ኦሪት ዘኍልቍ (Numbers)

እሱ ተከታታይ ጅማሬዎችን ያሳያል – የዓለም መጀመሪያ ፣ የሰው ልጅ እና እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የገባውን ቃል ኪዳን። የመጀመሪያው መጽሐፍ ዘፍጥረት በእግዚአብሔር ዓለም ፍጥረት ተከፈተ። የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ባለመታዘዙ የሰው ልጅ ብዛት ወደ ተለያዩ ብሔሮች እና ቋንቋዎች ሲከፋፈል ፍጹምው ዓለም በክፋት ውስጥ ይወድቃል።

መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ያንብቡ

ኦሪት ዘኍልቍ (Numbers)

1 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን፥ ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ዓመት እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ ድምር፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ በየስማቸው ቍጥር፥ ወንዱን በየራሱ፥ ውሰዱ።
3 ፤ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን፥ ከእስራኤል ወደ ሰልፍ የሚወጡትን ሁሉ፥ አንተና አሮን በየሠራዊቶቻቸው ቍጠሩአቸው።
4 ፤ ከየነገዱም አንድ ሰው የአባቶቹ ቤት አለቃ ከእናንተ ጋር ይሁን።
5 ፤ ከእናንተም ጋር የሚቆሙት ሰዎች ስሞቻቸው እነዚህ ናቸው፤ ከሮቤል የሰዲዮር ልጅ
6 ፤ ኤሊሱር፥ ከስምዖን የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል፥
7 ፤ ከይሁዳ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን፥
8፤ ከይሳኮር የሶገር ልጅ ናትናኤል፥
9-10፤ ከዛብሎን የኬሎን ልጅ ኤልያብ፥ ከዮሴፍ ልጆች ከኤፍሬም የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ፥ ከምናሴ የፍዳሱ ልጅ ገማልኤል፥
11-12፤ ከብንያም የጋዴዮን ልጅ አቢዳን፥ ከዳን የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር፥
13 ፤ ከአሴር የኤክራን ልጅ ፋግኤል፥
14 ፤ ከጋድ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ፥
15 ፤ ከንፍታሌም የዔናን ልጅ አኪሬ።
16 ፤ ከማኅበሩ የተመረጡ የእስራኤል አእላፍ ታላላቆች፥ የአባቶቻቸው ነገድ አለቆች እነዚህ ናቸው።
17 ፤ ሙሴና አሮንም እነዚህን በስማቸው የተጠሩትን ሰዎች ወሰዱአቸው፤
18 ፤ በሁለተኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ማኅበሩን ሁሉ ሰበሰቡአቸው፤ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን በየራሱ በየወገኑም በየአባቶቻቸውም ቤቶች በየስማቸው ቍጥር ትውልዳቸውን ተናገሩ።
19 ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ በሲና ምድረ በዳ ቈጠራቸው።
20 ፤ የእስራኤል በኵር የሮቤል ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
21 ፤ ከሮቤል ነገድ የተቈጠሩ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
22 ፤ የስምዖን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች የተቈጠሩ፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
23 ፤ ከስምዖን ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ።
24 ፤ የጋድ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
25 ፤ ከጋድ ነገድ የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ አምሳ ነበሩ።
26 ፤ የይሁዳ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
27 ፤ ከይሁዳ ነገድ የተቈጠሩት ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
28 ፤ የይሳኮር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
29 ፤ ከይሳኮር ነገድ የተቈጠሩት አምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
30 ፤ የዛብሎን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
31 ፤ ከዛብሎን ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
32 ፤ ከዮሴፍ ልጆች፥ የኤፍሬም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
33 ፤ ከኤፍሬም ነገድ የተቈጠሩት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
34 ፤ የምናሴ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
35 ፤ ከምናሴ ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
36 ፤ የብንያም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
37 ፤ ከብንያም ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
38 ፤ የዳን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
39 ፤ ከዳን ነገድ የተቈጠሩት ስድሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ።
40 ፤ የአሴር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
41 ፤ ከአሴር ነገድ የተቈጠሩት አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
42 ፤ የንፍታሌም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
43 ፤ ከንፍታሌም ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
44 ፤ የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን አሥራ ሁለቱም የእስራኤል አለቆች የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው፤ እያንዳንዱ የአባቶቹ ቤት አለቃ ነበረ።
45 ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተቈጠሩት ሁሉ፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
46 ፤ የተቈጠሩት ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ነበሩ።
47 ፤ ሌዋውያን ግን በየአባቶቻቸው ነገድ ከእነርሱ ጋር አልተቈጠሩም።
48 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። የሌዊን ነገድ አትቍጠረው፥
49 ፤ ቍጥራቸውንም ከእስራኤል ልጆች ጋር አታድርግ፤
50 ፤ ነገር ግን በምስክሩ ማደሪያና በዕቃዎች ሁሉ ለእርሱም በሚሆነው ነገር ሁሉ ላይ ሌዋውያንን አቁማቸው። ማደሪያውንና ዕቃዎችን ሁሉ ይሸከሙ፥ ያገልግሉትም፥ በማደሪያውም ዙሪያ ይስፈሩ።
51 ፤ ማደሪያውም ሲነሣ ሌዋውያን ይንቀሉት፤ ማደሪያውም በሰፈረ ጊዜ ሌዋውያን ይትከሉት፤ ሌላ ሰው ግን ቢቀርብ ይገደል።
52 ፤ የእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ በየሰፈሩ፥ በየዓላማውም፥ በየጭፍራውም ይሰፍራሉ።
53 ፤ ነገር ግን በእስራኤል ልጆች ላይ ቍጣ እንዳይወርድ ሌዋውያን በምስክሩ ማደሪያ ዙሪያ ይስፈሩ፤ ሌዋውያንም የምስክሩን ማደሪያ ይጠብቁ።
54 ፤ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረጉ።

1 ፤ እግዚአብሔርም ለሙሴና ለአሮን እንዲህ ብሎ ተናገረ።
2 ፤ የእስራኤል ልጆች እያንዳንዱ በየዓላማው በየአባቶቻቸው ቤቶች ምልክት ይስፈሩ፤ በመገናኛው ድንኳን አፋዛዥ ዙሪያ ይስፈሩ።
3 ፤ በምሥራቅ በኩል ወደ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት እንደ ሠራዊቶቻቸው የይሁዳ ሰፈር ዓላማ ሰዎች ይሆናሉ፤ የይሁዳ ልጆችም አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበረ።
4 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
5 ፤ በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የይሳኮር ነገድ ይሆናሉ፤ የይሳኮርም ልጆች አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል ነበረ።
6 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
7 ፤ በእነርሱም አጠገብ የዛብሎን ነገድ ነበረ፤ የዛብሎንም ልጆች አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ነበረ።
8 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
9 ፤ ከይሁዳ ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ሰማንያ ስድስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። እነዚህም አስቀድመው ይጓዛሉ።
10 ፤ በደቡብ በኩል በየሠራዊቶቻቸው የሮቤል ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የሮቤልም ልጆች አለቃ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር ነበረ።
11 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
12 ፤ በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የስምዖን ነገድ ናቸው፤ የስምዖንም ልጆች አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል ነበረ።
13 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ።
14 ፤ በእነርሱም አጠገብ የጋድ ነገድ ነበረ፤ የጋድም ልጆች አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ ነበረ።
15 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ አምሳ ነበሩ።
16 ፤ ከሮቤል ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ አምሳ አንድ ሺህ አራት መቶ አምሳ ነበሩ። እነርሱም ቀጥለው ይጓዛሉ።
17 ፤ ከዚያም በኋላ የመገናኛው ድንኳን በሰፈሮቹም መካከል የሌዋውያን ሰፈር ይጓዛል፤ እንደ ሰፈራቸው ሰው ሁሉ በየስፍራው በየዓላማውም ይጓዛሉ።
18 ፤ በምዕራብ በኩል እንደ ሠራዊቶቻቸው የኤፍሬም ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የኤፍሬም ልጆች አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ ነበረ።
19 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
20 ፤ በእነርሱም አጠገብ የምናሴ ነገድ ይሆናል፤ የምናሴም ልጆች አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል ነበረ።
21 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
22 ፤ በእነርሱም አጠገብ የብንያም ነገድ ይሆናል፤ ይብንያምም ልጆች አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን ነበረ።
23 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
24 ፤ ከኤፍሬም ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ስምንት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ። እነርሱም ሦስተኛ ሆነው ይጓዛሉ።
25 ፤ በሰሜን በኩል እንደ ሠራዊቶቻቸው የዳን ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የዳንም ልጆች አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር ነበረ።
26 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ስድሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ።
27 ፤ በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የአሴር ነገድ ይሆናሉ፤ የአሴርም ልጆች አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል ነበረ።
28 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
29 ፤ በእነርሱም አጠገብ የንፍታሌም ነገድ ይሆናል፤ የንፍታሌምም ልጆች አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ ነበረ።
30 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
31 ፤ ከዳን ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ መቶ አምሳ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። እነርሱም በየዓላሞቻቸው በመጨረሻ ይጓዛሉ።
32 ፤ ከእስራኤል ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች የተቈጠሩ እነዚህ ናቸው፤ ከየሰፈሩ በየሠራዊቶቻቸው የተቈጠሩ ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ነበሩ።
33 ፤ ሌዋውያን ግን እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም።<br id=”3″>
34 ፤ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ በዓላሞቻቸው አጠገብ ሰፈሩ፥ እንዲሁም በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች ተጓዙ።

1 ፤ እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ላይ ሙሴን በተናገረበት ቀን የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበረ።
2 ፤ የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው፤ በኵሩ ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር።
3 ፤ የተቀቡ ካህናት በክህነትም ያገለግሉ ዘንድ የቀደሳቸው የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው።
4 ፤ ናዳብና አብዩድ በሲና ምድረ በዳ በእግዚአብሔር ፊት ልዩ እሳት ባቀረቡ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ፤ ልጆችም አልነበሩአቸውም። አልዓዛርና ኢታምር በአባታቸው በአሮን ፊት በክህነት ያገለግሉ ነበር።
5 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
6 ፤ የሌዊን ነገድ አቅርበህ ያገለግሉት ዘንድ በካህኑ በአሮን ፊት አቁማቸው።
7 ፤ የማደሪያውንም ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ እርሱንና ማኅበሩን ሁሉ ለማገልገል የሚያስፈልገውን ነገር በመገናኛው ድንኳን ፊት ይጠብቁ።
8 ፤ የማደሪያውንም ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ የመገናኛውን ድንኳን ዕቃ ሁሉ ይጠብቁ፥ የእስራኤልን ልጆች ለማገልገል የሚያስፈልገውንም ነገር ይጠብቁ።
9 ፤ ሌዋውያንንም ለአሮንና ለልጆቹ ትሰጣለህ፤ ከእስራኤል ልጆች ለእርሱ ፈጽመው ተሰጡ።
10 ፤ አሮንንና ልጆቹን አቁማቸው፥ ክህነታቸውንም ይጠብቁ፤ ሌላ ሰውም ቢቀርብ ይገደል።
11 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
12 ፤ እነሆ፥ እኔ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ማኅፀን በሚከፍተው በበኵሩ ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ፤
13 ፤ በኵር ሁሉ ለእኔ ነውና ሌዋውያን ለእኔ ይሁኑ፤ በግብፅ ምድር በኵርን ሁሉ በመታሁ ቀን፥ ከእስራኤል ዘንድ በኵርን ሁሉ፥ ሰውንና እንስሳን፥ ለእኔ ለይቼአለሁ፤ ለእኔ ይሁኑ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
14 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው።
15 ፤ የሌዊን ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገናቸውም ቍጠር፤ ወንዱን ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን ቍጠራቸው።
16 ፤ ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ቃል እንዳዘዘው ቈጠራቸው።
17 ፤ የሌዊ ልጆች በየስማቸው እነዚህ ናቸው፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ።
18 ፤ የጌድሶንም ልጆች ስሞች በየወገናቸው እነዚህ ናቸው፤ ሎቤኒ፥ ሰሜኢ።
19 ፤ የቀዓትም ልጆች በየወገናቸው እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል።
20 ፤ የሜራሪም ልጆች በየወገናቸው፤ ሞሖሊ፥ ሙሲ። የሌዋውያን ወገኖች በየአባቶቻቸው ቤቶች እነዚህ ናቸው።
21 ፤ ለጌድሶን የሎቤናውያን ወገን የሰሜአውያንም ወገን ነበሩት፤ የጌድሶናውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው።
22 ፤ ከእነርሱ የተቈጠሩት የወንዶች ሁሉ ቍጥር ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
23 ፤ የጌድሶናውያን ወገኖች ከማደሪያው በኋላ በምዕራብ ብኩል ይሰፍራሉ።
24 ፤ የጌድሶናውያንም አባቶች ቤት አለቃ የዳኤል ልጅ ኤሊሳፍ ይሆናል።
25 ፤ ጌድሶናውያንም በመገናኛው ድንኳን የሚጠብቁት ማደሪያው፥ ድንኳኑም፥ መደረቢያውም፥ የመገናኛው ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥
26 ፤ በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለው የአደባባዩ መጋረጆች፥ የአደባባዩም ደጃፍ መጋረጃ፥ ለማገልገሉም ያሉት ገመዶች ሁሉ ይሆናል።
27 ፤ ከቀዓትም የእንበረማውያን ወገን፥ የይስዓራውያንም ወገን፥ የኬብሮናውያንም ወገን፥ የዑዝኤላውያንም ወገን ነበሩ፤ የቀዓታውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው።
28 ፤ ወንዶች ሁሉ እንደ ቍጥራቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ፤ መቅደሱንም ይጠብቁ ነበር።
29 ፤ የቀዓት ልጆች ወገኖች በማደሪያው አጠገብ በደቡብ በኩል ይሰፍራሉ።
30 ፤ የቀዓታውያንም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የዑዝኤል ልጅ ኤሊሳፈን ይሆናል።
31 ፤ ታቦቱንም፥ ገበታውንም፥ መቅረዙንም፥ መሠዊያዎቹንም፥ የሚያገለግሉበትንም የመቅደሱን ዕቃ፥ መጋረጃውንም፥ ማገልገያውንም ሁሉ ይጠብቃሉ።
32 ፤ የሌዋውያንም አለቆች አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ይሆናል፤ እርሱም መቅደሱን በሚጠብቁት ላይ ይሆናል።
33 ፤ ከሜራሪ የሞሖላውያን ወገን የሙሳያውያንም ወገን ነበሩ፤ የሜራሪ ወገኖች እነዚህ ናቸው።
34 ፤ ከእነርሱም ወንዶች ሁሉ እንደ ቍጥራቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
35 ፤ የሜራሪም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የአቢካኢል ልጅ ሱሪኤል ነበረ፤ በማደሪያው አጠገብ በሰሜን በኩል ይሰፍራሉ።
36 ፤ የሜራሪም ልጆች የሚጠብቁት የማደሪያው ሳንቆች፥ መወርወሪያዎችም፥ ተራዳዎችም፥ እግሮቹም፥ ዕቃውም ሁሉ፥
37 ፤ ማገልገያውም ሁሉ፥ በዙሪያውም የሚቆሙ የአደባባይ ምሰሶች፥ እግሮቹም፥ ካስማዎቹም፥ አውታሮቹም ይሆናሉ።
38 ፤ በማደሪያውም ፊት በምሥራቅ በኩል በመገናኛው ድንኳን ፊት በስተ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት ሙሴና አሮን ልጆቹም ይሆናሉ፥ መቅደሱንም ለእስራኤል ልጆች ይጠብቃሉ፤ ልዩም ሰው ቢቀርብ ይገደል።
39 ፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ ከሌዋውያን ወንዶች ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ በየወገናቸው የተቈጠሩት ሁሉ ሀያ ሁለት ሺህ ነበሩ።
40 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የእስራኤልን ልጆች ወንዱን በኵር ሁሉ ቍጠር፤ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን የስማቸውን ቍጥር ውሰድ፤
41 ፤ ሌዋውያንንም በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእስራኤል ልጆች እንስሶች በኵር ሁሉ ፋንታ ለእኔ ለእግዚአብሔር ውሰድ አለው።
42 ፤ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በኵር ሁሉ ቈጠረ።
43 ፤ ከእነርሱም የተቈጠሩ ወንዶች በኵሮች ሁሉ የበስማቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበሩ።
44 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
45 ፤ ሌዋውያንን በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእንስሶቻቸው ፋንታ ውሰድ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
46 ፤ በሌዋውያን ላይ ከእስራኤል ልጆች በኵር ስለ ተረፉት ስለ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ቤዛ፥ በየራሱ አምስት ሰቅል ውሰድ፤
47 ፤ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ትወስዳለህ፤ ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ነው።
48 ፤ ስለ ተረፉትም የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።
49 ፤ ሙሴም በሌዋውያን ከተቤዡት በላይ ከተረፉት ዘንድ የመቤዣውን ገንዘብ ወሰደ።
50 ፤ ከእስራኤል ልጆች በኵሮች ገንዘቡን ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ወሰደ።
51 ፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል፥ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው፥ ሙሴ የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ።

1 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
2 ፤ ከሌዊ ልጆች መካከል በየወገናቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች የቀዓትን ልጆች ድምር ውሰድ፤
3 ፤ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ በመገናኛው ድንኳን ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡበትን ሁሉ ትደምራለህ።
4 ፤ በመገናኛው ድንኳን በንዋየ ቅድሳቱ ዘንድ የቀዓት ልጆች ሥራ ይህ ነው፤
5 ፤ ከሰፈሩ በተነሡ ጊዜ አሮንና ልጆቹ ገብተው የሚሸፍነውን መጋረጃ ያውርዱ፥ የምስክሩንም ታቦት ይጠቅልሉበት፤
6 ፤ በላዩም የአቆስጣውን ቁርበት መሸፈኛ ያድርጉበት፥ ከእርሱም በላይ ሁለንተናው ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።
7 ፤ በገጽ ኅብስት ገበታ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤ በእርሱም ላይ ወጭቶቹን፥ ጭልፋዎቹንም፥ ጽዋዎቹንም፥ ለማፍሰስም መቅጃዎቹን ያድርጉ፤ ሁልጊዜም የሚኖር እንጀራ በእርሱ ላይ ይሁን።
8 ፤ በእነርሱም ላይ ቀይ መጐናጸፊያ ይዘርጉ፥ በአቆስጣውም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።
9 ፤ ሰማያዊውንም መጐናጸፊያ ይውሰዱ፥ የሚያበራውንም መቅረዝ፥ ቀንዲሎቹንም፥ መኰስተሪያዎቹንም፥ የኩስታሪ ማድረጊያዎቹንም፥ እርሱንም ለማገልገል የዘይቱን ዕቃዎች ሁሉ ይሸፍኑ፤
10 ፤ እርሱንና ዕቃዎቹን ሁሉ በአቆስጣ ቁርበት መሸፈኛ ውስጥ ያድርጉ፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉት።
11 ፤ በወርቁም መሠዊያ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።
12 ፤ በመቅደስም ውስጥ የሚያገልግሉበትን የማገልገያውን ዕቃ ሁሉ ይውሰዱ፥ በሰማያዊውም መጐናጸፊያ ውስጥ ያስቀምጡት፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉት።
13 ፤ አመዱንም ከመሠዊያው ላይ ያስወግዱ፥ ሐምራዊውንም መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤
14 ፤ የሚያገለግሉበትን ዕቃውን ሁሉም ማንደጃዎቹን ሜንጦቹንም መጫሪያዎቹንም ድስቶቹንም፥ የመሠዊያውን ዕቃ ሁሉ ያስቀምጡበት፤ በእርሱም የአቆስጣን ቁርበት መሸፈኛ ይዘርጉ፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።
15 ፤ ከሰፈሩም ሲነሡ፥ አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና የመቅደሱን ዕቃ ሁሉ ከሸፈኑ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ የቀዓት ልጆች ሊሸከሙት ይመጣሉ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅድሳቱን አይንኩ። በመገናኛው ድንኳን ዘንድ የቀዓት ልጆች ሸክም ይህ ነው።
16 ፤ የካህኑም የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት በጣፋጩም ዕጣን ላይ፥ ሁልጊዜም በሚቀርበው በእህሉ ቍርባንና በቅባቱ ዘይት ላይ ይሾም፤ ማደሪያውን ሁሉ፥ በእርሱም ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ መቅደሱንና ዕቃውን ይጠብቃል።
17 ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
18 ፤ የቀዓትን ወገኖች ነገድ ከሌዋውያን መካከል አታጥፉአቸው፤
19 ፤ ነገር ግን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በቀረቡ ጊዜ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እንጂ እንዳይሞቱ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ አሮንና ልጆቹ ይግቡ፥ ለሰውም ሁሉ ሥራውንና ሸክሙን ይዘዙ፤
20 ፤ ነገር ግን እንዳይሞቱ ንዋየ ቅድሳቱን ለድንገት እንኳ ለማየት አይግቡ።
21 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
22 ፤ የጌድሶንን ልጆች ድምር ደግሞ በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገኖቻቸውም ውሰድ።
23 ፤ የመገናኛውን ድንኳን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ቍጠራቸው።
24 ፤ የጌድሶናውያን ወገኖች ሥራ በማገልገልና በመሸከም ይህ ነው፤
25 ፤ የማደሪያውን መጋረጆች፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ መደረቢያውን፥ በላዩም ያለውን የአቆስጣውን ቁርበት መደረቢያ፥ የመገናኛውንም ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥
26 ፤ በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለውን የአደባባዩን መጋረጃ፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቻቸውንም፥ ለማገልገልም የሚሠሩበትን ዕቃ ሁሉ ይሸከሙ፤ በዚህ ያገልግሉ።
27 ፤ የጌድሶናውያን አገልግሎት ሁሉ፥ ሸክማቸውም ሁሉ፥ ሥራቸውም ሁሉ በአሮንና በልጆቹ ትእዛዝ ይሁን፤ የሚደርስባቸውንም ሸክም ሁሉ ትነግሩአቸዋላችሁ።
28 ፤ የጌድሶናውያን ወገኖች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ይህ ነው፤ ከካህኑ ከአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች ይሆናሉ።
29 ፤ የሜራሪንም ልጆች በየወገናቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቍጠራቸው።
30 ፤ የመገናኛውን ድንኳን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ቍጠራቸው።
31 ፤ በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ባለው አገልግሎታቸው ሁሉ፥ የማደሪያው ሳንቆች፥ መወርወሪያዎቹም፥ ተራዳዎቹም፥ እግሮቹም፥
32 ፤ በዙሪያውም የሚቆሙት የአደባባዩ ምሰሶች፥ እግሮቹም፥ ካስማዎቹም፥ አውታሮቹም፥ ዕቃዎቹና ማገልገያዎቹ ሸክማቸው ነው፤ የሚጠብቁትንም የሸክማቸውን ዕቃ ሁሉ በስማቸው ቍጠሩ።
33 ፤ የሜራሪ ልጆች ወገኖች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ከካህኑ ክአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች በየአገልግሎታቸው ሁሉ ይህ ነው።
34 ፤ ሙሴና አሮንም የሕቡም አለቆች የቀዓትን ልጆች በየወገናቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቈጠሩአቸው።
35 ፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ወደ አገግሎት የገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉትን ቈጠሩአቸው፤
36 ፤ በየወገናቸውም ከእነርሱ የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ነበሩ።
37 ፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከቀዓታውያን ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው።
38 ፤ በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት የጌድሶን ልጆች፥
39 ፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የገቡት፥ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥
40 ፤ በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሠላሳ ነበሩ።
41 ፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከጌድሶን ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው።
42 ፤ በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥
43 ፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ወደ አገልግሎት የገቡት ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥
44 ፤ በየወገናቸው የተቈጠሩት ሦስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
45 ፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው።
46 ፤ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች ከሌዋውያን የተቈጠሩት ሁሉ፥ ሙሴና አሮን የእስራኤልም አለቆች የቈጠሩአቸው፥
47 ፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራውን ለመሥራትና ዕቃውን ለመሸከም የገቡት ሁሉ፥ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥
48 ፤ ከእነርሱ የተቈጠሩት ስምንት ሺህ እምስት መቶ ሰማንያ ነበሩ።
49 ፤ እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ እያንዳንዳቸው በየአገልግሎታቸውና በየሸክማቸው በሙሴ እጅ ተቈጠሩ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ በእርሱ ተቈጠሩ።

1 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ የእስራኤል ልጆች ለምጻሙን ሁሉ፥ ፈሳሽ ነገርም ያለበትን ሁሉ፥ በሬሳም የረከሰውን ሁሉ ከሰፈሩ እንዲያወጡ እዘዛቸው፤
3 ፤ ወንዱንና ሴቱን አውጡ፤ እኔ በመካከሉ የማድርበትን ሰፈራቸውን እንዳያረክሱ ከሰፈሩ አውጡአቸው።
4 ፤ የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፥ ከሰፈሩ አወጡአቸው፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው፥ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ።
5 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
6 ፤ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። ወንድ ወይም ሴት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይተላለፍ ዘንድ ሰው የሚሠራውን ኃጢአት ቢሠራ፥ በዚያም ሰው ላይ በደል ቢሆን፥ በሠራው ኃጢአት ይናዘዝ፤
7 ፤ የወሰደውንም በሙሉ ይመልስ አምስተኛውንም ይጨምርበት፥ ለበደለውም ሰው ይስጠው።
8 ፤ ነገር ግን ይመልስለት ዘንድ ሰውዮው ዘመድ ባይኖረው፥ ስለ በደል ለእግዚአብሔር የሚመልሰው ነገር ለካህኑ ይሁን፥ ይህም ስለ እርሱ ማስተሰረያ ከሚደረግበት አውራ በግ በላይ ይጨመር።
9 ፤ የእስራኤልም ልጆች ለካህኑ የሚያቀርቡት የተቀደሰ የማንሣት ቍርባን ሁሉ ለእርሱ ይሁን።
10 ፤ የተቀደሰ የሰው ነገር ሁሉ፥ ሰውም ለካህኑ የሚሰጠው ሁሉ ለእርሱ ይሁን።
11 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
12 ፤ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። የማንኛውም ሰው ሚስት ከእርሱ ፈቀቅ ብትል፥ በእርሱም ላይ ብትበድል፥
13 ፤ ከሌላም ሰው ጋር ብትተኛ፥ ከባልዋም ዓይን ቢሸሸግ፥ እርስዋም ተሰውራ ብትረክስ፥ ምስክርም ባይኖርባት፥ በምንዝርም ባትገኝ፥
14 ፤ በባልዋም ላይ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ እርስዋም ስትረክስ ስለ ሚስቱ ቢቀና፤ ወይም እርስዋ ሳትረክስ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ ስለ ሚስቱም ቢቀና፤
15 ፤ ያ ሰው ሚስቱን ወደ ካህኑ ያምጣት፥ የኢፍ መስፈሪያም አሥረኛ እጅ ገብስ ዱቄት ቍርባን ስለ እርስዋ ያምጣ፤ የቅንዓት ቍርባን ነውና፥ ኃጢአትንም የሚያሳስብ የመታሰቢያ ቍርባን ነውና ዘይት አያፍስስበት፥ ዕጣንም አይጨምርበት።
16 ፤ ካህኑም ያቀርባታል በእግዚአብሔርም ፊት ያቆማታል፤
17 ፤ ካህኑም የተቀደሰ ውኃ በሸክላ ዕቃ ይወስዳል፤ ካህኑም በማደሪያው ውስጥ ካለው ትቢያ ወስዶ በውኃ ላይ ይረጨዋል፤
18 ፤ ካህኑም ሴቲቱን በእግዚአብሔር ፊት ያቆማታል፥ የሴቲቱንም ራስ ይገልጣል፥ በእጅዋም ለመታሰቢያ የሚሆነውን የእህል ቍርባን፥ ለቅንዓት ቍርባን፥ ያኖራል፤ በካህኑም እጅ እርግማንን የሚያመጣው መራራ ውኃ ይሆናል።
19 ፤ ካህኑም ያምላታል፥ ሴቲቱንም እንዲህ ይላታል። ሌላ ወንድ አልተኛሽ፥ ባልሽንም አልተውሽ፥ ራስሽንም አላረከስሽ እንደ ሆነ፥ እርግማንን ከሚያመጣ ከዚህ መራራ ውኃ ንጹሕ ሁኚ፤
20 ፤ ነገር ግን ባልሽን ትተሽ ረክሰሽ እንደ ሆነ፥ ከባልሽም ሌላ ከወንድ ጋር ተኝተሽ እንደሆነ፤
21 ፤ ካህኑም ሴቲቱን በመርገም መሐላ ያምላታል፥ ካህኑም ሴቲቱን። እግዚአብሔር ጭንሽን እያሰለሰለ ሆድሽንም እየነፋ፥ እግዚአብሔር ለመርገምና ለመሐላ በሕዝብሽ መካከል ያድርግሽ፤
22 ፤ እርግማንንም የሚያመጣ ይህ ውኃ ወደ ሆድሽ ይግባ፥ ሆድሽንም ይንፋው፥ ጭንሽንም ያበስብሰው ይላታል፤ ሴቲቱም። አሜን አሜን ትላለች።
23 ፤ ካህኑም እነዚህን መርገሞች በሰሌዳ ይጽፈዋል፥ በመራራውም ውኃ ይደመስሰዋል፤
24 ፤ እርግማን የሚያመጣውንም መራራ ውኃ ለሴቲቱ ይጠጣታል፤ የእርግማኑም ውኃ በገባባት ጊዜ መራራ ይሆናል።
25 ፤ ካህኑም የቅንዓቱን የእህል ቍርባን ከሴቲቱ እጅ ይወስዳል፥ የእህሉንም ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዘዋል፥ ወደ መሠዊያውም ያመጣዋል፤
26 ፤ ካህኑም ከእህሉ ቍርባን አንድ እፍኝ ሙሉ ለመታሰቢያው ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፥ ከዚያም በኋላ ለሴቲቱ ውኃውን ያጠጣታል።
27 ፤ ውኃውን ካጠጣት በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ ረክሳና በባልዋ ላይ አመንዝራ እንደ ሆነች፥ እርግማንን የሚያመጣው ውኃ ገብቶ መራራ ይሆንባታል፥ ሆድዋም ይነፋል፥ ጭንዋም ይሰለስላል፤ ሴቲቱም በሕዝብዋ መካከል ለመርገም ትሆናለች።
28፤ ያልረከሰች ያለ ነውርም እንደ ሆነች፥ ንጹሕ ትሆናለች፥ ልጆችንም ታረግዛለች።
29-30፤ ሴት ባልዋን ትታ በረከሰች ጊዜ፥ ወይም በሰው ላይ የቅንዓት መንፈስ በመጣበት ጊዜ፥ ስለ ሚስቱም በቀና ጊዜ፥ የቅንዓት ሕግ ይህ ነው፤ ሴቲቱንም በእግዚአብሔር ፊት ያቁማት፥ ካህኑም እንደዚህ ሕግ ሁሉ ያድርግባት።
31፤ ሰውዮውም ከኃጢአት ንጹሕ ይሆናል፥ ሴቲቱም ኃጢአትዋን ትሸከማለች።

1 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። ሰው ወይም ሴት ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ያደርግ ዘንድ የናዝራዊነት ስእለት ቢሳል፥
3 ፤ ከወይን ጠጅና ከሚያሰክር መጠጥ ራሱን የተለየ ያድርግ፤ ከወይን ወይም ከሌላ ነገር የሚገኘውን ሆምጣጤ አይጠጣ፥ የወይንም ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን እሸት ወይም ዘቢብ አይብላ።
4 ፤ ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ከወይን የሆነውን ነገር ሁሉ ከውስጡ ፍሬ ጀምሮ እስከ ገፈፎው ድረስ አይብላ።
5 ፤ ራሱን ለመለየት ስእለት ባደረገበት ወራት ሁሉ በራሱ ላይ ምላጭ አይደርስም፤ ለእግዚአብሔር የተለየበት ወራት እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰ ይሆናል፥ የራሱንም ጠጕር ያሳድጋል።
6 ፤ ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ።
7 ፤ ለአምላኩ ያደረገው እስለት በራሱ ላይ ነውና አባቱ ወይም እናቱ ወይም ወንድሙ ወይም እኅቱ ሲሞቱ ሰውነቱን አያርክስባቸው።
8 ፤ ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው።
9 ፤ ሰውም በአጠገቡ ድንገት ቢሞት የተለየውንም ራሱን ቢያረክስ፥ እርሱ በሚነጻበት ቀን ራሱን ይላጭ፤ በሰባተኛው ቀን ይላጨው።
10 ፤ በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ያምጣ፤
11 ፤ ካህኑም አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርበዋል፤ በሬሳም የተነሣ ኃጢአት ሠርቶአልና ያስተሰርይለታል፥ በዚያም ቀን ራሱን ይቀድሰዋል።
12 ፤ ራሱን የተለየ ያደረገበትን ወራትም ለእግዚአብሔር ይቀድሳል፥ የአንድ ዓመትም ተባት ጠቦት ለበደል መሥዋዕት ያምጣ፤ ናዝራዊነቱ ግን ረክሶአልና ያለፈው ወራት ሁሉ ከንቱ ይሆናል።
13 ፤ የመለየቱ ወራት በተፈጸመ ጊዜ የናዝራዊው ሕግ ይህ ነው፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይቅረብ፤
14 ፤ ቍርባኑንም ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለባትን የአንድ ዓመት እንስት ጠቦት ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለበትን አውራ በግ ለደኅንነት መሥዋዕት፥
15 ፤ አንድ ሌማትም ቂጣ እንጀራ፥ በዘይት የተለወሰ ከመልካም ዱቄትም የተሠሩ እንጐቻዎች፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ የእህሉንም ቍርባን፥ የመጠጡንም ቍርባን ያቅርብ።
16 ፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባቸዋል፥ የኃጢአቱንም መሥዋዕት የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ያሳርግለታል።
17 ፤ አውራውንም በግ ለደኅንነት መሥዋዕት ከሌማቱ ቂጣ እንጀራ ጋር ወደ እግዚአብሔር ያቀርባል፤ ካህኑም ደግሞ የእህሉን ቍርባንና የመጠጡን ቍርባን ያቀርባል።
18 ፤ ናዝራዊውም የተለየውን የራሱን ጠጕር በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ይላጫል፥ የመለየቱንም ራስ ጠጕር ወስዶ ከደኅንነት መሥዋዕት በታች ወዳለው እሳት ይጥለዋል።
19 ፤ ካህኑም የተቀቀለውን የአውራውን በግ ወርች፥ ከሌማቱም አንድ ቂጣ እንጐቻ አንድም ስስ ቂጣ ይወስዳል፥ የተለየውንም የራስ ጠጕር ከተላጨ በኋላ በናዝራዊው እጆች ላይ ያኖራቸዋል፤
20 ፤ ካህኑም እነዚህን ለመወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ ይህም ከሚወዘወዘው ፍርምባና ከሚነሣው ወርች ጋር ለካህኑ የተቀደሰ ነው። ከዚያም በኋላ ናዝራዊው ወይን ይጠጣ ዘንድ ይችላል።
21 ፤ ስእለቱን የተሳለው የናዝራዊ፥ እጁም ከሚያገኘው ሌላ ስለ ናዝራዊነቱ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የቍርባኑ ሕግ ይህ ነው፤ ስእለቱን እንደ ተሳለ እንደ ናዝራዊነቱ ሕግ እንዲሁ ያደርጋል።
22 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
23 ፤ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው። የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩአቸው እንዲህ በሉአቸው።
24 ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ፥ ይጠብቅህም፤
25 ፤ እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም፤
26 ፤ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፥ ሰላምንም ይስጥህ።
27 ፤ እንዲሁ ስሜን በእስራኤል ልጆች ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እባርካቸዋለሁ።

1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ማደሪያውን ፈጽሞ ከተከለ በኋላ፥ እርሱንና ዕቃውን ሁሉ ከቀባና ከቀደሰ በኋላ፥ መሠዊያውንና ዕቃውንም ሁሉ ከቀባና ከቀደሰ በኋላ፤
2 ፤ የእስራኤል አለቆች፥ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ቍርባናቸውን አቀረቡ፤ እነዚህም ከተቈጠሩት በላይ የተሾሙ የነገዶች አለቆች ነበሩ።
3 ፤ መባቸውንም በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ፥ የተከደኑ ስድስት ሰረገሎች አሥራ ሁለትም በሬዎች፤ በየሁለቱም አለቆች አንድ ሰረገላ አቀረቡ፥ ሁሉም እያንዳንዱ አንድ በሬ በማደሪያው ፊት አቀረቡ።
4 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
5 ፤ ለመገናኛው ድንኳን ማገልገል ይሆን ዘንድ ከእነርሱ ተቀብለህ ለሌዋውያን ለእያንዳንዱ እንደ አገልግሎታቸው ስጣቸው።
6 ፤ ሙሴም ሰረገሎችንና በሬዎችን ተቀብሎ ለሌዋውያን ሰጣቸው።
7 ፤ ለጌድሶን ልጆች እንደ አገልግሎታቸው ሁለት ሰረገሎችንና አራት በሬዎችን ሰጣቸው።
8 ፤ ከካህኑም ከአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች ላሉት ለሜራሪ ልጆች እንደ አገልግሎታቸው አራት ሰረገሎችንና ስምንት በሬዎችን ሰጣቸው።
9 ፤ ለቀዓት ልጆች ግን መቅደሱን ማገልገል የእነርሱ ነውና፥ በትከሻቸውም ይሸከሙት ነበርና ምንም አልሰጣቸውም።
10 ፤ መሠዊያውም በተቀባ ቀን አለቆቹ መሠዊያውን ለመቀደስ ቍርባንን አቀረቡ፤ አለቆችም መባቸውን በመሠዊያው ፊት አቀረቡ።
11 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። አለቆቹ መሠዊያውን ለመቀደስ መባቸውን እያንዳንዱ በቀን በቀኑ ያቅርቡ አለው።
12 ፤ በመጀመሪያውም ቀን መባውን ያቀረበ ከይሁዳ ነገድ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበረ።
13 ፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
14 ፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
15 ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
16 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
17 ፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የአሚናዳብ ልጅ የነአሶን መባ ይህ ነበረ።
18 ፤ በሁለተኛውም ቀን የይሳኮር አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል አቀረበ።
19 ፤ ለመባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉትን፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነውን አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነውን አንድ የብር ድስት፤
20 ፤ ዕጣንም የተሞላውን ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነውን አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
21 ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
22 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
23 ፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቀረበ፤ የሶገር ልጅ የናትናኤ መባ ይህ ነበረ።
24 ፤ በሦስተኛውም ቀን የዛብሎን ልጆች አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ፤
25 ፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
26 ፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
27 ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
28 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
29 ፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የኬሎን ልጅ የኤልያብ መባ ይህ ነበረ።
30 ፤ በአራተኛውም ቀን የሮቤል ልጆች አለቃ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር፤
31 ፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
32 ፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
33 ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
34 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
35 ፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የሰዲዮር ልጅ የኤሊሱር መባ ይህ ነበረ።
36 ፤ በአምስተኛውም ቀን የስምዖን ልጆች አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል፤
37 ፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
38 ፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
39 ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
40 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
41 ፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የሱሪሰዳይ ልጅ የሰለሚኤል መባ ይህ ነበረ።
42 ፤ በስድስተኛውም ቀን የጋድ ልጆች አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ፤
43 ፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ማዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
44 ፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
45 ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
46 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
47 ፤ ለደኅነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የራጉኤል ልጅ የኤሊሳፍ መባ ይህ ነበረ።
48 ፤ በሰባተኛውም ቀን የኤፍሬም ልጆች አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ፤
49 ፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑ ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
50 ፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
51 ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
52 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
53 ፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የዓሚሁድ ልጅ የኤሊሳማ መባ ይህ ነበረ።
54 ፤ በስምንተኛውም ቀን የምናሴ ልጆች አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል፤
55 ፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
56 ፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
57 ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
58 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
59 ፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የፍዳሱር ልጅ የገማልኤል መባ ነበረ።
60 ፤ በዘጠነኛውም ቀን የብንያም ልጆች አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን፤
61 ፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
62 ፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
63 ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
64 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
65 ፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የጋዴዮን ልጅ የአቢዳን መባ ይህ ነበረ።
66 ፤ በአሥረኛውም ቀን የዳን ልጆች አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር፤
67 ፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
68 ፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
69 ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
70 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
71 ፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የአሚሳዳይ ልጅ የአኪዔዘር መባ ይህ ነበረ።
72 ፤ በአሥራ አንደኛውም ቀን የአሴር ልጆች አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል፤
73 ፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
74 ፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
75 ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
76 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
77 ፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የኤክራን ልጅ የፋግኤል መባ ይህ ነበረ።
78 ፤ በአሥራ ሁለተኛውም ቀን የንፍታሌም ልጆች አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ፤
79 ፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
80 ፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
81 ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥
82 ፤ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
83 ፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የዔናን ልጅ የአኪሬ መባ ይህ ነበረ።
84 ፤ መሠዊያው በተቀባ ቀን የእስራኤል አለቆች ለመቀደሻው ያቀረቡት ቍርባን ይህ ነበረ፤ አሥራ ሁለት የብር ወጭቶች፥ አሥራ ሁለት የብር ድስቶች፥ አሥራ ሁለት የወርቅ ጭልፋዎች፤
85 ፤ እያንዳንዱም የብር ወጭት መቶ ሠላሳ ሰቅል፥ እያንዳንዱም ድስት ሰባ ሰቅል ነበረ፤ የዚህም ዕቃ ሁሉ ብር በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ።
86 ፤ ዕጣንም የተሞሉ አሥራ ሁለቱ የወርቅ ጭልፋዎች፥ እያንዳንዱ በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን አሥር አሥር ሰቅል ነበረ፤ የጭልፋዎቹ ወርቅ ሁሉ መቶ ሀያ ሰቅል ነበረ።
87 ፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት ከብት ሁሉ ከእህሉ ቍርባን ጋር አሥራ ሁለት ወይፈኖች፥ አሥራ ሁለትም አውራ በጎች፥ አሥራ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ነበሩ፤ የኃጢአትም መሥዋዕት አውራ ፍየሎች አሥራ ሁለት ነበሩ።
88 ፤ የደኅንነትም መሥዋዕት ከብት ሁሉ ሀያ አራት በሬዎች፥ ስድሳም አውራ በጎች፥ ስድሳም አውራ ፍየሎች፥ ስድሳም የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበሩ። መሠዊያው ከተቀባ በኋላ ለመቀደሻው የቀረበ ቍርባን ይህ ነበረ።
89 ፤ ሙሴም ወደ መገናኛው ድንኳን እርሱን ለመነጋገር በገባ ጊዜ በምስክሩ ታቦት ላይ ካለው ከስርየት መክደኛ በላይ ከኪሩቤልም መካከል ድምፁ ሲናገረው ይሰማ ነበር፤ እርሱም ይናገረው ነበር።

1 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ መብራቶቹን ስትለኵስ ሰባቱ መብራቶች በመቅረዙ ፊት ያበራሉ ብለህ ለአሮን ንገረው።
3 ፤ አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ በመቅረዙ ፊት መብራቶቹን ለኰሰ።
4 ፤ መቅረዙም እንዲህ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ተሠራ፤ እስከ አገዳውና እስከ አበቦቹ ድረስ ከተቀጠቀጠ ሥራ ነበረ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳሳየው ምሳሌ መቅረዙን እንዲሁ አደረገ።
5 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
6 ፤ ከእስራኤል ልጆች መካከል ሌዋውያንን ወስደህ አንጻቸው።
7 ፤ ታነጻቸው ዘንድ እንዲህ ታደርግላቸዋለህ፤ ኃጢአትን የሚያነጻውን ውኃ እርጫቸው፥ በገላቸውም ሁሉ ምላጭ ያሳልፉ፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፥ ይታጠቡም።
8 ፤ ወይፈንን፥ ለእህሉም ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄትን ይውሰዱ፥ ሌላውንም ወይፈን ለኃጢአት መሥዋዕት ውሰድ።
9 ፤ ሌዋውያንንም በመገናኛው ድንኳን ፊት አቅርብ፤ የእስራኤልንም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስብ።
10 ፤ ሌዋውያንንም በእግዚአብሔር ፊት አቅርባቸው፤ የእስራኤልም ልጆች በሌዋውያን ላይ እጃቸውን ይጫኑባቸው።
11 ፤ አሮንም ሌዋውያን እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ከእስራኤል ልጆች መካከል ስጦታ አድርጎ፥ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ።
12 ፤ ሌዋውያኑም በወይፈኖቹ ራሶች ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ፤ ለሌዋውያንም ስለ ማስተስረያ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርብ።
13 ፤ ሌዋውያንንም በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ስጦታ አድርገህ አቅርባቸው።
14 ፤ እንዲሁ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ።
15 ፤ ከዚያም በኋላ ሌዋውያን የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ፤ ታነጻቸውማለህ፥ ስጦታም አድርገህ ታቀርባቸዋለህ።
16 ፤ እነርሱም ከእስራኤል ልጆች መካከል ፈጽሞ ለእኔ ተሰጥተዋልና፤ በእስራኤል ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ማኅፀን በሚከፍት ሁሉ ፋንታ ለእኔ ወስጄአቸዋለሁ።
17 ፤ በግብፅ ምድር ያለውን በኵር ሁሉ በገደልሁበት ቀን የእስራኤልን ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ሰው ወይም እንስሳ፥ ለእኔ ቀድሼአቸዋለሁና የእኔ ናቸው።
18 ፤ በእስራኤልም ልጆች በኵራት ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ወስጄአለሁ።
19 ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ መቅደሱ በቀረቡ ጊዜ መቅሠፍት እንዳያገኛቸው፥ ለእስራኤል ልጆች ያስተሰርዩላቸው ዘንድ፥ የእስራኤልንም ልጆች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለአሮንና ለልጆቹ ስጦታ አድርጌ ሰጥቼአቸዋለሁ።
20 ፤ ሙሴና አሮን የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲሁ በሌዋውያን ላይ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉላቸው።
21 ፤ ሌዋውያንም ከኃጢአት ተጣጠቡ፥ ልብሳቸውንም አጠቡ፤ አሮንም ስጦታ አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት አቀረባቸው፥ አሮንም ያነጻቸው ዘንድ አስተሰረየላቸው።
22 ፤ ከዚያም በኋላ ሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በአሮንና በልጆቹ ፊት አገልግሎታቸውን ይሠሩ ዘንድ ገቡ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረጉላቸው።
23 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
24 ፤ የሌዋውያን ሕግ ይህ ነው፤ ከሀያ አምስት ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት በመገናኛው ድንኳን ሥራ ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ።
25 ፤ ዕድሜአቸውም አምሳ ዓመት ሲሞላ የአገልግሎታቸውን ሥራ ይተዋሉ፥ ከዚያም በኋላ አይሠሩም፤
26 ፤ የተሰጣቸውን ይጠብቁ ዘንድ ወንድሞቻቸውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለግላሉ፤ የድንኳኑን አገልግሎት አይሠሩም። እንዲሁ ስለ ሥራቸው በሌዋውያን ላይ ታደርጋለህ።

1 ፤ ከግብፅ ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በሲና ምድረ በዳ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ የእስራኤል ልጆች በጊዜው ፋሲካውን ያድርጉ፤
3 ፤ በዚህ ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በጊዜው አድርጉት፤ እንደ ሥርዓቱ ሁሉ እንደ ፍርዱም ሁሉ አድርጉት።
4 ፤ ሙሴም ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች ተናገራቸው።
5 ፤ በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በሲና ምድረ በዳ ፋሲካን አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ።
6 ፤ በሞተ ሰው ሬሳ የረከሱ ሰዎችም ነበሩ፥ ስለዚህም በዚያ ቀን ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ አልቻሉም። በዚያም ቀን ወደ ሙሴና ወደ አሮን ቀረቡ።
7 ፤ እነዚያም ሰዎች። በሞተ ሰው ሬሳ ረክሰናል፤ በእስራኤል ልጆች መካከል በጊዜው ቍርባን ለእግዚአብሔር እንዳናቀርብ ስለ ምን እንከለከላለን? አሉት።
8 ፤ ሙሴም። እግዚአብሔር ስለ እናንተ የሚያዝዘውን እስክሰማ ድረስ ቈዩ አላቸው።
9 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
10 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ከእናንተ ወይም ከትውልዶቻችሁ ዘንድ ሰው በሬሳ ቢረክስ፥ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ፥ እርሱ ደግሞ ለእግዚአብሔር ፋሲካን ያድርግ።
11 ፤ በሁለተኛው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ ያድርጉት፤ ከቂጣ እንጀራና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት።
12 ፤ ከእርሱም እስከ ነገ ምንም አያስቀሩ፥ ከእርሱም አጥንትን አይስበሩ፤ እንደ ፋሲካ ሥርዓት ሁሉ ያድርጉት።
13 ፤ ነገር ግን ንጹሕ የሆነ ሰው በመንገድም ላይ ያልሆነ ፋሲካን ባያደርግ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ የእግዚአብሔርን ቍርባን በጊዜው አላቀረበምና ያ ሰው ኃጢአቱን ይሸከማል።
14 ፤ በመካከላችሁም መጻተኛ ቢኖር፥ ለእግዚአብሔር ፋሲካን ያደርግ ዘንድ ቢወድድ፥ እንደ ፋሲካ ሥርዓት እንደ ፍርዱም እንዲሁ ያድርግ፤ ለመጻተኛና ለአገር ልጅ አንድ ሥርዓት ይሁንላችሁ።
15 ፤ ማደሪያውም በተተከለ ቀን ደመናው የምስክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ከማታም ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ በማደሪያው ላይ እንደ እሳት ይመስል ነበር።
16 ፤ እንዲሁ ሁልጊዜ ነበረ፤ በቀን ደመና በሌሊትም የእሳት አምሳል ይሸፍነው ነበር።
17 ፤ ደመናውም ከድንኳኑ ላይ በተነሣ ጊዜ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፤ ደመናውም በቆመበት ስፍራ በዚያ የእስራኤል ልጆች ይሰፍሩ ነበር።
18 ፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር። ደመናው በማደሪያው ላይ በተቀመጠበት ዘመን ሁሉ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር።
19 ፤ ደመናውም በማደሪያው ላይ ብዙ ቀን በተቀመጠ ጊዜ የእስራኤል ልጆች የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር።
20 ፤ አንዳንድ ጊዜ ደመናው ጥቂት ቀን በማደሪያው ላይ ይሆን ነበር፤ በዚያን ጊዜ እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፤ እንደ እግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር።
21 ፤ አንዳንድ ጊዜም ደመናው ከማታ ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ ይቀመጥ ነበር፤ በጥዋትም ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር፤ በቀንም በሌሊትም ቢሆን፥ ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር።
22 ፤ ደመናውም ሁለት ቀን ወይም አንድ ወር ወይም አንድ ዓመት ቆይቶ በማደሪያው ላይ ቢቀመጥ የእስራኤል ልጆች በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር፤ ነገር ግን በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር።
23 ፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር፥ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር።

1 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ሁለት የብር መለከቶች አጠፍጥፈህ ለአንተ አድርግ፤ ማኅበሩን ለመጥራት ከሰፈራቸውም ለማስጓዝ ይሁኑልህ።
3 ፤ ሁለቱም መለከቶች በተነፉ ጊዜ ማኅበሩ ሁሉ ወደ አንተ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይሰብሰቡ።
4 ፤ አንድ መለከት ሲነፋ ታላላቆቹ የእስራኤል አእላፍ አለቆች ወደ አንተ ይሰብሰቡ።
5 ፤ መለከትንም ከፍ ባለ ድምፅ ስትነፉ በምሥራቅ በኩል የሰፈሩት ይጓዙ።
6 ፤ ሁለተኛውንም ከፍ ባለ ድምፅ ስትነፉ በደቡብ በኩል የሰፈሩት ይጓዙ፤ ለማስጓዝ መለከትን ይነፋሉ።
7 ፤ ጉባኤውም በሚሰበሰብበት ጊዜ ንፉ፥ ነገር ግን ድምፁን ከፍ አታድርጉት።
8 ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ መለከቶቹን ይንፉ፤ እነርሱም ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ይሁኑ።
9 ፤ በሚገፋችሁም ጠላት ላይ በምድራችሁ ወደ ሰልፍ ስትወጡ ከፍ ባለ ድምፅ መለከቶቹን ንፉ፤ በእግዚአብሔርም በአምላካችሁ ፊት ትታሰባላችሁ፥ ከጠላቶቻችሁም ትድናላችሁ።
10 ፤ ደግሞ በደስታችሁ ቀን፥ በበዓላታችሁም ዘመን፥ በወርም መባቻ፥ በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በደኅንነት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቶቹን ንፉ፤ እነርሱም በአምላካችሁ ፊት ለመታሰቢያ ይሆኑላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
11 ፤ በሁለተኛውም ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያኛው ቀን እንዲህ ሆነ፤ ደመናው ከምስክሩ ማደሪያ ላይ ተነሣ።
12 ፤ የእስራኤልም ልጆች ከሲና ምድረ በዳ በየጕዞአቸው ተጓዙ፤ ደመናውም በፋራን ምድረ በዳ ቆመ።
13 ፤ በመጀመሪያም እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ ተጓዙ።
14 ፤ በመጀመሪያም የይሁዳ ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን አለቃ ነበረ።
15 ፤ በይሳኮርም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የሶገር ልጅ ናትናኤል አለቃ ነበረ።
16 ፤ በዛብሎንም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የኬሎን ልጅ ኤልያብ አለቃ ነበረ።
17 ፤ ማደሪያውም ተነቀለ፤ ማደሪያውንም የተሸከሙ የጌድሶን ልጆችና የሜራሪ ልጆች ተጓዙ።
18 ፤ የሮቤልም ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር አለቃ ነበረ።
19 ፤ በስምዖንም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል አለቃ ነበረ።
20 ፤ በጋድም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ አለቃ ነበረ።
21 ፤ ቀዓታውያንም መቅደሱን ተሸክመው ተጓዙ፤ እነዚህም እስኪመጡ ድረስ እነዚያ ማደሪያውን ተከሉ።
22 ፤ የኤፍሬምም ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ አለቃ ነበረ።
23 ፤ በምናሴም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል አለቃ ነበረ።
24 ፤ በብንያምም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን አለቃ ነበረ።
25 ፤ ከሰፈሮቹ ሁሉ በኋላ የሆነ የዳን ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር አለቃ ነበረ።
26 ፤ በአሴርም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የኤክራን ልጅ ፋግኤል አለቃ ነበረ።
27 ፤ በንፍታሌምም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የዔናን ልጅ አኪሬ አለቃ ነበረ።
28 ፤ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ጕዞ በየሠራዊታቸው ነበረ፤ እነርሱም ተጓዙ።
29 ፤ ሙሴም የሚስቱን አባት የምድያማዊውን የራጉኤልን ልጅ ኦባብን። እግዚአብሔር። ለእናንተ እሰጠዋለሁ ወዳለው ስፍራ እንሄዳለን፤ እግዚአብሔር ስለ እስራኤል መልካምን ነገር ተናግሮአልና አንተ ከእኛ ጋር ና፥ መልካምን እናደርግልሃለን አለው።
30 ፤ እርሱም። አልሄድም፥ ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ዘመዶቼ እሄዳለሁ አለው።
31 ፤ እርሱም። እባክህ፥ በምድረ በዳ የምንሰፍርበትን አንተ ታውቃለህና፥ እንደ ዓይኖቻችንም ትሆንልናለህና አትተወን፤
32 ፤ ከእኛም ጋር ብትሄድ እግዚአብሔር ከሚያደርግልን መልካም ነገር ሁሉ እኛ ለአንተ እናደርጋለን አለ።
33 ፤ ከእግዚአብሔርም ተራራ የሦስት ቀን መንገድ ያህል ተጓዙ፤ የእግዚአብሔርም የኪዳኑ ታቦት የሚያድርበትን ስፍራ ይፈልግላቸው ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ ቀደማቸው።
34 ፤ ከሰፈራቸውም በተጓዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ደመና ቀን ቀን በላያቸው ነበረ።
35 ፤ ሙሴም ታቦቱ በተጓዘ ጊዜ። አቤቱ፥ ተነሣ፥ ጠላቶችህም ይበተኑ፥ የሚጠሉህም ከፊትህ ይሽሹ ይል ነበር።
36 ፤ ባረፈም ጊዜ። አቤቱ፥ ወደ እስራኤል እልፍ አእላፋት ተመለስ ይል ነበር።

1 ፤ ሕዝቡም ክፉ ሆነው በእግዚአብሔር ላይ አጕረመረሙ፤ እግዚአብሔርም ሰምቶ ተቈጣ፤ የእግዚአብሔርም እሳት በመካከላቸው ነደደች፥ የሰፈሩንም ዳር በላች።
2 ፤ ሕዝቡም ወደ ሙሴ ጮኹ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እሳቲቱም ጠፋች።
3 ፤ የእግዚአብሔርም እሳት በመካከላቸው ስለነደደች የዚያን ስፍራ ስም ተቤራ ብሎ ጠራው።
4 ፤ በመካከላቸውም የነበሩ ልዩ ልዩ ሕዝብ እጅግ ጐመጁ፤ የእስራኤል ልጆች ደግሞ ያለቅሱ ነበር። የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል?
5 ፤ በግብፅ ያለ ዋጋ እንበላው የነበረውን ዓሣ፥ ዱባውንም፥ በጢኹንም፥ ኩራቱንም፥ ቀዩንም ሽንኩርት፥ ነጩንም ሽንኩርት እናስባለን፤
6 ፤ አሁን ግን ሰውነታችን ደረቀች፤ ዓይናችንም ከዚህ መና በቀር ምንም አታይም አሉ።
7 ፤ መናውም እንደ ድንብላል ዘር ነበረ፥ መልኩም ሙጫ ይመስል ነበር።
8 ፤ ሕዝቡም እየዞሩ ይለቅሙ ነበር፥ በወፍጮም ይፈጩት፥ ወይም በሙቀጫ ይወቅጡት፥ በምንቸትም ይቀቅሉት ነበር፥ እንጐቻም ያደርጉት ነበር፤ ጣዕሙም በዘይት እንደ ተለወሰ እንጐቻ ነበረ።
9 ፤ ሌሊትም ጠል በሰፈሩ ላይ በወረደ ጊዜ መናው በላዩ ይወርድ ነበር።
10 ፤ ሙሴም ሕዝቡ በወገኖቻቸው፥ ሰው ሁሉ በድንኳኑ ደጃፍ፥ ሲያለቅሱ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ እጅግ ነደደ፤ ሙሴም ተቈጣ።
11 ፤ ሙሴም እግዚአብሔርን አለው። ለምን በባሪያህ ላይ ክፉ አደረግህ? ለምንስ በፊትህ ሞገስ አላገኘሁም? ለምንስ የዚህን ሕዝብ ሁሉ ሸክም በእኔ ላይ አደረግህ?
12 ፤ አንተ ለአባቶቻቸው ወደ ማልህላቸው ምድር አደርሳቸው ዘንድ። ሞግዚት የሚጠባውን ልጅ እንድታቀፍ በብብትህ እቀፋቸው የምትለኝ፥ በውኑ ይህን ሕዝብ ሁሉ እኔ ፀነስሁትን? ወለድሁትንስ?
13 ፤ በፊቴ ያለቅሳሉና። የምንበላውን ሥጋ ስጠን ይላሉና ለዚህ ሕዝብ ሁሉ የምሰጠው ሥጋ ከወዴት እወስዳለሁ?
14 ፤ እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ልሸከም አልችልም።
15 ፤ እንዲህስ ከምታደርግብኝ፥ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ በእኔ ላይ የሚሆነውን መከራ እንዳላይ፥ እባክህ፥ ፈጽሞ ግደለኝ።
16 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ከእስራኤል ሽማግሌዎች፥ በሕዝቡ ላይ ሽማግሌዎችና አለቆች ይሆኑ ዘንድ የምታውቃቸውን፥ ሰባ ሰዎች ሰብስብልኝ፥ ወደ መገናኛውም ድንኳን አምጣቸው፥ በዚያም ከአንተ ጋር አቁማቸው።
17 ፤ እኔም እወርዳለሁ፥ በዚያም እነጋገርሃለሁ፥ በአንተ ካለውም መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርገዋለሁ፤ አንተም ብቻ እንዳትሸከም የሕዝቡን ሸክም ከአንተ ጋር ይሸከማሉ።
18 ፤ ሕዝቡንም በላቸው። የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብፅ ደኅና ነበረልን እያላችሁ ያለቀሳችሁት ወደ እግዚአብሔር ጆሮ ደርሶአልና ለነገ ተቀደሱ፥ ሥጋንም ትበላላችሁ፤ እግዚአብሔርም ሥጋን ይሰጣችኋል፥ ትበሉማላችሁ።
19 ፤ አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ወይም አምስት ቀን ወይም አሥር ቀን ወይም ሀያ ቀን አትበሉም፤
20 ፤ ነገር ግን በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን ንቃችኋልና፥ በፊቱም። ለምን ከግብፅ ወጣን? ብላችሁ አልቅሳችኋልና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ እስኪሰለቻችሁም ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ።
21 ፤ ሙሴም። እኔ በመካከላቸው ያለሁ ሕዝብ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ናቸው፤ አንተም። ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ አልህ።
22 ፤ እነርሱን የሚያጠግብ የበሬና የበግ መንጋ ይታረድን? ወይስ የባሕርን ዓሣ ሁሉ ያጠግባቸው ዘንድ ይሰበሰብላቸዋልን? አለ።
23 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። በውኑ የእግዚአብሔር እጅ አጭር ሆነ? አሁን ቃሌ ይፈጸም ወይስ አይፈጸም እንደ ሆነ አንተ ታያለህ አለው።
24 ፤ ሙሴም ወጣ የእግዚአብሔርንም ቃሎች ለሕዝቡ ነገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው።
25 ፤ እግዚአብሔር በደመናው ወረደ፥ ተናገረውም፥ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አደረገ፤ መንፈሱም በላያቸው ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋል ግን አልተናገሩም።
26 ፤ ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈር ቀርተው ነበር፥ የአንዱም ስም ኤልዳድ የሁለተኛውም ሞዳድ ነበረ፤ መንፈስም ወረደባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ ወደ ድንኳኑ ግን አልወጡም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ሳሉ ትንቢት ተናገሩ።
27 ፤ አንድ ጐበዝ ሰው እየሮጠ መጥቶ። ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈር ትንቢት ይናገራሉ ብሎ ለሙሴ ነገረው።
28 ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ። ጌታዬ ሙሴ ሆይ፥ ከልክላቸው አለው።
29 ፤ ሙሴም። የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያወርድ፤ አንተ ስለእኔ ትቀናለህን? አለው።
30 ፤ ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ።
31 ፤ ነፋስም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፥ ከባሕርም ድርጭቶችን አመጣ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚህ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚያ በሰፈሩ ላይ በተናቸው፤ በዚያም በሰፈሩ ዙሪያ ከፍታው ከምድር ወደ ላይ ሁለት ክንድ ነበረ።
32 ፤ በዚያም ቀን ሁሉ በሌሊትም ሁሉ በነጋውም ሁሉ ሕዝቡ ተነሥተው ድርጭትን ሰበሰቡ፤ ከሁሉ ጥቂት የሰበሰበ አሥር የቆሮስ መስፈሪያ የሚያህል ሰበሰበ፤ በሰፈሩም ዙሪያ ሁሉ አሰጡት።
33 ፤ ሥጋውም ገና በጥርሳቸው መካከል ሳለ ሳያኝኩትም፥ የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት እጅግ መታ።
34 ፤ የጐመጁ ሕዝብ በዚያ ተቀብረዋልና የዚያ ስፍራ ስም የምኞት መቃብር ተብሎ ተጠራ።
35 ፤ ሕዝቡም ከምኞት መቃብር ወደ ሐጼሮት ተጓዙ በሐጼሮትም ተቀመጡ።

1 ፤ ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ።
2 ፤ እነርሱም። በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን? አሉ፤ እግዚአብሔርም ሰማ።
3 ፤ ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ።
4 ፤ እግዚአብሔርም ወዲያው ሙሴንና አሮንን ማርያምንም። ሦስታችሁ ወደ መገኛኛው ድንኳን ውጡ ብሎ ተናገረ፤ ሦስቱም ወጡ።
5 ፤ እግዚአብሔርም በደመና ዓምድ ወረደ፥ በድንኳኑም ደጃፍ ቆመ፤ አሮንንና ማርያምን ጠራ፥ ሁለቱም ወጡ።
6 ፤ እርሱም። ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ።
7 ፤ ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው።
8 ፤ እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፥ በምሳሌ አይደለም፤ የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል፤ በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለ ምን አልፈራችሁም? አለ።
9 ፤ እግዚአብሔርም ተቈጥቶባቸው ሄደ።
10 ፤ ደመናውም ከድንኳኑ ተነሣ፤ እነሆም፥ ማርያም ለምጻም ሆነች፥ እንደ አመዳይም ነጭ ሆነች፤ አሮንም ማርያምን ተመለከተ፥ እነሆም፥ ለምጻም ሆና ነበር።
11 ፤ አሮንም ሙሴን። ጌታዬ ሆይ፥ ስንፍና አድርገናልና፥ በድለንማልና እባክህ፥ ኃጢአት አታድርግብን።
12 ፤ ከእናቱ ሆድ በወጣ ጊዜ ግማሽ ሥጋው ተበልቶ እንደ ሞተ እርስዋ አትሁን።
13 ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር እየጮኸ። አቤቱ፥ እባክህ፥ አድናት አለው።
14 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። አባትዋ ምራቁን በፊትዋ ቢተፋባት ስንኳ ሰባት ቀን ታፍር ዘንድ ይገባት ነበር፤ ሰባት ቀን ከሰፈር ውጭ ተዘግታ ትቀመጥ፥ ከዚያም በኋላ ትመለስ አለው።
15 ፤ ማርያምም ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን ተዘግታ ተቀመጠች፤ ማርያምም እስክትመለስ ድረስ ሕዝቡ አልተጓዙም።
16 ፤ ከዚያም በኋላ ሕዝቡ ከሐጼሮት ተጓዙ፥ በፋራንም ምድረ በዳ ሰፈሩ።

1 ፤ አብራምም ከግብፅ ወጣ፤ እርሱና ሚስቱ ለእርሱ የነበረውም ሁሉ ሎጥም ከእርሱ ጋር ወደ አዜብ ወጡ።
2 ፤ አብራምም በከብት በብርና በወርቅ እጅግ በለጠገ።
3 ፤ ከአዜብ ባደረገው በጕዞውም ወደ ቤቴል በኩል ሄደ፤ ያም ስፍራ አስቀድሞ በቤቴልና በጋይ መካከል ድንኳን ተክሎበት የነበረው ነው፤
4 ፤ ያም ስፍራ አስቀድሞ መሠውያ የሠራበት ነው፤ በዚያም አብራም የእግዚአብሔርን ስም ጠራ።
5 ፤ ከአብራም ጋር የሄደው ሎጥ ደግሞ የላምና የበግ መንጋ ድንኳንም ነበረው።
6 ፤ በአንድነትም ይቀመጡ ዘንድ ምድር አልበቃቸውም የነበራቸው እጅግ ነበረና በአንድነት ሊቀመጡ አልቻሉም።
7 ፤ የአብራምንና የሎጥን መንጎች በሚጠብቁት መካከልም ጠብ ሆነ በዚያም ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያች ምድር ተቀምጠው ነበር።
8 ፤ አብራምም ሎጥን አለው። እኛ ወንድማማች ነንና በእኔና በአንተ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ።
9 ፤ ምድር ሁሉ በፊትህ አይደለችምን? ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ አንተ ግራውን ብትወስድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተም ቀኙን ብትወስድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ።
10 ፤ ሎጥም ዓይኑን አነሣ፥ በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውንም አገር ሁሉ ውኃ የሞላበት መሆኑን አየ፤ እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ አስቀድሞ እስከ ዞዓር ድረስ እንደ እግዚአብሔር ገነት በግብፅ ምድር አምሳል ነበረ።
11 ፤ ሎጥም በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውን አገር ሁሉ መረጠ፤ ሎጥም ወደ ምሥራቅ ተጓዘ፤ አንዱም ከሌላው እርስ በርሳቸው ተለያዩ።
12 ፤ አብራም በከነዓን ምድር ተቀመጠ ሎጥም በአገሩ ሜዳ ባሉት ከተሞች ተቀመጠ፥ እስከ ሰዶምም ድረስ ድንኳኑን አዘዋወረ።
13 ፤ የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጢአተኞች ነበሩ።
14 ፤ ሎጥ ከተለየው በኋላም እግዚአብሔር አብራምን አለው። ዓይንህን አንሣና አንተ ካለህበት ስፍራ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ እይ፤
15 ፤ የምታያትን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁና።
16 ፤ ዘርህንም እንደ ምድር አሸዋ አደርጋለሁ፤ የምድርን አሸዋን ይቈጥር ዘንድ የሚችል ሰው ቢኖር ዘርህ ደግሞ ይቈጠራል።
17 ፤ ተነሣ በምድር በርዝመትዋም በስፋትዋም ሂድ እርስዋን ለአንተ እሰጣለሁና።
18 ፤ አብራምም ድንኳኑን ነቀለ መጥቶም በኬብሮን ባለው በመምሬ የአድባር ዛፍ ተቀመጠ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ።

1 ፤ ማኅበሩም ሁሉ ድምፃቸውን አንሥተው ጮኹ፤ ሕዝቡም በዚያ ሌሊት አለቀሱ።
2 ፤ የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ። በግብፅ ምድር ሳለን ምነው በሞትን ኖሮ! ወይም በዚህ ምድረ በዳ ምነው በሞትን ኖሮ!
3 ፤ እግዚአብሔርም በሰይፍ እንሞት ዘንድ ወደዚች ምድር ለምን ያገባናል? ሴቶቻችንና ልጆቻችን ምርኮ ይሆናሉ፤ ወደ ግብፅ መመለስ አይሻለንምን? አሉአቸው።
4 ፤ እርስ በርሳቸውም። ኑ፥ አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ ተባባሉ።
5 ፤ ሙሴና አሮንም በእስራኤል ልጆች ጉባኤ ፊት በግምባራቸው ወደቁ።
6 ፤ ምድርን ከሰለሉት ጋር የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤
7 ፤ ለእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ። ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም ናት።
8 ፤ እግዚአብሔርስ ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል እርስዋንም ይሰጠናል።
9 ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፍፎአል፥ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው ብለው ተናገሩአቸው።
10 ፤ ማኅበሩ ሁሉ ግን በድንጋይ ይወግሩአቸው ዘንድ ተማከሩ። የእግዚአብሔርም ክብር ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ተገለጠ።
11 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? በፊቱስ ባደረግሁት ተአምራት ሁሉ እስከ መቼ አያምንብኝም?
12 ፤ ከርስታቸው አጠፋቸው ዘንድ በቸነፈር እመታቸዋለሁ፤ አንተም ከእነርሱ ለሚበዛና ለሚጠነክር ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው።
13 ፤ ሙሴም እግዚአብሔርን አለው። ግብፃውያን ይሰማሉ፤ ይህን ሕዝብ ከመካከላቸው በኃይልህ አውጥተኸዋልና፤
14 ፤ ለዚችም ምድር ሰዎች ይናገራሉ። አንተ እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ መካከል እንደ ሆንህ ሰምተዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ ፊት ለፊት ተገልጠሃል፥ ደመናህም በላያቸው ቆሞአል፥ በቀንም በደመና ዓምድ፥ በሌሊትም በእሳት ዓምድ በፊታቸው ትሄዳለህ።
15 ፤ ይህን ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ብትገድል ዝናህን የሰሙ አሕዛብ።
16፤ እግዚአብሔር ይህን ሕዝብ ወደ ማለላቸው ምድር ያገባቸው ዘንድ አልቻለምና በምድረ በዳ ገደላቸው ብለው ይናገራሉ።
17-18፤ አሁንም፥ እባክህ። እግዚአብሔር ታጋሽና ምሕረቱ የበዛ፥ አበሳንና መተላለፍን ይቅር የሚል፥ ኃጢአተኞችንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን ኃጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ በልጆች ላይ የሚያመጣ ነው ብለህ እንደ ተናገርህ፥ የጌታ ኃይል ታላቅ ይሁን።
19 ፤ ይህን ሕዝብ ከግብፅ ምድር ካወጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው፥ እባክህ፥ እንደ ምሕረትህ ብዛት የዚህን ሕዝብ ኃጢአት ይቅር በል።
20 ፤ እግዚአብሔርም አለ። እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ፤
21 ፤ ነገር ግን እኔ ሕያው ነኛ በእውነት የእግዚአብሔር ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል።
22 ፤ በግብፅ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ተአምራቴንና ክብሬን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ አሥር ጊዜ ስለ ተፈታተኑኝ፥
23 ፤ ነገሬንም ስላልሰሙ፥ በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ ከእነርሱም የናቀኝ ሰው ሁሉ አያያትም፤
24 ፤ ባሪያዬ ካሌብ ግን ሌላ መንፈስ ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ ፈጽሞም ስለተከተለኝ እርሱ ወደ ገባባት ምድር አገባዋለሁ፤ ዘሩም ይወርሳታል።
25 ፤ አማሌቅና ከነዓናዊውም በሸለቆው ውስጥ ተቀምጦአል፤ በነጋው ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ።
26 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
27 ፤ የሚያጕረመርምብኝን ይህን ክፉ ሕዝብ እስከ መቼ እታገሠዋለሁ? በእኔ ላይ የሚያጕረመርሙትን የእስራኤልን ልጆች ማጕረምረም ሰማሁ።
28 ፤ እንዲህ በላቸው። እኔ ሕያው ነኝና በጆሮዬ እንደ ተናገራችሁት እንዲሁ በእውነት አደርግባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤
29 ፤ በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ፤ የተቆጠራችሁ ሁሉ፥ እንደቁጥራችሁ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የሆነ ሁሉ፥ እናንተ ያጕረመረማችሁብኝ፥
30 ፤ ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር በእርስዋ አስቀምጣችሁ ዘንድ እጄን ዘርግቼ ወደ ማልሁላችሁ ምድር በእውነት እናንተ አትገቡም።
31 ፤ ምርኮኛ ይሆናሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን እነርሱን አገባቸዋለሁ፥ እናንተም የናቃችኋትን ምድር ያውቃሉ።
32 ፤ እናንተ ግን በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ።
33 ፤ ልጆቻችሁም በምድረ በዳ አርባ ዓመት ይቅበዘበዛሉ፥ በድኖቻችሁም በምድረ በዳ እስኪጠፉ ድረስ ግልሙትናችሁን ይሸከማሉ።
34 ፤ ምድሪቱን በሰላለችሁባት ቀን ቍጥር፥ አርባ ቀን፥ ስለ አንድ ቀንም አንድ ዓመት፥ ኃጢአታችሁን አርባ ዓመት ትሸከማላችሁ፥ ቍጣዬንም ታውቃላችሁ።
35 ፤ እኔ እግዚአብሔር። በእኔ ላይ በተሰበሰበ በዚህ ክፉ ማኅበር ሁሉ ላይ እንዲህ አደርጋለሁ ብዬ ተናገርሁ፤ በዚህ ምድረ በዳ ያልቃሉ፥ በዚያም ይሞታሉ።
36 ፤ ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሙሴ ልኮአቸው የተመለሱት ሰዎች ክፉ ወሬም ስለ ምድሪቱ እያወሩ በእርሱ ላይ ማኅበሩ ሁሉ እንዲያጕረመርሙ ያደረጉ፥
37 ፤ ክፉ ወሬ ያወሩ እነዚያ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት በመቅሠፍት ሞቱ።
38 ፤ ነገር ግን ምድሪቱን ሊሰልሉ ከሄዱ ሰዎች የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ በሕይወት ተቀመጡ።
39 ፤ ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ነገረ፥ ሕዝቡም እጅግ አዘኑ።
40 ፤ በነጋውም ማልደው ተነሡ፥ ወደ ተራራውም ራስ መጥተው። እነሆ፥ መጣን፤ እኛ በድለናልና እግዚአብሔር ወዳለው ስፍራ እንወጣለን አሉ።
41 ፤ ሙሴም አለ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? አይጠቅማችሁም።
42 ፤ እግዚአብሔር በእናንተ መካከል አይደለምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትወድቁ አትውጡ።
43 ፤ አማሌቃዊና ከነዓናዊ በፊታችሁ ናቸውና በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ እግዚአብሔርን ከመከተል ተመልሳችኋልና እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይሆንም።
44 ፤ እነርሱ ግን ወደ ተራራው ራስ ሊወጡ ደፈሩ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦትና ሙሴ ከሰፈሩ አልተነሡም።
45 ፤ በዚያም ተራራ ላይ የተቀመጡ አማሌቃዊና ከነዓናዊ ወረዱ፥ መትተዋቸውም እስከ ሔርማ ድረስ አሳደዱአቸው።

1 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደምሰጣችሁ ወደ መኖሪያችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥
3 ፤ ስእለታችሁን ልትፈጽሙ፥ ወይም በፈቃዳችሁ፥ ወይም በበዓላችሁ፥ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ ታደርጉ ዘንድ ከበሬ ወይም ከበግ መንጋ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም መሥዋዕት የሚሆን የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ብታቀርቡ፥
4-5፤ ቍርባኑን ለእግዚአብሔር የሚያቀርብ ከሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ከሌላ መሥዋዕት ጋር ለእያንዳንዱ ጠቦት የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን፥ የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ያዘጋጃል።
6-7፤ ለአንዱም አውራ በግ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የኢን መስፈሪያ ሢሶ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን ታዘጋጃለህ፤ የኢን መስፈሪያ ሢሶም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ታቀርባለህ።
8 ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት ወይም ስእለትን ለመፈጸም ወይም ለደኅንነት መሥዋዕት ወይፈንን ለእግዚአብሔር ብታዘጋጅ
9 ፤ ከወይፈኑ ጋር የኢን መስፈሪያ ግማሽ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን ታቀርባለህ።
10 ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት ለተደረገ ቍርባን፥ የኢን መስፈሪያ ግማሽ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ታቀርባለ።
11 ፤ እንዲሁ ለእያንዳንዱ ወይፈን ወይም ለእያንዳንዱ አውራ በግ ወይም ለእያንዳንዱ ተባት የበግ ወይም የፍየል ጠቦት ይደረጋል።
12 ፤ እንዳዘጋጃችሁት ቍጥር፥ እንዲሁ እንደ ቍጥራቸው ለእያንዳንዱ ታደርጋላችሁ።
13 ፤ የአገር ልጅ ሁሉ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ቍርባን በእሳት ባቀረበ ጊዜ እንዲሁ ያደርጋል።
14 ፤ መጻተኛም ከእናንተ ጋር ቢቀመጥ፥ ወይም በትውልዳችሁ መካከል ማንም ሰው ቢኖር፥ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ቍርባን በእሳት ቢያቀርብ፥ እናንተ የምታደርጉትን እርሱ እንዲሁ ያደርጋል።
15 ፤ ለእናንተ በጉባኤው ላላችሁ በእናንተም መካከል ለሚቀመጥ መጻተኛ አንድ ሥርዓት ይሆናል፥ ለልጅ ልጃችሁም የዘላለም ሥርዓት ይሆናል፤ እናንተ እንደ ሆናችሁ እንዲሁ በእግዚአብሔር ፊት መጻተኛ ይሆናል።
16 ፤ ለእናንተና ከእናንተ ጋር ለሚቀመጥ መጻተኛ አንድ ሕግና አንድ ፍርድ ይሆናል።
17 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
18 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደማመጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥
19 ፤ እናንተ የምድሪቱን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን ታደርጋላችሁ።
20 ፤ መጀመሪያ ከምታደርጉት ሊጥ አንድ እንጐቻ ለማንሣት ቍርባን ታቀርባላችሁ፤ ከአውድማም እንደምታነሡት ቍርባን እንዲሁ ታነሣላችሁ።
21 ፤ መጀመሪያ ከምታደርጉት ሊጥ የማንሣት ቍርባን እስከ ልጅ ልጃችሁ ለእግዚአብሔር ትሰጣላችሁ።
22 ፤ ብትስቱም፥ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዛቸውን እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥
23 ፤ እግዚአብሔር ካዘዘበት ከፊተኛው ቀን ጀምሮ ወደ ፊትም እስከ ልጅ ልጃችሁ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ያዘዛችሁን ሁሉ ባታደርጉ፥
24 ፤ ማኅበሩ ሳያውቁ በስሕተት ቢደረግ፥ ማኅበሩ ሁሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋር እንደ ሕጉ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን አንድ ወይፈን፥ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ያቀርባሉ።
25 ፤ ካህኑም ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ያስተሰርይላቸዋል፥ ስሕተትም ነበረና ይሰረይላቸዋል፤ ስለ ስሕተታቸውም ለእግዚአብሔር ቍርባናቸውን በእሳት አቅርበዋል፥ ለእግዚአብሔርም የኃጢአታቸውን መሥዋዕት አቅርበዋል።
26 ፤ በሕዝቡም ሁሉ ዘንድ ያለ እውቀት ተደርጎአልና ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በመካከላቸውም ለሚኖሩት መጻተኞች ስርየት ይደረግላቸዋል።
27 ፤ አንድ ሰው ሳያውቅ ኃጢአት ቢሠራ፥ ለኃጢአት መሥዋዕት አንዲት የአንድ ዓመት እንስት ፍየል ያቀርባል።
28 ፤ ኃጢአት ሠርቶ ሳያውቅ፥ ለሳተ ለዚያ ሰው ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፥ ይሰረይለትማል።
29 ፤ ትውልዱ በእስራኤል ልጆች መካከል ቢሆን፥ ወይም በመካከላቸው የሚቀመጥ መጻተኛ ቢሆን፥ ሳያውቅ ኃጢአትን ለሚሠራ ሁሉ ሕጉ አንድ ይሆንለታል።
30 ፤ የአገር ልጅ ቢሆን ወይም መጻተኛ ቢሆን፥ አንዳች በትዕቢት የሚያደርግ ሰው እግዚአብሔርን ሰድቦአል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል።
31 ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቀ፥ ትእዛዙንም ስለ ሰበረ፥ ያ ሰው ፈጽሞ ይጥፋ፤ ኃጢአቱ በራሱ ላይ ነው።
32 ፤ የእስራኤልም ልጆች በምድረ በዳ ሳሉ አንድ ሰው በሰንበት ቀን እንጨት ሲለቅም አገኙ።
33 ፤ እንጨትም ሲለቅም ያገኙት ሰዎች ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ ማኅበሩም ሁሉ አመጡት።
34 ፤ ያደርጉበትም ዘንድ የሚገባው አልተገለጠምና በግዞት አስቀመጡት።
35 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ሰውየው ፈጽሞ ይገደል፤ ከሰፈሩ ውጭ ማኅበሩ ሁሉ በድንጋይ ይውገሩት አለው።
36 ፤ ማኅበሩም ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አወጡት፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ወገሩት።
37 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
38 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው። እነርሱም ትውልዶቻቸውም በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ ያደርጉ ዘንድ፥ በዘርፉም ሁሉ ላይ ሰማያዊ ፈትል ያደርጉ ዘንድ እዘዛቸው።
39 ፤ የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ፥ እርስዋን በመከተል ያመነዘራችሁባትን የልባችሁንና የዓይኖቻችሁን ፈቃድ እንዳትከተሉ፥
40 ፤ ትእዛዜን ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ፥ ለአምላካችሁም ቅዱሳን ትሆኑ ዘንድ ዘርፉ በልብሳችሁ ላይ እንዲታይ ይሁን።
41 ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ አምላክ እሆናችሁ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

1 ፤ የሌዊም ልጅ የቀዓት ልጅ የይስዓር ልጅ ቆሬ ከሮቤልም ልጆች የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን የፋሌትም ልጅ ኦን በሙሴ ላይ ተነሡ። ች የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን የፋሌትም ልጅ ኦን በሙሴ
2 ፤ ከእስራኤልም ልጆች ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች ከእነርሱ ጋር ወሰዱ፤ ከጉባኤው የተመረጡ ዝናቸውም የተሰማ የማኅበሩ አለቆች ነበሩ።
3 ፤ በሙሴና በአሮን ላይ ተሰብስበው። ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችኋል፤ በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ? አሉ።
4 ፤ ሙሴም በሰማ ጊዜ በግምባሩ ወደቀ፤
5 ፤ ለቆሬም ለወገኑም ሁሉ። ነገ እግዚአብሔር ለእርሱ የሚሆነውን፥ ቅዱስም የሚሆነውን ያስታውቃል፤ የመረጠውንም ሰው ወደ እርሱ ያቀርበዋል።
6 ፤ እንዲሁ አድርጉ፤ ቆሬና ወገንህ ሁሉ፥ ጥናዎቹን ውሰዱ፤
7 ፤ ነገም በእግዚአብሔር ፊት እሳት አድርጉባቸው፥ ዕጣንም ጨምሩባቸው፤ እንዲህም ይሆናል፤ እግዚአብሔር የሚመርጠው እርሱ ቅዱስ ይሆናል፤ እናንተ የሌዊ ልጆች ሆይ እጅግ አብዝታችኋል ብሎ ተናገራቸው።
8 ፤ ሙሴም ቆሬን አለው። እናንተ የሌዊ ልጆች፥ ስሙ፤
9 ፤ የእስራኤል አምላክ ከእስራኤል ማኅበር የለያችሁ፥ የእግዚአብሔርንም ማደሪያ አገልግሎት ትሠሩ ዘንድ፥ እንድታገለግሉአቸውም በማኅበሩ ፊት ትቆሙ ዘንድ ወደ እርሱ ያቀረባችሁ አይበቃችሁምን?
10 ፤ አንተን ከአንተም ጋር የሌዊን ልጆች ወንድሞችህን ሁሉ ወደ እርሱ አቅርቦአል፤ ክህነትንም ደግሞ ትፈልጋላችሁን?
11 ፤ ስለዚህም አንተና ወገንህ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ተሰብስባችኋል፤ በእርሱም ላይ ታጕረመርሙ ዘንድ አሮን ማን ነው?
12 ፤ ሙሴም የኤልያብን ልጆች ዳታንና አቤሮንን እንዲጠሩአቸው ላከ፤ እነርሱም። አንመጣም፤
13 ፤ በምድረ በዳ ትገድለን ዘንድ ወተትና ማር ከምታፈስሰው ምድር ያወጣኸን አይበቃህምን? ደግመህ በእኛ ላይ ራስህን አለቃ ታደርጋለህን?
14 ፤ ደግሞ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር አላገባኸንም፥ እርሻና ወይንም አላወረስኸንም፤ የእነዚህንስ ሰዎች ዓይኖቻቸውን ታወጣለህን? አንመጣም አሉ።
15 ፤ ሙሴም እጅግ ተቈጣ፥ እግዚአብሔርንም። ወደ ቍርባናቸው አትመልከት፤ እኔ ከእነርሱ አንድ አህያ ስንኳ አልወሰድሁም፥ ከእነርሱም አንድ ሰው አልበደልሁም አለው።
16 ፤ ሙሴም ቆሬን። ነገ አንተ፥ ወገንህም ሁሉ፥ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ሁኑ፤
17 ፤ ሁላችሁም ጥናዎቻችሁን ውሰዱ፥ ዕጣንም አድርጉባቸው፥ እያንዳንዳችሁም ጥናዎቻችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት አምጡ፥ ሁለት መቶ አምሳ ጥናዎች፤ አንተ ደግሞ አሮንም ጥናዎቻችሁን አምጡ አለው።
18 ፤ እያንዳንዱም ጥናውን ወሰደ፥ እሳትም አደረገበት፥ ዕጣንም ጨመረበት፥ ከሙሴና ከአሮንም ጋር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቆመ።
19 ፤ ቆሬም ማኅበሩን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእነርሱ ላይ ሰበሰበ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለማኅበሩ ሁሉ ተገለጠ።
20 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
21 ፤ ሁሉን በቅጽበት አጠፋቸው ዘንድ ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ።
22 ፤ እነርሱም በግምባራቸው ወድቀው። አምላክ ሆይ፥ አንተ የሰው ሁሉ ነፍስ አምላክ፥ አንድ ሰው ኃጢአት ቢሠራ አንተ በማኅበሩ ሁሉ ላይ ትቈጣለህን? አሉ።
23 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
24 ፤ ለማኅበሩ። ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ዙሪያ ፈቀቅ በሉ ብለህ ንገራቸው።
25 ፤ ሙሴም ተነሥቶ ወደ ዳታንና ወደ አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ተከተሉት።
26 ፤ ማኅበሩንም። እባካችሁ፥ ከእነዚህ ክፉዎች ድንኳን ፈቀቅ በሉ፤ በኃጢአታቸውም ሁሉ እንዳትጠፉ ለእነርሱ የሆነውን ሁሉ አትንኩ ብሎ ተናገራቸው።
27 ፤ ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ከዙሪያውም ሁሉ ፈቀቅ አሉ፤ ዳታንና አቤሮንም ሴቶቻቸውም ልጆቻቸውም ሕፃናቶቻቸውም ወጥተው በድንኳኖቻቸው ደጃፍ ቆሙ።
28 ፤ ሙሴም አለ። ይህን ሥራ ሁሉ አደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ላከኝ እንጂ ከልቤ እንዳይደለ በዚህ ታውቃላችሁ።
29 ፤ እነዚህ ሰዎች ሰው እንደሚሞት ቢሞቱ፥ ወይም እንደ ሰው ሁሉ ቢቀሠፉ እግዚአብሔር አልላከኝም።
30 ፤ እግዚአብሔር ግን አዲስ ነገር ቢፈጥር፥ ምድርም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ለእነርሱም ያለውን ሁሉ ብትውጣቸው፥ በሕይወታቸውም ወደ ሲኦል ቢወርዱ፥ ያን ጊዜ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን እንደ ናቁ ታውቃላችሁ።
31 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ይህን ቃል ሁሉ መናገር በፈጸመ ጊዜ ከበታቻቸው ያለው መሬት ተሰነጠቀ፤
32 ፤ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ቤተ ሰቦቻቸውንም፥ ለቆሬም የነበሩትን ሰዎች ሁሉ፥ ዕቃዎቻቸውንም ሁሉ ዋጠቻቸው።
33 ፤ እነርሱም ለእነርሱም የነበሩ ሁሉ በሕይወታቸው ወደ ሲኦል ወረዱ፤ ምድሪቱም ተዘጋችባቸው፥ ከጉባኤውም መካከል ጠፉ።
34 ፤ በዙሪያቸው የነበሩ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ከጩኸታቸው የተነሣ። ምድሪቱ እንዳትውጠን ብለው በረሩ።
35 ፤ እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥታ ያጥኑ የነበሩትን ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች በላች።
36 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
37 ፤ ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአልዓዛር እንዲህ ብለህ ንገረው። ተቀድሰዋልና ጥናዎቹን ከተቃጠሉት ዘንድ ውሰድ፥ እሳቱንም ወደ ውጭ ጣለው፤
38 ፤ በኃጢአታቸው ሰውነታቸውን ያጠፉትን የእነዚያን ሰዎች ጥናዎች ጠፍጥፈህ ለመሠዊያ መለበጫ አድርጋቸው፤ በእግዚአብሔር ፊት አቅርበዋቸዋልና የተቀደሱ ናቸው፥ ለእስራኤልም ልጆች ምልክት ይሆናሉ።
39 ፤ ካህኑም አልዓዛር የተቃጠሉት ሰዎች ያቀረቡአቸውን የናስ ጥናዎች ወስዶ ጠፍጥፎም ለመሠዊያው መለበጫ አደረጋቸው።
40 ፤ በቆሬና በወገኑ የደረሰው እንዳይደርስበት፥ ከአሮን ልጆች ያልሆነ ሌላ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ዕጣን ያጥን ዘንድ እንዳይቀርብ፥ እግዚአብሔር በሙሴ እንደ ተናገረው፥ ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ አደረጋቸው።
41 ፤ በነጋውም የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ። እናንተ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ገድላችኋል ብለው በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ።
42 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ማኅበሩ በሙሴና በአሮን ላይ በተሰበሰቡ ጊዜ ወደ መገናኛው ድንኳን አዩ፤ እነሆም፥ ደመናው ሸፈነው፥ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠ።
43 ፤ ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት መጡ።
44 ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
45 ፤ ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ፥ እኔም በቅጽበት አጠፋቸዋለሁ። በግምባራቸውም ወደቁ።
46 ፤ ሙሴም አሮንን። ጥናህን ውሰድ፥ ከመሠዊያውም ላይ እሳት አድርግበት፥ ዕጣንም ጨምርበት፥ ወደ ማኅበሩም ፈጥነህ ውሰደው አስተስርይላቸውም፤ ከእግዚአብሔር ፊት ቍጣ ወጥቶአልና መቅሠፍት ጀምሮአል አለው።
47 ፤ አሮንም ሙሴ እንደ ተናገረው ጥናውን ወስዶ ወደ ጉባኤው መካከል ሮጠ፤ እነሆም፥ መቅሠፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር፤ ዕጣንም ጨመረ፥ ለሕዝቡም አስተሰረየላቸው።
48 ፤ በሙታንና በሕያዋን መካከል ቆመ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ።
49 ፤ በቆሬም ምክንያት ከሞቱት ሌላ በመቅሠፍቱ የሞቱት አሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ።
50 ፤ አሮንም ወደ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተመለሰ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ።

1 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው፥ ከእነርሱም ከእያንዳንዱ ከየአባቶቻቸው ቤት አንድ አንድ በትር፥ ከአለቆቻቸው ከየአባቶቻቸው ቤት አሥራ ሁለት በትሮች፥ ውሰድ፤ የእያንዳንዱንም ስም በየበትሩ ላይ ጻፍ።
3 ፤ አንድ በትርም ለአባቶቻቸው ቤት አለቃ ይሆናልና በሌዊ በትር ላይ የአሮንን ስም ጻፍ።
4 ፤ እኔ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት አኑራቸው።
5 ፤ እንዲህም ይሆናል፤ የመረጥሁት ሰው በትር ታቈጠቁጣለች፤ በእናንተም ላይ የሚያጕረመርሙባችሁን የእስራኤልን ልጆች ማጕረምረም ከእኔ ዘንድ አጠፋለሁ።
6 ፤ ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገራቸው፤ አለቆቻቸው ሁሉ አሥራ ሁለት በትሮች፥ እያንዳንዱም አለቃ በየአባቱ ቤት አንድ አንድ በትር፥ ሰጡት፤ የአሮንም በትር በበትሮቻቸው መካከል ነበረች።
7 ፤ ሙሴም በትሮቹን በእግዚአብሔር ፊት በምስክሩ ድንኳን ውስጥ አኖራቸው።
8 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ውስጥ ገባ፤ እነሆም፥ ለሌዊ ቤት የሆነች የአሮን በትር አቈጠቈጠች፥ ለመለመችም፥ አበባም አወጣች፥ የበሰለ ለውዝም አፈራች።
9 ፤ ሙሴም በትሮችን ሁሉ ከእግዚአብሔር ፊት ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አወጣቸው፤ እነርሱም አዩ፥ እያንዳንዱም በትሩን ወሰደ።
10 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የአሮንን በትር ወደ ምስክሩ ፊት መልስ፤ ማጕረምረማቸው ከእኔ ዘንድ እንዲጠፋ እነርሱም እንዳይሞቱ ለሚያምፁብኝ ልጆች ምልክት ሆና ትጠበቅ አለው።
11 ፤ ሙሴም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንዲሁ አደረገ።
12 ፤ የእስራኤልም ልጆች ሙሴን።እነሆ፥ እንሞታለን፥ እንጠፋለን፥ ሁላችንም እንጠፋለን።
13 ፤ የሚቀርብ ሁሉ፥ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ የሚቀርብ፥ ይሞታል፤ በውኑ ሁላችን እንሞታለንን? ብለው ተናገሩት።

1 ፤ እግዚአብሔርም አሮንን አለው። አንተ ከአንተም ጋር ልጆችህና የአባቶችህ ቤት የመቅደስን ኃጢአት ትሸከማላችሁ፤ አንተም ከአንተም ጋር ልጆችህ የክህነታችሁን ኃጢአት ትሸከማላችሁ።
2 ፤ ደግሞም የአባትህን የሌዊን ነገድ ወንድሞችህን ከአንተ ጋር አቅርብ፤ ከአንተም ጋር በአንድነት ይሁኑ፥ ያገልግሉህም፤ አንተ ግን ከአንተም ጋር ልጆችህ በምስክሩ ድንኳን ፊት ትሆናላችሁ።
3 ፤ እነርሱም ትእዛዝህን የድንኳኑንም ሁሉ አገግሎት ይጠብቁ፤ ነገር ግን እንዳይሞቱ፥ እናንተም ደግሞ ከእነርሱ ጋር እንዳትሞቱ፥ እነርሱ ወደ መቅደሱ ዕቃና ወደ መሠዊያው አይቅረቡ።
4 ፤ ነገር ግን ከእናንተ ጋር በአንድነት ይሁኑ፥ ለድንኳኑም አገልግሎት ሁሉ የመገናኛውን ድንኳን ይጠብቁ፤ ሌላም ሰው ወደ እናንተ አይቅረብ።
5 ፤ እንደ ገና በእስራኤል ልጆች ላይ ቍጣ እንዳይሆንባቸው እናንተ መቅደሱንና መሠዊያውን ጠብቁ።
6 ፤ እኔም፥ እነሆ፥ ሌዋውያንን ወንድሞቻችሁን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ፤ የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ያደርጉ ዘንድ ለእግዚአብሔር የተሰጡ ለእናንተ ስጦታ ናቸው።
7 ፤ አንተም ከአንተም ጋር ልጆችህ ለመሠዊያው ሥራ የሚሆነውን ሁሉ፥ በመጋረጃውም ውስጥ የሚሆነውን ታደርጉ ዘንድ ክህነታችሁን ጠብቁ፥ አገልግሉም፤ ክህነቱን ለስጦታ አገልግሎት ሰጥቼአችኋለሁ፤ ሌላም ሰው ቢቀርብ ይገደል።
8 ፤ እግዚአብሔርም አሮንን ተናገረው እንዲህም አለው። እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ለእኔ የቀደሱትን የማንሣት ቍርባኔን ሁሉ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ፤ ስለ መቀባትህ ለአንተና ለልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘላለም ሰጥቼሃለሁ።
9 ፤ በእሳት ከሚቀርበው ከተቀደሰው ይህ ለአንተ ይሆናል፤ ለእኔ የሚያመጡት መባቸው ሁሉ፥ የእህሉ ቍርባናቸው ሁሉ፥ የኃጢአታቸውም መስዋዕት ሁሉ፥ የበደላቸውም መሥዋዕት ሁሉ፥ ለአንተ ለልጆችህም የተቀደሰ ይሆናል።
10 ፤ በተቀደሰ ስፍራ ብላው፤ ወንዶች ሁሉ ይብሉት፤ የተቀደሰ ይሆንልሃል።
11 ፤ ይህም ለአንተ ነው፤ የእስራኤል ልጆች ለስጦታ ያቀረቡትን የማንሣትና የመወዝወዝ ቍርባን ሁሉ ለአንተ ከአንተም ጋር ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘላለም ሰጥቼሃለሁ፤ በቤትህ ውስጥ ንጹሕ የሆነ ሁሉ ይብላው።
12 ፤ ለእግዚአብሔር ከሚሰጡት የፍሬ መጀመሪያ ከዘይትና ከወይን ከእህልም የተመረጠውን ሁሉ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።
13 ፤ ወደ እግዚአብሔር የሚያመጡት በምድራቸው ያለው ሁሉ የፍሬ መጀመሪያ ለአንተ ይሆናል፤ በቤትህ ውስጥ ንጹሕ የሆነ ሁሉ ይብላው።
14 ፤ በእስራኤል ዘንድ እርም የሆነው ሁሉ ለአንተ ይሆናል።
15 ፤ ከሰው ወይም ከእንስሳ ቢሆን፥ ለእግዚአብሔር ከሚያቀርቡት ሥጋ ሁሉ ማኅፀን የሚከፍት ሁሉ ለአንተ ይሆናል፤ ነገር ግን የሰውን በኵራት ፈጽሞ ትቤዠዋለህ፥ ያልነጻውንም እንስሳ በኵራት ትቤዠዋለህ።
16 ፤ ከአንድ ወር ጀምሮ የምትቤዠውን እንደ ግምትህ ትቤዠዋለህ፤ ግምቱም እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን አምስት ሰቅል ይሆናል፤ እርሱም ሀያ አቦሊ ነው።
17 ፤ ነገር ግን የላም በኵራት ወይም የበግ በኵራት ወይም የፍየል በኵራት አትቤዥም፤ የተቀደሱ ናቸው፤ ደማቸውን በመሠዊያው ላይ ትረጨዋለህ፥ ስባቸውንም ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለእሳት ቍርባን ታቃጥለዋለህ።
18 ፤ ሥጋቸውም ለአንተ ይሆናል፤ እንደ መወዝወዝ ፍርምባ እንደ ቀኙም ወርች ለአንተ ይሆናል።
19 ፤ የእስራኤል ልጆች ከተቀደሰው ነገር ሁሉ አንሥተው ለእግዚአብሔር ያቀረቡትን ለአንተ ከአንተም ጋር ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘላለም ሰጥቼሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ለአንተ ከአንተም ጋር ለዘርህ የጨው ቃል ኪዳን ለዘላለም ነው።
20 ፤ እግዚአብሔርም አሮንን አለው። በምድራቸው ርስት በመካከላቸውም ድርሻ አይሆንልህም፤ በእስራኤል ልጆች መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ።
21 ፤ ለሌዊም ልጆች፥ እነሆ፥ በመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ስለሚያገለግሉ፥ የእስራኤልን ልጆች አሥራት ርስት አድርጌ ሰጥቼአለሁ።
22 ፤ ከዚህም በኋላ ኃጢአትን እንዳይሸከሙ እንዳይሞቱም፥ የእስራኤል ልጆች ወደ መገናኛው ድንኳን አይቅረቡ።
23 ፤ ሌዋውያን ግን የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ይሥሩ፥ እነርሱም ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ፤ ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል፤ በእስራኤልም ልጆች መካከል ርስት አይወርሱም።
24 ፤ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን የሚያቀርቡትን የእስራኤልን ልጆች አሥራት ለሌዋውያን ርስት አድርጌ ሰጥቼአለሁ፤ ስለዚህ። በእስራኤል ልጆች መካከል ርስት አይወርሱም አልኋቸው።
25 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
26 ፤ ለሌዋውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ከእስራኤል ልጆች ለእናንተ ርስት አድርጌ የሰጠኋችሁን አሥራት በተቀበላችሁ ጊዜ፥ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን የአሥራት አሥራት ታቀርባላችሁ።
27 ፤ የማንሣት ቍርባናችሁም እንደ አውድማው እህልና እንደ ወይን መጭመቂያው ፍሬ ይቈጠርላችኋል።
28 ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ከእስራኤል ልጆች ከምትቀበሉት አሥራት ሁሉ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን ታቀርባላችሁ፤ የእግዚአብሔርንም የማንሣት ቍርባን ለካህኑ ለአሮን ትሰጣላችሁ።
29 ፤ ከምትቀበሉት ስጦታ ሁሉ፥ ከተመረጠው ከተቀደሰውም ድርሻ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን የማንሣት ቍርባን ሁሉ ታቀርባላችሁ።
30 ፤ ስለዚህ ትላቸዋለህ። ከእርሱ የተመረጠውን ባነሣችሁ ጊዜ እንደ አውድማው እህልና እንደ ወይን መጭመቂያው ፍሬ ለሌዋውያን ይቈጠራል።
31 ፤ እናንተም ቤተ ሰቦቻችሁም፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የማገልገላችሁ ዋጋ ነውና በሁሉ ስፍራ ትበሉታላችሁ።
32 ፤ የተመረጠውንም ከእርሱ ባነሣችሁ ጊዜ ስለ እርሱ ኃጢአትን አትሸከሙም፤ እንዳትሞቱም የእስራኤል ልጆች የቀደሱትን አታረክሱም።

1 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
2 ፤ እግዚአብሔር ያዘዘው የሕጉ ትእዛዝ ይህ ነው፤ መልካሚቱን፥ ነውርም የሌለባትን፥ ቀንበርም ያልተጫነባትን ቀይ ጊደር ያመጡልህ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው።
3 ፤ እርስዋንም ለካህኑ ለአልዓዛር ትሰጣላችሁ፥ እርስዋንም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወስዳታል፥ አንድ ሰውም በፊቱ ያርዳታል።
4 ፤ ካህኑም አልዓዛር ከደምዋ በጣቱ ይወስዳል፥ ከደምዋም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ሰባት ጊዜ ይረጫል።
5 ፤ ጊደሪቱም በፊቱ ትቃጠላለች፤ ቁርበትዋም ሥጋዋም ደምዋም ፈርስዋም ይቃጠላል።
6 ፤ ካህኑም የዝግባ እንጨት ሂሶጵም ቀይ ግምጃም ወስዶ ጊደሪቱ በምትቃጠልበት እሳት መካከል ይጥለዋል።
7 ፤ ካህኑም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል፤ ካህኑም እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል።
8 ፤ ያቃጠላትም ሰው ልብሱን በውኃ ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።
9 ፤ ንጹሕም ሰው የጊደሪቱን አመድ ያከማቻል ከሰፈሩም ውጭ በንጹሕ ስፍራ ያኖረዋል፤ ርኵሰትም ለሚያነጻ ውኃ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ይጠበቃል፤ ከኃጢአት ለማንጻት የሚሆን ነው።
10 ፤ የጊደሪቱንም አመድ ያከማቸ ሰው ልብሱን ያጥባል እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸውም ለሚኖር መጻተኛ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል።
11 ፤ የሞተውን ሰው በድን የሚነካ ሰባት ቀን ርኵስ ይሆናል፤
12 ፤ በዚህም ውኃ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ያጠራል፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ባያጠራ ንጹሕ አይሆንም።
13 ፤ የሞተውን ሰው በድን የነካ ሁለመናውን ባያጠራ የእግዚአብሔርን ማደሪያ ያረክሳል፤ ያ ሰው ከእስራኤል ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ በእርሱም ላይ የሚያነጻ ውኃ አልተረጨምና ርኩስ ይሆናል፤ ርኵሰቱ ገና በእርሱ ላይ ነው።
14 ፤ ሰው በድንኳን ውስጥ ቢሞት ሕጉ ይህ ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባ ሁሉ በድንኳኑም ውስጥ ያለው ሁሉ ሰባት ቀን ርኵስ ይሆናል።
15 ፤ መክደኛው ያልታሰረ የተከፈተ ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው።
16 ፤ በሜዳም በሰይፍ የተገደለውን ወይም የሞተውን በድን ወይም የሰውን አጥንት ወይም መቃብር የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል።
17 ፤ ከኃጢአት ለማንጻት እንድትሆን ከተቃጠለችው ጊደር አመድ ለርኩሱ ይወስዱለታል፥ በዕቃውም ውስጥ የምንጭ ውኃ ይቀላቀልበታል።
18 ፤ ንጹሕም ሰው ሂሶጱን ወስዶ በውኃው ውስጥ ያጠልቀዋል፤ በድንኳኑም፥ በዕቃውም ሁሉ፥ በዚያም ባሉ ሰዎች ላይ፥ አጥንቱንም ወይም የተገደለውን ወይም የሞተውን ወይም መቃብሩን በነካው ላይ ይረጨዋል፤
19 ፤ ንጹሑም በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን በርኩሱ ላይ ይረጨዋል፤ ባሰባተኛውም ቀን ያጠራዋል፤ እርሱም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ በማታም ጊዜ ንጹሕ ይሆናል።
20 ፤ ሰውም ርኩስ ቢሆን ሁለመናውንም ባያጠራ፥ ያ ሰው የእግዚአብሔርን መቅደስ አርክሶአልና ከጉባኤው መካከል ተለይቶ ይጠፋል፤ በሚያነጻ ውኃ አልተረጨም፤ ርኩስ ነው።
21 ፤ ይህም የዘላለም ሥርዓት ይሆንላችኋል፤ የሚያነጻውን ውኃ የሚረጭ ሰው ልብሱን ያጥባል፤ የሚያነጻውንም ውኃ የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
22 ፤ ርኩሱም የሚነካው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ የሚነካውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

1 ፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በመጀመሪያው ወር ወደ ጺን ምድረ በዳ መጡ፤ ሕዝቡም በቃዴስ ተቀመጡ፤ ማርያምም በዚያ ሞተች፥ በዚያም ተቀበረች።
2 ፤ ለማኅበሩም ውኃ አልነበረም፤ በሙሴና በአሮንም ላይ ተሰበሰቡ።
3 ፤ ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት፥ እንዲህም ብለው ተናገሩት። ወንድሞቻችን በእግዚአብሔር ፊት በሞቱ ጊዜ እኛም ምነው በሞትን ኖሮ!
4 ፤ እኛ ከብቶቻችንም በዚያ እንሞት ዘንድ የእግዚአብሔርን ጉባኤ ወደዚህ ምድረ በዳ ለምን አመጣችሁ?
5 ፤ ወደዚህ ክፉ ስፍራ ታመጡን ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? ዘርና በለስ ወይንም ሮማንም የሌለበት ስፍራ ነው፤ የሚጠጣም ውኃ የለበትም።
6 ፤ ሙሴና አሮንም ከጉባኤው ፊት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሂደው በግምባራቸው ወደቁ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠላቸው።
7 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
8 ፤ በትርህን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን ሰብስቡ፥ ድንጋዩም ውኃን እንዲሰጥ እነርሱ ሲያዩ ተናገሩት፤ ከድንጋዩም ውኃ ታወጣላቸዋለህ፤ እንዲሁም ማኅበሩን ከብቶቻቸውንም ታጠጣላቸዋለህ።
9 ፤ ሙሴም እንደ ታዘዘ በትሩን ከእግዚአብሔር ፊት ወሰደ።
10 ፤ ሙሴና አሮንም ጉባኤውን በድንጋዩ ፊት ሰብስበው። እናንተ ዓመፀኞች፥ እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ ከዚህ ድንጋይ ውኃን እናወጣላችኋለን? አላቸው።
11 ፤ ሙሴም እጁን ዘርግቶ ድንጋዩን ሁለት ጊዜ በበትሩ መታው፤ ብዙም ውኃ ወጣ፥ ማኅበሩም ከብቶቻቸውም ጠጡ።
12 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን። በእስራኤል ልጆች ፊት ትቀድሱኝ ዘንድ በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይህን ጉባኤ ይዛችሁ አትገቡም አላቸው።
13 ፤ የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ላይ ጠብ ያደረጉበት፥ እርሱም ቅዱስ መሆኑን የገለጠበት ይህ የመሪባ ውኃ ነው።
14 ፤ ሙሴም ከቃዴስ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ መልእክተኞችን እንዲህ ብሎ ላከ። ወንድምህ እስራኤል እንዲህ ይላል። ያገኘንን መከራ ሁሉ አንተ ታውቃለህ፤
15 ፤ አባቶቻችን ወደ ግብፅ ወረዱ፥ በግብፅም እጅግ ዘመን ተቀመጥን ግብፃውያንም እኛንና አባቶቻችንን በደሉ፤
16 ፤ ወደ እግዚአብሔርም በጮኽን ጊዜ ድምፃችንን ሰማ፥ መልአክንም ሰድዶ ከግብፅ አወጣን፤ እነሆም፥ በምድርህ ዳርቻ ባለችው ከተማ በቃዴስ ተቀምጠናል።
17 ፤ እባክህ፥ በምድርህ ላይ እንለፍ፤ ወደ እርሻም ወደ ወይንም አንገባም፥ ከጕድጓዶችም ውኃን አንጠጣም፤ በንጉሡ ጐዳና እንሄዳለን፥ ዳርቻህንም እስክናልፍ ድረስ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አንልም።
18 ፤ ኤዶምያስም። በሰይፍ እንዳልገጥምህ በምድሬ ላይ አታልፍም አለው።
19 ፤ የእስራኤልም ልጆች። በጐዳናው እንሄዳለን፥ እኔም ከብቶቼም ከውኃህ ብንጠጣ ዋጋውን እንከፍላለን፥ ሌላም ምንም አናደርግም፤ ብቻ በእግራችን እንለፍ አሉት።
20 ፤ እርሱም። አታልፍም አለ። ኤዶምያስም በብዙ ሕዝብና በጽኑ እጅ ሊገጥመው ወጣ።
21 ፤ ኤዶምያስም እስራኤል በዳርቻው እንዳያልፍ ከለከለ፤ ስለዚህ እስራኤል ከእርሱ ተመለሰ።
22 ፤ ከቃዴስም ተጓዙ፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ወደ ሖር ተራራ መጡ።
23 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
24 ፤ አሮን ወደ ወገኑ ይከማች፤ በመሪባ ውኃ ዘንድ በቃሌ ላይ ስለ ዐመፃችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደ ሰጠኋት ምድር አይገባም።
25 ፤ አሮንና ልጁን አልዓዛርን ይዘህ ወደ ሖር ተራራ ላይ አምጣቸው፤
26 ፤ ከአሮንም ልብሱን አውጣ፥ ልጁንም አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም ወደ ወገኑ ይከማች፥ በዚያም ይሙት።
27 ፤ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘ አደረገ፤ ማኅበሩም ሁሉ እያዩ ወደ ሖር ተራራ ወጡ።
28 ፤ ሙሴም የአሮንን ልብስ አወጣ፥ ልጁንም አልዓዛርን አለበሰው፤ አሮንም በዚያ በተራራው ራስ ላይ ሞተ፤ ሙሴና አልዓዛርም ከተራራው ወረዱ።
29 ፤ ማኅበሩም ሁሉ አሮን እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ፥ የእስራኤል ቤት ሁሉ ለአሮን ሠላሳ ቀን አለቀሱ።

1 ፤ በደቡብም በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ በአታሪም መንገድ እስራኤል እንደ መጡ ሰማ፤ ከእስራኤልም ጋር ሰልፍ አደረገ ከእነርሱም ምርኮ ማረከ።
2 ፤ እስራኤልም ለእግዚአብሔር። እነዚህን አሳልፈህ በእጄ ብትሰጣቸው ከተሞቻቸውን እርም ብዬ አጠፋለሁ ብሎ ስእለት ተሳለ።
3 ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ድምፅ ሰማ፥ ከነዓናውያንንም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱንም ከተሞቻቸውንም እርም ብለው አጠፉ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ሔርማ ብለው ጠሩት።
4 ፤ ከሖርም ተራራ ከኤዶምያስ ምድር ርቀው ሊዞሩ በኤርትራ ባሕር መንገድ ተጓዙ፤ የሕዝቡም ሰውነት ከመንገዱ የተነሣ ደከመ።
5 ፤ ሕዝቡም በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ። በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃ የለም፤ ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ ብለው ተናገሩ።
6 ፤ እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ እባቦችን ሰደደ፥ ሕዝቡንም ነደፉ፤ ከእስራኤልም ብዙ ሰዎች ሞቱ።
7 ፤ ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው። በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ስለ ተናገርን በድለናል፤ እባቦችን ከእኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን አሉት።
8 ፤ ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ። እግዚአብሔርም ሙሴን። እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል፤ የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል አለው።
9 ፤ ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ።
10 ፤ የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኦቦትም ሰፈሩ።
11 ፤ ከኦቦትም ተጕዘው በሞዓብ ፊት ለፊት ባለችው ምድረ በዳ፥ በፀሐይ መውጫ በኩል፥ በዒዬዓባሪም ሰፈሩ።
12 ፤ ከዚያም ተጕዘው በዘሬድ ሸለቆ ሰፈሩ።
13 ፤ ከዚያም ተጕዘው ከአሞራውያን ዳርቻ በሚወጣው ምድረ በዳ ውስጥ በአሮኖን ማዶ ሰፈሩ፤ አሮኖን በሞዓብና በአሞራውያን መካከል ያለ የሞዓብ ዳርቻ ነውና።
14 ፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር የጦርነት መጽሐፍ እንዲህ ተባለ። ዋሄብ በሱፋ፥ የአርኖንም ሸለቆች፥
15 ፤ ወደ ዔር ማደሪያ የሚወርድ በሞዓብም ዳርቻ የሚጠጋ የሸለቆች ፈሳሽ።
16 ፤ ከዚያም ወደ ብኤር ተጓዙ፤ ይኸውም እግዚአብሔር ሙሴን። ሕዝቡን ሰብስብ ውኃንም እሰጣቸዋለሁ ብሎ የተናገረለት ጕድጓድ ነው።
17 ፤ በዚያም ጊዜ እስራኤል ይህን መዝሙር ዘመረ። አንተ ምንጭ ሆይ፥ ፍለቅ፤ እናንተ ዘምሩለት፤
18 ፤ በበትረ መንግሥት በበትራቸውም የሕዝብ አዛውንቶች ያጐደጐዱት፥ አለቆችም የቈፈሩት ጕድጓድ።
19 ፤ ከምድረ በዳም ወደ መቴና ተጓዙ፤ ከመቴናም ወደ ነሃሊኤል፥ ከነሃሊኤልም ወደ ባሞት፥
20 ፤ ከባሞትም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ በሞዓብ በረሀ ወዳለው ሸለቆ ተጓዙ።
21-22፤ እስራኤልም። በምድርህ ላይ እንለፍ፤ ወደ እርሻና ወደ ወይን ቦታ አንገባም፤ ከጕድጓድም ውኃን አንጠጣም፤ ከምድርህ ዳርቻ እስክንወጣ ድረስ በንጉሥ ጐዳና እንሄዳለን ብለው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልእክተኞችን ላኩ።
23 ፤ ሴዎንም እስራኤል በምድሩ ላይ ያልፍ ዘንድ እንቢ አለ፤ ሴዎንም ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፥ እስራኤልንም ለመውጋት ወደ ምድረ በዳ ወጣ፥ ወደ ያሀጽም መጣ፥ ከእስራኤልም ጋር ተዋጋ።
24 ፤ እስራኤልም በሰይፍ መታው፥ ምድሩንም ከአርኖን ጀምሮ እስከ አሞን ልጆች እስከ ያቦቅ ድረስ ወረሰ፤ የአሞንም ልጆች ዳርቻ የጸና ነበረ።
25 ፤ እስራኤልም እነዚህን ከተሞች ሁሉ ወሰደ፤ እስራኤልም በአሞራውያን ከተሞች ሁሉ በሐሴቦንና በመንደሮቹ ሁሉ ተቀመጠ።
26 ፤ ሐሴቦንም የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተማ ነበረ፤ እርሱም የፊተኛውን የሞዓብን ንጉሥ ወግቶ እስከ አርኖን ድረስ ምድሩን ሁሉ ከእጁ ወስዶ ነበር።
27 ፤ ስለዚህ በምሳሌ እንዲህ ተብሎ ተነገረ። ወደ ሐሴቦን ኑ፤ የሴዎን ከተማ ይሠራ፥ ይመሥረት፤
28 ፤ እሳት ከሐሴቦን፥ ነበልባልም ከሴዎን ከተማ ወጣ፤ የሞዓብን ዔር፥ የአርኖንን ተራራ አለቆች በላ፤
29 ፤ ሞዓብ ሆይ፥ ወዮልህ! የከሞስ ሕዝብ ሆይ፥ ጠፋህ፤ ወንዶች ልጆቹን ለሽሽት፥ ሴቶች ልጆቹንም ለምርኮ፥ ለአሞራውያን ንጉሥ ለሴዎን ሰጠ።
30 ፤ ገተርናቸው፤ ከሐሴቦን እስከ ዴቦን ድረስ ጠፉ፤ ኖፋም እስኪደርሱ እስከ ሜድባ አፈረስናቸው።
31 ፤ እስራኤልም እንደዚህ በአሞራውያን ምድር ተቀመጡ።
32 ፤ ሙሴም ሰላዮችን ወደ ኢያዜር ሰደደ፤ መንደሮችዋንም ወሰዱ፥ በዚያም የነበሩትን አሞራውያን አባረሩ።
33 ፤ ተመልሰውም በበሳን መንገድ ወጡ፤ የባሳንም ንጉሥ ዐግ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር በኤድራይ ይወጋቸው ዘንድ ወጣ።
34 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሪቱንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦንም በተቀመጠው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግህ እንዲሁ ታደርግበታለህ አለው።
35 ፤ እርሱንና ልጆቹን ሕዝቡንም ሁሉ መቱ ሰውም አልቀረለትም፤ ምድሩንም ወረሱ።

1 ፤ የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በዮርዳኖስ ማዶ ባለው በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ።
2 ፤ የሴፎር ልጅ ባላቅ እስራኤል በአሞራውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ አየ።
3 ፤ ብዙም ነበረና ሞዓብ ከሕዝቡ እጅግ ፈራ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ሞዓብ ደነገጠ።
4 ፤ ሞዓብም የምድያምን ሽማግሌዎች። በሬ የለመለመውን ሣር እንደሚጨርስ ይህ ጭፍራ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ይጨርሳል አላቸው። በዚያን ጊዜም የሴፎር ልጅ ባላቅ የሞዓብ ንጉሥ ነበረ።
5-6፤ በወንዙ አጠገብ ባለችው በሕዝቡ ልጆች ምድር በፋቱራ ወደ ተቀመጠው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም። እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ አለ፤ እነሆም፥ የምድሩን ሁሉ ፊት ሸፈነ፥ በአቅራቢያችንም ተቀምጦአል፤ አሁንም ይህ ሕዝብ ከእኔ ይበልጣልና ልወጋቸውና ከምድሪቱ ላሳድዳቸው እችል እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ና ርገምልኝ፤ አንተ የመረቅኸው ምሩቅ የረገምኸውም ርጉም እንደ ሆነ አውቃለሁና ብሎ ይጠሩት ዘንድ መልእክተኞቹን ላከ።
7 ፤ የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም የምዋርቱን ዋጋ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለዓምም መጡ፥ የባላቅንም ቃል ነገሩት።
8 ፤ እርሱም። ዛሬ ሌሊት በዚህ እደሩ፥ እግዚአብሔርም እንደሚነግረኝ እመልስላችኋለሁ አላቸው፤ የሞዓብም አለቆች በበለዓም ዘንድ ተቀመጡ።
9 ፤ እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ። እነዚህ በአንተ ዘንድ ያሉ ሰዎች እነማን ናቸው? አለው።
10-11፤ በለዓምም እግዚአብሔርን። የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ። እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ የምድርን ፊት ሸፈነ፥ አሁንም ና እርሱንም ርገምልኝ፤ ምናልባት እወጋው አሳድደውም ዘንድ እችል እንደ ሆነ ብሎ ወደ እኔ ልኮአል አለው።
12 ፤ እግዚአብሔርም በለዓምን። ከእነርሱ ጋር አትሂድ፤ የተባረከ ነውና ሕዝቡን አትረግምም አለው።
13 ፤ በለዓምም ሲነጋ ተነሥቶ የባላቅን አለቆች። ከእናንተ ጋር እሄድ ዘንድ እግዚአብሔር አልፈቀደምና ወደ ምድራችሁ ሂዱ አላቸው።
14 ፤ የሞዓብ አለቆች ተነሡ፥ ወደ ባላቅም መጥተው። በለዓም ከእኛ ጋር ይመጣ ዘንድ አልፈቀደም አሉት።
15 ፤ ባላቅም ደግሞ ከፊተኞች የበዙና የከበሩ ሌሎችን አለቆች ሰደደ።
16-17፤ ወደ በለዓምም መጥተው። የሴፎር ልጅ ባላቅ። ክብርህን እጅግ ታላቅ አደርገዋለሁና፥ የተናገርኸውንም ሁሉ አደርግልሃለሁና እባክህ፥ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ ምንም አይከልክልህ፤ እባክህ፥ ና፥ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ አለ ብለው ነገሩት።
18 ፤ በለዓምም መልሶ የባላቅን ባሪያዎች። ባላቅ በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ፥ በትንሹ ወይም በትልቁ ቢሆን የአምላኬን የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤
19 ፤ አሁንም እግዚአብሔር ደግሞ የሚነግረኝን አውቅ ዘንድ፥ እባካችሁ፥ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ አላቸው።
20 ፤ እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ። ሰዎቹ ይጠሩህ ዘንድ መጥተው እንደ ሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱም ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ታደርጋለህ አለው።
21 ፤ በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፥ አህያይቱንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ።
22 ፤ እርሱም ስለ ሄደ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሊቋቋመው በመንገድ ላይ ቆመ። እርሱም በአህያይቱ ላይ፥ ሁለቱም ሎሌዎቹ ከእርሱ ጋር ነበሩ።
23 ፤ አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየች፤ ከመንገዱም ፈቀቅ ብላ ወደ እርሻው ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገድ ይመልሳት ዘንድ አህያይቱን መታት።
24 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከወይኑ ቦታዎች መካከል በወዲያና በወዲህ ወገን ግንብ በነበረበት በጠባብ መንገድ ላይ ቆመ።
25 ፤ አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፥ የበለዓምንም እግር ከቅጥሩ ጋር አጣበቀች፤ እርሱም ደግሞ መታት።
26 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ ፊት ሄደ፥ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ።
27 ፤ አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አየች፥ ከበለዓምም በታች ተኛች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጣ፥ አህያይቱንም በበትሩ ደበደባት።
28 ፤ እግዚአብሔርም የአህያይቱን አፍ ከፈተ፥ በለዓምንም። ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌብህ ነው? አለችው።
29 ፤ በለዓምም አህያይቱን። ስላላገጥሽብኝ ነው፤ በእጄስ ሰይፍ ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር አላት።
30 ፤ አህያይቱም በለዓምን። ከብዙ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ እንዲህ አደርግ ዘንድ ልማዴ ነበረን? አለችው። እርሱም። እንዲህ አላደረግሽብኝም አላት።
31 ፤ እግዚአብሔርም የበለዓምን ዓይኖች ከፈተ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደቀ።
32 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ። አህያህን ሦስት ጊዜ ለምን መታህ? እነሆ፥ መንገድህ በፊቴ ጠማማ ነውና እቋቋምህ ዘንድ ወጥቼአለሁ፤
33 ፤ አህያይቱም አይታኝ ከፊቴ ሦስት ጊዜ ፈቀቅ አለች፤ ከፊቴስ ፈቀቅ ባላለች በእውነት አሁን አንተን በገደልሁህ፥ እርስዋንም ባዳንኋት ነበር አለው።
34 ፤ በለዓምም የእግዚአብሔርን መልአክ። በድያለሁ፤ አንተ በመንገድ ላይ በፊቴ እንደቆምህብኝ አላወቅሁም፤ እንግዲህም አሁን አትወድድ እንደ ሆነ እመለሳለሁ አለው።
35 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በለዓምን። ከሰዎቹ ጋር ሂድ፥ ነገር ግን የምናገርህን ቃል ብቻ ትናገራለህ አለው። በለዓምም ከባላቅ አለቆች ጋር ሄደ።
36 ፤ ባላቅም በለዓም እንደ መጣ በሰማ ጊዜ በአርኖን ዳር ዳርቻ በመጨረሻ ወዳለችው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊገናኘው ወጣ።
37 ፤ ባላቅም በለዓምን። በውኑ አንተን ለመጥራት አልላክሁብህምን? ለምንስ ወደ እኔ አልመጣህም? በውኑ አንተን ለማክበር እኔ አልችልምን? አለው።
38 ፤ በለዓምም ባላቅን። እነሆ፥ ወደ አንተ መጥቼአለሁ፤ በውኑ አሁን አንዳችን ነገር እናገር ዘንድ እችላለሁን? እግዚአብሔር በአፌ የሚያደርገውን ቃል እርሱን እናገራለሁ አለው።
39 ፤ በለዓምም ከባላቅ ጋር ሄደ፥ ወደ ቂርያት ሐጾትም መጡ።
40 ፤ ባላቅም በሬዎችንና በጎችን አርዶ ወደ በለዓም ከእርሱም ጋር ወዳሉት አለቆች ላከ።
41 ፤ በነጋውም ባላቅ በለዓምን ይዞ ወደ በኣል ኮረብታ መስገጃ አወጣው፤ በዚያም ሆኖ የሕዝቡን ዳርቻ አየ።

1 ፤ በለዓምም ባላቅን። ሰባት መሠዊያ በዚህ ሥራልኝ፥ ሰባትም ወይፈን ሰባትም አውራ በግ በዚህ አዘጋጅልኝ አለው።
2 ፤ ባላቅም በለዓም እንደ ተናገረ አደረገ፤ ባላቅና በለዓምም በየመሠዊያው ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረጉ።
3 ፤ በለዓምም ባላቅን። በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ፥ እኔም እሄዳለሁ፤ ምናልባት እግዚአብሔር ሊገናኘኝ ይመጣል፤ እርሱም የሚገልጥልኝን እነግርሃለሁ አለው። ወደ ጉብታም ሄደ።
4 ፤ እግዚአብሔርም ከበለዓም ጋር ተገናኘ፤ እርሱም። ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጀሁ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረግሁ አለው።
5 ፤ እግዚአብሔርም ቃልን በበለዓም አፍ አድርጎ። ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም በል አለው።
6 ፤ ወደ እርሱም ተመለሰ፥ እነሆም፥ እርሱና የሞዓብ አለቆች ሁሉ በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር።
7 ፤ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። ባላቅ ከአራም አመጣኝ፥ የሞዓብ ንጉሥ ከምሥራቅ ተራሮች፤ ና፥ ያዕቆብን ርገምልኝ፤ ና፥ እስራኤልን ተጣላልኝ ብሎ።
8 ፤ እግዚአብሔር ያልረገመውን እንዴት እረግማለሁ?
9 ፤ በአምቦች ራስ ላይ ሆኜ አየዋለሁ፥ በኮረብቶችም ላይ ሆኜ እመለከተዋለሁ፤ እነሆ፥ ብቻውን የሚቀመጥ ሕዝብ ነው፥ በአሕዛብም መካከል አይቈጠርም።
10 ፤ የያዕቆብን ትቢያ ማን ይቈጥራል? የእስራኤልስ እርቦ ማን ይቈጥራል? የጻድቃንን ሞት እኔ ልሙት፥ ፍጻሜዬም እንደ እርሱ ፍጻሜ ትሁን።
11 ፤ ባላቅም በለዓምን። ያደረግህብኝ ምንድር ነው? ጠላቶቼን ትረግምልኝ ዘንድ ጠራሁህ፤ እነሆም፥ ፈጽመህ ባረክሃቸው አለው።
12 ፤ እርሱም መልሶ። በውኑ እግዚአብሔር በአፌ ያደረገውን እናገር ዘንድ አልጠነቀቅምን? አለው።
13 ፤ ባላቅም። በዚያ ሆነህ ታያቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ ከእኔ ጋር ወደ ሌላ ቦታ ና ዳርቻቸውንም ብቻ ታያለህ፥ ሁሉን ግን አታይም፤ በዚያም ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ አለው።
14 ፤ ወደ ጾፊምም ሜዳ ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ ላይ ወሰደው፤ ሰባትም መሠዊያዎች ሠራ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈን አንድም አውራ በግ አሳረገ።
15 ፤ ባላቅንም። እኔ ወደዚያ ለመገናኘት ስሄድ በዚህ በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ አለው።
16 ፤ እግዚአብሔርም በለዓምን ተገናኘ፥ ቃልንም በአፉ አድርጎ። ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም በል አለው።
17 ፤ ወደ እርሱም መጣ፥ እነሆም፥ እርሱ ከእርሱም ጋር የሞዓብ አለቆች በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር፤ ባላቅም። እግዚአብሔር የተናገረው ምንድር ነው? አለው።
18 ፤ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። ባላቅ ሆይ፥ ተነሣ፥ ስማ፤ የሴፎር ልጅ ሆይ፥ አድምጠኝ፤
19 ፤ ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም። እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን?
20 ፤ እነሆ፥ ለመባረክ ትእዛዝን ተቀብያለሁ፤ እርሱ ባርኮአል፥ እመልሰውም ዘንድ አልችልም።
21 ፤ በያዕቆብ ላይ ክፋትን አልተመለከተም፥ በእስራኤልም ጠማምነትን አላየም፤ አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው፥ የንጉሥም እልልታ በመካከላቸው አለ።
22 ፤ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶአቸዋል፤ ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው።
23 ፤ በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፥ በእስራኤልም ላይ ምዋርት የለም፤ በጊዜው ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል። እግዚአብሔር ምን አደረገ! ይባላል።
24 ፤ እነሆ፥ ሕዝቡ እንደ እንስት አንበሳ ይቆማል፥ እንደ አንበሳም ይነሣል፤ ያደነውን አስኪበላ፥ የገደለውንም ደሙን እስኪጠጣ አይተኛም።
25 ፤ ባላቅም በለዓምን። ከቶ አትርገማቸው፥ ከቶም አትባርካቸው አለው።
26 ፤ በለዓምም መልሶ ባላቅን። እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ አደርጋለሁ ብዬ አልተናገርሁህምን? አለው።
27 ፤ ባላቅም በለዓምን። ና፥ ወደ ሌላ ስፍራ እወስድሃለሁ፤ ምናልባት በዚህ ሆነህ እነርሱን ትረግምልኝ ዘንድ እግዚአብሔር ይወድዳል አለው።
28 ፤ ባላቅም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፌጎር ላይ በለዓምን ወሰደው።
29 ፤ በለዓምም ባላቅን። በዚህ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፥ በዚህም ሰባት ወይፈን ሰባትም አውራ በግ አዘጋጅልኝ አለው።
30 ፤ ባላቅም በለዓም እንዳለው አደረገ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረገ።

1 ፤ በለዓምም እግዚአብሔር እስራኤልን ይባርክ ዘንድ እንዲወድድ ባየ ጊዜ፥ አስቀድሞ ያደርግ የነበረውን አስማት ይሻ ዘንድ አልሄደም፤ ነገር ግን ወደ ምድረ በዳ ፊቱን አቀና።
2 ፤ በለዓምም ዓይኑን አንሥቶ እስራኤል በየነገዱ ተቀምጦ አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ መጣ።
3 ፤ ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዓይኖቹ የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤
4 ፤ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል።
5 ፤ ያዕቆብ ሆይ፥ ድንኳኖችህ፥ እስራኤል ሆይ ማደሪያዎችህ ምንኛ ያምራሉ!
6 ፤ እንደ ሸለቆች፥ በወንዝ ዳር እንዳሉ አትክልቶች፥ እግዚአብሔር እንደ ተከለው እሬት በውኃም ዳር እንዳሉ ዝግባዎች ተዘርግተዋል።
7 ፤ ከማድጋዎቹ ውኃ ይፈስሳል፥ ዘሩም በብዙ ውኆች ይሆናል፥ ንጉሡም ከአጋግ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፥ መንግሥቱም ይከበራል።
8 ፤ እግዚአብሔርም ከግብፅ አውጥቶታል፤ ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው፤ ጠላቶቹን አሕዛብን ይበላል፥ አጥንቶቻቸውንም ይሰባብራል፥ በፍላጾቹም ይወጋቸዋል።
9 ፤ እንደ አንበሳ ዐርፎ ተኝቶአል፥ እንደ እንስቲቱም አንበሳ ተጋድሞአል፤ ማን ያስነሣዋል? የሚመርቅህ ሁሉ የተመረቀ ይሁን፥ የሚረግምህም ሁሉ የተገመ ይሁን።
10 ፤ የባላቅም ቍጣ በበለዓም ላይ ነደደ፤ እጆቹንም አጨበጨበ፤ ባላቅም በለዓምን። ጠላቶቼን ትረግም ዘንድ ጠራሁህ፥ እነሆም፥ ሦስት ጊዜ ፈጽመህ መረቅሃቸው፤ አሁንም እንግዲህ ወደ ስፍራህ ሽሽ፤
11 ፤ እኔ አከብርህ ዘንድ ወድጄ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን፥ እነሆ፥ ክብርህን ከለከለ አለው።
12-13፤ በለዓምም ባላቅን አለው። ባላቅ በቤቱ የሞላውን ብርና ወርቅ ቢሰጠኝ፥ መልካሙን ወይም ክፉውን ከልቤ ለማድረግ የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ እግዚአብሔር የተናገረውን እርሱን እናገራለሁ ብዬ ወደ እኔ ለላክሃቸው መልእክተኞች አልተናገርኋቸውምን?
14 ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ ወደ ሕዝቤ እሄዳለሁ፤ ና፥ ይህ ሕዝብ በኋለኛው ዘመን በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን እነግርሃለሁ።
15 ፤ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤
16 ፤ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ የልዑልንም እውቀት የሚያውቅ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል።
17 ፤ አየዋለሁ፥ አሁን ግን አይደለም፤ እመለከተዋለሁ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ ከእስራኤል በትር ይነሣል፥ የሞዓብንም ማዕዘኖች ይመታል፥ የሤትንም ልጆች ያጠፋል።
18 ፤ ኤዶምያስም ርስቱ ይሆናል፥ ጠላቱ ሴይር ደግሞ ርስቱ ይሆናል፤ እስራኤልም በኃይል ያደርጋል።
19 ፤ ከያዕቆብም የሚወጣ ገዥ ይሆናል፥ ከከተማውም የቀሩትን ያጠፋል።
20 ፤ አማሌቅንም አይቶ ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። አማሌቅ የአሕዛብ አለቃ ነበረ፤ ፍጻሜው ግን ወደ ጥፋት ይመጣል።
21 ፤ ቄናውያንንም አይቶ ምሳሌውን ይምስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። ማደሪያህ የጸና ነው፥ ጎጆህም በአምባ ላይ ተሠርቶአል፤
22 ፤ ነገር ግን አሦር እስኪማርክህ ድረስ ቄናዊው ለጥፋት ይሆናል።
23 ፤ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። እግዚአብሔር ይህን ሲያደርግ አወይ! ማን በሕይወት ይኖራል?
24 ፤ ከኪቲም ዳርቻ መርከቦች ይመጣሉ፥ አሦርንም ያስጨንቃሉ፥ ዔቦርንም ያስጨንቃሉ፤ እርሱም ደግሞ ወደ ጥፋት ይመጣል።
25 ፤ በለዓምም ተነሣ፥ ተመልሶም ወደ ስፍራው ሄደ፤ ባላቅም ደግሞ መንገዱን ሄደ።

1 ፤ እስራኤልም በሰጢም ተቀመጡ፤ ሕዝቡም ከሞዓብ ልጆች ጋር ያመነዝሩ ጀመር።
2 ፤ ሕዝቡንም ወደ አምላኮቻቸው መሥዋዕት ጠሩ፤ ሕዝቡም በሉ፥ ወደ አምላኮቻቸውም ሰገዱ።
3 ፤ እስራኤልም ብዔልፌጎርን ተከተለ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ።
4 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የእግዚአብሔር የቍጣው ጽናት ከእስራኤል እንዲመለስ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ ወስደህ በፀሐዩ ፊት ወደ እግዚአብሔር ስቀላቸው አለው።
5 ፤ ሙሴም የእስራኤልን ዳኞች። እናንተ ሁሉ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሰዎቻችሁን ግደሉ አላቸው።
6 ፤ እነሆም፥ ከእስራኤል ልጆች አንዱ መጥቶ በሙሴና በእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ፊት ምድያማዊቱን አንዲቱን ሴት ወደ ወንድሞቹ አመጣት፤ እነርሱም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ያለቅሱ ነበር።
7 ፤ የካህኑም የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባየው ጊዜ ከማኅበሩ መካከል ተነሥቶ በእጁ ጦር አነሣ፤
8 ፤ ያንንም የእስራኤልን ሰው ተከትሎ ወደ ድንኳኑ ገባ። እስራኤላዊውንም ሰውና ሴቲቱን ሁለቱን ሆዳቸውን ወጋቸው። ከእስራኤልም ልጆች መቅሠፍቱ ተከለከለ።
9 ፤ በመቅሠፍትም የሞተው ሀያ አራት ሺህ ነበረ።
10 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
11 ፤ የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በቅንዓቴ በመካከላቸው ቀንቶአልና ቍጣዬን ከእስራኤል ልጆች መለሰ፤ እኔም የእስራኤልን ልጆች በቅንዓቴ አላጠፋሁም።
12 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሰላሜን ቃል ኪዳን እሰጠዋለሁ።
13 ፤ ለአምላኩም ቀንቶአልና፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተስርዮአልና ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘላለም ክህነት ቃል ኪዳን ይሆንለታል።
14 ፤ ከምድያማዊቱም ጋር የተገደለው የእስራኤላዊው ሰው ስም ዘንበሪ ነበረ፤ የአባቱ ቤት አለቃ የስምዖናውያን የሆነ የሰሉ ልጅ ነበረ።
15 ፤ የተገደለችውም ምድያማዊት ስምዋ ከስቢ ነበረ፤ እርስዋም የሱር ልጅ ነበረች፤ እርሱም በምድያም ዘንድ የአባቱ ቤት ወገን አለቃ ነበረ።
16 ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
17-18፤ በፌጎር በመቅሠፍቱ ቀን ስለተገደለችው ስለ ምድያም አለቃ ልጅ ስለ እኅታቸው ስለ ከስቢ በፌጎር ምክንያት በሸነገሉአችሁ ሽንገላ አስጨንቀዋችኋልና ምድያማውያንን አስጨንቁአቸው ግደሉአቸውም።

1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ መቅሠፍቱ ከሆነ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴንና የካህኑን የአሮን ልጅ አልዓዛርን።
2 ፤ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን፥ በእስራኤል ወደ ሰልፍ የሚወጣውን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ በየአባቶቻቸው ቤት ቍጠሩ ብሎ ተናገራቸው።
3 ፤ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ።
4 ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ከግብፅም ምድር የወጡትን የእስራኤልን ልጆች እንዳዘዛቸው፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን ሕዝቡን ቍጠሩ ብለው ተናገሩአቸው።
5 ፤ የእስራኤል በኵር ሮቤል፤ የሮቤል ልጆች፤ ከሄኖኅ የሄኖኀውያን ወገን፥ ከፈሉስ የፈሉሳውያን ወገን፥
6 ፤ ከአስሮን የአስሮናውያን ወገን፥ ከከርሚ የከርማውያን ወገን።
7 ፤ እነዚህ የሮቤላውያን ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበሩ።
8 ፤ የፈሉስም ልጆች፤ ኤልያብ።
9 ፤ የኤልያብም ልጆች፤ ነሙኤል፥ ዳታን፥ አቤሮን፤ እነዚህ ዳታንና አቤሮን ከማኅበሩ የተመረጡ ነበሩ፤ ከቆሬ ወገን ጋር በእግዚአብሔር ላይ ባመፁ ጊዜ ሙሴንና አሮንን ተጣሉ፤
10 ፤ ያም ወገን በሞተ ጊዜ ምድሪቱ አፍዋን ከፍታ ከቆሬ ጋር ዋጠቻቸው፤ በዚያም ጊዜ እሳቲቱ ሁለት መቶ አምሳውን ሰዎች አቃጠለቻቸው፤ እነርሱም ለምልክት ሆኑ።
11 ፤ የቆሬ ልጆች ግን አልሞቱም።
12 ፤ የስምዖን ልጆች በየወገናቸው፤ ከነሙኤል የነሙኤላውያን ወገን፥ ከያሚን የያሚናውያን ወገን፥ ከያኪን የያኪናውያን ወገን፥ ከዛራ የዛራውያን ወገን፥
13 ፤ ከሳኡል የሳኡላውያን ወገን።
14 ፤ እነዚህ የስምዖናውያን ወገኖች ናቸው፤ ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
15 ፤ የጋድ ልጆች በየወገናቸው፤ ከጽፎን የጽፎናውያን ወገን፥ ከሐጊ የሐጋውያን ወገን፥
16 ፤ ከሹኒ የሹናውያን ወገን፥ ከኤስናን የኤስናናውያን ወገን፥ ከዔሪ የዔራውያን ወገን፥
17 ፤ ከአሮድ የአሮዳውያን ወገን፥ ከአርኤሊ የአርኤላውያን ወገን።
18 ፤ እነዚህ የጋድ ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
19 ፤ የይሁዳ ልጆች ዔርና አውናን፤ ዔርና አውናንም በከነዓን ምድር ሞቱ።
20 ፤ የይሁዳም ልጆች በየወገናቸው፤ ከሴሎም የሴሎማውያን ወገን፥ ከፋሬስ የፋሬሳውያን ወገን፥ ከዛራ የዛራውያን ወገን።
21 ፤ የፋሬስም ልጆች፤ ከኤስሮም የኤስሮማውያን ወገን፥ ከሐሙል የሐሙላውያን ወገን።
22 ፤ እነዚህ የይሁዳ ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ሰባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
23 ፤ የይሳኮር ልጆች በየወገናቸው፤ ከቶላ የቶላውያን ወገን፥ ከፉዋ የፉዋውያን ወገን፥
24 ፤ ከያሱብ የያሱባውያን ወገን፥ ከሺምሮን የሺምሮናውያን ወገን።
25 ፤ እነዚህ የይሳኮር ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ስድሳ አራት ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ።
26 ፤ የዛብሎን ወገኖች በየወገናቸው፤ ከሴሬድ የሴሬዳውያን ወገን፥ ከኤሎን የኤሎናውያን ወገን፥ ከያሕልኤል የያሕልኤላውያን ወገን።
27 ፤ እነዚህ የዛብሎናውያን ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ስድሳ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
28 ፤ የዮሴፍ ልጆች በየወገናቸው፤ ምናሴና ኤፍሬም።
29 ፤ የምናሴ ልጆች፤ ከማኪር የማኪራውያን ወገን፤ ማኪርም ገለዓድን ወለደ፤ ከገለዓድ የገልዓዳውያን ወገን።
30 ፤ የገለዓድ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከኢዔዝር የኢዔዝራውያን ወገን፥ ከኬሌግ የኬሌጋውያን ወገን፥
31 ፤ ከአሥሪኤል የአሥሪኤላውያን ወገን፥
32 ፤ ከሴኬም የሴኬማውያን ወገን፥ ከሸሚዳ የሸሚዳውያን ወገን፥ ከኦፌር የኦፌራውያን ወገን።
33 ፤ የኦፌርም ልጅ ሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ የሰለጰዓድም የሴቶች ልጆቹ ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ።
34 ፤ እነዚህ የምናሴ ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አምሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ።
35 ፤ በየወገናቸው የኤፍሬም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሱቱላ የሱቱላውያን ወገን፥ ከቤኬር የቤኬራውያን ወገን፥ ከታሐን የታሐናውያን ወገን።
36 ፤ እነዚህ የሱቱላ ልጆች ናቸው፤ ከዔዴን የዔዴናውያን ወገን። ከዔዴን የዔዴናውያና ወገን።
37 ፤ እነዚህ የኤፍሬም ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የዮሴፍ ልጆች እነዚህ ናቸው።
38 ፤ የብንያም ልጆች በየወገናቸው፤ ከቤላ የቤላውያን ወገን፥ ከአስቤል የአስቤላውያን ወገን፥ ከአኪራን የአኪራናውያን ወገን፥ ከሶፋን የሶፋናውያን ወገን፥
39 ፤ ከሑፋም የሑፋማውያን ወገን።
40 ፤ የቤላም ልጆች፤ አርድና ናዕማን፤ ከአርድ የአርዳውያን ወገን፥ ከናዕማን የናዕማናውያን ወገን።
41 ፤ በየወገናቸው የብንያም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
42 ፤ በየወገናቸው የዳን ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሰምዔ የሰምዔያውያን ወገን፤ በየወገናቸው የዳን ወገኖች እነዚህ ናቸው።
43 ፤ የሰምዔያውያን ወገኖች ሁሉ ከእነርሱ እንደ ተቈጠሩ ስድሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
44 ፤ የአሴር ልጆች በየወገናቸው፤ ከዪምና የዪምናውያን ወገን፥ ከየሱዋ የየሱዋውያን ወገን፥ ከበሪዓ የበሪዓውያን ወገን።
45 ፤ ከበሪዓ ልጆች፤ ከሔቤር የሔቤራውያን ወገን፥ ከመልኪኤል የመልኪኤላውያን ወገን።
46 ፤ የአሴርም የሴት ልጁ ስም ሤራሕ ነበረ።
47 ፤ እነዚህ የአሴር ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
48 ፤ የንፍታሌም ልጆች በየወገናቸው፤ ከያሕጽኤል የያሕጽኤላውያን ወገን፥ ከጉኒ የጉናውያን ወገን፥
49 ፤ ከዬጽር የዬጽራውያን ወገን፥ ከሺሌም የሺሌማውያን ወገን።
50 ፤ በየወገናቸው የንፍታሌም ወገኖች እነዚህ ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
51 ፤ ከእስራኤል ልጆች የተቈጠሩት እነዚህ ናቸው፤ ስድስት መቶ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበሩ።
52 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
53 ፤ ለእነዚህ በየስማቸው ቍጥር ምድሪቱ ርስት ሆና ትከፈላለች።
54 ፤ ለብዙዎቹ እንደ ብዛታቸው፥ ለጥቂቶቹም እንደ ጥቂትነታቸው መጠን ርስትን ትሰጣቸዋለህ። ለሁሉ እንደ ቍጥራቸው መጠን ርስታቸው ይሰጣቸዋል።
55 ፤ ነገር ግን ምድሪቱ በዕጣ ትከፈላለች፤ እንደ አባቶቻቸው ነገድ ስም ይወርሳሉ።
56 ፤ በብዙዎችና በጥቂቶች መካከል ርስታቸው በዕጣ ትከፈላለች።
57 ፤ ከሌዋውያንም በየወገናቸው የተቈጠሩት እነዚህ ናቸው፤ ከጌድሶን የጌድሶናውያን ወገን፥ ከቀዓት የቀዓታውያን ወገን፥ ከሜራሪ የሜራራውያን ወገን።
58 ፤ እነዚህ የሌዊ ወገኖች ናቸው፤ የሊብናውያን ወገን፥ የኬብሮናውያን ወገን፥ የሞሖላውያን ወገን፥ የሙሳውያን ወገን፥ የቆሬያውያን ወገን። ቀዓትም እንበረምን ወለደ።
59 ፤ የእንበረም ሚስት ስም ዮካብድ ነበረ። እርስዋ በግብፅ ከሌዊ የተወለደች የሌዊ ልጅ ነበረች፤ ለእንበረምም አሮንንና ሙሴን እኅታቸውንም ማርያምን ወለደችለት።
60 ፤ ለአሮንም ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር ተወለዱለት።
61 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ሌላ እሳት ባቀረቡ ጊዜ ናዳብና አብዩድ ሞቱ።
62 ፤ ከአንድ ወርም ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉ ወንዶች ሁሉ ከእነርሱ የተቈጠሩ ሀያ ሦስት ሺህ ነበሩ። ከእስራኤልም ልጆች መካከል ርስት አልተሰጣቸውምና ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም።
63 ፤ በሞዓብ ሜዳ ላይ በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት ሲቈጥሩ፥ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር የቈጠሩአቸው የእስራኤል ልጆች እነዚህ ናቸው።
64 ፤ ነገር ግን ሙሴና ካህኑ አሮን በሲና ምድረ በዳ የእስራኤልን ልጆች በቈጠሩአቸው ጊዜ ከነበሩት ከእነዚያ መካከል አንድም ሰው አልነበረም።
65 ፤ እግዚአብሔር ስለ እነርሱ። በእውነት በምድረ በዳ ይሞታሉ ብሎ ተናግሮአልና። ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ ከነዌም ልጅ ከኢያሱ በቀር ከእነርሱ አንድ ሰው ስንኳ አልቀረም።

1 ፤ ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ወገኖች፥ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጅ የኦፌር ልጅ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች ቀረቡ፤ የእነዚህም ሴቶች ልጆች ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ።
2 ፤ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በሙሴና በካህኑ በአልዓዛር በአለቆቹም በማኅበሩም ሁሉ ፊት ቆመው።
3 ፤ አባታችን በምድረ በዳ ሞተ፤ በራሱ ኃጢአት ሞተ እንጂ ከቆሬ ጋር በእግዚአብሔር ላይ በተሰበሰቡ ወገን መካከል አልነበረም፤ ወንዶችም ልጆች አልነበሩትም።
4 ፤ ወንድ ልጅስ ባይኖረው የአባታችን ስም ከወገኑ መካከል ለምን ይጠፋል? በአባታችን ወንድሞች መካከል ርስትን ስጠን አሉ።
5 ፤ ሙሴም ነገራቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረበ።
6 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
7 ፤ የሰለጰዓድ ልጆች እውነት ተናግረዋል፤ በአባታቸው ወንድሞች መካከል የርስት ድርሻ ስጣቸው፤ የአባታቸውን ርስት ለእነርሱ አሳልፈህ ስጥ።
8 ፤ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ሰው ቢሞት ወንድ ልጅም ባይኖረው፥ ርስቱ ለሴት ልጁ ይለፍ፤
9 ፤ ሴት ልጅም ባትኖረው ርስቱን ለወንድሞቹ ስጡ፤
10 ፤ ወንድሞችም ባይኖሩት ርስቱን ለአባቱ ወንድሞች ስጡ፤
11 ፤ የአባቱም ወንድሞች ባይኖሩት ከወገኑ ለቀረበ ዘመድ ርስቱን ስጡ እርሱም ይውረሰው፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘ ለእስራኤል ልጆች ሥርዓትና ፍርድ ይሁን።
12 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደዚህ ወደ ዓባሪም ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች የሰጠኋትን ምድር እይ፤
13 ፤ ባየሃትም ጊዜ ወንድምህ አሮን እንደ ተከማቸ አንተ ደግሞ ወደ ወገንህ ትከማቻለህ።
14 ፤ እናንተ በጺን ምድረ በዳ በማኅበሩ ጠብ በቃሌ ላይ ዐምፃችኋልና፥ በእነርሱም ፊት በውኃው ዘንድ አልቀደሳችሁኝምና። ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ያለው የመሪባ ውኃ ነው።
15 ፤ ሙሴም እግዚአብሔርን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
16-17፤ የእግዚአብሔር ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን፥ በፊታቸው የሚወጣውን በፊታቸውም የሚገባውን የሚያስወጣቸውንም የሚያስገባቸውንም ሰው የሥጋ ሁሉ መንፈስ አምላክ እግዚአብሔር በማኅበሩ ላይ ይሹመው።
18 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። መንፈስ ያለበትን ሰው የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በላዩ ጫንበት፤
19 ፤ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቁመው፥ እነርሱም እያዩ እዘዘው።
20 ፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ አኑርበት።
21 ፤ በካህኑም በአልዓዛር ፊት ይቁም፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት በኡሪም ፍርድ ይጠይቅለት፤ እርሱ ከእርሱም ጋር የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በቃሉ ይውጡ፥ በቃሉም ይግቡ።
22 ፤ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቆመው፤
23 ፤ እግዚአብሔርም በሙሴ እንደ ተናገረ፥ እጁን በላዩ ጫነበት፥ አዘዘውም።

1 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። መብሌን፥ ለእኔ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የተደረገውን ቍርባኔን፥ መባዬን በየጊዜው ታቀርቡልኝ ዘንድ ጠብቁ።
3 ፤ እንዲህም በላቸው። በእሳት ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት ቍርባን ይህ ነው፤ ለዘወትር ለሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለባቸውን ሁለት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ዕለት ዕለት ታቀርባላችሁ።
4 ፤ አንዱን ጠቦት በማለዳ፥ ሌላውንም ጠቦት በማታ አቅርብ፤
5 ፤ ለእህልም ቍርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ተወቅጦ በተጠለለ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት ታቀርባለህ።
6 ፤ በእሳት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የቀረበ በሲና ተራራ የተሠራ ለዘወትር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።
7 ፤ የመጠጡ ቍርባን ለአንድ ጠቦት የኢን መስፈሪያ አራተኛው እጅ ነው፤ በመቅደሱ ውስጥ ለእግዚአብሔር ለመጠጥ ቍርባን መጠጥ ታፈስሳለህ።
8 ፤ ሌላውንም ጠቦት በማታ ጊዜ ታቀርባለህ፤ የእህሉን ቍርባንና የመጠጡን ቍርባን በማለዳ እንዳቀረብህ በእሳት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ታቀርበዋለህ።
9 ፤ በሰንበትም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ለእህልም ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት፥ የመጠጡንም ቍርባን ታቀርባላችሁ።
10 ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ፥ በየሰንበቱ ሁሉ የምታቀርቡት የሚቃጠለው መሥዋዕት ይህ ነው።
11 ፤ በወሩም መባቻ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውርም የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
12 ፤ ለእያንዳንዱም ወይፈን ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ መልካም ዱቄት፥ ለአውራው በግም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት፥
13 ፤ ለእያንዳንዱም ጠቦት ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት ታቀርባላችሁ።
14 ፤ የመጠጥ ቍርባናቸውም ለአንድ ወይፈን የኢን ግማሽ፥ ለአውራው በግም የኢን ሢሶ፥ ለአንዱም ጠቦት የኢን አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ይሆናል፤ ይህ ለዓመቱ የወር መባቻ ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።
15 ፤ ለእግዚአብሔርም ለኃጢአት መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከመጠጡ ቍርባን ሌላ ይቀርባል።
16 ፤ በመጀመሪያው ወር ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው።
17 ፤ ከዚህም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን በዓል ይሆናል ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ።
18 ፤ በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆናል፤ በእርሱም የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።
19 ፤ በእሳትም የተደረገውን ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፤ ነውር የሌለባቸው ይሁኑላችሁ።
20 ፤ የእህል ቍርባናቸውንም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለአንድ ወይፈን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራውም በግ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥
21 ፤ ለሰባቱም ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ጠቦት ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ።
22 ፤ ማስተስረያ የሚሆንላችሁን አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ።
23 ፤ ማልዶ ከሚቀርበው በዘወትር ከሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ እነዚህን ታቀርባላችሁ።
24 ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚደረገውን የቍርባኑን መብል ሰባት ቀን በየዕለቱ እንዲሁ ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከመጠጡ ቍርባን ሌላ ይቀርባል።
25 ፤ በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።
26 ፤ ደግሞ በበኵራት ቀን ከሰባቱ ሱባዔ በዓላችሁ አዲሱን የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ባቀረባችሁ ጊዜ፥ የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችኋል፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።
27 ፤ ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
28 ፤ ለእህል ቍርባናቸው በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለእያንዳንዱ ወይፈን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአንዱም አውራ በግ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥
29 ፤ ለሰባቱም ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ጠቦት ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ።
30 ፤ ማስተስረያ የሚሆንላችሁን አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ።
31 ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ሌላ እነርሱንና የመጠጥ ቍርባናቸውን ታቀርባላችሁ፤ ነውርም የሌለባቸው ይሁኑ።

1 ፤ በሰባተኛውም ወር ከወሩ በመጀመሪያ ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፤ መለከቶች የሚነፉበት ቀን ነው።
2 ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
3 ፤ ለእህል ቍርባናቸው በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለወይፈኑ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራው በግ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥
4 ፤ ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ።
5 ፤ ማስተስረያም የሚሆንላችሁን አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ።
6 ፤ በወሩ መባቻ ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ በዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ፥ እንደ ሕጋቸው ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርቡ ናቸው።
7 ፤ ከዚህም ከሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁን አስጨንቁት፤ ከሥራ ሁሉ ምንም አታድርጉ።
8 ፤ ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ ነውር የሌለባቸው ይሁኑ።
9 ፤ ለእህል ቍርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለወይፈኑ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራው በግ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥
10 ፤ ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ፥
11 ፤ ለኃጢአት መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ። ከሚያስተሰርየው ከኃጢአት መሥዋዕት፥ በዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጥ ቍርባናቸውም ሌላ አቅርቡት።
12 ፤ ከሰባተኛውም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፥ ሰባት ቀንም ለእግዚአብሔር በዓል አድርጉ።
13 ፤ ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አሥራ ሦስት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ነውር የሌለባቸውም ይሁኑ።
14 ፤ ለእህል ቍርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለአሥራ ሦስት ወይፈኖች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለሁለቱ አውራ በጎች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥
15 ፤ ለአሥራ አራቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ፥
16 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ የሚቀርቡ ናቸው።
17 ፤ በሁለተኛውም ቀን አሥራ ሁለት ወይፈኖችን፥ ሁለት አውራ በጎችን፥ ነውር የሌለባቸው አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶችን፥
18 ፤ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥
19 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየልን ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባናቸው ሌላ የሚቀርቡ ናቸው።
20 ፤ በሦስተኛውም ቀን አሥራ አንድ ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
21 ፤ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥
22 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
23 ፤ በአራተኛውም ቀን አሥር ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
24 ፤ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸውም መጠን እንደ ሕጉ፥
25 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
26 ፤ በአምስተኛውም ቀን ዘጠኝ ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
27 ፤ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥
28 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
29 ፤ በስድስተኛውም ቀን ስምንት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
30 ፤ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥
31 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
32 ፤ በሰባተኛውም ቀን ሰባት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
33 ፤ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥
34 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
35 ፤ በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።
36 ፤ ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ።
37 ፤ የእህል ቍርባናቸውና የመጠጥ ቍርባናቸው ለወይፈኑ ለአውራውም በግ ለጠቦቶቹም እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ይሆናሉ።
38 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ የሚቀርቡ ናቸው።
39 ፤ እነዚህንም፥ ከስእለታችሁና በፈቃዳችሁ ከምታመጡት ሌላ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለእህልም ለመጠጥም ቍርባን፥ ለደኅንነትም መሥዋዕታችሁ በበዓላችሁ ጊዜ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።
40 ፤ ሙሴም ለእስራኤል ልጆች እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ ነገራቸው።

1 ፤ ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ነገዶች አለቆች እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው።
2 ፤ ሰው ለእግዚአብሔር ስእለት ቢሳል፥ ወይም ራሱ በመሐላ ቢያስር፥ ቃሉን አይስበር፤ ከአፉ እንደ ወጣው ሁሉ ያድርግ።
3 ፤ ሴትም ደግሞ ለእግዚአብሔር ስእለት ብትሳል፥ እርስዋም በአባትዋ ቤት ሳለች በብላቴንነትዋ ጊዜ ራስዋን በመሐላ ብታስር፥
4 ፤ አባትዋም ራስዋን ያሰረችበትን መሐላ ስእለትዋንም ቢሰማ፥ አባትዋም ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ሁሉ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል።
5 ፤ አባትዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ ስእለትዋ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላዋ አይጸኑም፤ አባትዋ ከልክሎአታልና እግዚአብሔር ይቅር ይላታል።
6 ፤ በተሳለችም ጊዜ ራስዋንም በመሐላ ያሰረችበት ነገር ከአፍዋ በወጣ ጊዜ ባል ያገባች ብትሆን፥
7 ፤ ባልዋም ቢሰማ፥ በሰማበትም ቀን ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ይጸናል።
8 ፤ ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ በእርስዋ ላይ ያለውን ስእለትዋን ራስዋንም በመሐላ ያሰረችበትን የአፍዋን ነገር ከንቱ ያደርገዋል፤ እግዚአብሔርም ይቅር ይላታል።
9 ፤ ባልዋ የሞተባት ወይም የተፋታች ግን ስእለትዋ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ይጸኑባታል።
10 ፤ ሴትም በባልዋ ቤት ሳለች ብትሳል፥ ወይም ራስዋን በመሐላ ብታስር፥
11 ፤ ባልዋም ሰምቶ ዝም ቢላት ባይከለክላትም፥ ስእለትዋ ሁሉ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል።
12 ፤ ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ከንቱ ቢያደርገው፥ ስለ ስእለትዋ ወይም ራስዋን ስላሰረችበት መሐላ ከአፍዋ የወጣው ነገር አይጸናም፤ ባልዋ ከንቱ አድርጎታል፤ እግዚአብሔርም ይቅር ይላታል።
13 ፤ ስእለትዋን ሁሉ ነፍስዋንም የሚያዋርደውን መሐላ ሁሉ ባልዋ ያጸናዋል፥ ባልዋም ከንቱ ያደርገዋል።
14 ፤ ባልዋ ግን በየዕለቱ ዝም ቢላት፥ ስእለትዋን ሁሉ በእርስዋም ላይ ያለውን መሐላ ሁሉ አጽንቶታል፤ በሰማበት ቀን ዝም ብሎአታልና አጽንቶታል።
15 ፤ ከሰማው በኋላ ግን ከንቱ ቢያደርገው ኃጢአትዋን ይሸከማል።
16 ፤ እርስዋ በብላቴንነትዋ ጊዜ በአባትዋ ቤት ሳለች በአባትና በልጂቱ መካከል፥ ወይም በባልና በሚስት መካከል ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘው ሥርዓት ይህ ነው።

1 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ስለ እስራኤል ልጆች በቀል ምድያማውያንን ተበቀል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ወገኖችህ ትከማቻለህ።
3 ፤ ሙሴም ሕዝቡን። ከእናንተ መካከል ሰዎች ለጦርነት ይሰለፉ፤ ስለ እግዚአብሔር በቀል ምድያምን ይበቀሉ ዘንድ በምድያም ላይ ይሂዱ፤
4 ፤ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ከየነገዱ አንድ ሺህ ሰው ወደ ጦርነት ስደዱ ብሎ ተናገራቸው።
5 ፤ ከእስራኤልም አእላፋት አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ፥ ለጦርነት የተሰለፉ ሰዎች ተሰጡ።
6 ፤ ሙሴም ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ ወደ ጦርነት ሰደደ፤ እነርሱንና የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ወደ ጦርነት ሰደዳቸው፤ የመቅደሱንም ዕቃ የሚነፋውንም መለከት በእጁ ሰጠው።
7 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘ ከምድያም ጋር ተዋጉ፥ ወንዶችንም ሁሉ ገደሉ።
8 ፤ ከተገደሉትም ጋር የምድያምን ነገሥታት ገደሉአቸው፤ አምስቱም የምድያም ነገሥታት ኤዊ፥ ሮቆም፥ ሱር፥ ሑር፥ ሪባ ነበሩ፤ የቢዖርንም ልጅ በለዓምን ደግሞ በሰይፍ ገደሉት።
9 ፤ የእስራኤልም ልጆች የምድያምን ሴቶችና ልጆቻቸውን ማረኩ፤ እንስሶቻቸውንና መንጎቻቸውንም ዕቃቸውንም ሁሉ በዘበዙ።
10 ፤ የተቀመጡባቸውን ከተሞቻቸውን ሁሉ ሰፈሮቻቸውንም ሁሉ በእሳት አቃጠሉ።
11 ፤ የሰውንና የእንስሳን ምርኮና ብዝበዛ ሁሉ ወሰዱ።
12 ፤ የማረኩአቸውንም ሰዎች ምርኮውንና ብዝበዛውን ወደ ሙሴና ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር፥ በዮርዳኖስም አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ወዳለው ሰፈር አመጡ።
13 ፤ ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም የማኅበሩም አለቆች ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ ሊገናኙአቸው ወጡ።
14 ፤ ሙሴም ከዘመቻ በተመለሱት በጭፍራ አለቆች፥ በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ።
15 ፤ ሙሴም አላቸው። በውኑ ሴቶችን ሁሉ አዳናችኋቸውን?
16 ፤ እነሆ፥ እነዚህ በፌጎር ምክንያት በበለዓም ምክር እግዚአብሔርን ይበድሉ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ዕንቅፋት ሆኑ፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሠፍት ሆነ።
17 ፤ አሁን እንግዲህ ከልጆቹ ወንዱን ሁሉ ግደሉ፥ ወንድንም በመኝታ የሚያውቁትን ሴቶች ሁሉ ግደሉ።
18 ፤ ወንድን የማያውቁትን ሴቶች ልጆችን ሁሉ ግን ለራሳችሁ አድኑአቸው።
19 ፤ ከሰፈሩም ውጭ ሰባት ቀን ስፈሩ፤ ሰውን የገደለ ሁሉ የተገደለውንም የዳሰሰ ሁሉ፥ እናንተ የማረካችኋቸውም በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሰውነታችሁን ንጹሕ አድርጉ።
20 ፤ ልብስንም፥ ከቁርበትም የተዘጋጀውን ሁሉ፥ ከፍየልም ጠጕር ከእንጨትም የተሠራውን ሁሉ ንጹሕ አድርጉ።
21 ፤ ካህኑም አልዓዛር ከሰልፍ የመጡትን ሰዎች አላቸው። እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘው የሕጉ ሥርዓት ይህ ነው፤
22 ፤ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንም፥ ብረቱንም፥ ቆርቆሮውንም፥
23 ፤ አረሩንም፥ በእሳት ለማለፍ የሚችለውን ሁሉ በእሳት ታሳልፉታላችሁ፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በማንጻት ውኃ ደግሞ ይጠራል። በእሳትም ለማለፍ የማይችለውን በውኃ ታሳልፉታላችሁ።
24 ፤ በሰባተኛውም ቀን ልብሳችሁን እጠቡ፥ ንጹሕም ትሆናላችሁ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ትቀርባላችሁ።
25 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
26 ፤ አንተና ካህኑ አልዓዛር የማኅበሩም አባቶች አለቆች የተማረኩትን ሰውና እንስሳ ቍጠሩ።
27 ፤ ምርኮውንም በተዋጉትና ወደ ሰፍል በወጡት፥ በማኅበሩም ሁሉ መካከል አስተካክለህ ክፈል።
28 ፤ ከእነዚያም ከተዋጉት ወደ ሰልፍም ከወጡት ሰልፈኞች ዘንድ፥ ከሰዎችም ከበሬዎችም ከአህዮችም ከመንጎችም ከአምስት መቶ አንድ ለእግዚአብሔር ግብር አውጣ።
29 ፤ ከድርሻቸው ወስደህ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን ለካህኑ ለአልዓዛር ስጠው።
30 ፤ ከእስራኤልም ልጆች ድርሻ ከሰዎች ከበሬዎችም ከአህዮችም ከመንጎችም ከከብቶችም ሁሉ ከአምሳ አንድ ትወስዳለህ፥ የእግዚአብሔርንም ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ለሌዋውያን ትሰጣለህ።
31 ፤ ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።
32 ፤ ወደ ሰልፍ የወጡ ሰዎችም ከወሰዱት ብዝበዛ ያስቀሩት ምርኮ እንዲህ ሆነ፤ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺህ በጎች፥
33-34፤ ሰባ ሁለት ሺህ በሬዎች፥ ስድሳ አንድ ሺህ አህዮች፥
35 ፤ ወንድ ከማያውቁ ሴቶችም ሠላሳ ሁለት ሺህ ነፍስ።
36 ፤ በዘመቻም ለነበሩ ሰዎች ድርሻ የሆነ እኵሌታ ከበግ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች ነበረ፥
37 ፤ ከበጎችም የእግዚአብሔር ግብር ስድስት መቶ ሰባ አምስት ነበረ።
38 ፤ በሬዎችም ሠላሳ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ሰባ ሁለት ነበረ።
39 ፤ አህዮቹም ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ስድሳ አንድ ነበረ።
40 ፤ ሰዎቹም አሥራ ስድስት ሺህ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ሠላሳ ሁለት ነበረ።
41 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን የሆነውን ግብር ለካህኑ ለአልዓዛር ሰጠው።
42 ፤ ከእስራኤል ልጆች እኩሌታም፥ ወደ ሰልፍ ከወጡት ወንዶች ላይ ሙሴ የለየው፥
43 ፤ የማኅበሩ ድርሻ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች፥
44 ፤ ሠላሳ ስድስት ሺህ በሬዎች፥
45 ፤ ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ አህዮች፥
46 ፤ አሥራ ስድስት ሺህ ሰዎች ነበሩ።
47 ፤ ከእስራኤል ልጆች ድርሻ ሙሴ ከሰውና ከእንስሳ ከአምሳ አንድ ወሰደ፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የእግዚአብሔርን ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ሰጠ።
48 ፤ በሠራዊት አእላፋት ላይ የተሾሙት አለቆች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች፥ ወደ ሙሴ ቀረቡ፥
49 ፤ ሙሴንም። እኛ ባሪያዎችህ ወደ ሰልፍ የወጡትን ከእጃችን በታች ያሉትን ቈጠርን፥ ከእኛም አንድ አልጐደለም።
50 ፤ ሰውም ሁሉ ካገኘው ከወርቅ ዕቃ፥ ከእግር አልቦም፥ ከአምባርም፥ ከቀለበትም፥ ከጕትቻም፥ ከድሪውም ለነፍሳችን በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይልን ዘንድ ለእግዚአብሔር መባ አምጥተናል አሉት።
51 ፤ ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ወርቁንና በልዩ ልዩ የተሠራውን ዕቃ ሁሉ ከእጃቸው ተቀበሉ።
52 ፤ ሻለቆችም የመቶ አለቆችም ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን ያቀረቡት ወርቅ ሁሉ አሥራ ስድስት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ሰቅል ነበረ።
53 ፤ ወደ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ሁሉ ከምርኮአቸው ለራሳቸው ወሰዱ።
54 ፤ ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ወርቁን ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ወስደው በእግዚአብሔር ፊት ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ወደ መገናኛው ድንኳን አገቡት።

1 ፤ የሮቤልና የጋድ ልጆችም እጅግ ብዙ እንስሶች ነበሩአቸው፤ እነሆም፥ የኢያዜር ምድርና የገለዓድ ምድር ለእንስሶች የተመቸ ስፍራ እንደ ነበረ ባዩ ጊዜ፥
2 ፤ የጋድና የሮቤል ልጆች መጥተው ሙሴንና ካህኑን አልዓዛርን የማኅበሩንም አለቆች እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው።
3-4፤ እግዚአብሔር በእስራኤል ማኅበር ፊት የመታው ምድር፥ አጣሮት፥ ዲቦን፥ ኢያዜር፥ ነምራ፥ ሐሴቦን፥ ኤልያሊ፥ ሴባማ፥ ናባው፥ ባያን፥ ለእንስሶች የተመቸ ምድር ነው፤ ለእኛም ለባሪያዎችህ እንስሶች አሉን።
5 ፤ እኛስ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝተን እንደ ሆነ ይህን ምድር ለባሪያዎችህ ርስት አድርገህ ስጠን፤ ወደ ዮርዳኖስም ማዶ አታሻግረን።
6 ፤ ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች አላቸው። ወንድሞቻችሁ ወደ ጦርነት ሲሄዱ እናንተ በዚህ ትቀመጣላችሁን?
7 ፤ እግዚአብሔር ወደሚሰጣቸው ምድር እንዳይሻገሩ የእስራኤልን ልጆች ልብ ለምን ታደክማላችሁ?
8 ፤ ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ ከቃዴስ በርኔ በሰደድኋቸው ጊዜ አባቶቻችሁ እንዲህ አደረጉ።
9 ፤ ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ በሄዱ ጊዜ፥ ምድሪቱንም ባዩ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ የእስራኤልን ልጆች ልብ አደከሙ።
10 ፤ በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ቍጣ ነደደ፥
11-12፤ እርሱም። በእውነት እግዚአብሔርን ፈጽመው ከተከተሉ ከእነዚህ ከቄኔዛዊው ከዮፎኔ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር፥ ከግብፅ የወጡት ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት ሰዎች እኔን ፈጽመው አልተከተሉምና ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጥ ዘንድ የማልሁበትን ምድር አያዩም ብሎ ማለ።
13 ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ጸና፥ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ያደረገ ትውልድ ሁሉ እስኪጠፋ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ ውስጥ አቅበዘበዛቸው።
14 ፤ እነሆም፥ የእግዚአብሔርን መዓት በእስራኤል ላይ አብዝታችሁ ትጨምሩ ዘንድ እናንተ የኃጢአተኞች ትውልድ በአባቶቻችሁ ፋንታ ቆማችኋል።
15 ፤ እርሱን ከመከተል ብትመለሱ እርሱ ሕዝቡን በምድረ በዳ ደግሞ ይተዋል፤ ይህንንም ሕዝብ ሁሉ ታጠፋላችሁ።
16 ፤ ወደ እርሱም ቀርበው አሉት። በዚህ ለእንስሶቻችን በረቶች ለልጆቻችንም ከተሞች እንሠራለን፤
17 ፤ እኛ ግን ለጦርነት ተዘጋጅተን ወደ ስፍራቸው እስክናገባቸው ድረስ በእስራኤል ልጆች ፊት እንሄዳለን፤ በዚህም ምድር ስላሉ ሰዎች ልጆቻችን በተመሸጉ ከተሞች ይቀመጣሉ።
18 ፤ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ርስታቸውን እስኪወርሱ ድረስ ወደ ቤቶቻችን አንመለስም፤
19 ፤ ከዮርዳኖስ ወዲህ ወደ ምሥራቅ ርስታችን ደርሶናልና እኛ ከዮርዳኖስ ማዶ ወደዚያ ከእነርሱ ጋር ርስት አንወርስም።
20 ፤ ሙሴም አላቸው። ይህንስ ነገር ብታደርጉ፥ ተዘጋጅታችሁም በእግዚአብሔር ፊት ወደ ሰልፍ ብትሄዱ፥
21 ፤ እርሱም ጠላቶቹን ከፊቱ እስኪያሳድድ ድረስ ምድሪቱም በእግዚአብሔር ፊት ድል እስክትሆን ድረስ ከእናንተ ሰው ሁሉ ጋሻ ጦሩን ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገር፥
22 ፤ ከዚያ በኋላ ትመለሳላችሁ፥ በእግዚአብሔርም ፊት በእስራኤል ዘንድ ንጹሐን ትሆናላችሁ፤ ይህች ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ርስት ትሆንላችኋለች።
23 ፤ እናንተ ግን እንዲህ ባታደርጉ፥ እነሆ፥ እግዚአብሔርን ትበድላላችሁ፤ ኃጢአታችሁም እንዲያገኛችሁ እወቁ።
24 ፤ ለልጆቻችሁ ከተሞች፥ ለበጎቻችሁም በረቶች ሥሩ፤ ከአፋችሁም የወጣውን ነገር አድርጉ።
25 ፤ የጋድና የሮቤልም ልጆች ሙሴን እንዲህ ብለው ተናገሩት። እኛ ባሪያዎችህ ጌታችን እንዳዘዘ እናደርጋለን።
26 ፤ ልጆቻችን፥ ሚስቶቻችንም፥ መንጎቻችንም፥ እንስሶቻችንም ሁሉ በዚያ በገለዓድ ከተሞች ይሆናሉ፤
27 ፤ እኛ ባሪያዎችህ ግን ሁላችን ጋሻ ጦራችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ጌታችን እንደ ተናገረ ወደ ጦርነት እንሄዳለን።
28 ፤ ሙሴም ካህኑን አልዓዛርን የነዌንም ልጅ ኢያሱን የእስራኤልንም ልጆች ነገድ አለቆች ስለ እነርሱ አዘዘ።
29 ፤ ሙሴም። የጋድና የሮቤል ልጆች ሁላቸው ጋሻ ጦራቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገሩ፥ ምድሪቱንም ድል ብትነሡ፥ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ትሰጡአቸዋላችሁ።
30 ፤ ጋሻ ጦራቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር ባይሻገሩ ግን በከነዓን ምድር በእናንተ መካከል ርስታቸውን ይወርሳሉ አላቸው።
31 ፤ የጋድና የሮቤልም ልጆች መልሰው። እግዚአብሔር ለእኛ ለባሪያዎችህ እንደ ተናገረ እንዲሁ እናደርጋለን።
32 ፤ ጋሻ ጦራችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ወደ ከነዓን ምድር እንሻገራለን፥ ከዮርዳኖስም ማዶ ከወዲሁ የወረስነው ርስት ይሆንልናል አሉት።
33 ፤ ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች ለዮሴፍም ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ፥ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ግዛት፥ ምድሪቱንና በዙሪያዋ ያሉትን ከተሞች ሰጣቸው።
34 ፤ የጋድም ልጆች ዲቦንን፥ አጣሮትን፥ አሮዔርን፥
35 ፤ ዓጥሮትሽፋንን፥ ኢያዜርን፥ ዮግብሃን፥
36 ፤ ቤትነምራን፥ ቤትሃራንን የተመሸጉ ከተሞች አድርገው ሠሩ፤ የበጎች በረቶችንም ሠሩ።
37 ፤ የሮቤልም ልጆች ሐሴቦንን፥ ኤልያሊን፥
38 ፤ ቂርያታይምን፥ ስማቸውም የተለወጠውን ናባውን፥ በኣልሜዎንን፥ ሴባማን ሠሩ፤ እነዚህንም የሠሩአቸውን ከተሞች በሌላ ስም ጠሩአቸው።
39 ፤ የምናሴም ልጅ የማኪር ልጆች ወደ ገለዓድ ሄዱ፥ ወሰዱአትም፥ በእርስዋም የነበሩትን አሞራውያንን አሳደዱ።
40 ፤ ሙሴም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ገለዓድን ሰጠ፤ በእርስዋም ተቀመጠ።
41 ፤ የምናሴም ልጅ ኢያዕር ሄዶ መንደሮችዋን ወሰደ፥ የኢያዕርም መንደሮች ብሎ ጠራቸው።
42 ፤ ኖባህም ሄደ ቄናትንም መንደሮችዋንም ወሰደ፥ በስሙም ኖባህ ብሎ ጠራቸው።

1 ፤ የእስራኤልም ልጆች ጕዞ ከሙሴና ከአሮን እጅ በታች በጭፍሮቻቸው ከግብፅ በወጡ ጊዜ እንዲህ ነበረ።
2 ፤ ሙሴም በእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደ ጕዞአቸው አወጣጣቸውን ጻፈ፤ እንደ አወጣጣቸውም ጕዞአቸው እንዲህ ነበረ።
3 ፤ በመጀመሪያው ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን ከራምሴ ተጓዙ፤ ከፋሲካ በኋላ በነጋው የእስራኤል ልጆች ግብፃውያን ሁሉ እያዩ ከፍ ባለች እጅ ወጡ።
4 ፤ በዚያም ጊዜ ግብፃውያን እግዚአብሔር የገደላቸውን በኵሮቻቸውን ይቀብሩ ነበር፤ በአማልክቶቻቸውም ደግሞ እግዚአብሔር ፈረደባቸው።
5 ፤ የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተጕዘው በሱኮት ሰፈሩ።
6 ፤ ከሱኮትም ተጕዘው በምድረ በዳ ዳርቻ ባለች በኤታም ሰፈሩ።
7 ፤ ከኤታምም ተጕዘው በበኣልዛፎን ፊት ወደ ነበረች ወደ ፊሀሒሮት ተመለሱ፤ በሚግዶልም ፊት ለፊት ሰፈሩ።
8 ፤ ከፊሀሒሮትም ተጕዘው በባሕሩ ውስጥ ወደ ምድረ በዳ አለፉ፤ በኤታምም በረሀ የሦስት ቀን መንገድ ሄደው በማራ ሰፈሩ።
9 ፤ ከማራም ተጕዘው ወደ ኤሊም መጡ፤ በኤሊምም አሥራ ሁለት የውኃ ምንጮች ሰባ ዘንባቦችም ነበሩ፤ በዚያም ሰፈሩ።
10 ፤ ከኤሊምም ተጕዘው በኤርትራ ባሕር ዳር ሰፈሩ።
11 ፤ ከኤርትራም ባሕር ተጕዘው በሲን ምድረ በዳ ሰፈሩ።
12 ፤ ከሲን ምድረ በዳም ተጕዘው በራፋቃ ሰፈሩ።
13 ፤ ከራፋቃም ተጕዘው በኤሉስ ሰፈሩ።
14 ፤ ከኤሉስም ተጕዘው በራፊዲም ሰፈሩ፤ በዚያም ሕዝቡ የሚጠጡት ውኃ አልነበረም።
15 ፤ ከራፊዲምም ተጕዘው በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ።
16 ፤ ከሲናም ምድረ በዳ ተጕዘው በምኞት መቃብር ሰፈሩ።
17 ፤ ከምኞት መቃብርም ተጕዘው በሐጼሮት ሰፈሩ።
18 ፤ ከሐጼሮትም ተጕዘው በሪትማ ሰፈሩ።
19 ፤ ከሪትማም ተጕዘው በሬሞን ዘፋሬስ ሰፈሩ።
20 ፤ ከሬሞን ዘፋሬስም ተጕዘው በልብና ሰፈሩ።
21 ፤ ከልብናም ተጕዘው በሪሳ ሰፈሩ።
22 ፤ ከሪሳም ተጕዘው በቀሄላታ ሰፈሩ።
23 ፤ ከቀሄላታም ተጕዘው በሻፍር ተራራ ሰፈሩ።
24 ፤ ከሻፍር ተራራም ተጕዘው በሐራዳ ሰፈሩ።
25 ፤ ከሐራዳም ተጕዘው በመቅሄሎት ሰፈሩ።
26 ፤ ከመቅሄሎትም ተጕዘው በታሐት ሰፈሩ።
27 ፤ ከታሐትም ተጕዘው በታራ ሰፈሩ።
28 ፤ ከታራም ተጕዘው በሚትቃ ሰፈሩ።
29 ፤ ከሚትቃም ተጕዘው በሐሽሞና ሰፈሩ።
30 ፤ ከሐሽሞናም ተጕዘው በሞሴሮት ሰፈሩ።
31 ፤ ከሞሴሮትም ተጕዘው በብኔያዕቃን ሰፈሩ።
32 ፤ ከብኔያዕቃንም ተጕዘው በሖርሃጊድጋድ ሰፈሩ።
33 ፤ ከሖርሃጊድጋድም ተጕዘው በዮጥባታ ሰፈሩ።
34 ፤ ከዮጥባታም ተጕዘው በዔብሮና ሰፈሩ።
35 ፤ ከዔብሮናም ተጕዘው በዔጽዮንጋብር ሰፈሩ።
36 ፤ ከዔጽዮንጋብርም ተጕዘው በጺን ምድረ በዳ ሰፈሩ፤ ይህችም ቃዴስ ናት።
37 ፤ ከቃዴስም ተጕዘው በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ ሰፈሩ።
38 ፤ ካህኑም አሮን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ሖር ተራራ ላይ ወጣ፥ በዚያም የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በአርባኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ሞተ።
39 ፤ አሮንም በሖር ተራራ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሀያ ሦስት ዓመት ነበር።
40 ፤ በከነዓን ምድርም በደቡብ በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ የእስራኤል ልጆች እንደ መጡ ሰማ።
41 ፤ እነርሱም ከሖር ተራራ ተጕዘው በሴልሞና ሰፈሩ።
42 ፤ ከሴልሞናም ተጕዘው በፉኖን ሰፈሩ።
43 ፤ ከፉኖንም ተጕዘው በኦቦት ሰፈሩ።
44 ፤ ከኦቦትም ተጕዘው በሞዓብ ዳርቻ ባለው በጋይ ሰፈሩ።
45 ፤ ከጋይም ተጕዘው በዲቦንጋድ ሰፈሩ።
46 ፤ ከዲቦንጋድም ተጕዘው በዓልሞንዲብላታይም ሰፈሩ።
47 ፤ ከዓልሞንዲብላታይምም ተጕዘው በናባው ፊት ባሉ በዓብሪም ተራሮች ላይ ሰፈሩ።
48 ፤ ከዓብሪምም ተራሮች ተጕዘው በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ባለው በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፈሩ።
49 ፤ በዮርዳኖስም አጠገብ በሞዓብ ሜዳ ላይ ከቤትየሺሞት እስከ አቤልሰጢም ድረስ ሰፈሩ።
50 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው።
51 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥
52 ፤ የአገሩን ሰዎች ሁሉ ከፊታችሁ ታሳድዳላችሁ፥ የተቀረጹትንም ድንጋዮቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ በኮረብታ ላይ ያሉትን መስገጃዎቻቸውንም ታፈርሳላችሁ፤
53 ፤ ምድሪቱንም ለእናንተ ርስት አድርጌ ሰጥቼአችኋለሁና ምድሪቱን ትወርሱአታላችሁ ትቀመጡባታላችሁም።
54 ፤ ምድሪቱንም በየወገኖቻችሁ በዕጣ ትወርሳላችሁ፤ ለብዙዎች እንደ ብዛታቸው ለጥቂቶቹም እንደ ጥቂትነታቸው መጠን ርስትን ትሰጣላችሁ፤ እያዳንዱ ሁሉ ዕጣ እንደ ወደቀለት በዚያ ርስቱ ይሆናል፤ በየአባቶቻችሁ ነገዶች ትወርሳላችሁ።
55 ፤ የአገሩንም ሰዎች ከፊታችሁ ባታሳድዱ፥ ያስቀራችኋቸው ለዓይናችሁ እንደ እሾህ ለጎናችሁም እንደሚወጋ ነገር ይሆኑባችኋል፥ በምትቀመጡባትም ምድር ያስጨንቁአችኋል።
56 ፤ እኔም በእነርሱ አደርገው ዘንድ ያሰብሁትን በእናንተ አደርግባችኋለሁ።

1 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ ርስት ትሆናችሁ ዘንድ በዕጣ የምትደርሳችሁ ምድር፥ በዳርቻዋ ያለች የከነዓን ምድር፥
3 ፤ ይህች ናት፤ የደቡቡ ወገን ከጺን ምድረ በዳ በኤዶምያስ በኩል ይሆናል፤ የደቡቡም ዳርቻ ከጨው ባሕር ዳር በምሥራቅ በኩል ይጀምራል፤
4 ፤ ዳርቻችሁም በአቅረቢም ዐቀበት በደቡብ በኩል ይዞራል ወደ ጺንም ያልፋል፤ መውጫውም በቃዴስ በርኔ በደቡብ በኩል ይሆናል፤ ወደ ሐጸርአዳር ይሄዳል ወደ ዓጽሞንም ያልፋል፤
5 ፤ ዳርቻውም ከዓጽሞን ወደ ግብፅ ወንዝ ይዞራል፥ መውጫውም በባሕሩ በኩል ይሆናል።
6 ፤ ለምዕራብም ዳርቻ ታላቁ ባሕር ዳርቻችሁ ይሆናል፤ ይህ የምዕራብ ዳርቻችሁ ይሆናል።
7 ፤ የሰሜንም ዳርቻችሁ ይህ ይሆናል፤ ከታላቁ ባሕር ወደ ሖር ተራራ ምልክት ታመለክታላችሁ፤
8 ፤ ከሖርም ተራራ ወደ ሐማት መግቢያ ምልክት ታመለክታላችሁ የዳርቻውም መውጫ በጽዳድ ይሆናል፤
9 ፤ ዳርቻውም ወደ ዚፍሮን ያልፋል እስከ ሐጸርዔናንም ድረስ ይወጣል፤ ይህ የሰሜን ዳርቻችሁ ይሆናል።
10 ፤ የምሥራቁንም ዳርቻችሁን ከሐጸርዔናን ወደ ሴፋማ ምልክት ታመለክታላችሁ፤
11 ፤ ዳርቻውም ከሴፋማ በዓይን ምሥራቅ ወዳለው ወደ ሪብላ ይወርዳል፤ እስከ ኪኔሬት የባሕር ወሽመጥ በምሥራቅ በኩል ይደርሳል፤
12 ፤ ዳርቻውም ወደ ዮርዳኖስ ይወርዳል፥ መውጫውም በጨው ባሕር ይሆናል። ምድራችሁ እንደ ዳርቻዋ በዙሪያዋ ይህች ናት።
13 ፤ ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው። እግዚአብሔር ለዘጠኝ ነገድ ተኩል ይሰጡአቸው ዘንድ ያዘዘ በዕጣ የምትወርሱአት ምድር ይህች ናት፤
14 ፤ የሮቤልም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የጋድም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን ወርሰዋል።
15 ፤ እነዚህ ሁለቱ ነገድና የአንዱ ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን በዮርዳኖስ ማዶ በኢያሪኮ አንጻር በምሥራቅ በኩል ወረሱ።
16 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
17 ፤ ምድሪቱን ርስት አድርገው የሚከፍሉላችሁ ሰዎች ስማቸው ይህ ነው፤ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ።
18 ፤ ምድሪቱንም ርስት አድርገው ይከፍሉ ዘንድ ከየነገዱ አንድ አንድ አለቃ ትወስዳላችሁ።
19 ፤ የሰዎቹም ስም ይህ ነው፤ ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፥
20 ፤ ከስምዖን ልጆች ነገድ የዓሚሁድ ልጅ ሰላሚኤል፥
21 ፤ ከብንያም ነገድ የኪስሎን ልጅ ኤልዳድ፥
22 ፤ ከዳን ልጆች ንገድ አንድ አለቃ የዮግሊ ልጅ ቡቂ፥
23 ፤ ከዮሴፍም ልጆች ከምናሴ ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሱፊድ ልጅ አኒኤል፥
24 ፤ ከኤፍሬም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሺፍጣን ልጅ ቀሙኤል፥
25 ፤ ከዛብሎን ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የፈርናክ ልጅ ኤሊሳፈን፥
26 ፤ ከይሳኮር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሖዛ ልጅ ፈልጢኤል፥
27 ፤ ከአሴር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሴሌሚ ልጅ አሒሁድ፥
28 ፤ ከንፍታሌም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ፈዳሄል።
29 ፤ እግዚአብሔር በከነዓን ምድር ለእስራኤል ልጆች ርስታቸውን ይከፍሉ ዘንድ ያዘዛቸው እነዚህ ናቸው።

1 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ሜዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ሌዋውያን የሚቀመጡባቸውን ከተሞች ከርስታቸው ይሰጡ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው፤ በከተሞቹም ዙሪያ ያለውን መሰምርያ ለሌዋውያን ስጡ።
3 ፤ እነርሱም በከተሞቹ ውስጥ ይቀመጣሉ፤ መሰምርያቸውም ለከብቶቻቸው ለእንስሶቻቸውም ለእነርሱም ላለው ሁሉ ይሁን።
4 ፤ ለሌዋውያንም የምትሰጡት የከተማ መሰምርያ በከተማው ዙሪያ ከቅጥሩ ወደ ውጭ አንድ ሺህ ክንድ ይሁን።
5 ፤ ከከተማው ውጭ በምሥራቅ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በደቡብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በምዕራብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በሰሜንም በኩል ሁለት ሺህ ክንድ ትከነዳላችሁ፥ ከተማውም በመካከል ይሆናል፤ ይህም የከተሞቹ መሰምርያ ይሆንላቸዋል።
6 ፤ ለሌዋውያንም የምትሰጡአቸው ስድስቱ የመማፀኛ ከተሞች ናቸው፤ እነርሱም ነፍሰ ገዳይ ይሸሽባቸው ዘንድ የምትሰጡአቸው ናቸው፤ ከእነዚህም ሌላ አርባ ሁለት ከተሞች ትሰጣላችሁ።
7 ፤ ለሌዋውያን የምትሰጡአቸው ከተሞች ሁሉ አርባ ስምንት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከመሰምርያቸው ጋር ትሰጡአቸዋላችሁ።
8 ፤ ከእስራኤል ልጆች ርስት ለሌዋውያን የምትሰጡአቸውን ከተሞች እንዲሁ ስጡ፤ ከብዙዎቹ ብዙ፥ ከጥቂቶቹ ጥቂት ትወስዳላችሁ፤ እያንዳንዱ እንደ ወረሱት እንደ ርስታቸው መጠን ከከተሞቻቸው ለሌዋውያን ይሰጣሉ።
9 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
10 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥
11 ፤ በስሕተት ነፍስ የገደለ ወደዚያ ይሸሽ ዘንድ የመማፀኛ ከተሞች እንዲሆኑላችሁ ከተሞችን ለእናንት ለዩ።
12 ፤ ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ እንዳይሞት፥ ከተሞቹም ከደም ተበቃይ የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ።
13 ፤ የምትሰጡአቸውም ስድስቱ ከተሞች የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ።
14 ፤ በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፥ በከነዓንም ምድር ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፤ የመማፀኛ ከተሞች ይሆናሉ።
15 ፤ በስሕተት ነፍስ የገደለ ይሸሽበት ዘንድ እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸው ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች መማፀኛ ይሆናሉ።
16 ፤ በብረት መሣርያ እስኪሞት ድረስ ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል።
17 ፤ ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው ድንጋይ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል።
18 ፤ ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው በእንጨት መሣርያ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል።
19 ፤ ደም ተበቃዩ ራሱ ነፍሰ ገዳዩን ይግደል፤ ባገኘው ጊዜ ይግደለው።
20 ፤ እስኪሞት ድረስ በጥላቻ ቢደፋው፥ ወይም ሸምቆ አንዳች ነገር ቢጥልበት፥
21 ፤ ወይም በጥላቻ እስኪሞት ድረስ በእጁ ቢመታው፥ የመታው ፈጽሞ ይገደል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ደም ተበቃዩ ባገኘው ጊዜ ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው።
22 ፤ ነገር ግን ያለ ጥላቻ ድንገት ቢደፋው፥ ሳይሸምቅም አንዳች ነገር ቢጥልበት፥
23 ፤ ወይም ሳያየው እስኪሞት ድረስ ሰው የሚሞትበትን ድንጋይ ቢጥልበት፥ ጠላቱም ባይሆን፥ ክፉም ያደርግበት ዘንድ ባይሻ፥
24 ፤ ማኅበሩ በመቺውና በደም ተባቃዩ መካከል ፍርድን እንደዚሁ ይፍረድ፤
25 ፤ ማኅበሩም ነፍሰ ገዳዩን ከደም ተበቃዩ እጅ ያድነዋል፥ ማኅበሩም ወደ ሸሸበት ወደ መማፀኛ ከተማ ይመልሰዋል፤ በቅዱስ ዘይትም የተቀባው ዋነኛው ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቀመጣል።
26 ፤ ነፍሰ ገዳዩ ግን ከሸሸበት ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ቢወጣ፥
27 ፤ ደም ተበቃዩም ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ውጭ ቢያገኘው፥ ደም ተበቃዩም ነፍሰ ገዳዩን ቢገድለው፥ የደም ዕዳ አይሆንበትም፤
28 ፤ ዋነኛው ካህን እስኪሞት ድረሰ በመማፀኛው ከተማ ውስጥ መቀመጥ ይገባው ነበርና። ዋነኛው ካህን ከሞተ በኋላ ግን ነፍሰ ገዳዩ ወደ ርስቱ ምድር ይመለሳል።
29 ፤ እነዚህም ነገሮች ለልጅ ልጃችሁ በማደሪያችሁ ሁሉ ሥርዓትና ፍርድ ይሁኑላችሁ።
30 ፤ ነፍሰ ገዳይ ሁሉ በምስክሮች አፍ ይገደላል፤ በአንድ ምስክር ግን ማናቸውንም ሰው መግደል አይገባም።
31 ፤ ሞት የተፈረደበትን ነፍሰ ገዳዩንም ለማዳን የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፤ እርሱ ፈጽሞ ይገደል።
32 ፤ ዋነኛው ካህን ሳይሞት ወደ ምድሩ ይመለስ ዘንድ ወደ መማፀኛው ከተማ ከሸሸው የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ።
33 ፤ ደም ምድሪቱን ያረክሳታልና የምትኖሩባትን ምድር አታርክሱአት፤ በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነ በቀር ምድሪቱ ከፈሰሰባት ደም አትነጻም።
34 ፤ እኔ እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁና የምትኖሩባትን በመካከልዋም የማድርባትን ምድር አታርክሱአት።

1 ፤ ከዮሴፍ ልጆች ወገኖች የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጆች ወገን አለቆች ቀረቡ፥ በሙሴና በእስራኤልም ልጆች አባቶች አለቆች ፊት ተናገሩ፤
2 ፤ አሉም። ምድሪቱን ለእስራኤል ልጆች ርስት አድርገህ በዕጣ ከፍለህ ትሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር አንተን ጌታችንን አዘዘህ፤ እግዚአብሔርም የወንድማችንን የሰለጰዓድን ርስት ለሴቶች ልጆቹ ትሰጥ ዘንድ አንተን ጌታችንን አዘዘ።
3 ፤ ከሌላም ከእስራኤል ልጆች ነገድ ባል ቢያገቡ፥ ርስታቸው ከአባቶቻችን ርስት ይነቀላል፥ እነርሱም ለሚሆኑበት ለሌላው ነገድ ርስት ይጨመራል፤ እንደዚህም የርስታችን ዕጣ ይጐድላል።
4 ፤ ለእስራኤልም ልጆች ኢዮቤልዩ በመጣ ጊዜ ርስታቸው ለሚሆኑበት ነገድ ርስት ይጨመራል፤ እንደዚህም ርስታቸው ከአባቶቻችን ነገድ ርስት ይጐድላል።
5 ፤ ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንደ እግዚአብሔር ቃል እንዲህ ብሎ አዘዛቸው። የዮሴፍ ልጆች ነገድ በእውነት ተናገሩ።
6 ፤ እግዚአብሔር ስለ ሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ የወደዱትን ያግቡ፤ ነገር ግን ከአባታቸው ነገድ ብቻ ያግቡ።
7 ፤ እንደዚህም የእስራኤል ልጆች ርስት ከነገድ ወደ ነገድ ምንም አይተላለፍ፤ ከእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ወደ አባቶቹ ነገድ ርስት ይጠጋ።
8 ፤ ከእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ሰው የአባቶቹን ርስት ይወርስ ዘንድ፥ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ ርስት ያላት ሴት ልጅ ሁሉ ከአባትዋ ነገድ ባል ታግባ።
9 ፤ እንደዚህም ከአንድ ነገድ ወደ ሌላ ነገድ ምንም ርስት አይተላለፍ ከእስራኤልም ልጆች ነገድ እያንዳንዱ ወደ ርስቱ ይጠጋ።
10 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች አደረጉ።
11 ፤ የሰለጰዓድ ልጆች ማህለህ፥ ቲርጻ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ኑዓ ከአባታቸው ወንድሞች ልጆች ጋር ተጋቡ።
12 ፤ ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ልጆች ወገኖች ባሎቻቸውን አገቡ፥ ርስታቸውም በአባታቸው ነገድ ጸና።
13 ፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ የእስራኤልን ልጆች በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ሜዳ ያዘዛቸው ትእዛዝና ፍርድ እነዚህ ናቸው።

Latest News

ilovejesus1.com

My name is Eden Fessehaye and i build ilovejesus1.com website for everyone to have access to the bible and audio bible as well.  There is Amharic, Tigrigna and English bible.  Also, the English bible can be translated to any languages for everyone to have access to...

Trust in Christ and receive Him as your Savior.

Christ is ready. “Here I am! I stand at the door and knock. If anyone hears my voice and opens the door, I will go in” (Revelation 3:20). Receive him now. “Yet to all who received him, to those who believed in his name, he gave the right to become children of God”...

You must repent and ask God for forgiveness.

“He who conceals his sins does not prosper, but whoever confesses and renounces them finds mercy” (Proverbs 28:13).  Forgiveness is promised. “If we confess our sins, he is faithful and just and will forgive us our sins and purify us from all unrighteousness” (1 John...

Jesus Christ died and rose again for our sins.

Jesus Christ died in our place. “But God demonstrates his own love for us in this: While we were still sinners, Christ died for us” (Romans 5:8). He is the way to new life. “Therefore, if anyone is in Christ, he is a new creation; the old has gone, the new has come!”...

Sin separates you from God

Everyone has sinned. “For all have sinned and fall short of the glory of God” (Romans 3:23). Sin brings death. “For the wages of sin is death” (Romans 6:23). “For it is by grace you have been saved, through faith and this not from yourselves, it is the gift of God-not...

Recognize that God loves you

“For God so loved the world that he gave his one and only Son, that whoever believes in him shall not perish but have eternal life” (John 3:16). He has new life for you. “I have come that they may have life, and have it to the full” (John 10:10).

The light of Jesus

Then Jesus again spoke to them, saying, “I am the Light of the world; he who follows Me will not walk in the darkness, but will have the Light of life.” (John 8:12, NASB) While I am in the world, I am the Light of the world.”...

Second Coming of Christ

Revelation 7:14 - “...they are the people who are coming out safely through the terrible tribulation. The blood of the Lamb has washed and made white their robes.” Revelation 19:7 - “They will be Christ's bride and will have...

ilovejesus1.com

My name is Eden Fessehaye and i build ilovejesus1.com website for everyone to have access to the bible and audio bible as well.  There is Amharic, Tigrigna and English bible.  Also, the English bible can be translated to any languages for everyone to have access to...

Trust in Christ and receive Him as your Savior.

Christ is ready. “Here I am! I stand at the door and knock. If anyone hears my voice and opens the door, I will go in” (Revelation 3:20). Receive him now. “Yet to all who received him, to those who believed in his name, he gave the right to become children of God”...

You must repent and ask God for forgiveness.

“He who conceals his sins does not prosper, but whoever confesses and renounces them finds mercy” (Proverbs 28:13).  Forgiveness is promised. “If we confess our sins, he is faithful and just and will forgive us our sins and purify us from all unrighteousness” (1 John...