኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የዚህን ቀን፥ የዛሬን ቀን ስም ጻፍ፤ በዚህ ቀን የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ቀረበ።
3 ፤ ለዓመፀኛውም ቤት ምሳሌን ተናገር እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጣድ፥ ምንቸቲቱን ጣድ፥ ውኃም ጨምርባት።
4 ፤ ቍራጭዋንም፥ መልካሙን ቍራጭ ሁሉ፥ ጭኑንና ወርቹን በእርስዋ ውስጥ ሰብስብ፥ የተመረጡትንም አጥንቶች ሙላባት።
5 ፤ ከመንጋው የተመረጠውን ውሰድ፥ አጥንቶቹም እንዲበስሉ እንጨት በበታችዋ ማግድ፤ አጥንቶቹም በውስጥዋ ይቀቀሉ።
6 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዝገትዋ ላለባት ዝገትዋም ከእርስዋ ላልወጣ ምንቸት፥ ለደም ከተማ ወዮላት! ቍራጭ ቍራጩን አውጣ፤ ዕጣ አልወደቀባትም።
7 ፤ ደምዋ በውስጥዋ አለ። በተራቈተ ድንጋይ ላይ አደረገችው እንጂ በአፈር ይከደን ዘንድ በመሬት ላይ አላፈሰሰችውም፤
8 ፤ መዓቴን አወጣ ዘንድ፥ በቀሌንም እበቀል ዘንድ፥ ደምዋ እንዳይከደን በተራቈተ ድንጋይ ላይ አደረግሁ።
9 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለደም ከተማ ወዮላት! እኔ ደግሞ ማገዶዋን ታላቅ አደርገዋለሁ።
10 ፤ እንጨቱን አብዛ፤ እሳቱን አንድድ፤ ሥጋውን ቀቅል፤ መረቁን አጣፍጠው፤ አጥንቶቹ ይቃጠሉ።
11 ፤ ትሞቅም ዘንድ ናስዋም ትግል ዘንድ ርኵሰትዋም በውስጥዋ ይቀልጥ ዘንድ ዝገትዋም ይጠፋ ዘንድ ባዶዋን በፍም ላይ አድርጋት።
12 ፤ በከንቱ ደከመች፤ ሆኖም ዝገትዋ በእሳት ስንኳ አልለቀቀም።
13 ፤ በርኵሰትሽ ሴሰኝነት አለ፤ አነጻሁሽ አልነጻሽምና መዓቴን በላይሽ እስክጨርስ ድረስ እንግዲህ ከርኵሰትሽ አትነጺም።
14 ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ ይመጣል፥ እኔም አደርገዋለሁ፤ አልመለስም፥ አልራራም፥ አልጸጸትም፤ እንደ መንገድሽና እንደ ሥራሽ ይፈርዱብሻል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
16 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ የዓይንህን አምሮት በመቅሠፍት እወስድብሃለሁ፤ አንተም ወይ አትበል አታልቅስም እንባህንም አታፍስስ።
17 ፤ በቀስታ ተክዝ፤ ለምዋቾችም አታልቅስ፥ መጠምጠሚያህን በራስህ ላይ አድርግ፥ ጫማህንም በእግርህ አጥልቅ፥ ከንፈሮችህንም አትሸፍን የሰዎችንም እንጀራ አትብላ።
18 ፤ እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፥ ወደ ማታም ሚስቴ ሞተች፤ በነጋውም እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ።
19 ፤ ሕዝቡም። ይህ የምታደርገው ነገር ለእኛ ምን እንደ ሆነ አትነግረንምን? አሉኝ።
20 ፤ እኔም እንዲህ አልኋቸው። የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
21 ፤ ለእስራኤል ቤት ተናገር እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የኃይላችሁን ትምክሕት፥ የዓይናችሁን አምሮት፥ የነፍሳችሁን ምኞት መቅደሴን አረክሳለሁ፤ ያስቀራችኋቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።
22 ፤ እኔም እንዳደረግሁ እናንተ ታደርጋላችሁ፤ ከንፈራችሁን አትሸፍኑም የሰዎችንም እንጀራ አትበሉም።
23 ፤ መጠምጠሚያችሁም በራሳችሁ ጫማችሁም በእግራችሁ ይሆናል፤ ዋይ አትሉም አታለቅሱምም፤ በኃጢአታችሁም ትሰለስላላችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ታንጐራጕራላችሁ።
24 ፤ ሕዝቅኤልም ምልክት ይሆናችኋል፤ እርሱ እንዳደረገ ሁሉ እናንተ ታደርጋላችሁ፤ ይህም በመጣ ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
25 ፤ አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ኃይላቸውን፥ የተመኩበትንም ደስታ፥ የዓይናቸውን አምሮት፥ የነፍሳቸውንም ምኞት፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በወሰድሁባቸው ቀን፥
26 ፤ በዚያ ቀን ያመለጠው ይህን ነገር በጆሮህ ያሰማ ዘንድ ወደ አንተ ይመጣል። 
27 ፤ በዚያ ቀን አፍህ ላመለጠው ይከፈታል፥ አንተም ትናገራለህ ከዚያ ወዲያም ዲዳ አትሆንም፤ ምልክትም ትሆናቸዋለህ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ አሞን ልጆች አቅንተህ ትንቢት ተናገርባቸው።
3 ፤ ለአሞንም ልጆች እንዲህ በል። የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። መቅደሴ በረከሰ ጊዜ የእስራኤልም ምድር ባድማ በሆነች ጊዜ የይሁዳም ቤት በተማረኩ ጊዜ ስለ እነርሱ እሰይ ብለሃልና
4 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ ርስት አድርጌ ለምሥራቅ ልጆች አሳልፌ አሰጥሃለሁ፥ እነርሱም በአንተ ውስጥ ይሰፍራሉ፥ ማደሪያዎቻቸውንም በአንተ ዘንድ ይሠራሉ፤ ፍሬህን ይበላሉ ወተትህንም ይጠጣሉ፤
5 ፤ የአሞንን ከተማ ለግመሎች ማሰማርያ፥ የአሞንንም ልጆች ለመንጋ መመሰጊያ አደርጋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
6 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። በእጅህ አጨብጭበሃልና፥ በእግርህም አሸብሽበሃልና፥ በእስራኤልም ምድር ላይ በነፍስህ ንቀት ሁሉ ደስ ብሎሃልና
7 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ እጄን ዘርግቼብሃለህ፥ ለአሕዛብም አስበዘብዝሃለሁ፥ ከአሕዛብም ለይቼ እቈርጥሃለሁ፥ ከአገሮችም አጠፋሃለሁ እፈጅህማለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ።
8 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሞዓብና ሴይር። እነሆ፥ የይሁዳ ቤት እንደ አሕዛብ ሁሉ ነው ብለዋልና
9 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሞዓብን ጫንቃ ከከተሞቹ፥ በዳርቻው ካሉት የምድሩ ትምክሕት ከሆኑት ከተሞቹ፥ ከቤትየሺሞት፥ ከበኣልሜዎን፥
10 ፤ ከቂርያታይም፥ ከአሞን ልጆች ጋር ለምሥራቅ ልጆች እከፍታለሁ። የአሞን ልጆች በአሕዛብ መካከል ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይታሰቡ ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ።
11 ፤ በሞዓብም ላይ ፍርድን አደርጋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
12 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ኤዶምያስ በይሁዳ ቤት ላይ በቀል አድርጎአልና፥ ቂም ይዞአልና፥ ብድራትንም አስከፍሎአልና
13 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እጄን በኤዶምያስ ላይ እዘረጋለሁ ከእርስዋም ዘንድ ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፥ ከቴማንም ጀምሮ ባድማ አደርጋታለሁ፥ እስከ ድዳንም ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ።
14 ፤ በሕዝቤ በእስራኤል እጅ ኤዶምያስን እበቀላለሁ፤ እንደ ቍጣዬና እንደ መዓቴም መጠን በኤዶምያስ ያደርጋሉ፤ በቀሌንም ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ፍልስጥኤማውያን በቀልን አድርገዋልና፥ በዘወትርም ጠላትነት ያጠፉ ዘንድ በነፍሳቸው ንቀት ተበቅለዋልና
16 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እጄን በፍልስጥኤማውያን ላይ እዘረጋለሁ፥ ከሊታውያንንም እቈርጣለሁ፥ የባሕሩንም ዳር ቅሬታ አጠፋለሁ። 
17 ፤ በመዓት መቅሠፍትም ታላቅ በቀል አደርግባቸዋለሁ፤ በቀሌንም በላያቸው ባደረግሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ አንደኛው ዓመት ከወሩ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጢሮስ በኢየሩሳሌም ላይ። እሰይ፥ የአሕዛብ በር የነበረች ተሰብራለች ወደ እኔም ተመልሳለች፤ እርስዋ ፈርሳለችና እኔ እሞላለሁ ብላለችና
3 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጢሮስ ሆይ፥ እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ባሕርም ሞገድዋን እንደምታወጣ እንዲሁ ብዙ አሕዛብን አወጣብሻለሁ።
4 ፤ የጢሮስንም ቅጥሮች ያጠፋሉ ግንቦችዋንም ያፈርሳሉ፤ ትቢያዋንም ከእርስዋ እፍቃለሁ፥ የተራቈተ ድንጋይም አደርጋታለሁ።
5 ፤ በባሕር ውስጥ የመረብ ማስጫ ትሆናለች፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለአሕዛብም ብዝበዛ ትሆናለች።
6 ፤ በሜዳ ያሉትም ሴቶች ልጆችዋ በሰይፍ ይገደላሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
7 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ከሰሜን የነገሥታት ንጉሥ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን ከፈረሶችና ከሰረገሎች ከፈረሰኞችም ከጉባኤና ከብዙ ሕዝብ ጋር በጢሮስ ላይ አመጣለሁ።
8 ፤ በሜዳ ያሉትን ሴቶች ልጆችሽን በሰይፍ ይገድላቸዋል፥ አምባም ይሠራብሻል አፈርንም ይደለድልብሻል ጋሻም ያነሣብሻል።
9 ፤ ማፍረሻውን በቅጥርሽ ላይ ያደርጋል፥ ግንቦችሽንም በምሳር ያፈርሳል።
10 ፤ ከፈረሶቹም ብዛት የተነሣ ትቢያቸው ይከድንሻል፤ ሰዎችም በተናደች ቅጥር ወደ ከተማ እንደሚገቡ እርሱ በበሮችሽ ሲገባ፥ ከፈረሰኞችና ከመንኰራኵሮች ከሰረገሎችም ድምፅ የተነሣ ቅጥርሽ ትናወጣለች።
11 ፤ በፈረሶቹ ኮቴ ጎዳናዎችሽን ሁሉ ይረመርማል፥ ሕዝብሽንም በሰይፍ ይገድላል፥ የብርታትሽም ሐውልት ወደ ምድር ይወድቃል።
12 ፤ ብልጥግናሽንም ይማርካሉ፥ ሸቀጥሽንም ይበዘብዛሉ፤ ቅጥርሽንም ያፈርሳሉ፥ ተድላ የምታደርጊባቸውን ቤቶችሽን ያጠፋሉ፤ ድንጋይሽንና እንጨትሽን መሬትሽንም በባሕር ውስጥ ይጥላሉ።
13 ፤ የዘፋኞችሽንም ብዛት ዝም አሰኛለሁ፤ የመሰንቆሽም ድምፅ ከዚያ ወዲያ አይሰማም።
14 ፤ የተራቈተ ድንጋይ አደርግሻለሁ የመረብም ማስጫ ትሆኛለሽ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አትሠሪም፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
15 ፤ ጌታ እግዚአብሔር ጢሮስን እንዲህ ይላታል። የተወጉት ባንቋረሩ ጊዜ፥ በውስጥሽ እልቂት በሆነ ጊዜ፥ ከውድቀትሽ ድምፅ የተነሣ ደሴቶች ይነዋወጡ የለምን?
16 ፤ የባሕርም አለቆች ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፤ መጐናጸፊያቸውን ያወጣሉ ወርቀ ዘቦ ልብሳቸውንም ያወልቃሉ፤ መንቀጥቀጥን ለብሰው በመሬት ላይ ይቀመጣሉ፥ ሁልጊዜም ይንቀጠቀጣሉ በአንቺም ይደነቃሉ።
17 ፤ በአንቺም ላይ ሙሾ ያሞሻሉ፥ እንዲህም ይሉሻል። በባሕር የተቀመጥሽ በባሕርም ውስጥ የጸናሽ፥ ከሚቀመጡብሽም ጋር በዙሪያሽ የሚኖሩትን ሁሉ ያስፈራሽ፥ የከበርሽ ከተማ ሆይ፥ እንዴት ጠፋሽ!
18 ፤ አሁን በውድቀትሽ ቀን ደሴቶች ይንቀጠቀጣሉ፥ በባሕርም ውስጥ ያለ ደሴቶች ከመጥፋትሽ የተነሣ ይደነግጣሉ።
19 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ሰው እንደሌለባቸው ከተሞች ባድማ ከተማ ባደረግሁሽ ጊዜ፥ ቀላዩንም ባወጣሁብሽ ጊዜ ብዙ ውኆችም በከደኑሽ ጊዜ፥
20 ፤ የቀድሞ ሕዝብ ወዳሉበት ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋር አወርድሻለሁ፤ የሚኖርብሽም እንዳይገኝ ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ቀድሞ በፈረሰችው ስፍራ፥ በታችኛይቱ ምድር አኖርሻለሁ፤ ጌጥሽንም በሕያዋን ምድር አላኖርም። 
21 ፤ ለድንጋጤ አደርግሻለሁ እንግዲህም አትኖሪም፤ ትፈለጊአለሽ ለዘላለምም አትገኚም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ጢሮስ ሙሾ አድርግ፥
3 ፤ በባሕር መግቢያ የምትኖር በብዙም ደሴቶች ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ጋር ንግድን የምታደርግ ጢሮስንም እንዲህ በላት። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጢሮስ ሆይ፥ አንቺ። በውበት ፍጹም ነኝ ብለሻል።
4 ፤ ዳርቻሽ በባሕር ውስጥ ነው፤ ሠሪዎችሽ ውበትሽን ፈጽመዋል።
5 ፤ ሳንቃዎችሽን ሁሉ ከሳኔር ጥድ ሠርተዋል፥ ደቀልንም ይሠሩልሽ ዘንድ ከሊባኖስ ዝግባ ወስደዋል።
6 ፤ ከባሳን ኮምቦል መቅዘፊያሽን ሠርተዋል፥ በዝሆን ጥርስ ከታሻበ ከኪቲም ደሴቶች ዛፍ መቀመጫዎችሽን ሠርተዋል።
7 ፤ ዓላማ እንዲሆንልሽ ሸራሽ ከግብጽ በፍታና ከወርቅ ዘቦ ተሠርቶአል፥ መደረቢያሽም ከኤሊሳ ደሴቶች ሰማያዊና ቀይ ሐር ተሠርቶአል።
8 ፤ የሲዶናና የአራድ ሰዎች ቀዛፎችሽ ነበሩ፤ ጢሮስ ሆይ፥ ጥበበኞችሽ በአንቺ ዘንድ ነበሩ የመርከቦችሽም መሪዎች ነበሩ።
9 ፤ በአንቺ ውስጥ የነበሩ የጌባል ሽማግሌዎችና ጥበበኞችዋ ስብራትሽን ይጠግኑ ነበር፤ ከአንቺም ጋር ይነግዱ ዘንድ የባሕር መርከቦች ሁሉና መርከበኞቻቸው በመካከልሽ ነበሩ።
10 ፤ ፋርስና ሉድ ፉጥም በሠራዊትሽ ሰልፈኞችሽ ነበሩ፤ ጋሻና ራስ ቍርም በአንቺ ውስጥ ያንጠለጥሉ ነበር፤ እነርሱም ውበትሽን ሰጡ።
11 ፤ የአራድ ሰዎችና ሠራዊቶችሽ በቅጥሮችሽ ላይ በዙሪያ ነበሩ፥ ገማዳውያንም በግንቦችሽ ውስጥ ነበሩ፤ ጋሻቸውንም በዙሪያ በቅጥርሽ ላይ አንጠለጠሉ፥ ውበትሽንም ፈጽመዋል።
12 ፤ ከብልጥግናሽ ሁሉ ብዛት የተነሣ ተርሴስ ነጋዴሽ ነበረች፤ በብርና በብረት በቈርቈሮና በእርሳስ ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር።
13 ፤ ያዋንና ቶቤል ሞሳሕም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ የሰዎችን ነፍሳትና የናሱን ዕቃ ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር።
14 ፤ ከቴርጋማ ቤትም የነበሩት ሰዎች በፈረሶችና በፈረሰኞች በበቅሎዎችም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር።
15 ፤ የድዳን ሰዎች ነጋዴዎችሽ ነበሩ። ብዙ ደሴቶች የእጅሽ ገበያዎች ነበሩ፤ ይለውጡ ዘንድ የዝሆን ጥርስና ዞጲ አመጡልሽ።
16 ፤ ከሥራሽ ብዛት የተነሣ ሶርያ ነጋዴሽ ነበረች በበሉርና በቀይ ሐር በወርቀ ዘቦም በጥሩ በፍታም በዛጐልም በቀይ ዕንቍም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር።
17 ፤ ይሁዳና የእስራኤል ምድር ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ የሚኒትን ስንዴ ጣፋጭም እንጐቻ፥ ማር ዘይትም በለሳንም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር።
18 ፤ ከሥራሽ ብዛትና ከብልጥግናሽ ሁሉ ብዛት የተነሣ ደማስቆ ነጋዴሽ ነበረች፤ በኬልቦን የወይን ጠጅ በነጭም በግ ጠጕር ይነግዱ ነበር።
19 ፤ ዌንዳንና ያዋን ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር፤ ከኦሴል የተሠራ ብረትና ብርጕድ ቀረፋም ሸቀጥሽ ነበረ።
20 ፤ ድዳን በከብት ላይ ለመቀመጥ በመረሻት ነጋዴሽ ነበረች።
21 ፤ ዓረብና የቄዳር አለቆች ሁሉ የእጅሽ ነጋዴዎች ነበሩ፤ በጠቦቶችና በአውራ በጎች በፍየሎችም በእነዚህ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር።
22 ፤ የሳባና የራዕማ ነጋዴዎች እነዚህ ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ በጥሩ ሽቶና በክብር ድንጋይ ሁሉ በወርቅም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር።
23 ፤ ካራንና ካኔ ዔድንም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ አሦርና ኪልማድ ነጋዴዎችሽ ነበሩ።
24 ፤ እነዚህ ባማረ ልብስ በሰማያዊ ካባ በወርቀ ዘቦም፥ በዝግባ በተሠራች በገመድም በታሰረች በግምጃም በተሞላች ሳጥን በገበያሽ ይነግዱ ነበር።
25 ፤ የተርሴስ መርከቦች ሸቀጥሽን የሚሸከሙ ነበሩ፤ አንቺም ተሞልተሽ ነበር በባሕርም ውስጥ እጅግ ከበርሽ።
26 ፤ ቀዛፊዎችሽ ወደ ትልቁ ወኃ አመጡሽ፤ የምሥራቅ ነፋስ በባሕር ውስጥ ሰበረሽ።
27 ፤ ብልጥግናሽና ሸቀጥሽ ንግድሽም መርከበኞችሽም መርከብ መሪዎችሽም ሰባራሽንም የሚጠግኑ ነጋዴዎችሽም በአንቺም ዘንድ ያሉ ሰልፈኞችሽ ሁሉ በውስጥሽ ካሉት ጉባኤ ሁሉ ጋር በወደቅሽበት ቀን በባሕር ውስጥ ይወድቃሉ።
28 ፤ ከመርከብ መሪዎች ጩኸት ድምፅ የተነሣ በዙሪያሽ ያሉ ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ።
29 ፤ ቀዛፊዎችም ሁሉ መርከበኞችም መርከብ መሪዎችም ሁሉ ከመርከቦቻቸው ይወርዳሉ በመሬትም ላይ ይቆማሉ፤
30 ፤ ድምፃቸውንም በአንቺ ላይ ያሰማሉ፥ ምርር ብለውም ይጮኻሉ፥ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ይነሰንሳሉ፥ በአመድም ውስጥ ይንከባለላሉ፤
31 ፤ ስለ አንቺም የራሳቸውን ጠጕር ይላጫሉ ማቅም ያሸርጣሉ በነፍስ ምሬትም ስለ አንቺ መራራ ልቅሶ ያለቅሳሉ።
32 ፤ በትካዜያቸውም ልቅሶ ያነሡልሻል፥ ስለ አንቺም ሙሾ ያሞሻሉ እንዲህም ይላሉ። በባሕር መካከል ጠፍቶ እንደ ቀረ እንደ ጢሮስ ያለ ማን ነው?
33 ፤ ሸቀጥሽ ከባሕር በወጣ ጊዜ ብዙ አሕዛብን አጥግበሻል፤ በብልጥግናሽና በንግድሽ ብዛት የምድርን ነገሥታት ባለ ጠጎች አድርገሻል።
34 ፤ አሁን ግን በጥልቅ ውኃ ውስጥ በባህር ተሰብረሻል ንግድሽና ጉባኤሽ ሁሉ በመካከልሽ ወድቀዋል።
35 ፤ በደሴቶሽ የሚኖሩ ሁሉ ተደንቀውብሻል፥ ነገሥታቶቻቸውም እጅግ ፈርተዋል ፊታቸውም ተለውጦአል። 
36 ፤ የአሕዛብ ነጋዴዎች አፍዋጩብሽ፤ አንቺ ለድንጋጤ ሆነሻል፥ እስከ ዘላለምም አትገኚም።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የጢሮስን ገዥ እንዲህ በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ልብህ ኰርቶአል አንተም። እኔ አምላክ ነኝ፥ በእግዚአብሔር ወንበር በባሕር መካከል ተቀምጫለሁ ብለሃል፤ ነገር ግን ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ ብታደርግም አንተ ሰው ነህ እንጂ አምላክ አይደለህም።
3 ፤ እነሆ፥ ከዳንኤል ይልቅ ጥበበኛ ነህ፥ ምሥጢርም ሁሉ ከአንተ የተሸሸገ አይደለም።
4 ፤ በጥበብህና በማስተዋልህ ብልጥግናን ለራስህ አግኝተሃል ወርቅና ብርም በግምጃ ቤትህ ውስጥ ሰብስበሃል።
5 ፤ በታላቅ ጥበብህና በንግድህ ብልጥግናህን አብዝተሃል በብልጥግናህም ልብህ ኰርቶአል።
6 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ አድርገሃልና
7 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሌላ አገር ሰዎችን፥ የአሕዛብን ጨካኞች፥ አመጣብሃለሁ፤ ሰይፋቸውንም በጥበብህ ውበት ላይ ይመዝዛሉ ክብርህንም ያረክሳሉ።
8 ፤ ወደ ጕድጓድ ያወርዱሃል፤ ተገድለው እንደ ሞቱ በባሕር ውስጥ ትሞታለህ።
9 ፤ በውኑ በገዳይህ ፊት። እኔ አምላክ ነኝ ትላለህን? ነገር ግን በገዳይህ እጅ ሰው ነህ እንጂ አምላክ አይደለህም።
10 ፤ በእንግዶች እጅ ያልተገረዙትን ሰዎች ሞት ትሞታለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
11 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
12 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በጢሮስ ንጉሥ ላይ ሙሾ አሞሽተህ እንዲህ በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጥበብን የተሞላህ ውበትህም የተፈጸመ መደምደሚያ አንተ ነህ።
13 ፤ በእግዚአብሔር ገነት በዔድን ነበርህ፤ የከበረ ዕንቍስ ሁሉ፥ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ አልማዝ፥ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ፥ ሰንፔር፥ በሉር፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ወርቅ፥ ልብስህ ነበረ፤ የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ፤ በተፈጠርህበት ቀን ተዘጋጅተው ነበር።
14 ፤ አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ተራራ ላይ አኖርሁህ፤ በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ።
15 ፤ ከተፈጠርህበት ቀን ጀምረህ በደል እስኪገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍጹም ነበርህ።
16 ፤ በንግድህ ብዛት ግፍ በውስጥህ ተሞላ ኃጢአትንም ሠራህ፤ ስለዚህ እንደ ርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ተራራ ጣልሁህ፤ የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ፥ ከእሳት ድንጋዮች መካከል አጠፋሁህ።
17 ፤ በውበትህ ምክንያት ልብህ ኰርቶአል፤ ከክብርህ የተነሣ ጥበብህን አረከስህ፤ በምድር ላይ ጣልሁህ ያዩህም ዘንድ በነገሥታት ፊት ሰጠሁህ።
18 ፤ በበደልህ ብዛት በንግድህም ኃጢአት መቅደስህን አረከስህ፤ ስለዚህ እሳትን ከውስጥህ አውጥቻለሁ እርስዋም በልታሃለች፥ በሚያዩህም ሁሉ ፊት በምድር ላይ አመድ አድርጌሃለሁ።
19 ፤ በአሕዛብም ውስጥ የሚያውቁህ ሁሉ ይደነቁብሃል፤ አንተም ለድንጋጤ ሆነሃል፥ እስከ ዘላለምም አትገኝም።
20 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
21 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ሲዶና አቅንተህ ትንቢት ተናገርባት፥ እንዲህም በል።
22 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሲዶና ሆይ፥ እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ በውስጥሽም እከብራለሁ፤ ፍርድንም ባደረግሁባት ጊዜ በተቀደስሁባትም ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
23 ፤ ቸነፈርንም በእርስዋ ላይ፥ ደምንም በጎዳናዋ እሰድዳለሁ፤ ከዙሪያዋ በላይዋ ባለ ሰይፍ የተወጉ በመካከልዋ ይወድቃሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
24 ፤ ከእንግዲህም ወዲያ ለእስራኤል ቤት የሚወጋ እሾህ፥ በዙሪያቸውም ካሉ ካናቋቸው ሁሉ የሚያቈስል ኵርንችት አይሆንም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
25 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእስራኤልን ቤት ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ በሰበሰብሁ ጊዜ፥ በአሕዛብም ፊት በተቀደስሁባቸው ጊዜ፥ ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድራቸው ይቀመጣሉ። 
26 ፤ ተዘልለውም ይቀመጡባታል፤ ቤቶችንም ይሠራሉ ወይኑንም ይተክላሉ በዙሪያቸውም ባሉ በሚንቋቸው ሁሉ ላይ ፍርድን ባደረግሁ ጊዜ ተዘልለው ይቀመጣሉ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

1 ፤ በአሥረኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሁለተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ አድርግ፥ በእርሱና በግብጽ ሁሉ ላይም ትንቢት ተናገር፥
3 ፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በወንዞች መካከል የምትተኛና። ወንዙ የእኔ ነው ለራሴም ሠርቼዋለሁ የምትል ታላቅ አዞ፥ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ሆይ፥ እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ።
4 ፤ በመንጋጋህ መቃጥን አገባብሃለሁ፥ የወንዞችህንም ዓሦች ወደ ቅርፊትህ አጣብቃለሁ፤ ከወንዞችህም መካከል አወጣሃለሁ፥ የወንዞችህም ዓሦች ሁሉ ወደ ቅርፊትህ ይጣበቃሉ።
5 ፤ አንተንና የወንዞችህን ዓሦች ሁሉ ወደ ምድረ በዳ እጥላለሁ፥ በምድርም ፊት ላይ ትወድቃለህ እንጂ አትከማችም አትሰበሰብም መብልም አድርጌ ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች ሰጥቼሃለሁ።
6 ፤ በግብጽም የሚኖሩ ሁሉ ለእስራኤል ቤት የሸንበቆ በትር ሆነዋልና እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
7 ፤ በእጅ በያዙህ ጊዜ ተሰበርህ ጫንቃቸውንም ሁሉ አቈሰልህ፤ በተደገፉብህም ጊዜ ተሰበርህ ወገባቸውንም ሁሉ አንቀጠቀጥህ።
8 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሰይፍ አመጣብሃለሁ፥ ሰውንና እንስሳንም ከአንተ ዘንድ አጠፋለሁ።
9 ፤ የግብጽም ምድር ባድማና ውድማ ትሆናለች፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ አንተ። ወንዙ የእኔ ነው የሠራሁትም እኔ ነኝ ብለሃልና።
10 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ በአንተና በወንዞችህ ላይ ነኝ፥ የግብጽንም ምድር ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔና እስከ ኢትዮጵያ ዳርቻ ድረስ ውድማና ባድማ አደርጋታለሁ።
11 ፤ የሰው እግር አያልፍባትም የእንስሳም ኮቴ አያልፍባትም፥ እስከ አርባ ዓመትም ድረስ ማንም አይኖርባትም።
12 ፤ ባድማም በሆኑ ምድሮች መካከል የግብጽን ምድር ባድማ አደርጋታለሁ፥ በፈረሱትም ከተሞች መካከል ከተሞችዋ አርባ ዓመደ ፈርሰው ይቀመጣሉ፤ ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናቸዋለሁ በአገሮችም እዘራቸዋለሁ።
13 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከአርባ ዓመት በኋላ ግብጻውያንን ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ እሰበስባለሁ፤
14 ፤ የግብጽንም ምርኮ እመልሳለሁ፥ ወደ ተወለዱባትም ምድር ወደ ጳትሮስ እመልሳቸዋለሁ፤ በዚያም የተዋረደች መንግሥት ይሆናሉ።
15 ፤ ከሌሎች መንግሥታት ሁሉ ይልቅ የተዋረደች ትሆናለች፤ ከእንግዲህ ወዲያ በአሕዛብ ላይ ከፍ አትልም፤ በአሕዛብም ላይ እንዳይገዙ አሳንሳቸዋለሁ።
16 ፤ የእስራኤል ቤት እነርሱን በተከተሉ ጊዜ እርስዋ በደልን ታሳስባለች፥ ከእንግዲህም ወዲያ መታመኛ አትሆንላቸውም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
17 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በሀያ ሰባተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
18 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሠራዊቱን በጢሮስ ላይ ጽኑ አገልግሎት አስገለገለ፤ ራስ ሁሉ የተላጨ ጫንቃም ሁሉ የተላጠ ሆኖአል፤ ነገር ግን በላይዋ ስላገለገለው አገልግሎት እርሱና ሠራዊቱ ደመወዝ ከጢሮስ አልተቀበሉም።
19 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የግብጽን ምድር ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጠዋለሁ፥ ብዛትዋንም ይወስዳል ምርኮዋንም ይማርካል ብዝበዛዋንም ይበዘብዛል፤ ይህም ለሠራዊቱ ደመወዝ ይሆናል።
20 ፤ ስለ እኔ ሠርተዋልና ስለ አገልግሎቱ ደመወዝ የግብጽን ምድር ሰጥቼዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 
21 ፤ በዚያ ቀን ለእስራኤል ቤት ቀንድን አበቅላለሁ፥ በመካከላቸውም ለአንተ የተከፈተ አፍን እሰጣለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዋይ! በሉ፥ ለቀኑ ወዮ! ቀኑ ቅርብ ነው፥
3 ፤ የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የአሕዛብ ጊዜ ይሆናል።
4 ፤ ሰይፍ በግብጽ ላይ ይመጣል፥ ሁከትም በኢትዮጵያ ይሆናል፤ የተገደሉትም በግብጽ ውስጥ ይወድቃሉ፥ ብዛትዋንም ይወስዳሉ፥ መሠረትዋም ይፈርሳል።
5 ፤ ኢትዮጵያና ፉጥ ሉድም የተደባለቀም ሕዝብ ሁሉ ኩብም ቃል ኪዳንም የገባችው ምድር ልጆች ከእነርሱ ጋር በሰይፍ ይወድቃሉ።
6 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ግብጽን የሚደግፉ ይወድቃሉ፥ የኃይልዋም ትዕቢት ይወርዳል፤ ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔ ድረስ በእርስዋ ውስጥ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
7 ፤ ባድማም በሆኑ አገሮች መካከል ባድማ ይሆናሉ፥ ከተሞችዋም በፈረሱ ከተሞች መካከል ይሆናሉ።
8 እሳትንም በግብጽ ባነደድሁ ጊዜ ረዳቶችዋም ሁሉ በተሰበሩ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
9 በዚያ ቀን መልእክተኞች ተዘልለው የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንን ለማስፈራት ከፊቴ በመርከብ ይወጣሉ፤ እንደ ግብጽም ቀን ሁከት ይሆንባቸዋል፤ እነሆ፥ ይመጣልና።
10 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የግብጽን ብዛት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ እሽራለሁ።
11 እርሱና የአሕዛብ ጨካኞች ሕዝቡ ምድሪቱን ለማጥፋት ይመጣሉ፤ ሰይፋቸውንም በግብጽ ላይ ይመዝዛሉ ምድሪቱንም በተገደሉት ይሞላሉ።
12 ፤ ወንዞችንም ምድረ በዳ አደርጋለሁ ምድሪቱንም በክፉ ሰዎች እጅ እሸጣለሁ፥ ምድሪቱንና ሙላዋንም በእንግዶች እጅ ባድማ አደርጋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬያለሁ።
13 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጣዖቶቹን አጠፋለሁ ምስሎችንም ከሜምፎስ እሽራለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ በግብጽ ምድር አለቃ አይሆንም፥ በግብጽም ምድር ላይ ፍርሃትን አደርጋለሁ።
14 ፤ ጳትሮስንም አፈርሳለሁ፥ በጣኔዎስም እሳትን አነድዳለሁ፥ በኖእ ላይም ፍርድን አደርጋለሁ።
15 ፤ በግብጽም ምሽግ በሲን ላይ መዓቴን አፈስሳለሁ፥ የኖእንም ብዛት አጠፋለሁ።
16 ፤ በግብጽም እሳትን አነድዳለሁ፥ ሲንም ትጨነቃለች ኖእም ትሰበራለች፥ በሜምፎስም በየቀኑ ጠላቶች ይሆኑባታል።
17 ፤ የሄልዮቱ ከተማና የቡባስቱም gWlማሶች በሰይፍ ይወድቃሉ ሴቶችም ይማረካሉ።
18 ፤ የግብጽን ቀንበር በዚያ በሰበርሁ ጊዜ በጣፍናስ ቀኑ ይጨልማል የኃይልዋም ትዕቢት ይጠፋባታል፤ ደመናም ይጋርዳታል፥ ሴቶች ልጆችዋም ይማረካሉ።
19 ፤ እንዲሁ በግብጽ ላይ ፍርድን አደርጋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
20 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ አንደኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
21 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የግብጽን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬያለሁ፤ እነሆም፥ በጨርቅ በመጠቅለል ይፈወስ ዘንድ ሰይፉንም ለመያዝ እንዲበረታ አልታሰረም።
22 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እኔ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ነኝ፥ የጸናችውንና የተሰበረችውንም ክንዱን እሰብራለሁ፥ ሰይፉንም ከእጁ አስረግፈዋለሁ።
23 ፤ ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናለሁ ወደ አገሮችም እዘራቸዋለሁ።
24 ፤ የባቢሎንንም ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ ሰይፌንም በእጁ እሰጣለሁ፤ የፈርዖንን ክንድ ግን እሰብራለሁ፥ ተወግቶም በሚሞተው እንጕርጕሮ በፊቱ ያንጐራጕራል።
25 ፤ የባቢሎንንም ንጉሥ ክንድ አጸናለሁ የፈርዖንም ክንድ ይወድቃል፤ ሰይፌንም በባቢሎን ንጉሥ እጅ በሰጠሁ ጊዜ እርሱም በግብጽ ምድር ላይ በዘረጋው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 
26 ፤ ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናለሁ ወደ አገሮችም እዘራቸዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ አንደኛው ዓመት በሦስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንንና የሕዝቡን ብዛት እንዲህ በላቸው። በታላቅነትህ ማንን መስለሃል?
3 ፤ እነሆ፥ አሦር ጫፉ እንደ ተዋበ፥ ችፍግነቱ ጥላ እንደ ሰጠ፥ ቁመቱም እንደ ረዘመ፥ ራሱም በደመናዎች መካከል እንደ ነበረ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ነበረ።
4 ፤ ውኆችም አበቀሉት፥ ቀላይም አሳደገው፥ ወንዞችም በተተከለበት ዙሪያ ይጐርፉ ነበር፥ ፈሳሾቹንም ወደ ምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ ሰደደ።
5 ፤ ስለዚህ ቁመቱ ከምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ አለ፥ ቅርንጫፎቹም በዙ፥ ጫፎቹንም ባበቀለ ጊዜ ከብዙ ውኆች የተነሣ ረዘሙ።
6 ፤ የሰማይ ወፎች ሁሉ ጎጆቻቸውን በቅርንጫፎቹ ላይ አደረጉ፥ የምድርም አራዊት ሁሉ ከጫፎቹ በታች ተዋለዱ፥ ከጥላውም በታች ታላላቆች አሕዛብ ሁሉ ይቀመጡ ነበር።
7 ፤ ሥሩም በብዙ ውኃ አጠገብ ነበረና በታላቅነቱና በጫፎቹ ርዝመት የተዋበ ነበረ።
8 ፤ በእግዚአብሔር ገነት የነበሩ ዝግባዎች አላጨለሙትም፥ ጥዶችም ቅርጫፎቹን አስታ የሚባለውም ዛፍ ጫፎቹን አይመሳሰሉትም ነበር፤ የእግዚአብሔርም ገነት ዛፍ ሁሉ በውበቱ አይመሳሰለውም ነበር።
9 ፤ በጫፎቹም ብዛት ውብ አደረግሁት በእግዚአብሔርም ገነት በዔድን የነበሩ ዛፎች ሁሉ ቀኑበት።
10 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ቁመትህ ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ ራሱንም በደመናዎች መካከል አድርጎአልና፥
11 ፤ ልቡም በቁመቱ ኰርቶአልና ከአሕዛብ በጨካኙ እጅ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እርሱም እንደ ክፋቱ መጠን ያደርግበታል እኔም አሳድደዋለሁ።
12 ፤ የሌላ አገር ሰዎች፥ የአሕዛብ ጨካኞች የሆኑ፥ ቈርጠው ጣሉት፤ በተራሮችና በሸለቆች ሁሉ ውስጥ ጫፎቹ ወደቁ፥ ቅርንጫፎቹም በምድር ፈሳሾች ሁሉ ላይ ተሰባበሩ፥ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ከጥላው ተመልሰው ተዉት።
13፤14 ፤ ወደ ጕድጓድ በሚወርዱ በሰው ልጆች መካከል ሁላቸው ለታችኛው ምድር ለሞት አልፈው ተሰጥተዋልና በውኃ አጠገብ ያሉ ዛፎች ሁሉ በቁመታቸው እንዳይረዝሙ፥ ራሳቸውንም በደመናዎች መካከል እንዳያደርጉ፥ ውኃንም የሚጠጡ ኃያላኖቻቸው ሁሉ በቁመታቸው እንዳይቆሙ፥ በወደቀው ግንድ ላይ የሰማይ ወፎች ሁሉ ይቀመጣሉ የምድርም አራዊት ሁሉ በቅርንጫፎቹ ላይ ይሆናሉ።
15 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ ሲኦል በወረደበት ቀን ልቅሶ አስለቀስሁ፤ ቀላዩንም ስለ እርሱ ሸፈንሁት ፈሳሾቹንም ከለከልሁ ታላላቆችም ውኆች ተከለከሉ፤ ሊባኖስንም ስለ እርሱ አሳዘንሁት፥ የዱርም ዛፎች ሁሉ ስለ እርሱ ዛሉ።
16 ፤ ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ወደ ሲኦል በጣልሁት ጊዜ ከመውደቁ ድምፅ የተነሣ አሕዛብን እንቀጠቀጥሁ፤ ውኃም የሚጠጡ ሁሉ፥ ምርጦችና መልካካሞች የሊባኖስ ዛፎች፥ የዔድን ዛፎች ሁሉ በታችኛው ምድር ውስጥ ተጽናንተዋል።
17 ፤ ክንዱም ወደ ነበሩት በአሕዛብም መካከል በጥላው ወደ ተቀመጡት፥ በሰይፍ ወደ ተገደሉት ሰዎች ወደ ሲኦል ከእርሱ ጋር ወረዱ። 
18 ፤ በክብርና በታላቅነት በዔድን ዛፎች መካከል ማንን መስለሃል? ነገር ግን ከዔድን ዛፎች ጋር ወደ ታችኛው ምድር ያወርዱሃል፥ በሰይፍም በተገደሉት ባልተገረዙት መካከል ትተኛለህ። ይህም ፈርዖንና የሕዝቡ ብዛት ሁሉ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በለው። የአሕዛብን አንበሳ መስለህ ነበር፥ ነገር ግን እንደ ባሕር ዘንዶ ሆነሃል፤ በወንዞችህም ወጥተሃል፥ ወኃውንም በእግርህ አደፍርሰሃል፥ ወንዞችህንም አሳድፈሃል።
3 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በብዙ አሕዛብ ጉባኤ መረቤን እዘረጋብሃለሁ፥ እነርሱም በመረቤ ያወጡሃል።
4 ፤ በምድርም ላይ እተውሃለሁ፥ በምድረ በዳም ፊት እጥልሃለሁ፥ የሰማይንም ወፎች ሁሉ አሳርፍብሃለሁ፥ የምድርንም አራዊት ሁሉ ከአንተ አጠግባቸዋለሁ።
5 ፤ ሥጋህን በተራሮች ላይ አደርጋለሁ ሸለቆቹንም በሬሳህ ክምር እሞላለሁ።
6 ፤ የምትዋኝባትንም ምድር እስከ ተራሮች ድረስ በደምህ አጠጣለሁ፥ መስኖችም ከአንተ ይሞላሉ።
7 ፤ ባጠፋሁህም ጊዜ ሰማዮችን እሸፍናለሁ፥ ከዋክብቶችንም አጨልማለሁ፤ ፀሐዩንም በደመና እሸፍናለሁ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም።
8 ፤ የሰማይን ብርሃኖች ሁሉ በላይህ አጨልማለሁ፥ በምድርህም ላይ ጨለማ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
9 ፤ በማታውቃቸውም አገሮች ባሉ በአሕዛብ ዘንድ ጥፋትህን ባመጣሁ ጊዜ የብዙ ሕዝብን ልብ አስጨንቃለሁ።
10 ፤ ብዙም አሕዛብን አስደንቅብሃለሁ ሰይፌንም በፊታቸው ባወዛወዝሁ ጊዜ ነገሥታቶቻቸው ስለ አንተ እጅግ አድርገው ይፈራሉ፤ በወደቅህበትም ቀን እያንዳንዱ ስለ ነፍሱ በየጊዜው ሁሉ ይንቀጠቀጣል።
11 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ ይመጣብሃል።
12 ፤ በኃያላን ሰይፍ የሕዝብህን ብዛት እጥላለሁ፤ ሁሉ የአሕዛብ ጨካኞች ናቸው፤ የግበጽንም ትዕቢት ያጠፋሉ ብዛትዋም ሁሉ ይጠፋል።
13 ፤ በብዙም ውኃ አጠገብ ያሉትን እንስሶች ሁሉ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ የሰው እግር አያደፈርሰውም የእንስሳም ኮቴ አይረግጠውም።
14 ፤ በዚያን ጊዜ ውኃቸውን አጠራለሁ፥ ወንዞቻቸውም እንደ ዘይት እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15 ፤ የግብጽንም ምድር ባድማና ውድማ ባደረግሁ ጊዜ፥ ሞላዋንም ያጣች ምድር ባደረግኋት ጊዜ፥ የሚኖሩባትንም ሁሉ በቀሠፍሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
16 ፤ የሚያለቅሱበት ልቅሶ ይህ ነው፤ የአሕዛብ ቈነጃጅት ያለቅሱበታል፤ ስለ ግብጽና ስለ ብዛትዋ ሁሉ ያለቅሱበታል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
17 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
18 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ብዛት ዋይ በል፥ እርስዋንና የብርቱዎችን አሕዛብ ሴቶች ልጆች ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ወደ ታችኛው ምድር ጣላቸው።
19 ፤ በውበት የምትበልጪው ማን ነው? ውረጂ ካልተገረዙትም ጋር ተኚ።
20 ፤ በሰይፍ በተገደሉት መካከል ይወድቃሉ፤ ለሰይፍ ተሰጥታለች፤ እርስዋንና ብዛትዋን ሁሉ ጐትቱ።
21 ፤ የኃያላን አለቆች በሲኦል ውስጥ ሆነው ከረዳቶቹ ጋር ይናገሩታል፤ በሰይፍም የተገደሉት ያልተገረዙ ወርደው ተኝተዋል።
22 ፤ አሦርና ጉባኤዋ ሁሉ በዚያ አሉ፤ መቃብራቸው በዙሪያቸው ነው፤ ሁሉም በሰይፍ ወድቀው ተገደሉ።
23 ፤ መቃብራቸው በጕድጓዱ በውስጠኛው ክፍል ነው፥ ጉባኤዋም በመቃብርዋ ዙሪያ ነው፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል።
24 ፤ ኤላምም በዚያ አለች ብዛትዋም ሁሉ በመቃብርዋ ዙሪያ ነው፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል ሳይገረዙም ወደ ታችኛው ምድር ወርደዋል፥ ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል።
25 ፤ በተገደሉት መካከል ከብዛትዋ ሁሉ ጋር መኝታን አድርገውላታል፤ መቃብርዋ በዙሪያዋ ነው ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የተገደሉ ናቸው፤ በሕያዋንም ምድር ያስፈሩ ነበር ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል፥ በተገደሉትም መካከል ተሰጥተዋል።
26 ፤ ሞሳሕና ቶቤል ብዛታቸውም ሁሉ በዚያ አሉ መቃብራቸውም በዙሪያቸው ነው፤ ሁሉም ሳይገረዙ በሰይፍ ተገድለዋል፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ነበርና።
27 ፤ በሕያዋንም ምድር ኃያላኑን ያስፈሩ ነበርና መሣሪያቸውን ይዘው ወደ ሲኦል ከወረዱ፥ ሰይፋቸውንም ከራሳቸው በታች ካደረጉ፥ ኃጢአታቸውም በአጥንታቸው ላይ ከሆነ ጋር ከወደቁ ካልተገረዙ ኃያላን ጋር ይተኛሉ።
28 ፤ አንተም ባልተገረዙት መካከል ትሰበራለህ፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ትተኛለህ።
29 ፤ ኤዶምያስና ነገሥታቶችዋ አለቆችዋም ሁሉ በዚያ አሉ፤ በሰይፍ ከተገደሉት ጋር በኃይላቸው ተኝተዋል፤ ካልተገረዙትና ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ይተኛሉ።
30 ፤ የሰሜን አለቆች ሁሉ ሲዶናውያንም ሁሉ ከተገደሉት ጋር ወርደው በዚያ አሉ፤ በኃይላቸውም ያስፈሩ በነበረው ፍርሃት አፍረዋል፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ሳይገረዙ ተኝተዋል፥ ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱት ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል።
31 ፤ በሰይፍ የተገደሉ ፈርዖንና ሠራዊቱ ሁሉ ያዩአቸዋል ፈርዖንም ስለ ብዛቱ ሁሉ ይጽናናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 
32 ፤ መፈራቱን በሕያዋን ምድር አድርጌአለሁ፥ ፈርዖንና ብዛቱም ሁሉ በሰይፍ በተገደሉት ባልተገረዙት መካከል ይተኛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለሕዝብህ ልጆች ተናገር እንዲህም በላቸው። ሰይፍን በምድር ላይ ባመጣሁ ጊዜ፥ የምድር ሕዝብ ከመካከላቸው ሰውን ወስደው ለራሳቸው ጕበኛ ቢያደርጉ፥
3 ፤ እርሱም በምድር ላይ የመጣውን ሰይፍ ባየ ጊዜ መለከትን ቢነፋ ሕዝቡንም ቢያስጠነቅቅ፥
4 ፤ የመለከቱን ድምፅ የሚሰማ ሰው ባይጠነቀቅ፥ ሰይፍ መጥቶ ቢወስደው፥ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል።
5 ፤ የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ስላልተጠነቀቀ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅስ ኖሮ ነፍሱን ባዳነ ነበር።
6 ፤ ጕበኛው ግን ሰይፍ ሲመጣ ቢያይ መለከቱንም ባይነፋ ሕዝቡንም ባያስጠነቅቅ ሰይፍም መጥቶ አንድ ሰው ከእርሱ ቢወስድ፥ እርሱ በኃጢአቱ ተወስዶአል ደሙን ግን ከጕበኛው እጅ እፈልጋለሁ።
7 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፤ ከአፌ ቃሌን ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው።
8 ፤ ኃጢአተኛውን። ኃጢአተኛ ሆይ፥ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ ኃጢአተኛውን ከመንገዱ ታስጠነቅቅ ዘንድ ባትናገር ያ ኃጢአተኛ በኃጢአቱ ይሞታል፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።
9 ፤ ነገር ግን ከመንገዱ ይመለስ ዘንድ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቀው እርሱም ከመንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል።
10 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤልን ቤት። እናንተ። በደላችንና ኃጢአታችን በላያችን አሉ እኛም ሰልስለንባቸዋል፤ እንዴትስ በሕይወት እንኖራለን? ብላችሁ ተናግራችኋል በላቸው።
11 ፤ እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ተመለሱ፥ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው።
12 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህን ልጆች እንዲህ በላቸው። በበደለበት ቀን የጻድቅ ጽድቁ አያድነውም፥ ኃጢአተኛም ከኃጢአቱ በተመለሰበት ቀን በኃጢአቱ አይሰናከልም፤ ጻድቁም ኃጢአት በሠራበት ቀን በጽድቁ በሕይወት አይኖርም።
13 ፤ እኔ ጻድቁን። በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ በጽድቁ ታምኖ ኃጢአት ቢሠራ በሠራው ኃጢአት ይሞታል እንጂ ጽድቁ አይታሰብለትም።
14 ፤ እኔም ኃጢአተኛውን። በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥
15 ፤ ኃጢአተኛውም መያዣን ቢመልስ የነጠቀውንም ቢመልስ በሕይወትም ትእዛዝ ቢሄድ ኃጢአትም ባይሠራ፥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።
16 ፤ የሠራው ኃጢአት ሁሉ አይታሰብበትም፤ ፍርድንና ቅን ነገርን አድርጎአል፤ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።
17 ፤ ነገር ግን የሕዝብህ ልጆች። የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ይላሉ፤ ነገር ግን የእነርሱ መንገድ የቀና አይደለም።
18 ፤ ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአትን ቢሠራ ይሞትባታል።
19 ፤ ኃጢአተኛውም ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ በሕይወት ይኖርበታል።
20 ፤ እናንተ ግን። የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።
21 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በተማረክን በአሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ። ከተማይቱ ተመታች አለኝ።
22 ፤ ያመለጠውም ሳይመጣ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ በነጋውም ወደ እኔ እስኪመጣ ድረስ አፌን ከፈተ፤ አፌም ተከፈተች ከዚያም በኋላ እኔ ዲዳ አልሆንሁም።
23 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
24 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር ባሉ በባድማ ስፍራዎች የተቀመጡ። አብርሃም ብቻውን ሳለ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛም ብዙዎች ነን ምድሪቱም ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች ይላሉ።
25 ፤ ስለዚህ እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከደም ጋር ትበላላችሁ፥ ዓይናችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፥ ደምንም ታፈስሳላችሁ፤ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን?
26 ፤ ሰይፋችሁን ይዛችሁ ቆማችኋል፥ ርኩስ ነገርን ታደርጋላችሁ፥ የባልንጀሮቻችሁንም ሚስቶች ታስነውራላችሁ፤ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን?
27 ፤ እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና በባድማ ስፍራዎች ያሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ በምድረ በዳ ያለውን ለአራዊት መብል አድርጌ እሰጣለሁ፥ በአምባዎችና በዋሾች ያሉ በቸነፈር ይሞታሉ።
28 ፤ ምድሪቱንም ባድማና ውድማ አደርጋታለሁ የኃይልዋም ትዕቢት ይቀራል፥ የእስራኤልም ተራሮች ባድማ ይሆናሉ፥ ማንም አያልፍባቸውም።
29 ፤ ስላደረጉትም ርኵሰት ሁሉ ምድሪቱን ባድማና ውድማ ባደርግሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
30 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህ ልጆች በቅጥር አጠገብና በቤት ደጆች ውስጥ ስለ አንተ ይናገራሉ፥ እርስ በርሳቸውም፥ አንዱ ከአንዱ ጋር። እንሂድና እግዚአብሔር ያለው ቃል ምን እንደ ሆነ እንስማ ብለው ይናገራሉ።
31 ፤ ሕዝብ እንደሚመጣ ወደ አንተ ይመጣሉ፥ እንደ ሕዝቤም በፊትህ ይቀመጣሉ፥ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም፤ በአፋቸው ብዙ ፍቅር ይገልጣሉ፥ ልባቸው ግን ስስታቸውን ትከተላለች።
32 ፤ እነሆ፥ አንተ መልካም ድምፅ እንዳለው እንደሚወደድ መዝሙር ማለፊያም አድርጎ በገና እንደሚጫወት ሰው ሆነህላቸዋል፤ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም። 
33 ፤ እነሆ፥ ይህ ይመጣል፤ በመጣም ጊዜ እነርሱ ነቢይ በመካከላቸው እንደ ነበረ ያውቃሉ።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፥ እረኞችንም እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን?
3 ፤ ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም።
4 ፤ የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው።
5 ፤ እረኛንም በማጣት ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም።
6 ፤ በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በጎቼም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ የሚሻም የሚፈልግም አልነበረም።
7 ፤ ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤
8 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና እረኛ ስለሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና
9 ፤ ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤
10 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በእረኞች ላይ ነኝ፥ በጎቼንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ በጎቼንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያሰማሩም፤ በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም።
11 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ እፈልግማለሁ።
12 ፤ እረኛ በተበተኑት በጎች መካከል ባለ ጊዜ መንጋውን እንደሚፈልግ፥ እንዲሁ በጎቼን እፈልጋለሁ፤ በደመናና በጨለማ ቀን ከተበተኑት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ።
13 ፤ ከአሕዛብም ዘንድ አወጣቸዋለሁ ከአገሮችም እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ አገራቸውም አመጣቸዋለሁ፤ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በፈሳሾችም አጠገብ በምድርም ላይ ሰዎች በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ አሰማራቸዋለሁ።
14 ፤ በመልካም ማሰማርያ እሰማራቸዋለሁ ጕረኖአቸውም በረጅሞቹ በእስራኤል ተራሮች ላይ ይሆናል፤ በዚያ በመልካም ጕረኖ ውስጥ ይመሰጋሉ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ ማሰማርያ ይሰማራሉ።
15 ፤ እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ አስመስጋቸውማለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
16 ፤ የጠፋውንም እፈልጋለሁ የባዘነውንም እመልሳለሁ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውንም አጠፋለሁ፤ በፍርድም እጠብቃቸዋለሁ።
17 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እናንተም መንጋዬ ሆይ፥ እነሆ፥ በበግና በበግ መካከል፥ በአውራ በግና በአውራ ፍየልም መካከል፥ እፈርዳለሁ።
18 ፤ የቀረውን ማሰማርያችሁን በእግራችሁ የረገጣችሁት፥ በመልካሙ ማሰማርያ መሰማራታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? የቀረውንስ ውኃ በእግራችሁ ያደፈረሳችሁት፥ ጥሩውን ውኃ መጠጣታችሁ ባይበቃችሁ ነውን?
19 ፤ በጎቼም በእግራችሁ በረገጣችሁት ይሰማራሉ በእግራችሁም ያደፈረሳችሁትን ይጠጣሉ።
20 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል። እነሆ፥ እኔ በወፈሩት በጎችና በከሱት በጎች መካከል እፈርዳለሁ።
21 ፤ እስክትበትኑአቸው ድረስ በእንቢያና በትከሻ ስለምትገፉአቸው የደከሙትንም ሁሉ በቀንዳችሁ ስለምትወጉአቸው፥
22 ፤ ስለዚህ መንጋዬን አድናለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ንጥቂያ አይሆኑም፤ በበግና በበግ መካከልም እፈርዳለሁ።
23 ፤ በላያቸውም አንድ እረኛ አቆማለሁ እርሱም ያሰማራቸዋል፥ እርሱም ባሪያዬ ዳዊት ነው፤ ያሰማራቸዋል እረኛም ይሆናቸዋል።
24 ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላክ እሆናቸዋለሁ ባሪያዬም ዳዊት በመካከላቸው አለቃ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።
25 ፤ የሰላምን ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር እገባለሁ ክፉዎችንም አራዊት ከምድር አጠፋለሁ፤ ተዘልለውም በምድረ በዳ ይኖራሉ በዱርም ውስጥ ይተኛሉ።
26 ፤ እነርሱንና በኮረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች ለበረከት አደርጋቸዋለሁ፥ ዝናቡንም በጊዜው አወርዳለሁ፤ የበረከት ዝናብ ይሆናል።
27 ፤ የምድረ በዳም ዛፍ ፍሬውን ይሰጣል ምድርም ቡቃያዋን ትሰጣለች፥ በምድራቸውም ተዘልለው ይኖራሉ የቀንበራቸውንም ማነቆ በሰበርሁ ጊዜ ከሚገዙአቸውም እጅ ባዳንኋቸው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
28 ፤ እንግዲህም ለአሕዛብ ንጥቂያ አይሆኑም የምድርም አራዊት አይበሉአቸውም፤ ተዘልለውም ይቀመጣሉ የሚያስፈራቸውም የለም።
29 ፤ የዝናን ተክል አቆምላቸዋለሁ እንግዲህም ከራብ የተነሣ በምድር አያልቁም፤ የአሕዛብንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አይሸከሙም።
30 ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ከእነርሱ ጋር እንዳለሁ፥ እነርሱም የእስራኤል ቤት ሕዝቤ እንደ ሆኑ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 
31 ፤ እናንተም በጎቼ፥ የማሰማርያዬ በጎች፥ ሰዎች ናችሁ እኔም አምላካችሁ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ሴይር ተራራ አድርግ፥ ትንቢትም ተናገርበት፥
3 ፤ እንዲህም በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሴይር ተራራ ሆይ፥ እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ እጄንም እዘረጋብሃለሁ ባድማና ውድማም አደርግሃለሁ።
4 ፤ ከተሞችህንም አፈራርሳቸዋለሁ፥ አንተም ባድማ ትሆናለህ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ።
5 ፤ የዘላለም ጥል ስላለህ በመከራቸውም ጊዜ በኋለኛይቱ የኃጢአታቸው ቀጠሮ ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በሰይፍ እጅ ጥለሃቸዋልና
6 ፤ ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና ለደም አሳልፌ እሰጥሃለሁ ደምም ያሳድድሃል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ደምን ስላልጠላህ ደም ያሳድድሃል።
7 ፤ የሴይርንም ተራራ ውድማ አደርገዋለሁ፥ የሚሄደውንና የሚመለሰውንም ከእርሱ አጠፋለሁ።
8 ፤ ተራሮቹንም በተገደሉት ሰዎች እሞላለሁ፤ በኮረብቶችህና በሸለቆችህ በፈሳሾችህም ሁሉ ላይ በሰይፍ የተገደሉት ሁሉ ይወድቃሉ።
9 ፤ ለዘላለምም ባድማ አደርግሃለሁ ከተሞችህም ሰው የማይኖርባቸው ይሆናሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
10 ፤ እግዚአብሔርም በዚያ ሳለ፥ አንተ። እነዚህ ሁለቱ ሕዝቦች እነዚህም ሁለቱ አገሮች ለእኔ ይሆናሉ እኛም እንወርሳቸዋለን ብለሃልና
11 ፤ ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና እንደ ቍጣህ መጠን እነርሱንም ጠልተህ እንዳደረግኸው እንደ ቅንዓትህ መጠን እኔ እሠራለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በፈረድሁብህም ጊዜ በእነርሱ ዘንድ የታወቅሁ እሆናለሁ።
12 ፤ አንተም። ፈርሰዋል መብልም ሆነው ለእኛ ተሰጥተዋል ብለህ በእስራኤል ተራሮች ላይ የተናገርኸውን ስድብ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሰማሁት ታውቃለህ።
13 ፤ በአፋችሁም ተመካችሁብኝ፥ ቃላችሁንም አበዛችሁብኝ፤ እኔም ሰምቼዋለሁ።
14 ፤ ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ምድር ሁሉ ደስ ሲላት አንተን ባድማ አደርግሃለሁ። 
15 ፤ የእስራኤል ቤት ርስት ባድማ ስለ ሆነ በላዩ ደስ እንዳለህ፥ እንዲሁ አደርግብሃለሁ፤ የሴይር ተራራ ሆይ፥ አንተና ኤዶምያስ ሁሉ ሁለንተናውም ባድማ ትሆናላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

1 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ተራሮች ትንቢት ተናግረህ። የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በል።
2 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጠላት በእናንተ ላይ። እሰይ፥ የጥንት ከፍታዎች ለእኛ ርስት ሆነዋል ብሎአልና
3 ፤ ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለቀሩት አሕዛብ ርስት ትሆኑ ዘንድ በዙሪያችሁ ያሉ ባድማ አድርገዋችኋልና፥ ውጠዋችሁማልና፥ እናንተም የተናጋሪዎች ከንፈር መተረቻና የአሕዛብ ማላገጫ ሆናችኋልና
4 ፤ ስለዚህ፥ እናንተ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኮረብቶች፥ ለፈሳሾችና ለሸለቆች ለምድረ በዳዎች ባዶ ለሆኑትም በዙሪያ ላሉት ለቀሩት አሕዛብ ምርኮና መሳቂያ ለሆኑት ከተሞች እንዲህ ይላል፤
5 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያሳድዱአትና ይበዘብዙአት ዘንድ በልባቸው ሁሉ ደስታና በነፍሳቸው ንቀት ምድሬን ርስት አድርገው ለራሳቸው በሰጡ በቀሩት አሕዛብና በኤዶምያስ ሁሉ ላይ በቅንዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ፤
6 ፤ ስለዚህ ስለ እስራኤል ምድር ትንቢት ተናገር፥ ለተራሮችና ለኮረብቶችም ለፈሳሾችና ለሸለቆችም እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የአሕዛብን ስድብ ስለ ተሸከማችሁ በቅንዓቴና በመዓቴ ተናግሬአለሁ፤
7 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዙሪያችሁ ያሉ አሕዛብ ስድባቸውን በእርግጥ ይሸከማሉ ብዬ ምያለሁ።
8 ፤ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ እናንተ ግን ቅርንጫፎቻችሁን ታቈጠቍጣላችሁ፥ ይመጡም ዘንድ ቀርበዋልና ለሕዝቤ ለእስራኤል ፍሬአቸሁን ትሰጣላችሁ።
9 ፤ እነሆ፥ እኔ ለእናንተ ነኝና፤ ወደ እናንተም እመለከታለሁ፥ እናንተም ትታረሳላችሁ ይዘራባችሁማል፤
10 ፤ እኔም የእስራኤልን ቤት ሰዎች ሁሉ ሁሉንም አበዛባችኋለሁ፥ በከተሞችም ሰዎች ይኖሩባቸዋል ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ፤
11 ፤ ሰውንና እንስሳውንም አበዛባችኋለሁ፥ እነርሱም ይበዛሉ ያፈሩማል፤ እንደ ጥንታችሁም ሰዎችን አኖርባችኋለሁ፥ ቀድሞም ካደረግሁላችሁ ይልቅ መልካም አደርግላችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
12 ፤ ሰዎችንም፥ ሕዝቤን እስራኤልን፥ በእናንተ ላይ አስሄዳቸዋለሁ፤ እነርሱም ይወርሱሻል ርስትም ትሆኛቸዋለሽ፥ ከእንግዲህም ወዲያ ልጅ አልባ አታደርጊአቸውም።
13 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነርሱ። ሰው በሊታ ምድር ነሽ ሕዝብሽንም ልጅ አልባ የምታደርጊ ነሽ ብለዋችኋልና
14 ፤ ስለዚህ ዳግመኛ ሰው በሊታ አትሆኝም፥ ዳግመኛም ሕዝብሽን ልጅ አልባ አታደርጊም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤
15 ፤ ዳግመኛም የአሕዛብን ውርደት አላሰማብሽም፥ ዳግመኛም የአሕዛብን ስድብ አትሸከሚም፥ ዳግመኛም ሕዝብሽን አታሰናክዪም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
16 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
17 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት በምድራቸው በተቀመጡ ጊዜ በመንገዳቸውና በሥራቸው አረከሱአት፥ መንገዳቸውም በፊቴ እንደ መርገም አደፍ ነበረ።
18 ፤ በምድር ላይ ስላፈሰሱት ደም በጣዖቶቻቸውም ስላረከሱአት መዓቴን አፈሰስሁባቸው፤
19 ፤ ወደ አሕዛብም በተንኋቸው ወደ አገሮችም ተዘሩ፤ እንደ መንገዳቸውና እንደ ሥራቸው መጠን ፈረድሁባቸው።
20 ፤ ወደ መጡባቸውም ወደ አሕዛብ በመጡ ጊዜ፥ ሰዎች እነርሱን። ከምድሩ የወጡ የእግዚአብሔር ሕዝብ እነዚህ ናቸው ሲሉአቸው ቅዱስ ስሜን አረከሱ።
21 ፤ እኔ ግን የእስራኤል ቤት በመጡባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሱት ስለ ቅዱስ ስሜ ስል ራራሁላቸው።
22 ፤ ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በመጣችሁባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ነው እንጂ ስለ እናንተ የምሠራ አይደለሁም።
23 ፤ በአሕዛብም ዘንድ የረከሰውን፥ በመካከላቸው ያረከሳችሁትን ስሜን እቀድሰዋለሁ፤ በዓይናቸውም ዘንድ በተቀደስሁባችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
24 ፤ ከአሕዛብም መካከል አወጣችኋለሁ ከየአገሩም ሁሉ እሰበስባችኋለሁ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ።
25 ፤ ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ።
26 ፤ አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ።
27 ፤ መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ።
28 ፤ ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።
29 ፤ ከርኵሰታችሁም ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህልንም እጠራዋለሁ አበዛውማለሁ ራብንም አላመጣባችሁም።
30 ፤ ደግሞም የራብን ስድብ ከአሕዛብ ዘንድ እንዳትሸከሙ የዛፍን ፍሬና የእርሻውን ቡቃያ አበዛለሁ።
31 ፤ ክፉውን መንገዳችሁንና መልካም ያይደለውን ሥራችሁንም ታስባላችሁ፥ ስለ በደላችሁና ስለ ርኵሰታችሁም ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ።
32 ፤ ይህን የሠራሁ ስለ እናንተ እንዳይደለ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ መንገዳችሁ እፈሩና ተዋረዱ።
33 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከኃጢአታችሁ ሁሉ ባነጻኋችሁበት ቀን በከተሞች ሰዎችን አኖራለሁ ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ።
34 ፤ ባድማ የነበረች በመንገደኛም ሁሉ ዓይን ዘንድ ባድማ የነበረች ምድር ትታረሳለች።
35 ፤ ሰዎችም። ባድማ የነበረች ይህች ምድር እንደ ዔድን ገነት ሆናለች፤ የፈረሱት ባድማ የሆኑት የጠፉትም ከተሞች ተመሽገዋል ሰውም የሚኖርባቸው ሆነዋል ይላሉ።
36 ፤ በዙሪያችሁም የቀሩት አሕዛብ እኔ እግዚአብሔር የፈረሱትን ስፍራዎች እንደ ሠራሁ ውድማ የሆነውንም እንደ ተከልሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፥ እኔም አደርገዋለሁ።
37 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለዚህ ደግሞ አደርግላቸው ዘንድ የእስራኤል ቤት ይሹኛል ሰውንም እንደ መንጋ አበዛላቸዋለሁ። 
38 ፤ እንደ ተቀደሱ በጎች፥ በበዓላቶችዋ ቀን እንደሚሆኑ እንደ ኢየሩሳሌም በጎች፥ እንዲሁ የፈለሱት ከተሞች በሰዎች መንጋ ይሞላሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

1 ፤ የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ ነበረ እግዚአብሔርም በመንፈሱ አወጣኝ አጥንቶችም በሞሉባት ሸለቆ መካከል አኖረኝ።
2 ፤ በእነርሱም አንጻር በዙሪያቸው አሳለፈኝ፤ እነሆም፥ በሸለቆው ፊት እጅግ ብዙ ነበሩ፥ እነሆም፥ እጅግ ደርቀው ነበር።
3 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን? አለኝ። እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁ።
4 ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው። እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ።
5 ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ትንፋሽን አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ።
6 ፤ ጅማትም እሰጣችኋለሁ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ በእናንተም ላይ ቁርበትን እዘረጋለሁ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
7 ፤ እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፤ ስናገርም ድምፅ ሆነ፥ እነሆም፥ መናወጥ ሆነ፥ አጥንቶችም አጥንት ከአጥንት ጋር ተቀራረቡ።
8 ፤ እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ጅማት ነበረባቸው ሥጋም ወጣ ቁርበትም በላያቸው ተዘረጋ፥ ትንፋሽ ግን አልነበረባቸውም።
9 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነፋስ ሆይ፥ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፥ እነዚህም የተገደሉት በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እፍ በልባቸው በል አለኝ።
10 ፤ እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ ትንፋሽም ገባባቸው ሕያዋንም ሆኑ፥ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።
11 ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች የእስራኤል ቤት ሁሉ ናቸው፤ እነሆ። አጥንቶቻችን ደርቀዋል ተስፋችንም ጠፍቶአል ፈጽመንም ተቈርጠናል ብለዋል።
12 ፤ ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሕዝቤ ሆይ፥ እነሆ፥ መቃብራችሁን እከፍታለሁ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ፥ ወደ እስራኤልም ምድር አገባችኋለሁ።
13 ፤ ሕዝቤ ሆይ፥ መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ ከመቃብራችሁም ባወጣኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
14 ፤ መንፈሴንም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፥ በገዛ ምድራችሁም አኖራችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ እንዳደረግሁም ታውቃላችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
15 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
16 ፤ አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ አንድ በትር ውሰድና። ለይሁዳና ለባልንጀሮቹ ለእስራኤል ልጆች ብለህ በላዩ ጻፍ፤ ሌላም በትር ውሰድና። የኤፍሬም በትር ለዮሴፍና ለባልንጀሮቹ ለእስራኤል ቤት ሁሉ ብለህ በላዩ ጻፍ።
17 ፤ አንድ በትርም እንዲሆኑ አንዱን ከሁለተኛው ጋር ለአንተ አጋጥም፥ በእጅህም ውስጥ አንድ ይሁኑ።
18 ፤ የሕዝብህም ልጆች። ይህ የምታደርገው ነገር ምን ማለት እንደሆነ አትነግረንምን? ብለው በተናገሩህ ጊዜ፥
19 ፤ አንተ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በኤፍሬም እጅ ያለውን የዮሴፍን በትር ባልንጀሮቹንም የእስራኤልን ነገዶች እወስዳለሁ፥ ከእርሱም ከይሁዳ በትር ጋር አጋጥማቸዋለሁ አንድ በትርም አደርጋቸዋለሁ፥ በእጄም ውስጥ አንድ ይሆናሉ በላቸው።
20 ፤ የምትጽፍባቸውም በትሮች በዓይናቸው ፊት በእጅህ ውስጥ ይሆናሉ።
21 ፤ አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የእስራኤልን ልጆች ከሄዱባቸው ከአሕዛብ መካከል እወስዳለሁ ከስፍራም ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ፤
22 ፤ በምድርም ላይ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፥ አንድ ንጉሥም በሁላቸው ላይ ይነግሣል፤ ከዚያ ወዲያ ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፥ ከዚያ ወዲያም ሁለት መንግሥቶች ሆነው አይለዩም።
23 ፤ ከዚያ ወዲያም በጣዖቶቻቸውና በርኵሰታቸው በመተላለፋቸውም ሁሉ አይረክሱም፥ ኃጢአትም ከሠሩባት ዓመፅ ሁሉ አድናቸዋለሁ አነጻቸውማለሁ፤ ሕዝብም ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
24 ፤ ባሪያዬም ዳዊት ንጉሥ ይሆናቸዋል፤ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል፤ በፍርዴም ይሄዳሉ ትእዛዜንም ይጠብቃሉ ያደርጓትማል።
25 ፤ አባቶቻችሁም በኖሩበት ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድር ይኖራሉ፤ እነርሱና ልጆቻቸው የልጅ ልጆቻቸውም ለዘላለም ይኖሩባታል፤ ባሪያዬም ዳዊት ለዘላለም አለቃ ይሆናቸዋል።
26 ፤ የሰላምም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደርጋለሁ፥ የዘላለምም ቃል ኪዳን ይሆንላቸዋል፤ እኔም እባርካቸዋለሁ አበዛቸውማለሁ መቅደሴንም ለዘላለም በመካከላቸው አኖራለሁ።
27 ፤ ማደሪያዬም በላያቸው ላይ ይሆናል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። 
28 ፤ መቅደሴም ለዘላለም በመካከላቸው በሆነ ጊዜ፥ እኔ እስራኤልን የምቀድሰው እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ።

1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን በጎግ ላይና በማጎግ ምድር ላይ፥ በሞሳሕና በቶቤል ዋነኛ አለቃ ላይ አቅናበት፥ ትንቢትም ተናገርበት፥
3 ፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሞሳሕና የቶቢል ዋነኛ አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ።
4 ፤ እመልስህማለሁ በመንጋጋህም ልጓም አገባብሃለሁ፥ አንተንና ሠራዊትህንም ሁሉ፥ ፈረሶችንና ፈረሰኞችን የጦር ልብስ የለበሱትን ሁሉ፥ ጋሻና ራስ ቍርን ሰይፍንም ያያዙትን ሁሉ፥ ታላቁን ወገን አወጣለሁ፥
5 ፤ ፋርስንና ኢትዮጵያን ፉጥንም ከእነርሱ ጋር ጋሻና የራስ ቍርን የለበሱትን ሁሉ፥
6 ፤ ጋሜርንና ጭፍሮቹን ሁሉ፥ በሰሜን ዳርቻም ያለውን የቴርጋማን ቤትና ጭፍሮቹን ሁሉ፥ ብዙዎችንም ሕዝቦች ከአንተ ጋር አወጣለሁ።
7 ፤ አንተና ወደ አንተ የተሰበሰቡ ወገኖችህ ሁሉ ተዘጋጁ፥ አንተም ራስህን አዘጋጅተህ አለቃ ሁናቸው።
8 ፤ ከብዙ ዘመንም በኋላ ትፈለጋለህ፤ በኋለኛውም ዘመን፥ የዘላለም ባድማ በነበሩ በእስራኤል ተራሮች ላይ ከብዙ ሕዝብ ውስጥ ወደ ተሰበሰበች፥ ከሰይፍ ወደ ተመለሰች ምድር ትገባለህ፤ እርስዋም ከሕዝብ ውስጥ ወጥታለች ሁሉም ሳይፈሩ ይቀመጡባታል።
9 ፤ አንተም ትወጣለህ፥ እንደ ዐወሎ ነፋስም ትመጣለህ፤ አንተና ጭፍሮችህ ሁሉ ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝብ ምድርን እንደ ደመና ትሸፍናላችሁ።
10 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚያ ቀን ነገር ወደ ልብህ ይገባል፥
11 ፤ ክፉ አሳብንም ታስባለህ፥ እንዲህም ትላለህ። ቅጥርን ወደሌላቸው መንደሮች እወጣለሁ፤ ተዘልለው ወደሚኖሩ፥ ሁላቸው ሳይፈሩ ያለ ቅጥርና ያለ መወርወሪያ ያለ መዝጊያም ወደሚቀመጡ እገባለሁ፤
12 ፤ ምርኮን ትማርክ ዘንድ ብዝበዛንም ትበዘብዝ ዘንድ፥ ባድማም በነበሩ አሁንም ሰዎች በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ላይ፥ ከአሕዛብም በተሰበሰበ፥ ከብትና ዕቃንም ባገኘ፥ በምድርም መካከል በተቀመጠ ሕዝብ ላይ እጅህን ትዘረጋ ዘንድ።
13 ፤ ሳባና ድዳን የተርሴስም ነጋዴዎች መንደሮችዋም ሁሉ። ምርኮን ትማርክ ዘንድ መጥተሃልን? ብዝበዛንስ ትበዘብዝ ዘንድ ብርንና ወርቅንስ ትወስድ ዘንድ ከብትንና ዕቃንስ ትወስድ ዘንድ እጅግስ ብዙ ምርኮ ትማርክ ዘንድ ወገንህን ሰብስበሃልን? ይሉሃል።
14 ፤ አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለዚህ ትንቢት ተናገር ጎግንም እንዲህ በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚያ ቀን ሕዝቤ እስራኤል ሳይፈራ በተቀመጠ ጊዜ አንተ አታውቀውምን?
15 ፤ አንተም፥ ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝብ ሁላቸው በፈረሶች ላይ የተቀመጡ፥ ታላቅ ወገንና ብርቱ ሠራዊት፥ ከሰሜን ዳርቻ ከስፍራችሁ ትመጣላችሁ።
16 ፤ ምድርንም ትሸፍን ዘንድ እንደ ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። በኋለኛው ዘመን ይሆናል፥ ጎግ ሆይ፥ በዓይናቸው ፊት በተቀደስሁብህ ጊዜ አሕዛብ ያውቁኝ ዘንድ በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።
17 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእነርሱ ላይ እንደማመጣህ በዚያች ዘመን ብዙ ዓመት ትንቢት በተናገሩ በባሪያዎቼ በእስራኤል ነቢያቶች በቀደመው ዘመን ስለ እርሱ የተናገርሁ አንተ ነህን?
18 ፤ በዚያም ቀን ጎግ በእስራኤል ምድር ላይ በመጣ ጊዜ መቅሠፍቴ በመዓቴ ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
19 ፤ በቅንዓቴና በመዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ። በእርግጥ በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር ጽኑ መናወጥ ይሆናል፤
20 ፤ ከፊቴም የተነሣ የባሕር ዓሣዎችና የሰማይ ወፎች የምድረ በዳም አራዊት በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ በምድርም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ፥ ተራሮችም ይገለባበጣሉ ገደላገደሎችም ይወድቃሉ ቅጥርም ሁሉ ወደ ምድር ይወድቃል።
21 ፤ በተራሮቼም ሁሉ በእርሱ ላይ ሰይፍን እጠራለሁ፥ የሰውም ሁሉ ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
22 ፤ በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ፤ ዶፍም የበረዶም ድንጋይ እሳትና ድኝም በእርሱና በጭፍሮቹ ከእርሱም ጋር ባሉ በብዙ ሕዝብ ላይ አዘንባለሁ። 
23 ፤ ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

1 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ በጎግ ላይ ትንቢትን ተናገር እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሞሳሕና የቶቤል ዋነኛ አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፤
2 ፤ እመልስሃለሁ፥ እነዳህማለሁ፥ ከሰሜንም ዳርቻ እጐትትሃለሁ፥ ወደ እስራኤልም ተራሮች አመጣሃለሁ።
3 ፤ ከግራ እጅህም ቀስትህን አስጥልሃለሁ፥ ከቀኝ እጅህም ፍላጾችህን አስረግፍሃለሁ።
4 ፤ አንተና ጭፍሮችህ ሁሉ ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝብ በእስራኤል ተራሮች ላይ ትወድቃላችሁ፤ ለሚናጠቁ ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊትም መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ።
5 ፤ አንተ በምድር ፊት ላይ ትወድቃለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
6 ፤ በማጎግም ላይ ሳይፈሩም በደሴቶች በሚቀመጡ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
7 ፤ ቅዱሱም ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ይታወቅ ዘንድ አደርጋለሁ፥ ቅዱሱንም ስሜን ከእንግዲህ ወዲህ አላስረክስም፤ አሕዛብም እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
8 ፤ እነሆ፥ ይመጣል ይሆንማል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያልሁት ቀን ይህ ነው።
9 ፤ በእስራኤልም ከተሞች የሚኖሩ ይወጣሉ፥ የጦር መሣሪያዎችንም በእሳት ያቃጥላሉ፤ አላባሽ ጋሻንና ጋሻን፥ ቀስትንና ፍላጻዎችን፥ ጎመድንና ጦርንም ያቃጥላሉ፤ ሰባት ዓመት በእሳት ያቃጥሉአቸዋል።
10 ፤ በጦር መሣሪያው እሳትን ያነድዳሉ እንጂ እንጨትን ከምድረ በዳ አይወስዱም ከዱርም አይቈርጡም፤ የገፈፉአቸውንም ይገፍፋሉ የበዘበዙአቸውንም ይበዘብዛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
11 ፤ በዚያም ቀን በእስራኤል ዘንድ በባሕር ምሥራቅ የሚያልፉበትን ሸለቆ የመቃብርን ስፍራ ለጎግ እሰጣለሁ፥ የሚያልፉትንም ይከለክላል፤ በዚያም ጎግንና ብዛቱን ሁሉ ይቀብራሉ፤ የሸለቆውንም ስም ሐሞንጎግ ብለው ይጠሩታል።
12 ፤ ምድሩንም ያጸዱ ዘንድ የእስራኤል ቤት ሰዎች ሰባት ወር ይቀብሩአቸዋል፥
13 ፤ የምድርም ሕዝብ ሁሉ ይቀብሩአቸዋል፥ በተመሰገንሁበትም ቀን ለክብር ይሆንላችኋል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
14 ፤ ምድርንም ለማጽዳት በምድሩ ላይ ወድቀው የቀሩትን የሚቀብሩ፥ ዘወትር በምድሩ ላይ የሚዞሩትን ሰዎች ይቀጥራሉ፤ ከሰባት ወርም በኋላ ይመረምራሉ።
15 ፤ በምድርም የሚዞሩት ያልፋሉ፤ የሰውንም አጥንት ቢያዩ፥ ቀባሪዎች በሐሞን ጎግ ሸለቆ እስኪቀብሩት ድረስ ምልክት ያኖሩበታል።
16 ፤ ደግሞም የከተማይቱ ስም ሐሞና ይባላል። እንዲሁ ምድሪቱን ያጸዳሉ።
17 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለወፎች ሁሉና ለምድር አራዊት ሁሉ እንዲህ በላቸው። ኑ፥ ተከማቹ፥ ሥጋንም ትበሉ ዘንድ ደምንም ትጠጡ ዘንድ በእስራኤል ተራሮች ላይ ወደማርድላችሁ መሥዋዕት፥ እርሱም ታላቅ መሥዋዕት፥ ከየስፍራው ሁሉ ተሰብሰቡ።
18 ፤ የኃያላኑን ሥጋ ትበላላችሁ የምድርንም አለቆች፥ የአውራ በጎችንና የጠቦቶችን፥ የፍየሎችንና የወይፈኖችን፥ የባሳንን ፍሪዳዎች ሁሉ፥ ደም ትጠጣላችሁ።
19 ፤ እኔም ከማርድላችሁ መሥዋዕት እስክትጠግቡ ድረስ ጮማ ትበላላችሁ እስክትሰክሩም ድረስ ደም ትጠጣላችሁ።
20 ፤ በሰደቃዬም ከፈረሶችና ከፈረሰኞች፥ ከኃያላንና ከሰልፈኞች ሁሉ ትጠግባላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
21 ፤ ክብሬንም በአሕዛብ መካከል አኖራለሁ አሕዛብም ሁሉ ያደርግሁትን ፍርዴን፥ በላያቸውም ያኖርኋትን እጄን ያያሉ።
22 ፤ ከእንግዲህም ወዲያ የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
23 ፤ አሕዛብም የእስራኤል ቤት በኃጢአታቸው ምክንያት እንደ ተማረኩ ያውቃሉ፤ ስለ በደሉኝ እኔም ፊቴን ከእነርሱ ስለ ሸሸግሁ፥ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ ሰጠኋቸው፥ እነርሱም ሁሉ በሰይፍ ወደቁ።
24 ፤ እንደ ርኵሰታቸውም እንደ መተላለፋቸውም መጠን አደረግሁባቸው ፊቴንም ከእነርሱ ሸሸግሁ።
25 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አሁን የያዕቆብን ምርኮ እመልሳለሁ ለእስራኤልም ቤት ሁሉ እራራለሁ፥ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ።
26፤27 ፤ ማንም ሳያስፈራቸው በምድራቸው ተዘልለው በተቀመጡ ጊዜ ከአሕዛብም ዘንድ በመለስኋቸው ጊዜ ከጠላቶቻቸውም ምድር በሰበሰብኋቸው ጊዜ በብዙ አሕዛብም ፊት በተቀደስሁባቸው ጊዜ፥ እፍረታቸውንና የበደሉኝን በደላቸውን ሁሉ ይሸከማሉ።
28 ፤ እኔም ወደ አሕዛብ አስማርኬአቸዋለሁና፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም ሰብስቤአቸዋለሁና እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ በዚያም ከእነርሱ አንድ ሰው ከእንግዲህ ወዲያ አልተውም፥ 
29 ፤ ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልሸሽግም፤ መንፈሴን በእስራኤል ቤት ላይ አፍስሻለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

1 ፤ በተማረክን በሀያ አምስተኛው ዓመት በዓመቱ መጀመሪያ ከወሩ በአሥረኛው ቀን፥ ከተማይቱ ከተመታች በኋላ በአሥራ አራተኛው ዓመት፥ በዚያው ቀን የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረ እርሱም ወደዚያ ወሰደኝ።
2 ፤ በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ እጅግም በረዘመ ተራራ ላይ አኖረኝ፥ በዚያም ላይ በደቡብ ወገን እንደ ከተማ ሆኖ የተሠራ ነገር ነበረ።
3 ፤ ወደዚያም አመጣኝ፥ እነሆም፥ መልኩ እንደ ናስ መልክ የመሰለ አንድ ሰው በዚያ ነበረ፥ በእጁም የተልባ እግር ገመድና የመለኪያ ዘንግ ነበረ፤ እርሱም በበሩ አጠገብ ቆሞ ነበር።
4 ፤ ሰውዬውም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ይህን አሳይህ ዘንድ አንተ ወደዚህ ተመርተሃልና በዓይንህ እይ በጆሮህም ስማ በማሳይህም ሁሉ ላይ ልብህን አድርግ፤ የምታየውንም ሁሉ ለእስራኤል ቤት ንገር አለኝ።
5 ፤ እነሆም፥ በቤቱ ውጭ በዙሪያው ቅጥር ነበረ፥ በሰውዬውም እጅ የክንዱ ልክ አንድ ክንድ ከጋት የሆነ ስድስት ክንድ ያለበት የመለኪያ ዘንግ ነበረ፤ የቅጥሩንም ስፋት አንድ ዘንግ ቁመቱንም አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ።
6 ፤ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተውም በር መጣ በደረጃዎቹም ላይ ወጣ፥ በበሩ በኩል ያለውንም የመድረኩን ወለል ወርዱን አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ።
7 ፤ የዘበኛውም ጓዳ ሁሉ ርዝመቱ አንድ ዘንግ፥ ወርዱም አንድ ዘንግ ነበረ፤ በዘበኛውም ጓዳዎች መካከል አምስት ክንድ ነበረ፤ በበሩም ደጀ ሰላም በስተ ውስጥ በኩል የሚገኝ የበሩ የመድረክ ወለል አንድ ዘንግ ነበረ።
8 ፤ በስተ ውስጥም ያለውን የበሩን ደጀ ሰላም አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ።
9 ፤ የበሩንም ደጀ ሰላም ስምንት ክንድ፥ የግንቡንም አዕማድ ወርድ ሁለት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም ደጀ ሰላም በስተ ውስጥ ነበረ።
10 ፤ የምሥራቁም በር የዘበኛ ጓዳዎች በዚህ በኩል ሦስት በዚያም በኩል ሦስት ነበሩ፥ ለሦስቱም አንድ ልክ ነበረ፤ የግንቡም አዕማድ ወርድ በዚህ በኩልና በዚያ በኩል አንድ ልክ ነበረ።
11 ፤ የበሩንም መግቢያ ወርድ አሥር ክንድ የበሩንም ርዝመት አሥራ ሦስት ክንድ አድርጎ ለካ።
12 ፤ በዘበኛ ጓዳዎችም ፊት በዚህ በኩል አንድ ክንድ በዚያም በኩል አንድ ክንድ የሆነ ዳርቻ ነበረ፤ የዘበኛ ጓዳዎቹም በዚህ በኩል ስድስት ክንድ በዚያም በኩል ስድስት ክንድ ነበሩ።
13 ፤ ከአንዱም የዘበኛ ጓዳ ደርብ ጀምሮ እስከ ሌላው ደርብ ድረስ የበሩን ወርድ ሀያ አምስት ክንድ አድርጎ ለካ፤ መዝጊያውና መዝጊያውም ትይዩ ነበረ።
14 ፤ ደጀ ሰላሙንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካ፤ በበሩም ደጀ ሰላም ዙሪያ አደባባይ ነበረ።
15 ፤ ከበሩም መግቢያ ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው የበሩ ደጀ ሰላም መጨረሻ ድረስ አምሳ ክንድ ነበረ።
16 ፤ በዘበኛ ጓዳዎቹም በበሩ ውስጥ በዙሪያው በነበሩትም በግንቡ አዕማድ የዓይነ ርግብ መስኮቶች ነበሩባቸው፤ ደግሞም በደጀ ሰላሙ ውስጥ በዙሪያው መስኮቶች ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ሁሉ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር።
17 ፤ ወደ ውጭውም አደባባይ አመጣኝ፥ እነሆም፥ በአደባባዩ ዙሪያ የተሠሩ ዕቃ ቤቶችና ወለል ነበሩ፤ በወለሉም ላይ ሠላሳ ዕቃ ቤቶች ነበሩ።
18 ፤ ወለሉም በበሮች አጠገብ ነበረ ይህም ታችኛው ወለል እንደ በሮቹ ርዝመት መጠን ነበረ።
19 ፤ ከታችኛውም በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው አደባባይ ፊት ድረስ ወርዱን አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
20 ፤ ወደ ሰሜንም መራኝ፥ እነሆም፥ በውጭው አደባባይ ያለ ወደ ሰሜን የሚመለከት በር ነበረ፤ ርዝመቱንና ወርዱንም ለካ፥
21 ፤ የዘበኛ ጓዳዎቹም በዚህ በኩል ሦስት በዚያም በኩል ሦስት ነበሩ፤ የግንቡ አዕማድና መዛነቢያዎቹም እንደ ፊተኛው በር ልክ ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
22 ፤ መስኮቶቹም መዛነቢያዎቹም የዘንባባ ዛፎቹም ወደ ምሥራቅ እንደሚመለከተው በር ልክ ነበሩ። ወደ እርሱም የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ መዛነቢያዎቹም በፊቱ ነበሩ።
23 ፤ በውስጠኛውም አደባባይ በሰሜኑና በምሥራቁ በኩል በሌላው በር አንጻር በር ነበረ፤ ከበርም ወደ በር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
24 ፤ ወደ ደቡብም መራኝ፥ እነሆም፥ ወደ ደቡብ የሚመለከት በር ነበረ፤ የግንቡን አዕማድና መዛነቢያዎቹንም እንደዚያው መጠን አድርጎ ለካ።
25 ፤ በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ እንደ እነዚያ መስኮቶች የሚመስሉ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
26 ፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ፥ መዛነቢያዎቹም በፊቱ ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ላይ አንዱ በዚህ አንዱም በዚያ ወገን ሆኖ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር።
27 ፤ በውስጠኛውም አደባባይ በደቡብ በኩል በር ነበረ፤ ከበር እስከ በር ድረስ በደቡብ በኩል መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
28 ፤ በደቡብም በር በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ አገባኝ፤ እንደዚያውም መጠን አድርጎ የደቡብን በር ለካ፤
29 ፤ እንደዚያውም መጠን አድርጎ የዘበኛ ጓዳዎቹንና የግንቡን አዕማድ መዛነቢያዎቹንም ለካ፤ በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
30 ፤ በዙሪያውም ደጀ ሰላሞች ነበሩ፤ ርዝመታቸውም ሀያ አምስት ክንድ ወርዳቸውም አምስት ክንድ ነበረ።
31 ፤ መዛነቢያዎቹም ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩ።
32 ፤ በውስጠኛውም አደባባይ በምሥራቅ በኩል አገባኝ፥ እንደዚያውም መጠን በሩን ለካ፤
33 ፤ እንደዚያውም መጠን የዘበኛ ጓዳዎቹንና የግንቡን አዕማድ መዛነቢያዎቹንም ለካ፤ በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፥ ርዝመቱም አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
34 ፤ መዛነቢያዎቹም በስተ ውጭ ወዳለው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
35 ፤ በሰሜንም ወዳለው በር አመጣኝ፥ እንደዚያውም መጠን ለካው፤
36 ፤ የዘበኛ ጓዳዎቹንና የግንቡን አዕማድ መዛነቢያዎቹንም ለካ፤ በዙሪያውም መስኮቶች ነበሩበት፥ ርዝመቱም አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
37 ፤ የግንቡም አዕማድ ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
38 ፤ በበሮቹም በግንብ አዕማድ አጠገብ ዕቃ ቤቱና መዝጊያው ነበሩ፤ በዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያጥቡ ነበር።
39 ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የኃጢአቱንና የበደሉንም መሥዋዕት ያርዱባቸው ዘንድ፥ በበሩ ደጀ ሰላም በዚህ ወገን ሁለት ገበታዎች፥ በዚያም ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ።
40 ፤ በሰሜን በኩል ባለው በር በስተ ውጭው፥ በመወጣጫው ደረጃዎች አጠገብ፥ በአንድ ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ፥ በሌላውም ወገን በበሩ ደጀ ሰላም በኩል ሁለት ገበታዎች ነበሩ።
41 ፤ በበሩ አጠገብ በዚህ ወገን አራት ገበታዎች በዚያም ወገን አራት ገበታዎች ነበሩ፤ መሥዋዕት የሚያርዱባቸው ገበታዎች ስምንት ነበሩ።
42 ፤ ስለሚቃጠለውም መሥዋዕት ርዝመታቸው ክንድ ተኩል ወርዳቸውም ክንድ ተኩል ቁመታቸውም አንድ ክንድ የሆኑ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን የሚያርዱበትን ዕቃ ያኖሩባቸው ዘንድ፥ ከተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ አራት ገበታዎች ነበሩ።
43 ፤ በዙሪያውም አንድ ጋት የሆነ ክፈፍ ወደ ውስጥ ተቀልብሶ ነበር፤ በገበታዎቹም ላይ የቍርባኑ ሥጋ ነበረባቸው።
44 ፤ ወደ ውስጠኛውም አደባባይ አገባኝ፥ እነሆም፥ ሁለት ቤቶች ነበሩ፤ አንዱ ወደ ሰሜን በሚመለከት በር አጠገብ ነበረ፥ መግቢያውም ወደ ደቡብ ይመለከት ነበር፤ ሌላውም ወደ ደቡብ በሚመለከተው በር አጠገብ ነበረ፥ መግቢያውም ወደ ሰሜን ይመለከት ነበር።
45 ፤ ሰውዬውም። ይህ ወደ ደቡብ የሚመለከት ቤት ለማገልገል ለሚተጉ ካህናት ነው።
46 ፤ ወደ ሰሜንም የሚመለከተው ቤት መሠዊያውን ለማገልገል ለሚተጉ ካህናት ነው፤ እነዚህ ከሌዊ ልጆች መካከል ያገለግሉት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ የሳዶቅ ልጆች ናቸው አለኝ።
47 ፤ አደባባዩንም በአራት ማዕዘኑ ርዝመቱን መቶ ክንድ ወርዱንም መቶ ክንድ አድርጎ ለካ፤ መሠዊያውም በቤቱ ፊት ነበረ።
48 ፤ ወደ ቤቱም ደጀ ሰላም አመጣኝ፥ የደጀ ሰላሙንም የግንብ አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያም ወገን አምስት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም ወርድ አሥራ አራት ክንድ ነበረ፥ በበሩም በዚህ ወገንና በዚያ ወገን የነበሩት ግንቦች ሦስት ሦስት ክንድ ነበሩ። 
49 ፤ የደጀ ሰላሙም ርዝመት ሀያ ክንድ ወርዱም አሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፥ ወደ እርሱም የሚያደርሱ አሥር ደረጃዎች ነበሩ፤ አንድ በዚህ ወገን አንድም በዚያ ወገን ሆነው በመቃኖቹ አጠገብ የግንብ አዕማድ ነበሩ።

1 ፤ ወደ መቅደሱም አገባኝ፥ የግንቡንም አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን ስድስት ክንድ በዚያም ወገን ስድስት ክንድ አድርጎ ለካ።
2 ፤ የመግቢያውም ወርድ አሥር ክንድ ነበረ፥ የመግቢያውም መቃኖች በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያም ወገን አምስት ክንድ ነበሩ፤ ርዝመቱንም አርባ ክንድ ወርዱንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካ።
3 ፤ ወደ ውስጥም ገባ፥ የመግቢያውንም የግንብ አዕማድ ወርድ ሁለት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የመግቢያውም ወርድ ስድስት ክንድ ነበረ፥ የመግቢያውም ግንብ ወርድ በዚህ ወገን ሰባት ክንድ በዚያም ወገን ሰባት ክንድ ነበረ።
4 ፤ በመቅደሱም ፊት ርዘመቱን ሀያ ክንድ ወርዱንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካና። ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው አለኝ።
5 ፤ የመቅደሱንም ግንብ ስድስት ክንድ አድርጎ፥ በመቅደሱም ዙሪያ ሁሉ ያሉትን የጓዳዎቹን ሁሉ ወርድ አራት ክንድ አድርጎ ለካ።
6 ፤ ጓዳዎቹም አንዱ ከአንዱ በላይ በሦስት ደርብ ነበሩ፥ በእያንዳንዱም ደርብ ሠላሳ ጓዳዎች ነበሩ። በመቅደሱም ግንብ ዙሪያ ደገፋዎች ይሆኑ ዘንድ አረፍቶች ነበሩ፥ በመቅደሱም ግንብ ውስጥ ደገፋዎች አልነበሩም።
7 ፤ በቤቱም ዙሪያ ባለ ግንብ ውስጥ በነበሩት አረፍቶች ምክንያት ላይኞቹ ጓዳዎች ከታችኞቹ ጓዳዎች ይበልጡ ነበር፤ ከታችኛውም ደርብ ወደ መካከለኛው ከመካከለኛውም ደርብ ወደ ላይኛው የሚወጣበት ደረጃ ነበረ።
8 ፤ ለመቅደሱም ከፍ ያለ ወለል በዙሪያው እንዳለው አየሁ፤ የጓዳዎቹም መሠረት ቁመቱ ሙሉ ዘንግ የሚያህል ስድስት ትልቅ ክንድ ነበረ።
9 ፤ የጓዳዎቹም የውጭው ግንብ ውፍረት አምስት ክንድ ነበረ፤ በመቅደሱም ጓዳዎች አጠገብ የቀረ አንድ ባዶ ስፍራ ነበረ።
10-11፤ በዚህም በባዶው ስፍራ አንዱ በሰሜን በኩል አንዱም በደቡብ በኩል የጓዳዎች መግቢያ ነበረ የባዶውም ስፍራ ወርድ በዙሪያ አምስት ክንድ ነበረ። በመቅደሱም ዙሪያ ወርዱ ሀያ ክንድ የሆነ ልዩ ስፍራ ነበረ።
12 ፤ በምዕራብም በኩል በልዩ ስፍራ አንጻር የነበረ ግቢ ስፋቱ ሰባ ክንድ ነበረ። በግቢውም ዙሪያ የነበረ ግንብ ውፍረቱ አምስት ክንድ ርዝመቱም ዘጠና ክንድ ነበረ።
13 ፤ የመቅደሱንም ርዝመት መቶ ክንድ፥ የልዩውን ስፍራና ግቢውን ከግንቡ ጋር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
14 ፤ ደግሞም በምሥራቅ በኩል የነበረውን የመቅደሱንና የልዩውን ስፍራ ወርድ አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
15 ፤ ወደ ኋላውም ባለው በልዩ ስፍራ አንጻር የነበረውን የግቢውን ርዝመት በዚህና በዚያም ከነበሩት ከግንቦቹ ጋር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
16 ፤ መድረኮቹ፥ መቅደሱና በስተ ውስጥ ያለው ክፍል ደጀ ሰላሙም በእንጨት ተለብጠው ነበር፥ በሦስቱም ዙሪያ የዓይነ ርግብ መስኮቶች ነበሩ። መቅደሱም በመድረኩ አንጻር ከመሬት ጀምሮ እስከ መስኮቶቹ ድረስ በእንጨት ተለብጦ ነበር፤ መስኮቶቹም የዓይነ ርግብ ነበሩ፤
17 ፤ በደጁም ላይ እስከ ውስጠኛው ክፍል ድረስ፥ በውጭም ግንቡ ሁሉ ውስጡም ውጭውም ተለብጦ ነበር።
18 ፤ ኪሩቤልና የዘንባባው ዛፎች ተቀርጸውበት ነበር፤ የዘንባባውም ዛፍ ከኪሩብና ከኪሩብ መካከል ነበረ፤ ለእያንዳንዱም ኪሩብ ሁለት ፊት ነበረው።
19 ፤ በአንድ ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ የሰው ፊት ይመለከት ነበር፥ በሌላውም ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ የአንበሳ ፊት ይመለከት ነበር፤ በቤቱ ሁሉ ዙሪያ እንደዚህ ተደርጎ ነበር።
20 ፤ ከመሬት አንሥቶ እስከ ደጁ ራስ ድረስ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር። የመቅደሱ ግንብ እንደዚህ ነበረ።
21 ፤ የመቅደሱ መቃኖችም አራት ማዕዘን ነበሩ፥ የመቅደሱ ፊትም መልኩ እንደ ሌላው መልክ ነበረ።
22 ፤ መሠዊያውም ቁመቱ ሦስት ክንድ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ወርዱም ሁለት ክንድ ሆኖ ከእንጨት ተሠርቶ ነበር፤ ማዕዘኖቹም እግሩም አገዳዎቹም ከእንጨት ተሠርተው ነበር፤ እርሱም። በእግዚአብሔር ፊት ያለችው ገበታ ይህች ናት አለኝ።
23 ፤ ለመቅደሱና ለተቀደሰው ስፍራ ሁለት መዝጊያዎች ነበሩአቸው።
24 ፤ ለእያንዳንዱ መዝጊያም ሁለት ተዘዋዋሪ ሳንቃዎች ነበሩት፤ ለአንዱ መዝጊያ ሁለት ለሌላውም መዝጊያ ሁለት ሳንቃዎች ነበሩት።
25 ፤ በግንቡም ላይ በተቀረጹት ዓይነት በእነዚህ በመቅደሱ መዝጊያዎች ላይ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር፤ በስተ ውጭም ባለው በደጀ ሰላሙ ፊት የእንጨት መድረክ ነበረ። 
26 ፤ በደጀ ሰላሙም በሁለቱ ወገን በዚህና በዚያ የዓይነ ርግብ መስኮቶችና የተቀረጹ የዘንባባ ዛፎች ነበሩበት፤ የመቅደሱም ጓዳዎችና የእንጨቱ መድረክ እንዲሁ ነበሩ።

1 ፤ በውጭም አደባባይ በሰሜኑ መንገድ አወጣኝ፥ በልዩውም ስፍራ አንጻርና በሰሜን በኩል ባለው ግቢ ፊት ለፊት ወዳለው ዕቃ ቤት አገባኝ።
2 ፤ መቶ ክንድ በሆነው ርዝመት ፊት በሰሜን በኩል መዝጊያ ነበረ ወርዱም አምሳ ክንድ ነበረ።
3 ፤ በውስጠኛውም አደባባይ በሀያው ክንድ አንጻር በውጭውም አደባባይ በወለሉ አንጻር በሦስት ደርብ በትይዩ የተሠራ መተላለፊያ ነበረ።
4 ፤ በዕቃ ቤቶቹም ፊት በስተ ውስጥ ወርዱ አሥር ክንድ ርዝመቱ መቶ ክንድ የሆነ መንገድ ነበረ፤ መዝጊያዎቻቸውም ወደ ሰሜን ይመለከቱ ነበር።
5 ፤ መተላለፊያውም አሳጥሮአቸዋልና ላይኞቹ ዕቃ ቤቶች ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ አጫጭር ነበሩ።
6 ፤ በሦስትም ደርብ ተሠርተው ነበርና፥ በአደባባዩም እንዳሉት አዕማድ፥ አዕማድ አልነበሩላቸውምና ስለዚህ ላይኞቹ ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ ጠባብ ነበሩ።
7 ፤ በውጭ በዕቃ ቤቶቹ አጠገብ ያለው፥ ወደ ውጭው አደባባይ የሚመለከተው ቅጥር፥ በዕቃ ቤቶች ትይዩ የሆነ፥ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ነበረ።
8 ፤ በመቅደሱ ፊት የነበሩት ዕቃ ቤቶች ርዝመታቸው መቶ ክንድ ሲሆን በውጭው አደባባይ በኩል የነበሩት ዕቃ ቤቶች ርዝመታቸው አምሳ ክንድ ነበረና።
9 ፤ ከእነዚህም ዕቃ ቤቶች በታች በስተ ምሥራቅ በኩል፥ ሰው ከውጭው አደባባይ የሚገባበት መግቢያ ነበረ። ይህም በቅጥሩ ራስ አጠገብ ነበረ።
10 ፤ በደቡብም በኩል በልዩው ስፍራና በግቢው አንጻር ዕቃ ቤቶች ነበሩ።
11 ፤ በስተ ፊታቸውም የነበረ መንገድ በሰሜን በኩል እንደ ነበረው እንደ ዕቃ ቤቶቹ መንገድ ምስያ ነበረ። ርዝመታቸውም ወርዳቸውም መውጫቸውም ሥርዓታቸውም መዝጊያዎቻቸውም በዚያው ልክ ነበረ።
12 ፤ በደቡብም በኩል ካሉት ዕቃ ቤቶች በታች በምሥራቅ በኩል በቅጥሩ ራስ አጠገብ መግቢያ ነበረ።
13 ፤ እንዲህም አለኝ። በልዩ ስፍራ አንጻር በሰሜንና በደቡብ በኩል ያሉ ዕቃ ቤቶች፥ እነርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ ካህናት ከሁሉ ይልቅ የተቀደሰውን ምግብ የሚበሉባቸው ቤቶች ናቸው። ስፍራው ቅዱስ ነውና በዚያ የተቀደሰውን ነገር የእህሉን ቍርባን የኃጢአቱንና የበደሉን መሥዋዕት ያኖራሉ።
14 ፤ ካህናቱም በገቡ ጊዜ ከመቅደሱ በውጭው አደባባይ አይወጡም፤ የሚያገለግሉበትን ልብሳቸውን ግን ቅዱስ ነውና በዚያ ያኖሩታል፥ ሌላም ልብስ ለብሰው ወደ ሕዝብ ይወጣሉ።
15 ፤ ውስጠኛውንም ቤት ለክቶ በፈጸመ ጊዜ ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር መንገድ አወጣኝ እርሱንም በዙሪያው ለካው።
16 ፤ የምሥራቁን ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
17 ፤ ዞረም፥ የሰሜኑንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
18 ፤ ዞረም፥ የደቡቡንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
19 ፤ ዞረም፥ የምዕራቡንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 
20 ፤ በአራቱ ወገን ለካው። የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን ይለይ ዘንድ ርዝመቱ አምስት መቶ ክንድ ወርዱም አምስት መቶ ክንድ የሆነ ቅጥር በዙሪያው ነበረ።

1 ፤ ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በር አመጣኝ።
2 ፤ እነሆም፥ የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ መንገድ መጣ፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውኆች ይተምም ነበር፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር ታበራ ነበር።
3 ፤ ያየሁትም ራእይ ከተማይቱን ለማጥፋት በመጣሁ ጊዜ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ ራእዩም በኮበር ወንዝ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ።
4 ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር ወደ መቅደሱ ገባ።
5 ፤ መንፈሱም አነሣኝ ወደ ውስጠኛውም አደባባይ አገባኝ፤ እነሆም፥ የእግዚአብሔር ክብር መቅደሱን ሞልቶት ነበር።
6 ፤ በመቅደሱም ሆኖ የሚናገረኝን ሰማሁ፥ በአጠገቤም ሰው ቆሞ ነበር።
7 ፤ እንዲህም አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል ለዘላለም የምቀመጥበት የዙፋኔ ስፍራና የእግሬ ጫማ መረገጫ ይህ ነው። ዳግመኛም የእስራኤል ቤትና ነገሥታቶቻቸው በግልሙትናቸውና በከፍታዎቻቸው ባለው በነገሥታቶቻቸው ሬሳ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም፤
8 ፤ መድረካቸውን በመድረኬ አጠገብ፥ መቃናቸውንም በመቃኔ አጠገብ አድርገዋልና። በእኔና በእነርሱም መካከል ግንብ ብቻ ነበረ፤ በሠሩትም ርኵሰት ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤ ስለዚህ በቍጣዬ አጠፋኋቸው።
9 ፤ አሁንም ግልሙትናቸውንና የነገሥታቶቻቸውን ሬሳ ከእኔ ዘንድ ያርቁ፥ እኔም ለዘላለም በመካከላቸው አድራለሁ።
10 ፤ አንተም የሰው ልጅ፥ ከኃጢአታቸው የተነሣ ያፍሩ ዘንድ ለእስራኤል ወገን ይህን ቤት አሳያቸው አምሳያውንም ይለኩ።
11 ፤ ከሠሩትም ሥራ ሁሉ የተነሣ ቢያፍሩ፥ የቤቱን መልክና ምሳሌውን መውጫውንም መግቢያውንም ሥርዓቱንም ሕጉንም ሁሉ አስታውቃቸው፤ ሥርዓቱንና ሕጉን ሁሉ ይጠብቁ ዘንድ ያደርጉትም ዘንድ በፊታቸው ጻፈው።
12 ፤ የቤቱ ሕግ ይህ ነው፤ በተራራው ራስ ላይ ዳርቻው ሁሉ በዙሪያው ከሁሉ ይልቅ የተቀደስ ይሆናል። እነሆ፥ የቤቱ ሕግ ይህ ነው።
13 ፤ የመሠዊያውም ልክ በክንድ ይህ ነው፥ ክንዱም ክንድ ተጋት ነው። የመሠረቱም ቁመቱ አንድ ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፥ አንድ ስንዝርም ክፈፍ ዳር ዳሩን በዙሪያው አለ፤ የመሠዊያው መሠረት እንዲሁ ነው።
14 ፤ በመሬቱም ላይ ካለው መሠረት ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ሁለት ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፤ ከትንሹም እርከን ጀምሮ እስከ ትልቁ እርከን ድረስ አራት ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ነው።
15 ፤ ምድጃውም አራት ክንድ ነው፤ በምድጃውም ላይ አንድ ክንድ ወደ ላይ ከፍ የሚሉ አራት ቀንዶች አሉበት።
16 ፤ የምድጃውም ርዝመት አሥራ ሁለት ክንድ ወርዱም አሥራ ሁለት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን ትክክል ነው።
17 ፤ የእርከኑም ርዝመት አሥራ አራት ክንድ ወርዱም አሥራ አራት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን ትክክል ነው፤ በዙሪያውም ያለው ክፈፍ እኩል ክንድ ነው፥ መሠረቱም በዙሪያው አንድ ክንድ ነው፤ ደረጃዎቹም ወደ ምሥራቅ ይመለከታሉ።
18 ፤ እንዲህም አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡበት ዘንድ ደሙንም ይረጩበት ዘንድ በሚሠሩበት ቀን የመሠዊያው ሕግ ይህ ነው።
19 ፤ ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ ለሚቀርቡ ከሳዶቅ ዘር ለሚሆኑ ለሌዋውያኑ ካህናት ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትሰጣቸዋለህ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
20 ፤ ከደሙም ትወስዳለህ፥ በአራቱ ቀንዶቹም በእርከኑም በአራቱ ማዕዘን ላይ በዙሪያውም ባለው ክፈፍ ላይ ትረጨዋለህ፤ እንዲሁ ታነጻዋለህ ታስተሰርይለትማለህ።
21 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትወስዳለህ፥ በመቅደሱም ውጭ በቤቱ በታዘዘው ስፍራ ይቃጠላል።
22 ፤ በሁለተኛውም ቀን ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ነውር የሌለበትን አውራ ፍየል ታቀርባለህ፤ በወይፈኑም እንዳነጹት እንዲሁ መሠዊያውን ያነጹበታል።
23 ፤ ማንጻቱንም ከፈጸምህ በኋላ ነውር የሌለበትን ወይፈን ከመንጋውም የወጣውን ነውር የሌለበትን አውራ በግ ታቀርባለህ።
24 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ታቀርባቸዋለህ፥ ካህናቱም ጨው ይጨምሩባቸዋል፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር ያቀርቡአቸዋል።
25 ፤ ሰባት ቀንም በየዕለቱ ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ ፍየልን ታቀርባለህ፥ ነውርም የሌለባቸውን አንድ ወይፈን ከመንጋውም የወጣውን አንድ አውራ በግ ያቀርባሉ።
26 ፤ ሰባት ቀን ለመሠዊያው ያስተሰርያሉ ያነጹትማል፥ እንዲሁም ይቀድሱታል። 
27 ፤ ቀኖቹንም በፈጸሙ ጊዜ በስምንተኛው ቀን ከዚያም በኋላ ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን የደኅንነትንም መሥዋዕታችሁን በመሠዊያው ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

1 ፤ ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር።
2 ፤ እግዚአብሔርም። ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል።
3 ፤ አለቃው ግን እርሱ በእግዚአብሔር ፊት እንጀራ ይበላ ዘንድ ይቀመጥበታል፤ በበሩ ደጀ ሰላም መንገድ ይገባል በዚያም መንገድ ይወጣል።
4 ፤ በሰሜኑም በር መንገድ በቤቱ ፊት አመጣኝ፤ እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ የእግዚአብሔር ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበር፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ።
5 ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ ልብ አድርግ ስለ እግዚአብሔርም ቤት ሥርዓትና ሕግ ሁሉ የምናገርህን ሁሉ በዓይንህ ተመልከት በጆሮህም ስማ፤ የቤቱንም መግቢያ የመቅደሱንም መውጫ ሁሉ ልብ አድርግ።
6 ፤ ለዓመፀኛው ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥
7 ፤ እንጀራዬን፥ ስብንና ደምን፥ በምታቀርቡበት ጊዜ በመቅደሴ ውስጥ ይሆኑ ዘንድ ቤቴንም ያረክሱ ዘንድ በልባቸውና በሥጋቸው ያልተገረዙትን እንግዶችን ሰዎች አግብታችኋልና፥ እነርሱም በርኵሰታችሁ ሁሉ ላይ ይጨመሩ ዘንድ ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና ርኵሰታችሁ ሁሉ ይብቃችሁ።
8 ፤ በመቅደሴ ውስጥ ለራሳችሁ ሥርዓቴን ጠባቂዎች አደረጋችሁ እንጂ የተቀደሰውን ነገሬን ሥርዓት አልጠበቃችሁም።
9 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእስራኤል ልጆች መካከል ካሉት ሁሉ በልቡና በሥጋው ያልተገረዘ እንግዳ ሁሉ ወደ መቅደሴ አይግባ።
10 ፤ ከእኔ ዘንድ የራቁ፥ እስራኤልም በሳቱ ጊዜ ጣዖታቸውን ተከትለው ከእኔ ዘንድ የሳቱ ሌዋውያን ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ።
11 ፤ ነገር ግን በመቅደሴ ውስጥ አገልጋዮች ይሆናሉ፥ በቤቱም በሮች በረኞች ይሆናሉ በቤቱም ውስጥ ያገለግላሉ፤ ለሕዝቡም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን ያርዳሉ፥ ያገለግሉአቸውም ዘንድ በፊታቸው ይቆማሉ።
12 ፤ በጣዖቶቻቸውም ፊት አገልግለዋቸው ነበሩና፥ ለእስራኤልም ቤት የኃጢአት ዕንቅፋት ሆነዋልና ስለዚህ እጄን በላያቸው አንሥቻለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይሸከማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
13 ፤ ካህናትም ይሆኑኝ ዘንድ ወደ እኔ አይቀርቡም፥ ወደ ተቀደሰውም ነገሬና ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ነገር አይቀርቡም፤ እፍረታቸውንና የሠሩትንም ርኵሰታቸውን ይሸከማሉ።
14 ፤ ነገር ግን ለአገልግሎቱ ሁሉና በእርሱ ውስጥ ለሚደረገው ሁሉ የቤቱን ሥርዓት ጠባቂዎች አደርጋቸዋለሁ።
15 ፤ ነገር ግን የእስራኤል ልጆች ከእኔ ዘንድ በሳቱ ጊዜ የመቅደሴን ሥርዓት የጠበቁ የሳዶቅ ልጆች ሌዋውያን ካህናት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ ይቀርባሉ፤ ስቡንና ደሙንም ወደ እኔ ያቀርቡ ዘንድ በፊቴ ይቆማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
16 ፤ ወደ መቅደሴም ይገባሉ ያገለግሉኝም ዘንድ ወደ ገበታዬ ይቀርባሉ ሥርዓቴንም ይጠብቃሉ።
17 ፤ ወደ ውስጠኛውም አደባባይ በር በገቡ ጊዜ የተልባ እግር ልብስ ይልበሱ፤ በውስጠኛውም አደባባይ በርና በቤቱ ውስጥ ባገለገሉ ጊዜ ከበግ ጠጕር አንዳች ነገር በላያቸው አይሁን።
18 ፤ በራሳቸው ላይ የተልባ እግር መጠምጠሚያ ይሁን፥ በወገባቸውም ላይ የተልባ እግር ሱሪ ይሁን፤ የሚያወዛም ነገር አይታጠቁ።
19 ፤ ወደ ውጭውም አደባባይ ወደ ሕዝብ በወጡ ጊዜ ያገለገሉበትን ልብሳቸውን ያውልቁ በተቀደሰውም ዕቃ ቤት ውስጥ ያኑሩት፥ ሕዝቡንም በልብሳቸው እንዳይቀድሱ ሌላውን ልብስ ይልበሱ።
20 ፤ ራሳቸውንም አይላጩ የራሳቸውንም ጠጕር ይከርከሙ እንጂ ጠጕራቸውን አያሳድጉ።
21 ፤ ካህናቱም ሁሉ በውስጠኛው አደባባይ ሲገቡ የወይን ጠጅ አይጠጡ።
22 ፤ መበለቲቱንና የተፈታችይቱን አያግቡ፤ ከእስራኤል ቤት ዘር ግን ድንግሊቱን ወይም የካህን ሚስት የነበረችይቱን መበለት ያግቡ።
23 ፤ በተቀደሰውና ባልተቀደሰው መካከል ይለዩ ዘንድ ሕዝቤን ያስተምሩ፥ ንጹሕና ንጹሕ ባልሆነው መካከል ይለዩ ዘንድ ያሳዩአቸው።
24 ፤ ክርክርም በሆነ ጊዜ ለመፍረድ ይቁሙ፤ እንደ ፍርዴ ይፍረዱ፤ በበዓላቴ ሁሉ ሕጌንና ሥርዓቴን ይጠብቁ፥ ሰንበታቴንም ይቀድሱ።
25 ፤ እንዳይረክሱም ወደ ሞተ ሰው አይግቡ፤ ነገር ግን ለአባት ወይም ለእናት ወይም ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ ወይም ለወንድም ወይም ላልተዳረች እኅት ይርከሱ።
26 ፤ ከነጻም በኋላ ሰባት ቀን ይቈጠርለት።
27 ፤ በመቅደስም ውስጥ ያገለግል ዘንድ ወደ ውስጠኛው አደባባይ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ቀን፥ የኃጢአትን መሥዋዕት ያቅርብ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
28 ፤ ርስት ይሆንላቸዋል፤ እኔ ርስታቸው ነኝ፤ በእስራኤልም ዘንድ ግዛት አትሰጡአቸው፤ እኔ ግዛታቸው ነኝ።
29 ፤ የእህሉን ቍርባንና የኃጢአትን መሥዋዕት የበደልንም መሥዋዕት ይበላሉ፤ በእስራኤልም ዘንድ እርም የሆነው ነገር ሁሉ ለእነርሱ ይሆናል።
30 ፤ የበኵራቱ ሁሉ መጀመሪያ ከየዓይነቱ ከቍርባናችሁም ሁሉ የማንሣት ቍርባን ሁሉ ለካህናት ይሆናል፤ በቤታችሁም ውስጥ በረከት ያድር ዘንድ የዱቄታችሁን በኵራት ለካህናቱ ትሰጣላችሁ። 
31 ፤ የበከተውንና የተሰበረውን፥ ወፍ ወይም እንስሳ ቢሆን፥ ካህናት አይብሉት።

1 ፤ ርስትም አድርጋችሁ ምድርን በዕጣ በምታካፍሉበት ጊዜ ከምድር የተቀደሰውን የዕጣ ክፍል መባ አድርጋችሁ ወደ እግዚአብሔር ታቀርባላችሁ። ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱም ሀያ ሺህ ክንድ ይሆናል፤ በዳርቻው ሁሉ ዙሪያውን የተቀደሰ ይሆናል።
2 ፤ ከእርሱም ርዝመቱ አምስት መቶ ወርዱም አምስት መቶ ክንድ አራት ማዕዘን የሆነ ቦታ ለመቅደሱ ይሆናል፤ በዙሪያውም ባዶ ስፍራ የሚሆን አምሳ ክንድ ይሆናል።
3 ፤ ከዚያው ልክ ደግሞ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱም አሥር ሺህ ክንድ የሆነ ስፍራ ትለካለህ፤ በእርሱም ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳን የሆነ መቅደስ ይሆናል።
4 ፤ ከምድርም የተቀደሰ የዕጣ ክፍል ይሆናል፤ እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ለሚቀርቡ ለመቅደሱ አገልጋዮች ለካህናቱ ይሆናል፥ ለቤቶቻቸውም የሚሆን ስፍራ ለመቅደስም የሚሆን የተቀደሰ ስፍራ ይሆናል።
5 ፤ ርዝመቱም ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም አሥር ሺህ የሆነ ዕፍራ ለቤቱ አገልጋዮች ለሌዋውያን ይሆናል፥ ለሚቀመጡባቸውም ከተሞች ለራሳቸውም የርስት ይዞታ ይሆናል።
6 ፤ ለከተማይቱም ይዞታ በተቀደሰው የዕጣ ክፍል መባ አጠገብ ወርዱ አምስት ሺህ ርዝመቱም ሀያ አምስት ሺህ የሆነውን ስፍራ ታደርጋላችሁ። እርሱም ለእስራኤል ቤት ሁሉ ይሆናል።
7 ፤ ለአለቃውም የሆነ የዕጣ ክፍል በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ አጠገብ በዚህና በዚያ ይሆናል፤ በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ ፊት በምዕራብ በኩል ወደ ምዕራብ በምሥራቅም በኩል ወደ ምሥራቅ ይሆናል፤ ርዝመቱም እንደ አንድ ነገድ ዕጣ ክፍል ሆኖ ከምድሩ ከምዕራቡ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ዳርቻ ድረስ ይሆናል።
8 ፤ ይህም በእስራኤል ዘንድ ይዞታ ይሆንለታል፥ አለቆቼም ለእስራኤል ቤት ምድሪቱን እንደ ነገዳቸው መጠን ይሰጡአቸዋል እንጂ ሕዝቤን ከእንግዲህ ወዲህ አያስጨንቋቸውም።
9 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእስራኤል አለቆች ሆይ፥ ይብቃችሁ፤ ግፍንና ብዝበዛን አስወግዱ፥ ፍርድንና ጽድቅንም አድርጉ፤ ቅሚያችሁን ከሕዝቤ ላይ አርቁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
10 ፤ እውነተኛ ሚዛን እውነተኛም የኢፍ መስፈሪያ እውነተኛውም የባዶስ መስፈሪያ ይሁንላችሁ።
11 ፤ የኢፍና የባዶስ መስፈሪያ አንድ ይሁን፤ የባዶስ መስፈሪያ የቆሮስ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል፥ የኢፍ መስፈሪያውም የቆሮስ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል ይሁን። መስፈሪያው እንደ ቆሮስ መስፈሪያ ይሁን።
12 ፤ ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ይሁን፤ ሀያ ሰቅል፥ ሀያ አምስት ሰቅል፥ አሥራ አምስት ሰቅል፥ ምናን ይሁንላችሁ።
13 ፤ የምታቀርቡት መባ ይህ ነው፤ ከአንድ ቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ የኢፍ መስፈሪያ ስድስተኛ ክፍል፥ ከአንድም ቆሮስ መስፈሪያ ገብስ የኢፍ መስፈሪያ ስድስተኛ ክፍል ትሰጣላችሁ።
14 ፤ የዘይቱም ደንብ፥ ከእያንዳንዱ የቆሮስ መስፈሪያ የባዶስን አሥረኛ ክፍል ትሰጣላችሁ፤ አሥር የባዶስ መስፈሪያ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ነውና።
15 ፤ ውኃም ካለበት ከእስራኤል ማሰማርያ ከመንጋው ከሁለቱ መቶ አንዱን የበግ ጠቦት ትሰጣላችሁ፤ ይህ ያስተሰርይላችሁ ዘንድ ለእህል ቍርባንና ለሚቃጠል መሥዋዕት ለደኅንነትም መሥዋዕት ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
16 ፤ የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ይህን መባ ለእስራኤል አለቃ ይሰጣሉ።
17 ፤ በየበዓላቱም በየመባቻውም በየሰንበታቱም በእስራኤልም ቤት ዓመት በዓል ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን የመጠጡንም ቍርባን መስጠት በአለቃው ላይ ይሆናል፤ እርሱ ለእስራኤል ቤት ያስተሰርይ ዘንድ የኃጢአቱን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቀርባል።
18 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ነውር የሌለበትን ወይፈን ውሰድ መቅደሱንም አንጻ።
19 ፤ ካህኑም ከኃጢአቱ መሥዋዕት ደም ወስዶ በመቅደሱ መቃኖችና በመሠዊያው እርከን በአራቱ ማዕዘን በውስጠኛውም አደባባይ በበሩ መቃኖች ላይ ይርጨው።
20 ፤ ከወሩም በሰባተኛው ቀን እንዲሁ አድርግ፥ ይኸውም ስለ ሳተውና ስላላወቀው ሁሉ ነው። እንዲሁም ስለ ቤቱ አስተስርዩ።
21 ፤ በመጀመሪያ ወር ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል ታደርጋላችሁ። እስከ ሰባት ቀንም ድረስ ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ።
22 ፤ በዚያም ቀን አለቃው ለራሱና ለአገሩ ሕዝብ ሁሉ የኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ያቅርብ።
23 ፤ በበዓሉም በሰባቱ ቀኖች የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ ሰባቱን ቀኖች በየዕለቱ ነውር የሌለባቸውን ሰባት ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ያቅርብ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት በየዕለቱ አንድ አውራ ፍየል ያቅርብ።
24 ፤ ለአንድም ወይፈን አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአንድም አውራ በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአንድም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ለእህል ቍርባን ያቅርብ። 
25 ፤ በሰባተኛውም ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን በበዓሉ ሰባት ቀኖች፥ የኃጢአቱን መሥዋዕት የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የእህሉንም ቍርባን ከዘይቱ ጋር እንዲሁ ያቅርብ።

1 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በውስጠኛው አደባባይ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር ሥራ በሚሠራበት በስድስቱ ቀን ተዘግቶ ይቈይ፤ ነገር ግን በሰንበት ቀንና በመባቻ ቀን ይከፈት።
2 ፤ አለቃውም በስተ ውጭ ባለው በር በደጀ ሰላሙ መንገድ ገብቶ በበሩ መቃን አጠገብ ይቁም፥ ካህናቱም የእርሱን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቅርቡ፥ እርሱም በበሩ መድረክ ላይ ይስገድ፤ ከዚያም በኋላ ይውጣ፥ በሩ ግን እስከ ማታ ድረስ አይዘጋ።
3 ፤ የአገሩም ሕዝብ በዚያ በር መግቢያ በእግዚአብሔር ፊት በሰንበታትና በመባቻ ይስገዱ።
4 ፤ አለቃውም በሰንበት ቀን ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለባቸው ስድስት የበግ ጠቦቶች ነውርም የሌለበት አንድ አውራ በግ ይሁን፤
5 ፤ የእህሉም ቍርባን ለአውራ በጉ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ይሁን፥ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባን እንደሚቻል ያህል ይሁን፥ ለአንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ያቅርብ።
6 ፤ በመባቻም ቀን ነውር የሌለበትን አንድ ወይፈን፥ ነውር የሌለባቸውንም ስድስት ጠቦቶችና አንድ አውራ በግ ያቅርብ፤
7 ፤ ለወይፈኑም አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአውራውም በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለጠቦቶቹም እንደ ተቻለው ያህል፥ ለአንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ለእህሉ ቍርባን ያቅርብ።
8 ፤ አለቃውም በሚገባበት ጊዜ በበሩ ደጀ ሰላም መንገድ ይግባ በዚያውም ይውጣ።
9 ፤ የአገሩ ሕዝብ ግን በየክብረ በዓሉ ቀን ወደ እግዚአብሔር ፊት በመጡ ጊዜ በሰሜን በር በኩል ሊሰግድ የሚገባው በደቡብ በር በኩል ይውጣ፥ በደቡብም በር የሚገባው በሰሜን በር በኩል ይውጣ፤ በፊት ለፊት ይውጣ እንጂ በገባበቱ በር አይመለስ።
10 ፤ በሚገቡበት ጊዜ አለቃው በመካከላቸው ይግባ በሚወጡበትም ጊዜ ይውጣ።
11 ፤ በበዓላትና በክብረ በዓል ቀኖች የእህሉ ቍርባን ለወይፈኑ አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለአውራ በጉ አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለጠቦቶቹም እንደሚቻለው ያህል፥ ለኢፍ መስፈሪያም አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይሆናል።
12 ፤ አለቃውም በፈቃዱ የሚያቀርበውን መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ ወይም በፈቃዱ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበውን የደኅንነቱን መሥዋዕት፥ ባቀረበ ጊዜ፥ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር ይከፈትለት፥ በሰንበትም ቀን እንደሚያደርግ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቅርብ፤ ከዚያም በኋላ ይውጣ፥ ከወጣም በኋላ በሩ ይዘጋ።
13 ፤ በየዕለቱም ለሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት በግ ጠቦት ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ በየማለዳው ያቅርበው።
14 ፤ ከእርሱም ጋር የእህልን ቍርባን፥ በኢን መስፈሪያ ሢሶ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ ስድስተኛ እጅ መልካም ዱቄትን፥ በየማለዳው ያቅርብ፤ ይህ በዘላለሙ ሥርዓት ለእግዚአብሔር የዘወትር የእህል ቍርባን ይሁን።
15 ፤ እንዲሁ ዘወትር ለሚቃጠለው መሥዋዕት ጠቦቱንና የእህሉን ቍርባን ዘይቱንም በየማለዳው ያቅርብ።
16 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አለቃው ከልጆቹ ለአንዱ ከርስቱ ስጦታ ቢሰጥ ለልጆቹ ይሁን፤ የርስት ይዞታ ይሆንላቸዋል።
17 ፤ ነገር ግን ከባሪያዎቹ ለአንዱ ከርስቱ ስጦታ ቢሰጥ እስከ ነጻነት ዓመት ድረሰ ለእርሱ ይሁን፥ ከዚያም በኋላ ለአለቃው ይመለስ፤ ርስቱ ግን ለልጆቹ ይሁን።
18 ፤ አለቃውም ሕዝቡን ከይዞታቸው ያወጣቸው ዘንድ ከርስታቸው በግድ አይውሰድ፤ ሕዝቤ ሁሉ ከይዞታቸው እንዳይነቀሉ ከገዛ ይዞታው ለልጆች ርስትን ይስጥ።
19 ፤ በበሩም አጠገብ ባለው መግቢያ ወደ ሰሜን ወደሚመለከተው ለካህናት ወደሚሆን ወደ ተቀደሰው ዕቃ ቤት አገባኝ፤ እነሆም፥ በኋላው በምዕራብ በኩል አንድ ስፍራ ነበረ።
20 ፤ እርሱም። ካህናቱ ሕዝቡን ለመቀደስ ወደ ውጭው አደባባይ እንዳያወጡ የበደሉን መሥዋዕትና የኃጢአቱን መሥዋዕት የሚቀቅሉበት፥ የእህሉንም ቍርባን የሚጋግሩበት ስፍራ ይህ ነው አለኝ።
21 ፤ በውጭው አደባባይ አወጣኝ በአደባባይም ወዳለው ወደ አራቱ ማዕዘን አዞረኝ፤ እነሆም፥ በአደባባዩ ማዕዘን ሁሉ አደባባይ ነበረ።
22 ፤ በአደባባዩ በአራቱ ማዕዘን ርዝመቱ አርባ ክንድ ወርዱም ሠላሳ ክንድ የሆነ የታጠረ አደባባይ ነበረ፤ በማዕዘኑ ላሉ ለእነዚህ ለአራቱ ስፍራዎች አንድ ልክ ነበረ።
23 ፤ በአራቱም ዙሪያ ሁሉ ግንብ ነበረ፥ በግንቡም ሥር በዙሪያው የመቀቀያ ቦታ ነበረ። 
24 ፤ እርሱም። እነዚህ የቤቱ አገልጋዮች የሕዝቡን መሥዋዕት የሚቀቅሉባቸው ስፍራዎች ናቸው አለኝ።

1 ፤ ወደ መቅደሱም መዝጊያ መለሰኝ፤ እነሆም፥ ውኃ ከቤቱ መድረክ በታች ወደ ምሥራቅ ይወጣ ነበር፥ የቤቱ ፊት ወደ ምሥራቅ ይመለከት ነበርና፤ ውኃውም ከቤቱ ከቀኝ ወገን በታች በመሠዊያው በደቡብ በኩል ይወርድ ነበር።
2 ፤ በሰሜኑም በር በኩል አወጣኝ፤ በስተ ውጭ ባለው መንገድ፥ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከት በስተ ውጭ ወዳለው በር አዞረኝ፤ እነሆም፥ ውኃው በቀኙ ወገን ይፈስስ ነበር።
3 ፤ ሰውዬውም ገመዱን በእጁ ይዞ ወደ ምሥራቅ ወጣ አንድ ሺህም ክንድ ለካ፥ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃም እስከ ቍርጭምጭሚት ደረሰ።
4 ፤ ደግሞ አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃውም እስከ ጕልበት ደረሰ። ደግሞም አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃውም እስከ ወገብ ደረሰ።
5 ፤ ደግሞ አንድ ሺህ ለካ ልሻገረውም የማልችለው ወንዝ ሆነ፤ ውኃውም ጥልቅ ነበረ፥ የሚዋኝበትም ውኃ ነበረ፤ ሰው ሊሻገረው የማይችለው ወንዝ ነበረ።
6 ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ አይተሃልን? አለኝ። አመጣኝም፥ ወደ ወንዙም ዳር መለሰኝ።
7 ፤ በተመለስሁም ጊዜ፥ እነሆ፥ በወንዙ ዳር በዚህና በዚያ እጅግ ብዙ ዛፎች ነበሩ።
8 ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። ይህ ውኃ ወደ ምሥራቅ ምድር ይወጣል ወደ ዓረባም ይወርዳል ወደ ባሕሩም ይገባል፤ ወደ ባሕሩም ወደ ረከሰው ውኃ በገባ ጊዜ ውኃው ይፈወሳል።
9 ፤ ሕያው ነፍስ ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ ወንዙ በመጣበት ስፍራ ሁሉ በሕይወት ይኖራል፤ ይህም ውኃ በዚያ ስለ ደረሰ ዓሣዎች እጅግ ይበዛሉ፤ የባሕሩም ውኃ ይፈወሳል፥ ወንዙም በሚመጣበት ያለው ሁሉ በሕይወት ይኖራል።
10 ፤ አጥማጆችም በዚያ ይቆማሉ፤ ከዓይንጋዲ ጀምሮ እስከ ዓይንኤግላይም ድረስ መረብ መዘርጊያ ይሆናል፤ ዓሣዎችም እንደ ታላቁ ባሕር ዓሣዎች በየወገናቸው እጅግ ይበዛሉ።
11 ፤ እረግረጉና እቋሪው ውኃ ግን ጨው እንደ ሆነ ይኖራል እንጂ አይፈወስም።
12 ፤ በወንዙም አጠገብ በዳሩ ላይ በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ሁሉ ይበቅላል፥ ቅጠሉም አይረግፍም ፍሬውም አይጐድልም፤ ውኃውም ከመቅደስ ይወጣልና በየወሩ ሁሉ የፍሬ በኵር ያገኛል፤ ፍሬውም ለመብል ቅጠሉም ለመድኃኒት ይሆናል።
13 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ርስት አድርጋችሁ ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ምድሪቱን የምትከፍሉበት ድንበር ይህ ነው። ለዮሴፍ ሁለት እድል ፈንታ ይሆናል።
14 ፤ ለአባቶቻችሁ እሰጣቸው ዘንድ ምዬ ነበርና እናንተ እኩል አድርጋችሁ ተካፈሉት ይህችም ምድር ርስት ትሆናችኋለች።
15 ፤ የምድሪቱም ድንበር ይህ ነው። በሰሜኑ ወገን ከታላቁ ባሕር ጀምሮ በሔትሎን መንገድ ወደ ጽዳድ መግቢያ፤
16 ፤ ሐማት፥ ቤሮታ፥ በደማስቆ ድንበርና በሐማት ድንበር መካከል ያለው ሲብራይም፥ በሐውራን ድንበር አጠገብ ያለው ሐጸርሃቲኮን።
17 ፤ ድንበሩ ከባሕሩ በደማስቆ ድንበር ላይ ያለው ሐጸርዔናን ይሆናል፥ በሰሜንም በኩል የሐማት ድንበር አለ። የሰሜኑ ድንበር ይህ ነው።
18 ፤ የምሥራቁም ድንበር በሐውራን በደማስቆና በገለዓድ በእስራኤልም ምድር መካከል ዮርዳኖስ ይሆናል። ከሰሜኑ ድንበር ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ባሕር እስከ ታማር ድረስ የምሥራቁ ድንበር ይህ ነው።
19 ፤ የደቡቡም ድንበር ከታማር ጀምሮ እስከ ሜርባ ቃዴስ ውኃ እስከ ግብጽ ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። የደቡቡ ድንበር ይህ ነው።
20 ፤ የምዕራቡም ድንበር ከደቡቡ ድንበር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ አንጻር ድረስ ታላቁ ባሕር ይሆናል። የምዕራቡ ድንበር ይህ ነው።
21 ፤ እንዲሁ ይህችን ምድር እንደ እስራኤል ነገዶች መጠን ለእናንተ ትካፈላላችሁ።
22 ፤ ለእናንተና በእናንተ መካከል ለሚቀመጡ በእናንተም መካከል ልጆችን ለሚወልዱ መጻተኞች ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ትካፈሉአታላችሁ፤ እነርሱም በእስራኤል ልጆች መካከል እንዳሉ የአገር ልጆች ይሆኑላችኋል፥ በእስራኤልም ነገዶች መካከል ከእናንተ ጋር ርስትን ይወርሳሉ። 
23 ፤ መጻተኛውም በማናቸውም ነገድ መካከል ቢቀመጥ በዚያ ርስቱን ትሰጡታላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

1 ፤ የነገዶችም ስም ይህ ነው። በሔትሎን መንገድ አጠገብ ወደ ሐማት መግቢያ በደማስቆም ድንበር ባለው በሐጸርዔናን በሐማትም አጠገብ በሰሜን በኩል ካለው ከሰሜን ድንበር ይጀምራል። ወርዳቸውም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሆናል። ለዳን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
2 ፤ ከዳንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለአሴር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
3 ፤ ከአሴርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለንፍታሌም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
4 ፤ ከንፍታሌም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለምናሴ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
5 ፤ ከምናሴም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለኤፍሬም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
6 ፤ ከኤፍሬምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለሮቤል አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
7 ፤ ከሮቤልም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሁዳ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
8 ፤ ከይሁዳም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለመባ የሆነ የዕጣ ክፍል ይሆናል፤ ወርዱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል ርዝመቱም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ከዕጣ ክፍሎች እንደ አንዱ ይሆናል፥ መቅደሱም በመካከሉ ይሆናል።
9 ፤ ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት መባ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ወርዱም ሃያ ሺህ ክንድ ይሆናል።
10 ፤ ለእነዚህም ለካህናቱ የተቀደሰ መባ ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ፥ በምዕራብም በኩል ወርዱ አሥር ሺህ፥ በምሥራቅም በኩል ወርዱ አሥር ሺህ፥ በደቡብም በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል። የእግዚአብሔርም መቅደስ በመካከሉ ይሆናል።
11 ፤ የእስራኤልም ልጆች በሳቱ ጊዜ፥ ሌዋውያን እንደ ሳቱ ላልሳቱት ሥርዓቴን ለጠበቁት ከሳዶቅ ልጆች ወገን ለተቀደሱት ካህናት ይሆናል።
12 ፤ ከምድርም መባ የተለየ መባ ይሆንላቸዋል፥ ከሁሉም ይልቅ የተቀደሰ ይሆናል፤ በሌዋውያን ድንበር አጠገብ ይሆናል።
13 ፤ በካህናቱም ድንበር አንጻር ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም አሥር ሺህ የሆነ ዕጣ ለሌዋውያን ይሆናል፤ ርዝመቱ ሁሉ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ሀያ ሺህ ክንድ ይሆናል።
14 ፤ ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ነውና ከእርሱ ምንም አይሸጡም አይለውጡምም፥ የምድሩም በኵራት አይፋለስም።
15 ፤ በሀያ አምስቱም ሺህ አንጻር አምስት ሺህ ወርድ ያለው የቀረ ስፍራ ለከተማይቱ ለጋራ ጉዳይዋ፥ ለመኖሪያ ለማስማርያም ይሆናል፤ ከተማይቱም በመካከሉ ትሆናለች።
16 ፤ ልክዋም ይህ ነው፤ በሰሜን በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በደቡብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምሥራቅም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምዕራብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል።
17 ፤ ለከተማይቱም ማሰማርያ ይኖራታል፤ በሰሜን በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በደቡብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምሥራቅም በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምዕራብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ ክንድ ይሆናል።
18 ፤ በተቀደሰው መባ አንጻር የተረፈው ርዝመቱ ወደ ምሥራቅ አሥር ሺህ ወደ ምዕራብም አሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። በተቀደሰው መባ አንጻር ይሆናል። ፍሬውም ከተማይቱን ለሚያገለግሉ ለመብል ይሆናል።
19 ፤ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማይቱን የሚያገለግሉ ያርሱታል።
20 ፤ መባው ሁሉ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ የተቀደሰውን መባ ከከተማይቱ ይዞታ ጋር አራት ማዕዘን አድርጋችሁ ትሰጣላችሁ።
21 ፤ በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ በዚህና በዚያ ወገን የቀረው ለአለቃው ይሆናል፤ በመባው በሀያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምሥራቁ ድንበር፥ በምዕራብም በኩል በሀያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምዕራቡ ድንበር፥ እንደ ዕጣ ክፍል ሁሉ መጠን፥ ለአለቃው ይሆናል፤ የተቀደሰውም መባና ቤተ መቅደሱ በመካከሉ ይሆናል።
22 ፤ የሌዋውያንም ርስት የከተማይቱም ይዞታ ለአለቃው በሆነው መካከል ይሆናል፤ በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል የአለቃ ዕጣ ክፍል ይሆናል።
23 ፤ ለቀሩትም ነገዶች እንዲህ ይሆናል፤ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለብንያም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
24 ፤ ከብንያምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለስምዖን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
25 ፤ ከስምዖንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሳኮር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
26 ፤ ከይሳኮርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለዛብሎን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
27 ፤ ከዛብሎንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለጋድ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
28 ፤ ከጋድም ድንበር ቀጥሎ በደቡብ በኩል ድንበሩ ከታማር ጀምሮ እስከ ሜሪባ ቃዴስ ውኃ እስከ ግብጽ ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል።
29 ፤ ርስት አድርጋችሁ ለእስራኤል ነገዶች በዕጣ የምታካፍሉአት ምድር ይህች ናት፥ የእያንዳንዱም ዕጣ እንደዚህ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
30 ፤ የከተማይቱም መውጫዎች እነዚህ ናቸው። በሰሜን ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው።
31 ፤ የከተማይቱ በሮች እንደ እስራኤል ነገዶች ስም ይሆናሉ፤ በሰሜን በኩል አንዱ የሮቤል በር አንዱም የይሁዳ በር አንዱም የሌዊ በር፥ ሦስት በሮች ይሆናሉ።
32 ፤ በምሥራቁም ወገን አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የዮሴፍ በር አንዱም የብንያም በር አንዱም የዳን በር ነው።
33 ፤ በደቡቡም ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የስምዖን በር አንዱም የይሳኮር በር አንዱም የዛብሎን በር ነው።
34 ፤ በምዕራቡም ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የጋድ በር አንዱም የአሴር በር አንዱም የንፍታሌም በር ነው። 
35 ፤ ዙሪያዋም አሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማይቱ ስም። እግዚአብሔር በዚያ አለ ተብሎ ይጠራል።

Latest News

ilovejesus1.com

My name is Eden Fessehaye and i build ilovejesus1.com website for everyone to have access to the bible and audio bible as well.  There is Amharic, Tigrigna and English bible.  Also, the English bible can be translated to any languages for everyone to have access to...

Trust in Christ and receive Him as your Savior.

Christ is ready. “Here I am! I stand at the door and knock. If anyone hears my voice and opens the door, I will go in” (Revelation 3:20). Receive him now. “Yet to all who received him, to those who believed in his name, he gave the right to become children of God”...

You must repent and ask God for forgiveness.

“He who conceals his sins does not prosper, but whoever confesses and renounces them finds mercy” (Proverbs 28:13).  Forgiveness is promised. “If we confess our sins, he is faithful and just and will forgive us our sins and purify us from all unrighteousness” (1 John...

Jesus Christ died and rose again for our sins.

Jesus Christ died in our place. “But God demonstrates his own love for us in this: While we were still sinners, Christ died for us” (Romans 5:8). He is the way to new life. “Therefore, if anyone is in Christ, he is a new creation; the old has gone, the new has come!”...

Sin separates you from God

Everyone has sinned. “For all have sinned and fall short of the glory of God” (Romans 3:23). Sin brings death. “For the wages of sin is death” (Romans 6:23). “For it is by grace you have been saved, through faith and this not from yourselves, it is the gift of God-not...

Recognize that God loves you

“For God so loved the world that he gave his one and only Son, that whoever believes in him shall not perish but have eternal life” (John 3:16). He has new life for you. “I have come that they may have life, and have it to the full” (John 10:10).

The light of Jesus

Then Jesus again spoke to them, saying, “I am the Light of the world; he who follows Me will not walk in the darkness, but will have the Light of life.” (John 8:12, NASB) While I am in the world, I am the Light of the world.”...

Second Coming of Christ

Revelation 7:14 - “...they are the people who are coming out safely through the terrible tribulation. The blood of the Lamb has washed and made white their robes.” Revelation 19:7 - “They will be Christ's bride and will have...

ilovejesus1.com

My name is Eden Fessehaye and i build ilovejesus1.com website for everyone to have access to the bible and audio bible as well.  There is Amharic, Tigrigna and English bible.  Also, the English bible can be translated to any languages for everyone to have access to...

Trust in Christ and receive Him as your Savior.

Christ is ready. “Here I am! I stand at the door and knock. If anyone hears my voice and opens the door, I will go in” (Revelation 3:20). Receive him now. “Yet to all who received him, to those who believed in his name, he gave the right to become children of God”...

You must repent and ask God for forgiveness.

“He who conceals his sins does not prosper, but whoever confesses and renounces them finds mercy” (Proverbs 28:13).  Forgiveness is promised. “If we confess our sins, he is faithful and just and will forgive us our sins and purify us from all unrighteousness” (1 John...

Cresta Help Chat
Send via WhatsApp
Translate »