መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 2 (kings 2)

እሱ ተከታታይ ጅማሬዎችን ያሳያል – የዓለም መጀመሪያ ፣ የሰው ልጅ እና እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የገባውን ቃል ኪዳን። የመጀመሪያው መጽሐፍ ዘፍጥረት በእግዚአብሔር ዓለም ፍጥረት ተከፈተ። የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ባለመታዘዙ የሰው ልጅ ብዛት ወደ ተለያዩ ብሔሮች እና ቋንቋዎች ሲከፋፈል ፍጹምው ዓለም በክፋት ውስጥ ይወድቃል።

መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ያንብቡ

መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 2 (kings 2)

1 ፤ አክዓብም ከሞተ በኋላ ሞዓብ በእስራኤል ላይ ዐመፀ።
2 ፤ አካዝያስም በሰማርያ በሰገነቱ ላይ ሳለ ከዓይነ ርግቡ ወድቆ ታመመ፤ እርሱም። ሂዱ ከዚህም ደዌ እድን እንደ ሆነ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ጠይቁ ብሎ መልእክተኞችን ላከ።
3 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ቴስብያዊውን ኤልያስን። ተነሣ፥ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣና። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቁ ዘንድ የምትሄዱት በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን?
4 ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም በላቸው አለው። ኤልያስም ሄደ።
5 ፤ መልእክተኞችም ወደ አካዝያስ ተመለሱ፥ እርሱም። ለምን ተመለሳችሁ? አላቸው።
6 ፤ እነርሱም። አንድ ሰው ሊገናኘን መጣና። ሂዱ፥ ወደ ላካችሁም ንጉሥ ተመልሳችሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቅ ዘንድ የላከህ በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን? ስለዚህ ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም በሉት አለን አሉት።
7 ፤ እርሱም። ሊገናኛችሁ የወጣው፥ ይህንስ ቃል የነገራችሁ ሰው መልኩ ምን ይመስላል? አላቸው።
8 ፤ እነርሱም። ሰውዮው ጠጕራም ነው፥ በወገቡም ጠፍር ታጥቆ ነበር አሉት። እርሱም። ቴስብያዊው ኤልያስ ነው አለ።
9 ፤ ንጉሡም የአምሳ አለቃውን ከአምሳ ሰዎች ጋር ሰደደ፥ ወደ እርሱም ወጣ፤ እነሆም፥ በተራራ ራስ ላይ ተቀምጦ ነበር። እርሱም። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ንጉሡ። ውረድ ይልሃል አለው።
10 ፤ ኤልያስም መልሶ የአምሳ አለቃውን። እኔስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንሁ እሳት ከሰማይ ትውረድ፥ አንተንም፥ አምሳውንም ሰዎችህን ትብላ አለው። እሳትም ከሰማይ ወርዳ እርሱንና አምሳውን ሰዎቹን በላች።
11 ፤ ደግሞም ሌላ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎች ጋር ላከበት፤ እርሱም። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ንጉሡ። ፈጥነህ ውረድ ይላል ብሎ ተናገረ።
12 ፤ ኤልያስም። እኔስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንሁ እሳት ከሰማይ ትውረድ፥ አንተንም አምሳውንም ሰዎችህን ትብላ አለው። የእግዚአብሔርም እሳት ከሰማይ ወርዳ እርሱንና አምሳውን ሰዎቹን በላች።
13 ፤ ደግሞም ሦስተኛ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎች ጋር ሰደደ፤ ሦስተኛውም የአምሳ አለቃ ወጥቶ በኤልያስ ፊት በጕልበቱ ተንበረከከና። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ነፍሴና የእነዚህ የአምሳው ባሪያዎችህ ነፍስ በፊትህ የከበረች ትሁን።
14 ፤ እነሆ፥ እሳት ከሰማይ ወርዳ የፊተኞቹን ሁለቱን የአምሳ አለቆችና አምሳ አምሳውን ሰዎቻቸውን በላች፤ አሁን ግን ነፍሴ በፊትህ የከበረች ትሁን ብሎ ለመነው።
15 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ኤልያስን። ከእርሱ ጋር ውረድ፥ አትፍራውም አለው። ተነሥቶም ከእርሱ ጋር ወደ ንጉሡ ወረደ።
16 ፤ ኤልያስም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቅ ዘንድ መልእክተኞችን ልከሃልና ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም አለው።
17 ፤ ኤልያስም እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ሞተ። ልጅም አልነበረውምና በይሁዳ ንጉሥ በኢዮሣፍጥ ልጅ በኢዮራም በሁለተኛው ዓመት ወንድሙ ኢዮራም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
18 ፤ አካዝያስ ያደረገው የቀረው ነገር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?

1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ሊያወጣው በወደደ ጊዜ ኤልያስ ከኤልሳዕ ጋር ከጌልገላ ተነሣ።
2 ፤ ኤልያስም ኤልሳዕን። እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ልኮኛልና በዚህ ቆይ አለው። ኤልሳዕም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ። ወደ ቤቴልም ወረዱ።
3 ፤ በቤቴልም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ወጥተው። እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን? አሉት። እርሱም። አዎን፥ አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ አላቸው።
4 ፤ ኤልያስም። ኤልሳዕ ሆይ፥ እግዚአብሔር ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ አለው። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ።
5 ፤ ወደ ኢያሪኮም መጡ። በኢያሪኮም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ቀርበው። እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን? አሉት። እርሱም። አዎን አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ ብሎ መለሰ።
6 ፤ ኤልያስም። እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ አለው። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ። ሁለቱም ሄዱ።
7 ፤ ከነቢያትም ልጆች አምሳ ሰዎች ሄዱ፥ በፊታቸውም ርቀው ቆሙ፤ እነዚህም ሁለቱ በዮርዳኖስ ዳር ቆመው ነበር።
8 ፤ ኤልያስም መጐናጸፊያውን ወስዶ ጠቀለለው፥ ውኃውንም መታ፥ ወዲህና ወዲያም ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ተሻገሩ።
9 ፤ ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን። ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን አለው፤ ኤልሳዕም። መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ አለ።
10 ፤ እርሱም። አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል፤ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም አለ።
11 ፤ ሲሄዱም። እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ።
12 ፤ ኤልሳዕም አይቶ። አባቴ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች፥ ብሎ ጮኸ። ከዚያም ወዲያ አላየውም፤ ልብሱንም ይዞ ከሁለት ተረተረው።
13 ፤ ከኤልያስም የወደቀውን መጐናጸፊያ አነሣ፥ ተመልሶም በዮርዳኖስ ዳር ቆመ።
14 ፤ ከኤልያስም የወደቀውን መጎናጸፊያ ወስዶ ውኃውን መታና። የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው? አለ፤ ውኃውንም በመታ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተከፈለ፤ ኤልሳዕም ተሻገረ።
15 ፤ ከኢያሪኮም መጥተው በአንጻሩ የነበሩት የነቢያት ልጆች ባዩት ጊዜ። የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል አሉ። ሊገናኙትም መጥተው በፊቱ ወደ ምድር ተደፉ።
16 ፤ እነርሱም። እነሆ፥ ከባሪያዎችህ ጋር አምሳ ኃያላን ሰዎች አሉ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወደ አንድ ተራራ ወይም ወደ አንድ ሸለቆ ጥሎት እንደ ሆነ፥ ሄደው ጌታህን ይፈልጉት ዘንድ እንለምንሃለን አሉት። እርሱም። አትስደዱ አላቸው።
17 ፤ እስኪያፍርም ድረስ ግድ ባሉት ጊዜ። ስደዱ አለ፤ አምሳም ሰዎች ሰደዱ፤ ሦስት ቀንም ፈልገው አላገኙትም።
18 ፤ በኢያሪኮም ተቀምጦ ሳለ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም። አትሂዱ አላልኋችሁምን? አላቸው። v
19 ፤ የከተማይቱም ሰዎች ኤልሳዕን። እነሆ፥ ጌታችን እንደምታይ የዚች ከተማ ኑሮ መልካም ነው፤ ውኃው ግን ክፉ ነው፥ ምድሪቱም ፍሬዋን ትጨነግፋለች አሉት።
20 ፤ እርሱም። አዲስ ማሰሮ አምጡልኝ፥ ጨውም ጨምሩበት አለ፤ ያንንም አመጡለት።
21 ፤ ውኃው ወዳለበቱም ምንጭ ወጥቶ ጨው ጣለበትና። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህን ውኃ ፈውሼዋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ሞትና ጭንገፋ አይሆንበትም አለ።
22 ፤ ኤልሳዕም እንደ ተናገረው ነገር ውኃው እስከ ዛሬ ድረስ ተፈውሶአል።
23 ፤ ከዚያም ወደ ቤቴል ወጣ፤ በመንገድም ሲወጣ ብላቴኖች ከከተማይቱ ወጥተው። አንተ መላጣ፥ ውጣ፤ አንተ መላጣ፥ ውጣ ብለው አፌዙበት።
24 ፤ ዘወርም ብሎ አያቸው፥ በእግዚአብሔርም ስም ረገማቸው፤ ከዱርም ሁለት ድቦች ወጥተው ከብላቴኖች አርባ ሁለቱን ሰባበሩአቸው።
25 ፤ ከዚያም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄደ፥ ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ።

1 ፤ በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሣፍጥ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፥ አሥራ ሁለትም ዓመት ነገሠ።
2 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ያሠራውን የበኣልን ሐውልት አርቆአልና እንደ አባቱና እንደ እናቱ አልነበረም።
3 ፤ ነገር ግን እስራኤልን ባሳታቸው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት ተያዘ፤ ከእርሱም አልራቀም።
4 ፤ የሞዓብም ንጉሥ ሞሳ ባለ በጎች ነበረ፤ ለእስራኤልም ንጉሥ የመቶ ሺህ ጠቦትና የመቶ ሺህ አውራ በጎች ጠጕር ይገብርለት ነበር።
5 ፤ አክዓብም ከሞተ በኋላ የሞዓብ ንጉሥ በእስራኤል ንጉሥ ላይ ዐመፀ።
6 ፤ በዚያም ጊዜ ንጉሡ ኢዮራም ከሰማርያ ወጥቶ እስራኤልን ሁሉ አሰለፈ።
7 ፤ ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ ኢዮሣፍጥ። የሞዓብ ንጉሥ ዐምፆብኛልና ከእኔ ጋር በሞዓብ ላይ ለሰልፍ ትሄዳለህን? ብሎ ላከ። እርሱም። እወጣለሁ፤ እኔ እንደ አንተ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፥ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው አለ።
8 ፤ ደግሞም። በምን መንገድ እንሄዳለን? አለ፤ እርሱም። በኤዶምያስ ምድረ በዳ መንገድ ብሎ መለሰ።
9 ፤ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ የኤዶምያስም ንጉሥ ሄዱ፤ የሰባትም ቀን መንገድ ዞሩ፤ ለሠራዊቱና ለተከተሉአቸውም እንስሶች ውኃ አልተገኘም።
10 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ። ወዮ! እግዚአብሔር በሞዓብ እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ዘንድ እነዚህን ሦስቱን ነገሥታት ጠርቶአልና ወዮ አለ።
11 ፤ ኢዮሣፍጥም። በእርሱ እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን? አለ። ከእስራኤልም ንጉሥ ባሪያዎች አንዱ። በኤልያስ እጅ ላይ ውኃ ያፈስስ የነበረው የሣፋጥ ልጅ ኤልሳዕ እዚህ አለ ብሎ መለሰ።
12 ፤ ኢዮሣፍጥም። የእግዚአብሔር ቃል በእርሱ ዘንድ ይገኛል አለ። የእስራኤል ንጉሥና ኢዮሣፍጥ የኤዶምያስም ንጉሥ ወደ እርሱ ወረዱ።
13 ፤ ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ። እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ወደ አባትህና ወደ እናትህ ነቢያት ሂድ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ። አይደለም፥ በሞዓብ እጅ ይጥላቸው ዘንድ እግዚአብሔር እነዚህን ሦስት ነገሥታት ጠርቶአል አለው።
14 ፤ ኤልሳዕም። በፊቱ የቆምሁት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን! የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ያላፈርሁ ብሆን ኖሮ አንተን ባልተመለከትሁና ባላየሁ ነበር።
15 ፤ አሁንም ባለ በገና አምጡልኝ አለ። ባለ በገናውም በደረደረ ጊዜ የእግዚአብሔር እጅ መጣችበት፤
16 ፤ እንዲህም አለ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህ ሸለቆ ሁሉ ጕድጓድ ቆፈሩ።
17 ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ነፋስ አታዩም፥ ዝናብም አታዩም፥ ይህ ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል፤ እናንተም ከብቶቻችሁም እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ።
18 ፤ ይህም በእግዚአብሔር ዓይን ቀላል ነገር ነው፤ ደግሞም ሞዓባውያንን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣል።
19 ፤ የተመሸጉትንና ያማሩትን ከተሞች ሁሉ ትመታላችሁ፥ የሚያፈሩትንም ዛፎች ሁሉ ትቈርጣላችሁ፥ የውኃውንም ምንጮች ሁሉ ትደፍናላችሁ፥ መልካሞችንም እርሻዎች ሁሉ በድንጋይ ታበላሻላችሁ።
20 ፤ በነጋውም የቍርባን ጊዜ ሲደርስ፥ እነሆ፥ ውኃ በኤዶምያስ መንገድ መጣ፥ ምድሪቱም ውኃ ሞላች።
21 ፤ ሞዓባውያንም ሁሉ ነገሥታት ሊወጉአቸው እንደ መጡ በሰሙ ጊዜ በወገባቸው ሰይፍ የሚታጠቁ ሁሉ ተሰበሰቡ፤ ወጥተውም በአገሩ ድንበር ላይ ቆሙ።
22 ፤ ማልደውም ተነሡ፤ ፀሐይም በውኃው ላይ አንጸባረቀ፥ ሞዓባውያንም በፊታቸው ውኃው እንደ ደም ቀልቶ አዩና። ይህ ደም ነው፤
23 ፤ በእርግጥ ነገሥታት እርስ በርሳቸው ተዋጉ፥ እርስ በርሳቸውም ተጋደሉ፤ ሞዓብ ሆይ፥ እንግዲህ ወደ ምርኮህ ሂድ አሉ።
24 ፤ ወደ እስራኤል ሰፈር በመጡ ጊዜ እስራኤላውያን ተነሥተው ሞዓባውያንን መቱ፥ እነርሱም ከፊታቸው ሸሹ፤ ሞዓባውያንንም እየመቱ ወደ አገሩ ውስጥ ገቡ።
25 ፤ ከተሞችንም አፈረሱ፤ በመልካሞቹም እርሻዎች ሁሉ ላይ እስኪሞሉ ድረስ እያንዳንዱ ሰው አንድ አንድ ድንጋይ ይጥል ነበር፤ የውኃውንም ምንጮች ሁሉ ደፈኑ፥ የሚያፈሩትንም ዛፎች ሁሉ ቈረጡ፤ የቂርሐራሴትን ድንጋዮች ብቻ አስቀሩ፤ ባለ ወንጭፎች ግን ከብበው መቱአት።
26 ፤ የሞዓብም ንጉሥ ሰልፍ እንደ በረታበት ባየ ጊዜ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰባት መቶ ሰዎች ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ ወደ ኤዶምያስም ንጉሥ ያልፉ ዘንድ ሞከሩ፤ አልቻሉምም።
27 ፤ በዚያም ጊዜ በእርሱ ፋንታ ንጉሥ የሚሆነውን የበኵር ልጁን ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በቅጥሩ ላይ አቀረበው። በእስራኤልም ዘንድ ታላቅ ቍጣ ሆነ፤ ከዚያም ርቀው ወደ ምድራቸው ተመለሱ።

1 ፤ ከነቢያትም ወገን ሚስቶች አንዲት ሴት። ባሌ ባሪያህ ሞቶአል፤ ባሪያህም እግዚአብሔርን ይፈራ እንደ ነበረ አንተ ታውቃለህ፤ ባለ ዕዳ ልጆቼን ባሪያዎች አድርጎ ሊወስዳቸው መጥቶአል ብላ ወደ ኤልሳዕ ጮኸች።
2 ፤ ኤልሳዕም። አደርግልሽ ዘንድ ምን ትሻለሽ? በቤትሽ ያለውን ንገሪኝ አላት። እርስዋም። ለእኔ ለባሪያህ ከዘይት ማሰሮ በቀር በቤቴ አንዳች የለኝም አለች።
3 ፤ እርሱም። ሄደሽ ከጐረቤቶችሽ ሁሉ ከሜዳ ባዶ ማድጋዎችን ተዋሺ፤ አታሳንሻቸውም አላት።
4 ፤ ገብተሽም ከአንቺና ከልጆችሽ በኋላ በሩን ዝጊ፥ ወደ እነዚህም ማድጋዎች ሁሉ ዘይቱን ገልብጪ፤ የሞላውንም ፈቀቅ አድርጊ አለ።
5 ፤ እንዲሁም ከእርሱ ሄዳ በሩን ከእርስዋና ከልጆችዋ በኋላ ዘጋች፤ እነርሱም ማድጋዎቹን ወደ እርስዋ ያመጡ ነበር፥ እርስዋም ትገለብጥ ነበር።
6 ፤ ማድጋዎቹም በሞሉ ጊዜ ልጅዋን። ደግሞም ማድጋ አምጣልኝ አለችው፤ እርሱም። ሌላ ማድጋ የለም አላት፤ ዘይቱም ቆመ።
7 ፤ መጥታም ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው፤ እርሱም። ሄደሽ ዘይቱን ሽጪ ለባለ ዕዳውም ክፈዪ፤ አንቺና ልጆችሽም ከተረፈው ተመገቡ አለ።
8 ፤ አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ ኤልሳዕ ወደ ሱነም አለፈ፥ በዚያም ታላቅ ሴት ነበረች፤ እንጀራ ይበላ ዘንድ የግድ አለችው፤ በዚያም ባለፈ ቍጥር እንጀራ ሊበላ ወደዚያ ይገባ ነበር።
9 ፤ ለባልዋም። ይህ በእኛ ዘንድ ሁልጊዜ የሚያልፈው ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆነ አውቃለሁ።
10 ፤ ትንሽ ቤት በሰገነቱ ላይ እንሥራ፤ በዚያም አልጋ ጠረጴዛ ወንበርና መቅረዝ እናኑርለት፤ ወደ እኛም ሲመጣ ወደዚያ ይገባል አለችው።
11 ፤ አንድ ቀንም ወደዚያ በመጣ ጊዜ ወደ ቤቱ ገብቶ በዚያ ዐረፈ።
12 ፤ ሎሌውንም ግያዝን። ይህችን ሱነማዊት ጥራ አለው።
13 ፤ በጠራትም ጊዜ በፊቱ ቆመች። እርሱም። እነሆ፥ ይህን ሁሉ አሳብ አሰብሽልኝ፤ አሁንስ ምን ላድርግልሽ? ለንጉሥ ወይስ ለሠራዊት አለቃ ልንገርልሽን? በላት አለው፤ እርስዋም። እኔ በወገኔ መካከል ተቀምጫለሁ ብላ መለሰች።
14 ፤ እርሱም። እንግዲህ ምን እናድርግላት? አለ። ግያዝም። ልጅ የላትም፤ ባልዋም ሸምግሎአል ብሎ መለሰ።
15 ፤ እርሱም። ጥራት አለ። በጠራትም ጊዜ በደጃፉ ቆመች።
16 ፤ እርሱም። በሚመጣው ዓመት በዚህ ወራት ወንድ ልጅ ትታቀፊአለሽ አለ፤ እርስዋም። አይደለም ጌታዬ፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ባሪያህን እንዳትዋሻት እለምንሃለሁ አለች።
17 ፤ ሴቲቱም ፀነሰች፥ በዚያም ወራት በአዲሱ ዓመት ኤልሳዕ እንዳላት ወንድ ልጅ ወለደች።
18 ፤ ሕፃኑም አደገ፥ አንድ ቀንም እህል አጫጆች ወዳሉበት ወደ አባቱ ወጣ።
19 ፤ አባቱንም። ራሴን ራሴን አለው፤ እርሱም ሎሌውን። ተሸክመህ ወደ እናቱ ውሰደው አለው።
20 ፤ አንሥቶም ወደ እናቱ ወሰደው፤ በጕልበትዋም ላይ እስከ ቀትር ድረስ ተቀመጠ፥ ሞተም።
21 ፤ ወጥታም በእግዚአብሔር ሰው አልጋ ላይ አጋደመችው፥ በሩንም ዘግታበት ወጣች።
22 ፤ ባልዋንም ጠርታ። ወደ እግዚአብሔር ሰው በፍጥነት ደርሼ እመለስ ዘንድ አንድ ሎሌና አንድ አህያ ላክልኝ አለችው።
23 ፤ እርሱም። መባቻ ወይም ሰንበት ያይደለ ዛሬ ለምን ትሄጂበታለሽ? አለ። እርስዋም። ደኅና ነው አለች።
24 ፤ አህያውንም አስጭና ሎሌዋን። ንዳ፥ ሂድ፤ እኔ ሳላዝዝህ አታዘግየኝ አለችው።
25 ፤ እንዲሁም ሄደች፥ ወደ እግዚአብሔርም ሰው ወደ ቀርሜሎስ ተራራ መጣች። የእግዚአብሔርም ሰው ከሩቅ ባያት ጊዜ ሎሌውን ግያዝን፥ እነኋት ሱነማዊቲቱ መጣች፤
26 ፤ ትቀበላትም ዘንድ ሩጥና። በደኅናሽ ነውን? ባልሽ ደኅና ነውን? ልጅሽስ ደኅና ነውን? በላት አለው። እርስዋም። ደኅና ነው አለች።
27 ፤ ወደ ተራራው ወደ እግዚአብሔር ሰው በመጣች ጊዜ እግሮቹን ጨበጠች፤ ግያዝም ሊያርቃት ቀረበ፤ የእግዚአብሔርም ሰው። ነፍስዋ አዝናለችና ተዋት፤ እግዚአብሔርም ያንን ከእኔ ሰውሮታል አልነገረኝምም አለ።
28 ፤ እርስዋም። በውኑ ከጌታዬ ልጅን ለመንሁን? እኔም አታታልለኝ አላልሁህምን? አለች።
29 ፤ ግያዝንም። ወገብህን ታጠቅ፥ በትሬንም በእጅህ ይዘህ ሂድ፤ ሰውም ብታገኝ ሰላም አትበል፥ እርሱም ሰላም ቢልህ አትመልስለት፤ በትሬንም በሕፃኑ ፊት ላይ አኑር አለው።
30 ፤ የሕፃኑም እናት። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! አልተውህም አለች፤ ተነሥቶም ተከተላት።
31 ፤ ግያዝም ቀደማቸው፥ በትሩንም በሕፃኑ ፊት ላይ አኖረው፤ ነገር ግን ድምፅ ወይም መስማት አልነበረም፤ እርሱንም ሊገናኘው ተመልሶ። ሕፃኑ አልነቃም ብሎ ነገረው።
32 ፤ ኤልሳዕም ወደ ቤት በገባ ጊዜ እነሆ፥ ሕፃኑ ሞቶ በአልጋው ላይ ተጋድሞ ነበር።
33 ፤ ገብቶም በሩን ከሁለቱ በኋላ ዘጋ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ።
34 ፤ መጥቶም በሕፃኑ ላይ ተኛ፤ አፉንም በአፉ፥ ዓይኑንም በዓይኑ፥ እጁንም በእጁ ላይ አድርጎ ተጋደመበት፤ የሕፃኑም ገላ ሞቀ።
35 ፤ ተመልሶም በቤቱ ውስጥ አንድ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተመላለሰ፤ ደግሞም ወጥቶ ሰባት ጊዜ በሕፃኑ ላይ ተጋደመ፤ ሕፃኑም ዓይኖቹን ከፈተ።
36 ፤ ግያዝንም ጠርቶ። ይህችን ሱነማዊት ጥራ አለው። ጠራትም፥ ወደ እርሱም በገባች ጊዜ። ልጅሽን አንሥተሽ ውሰጂ አላት።
37 ፤ ገብታም በእግሩ አጠገብ ወደቀች በምድርም ላይ ተደፋች፤ ልጅዋንም አንሥታ ወጣች።
38 ፤ ኤልሳዕም ዳግመኛ ወደ ጌልገላ መጣ፥ በምድርም ላይ ራብ ነበረ፤ የነቢያትም ልጆች በፊቱ ተቀምጠው ነበር፥ ሎሌውንም። ታላቁን ምንቸት ጣድ፥ ለነቢያት ልጆችም ወጥ ሥራ አለው።
39 ፤ አንዱም ቅጠላቅጠል ያመጣ ዘንድ ወደ ሜዳ ወጣ፥ የምድረበዳውንም ሐረግ አገኘ ከዚያም የበረሀ ቅል ሰበሰበ፥ ልብሱንም ሞልቶ ተመለሰ፥ መትሮም በወጡ ምንቸት ውስጥ ጨመረው፤ ምን እንደ ሆነ ግን አላወቁም።
40 ፤ ሰዎቹም ይበሉ ዘንድ ቀዱ፤ ወጡንም በቀመሱ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ በምንቸቱ ውስጥ ሞት አለ ብለው ጮኹ፤ ይበሉም ዘንድ አልቻሉም።
41 ፤ እርሱም። ዱቄት አምጡልኝ አለ፤ በምንቸቱም ውስጥ ጥሎ። ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ቅዱ አለ። በምንቸቱም ውስጥ ክፉ ነገር አልተገኘም።
42 ፤ አንድ ሰውም ከበኣልሻሊሻ የበኵራቱን እንጀራ፥ ሀያ የገብስ እንጀራ፥ የእህልም እሸት በአቁማዳ ይዞ ወደ እግዚአብሔር ሰው መጣ፤ እርሱም። ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ስጣቸው አለ።
43 ፤ ሎሌውም። ይህን እንዴት አድርጌ ለመቶ ሰው እሰጣለሁ? አለ። እርሱም። ይበላሉ ያተርፋሉም ብሎ እግዚአብሔር ተናግሮአልና ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ስጣቸው አለ።
44 ፤ እንዲሁም በፊታቸው አኖረው፥ እንደ እግዚአብሔርም ቃል በሉ፥ አተረፉም።

1 ፤ የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ ንዕማንም እግዚአብሔር በእርሱ እጅ ለሶርያ ደኅንነትን ስለ ሰጠ በጌታው ዘንድ ታላቅ ክቡር ሰው ነበረ፤ ደግሞም ጽኑዕ ኃያል ነበረ፥ ነገር ግን ለምጻም ነበረ።
2 ፤ ከሶርያውያንም አገር አደጋ ጣዮች ወጥተው ነበር፥ ከእስራኤልም ምድር ታናሽ ብላቴና ሴት ማርከው ነበር፤ የንዕማንንም ሚስት ታገለግል ነበር።
3 ፤ እመቤትዋንም። ጌታዬ በሰማርያ ካለው ከነቢዩ ፊት ቢደርስ ኖሮ ከለምጹ በፈወሰው ነበር አለቻት።
4 ፤ ንዕማንም ገብቶ ለጌታው። ከእስራኤል አገር የሆነች አንዲት ብላቴና እንዲህና እንዲህ ብላለች ብሎ ነገረው።
5 ፤ የሶርያም ንጉሥ ንዕማንን። ሂድ፥ ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እልካለሁ አለው። እርሱም ሄደ፥ አሥርም መክሊት ብር፥ ስድስት ሺህም ወርቅ፥ አሥርም መለውጫ ልብስ በእጁ ወሰደ።
6 ፤ ለእስራኤልም ንጉሥ። ይህች ደብዳቤ ወደ አንተ ስትደርስ ባሪያዬን ንዕማንን ከለምጹ ትፈውሰው ዘንድ እንደ ሰደድሁልህ እወቅ የሚል ደብዳቤ ወሰደ።
7 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ባነበበ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ። ሰውን ከለምጹ እፈውስ ዘንድ ይህ ሰው ወደ እኔ መስደዱ እኔ በውኑ ለመግደልና ለማዳን የምችል አምላክ ሆኜ ነውን? ተመልከቱ፥ የጠብ ምክንያትም እንደሚፈልግብኝ እዩ አለ።
8 ፤ የእግዚአብሔርም ሰው ኤልሳዕ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን እንደ ቀደደ በሰማ ጊዜ። ልብስህን ለምን ቀደድህ? ወደ እኔ ይምጣ፥ በእስራኤልም ዘንድ ነቢይ እንዳለ ያውቃል ብሎ ወደ ንጉሡ ላከ።
9 ፤ ንዕማንም በፈረሱና በሰረገላው መጣ፥ በኤልሳዕም ቤት ደጃፍ ውጭ ቆመ።
10 ፤ ኤልሳዕም። ሂድ፥ በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ታጠብ፤ ሥጋህም ይፈወሳል፥ አንተም ንጹሕ ትሆናለህ ብሎ ወደ እርሱ መልእክተኛ ላከ።
11 ፤ ንዕማን ግን ተቈጥቶ ሄደ፥ እንዲህም አለ። እነሆ፥ ወደ እኔ የሚመጣ፥ ቆሞም የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ፥ የለምጹንም ስፍራ በእጁ ዳስሶ የሚፈውሰኝ መስሎኝ ነበር።
12 ፤ የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋ ከእስራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን? በእነርሱስ ውስጥ መታጠብና መንጻት አይቻለኝም ኖሮአልን? ዘወርም ብሎ ተቈጥቶ ሄደ።
13 ፤ ባሪያዎቹም ቀርበው። አባት ሆይ፥ ነቢዩ ታላቅ ነገርስ እንኳ ቢነግርህ ኖሮ ባደረግኸው ነበር፤ ይልቁንስ። ታጠብና ንጹሕ ሁን ቢልህ እንዴት ነዋ! ብለው ተናገሩት።
14 ፤ ወረደም፥ የእግዚአብሔርም ሰው እንደ ተናገረው በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደ ገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ሆኖ ተመለሰ፥ ንጹሕም ሆነ።
15 ፤ እርሱም ከጭፍራው ሁሉ ጋር ወደ እግዚአብሔር ሰው ተመለሰ፥ ወጥቶም በፊቱ ቆመና። እነሆ፥ ከእስራኤል ዘንድ በቀር በምድር ሁሉ አምላክ እንደሌለ አወቅሁ፤ አሁንም ከባሪያህ በረከት ትቀበል ዘንድ እለምንሃለሁ አለ።
16 ፤ እርሱም። በፊቱ የቆምሁት ሕያው እግዚአብሔርን! አልቀበልም አለ። ይቀበለውም ዘንድ ግድ አለው፤ እርሱ ግን እንቢ አለ።
17 ፤ ንዕማንም። እኔ ባሪያህ ከእንግዲህ ወዲህ ከእግዚአብሔር በቀር ለሌሎች አማልክት የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት አላቀርብምና ሁለት የበቅሎ ጭነት አፈር እንድወስድ እሺ ትለኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።
18 ፤ እግዚአብሔርም ለእኔ ለባሪያህ በዚህ ነገር ብቻ ይቅር ይበለኝ፤ ጌታዬ በዚያ ይሰግድ ዘንድ እጄን ተደግፎ ወደ ሬሞን ቤት በገባ ጊዜ፥ እኔም በሬሞን ቤት በሰገድሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በዚህ ነገር ለእኔ ለባሪያህ ይቅር ይበለኝ አለ።
19 ፤ እርሱም። በደኅና ሂድ አለው። አንድ አግድመትም ያህል ከእርሱ ራቀ።
20 ፤ የእግዚአብሔርም ሰው ሎሌ ግያዝ። ጌታዬ ሶርያዊውን ይህን ንዕማንን ማረው፥ ካመጣለትም ነገር ምንም አልተቀበለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! በስተ ኋለው እሮጣለሁ፥ ከእርሱም አንዳች እወስዳለሁ አለ።
21 ፤ ግያዝም ንዕማንን ተከተለው፤ ንዕማንም ወደ እርሱ ሲሮጥ ባየው ጊዜ ሊገናኘው ከሰረገላው ወርዶ። ሁሉ ደኅና ነውን? አለው።
22 ፤ እርሱም። ደኅና ነው። አሁን ከነቢያት ወገን የሆኑት ሁለት ጕልማሶች ከተራራማው ከኤፍሬም አገር ወደ እኔ መጥተዋል፤ አንድ መክሊት ብርና ሁለት መለወጫ ልብስ ትሰጣቸው ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ጌታዬ ላከኝ አለ።
23 ፤ ንዕማንም። ሁለት መክሊት ትወስድ ዘንድ ይፈቀድልህ አለ፤ ግድ አለውም፤ ሁለቱንም መክሊት ብር በሁለት ከረጢት ውስጥ አሰረና ከሁለት መለወጫ ልብስ ጋር ለሁለት ሎሌዎቹ አስያዘ፤ እነርሱም ተሸክመው በፊቱ ሄዱ።
24 ፤ ወደ ኮረብታውም በመጣ ጊዜ ከእጃቸው ወስዶ በቤቱ ውስጥ አኖራቸው፤ ሰዎቹንም አሰናበተ፥ እነርሱም ሄዱ።
25 ፤ እርሱ ግን ገብቶ በጌታው ፊት ቆመ፤ ኤልሳዕም። ግያዝ ሆይ፥ ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም። እኔ ባሪያህ ወዴትም አልሄድሁም አለ።
26 ፤ እርሱም። ያ ሰው ከሰረገላው ወርዶ ሊቀበልህ በተመለሰ ጊዜ ልቤ ከአንተ ጋር አልሄደምን? ብሩንና ልብሱን፥ የወይራውንና የወይኑን ቦታ፥ በጎችንና በሬዎችን፥ ወንዶችንና ሴቶችን ባሪያዎች ትቀበል ዘንድ ይህ ጊዜው ነውን?
27 ፤ እንግዲህስ የንዕማን ለምጽ በአንተ ላይ፥ ለዘላለምም በዘርህ ላይ ይጣበቃል አለው። እንደ በረዶም ለምጻም ሆኖ ከእርሱ ዘንድ ወጣ።

1 ፤ የነቢያትም ልጆች ኤልሳዕን። እነሆ፥ በፊትህ የምንቀመጥበት ስፍራ ጠብቦናል።
2 ፤ ወደ ዮርዳኖስም እንሂድ፥ ከእኛም እያንዳንዱ ከዚያ ምሰሶ ያምጣ፥ የምንቀመጥበትንም ስፍራ በዚያ እንሥራ አሉት፤ እርሱም። ሂዱ አለ።
3 ፤ ከእነርሱም አንዱ። አንተ ደግሞ ከእኛ ከባሪያዎችህ ጋር ለመሄድ ፍቀድ አለ። እርሱም። እሄዳለሁ አለ።
4 ፤ ከእነርሱም ጋር ሄደ፤ ወደ ዮርዳኖስም በደረሱ ጊዜ እንጨት ቆረጡ።
5 ፤ ከእነርሱም አንዱ ምሰሶውን ሲቆርጥ የምሳሩ ብረት ወደ ውኃው ውስጥ ወደቀ፤ እርሱም። ጌታዬ ሆይ፥ ወየው! ወየው! የተዋስሁት ነበረ ብሎ ጮኽ።
6 ፤ የእግዚአብሔርም ሰው። የወደቀው ወዴት ነው? አለ ስፍራውንም አሳየው፤ እንጨትም ቆርጦ በዚያ ጣለው፥ ብረቱም ተንሳፈፈ።
7 ፤ እርሱም። ውሰደው አለ፤ እጁንም ዘርግቶ ወሰደው።
8 ፤ የሶርያም ንጉሥ ከእስራኤል ጋር ይዋጋ ነበር፤ ከባሪያዎቹም ጋር ተማክሮ። በዚህ ተደብቀን እንሰፍራለን አለ።
9 ፤ የእግዚአብሔርም ሰው። ሶርያውያን በዚያ ተደብቀዋልና በዚያ ስፍራ እንዳታልፍ ተጠንቀቅ ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ላከ።
10 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ነገረው ስፍራ ሰደደ፤ አንድ ጊዜም ሳይሆን፥ ሁለት ጊዜም ሳይሆን በዚያ ራሱን አዳነ።
11 ፤ የሶርያም ንጉሥ ልብ ስለዚህ እጅግ ታወከ፤ ባሪያዎቹንም ጠርቶ። ከእኛ ዘንድ ከእስራኤል ንጉሥ ጋር የተወዳጀ እንዳለ አትነግሩኝምን? አላቸው።
12 ፤ ከባሪያዎቹም አንዱ። ጌታዬ ሆይ፥ እንዲህ እኮ አይደለም፤ ነገር ግን በእልፍኝህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውን በእስራኤል ዘንድ ያለ ነቢይ ኤልሳዕ ለእስራኤል ንጉሥ ይነግረዋል አለ።
13 ፤ እርሱም። ልኬ አስይዘው ዘንድ ሄዳችሁ ወዴት እንደ ሆነ እዩ አለ። እነርሱም። እነሆ፥ በዶታይን አለ ብለው ነገሩት።
14 ፤ ወደዚያም ፈረሶችንና ሰረገሎችን እጅግም ጭፍራ ሰደደ፤ በሌሊትም መጥተው ከተማይቱን ከበቡ።
15 ፤ የእግዚአብሔር ሰው ሎሌ ማለዳ ተነሥቶ በወጣ ጊዜ፥ እነሆ፥ በከተማይቱ ዙሪያ ጭፍራና ፈረሶች ሰረገሎችም ነበሩ። ሎሌውም። ጌታዬ ሆይ፥ ወዮ! ምን እናደርጋለን? አለው።
16 ፤ እርሱም። ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ አለው።
17 ፤ ኤልሳዕም። አቤቱ፥ ያይ ዘንድ ዓይኖቹን፥ እባክህ፥ ግለጥ ብሎ ጸለየ። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዓይኖች ገለጠ፥ አየም፤ እነሆም፥ በኤልሳዕ ዙሪያ ያሉት የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተራራውን ሞልተውት ነበር።
18 ፤ ወደ እርሱም በወረዱ ጊዜ ኤልሳዕ። ይህን ሕዝብ ዕውር ታደርገው ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ኤልሳዕም እንደ ተናገረው ቃል ዕውር አደረጋቸው።
19 ፤ ኤልሳዕም። መንገዱ በዚህ አይደለም፥ ከተማይቱም ይህች አይደለችም፤ የምትሹትን ሰው አሳያችሁ ዘንድ ተከተሉኝ አላቸው፤ ወደ ሰማርያም መራቸው።
20 ፤ ወደ ሰማርያም በገቡ ጊዜ ኤልሳዕ። አቤቱ፥ ያዩ ዘንድ የእነዚህን ሰዎች ዓይኖች ግለጥ አለ፤ እግዚአብሔርም ዓይኖቻቸውን ገለጠ፥ እነርሱም አዩ። እነሆም፥ በሰማርያ መካከል ነበሩ።
21 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ባያቸው ጊዜ አልሳዕን። አባቴ ሆይ፥ ልግደላቸውን? ልግደላቸውን? አለው።
22 ፤ እርሱም። አትግደላቸው፤ በሰይፍህና በቀስትህ የማረክኸውን ትገድል ዘንድ ይገባሃልን? እንጀራና ውኃ በፊታቸው አኑርላቸው፥ በልተውና ጠጥተውም ወደ ጌታቸው ይሂዱ አለው።
23 ፤ ብዙም መብል አዘጋጀላቸው፤ በበሉና በጠጡ ጊዜም አሰናበታቸው፥ እነርሱም ወደ ጌታቸው ሄዱ። ከዚያም በኋላ የሶርያ አደጋ ጣዮች ወደ እስራኤል አገር አልመጡም።
24 ፤ ከዚያም በኋላ የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር ሠራዊቱን ሁሉ ሰበሰበ፥ ወጥቶም ሰማርያን ከበባት።
25 ፤ በሰማርያም ታላቅ ራብ ሆኖ ነበር፤ እነሆም፥ የአህያ ራስ በአምሳ ብር፥ የርግብም ኩስ የጎሞር ስምንተኛ የሚሆን በአምስት ብር እስኪሸጥ ድረስ ከበቡአት።
26 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በቅጥር ላይ በተመላለሰ ጊዜ አንዲት ሴት ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ እርዳኝ ብላ ወደ እርሱ ጮኸች።
27 ፤ እርሱም። እግዚአብሔር ያልረዳሽን እኔ እንዴት እረዳሻለሁ? ከአውድማው ወይስ ከመጥመቂያው ነውን? አለ።
28 ፤ ንጉሡም። ምን ሆነሻል? አላት፤ እርስዋም። ይህች ሴት። ዛሬ እንድንበላው ልጅሽን አምጪ፤ ነገም ልጄን እንበላለን አለችኝ።
29 ፤ ልጄንም ቀቅለን በላነው፤ በማግሥቱም። እንድንበላው ልጅሽን አምጪ አልኋት፤ ልጅዋንም ሸሸገችው ብላ መለሰችለት።
30 ፤ ንጉሡም የሴቲቱን ቃል ሰምቶ ልብሱን ቀደደ፤ በቅጥርም ይመላለስ ነበር፤ ሕዝቡም በስተ ውስጥ በሥጋው ላይ ለብሶት የነበረውን ማቅ አዩ።
31 ፤ ንጉሡም። የሣፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ዛሬ በላዩ ያደረ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፥ ይህንም ይጨምርብኝ አለ።
32 ፤ ኤልሳዕ ግን በቤቱ ተቀምጦ ነበር፥ ሽማግሌዎችም ከእርሱ ጋር ተቀምጠው ነበር፤ ንጉሡ ሰው ላካ፤ መልእክተኛውም ገና ሳይደርስ ለሽማግሌዎች። ይህ የነፍሰ ገዳይ ልጅ ራሴን ይቈርጥ ዘንድ እንደ ላከ እዩ፤ መልእከተኛውም በመጣ ጊዜ ደጁን ዘግታችሁ ከልክሉት፤ የጌታው የእግሩ ኮቴ በኋላው ነው አላቸው።
33 ፤ ሲናገራቸውም መልእክተኛው ወደ እርሱ ደረሰ፤ እርሱም። እነሆ፥ ይህ ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፥ እግዚአብሔርን ገና እጠብቅ ዘንድ ምንድር ነኝ? አለ።

1 ፤ ኤልሳዕም። የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለትም መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ይሸመታል አለ።
2 ፤ ንጉሡም በእጁ ተደግፎ የነበረ አለቃ ለእግዚአብሔር ሰው መልሶ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን? አለው። እርሱም። እነሆ፥ በዓይኖችህ ታየዋለህ፥ ከዚያም አትቀምስም አለ። ፕ
3 ፤ በበሩም መግቢያ አራት ለምጻም ሰዎች ነበሩ፤ እርስ በርሳቸውም። እስክንሞት ድረስ በዚህ ለምን እንቀመጣለን?
4 ፤ ወደ ከተማ እንገባ ዘንድ ብንወድድ ራብ በከተማ አለ፥ በዚያም እንሞታለን፤ በዚህም ብንቀመጥ እንሞታለን። እንግዲህ ኑ፥ ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሽሽ፤ በሕይወት ቢያኖሩን እንኖራለን፤ ቢገድሉንም እንሞታለን ተባባሉ።
5 ፤ ጨለምለም ባለ ጊዜ ወደ ሶርያውያን ሰፈር ይሄዱ ዘንድ ተነሡ፤ ወደ ሶርያውያንም ሰፈር መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ማንም አልነበረም።
6 ፤ እግዚአብሔር ለሶርያውያን የሰረገላና የፈረስ የብዙም ጭፍራ ድምፅ አሰምቶ ነበር፤ እርስ በርሳቸውም። እነሆ፥ የእስራኤል ንጉሥ የኬጢያውያንና የግብጻውያንን ነገሥት ቀጥሮ አምጥቶብናል ይባባሉ ነበር።
7 ፤ ስለዚህም ተነሥተው በጨለማ ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውንና ፈረሶቻቸውን አህዮቻቸውንና ሰፈሩን እንዳለ ትተው ነፍሳቸውን ያድኑ ዘንድ ሸሹ።
8 ፤ እነዚህም ለምጻሞች ወደ ሰፈሩ መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ ወደ አንድ ድንኳን ገብተው በሉ ጠጡም፥ ከዚያም ወርቅና ብር ልብስም ወሰዱ፥ ሄደውም ሸሸጉት፤ ተመልሰውም ወደ ሌላ ድንኳን ገቡ፥ ከዚያም ደግሞ ወስደው ሸሸጉ።
9 ፤ ከዚያም ወዲያ እርስ በርሳቸው። መልካም አላደረግንም፤ ዛሬ የመልካም ምስራች ቀን ነው፥ እኛም ዝም ብለናል፤ እስኪነጋም ድረስ ብንቆይ በደለኞች እንሆናለን፤ ኑ፥ እንሂድ፤ ለንጉሥ ቤተ ሰብ እንናገር ተባባሉ።
10 ፤ መጥተውም። ወደ ሶርያውያን ሰፈር መጣን፥ እነሆም፥ ፈረሶችና አህዮች ታስረው፥ ድንኳኖችም ተተክለው ነበር እንጂ ሰው አልነበረም፥ የሰውም ድምፅ አልነበረም ብለው ወደ ከተማይቱ ደጅ ጠባቂ ጮኹ።
11 ፤ የደጁም ጠባቂዎች ጠሩ፥ ለንጉሡም ቤት ውስጥ አወሩ።
12 ፤ ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ባሪያዎቹን። ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ እንደ ተራብን ያውቃሉ፤ ስለዚህ። ከከተማይቱ በወጡ ጊዜ በሕይወታቸው እንይዛቸዋለን፥ ወደ ከተማም እንገባለን ብለው በሜዳ ይሸሸጉ ዘንድ ከሰፈሩ ወጥተዋል አላቸው።
13 ፤ ከባሪያዎቹም አንዱ መልሶ። በከተማ ከቀሩት ፈረሶች አምስት ይውሰዱ፤ እነሆ፥ እንደ ቀሩት እንደ እስራኤል ወገን ሁሉ ናቸው፤ እነሆ፥ እንዳለቁ እንደ እስራኤል ወገን ሁሉ ናቸው፤ እንስደድም፥ እንይም አለ።
14 ፤ ሁለትም ሰረገሎች ከፈረሶች ጋር ወሰዱ፤ ንጉሡም። ሄዳችሁ እዩ ብሎ ከሶርያውያን ሠራዊት በኋላ ላከ።
15 ፤ በኋላቸው እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ሄዱ፤ እነሆም፥ ሶርያውያን ሲሸሹ የጣሉት ልብስና ዕቃ መንገዱን ሁሉ ሞልቶ ነበር። መልእክተኞችም ተመልሰው ለንጉሡ ነገሩት።
16 ፤ ሕዝቡም ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለትም መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ተሸመተ።
17 ፤ ንጉሡም ያን እጁን ይደግፈው የነበረውን አለቃ በሩን ይጠብቅ ዘንድ አቆመው። ሕዝቡም በበሩ ረገጠው፥ ንጉሡም ወደ እርሱ በወረደ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ተናገረው ሞተ።
18 ፤ የእግዚአብሔርም ሰው ለንጉሡ። ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር ሁለት መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል፥ አንድም መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል ይሸመታል ብሎ እንደ ተናገረው ነገር እንዲሁ ሆነ።
19 ፤ ያም አለቃ ለእግዚአብሔር ሰው መልሶ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን? ብሎ ነበር፤ እርሱም። እነሆ፥ በዓይኖችህ ታየዋለህ፥ ከዚያም አትቀምስም ብሎት ነበር።
20 ፤ እንዲሁም ደረሰበት፤ ሕዝቡም በበሩ ረገጠውና ሞተ።

1 ፤ ኤልሳዕም ልጅዋን ያስነሣላትን ሴት። አንቺ ከቤተ ሰብሽ ጋር ተነሥተሽ ሂጂ፥ በምታገኚውም ስፍራ ተቀመጪ፤ እግዚአብሔር ራብ ጠርቶአል፤ ሰባት ዓመትም በምድር ላይ ይመጣል ብሎ ተናገራት።
2 ፤ ሴቲቱም ተነሥታ እንደ እግዚአብሔር ሰው ቃል አደረገች፤ ከቤተ ሰብዋም ጋር ሄዳ በፍልስጥኤም አገር ሰባት ዓመት ተቀመጠች።
3 ፤ ሰባቱም ዓመት በተፈጸመ ጊዜ ሴቲቱ ከፍልስጥኤም አገር ተመለሰች፤ ስለ ቤትዋና ስለ መሬትዋ ልትጮኽ ወደ ንጉሡ ወጣች።
4 ፤ ንጉሡም ከእግዚአብሔር ሰው ሎሌ ከግያዝ ጋር። ኤልሳዕ ያደረገውን ተአምራት ሁሉ ንገረኝ እያለ ይጫወት ነበር።
5 ፤ እርሱም የሞተውን እንደ አስነሣ ለንጉሡ ሲናገር፥ እነሆ፥ ልጅዋን ያስነሣላት ሴት ስለ ቤትዋና ስለ መሬትዋ ወደ ንጉሥ ጮኸች፤ ግያዝም። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ሴቲቱ ይህች ናት፥ ኤልሳዕም ያስነሣው ልጅዋ ይህ ነው አለ።
6 ፤ ንጉሡም ሴቲቱን ጠየቀ፥ ነገረችውም። ንጉሡም። የነበረላትን ሁሉ፥ መሬትዋንም ከተወች ጀምራ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን የእርሻዋን ፍሬ ሁሉ መልስላት ብሎ ስለ እርስዋ ጃንደረባውን አዘዘ።
7 ፤ ኤልሳዕም ወደ ደማስቆ መጣ፤ የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር ታምሞ ነበር፤ ወሬኞችም። የእግዚአብሔር ሰው ወደዚህ መጥቶአል ብለው ነገሩት።
8 ፤ ንጉሡም አዛሄልን። ገጸ በረከት በእጅህ ወስደህ የእግዚአብሔርን ሰው ልትገናኝ ሂድ፤ በእርሱም አፍ። ከዚህ በሽታ እድናለሁን? ብለህ እግዚአብሔርን ጠይቅ አለው።
9 ፤ አዛሄልም ሊገናኘው ሄደ፥ ከእርሱም ጋር ከደማስቆ መልካሙን ነገር ሁሉ የአርባ ግመል ጭነት ገጸ በረከት ወሰደ፤ መጥቶም በፊቱ ቆመና። ልጅህ የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር። ከዚህ በሽታ እድናለሁን? ሲል ወደ አንተ ልኮኛል አለ።
10 ፤ ኤልሳዕም። ሂድ፥ መዳንስ ትድናለህ በለው፤ ነገር ግን እንዲሞት እግዚአብሔር አሳይቶኛል አለው።
11 ፤ እስኪያፍርም ድረስ ትኵር ብሎ ተመለከተው፤ የእግዚአብሔርም ሰው አነባ።
12 ፤ አዛሄልም። ጌታዬ ለምን ያነባል? አለ። እርሱም። በእስራኤል ልጆች ላይ የምታደርገውን ክፋት ስለማውቅ ነው፤ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፥ ጕልማሶቻቸውንም በሰይፍ ትገድላለህ፥ ሕፃናቶቻቸውንም ትፈጠፍጣለህ፥ እርጉዞቻቸውንም ትቀድዳለህ አለው።
13 ፤ አዛሄልም። ይህን ታላቅ ነገር አደርግ ዘንድ እኔ ውሻ ባሪያህ ምንድር ነኝ? አለ። ኤልሳዕም። አንተ በሶርያ ላይ ንጉሥ እንድትሆን እግዚአብሔር አሳይቶኛል አለው።
14 ፤ ከኤልሳዕም ርቆ ወደ ጌታው መጣ፤ እርሱም። ኤልሳዕ ምን አለህ? አለው።
15 ፤ እርሱም። እንድትፈወስ ነገረኝ አለው። በነጋውም ለሐፍ ወስዶ በውኃ ነከረው በፊቱም ላይ ሸፈነው፥ ሞተም። አዛሄልም በፋንታው ነገሠ።
16 ፤ በእስራኤልም ንጉሥ በአክዓብ ልጅ በኢዮራም በአምስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም ነገሠ።
17 ፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ።
18 ፤ የአክዓብንም ልጅ አግብቶ ነበርና የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ።
19 ፤ ነገር ግን ለእርሱና ለልጆቹ ለዘመኑ ሁሉ መብራት ይሰጠው ዘንድ ተስፋ እንደ ሰጠ፥ ስለ ባሪያው ስለ ዳዊት እግዚአብሔር ይሁዳን ያጠፋ ዘንድ አልወደደም።
20 ፤ በእርሱም ዘመን ኤዶምያስ ለይሁዳ እንዳይገብር ሸፈተ፥ በላያቸውም ንጉሥ አነገሡ።
21 ፤ ኢዮራምም ከሰረገሎቹ ሁሉ ጋር ወደ ጸዒር አለፈ፤ በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሰረገሎቹን አለቆች ከብበው የነበሩትን የኤዶምያስን ሰዎች መታ፤ ሕዝቡ ግን ወደ ድንኳኑ ሸሸ።
22 ፤ ኤዶምያስ ግን ለይሁዳ እንዳይገብር እስከ ዛሬ ድረስ ሸፈተ። በዚያም ዘመን ደግሞ ልብና ሸፈተ።
23 ፤ የተረፈውም የኢዮራም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
24 ፤ ኢዮራምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በፋንታውም ልጁ አካዝያስ ነገሠ።
25 ፤ በእስራኤል ንጉሥ በአክዓብ ልጅ በኢዮራም በአሥራ ሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ነገሠ።
26 ፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜ አካዝያስ የሀያ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አንድ ዓመት ነገሠ። እናቱም ጎቶልያ የተባለች የእስራኤል ንጉሥ የዘንበሪ ልጅ ነበረች።
27 ፤ በአክዓብም ቤት መንገድ ሄደ፥ እንደ አክዓብም ቤት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ ለአክዓብ ቤት አማች ነበረና።
28 ፤ ከአክዓብም ልጅ ከኢዮራም ጋር የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን በሬማት ዘገለዓድ ሊጋጠም ሄደ፤ ሶርያውንም ኢዮራምን አቆሰሉት።
29 ፤ ንጉሡም ኢዮራም ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን በሬማት ያቈሰሉትን ቍስል ይታከም ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ። የአክዓብም ልጅ ኢዮራም ታምሞ ነበርና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ሊያየው ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።

1 ፤ ነቢዩም ኤልሳዕ ከነቢያት ልጆች አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለው። ወገብህን ታጥቀህ ይህን የዘይት ማሰሮ በእጅህ ያዝ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድም ሂድ።
2 ፤ በዚያም በደረስህ ጊዜ የናሜሲን ልጅ የኢዮሣፍጥን ልጅ ኢዩን ታገኘዋለህ፤ ገብተህም ከወንድሞቹ መካከል አስነሣው፥ ወደ ጓዳም አግባው።
3 ፤ የዘይቱንም ማሰሮ ይዘህ በራሱ ላይ አፍስሰውና። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ በለው፤ በሩንም ከፍተህ ሽሽ፥ አትዘግይም።
4 ፤ እንዲሁም ጕልማሳው ነቢይ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሄደ።
5 ፤ በገባም ጊዜ፥ እነሆ፥ የሠራዊት አለቆች ተቀምጠው ነበር፤ እርሱም። አለቃ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ነገር አለኝ አለ። ኢዩም። ከማንኛችን ጋር ነው? አለ። እርሱም። አለቃ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ነው አለ።
6 ፤ ተነሥቶም ወደ ቤቱ ገባ፤ ዘይቱንም በራሱ ላይ አፍስሶ እንዲህ አለው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ።
7 ፤ የባሪያዎቼን የነቢያትን ደም፥ የእግዚአብሔርንም ባሪያዎች ሁሉ ደም ከኤልዛቤል እጅ እበቀል ዘንድ የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ።
8 ፤ የአክዓብም ቤት ሁሉ ይጠፋል፤ በእስራኤልም ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ ከአክዓብ አጠፋለሁ።
9 ፤ የአክዓብንም ቤት እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፥ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።
10 ፤ ኤልዛቤልንም በኢይዝራኤል እርሻ ውሾች ይበሉአታል፥ የሚቀብራትም አታገኝም። በሩንም ከፍቶ ሸሸ።
11 ፤ ኢዩም ወደ ጌታው ባሪያዎች ወጣ፤ እነርሱም። ደኅና ነውን? ይህ እብድ ለምን መጣብህ? አሉት። እርሱም። ሰውዮውንና ነገሩን ታውቃላችሁ አላቸው።
12 ፤ እነርሱም። ሐሰት ነው፤ ንገረን አሉት፤ እርሱም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ ብሎ እንዲህ እንዲህ ነገረኝ አላቸው።
13 ፤ ሁሉም ፈጥነው ልብሳቸውን ወሰዱ፥ በሰገነቱ መሰላል እርከን ላይ ከእግሩ በታች አነጠፉት፥ ቀንደ መለከትም እየነፉ፥ ኢዩ ነግሦአል አሉ።
14 ፤ እንዲሁም የናሜሲ ልጅ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዩ በኢዮራም ላይ ተማማለ። ኢዮራምና የእስራኤል ልጆች ሁሉ ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል የተነሣ ሬማት ዘገለዓድን ይጠብቁ ነበር።
15 ፤ ንጉሡ ኢዮራም ግን ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን ያቈሰሉትን ቍስል ይታከም ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ተመልሶ ነበር። ኢዩም። ልባችሁስ ከእኔ ጋር ከሆነ በኢይዝራኤል እንዳያወራ ማንም ከከተማ ኰብልሎ አይውጣ አለ።
16 ፤ ኢዮራምም በዚያ ታምሞ ተኝቶ ነበርና ኢዩ በሰረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ። የይሁዳም ንጉሥ አካዝያስ ኢዮራምን ለማየት ወርዶ ነበር።
17 ፤ በኢይዝራኤልም ግንብ ላይ የቆመው ሰላይ የኢዩ ጭፍራ ሲመታ አይቶ። ጭፍራ አያለሁ አለ። ኢዮራምም። የሚገናኘው ፈረሰኛ ላክ፥ እርሱም። ሰላም ነውን? ይበለው አለ።
18 ፤ ፈረሰኛውም ሊገናኘው ሄዶ። ንጉሡ እንዲህ ይላል። ሰላም ነውን? አለ። ኢዩም። አንተ ከሰላም ጋር ምን አለህ? ወደ ኋላዬ አልፈህ ተከተለኝ አለ። ሰላዩም። መልእክተኛው ደረሰባቸው፥ ነገር ግን አልተመለሰም ብሎ ነገረው።
19 ፤ ሁለተኛም ፈረሰኛ ሰደደ፥ ወደ እነርሱም ደርሶ። ንጉሡ እንዲህ ይላል። ሰላም ነውን?አለ። ኢዩም። አንተ ከሰላም ጋር ምን አለህ? ወደ ኋላዬ አልፈህ ተከተለኝ አለ።
20 ፤ ሰላዩም። ደረሰባቸው፥ ነገር ግን አልተመለሰም፤ በችኰላ ይሄዳልና አካሄዱ እንደ ናሜሲ ልጅ እንደ ኢዩ አካሄድ ነው ብሎ ነገረው።
21 ፤ ኢዮራምም። ሰረገላ አዘጋጁ አለ፤ ሰረገላውንም አዘጋጁለት። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮራም የይሁዳም ንጉሥ አካዝያስ በሰረገሎቻቸው ተቀምጠው ወጡ፥ ኢዩንም ሊገናኙት ሄዱ፤ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ እርሻ ውስጥ አገኙት።
22 ፤ ኢዮራምም ኢዩን ባየ ጊዜ። ኢዩ ሆይ፥ ሰላም ነውን? አለ። እርሱም። የእናትህ የኤልዛቤል ግልሙትናዋና መተትዋ ሲበዛ ምን ሰላም አለ? ብሎ መለሰ።
23 ፤ ኢዮራምም መልሶ ነዳና ሸሸ፥ አካዝያስንም። አካዝያስ ሆይ፥ ዓመፅ ነው አለው።
24 ፤ ኢዩም በእጁ ቀስቱን ለጠጠ፥ ኢዮራምንም በጫንቃው መካከል ወጋው፤ ፍላጻውም በልቡ አለፈ፥ ወደ ሰረገላውም ውስጥ ወደቀ።
25 ፤ ኢዩም አለቃውን ቢድቃርን እንዲህ አለው። አንሥተህ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ እርሻ ጣለው፥ አንተና እኔ ጎን ለጎን በፈረስ ተቀምጠን አባቱን አክዓብን በተከተልን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ይህን መከራ እንደ ተናገረበት አስብ።
26 ፤ በእውነት የናቡቴንና የልጆቹን ደም ትናንትና አይቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚህም እርሻ እመልስብሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ቃል ወስደህ በእርሻው ውስጥ ጣለው።
27 ፤ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ያንን ባየ ጊዜ በአትክልት ቤት መንገድ ሸሸ። ኢዩም። ይህን ደግሞ በሰረገላው ላይ ውጉት እያለ ተከተለው፤ በይብለዓምም አቅራቢያ ባለችው በጉር ዐቀበት ላይ ወጉት። ወደ መጊዶም ሸሸ፥ በዚያም ሞተ።
28 ፤ ባሪያዎቹም በሰረገላው ጭነው ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፥ በዳዊትም ከተማ በመቃብሩ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት።
29 ፤ በአክዓብም ልጅ በኢዮራም በአሥራ አንደኛው ዓመት አካዝያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ።
30 ፤ ኢዩም ወደ ኢይዝራኤል መጣ፤ ኤልዛቤልም በሰማች ጊዜ ዓይንዋን ተኳለች፥ ራስዋንም አስጌጠች፥ በመስኮትም ዘልቃ ትመለከት ነበር።
31 ፤ ኢዩም በበሩ ሲገባ። ጌታውን የገደለ ዘምሪ ሆይ፥ ሰላም ነውን? አለችው።
32 ፤ ፊቱንም ወደ መስኮቱ አንሥቶ። ከእኔ ጋር ማን ነው? አለ። ሁለት ሦስትም ጃንደረቦች ወደ እርሱ ተመለከቱ።
33 ፤ እርሱም። ወደ ታች ወርውሩአት አለ፤ ወረወሩአትም፥ ደምዋም በግንቡና በፈረሶቹ ላይ ተረጨ፥ ረገጡአትም።
34 ፤ በገባም ጊዜ በላ ጠጣም፤ ከዚያም በኋላ። ይህችን የተረገመች እዩ፤ የንጉሥ ልጅ ናትና ቅበሩአት አለ።
35 ፤ ሊቀብሩአትም በሄዱ ጊዜ ከአናትዋና ከእግርዋ ከመዳፍም በቀር ምንም አላገኙም።
36 ፤ ተመልሰውም ነገሩት፤ እርሱም። በባሪያው በቴስብያዊ ኤልያስ። በኢይዝራኤል እርሻ የኤልዛቤልን ሥጋ ውሾች ይበላሉ፤
37 ፤ የኤልዛቤልም ሬሳ በኢይዝራኤል እርሻ መሬት ላይ እንደ ፍግ ይሆናልና ማንም። ይህች ኤልዛቤል ናት ይል ዘንድ አይችልም ብሎ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው አለ።

1 ፤ ለአክዓብም በሰማርያ ሰባ ልጆች ነበሩት፤ ኢዩም ደብዳቤ ጻፈ፤ የአክዓብን ልጆች ለሚያሳድጉ ለሰማርያ ታላላቆችና ሽማግሌዎች።
2 ፤ ይህ ደብዳቤ አሁን በደረሳችሁ ጊዜ የጌታችሁ ልጆች ሰረገሎችና ፈረሶችም የተመሸገችም ከተማ መሣሪያዎችም በእናንተ ዘንድ አሉና፥
3 ፤ ከጌታችሁ ልጆች ደስ የሚያሰኛችሁንና የሚሻላችሁን ምረጡ፥ በአባቱም ዙፋን አስቀምጡት፥ ስለ ጌታችሁም ቤት ተዋጉ ብሎ ወደ ሰማርያ ሰደደ፤
4 ፤ እነርሱ ግን እጅግ ፈርተው። እነሆ፥ ሁለቱ ነገሥታት በፊቱ ይቆሙ ዘንድ አልቻሉም፤ እኛስ እንዴት እንቆማለን? አሉ።
5 ፤ የቤቱ አለቃ፥ የከተማይቱም አለቃ፥ ሽማግሌዎችና ልጆቹን የሚያሳድጉ። እኛ ባሪያዎችህ ነን፥ ያዘዝኸንም ሁሉ እናደርጋለን፤ ንጉሥም በላያችን አናነግሥም፤ የምትወድደውን አድርግ ብለው ወደ ኢዩ ላኩ።
6 ፤ ሁለተኛም። ወገኖቼስ እንደ ሆናችሁ፥ ነገሬንም ከሰማችሁ፥ የጌታችሁን ልጆች ራስ ቍረጡ፥ ነገም በዚህ ሰዓት ወደ ኢይዝራኤል ወደ እኔ ይዛችሁ ኑ ብሎ ደብዳቤ ጻፈላቸው። የንጉሡም ልጆች ሰባው ሰዎች በሚያሳድጓቸው በከተማይቱ ታላላቆች ዘንድ ነበሩ።
7 ፤ ደብዳቤውም በደረሳቸው ጊዜ የንጉሡን ልጆች ሰባውን ሰዎች ይዘው ገደሉአቸው፤ ራሳቸውንም በቅርጫት አድርገው ወደ እርሱ ወደ ኢይዝራኤል ላኩ።
8 ፤ መልእክተኛም መጥቶ። የንጉሡን ልጆች ራስ ይዘው መጥተዋል ብሎ ነገረው። እርሱም። እስከ ነገ ድረስ በበሩ አደባባይ ሁለት ክምር አድርጋችሁ አኑሩአቸው አለ።
9 ፤ በነጋውም ወጥቶ ቆመ፥ ሕዝቡንም ሁሉ። እናንተ ንጹሐን ናችሁ፤ እነሆ፥ ጌታዬን የወነጀልሁ የገደልሁትም እኔ ነኝ፤ እነዚህንስ ሁሉ የገደለ ማን ነው?
10 ፤ እግዚአብሔር በአክዓብ ቤት ላይ ከተናገረው ከእግዚአብሔር ቃል በምድር ላይ አንዳች እንዳይወድቅ አሁን እወቁ፤ እግዚአብሔር በባሪያው በኤልያስ የተናገረውን አድርጎአል አላቸው።
11 ፤ ኢዩም ከአክዓብ ቤት የቀረውን ሁሉ፥ ታላላቆቹንም ሁሉ፥ ወዳጆቹንና ካህናቱን ማንም ሳይቀር በኢይዝራኤል ገደላቸው።
12 ፤ ተነሥቶም ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በመንገድም ወዳለው ወደ በግ ጠባቂዎች ቤት በደረሰ ጊዜ፥
13 ፤ ኢዩ ከይሁዳ ንጉሥ ከአካዝያስ ወንድሞች ጋር ተገናኝቶ። እናንተ እነማን ናችሁ? አለ። እነርሱም። እኛ የአካዝያስ ወንድሞች ነን፤ የንጉሡንና የእቴጌይቱን ልጆች ደኅንነት ለመጠየቅ እንወርዳለን አሉት።
14 ፤ እርሱም። በሕይወታቸው ያዙአቸው አለ። ያዙአቸውም፥ በበግ ጠባቂዎችም ቤት አጠገብ ባለው ጕድጓድ አርባ ሁለቱን ሰዎች ገደሉአቸው፤ ማንንም አላስቀረም።
15 ፤ ከዚያም በሄደ ጊዜ የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን ተገናኘው፤ ደኅንነቱንም ጠይቆ። ልቤ ከልብህ ጋር እንደ ሆነ ያህል ልብህ ከልቤ ጋር በቅንነት ነውን? አለው፤ ኢዮናዳብም። እንዲሁ ነው አለው። ኢዩም። እንዲሁ እንደ ሆነስ እጅህን ስጠኝ አለ። እጁንም ሰጠው፤ ወደ ሰረገላውም አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጠውና።
16 ፤ ከእኔ ጋር ና፥ ለእግዚአብሔርም መቅናቴን እይ አለው። በሰረገላውም አስቀመጠው።
17 ፤ ወደ ሰማሪያም በመጣ ጊዜ ለኤልያስ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስኪያጠፋው ድረስ ከአክዓብ በሰማርያ የቀረውን ሁሉ ገደለ።
18 ፤ ኢዩም ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ። አክዓብ በኣልን በጥቂቱ አመለከው፤ ኢዩ ግን በብዙ ያመልከዋል።
19 ፤ አሁንም የባኣልን ነቢያት ሁሉ፥ አገልጋዮቹንም ሁሉ፥ ካህናቱንም ሁሉ ወደ እኔ ጥሩ፤ ማንም አይቅር፤ ለባኣል ታላቅ መሥዋዕት አቀርባለሁ፥ የቀረውም ሁሉ በሕይወት አይኖርም አላቸው። ኢዩም የበኣልን አገልጋዮች ያጠፋ ዘንድ በተንኰል ይህን አደረገ።
20 ፤ ኢዩም። ለበኣል ዋና ጉባኤ ቀድሱ አለ።
21 ፤ እነርሱም አወጁ። ኢዩም ወደ እስራኤል ሁሉ ላከ፥ የበኣልም አገልጋዮች ሁሉ መጡ፤ ሳይመጣ የቀረ አንድ ስንኳ አልነበረም። ወደ በኣልም ቤት ገቡ፥ የበኣልም ቤት ከዳር እስከ ዳር ድረስ ሞልቶ ነበር፤
22 ፤ ዕቃ ቤቱንም። ለበኣል አገልጋዮች ሁሉ ልብስ አውጣ አለው።
23 ፤ ልብሱንም አወጣላቸው። ኢዩም የሬካብም ልጅ ኢዮናዳብ ወደ በኣል ቤት ገቡ። የበኣልንም አገልጋዮች። መርምሩ፥ ከበኣል አገልጋዮች ብቻ በቀር እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ወገን በእናንተ ዘንድ አንድ እንኳ እንዳይኖር ተመልከቱ አላቸው።
24 ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕትም ያቀረቡ ዘንድ ገቡ፤ ኢዩም። በእጃችሁ አሳልፌ ከምሰጣችሁ ሰዎች አንድ ሰው ያመለጠ እንደ ሆነ ነፍሱ በዚያ ነፍስ ፋንታ ትሆናለች ብሎ በውጪ ሰማንያ ሰዎችን አዘጋጅቶ ነበር።
25 ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አቅርበው በፈጸሙ ጊዜ ኢዩ ዘበኞቹንና አለቆቹን። ግቡና ግደሉአቸው፤ አንድም አይውጣ አላቸው። በሰይፍም ስለት ገደሉአቸው፤ ዘበኞችና አለቆችም ወደ ውጭ ጣሉአቸው፥ ወደ በኣልም ቤት ከተማ ሄዱ።
26 ፤ ከበኣልም ቤት ሐውልቶቹን አወጡ አቃጠሉአቸውም።
27 ፤ የበኣልን ሐውልት ቀጠቀጡ፥ የበኣልንም ቤት አፈረሱ፥ እስከ ዛሬም ድረስ የውዳቂ መጣያ አደረጉት።
28 ፤ እንዲሁም ኢዩ በኣልን ከእስራኤል አጠፋ።
29 ፤ ነገር ግን እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት፥ በቤቴልና በዳን ከነበሩት ከወርቁ እምቦሶች፥ ኢዩ አልራቀም።
30 ፤ እግዚአብሔርም ኢዩን። በፊቴ ቅን ነገር አድርገሃልና፥ በልቤም ያለውን ሁሉ በአክዓብ ቤት ላይ አድርገሃልና ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ አለው።
31 ፤ ኢዩ ግን በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ሕግ በፍጹም ልቡ ይሄድ ዘንድ አልተጠነቀቀም፤ እስራኤልንም ካሳተው ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም።
32 ፤ በዚያም ወራት እግዚአብሔር እስራኤልን ይከፋፍላቸው ዘንድ ጀመረ፤ አዛሄልም በእስራኤል ዳርቻ ሁሉ መታቸው።
33 ፤ በዮርዳኖስ ምሥራቅ ያለውን የገለዓድን አገር ሁሉ፥ በአርኖን ወንዝ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ የጋድንና የሮቤልን የምናሴንም አገር፥ ገለዓድንና ባሳንን መታ።
34 ፤ የቀረውም የኢዩ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ ጭከናውም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
35 ፤ ኢዩም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ቀበሩት። በፋንታውም ልጁ ኢዮአካዝ ነገሠ።
36 ፤ ኢዩም በሰማርያ በእስራኤል ላይ የነገሠበት ዘመን ሀያ ስምንት ዓመት ነበረ።

1 ፤ የአካዝያስም እናት ጎቶልያ ልጅዋ እንደ ሞተ ባየች ጊዜ ተነሥታ የመንግሥትን ዘር ሁሉ አጠፋች።
2 ፤ የንጉሡ የኢዮራም ልጅ የአካዝያስ እኅት ዮሳቤት የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ወስዳ ከተገደሉት ከንጉሥ ልጆች መካከል ሰረቀችው፤ እርሱንና ሞግዚቱንም ወደ እልፍኝ ወሰደች፥ እንዳይገደልም ከጎቶልያ ሸሸጉት።
3 ፤ በእርስዋም ዘንድ ተሸሸጎ በእግዚአብሔር ቤት ስድስት ዓመት ያህል ተቀመጠ። ጎቶልያም በምድር ላይ ነገሠች።
4 ፤ በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ ልኮ በካራውያንና በዘበኞች ላይ ያሉትን የመቶ አለቆች ወሰደ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት አገባቸው፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በእግዚአብሔርም ቤት አማላቸው፥ የንጉሡንም ልጅ አሳያቸው።
5 ፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። እንዲህ አድርጉ፤ በሰንበት ቀን ከምትገቡት ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ የንጉሡን ቤት ዘብ ጠብቁ፤
6 ፤ ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ በሱር በር ሁኑ፤ አንዱም እጅ ከዘበኞች ቤት በኋላ ባለው በር ሁኑ፤ ቤቱንም ጠብቁ፥ ከልክሉም፤
7 ፤ ከእናንተም በሰንበት ቀን የምትወጡት ሁለቱ እጅ በንጉሥ ዙሪያ ሆናችሁ የእግዚአብሔርን ቤት ጠብቁ።
8 ፤ ንጉሡንም በዙሪያው ክበቡት፥ የጦር ዕቃችሁም በእጃችሁ ይሁን፤ በሰልፋችሁ መካከል የሚገባ ይገደል፤ ንጉሡም በወጣና በገባ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሁኑ።
9 ፤ መቶ አለቆችም ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ ከእነርሱም እያንዳንዱ በሰንበት ይገቡ የነበሩትን፥ በሰንበቱም ይወጡ የነበሩትን ሰዎች ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ።
10 ፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሡን የዳዊትን ጋሻና ጦር ሁሉ ለመቶ አለቆች ሰጣቸው።
11 ፤ ዘበኞቹም ሁሉ እያንዳንዳቸው የጦር ዕቃቸውን በእጃቸው ይዘው በንጉሡ ዙሪያ ከቤቱ ቀኝ እስከ ቤቱ ግራ ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ ቆሙ።
12 ፤ የንጉሡንም ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነበት፥ ምስክሩንም ሰጠው፤ ቀብተውም ንጉሥ አደረጉትና። ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ እያሉ እጃቸውን አጨበጨቡ።
13 ፤ ጎቶልያም የሠራዊቱንና የሕዝቡን ድምፅ በሰማች ጊዜ ወደ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ቤት መጣች።
14 ፤ እነሆም፥ ንጉሡ እንደ ተለመደው በዓምዱ አጠገብ ቆሞ፥ ከንጉሡም ጋር አለቆችና መለከተኞች ቆመው አየች፤ የአገሩም ሕዝብ ሁል ደስ ብሎአቸው ቀንደ መለከት ይነፉ ነበር። ጎቶልያም ልብስዋን ቀድዳ። ዓመፅ ነው፥ ዓመፅ ነው ብላ ጮኸች።
15 ፤ ካህኑም ዮዳሄ በጭፍራው ላይ የተሾሙትን የመቶ አለቆች። ወደ ሰልፉ መካከል አውጡአት፤ የሚከተላትንም በሰይፍ ግደሉት ብሎ አዘዛቸው፤ ካህኑ። በእግዚአብሔር ቤት አትገደል ብሎአልና።
16 ፤ እጃቸውንም በእርስዋ ላይ ጫኑ፥ በፈረሱም መግቢያ መንገድ ወደ ንጉሥ ቤት ወሰዱአት፥ በዚያም ገደሉአት።
17 ፤ ዮዳሄም የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔርና በንጉሡ በሕዝቡም መካከል ቃል ኪዳን አደረገ፤ ደግሞም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን አደረገ።
18 ፤ የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ወደ በኣል ቤት ሄደው አፈረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን አደቀቁ፥ የበኣልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት። ካህኑም ለእግዚአብሔር ቤት አስተዳዳሪዎችን ሾመ።
19 ፤ መቶ አለቆቹንና ካራውያንንም፥ ዘበኞችንና የአገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፤ ንጉሡንም ከእግዚአብሔር ቤት አወረዱት፥ በዘበኞችም በር መንገድ ወደ ንጉሡ ቤት አመጡት፤ በነገሥታቱም ዙፋን ተቀመጠ።
20 ፤ የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፥ ከተማይቱም ጸጥ አለች። ጎቶልያንም በንጉሡ ቤት አጠገብ በሰይፍ ገደሉአት።

1 ፤ ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ።
2 ፤ በኢዩ በሰባተኛው ዓመት ኢዮአስ መንገሥ ጀመረ፥ በኢየሩሳሌምም አርባ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች።
3 ፤ ካህኑ ዮዳሄም ያስተምረው በነበረ ዘመን ሁሉ ኢዮአስ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
4 ፤ ነገር ግን በኮረብቶቹ ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር።
5 ፤ ኢዮአስም ካህናቱን። ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚገባውን የተቀደሰውን ገንዘብ ሁሉ፥ ስለ ነፍሱም ዋጋ የሚቀርበውን ገንዘብ፥ በልባቸውም ፈቃድ ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚያመጡትን ገንዘብ ሁሉ፥
6 ፤ ካህናቱ እያንዳንዱ ሰው ከሚያመጣው ይውሰዱ በመቅደስም ውስጥ የተናዱትን ይጠግኑበት አላቸው።
7 ፤ ነገር ግን እስከ ንጉሡ እስከ ኢዮአስ እስከ ሀያ ሦስተኛው ዓመት ድረስ በመቅደሱ ውስጥ የተናዱትን ካህናቱ አልጠገኑትም ነበር።
8 ፤ ኢዮአስም ካህኑን ዮዳሄንና ካህናቱን ጠርቶ። በመቅደሱ ውስጥ የተናዱትን ስፍራዎች ስለ ምን አትጠግኑአቸውም? ከእንግዲህ ወዲያ ገንዘቡ ለቤቱ መጠገኛ ይሰጥ እንጂ ከሚያመጡት ሰዎች አትቀበሉ አላቸው።
9 ፤ ካህናቱም። ከሕዝቡ ገንዘቡን አንወስድም፥ በቤቱም ውስጥ የተናዱትን አንጠግንም ብለው እሺ አሉ።
10 ፤ ካህኑ ዮዳሄ ግን ሣጥን ወስዶ መክደኛውን ነደለው፥ በመሠዊያውም አጠገብ ወደ እግዚአብሔር ቤት በሚገቡበት መግቢያ በስተ ቀኝ አኖረው፤ ደጁንም የሚጠብቁ ካህናት ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጣውን ገንዘብ ሁሉ ያኖሩበት ነበር።
11 ፤ በሣጥንም ውስጥ ብዙ ገንዘብ መኖሩን ባዩ ጊዜ የንጉሡ ጸሐፊና የካህናቱ አለቃ ይመጡ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን ቈጥረው በከረጢት ውስጥ ያኖሩት ነበር።
12 ፤ የተመዘነውንም ገንዘብ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት በተሾሙት እጅ ይሰጡ ነበር።
13 ፤ የተናደውን የእግዚአብሔርን ቤት ለመጠገን መክፈል ለሚያሻው ሁሉ ድንጋይና እንጨት ይገዙ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቤት ለሚሠሩ አናጢዎችና ሠራተኞች ግንበኞችና ድንጋይ ወቃሪዎች ይሰጡት ነበር።
14 ፤ ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ቤት ከሚመጣው ገንዘብ ለእግዚአብሔር ቤት የሚሆኑ የብር ጽዋዎችና ጕጠቶች ድስቶችም መለከቶችም የወርቅና የብር ዕቃዎችም አልተሠሩም ነበር።
15 ፤ ነገር ግን ለሚሠሩት ይሰጡት ነበር፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ጠገኑበት።
16 ፤ ለሠራተኞችም ይከፍሉ ዘንድ ገንዘቡን የሚወስዱትን ሰዎች አይቆጣጠሩአቸውም ነበር፤ በታማኝነት ይሠሩ ነበርና።
17 ፤ ስለ በደልና ሰለ ኃጢአት መሥዋዕት የቀረበውም ገንዘብ ለካህናት ነበረ እንጂ ወደ እግዚአብሔር ቤት አያገቡትም ነበር።
18 ፤ በዚያም ወራት የሶርያ ንጉሥ አዛሄል ወጥቶ ጌትን ወጋ፥ ያዘውም፤ አዛሄልም ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት ፊቱን አቀና።
19 ፤ የይሁዳም ንጉሥ ኢዮአስ አባቶቹ የይሁዳ ነገሥታት ኢዮሣፍጥና ኢዮራም አካዝያስም የቀደሱትን ቅዱስ ነገር፥ እርሱም የቀደሰውን፥ በእግዚአብሔርም ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የተገኘውን ወርቅ ሁሉ ወሰደ፥ ወደ ሶርያም ንጉሥ ወደ አዛሄል ላከው። እርሱም ከኢየሩሳሌም ተመለሰ።
20 ፤ የቀረውም የኢዮአስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
21 ፤ ባሪያዎቹም ተነሥተው ዐመፁበት፥ ወደ ሲላ በሚወርደውም መንገድ በሚሎ ቤት ገደሉት። [..]፤ ባሪያዎቹም የሰምዓት ልጅ ዮዘካርና የሾሜር ልጅ ዮዛባት መቱት፥ ሞተም፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ ልጁም አሜስያስ በፋንታው ነገሠ።

1 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በአካዝያስ ልጅ በኢዮአስ በሀያ ሦስተኛው ዓመት የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ አሥራ ሰባትም ዓመት ነገሠ።
2 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፥ እስራኤልንም ያሳተውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን ኃጢአት ተከተለ፤ ከእርስዋም አልራቀም።
3 ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በዘመኑም ሁሉ በሶርያው ንጉሥ በአዛሄል እጅ፥ በአዛሄልም ልጅ በወልደ አዴር እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር።
4 ፤ ኢዮአካዝም እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን ያስጨነቀበትን ጭንቀት አይቶአልና ሰማው።
5 ፤ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ታዳጊ ሰጠ፥ ከሶርያውያንም እጅ ዳኑ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ ቀድሞው ጊዜ በድንኳናቸው ተቀመጡ።
6 ፤ ነገር ግን በእርስዋ ሄዱ እንጂ እስራኤልን ካሳተው ከኢዮርብዓም ቤት ኃጢአት አልራቁም፤ ደግሞም የማምለኪያ ዐፀድ በሰማርያ ቆሞ ቀረ።
7 ፤ ለኢዮአካዝም ከአምሳ ፈረሰኞች፥ ከአሥርም ሰረገሎች፥ ከአሥር ሺህም እግረኞች በቀር ሕዝብ አልቀረለትም፤ የሶርያ ንጉሥ አጥፍቶአቸዋልና፥ በአውድማም እንዳላ ዕብቅ አድቅቆአቸዋልና።
8 ፤ የቀረውም የኢዮአካዝ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጭከናውም፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
9 ፤ ኢዮአካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ቀበሩት፤ ልጁም ዮአስ በፋንታው ነገሠ።
10 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ አሥራ ስድስትም ዓመት ነገሠ።
11 ፤ በእግዚአብሔር ፊት ክፋ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን በሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት ሁሉ ሄደ እንጂ ከእርስዋ አልራቀም።
12 ፤ የቀረውም የዮአስ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ከይሁዳም ከአሜስያስ ጋር የተዋጋበት ጭከና፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
13 ፤ ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ ኢዮርብዓምም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ።
14 ፤ ኤልሳዕም በሚሞትበት በሽታ ታመመ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወደ እርሱ ወርዶ በፊቱ አለቀሰና። አባቴ ሆይ፥ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች አለ።
15 ፤ ኤልሳዕም። ቀስትና ፍላጻዎች ውሰድ አለው፤ ቀስቱንና ፍላጻዎችንም ወሰደ።
16 ፤ የእስራኤልንም ንጉሥ። እጅህን በቀስቱ ላይ ጫን አለው። እጁንም ጫነበት፤ ኤልሳዕም እጁን በንጉሡ እጅ ላይ ጭኖ።
17 ፤ የምስራቁን መስኮት ክፈት አለ፤ ከፈተውም። ኤልሳዕም። ወርውር አለ፤ ወረወረውም። እርሱም። የእግዚአብሔር መድኃኒት ፍላጻ ነው፤ በሶርያ ላይ የመድኃኒት ፍላጻ ነው፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ሶርያዊያንን በአፌቅ ትመታለህ አለ።
18 ፤ ደግሞም። ፍላጻዎቹን ውሰድ አለው፤ ወሰዳቸውም። የእስራኤልንም ንጉሥ። ምድሩን ምታው አለው። ሦስት ጊዜም መትቶ ቆመ።
19 ፤ የእግዚአብሔርም ሰው ተቆጥቶ። አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መትተኸው ኖሮ ሶርያን እስክታጠፋው ድረስ በመታኸው ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ሶርያን ትመታለህ አለ።
20 ፤ ኤልሳዕም ሞተ፥ ቀበሩትም። ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ ወደ አገሩ ይገቡ ነበር።
21 ፤ ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ፥ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት፤ የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዮው ድኖ በእግሩ ቆመ።
22 ፤ የሶርያም ንጉሥ አዛሄል በኢዮአካዝ ዘመን ሁሉ እስራኤልን አስጨነቀ፤
23 ፤ እግዚአብሔር ግን ራራላቸው፥ ማራቸውም፥ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ስላደረገውም ቃል ኪዳን እነርሱን ተመለከተ፤ ሊያጠፋቸውም አልወደደም፥ ፈጽሞም ከፊቱ አልጣላቸውም።
24 ፤ የሶርያም ንጉሥ አዛሄል ሞተ፤ ልጁም ወልደ አዴር በፋንታው ነገሠ።
25 ፤ አዛሄልም ከአባቱ ከኢዮአካዝ እጅ በሰልፍ የወሰዳቸውን ከተሞች የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከአዛሄል ልጅ ከወልደ አዴር እጅ ወሰደ። ዮአስም ሦስት ጊዜ መታው፥ የእስራኤልንም ከተሞች መለሰ።

1 ፤ በእስራኤል ንጉሥ በኢዮአካዝ ልጅ በዮአስ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ነገሠ።
2 ፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ። እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
3 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ኢዮአስ እንዳደረገ ሁሉ እንጂ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት አላደረገም።
4 ፤ ነገር ግን በኮረብቶቹ ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር።
5 ፤ መንግሥቱም በጸናለት ጊዜ አባቱን የገደሉትን ባሪያዎች ገደለ።
6 ፤ በሙሴ ሕግ መጽሐፍም እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔርም። ሁሉ በኃጢአቱ ይሙት እንጂ አባቶች በልጆች አይሙቱ፥ ልጆችም በአባቶች አይሙቱ ብሎ እንዳዘዘ የነፍሰ ገዳዮቹን ልጆች አልገደለም።
7 ፤ እርሱም በጨው ሸለቆ ከኤዶምያስ አሥር ሺህ ሰው ገደለ፤ ሴላን በሰልፍ ወስዶ ስምዋን እስከ ዛሬ ድረስ ዮቅትኤል ብሎ ጠራት።
8 ፤ በዚያን ጊዜም አሜስያስ። ና እርስ በርሳችን ፊት ለፊት እንተያይ ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ዮአስ መልእክተኞችን ላከ።
9 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ። የሊባኖስ ኵርንችት፥ ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው ብሎ ወደ ሊባኖስ ዝግባ ላከ፤ የሊባኖስም አውሬ አልፎ ኵርንችቱን ረገጠ።
10 ፤ ኤዶምያስን በእውነት መታህ፥ ልብህንም ከፍ ከፍ አደረግህ፤ በዚያ ተመካ፥ በቤትህም ተቀመጥ፤ አንተ ከይሁዳ ጋር ትወድቅ ዘንድ ስለ ምን መከራ ትሻለህ? ብሎ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ ላከ።
11 ፤ አሜስያስ ግን አልሰማም፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወጣ፥ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ባለች በቤት ሳሚስ እርስ በርሳቸው ተያዩ።
12 ፤ ይሁዳም በእስራኤል ፊት ተመታ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ።
13 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን በቤትሳሚስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር ከኤፍሬም በር ጀምሮ እስክ ማዕዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ አፈረሰ።
14 ፤ ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በእግዚአብሔርም ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ፥ በመያዣም የተያዙትን ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
15 ፤ የቀረውም ያደረገው የዮአስ ነገር፥ ጭከናውም፥ ከይሁዳም ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር እንደ ተዋጋ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
16 ፤ ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮርብዓም በፋንታው ነገሠ።
17 ፤ የይሁዳም ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከዮአስ ሞት በኋላ አሥራ አምስት ዓመት ኖረ።
18 ፤ የቀረውም የአሜስያስ ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
19 ፤ በኢየሩሳሌምም የዓመፅ መሐላ አደረጉበት፥ እርሱም ወደ ለኪሶ ኰበለለ፤ በኋላውም ወደ ለኪሶ ላኩ፥ በዚያም ገደሉት።
20 ፤ በፈረስም ጭነው አመጡት፥ በኢየሩሳሌምም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ።
21 ፤ የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ የአሥራ ስድስት ዓመት ልጅ የነበረውን ዓዛርያስን ወስዶ በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሠው።
22 ፤ ንጉሡም ከአባቶቹ ጋር ካንቀላፋ በኋላ፥ ኤላትን ሠርቶ ወደ ይሁዳ መለሳት።
23 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ ልጅ በአሜስያስ በአሥራ አምስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ አርባ አንድ ዓመትም ነገሠ።
24 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልንም ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት ሁሉ አልራቀም።
25 ፤ የጋትሔፌር በነበረው በአማቴ ልጅ በባሪያው በነቢዩ በዮናስ እጅ እንደ ተናገረው እንደ እስራኤል አምላክ እንደ እግዚአብሔር ቃል የእስራኤልን ድንበር ከሐማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ መለሰ።
26 ፤ የታሰረውና የተለቀቀውም እንደ ጠፋ፥ እስራኤልንም የሚረዳ እንዳልነበረ እግዚአብሔር እጅግ የመረረውን የእስራኤልን ጭንቀት አየ።
27 ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ስም ከሰማይ በታች ይደመስስ ዘንድ አልተናገረም፤ ነገር ግን በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም እጅ አዳናቸው።
28 ፤ የቀረውም የኢዮርብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጭከናውም፥ እንደ ተዋጋም፥ የይሁዳ የነበረውን ደማስቆንና ሐማትን ለእስራኤል እንደ መለሰ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
29 ፤ ኢዮርብዓምም ከአባቶቹ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ዘካርያ በፋንታው ነገሠ።

1 ፤ በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም በሀያ ሰባተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ ልጅ ዓዛርያስ ነገሠ።
2 ፤ መንገሥም በጀመረ ጊዜ የአሥራ ስድስት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
3 ፤ አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
4 ፤ ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር።
5 ፤ እግዚአብሔርም ንጉሡን ቀሠፈው፥ እስከሚሞትበትም ቀን ድረስ ለምጻም ሆነ፥ በተለየ ቤትም ይቀመጥ ነበር፥ የንጉሡም ልጅ ኢዮአታም በንጉሥ ቤት ላይ ሠልጥኖ ለአገሩ ሕዝብ ይፈርድ ነበር።
6 ፤ የቀረውም የዓዛርያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
7 ፤ ዓዛርያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
8 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ስድስት ወር ነገሠ።
9 ፤ አባቶቹም እንዳደረጉት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳታቸው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም።
10 ፤ የኢያቤስም ልጅ ሰሎም ተማማለበት፥ በይብልዓም መትቶ ገደለው፥ በእርሱም ፋንታ ነገሠ።
11 ፤ የቀረውም የዘካርያ ነገር፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
12 ፤ ለኢዩ። ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ ተብሎ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነበረ፤ እንዲሁም ሆነ።
13 ፤ በይሁዳ ንጉሠ በዖዝያን በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት የኢያቤስ ልጅ ሰሎም ነገሠ፤ በሰማርያም አንድ ወር ያህል ነገሠ።
14 ፤ የጋዲም ልጅ ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ወደ ሰማርያ መጣ፥ በሰማርያም የኢያቤስን ልጅ ሰሎምን መታ፥ ገደለውም፤ በእርሱም ፋንታ ነገሠ።
15 ፤ የቀረውም የሰሎም ነገር፥ የተማማለውም ዓመፅ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
16 ፤ በዚያን ጊዜም ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ቲፍሳን በእርስዋም ያሉትን ሁሉ ዳርቻዋንም መታ፤ ይከፍቱለትም ዘንድ አልወደዱምና መታት፤ በእርስዋም የነበሩትን እርጉዞች ሁሉ ቀደዳቸው።
17 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ላይ መንገሥ ጀመረ፤ በሰማርያም አሥር ዓመት ነገሠ።
18 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም።
19 ፤ በዘመኑም የአሦር ንጉሥ ፎሐ በምድሪቱ ላይ ወጣ፤ ምናሔምም መንግሥቱን በእጁ ያጸናለት ዘንድ የፎሐ እጅ ከእርሱ ጋር እንዲሆን አንድ ሺህ መክሊት ብር ሰጠው።
20 ፤ ምናሔምም ብሩን ለአሦር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ በእስራኤል ባለ ጠጎች ሁሉ ላይ በእያንዳንዱ ላይ አምሳ ሰቅል ብር አስገብሮ አወጣ። የአሦርም ንጉሥ ተመለሰ፥ በአገሪቱም አልተቀመጠም።
21 ፤ የቀረውም የምናሔም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
22 ፤ ምናሔም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ፋቂስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
23 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በአምሳኛው ዓመት የምናሔም ልጅ ፋቂስያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ ሁለት ዓመትም ነገሠ።
24 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም።
25 ፤ የሠራዊቱም አለቃ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ተማማለበት፥ በሰማርያም በንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ከአርጎብና ከአርያ ጋር መታው፤ ከእርሱም ጋር አምሳ የገለዓድ ሰዎች ነበሩ፤ ገደለውም፥ ፥ በእርሱም ፋንታ ነገሠ።
26 ፤ የቀረውም የፋቂስያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
27 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በአምሳ ሁለተኛው ዓመት የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ ሀያ ዓመትም ነገሠ።
28 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም።
29 ፤ በእስራኤልም ንጉሥ በፋቁሔ ዘመን የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ ዒዮንና አቤልቤትመዓካን፥ ያኖዋንም፥ ቃዴስንና አሶርንም፥ ገለዓድንና ገሊላንም፥ የንፍታሌምን አገር ሁሉ ወሰደ፤ ወደ አሦርም አፈለሳቸው።
30 ፤ በዖዝያንም ልጅ በኢዮአታም በሀያኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ ላይ ተማማለ፥ መትቶም ገደለው፥ በእርሱም ፋንታ ነገሠ።
31 ፤ የቀረውም የፋቁሔ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
32 ፤ በእስራኤል ንጉሥ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም ነገሠ።
33 ፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱ የሳዶቅ ልጅ ኢየሩሳ ነበረች።
34 ፤ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ አባቱ ዖዝያን እንዳደረገ ሁሉ እንዲሁ አደረገ።
35 ፤ ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። እርሱም የላይኛውን የእግዚአብሔርን ቤት በር ሠራ።
36 ፤ የቀረውም የኢዮአታም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
37 ፤ በዚያም ወራት እግዚአብሔር የሶርያን ንጉሥ ረአሶንንና የሮሜልዩን ልጅ ፋቁሔን በይሁዳ ላይ መስደድ ጀመረ።
38 ፤ ኢዮአታም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ ልጁም አካዝ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

1 ፤ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ በአሥራ ሰባተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአታም ልጅ አካዝ ነገሠ።
2 ፤ አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አላደረገም።
3 ፤ ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳሳደዳቸው እንደ አሕዛብ ርኵሰት ልጁን በእሳት አሳለፈው።
4 ፤ በመስገጃዎችና በኮረብቶቹ ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ይሠዋና ያጥን ነበር።
5 ፤ የዚያን ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ሊዋጉ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ አካዝንም ከበቡት፥ ሊያሸንፉት ግን አልቻሉም።
6 ፤ በዚያም ዘመን የሶርያ ንጉሥ ረአሶን ኤላትን ወደ ሶርያ መለሰ፥ አይሁድንም ከኤላት አሳደደ፤ ኤዶማውያንም ወደ ኤላት መጥተው እስከ ዛሬ ድረስ በእርስዋ ተቀምጠዋል።
7 ፤ አካዝም። እኔ ባሪያህና ልጅህ ነኝ፤ መጥተህ ከተነሡብን ከሶርያ ንጉሥና ከእስራኤል ንጉሥ እጅ አድነኝ ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር መልእክተኞችን ላከ።
8 ፤ አካዝም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የተገኘውን ብርና ወርቅ ወስዶ ወደ አሦር ንጉሥ ገጸ በረከት አድርጎ ሰደደው።
9 ፤ የአሦርም ንጉሥ ሰማው፤ የአሦርም ንጉሥ በደማስቆ ላይ ወጣባት ወሰዳትም፥ ሕዝብዋንም ወደ ቂር አፈለሳቸው፥ ረአሶንንም ገደለ።
10 ፤ ንጉሡም አካዝ የአሦርን ንጉሠ ቴልጌልቴልፌልሶርን ሊገናኘው ወደ ደማስቆ ሄደ፤ በደማስቆ የነበረውን መሠዊያ አየ፤ ንጉሡም አካዝ የመሠዊያውን ምሳሌና የአሠራሩን መልክ ወደ ካህኑ ወደ ኦርያ ላከው።
11 ፤ ካህኑም ኦርያ መሠዊያ ሠራ፤ ንጉሡ አካዝ ከደማስቆ ልኮ እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ ካህኑ ኦርያ ንጉሡ አካዝ ከደማስቆ እስኪመጣ ድረስ ሠራው።
12 ፤ ንጉሡም ከደማስቆ በመጣ ጊዜ መሠዊያውን አየ፤ ንጉሡም ወደ መሠዊያው ቀርቦ በእርሱ ላይ ወጣ።
13 ፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን አሳረገ፥ የመጠጡንም ቍርባን አፈሰሰ፥ የደኅንነቱንም መሥዋዕት ደም ረጨ።
14 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት የነበረውን የናሱን መሠዊያ ከመቅደሱ ፊት ከመሠዊያውና ከእግዚአብሔር ቤት መካከል ፈቀቅ አድርጎ በመሠውያው አጠገብ በሰሜን በኩል አኖረው።
15 ፤ ንጉሡም አካዝ። የሚቃጠለውን የጥዋት መሥዋዕት፥ የማታውንም የእህሉን ቍርባን፥ የንጉሡንም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን፥ ለአገሩም ሕዝብ የሚሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን የመጠጡንም ቍርባን በታላቁ መሠዊያ ላይ አቅርብ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ደም ሁሉ የሌላ መሥዋዕቱንም ደም ሁሉ ርጭበት፤ የናሱ መሠዊያ ግን እኔ እጠይቅበት ዘንድ ይሁን ብሎ ካህኑን ኦርያን አዘዘው።
16 ፤ ካህኑ ኦርያ ንጉሡ አካዝ እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።
17 ፤ ንጉሡም አካዝ የመቀመጫዎችን ክፈፍ ቈረጠ፥ ከእነርሱም የመታጠቢያውን ሰኖች ወሰደ፤ ኵሬውንም ከበታቹ ከነበሩት ከናሱ በሬዎች አወረደው፥ በጠፍጣፋውም ድንጋይ ላይ አኖረው።
18 ፤ በእግዚአብሔርም ቤት የዙፋኑን መሠረት ሠራ፤ ስለ አሦርም ንጉሥ በውጭ ያለውን የንጉሡን መንገድ ወደ እግዚአብሔር ቤት አዞረው።
19 ፤ የቀረውም አካዝ ያደረገው ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
20 ፤ አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ሕዝቅያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

1 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በአካዝ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ንጉሥ ሆነ፤ ዘጠኝ ዓመትም ነገሠ።
2 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ነገር ግን ከእርሱ አስቀድሞ እንደ ነበሩት እንደ እስራኤል ነገሥታት አይደለም።
3 ፤ የአሦርም ንጉሥ ስልምናሶር በእርሱ ላይ ወጣ፤ ሆሴዕም ተገዛለት፥ ግብርም አመጣለት።
4 ፤ የአሦርም ንጉሥ በሆሴዕ ላይ ዓመፅ አገኘ፤ መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ንጉሥ ወደ ሴጎር ልኮ ነበርና፤ እንደ ልማዱም በየዓመቱ ለአሦር ንጉሥ ግብር አልሰጠምና፤ ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ይዞ በወህኒ ቤት አሰረው።
5 ፤ የአሦርም ንጉሥ በምድር ሁሉ ላይ ወጣ፥ ወደ ሰማርያም ወጥቶ ሦስት ዓመት ከበባት።
6 ፤ በሆሴዕ በዘጠኝኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ወሰደ፥ እስራኤልንም ወደ አሦር አፈለሰ፥ በአላሔና በአቦር በጎዛንም ወንዝ በሜዶንም ከተሞች አኖራቸው።
7 ፤ የእስራኤልም ልጆች ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ፥ ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን በድለው ነበርና፥ ሌሎችንም አማልክት አምልከው ነበርና፥
8 ፤ እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ባሳደዳቸው በአሕዛብ ሥርዓት፥ የእስራኤልም ነገሥታት ባደረጓት ሥርዓት ሄደው ነበርና እንደዚህ ሆነ።
9 ፤ የእስራኤልም ልጆች በአምላካቸው በእግዚአብሔር ላይ ቅን ያልሆነን ንገር በስውር አደረጉ፤ በከተሞቻቸውም ሁሉ ከዘበኞች ግንብ ጀምሮ እስከ ተመሸገች ከተማ ድረስ በከፍታዎቹ ላይ መስገጃዎችን ሠሩ።
10 ፤ በረጃጅሙ ኮረብታ ሁሉ ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ ታች ሐውልቶችንና የማምለኪያ ዐፀዶችን ተከሉ፤
11 ፤ እግዚአብሔርም ከፊታቸው ያወጣቸው አሕዛብ እንዳደረጉት፥ በኮረብቶቹ መስገጃዎች ሁሉ ላይ ያጥኑ ነበር፤ እግዚአብሔርንም ያስቈጡ ዘንድ ክፉ ነገር አደረጉ፤
12 ፤ እግዚአብሔርም የከለከላቸውን ጣዖቶች አመለኩ።
13 ፤ እግዚአብሔርም። ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ለአባቶቻችሁም እንዳዘዝሁት፥ ባባሪያዎቼ በነቢያት የላክሁላችሁን ትእዛዜንና ሥርዓቴን ሕጌንም ሁሉ ጠብቁ ብሎ በነቢዩ ሁሉና በባለ ራእዩ አፍ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ መሰከረ።
14 ፤ ነገር ግን አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዳላመኑ እንደ አባቶቻቸው አንገት አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙም።
15 ፤ ሥርዓቱንም ከአባቶቻቸውም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን፥ ያጸናላቸውንም ምስክሩን ናቁ፤ ከንቱ ነገርንም ተከተሉ፥ ምናምንቴዎችም ሆኑ፥ እግዚአብሔርም እንደ እነርሱ እንዳይሠሩ ያዘዛቸውን በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብን ተከተሉ።
16 ፤ የአምላካቸውንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ ተዉ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም የሁለቱን እንቦሶች ምስሎች አደረጉ፥ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከሉ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገዱ፥ በኣልንም አመለኩ።
17 ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አሳለፉአቸው፥ ምዋርተኞችና አስማተኞችም ሆኑ፥ ያስቈጡትም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ።
18 ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፥ ከፊቱም ጣላቸው፤ ከይሁዳም ነገድ ብቻ በቀር ማንም አልቀረም።
19 ፤ ይሁዳም ደግሞ እስራኤል ባደረጋት ሥርዓት ሄደ እንጂ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም።
20 ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ዘር ሁሉ ጠላ፥ አስጨነቃቸውም፥ ከፊቱም እስኪጥላቸው ድረስ በበዝባዦች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።
21 ፤ እስራኤልንም ከዳዊት ቤት ለየ፤ የናባጥንም ልጅ ኢዮርብዓምን አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እግዚአብሔርን ከመከተል እስራኤልን መለሰ፥ ታላቅም ኃጢአት አሠራቸው።
22 ፤ የእስራኤልም ልጆች ኢዮርብዓም ባደረገው ኃጢአት ሁሉ ሄዱ፤
23 ፤ እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያቱ ሁሉ አፍ እንደ ተናገረው እስራኤልን ከፊቱ እስኪያወጣ ድረስ ከእርስዋ አልራቁም። እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከምድሩ ወደ አሦር ፈለሰ።
24 ፤ የአሦርም ንጉሥ ከባቢሎንና ከኩታ ከአዋና ከሐማት ከሴፈርዋይም ሰዎችን አመጣ፥ በእስራኤልም ልጆች ፋንታ በሰማርያ ከተሞች አኖራቸው፤ ሰማርያንም ወረሱአት፤ በከተሞችዋም ተቀመጡ።
25 ፤ በዚያም መቀመጥ በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ እግዚአብሔርም አንበሶች ሰደደባቸው፥ ይገድሉአቸውም ነበር።
26 ፤ ስለዚህም ለአሦር ንጉሥ። ያፈለስኻቸው፥ በሰማርያም ከተሞች ያኖርኻቸው የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁም፤ የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁምና አንበሶችን ሰድዶባቸዋል፥ እነሆም፥ ገደሉአቸው ብለው ተናገሩት።
27 ፤ የአሦርም ንጉሥ። ከዚያ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን ውሰዱ፤ ሄዶም በዚያ ይቀመጥ፥ የአገሩንም አምላክ ወግ ያስተምራቸው ብሎ አዘዘ።
28 ፤ ከሰማርያም ካፈለሱአቸው ካህናት አንዱ መጥቶ በቤቴል ተቀመጠ፥ እግዚአብሔርንም እንዴት እንዲፈሩት ያስተምራቸው ነበር።
29 ፤ በየሕዝባቸውም አምላካቸውን አደረጉ፥ ሰምራውያንም በሠሩት በኮረብታው መስገጃዎች ሕዝቡ ሁሉ በሚኖሩበት ከተሞቻቸው አኖሩአቸው።
30 ፤ የባቢሎንም ሰዎች ሱኮትበኖትን ሠሩ፤ የኩታም ሰዎች ኤርጌልን ሠሩ፤
31 ፤ የሐማትም ሰዎች አሲማትን ሠሩ፤ አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅን ሠሩ፤ የሴፈርዋይም ሰዎችም ለሴፈርዋይም አማልክት ለአድራሜሌክና ለአነሜሌክ ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ነበር።
32 ፤ እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፥ ከመካከላቸውም ለኮረብታው መስገጃዎች ካህናት አደረጉ፥ በኮረብታውም መስገጃዎች ይሠዉ ነበር።
33 ፤ እግዚአብሔርንም ሲፈሩ ከመካከላቸው እንደ ፈለሱት እንደ አሕዛብ ልማድ አምላካቸውን ያመልኩ ነበር።
34 ፤ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ቀደመው ልማድ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም፥ እግዚአብሔርም እስራኤል ብሎ የጠራውን የያዕቆብን ልጆች እንዳዘዛቸው ሥርዓትና ፍርድ ሕግና ትእዛዝም አያደርጉም።
35 ፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። ሌሎችን አማልክት አትፍሩ፥ አትስገዱላቸው፥ አታምልኩአቸው፥ አትሠዉላቸው፤
36 ፤ ነገር ግን በታላቅ ኃይል በተዘረጋችም ክንድ ከግብጽ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔር እርሱን ፍሩ፥ ለእርሱም ስገዱ፥ ለእርሱም ሠዉ፤
37 ፤ የጻፈላችሁንም ሥርዓትና ፍርድ ሕግና ትእዛዝም ለዘላለም ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ።
38 ፤ ከእናንተም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ።
39 ፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እርሱም ከጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ ያድናችኋል።
40 ፤ ነገር ግን እንደ ቀደመው ልማዳቸው አደረጉ እንጂ አልሰሙም።
41 ፤ እነዚህም አሕዛብ እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበር፤ ደግሞም የተቀረጹ ምስሎቻቸውን ያመልኩ ነበር፤ ልጆቻቸውም የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው እንዳደረጉ እንዲሁ እስከ ዛሬ ድረስ ያደርጋሉ።

1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በእስራኤል ንጉሥ በኤላ ልጅ በሆሴዕ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ ነገሠ።
2 ፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዘካርያስ ልጅ አቡ ነበረች።
3 ፤ እርሱም አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አደረገ።
4 ፤ በኮረብታም ያሉትን መስገጃዎች አስወገደ፥ ሐውልቶችንም ቀለጣጠመ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የእስራኤልም ልጆች እስከዚህ ዘመን ድረስ ያጥኑለት ነበርና ሙሴ የሠራውን የናሱን እባብ ሰባበረ፤ ስሙንም ነሑሽታን ብሎ ጠራው።
5 ፤ በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ታመነ፤ ከእርሱም በኋላ ከእርሱም በፊት ከነበሩት ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ እርሱን የሚመስል አልነበረም።
6 ፤ ከእግዚአብሔርም ጋር ተጣበቀ፥ እርሱንም ከመከተል አልራቀም፥ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዘውን ትእዛዛቱን ጠበቀ።
7 ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፥ የሚሄድበትም መንገድ ተከናወነለት፤ በአሦርም ንጉሥ ላይ ዐመፀ፥ አልገበረለትም።
8 ፤ ፍልስጥኤማውያንንም እስከ ጋዛና እስከ ዳርቻዋ ድረስ፥ ከዘበኞች ግንብ ጀምሮ እስከ ምሽጉ ከተማ ድረስ መታ።
9 ፤ በንጉሡ በሕዝቅያስ በአራተኛው ዓመት፥ በእስራኤል ንጉሥ በኤላ ልጅ በሆሴዕ በሰባተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ወጣ፥ ከበባትም።
10 ፤ ከሦስት ዓመት በኋላም ወሰዳት፤ በሕዝቅያስ በስድስተኛው ዓመት፥ በእስራኤል ንጉሥ በሆሴዕ በዘጠኝኛው ዓመት፥ ሰማርያ ተያዘች።
11 ፤ የአሦር ንጉሥ እስራኤልን ወደ አሦር አፈለሰ፥ በአላሔና በአቦር በጎዛንም ወንዝ በሜዶንም ከተሞች አኖራቸው፤
12 ፤ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙምና፥ ቃል ኪዳኑንም አፍርሰዋልና፥ የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አልሰሙምና፥ አላደረጉምና።
13 ፤ በንጉሡም በሕዝቅያስ በአሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጣ፥ ወሰዳቸውም።
14 ፤ የይሁዳም ንጉሥ ሕዝቅያስ። በድያለሁ፥ ከእኔ ተመለስ፤ የምትጭንብኝን ሁሉ እሸከማለሁ ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ለኪሶ ላከ። የአሦርም ንጉሥ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ላይ ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ ጫነበት።
15 ፤ ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የተገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው።
16 ፤ በዚያን ጊዜም ሕዝቅያስ ከእግዚአብሔር መቅደስ ደጆችና የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከለበጣቸው መቃኖች ወርቁን ቈረጠ፥ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠው።
17 ፤ የአሦርም ንጉሥ ተርታንንና ራፌስን ራፋስቂስንም ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላከ። ወጥተውም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ በመጡም ጊዜ በአጣቢው እርሻ መንገድ ባለችው በላይኛይቱ ኩሬ መስኖ አጠገብ ቆሙ።
18 ፤ ንጉሡንም ጠሩ፤ የቤቱም አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እነርሱ ወጡ።
19 ፤ ራፋስቂስም አላቸው። ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ይህ የምትታመንበት መተማመኛ ምንድር ነው?
20 ፤ የከንፈር ቃል ለሰልፍ ምክርና ኃይል እንደሚሆን ትናገራለህ፤ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው?
21 ፤ እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ በሸምበቆ በትር በግብጽ ትታመናለህ፤ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል ያቈስለውማል፤ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው።
22 ፤ እናንተም። በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትሉኝ፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን። በኢየሩሳሌም ባለው በዚህ መሠዊያ ፊት ሰገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያውቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን?
23 ፤ አሁን እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፥ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ።
24 ፤ ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሰኞች በግብጽ ስትታመን፥ ከጌታዬ ባሪያዎች የሚያንሰውን የአንዱ አለቃ ፊት ትቃወም ዘንድ እንዴት ይቻልሃል?
25 ፤ አሁን በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ይህን ስፍራ አጠፋ ዘንድ ወጥቻለሁን? እግዚአብሔር። ወደዚች አገር ወጥተህ አጥፋት አለኝ።
26 ፤ የኬልቅያስም ልጅ ኤልያቄም ሳምናስም ዮአስም ራፋስቂስን። እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን አሉት።
27 ፤ ራፋስቂስ ግን። ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ አንተና ወደ ጌታህ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡት ሰዎች አይደለምን? አላቸው።
28 ፤ ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በአይሁድ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኽ። የታላቁን የአሦር ንጉሥ ቃል ስሙ፤ ንጉሡ እንዲህ ይላል።
29 ፤ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤
30 ፤ ሕዝቅያስም። እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል፥ ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።
31 ፤ ሕዝቅያስንም አትስሙ፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ከእኔ ጋር ታረቁ ወደ እኔም ውጡ፥ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፤
32 ፤ ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን፥ ወይራና ማር ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ በሕይወት እንድትኖሩ እንዳትሞቱም ነው። ሕዝቅያስም። እግዚአብሔር ያድነናል ብሎ ቢያታልላችሁ አትስሙት።
33 ፤ በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን?
34 ፤ የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይምና የሄና የዒዋም አማልክት ወዴት አሉ?
35 ፤ ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከአገሮቹ አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው?
36 ፤ ሕዝቡም ዝም አሉ፥ አንዳችም አልመለሱለትም፤ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና።
37 ፤ የቤቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፥ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት።

1 ፤ ንጉሡም ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፥ ማቅም ለበሰ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገባ።
2 ፤ የቤቱንም አዛዥ ኤልያቄምን ጸሐፊውንም ሳምናስን የካህናቱንም ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ ነቢዩ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ኢሳይያስ ይሄዱ ዘንድ ላካቸው።
3 ፤ እነርሱም። ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል። ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ የዘለፋም ቀን ነው፤ ልጆች የሚወለዱበት ጊዜ ደርሶአል፥ ለመውለድም ኃይል የለም።
4 ፤ ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል ሁሉ አምላካህ እግዚአብሔር ይሰማ እንደ ሆነ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደ ሆነ፥ ስለዚህ ለቀረው ቅሬታ ጸልይ አሉት።
5 ፤ እንዲሁ የንጉሡ የሕዝቅያስ ባሪያዎች ወደ ኢሳይያስ መጡ።
6 ፤ ኢሳይያስም። ለጌታችሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች ስለ ሰደቡኝ፥ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ።
7 ፤ እነሆ፥ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፥ ወሬንም ይሰማል፥ ወደ ምድሩም ይመለሳል፤ በምድሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርገዋለሁ በሉት አላቸው።
8 ፤ የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ እንደ ራቀ ሰምቶ ነበርና ራፋስቂስ ተመልሶ በልብና ሲዋጋ አገኘው።
9 ፤ እርሱም። የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊወጋህ መጥቶአል የሚል ወሬ በሰማ ጊዜ ደግሞ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፥ እንዲህ ሲል።
10 ፤ ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ የምትታመንበት አምላክህ አያታልልህ።
11 ፤ እነሆ፥ የአሦር ነገሥታት በምድር ሁሉ ላይ ያደረጉትን፥ እንዴትስ እንዳጠፋአቸው ሰምተሃል፤ አንተስ ትድናለህን?
12 ፤ አባቶቼ ያጠፉአቸውን፥ ጎዛንን፥ ካራንን፥ ራፊስን፥ በተላሳር የነበሩትንም የዔድንን ልጆች፥ የአሕዛብ አማልክት አዳኑአቸውን?
13 ፤ የሐማት ንጉሥ፥ የአርፋድ ንጉሥ፥ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፥ የሄናና የዒዋ ንጉሥ ወዴት አሉ?
14 ፤ ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞች እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው።
15 ፤ ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ጸለየ። በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ አንተ ብቻህን የምድር ነገሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል።
16 ፤ አቤቱ፥ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ አቤቱ፥ ዓይንህን ክፈትና እይ፤ በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ የላከውን የሰናክሬምን ቃል ስማ።
17 ፤ አቤቱ፥ በእውነት የአሦር ነገሥታት አሕዛብንና ምድራቸውን አፍርሰዋል፥
18 ፤ አማልክቶቻቸውንም በእሳት ላይ ጥለዋል፤ የእንጨትና የድንጋይ የሰው እጅ ሥራ ነበሩ እንጂ አማልክት አልነበሩምና፤ ስለዚህ አጥፍተዋቸዋል።
19 ፤ እንግዲህም አምላካችን አቤቱ፥ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ እግዚአብሔር አምላክ እንደ ሆንህ ያውቁ ዘንድ ከእጁ እንድታድነን እለምንሃለሁ።
20 ፤ የአሞጽም ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ወደ ሕዝቅያስ ላካ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ የለመንኽውን ሰምቻለሁ።
21 ፤ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው። ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ቀላል አድርጋሃለች፥ በንቀትም ስቃብሃለች፤ የኢየሩሳሌም ልጅ በላይህ ራስዋን ነቅንቃብሃለች።
22 ፤ የተገዳደርኸው፥ የሰደብኸውስ ማን ነው? ቃልህንስ ከፍ ከፍ ያደረግኸው ዓይንህንም ወደ ላይ ያነሣኸው በማን ላይ ነው? በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው።
23 ፤ አንተስ። በሰረገላዬ ብዛት ወደ ተራሮች ከፍታ፥ ወደ ሊባኖስ ጥግ ላይ ወጥቻለሁ፤ ረጃጅሞቹንም ዝግባዎች የተመረጡትንም ጥዶች እቈርጣለሁ፥ ወደ አገሩም ዳርቻና ወደ ቀርሜሎስ ዱር እገባለሁ።
24 ፤ ቈፈርሁም፥ እንግዳውንም ውኃ ጠጣሁ፤ የተገደበውንም ውኃ ሁሉ በእግሬ ጫማ አደርቃለሁ ብለህ በመልእክተኞችህ እጅ በእግዚአብሔር ላይ ተገዳደርህ።
25 ፤ እኔ ጥንቱን እንደ ሠራሁት፥ ቀድሞውንም እንዳደረግሁት አልሰማህምን? አሁንም የተመሸጉትን ከተሞች የፍርስራሽ ክምር እስኪሆኑ ድረስ እንድታፈርስ አደረግሁህ።
26 ፤ ስለዚህም የሚኖሩባቸው ሰዎች እጃቸው ዝሎአል፥ ደንግጠውም ታውከዋል፤ እንደ ምድረ በዳ ሣር፥ እንደ ለምለምም ቡቃያ፥ በሰገነትም ላይ እንዳለ ሣር፥ ሳይሸት ዋግ እንደ መታውም እህል ሆነዋል።
27 ፤ እኔ ግን መቀመጫህንና መውጫህንም መግቢያህንም፥ በእኔም ላይ የተቈጠኸውን ቍጣ አውቄአለሁ።
28 ፤ ቍጣህና ትዕቢትህ ወደ ጆሮዬ ደርሶአልና ስለዚህ ስናጋዬን በአፍንጫህ፥ ልጓሜንም በከንፈርህ አደርጋለሁ፥ በመጣህበትም መንገድ እመልስሃለሁ።
29 ፤ ይህም ምልክት ይሆንሃል፤ በዚህ ዓመት የገቦውን፥ በሁለተኛውም ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤ በሦስተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፥ ታጭዱማላችሁ፥ ወይንንም ትተክላላችሁ፥ ፍሬውንም ትበላላችሁ።
30 ፤ ያመለጠው የይሁዳ ቤት ቅሬታ ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፥ ወደ ላይም ያፈራል።
31 ፤ ከኢየሩሳሌም ቅሬታ ከጽዮንም ተራራ ያመለጡት ይወጣሉና፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል።
32 ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ወደዚች ከተማ አይመጣም፥ ፍላጻንም አይወረውርባትም፥ በጋሻም አይመጣባትም፥ የአፈርንም ድልድል አይደለድልባትም።
33 ፤ በመጣበት መንገድ በዚያው ይመለሳል፥ ወደዚህችም ከተማ አይመጣም፥ ይላል እግዚአብሔር።
34 ፤ ስለ እኔም፥ ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ።
35 ፤ በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ።
36 ፤ የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፥ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ።
37 ፤ በአምላኩም በናሳራክ ቤት ሲሰግድ ልጆቹ አደራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፤ ወደ አራራትም አገር ኰበለሉ። ልጁም አስራዶን በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

1 ፤ በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስከ ሞት ድረስ ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል አለው።
2 ፤ ፊቱንም ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።
3 ፤ አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ፥ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ። ሕዝቅያስም እጅግ አድርጎ አለቀሰ።
4 ፤ ኢሳይያስም ወደ መካከለኛው ከተማ አደባባይ ሳይደርስ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት።
5 ፤ ተመልሰህ የሕዝቤን አለቃ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው። የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ እፈውስሃለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት ትወጣለህ።
6 ፤ በዕድሜህም ላይ አሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ፤ አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ስለ እኔም ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ።
7 ፤ ኢሳይስም፥ የበለስ ጥፍጥፍ አምጡልኝ አለ፤ አምጥተውም በእባጩ ላይ አደርጉለት፥ እርሱም ተፈወሰ።
8 ፤ ሕዝቅያስም ኢሳይያስን፥ እግዚአብሔር እንዲፈውሰኝ፥ እኔስ በሦስተኛው ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንድወጣ ምልክቱ ምንድር ነው? አለው።
9 ፤ ኢሳይያስም፥ እግዚአብሔር የተናገረውን ነገር እንዲፈጽመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክቱ ይህ ይሆንልሃል፤ ጥላው አሥር ደረጃ ወደ ፊት ይሄድ ዘንድ ወይም አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ ዘንድ ትወድዳለህን? አለ።
10 ፤ ሕዝቅያስም፥ ጥላው አሥር ደረጃ ቢጨምር ቀላል ነገር ነው፤ እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ጥላው አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ አለው።
11 ፤ ነቢዩም ኢሳይያስ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ ጥላውንም በአካዝ የጥላ ስፍራ ሰዓት ላይ በወረደበት መንገድ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ መለሰው።
12 ፤ በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን ሕዝቅያስ እንደ ታመመ ሰምቶ ነበርና ደብዳቤና እጅ መንሻ ወደ ሕዝቅያስ ላከ።
13 ፤ ሕዝቅያስም ደስ አለው፥ ግምጃ ቤቱንም ሁሉ፥ ብሩንና ወርቁንም፥ ቅመሙንና የከበረውንም ዘይት፥ መሣሪያም ያለበትን ቤት በቤተ መዛግብቱም የተገኘውን ሁሉ አሳያቸው በቤቱና በግዛቱ ሁሉ ካለው ሕዝቅያስ ያላሳያቸው የለም።
14 ፤ ነቢዩም ኢሳያሳ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ መጥቶ። እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? ከወዴትስ መጡልህ? አለው። ሕዝቅያስም። ከሩቅ አገር ከባቢሎን መጡ አለው።
15 ፤ እርሱም። በቤትህ ያዩት ምንድር ነው? አለው፤ ሕዝቅያስም። በቤቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በቤተ መዛግብቴ ካለው ያላሳየኋቸው የለም አለው።
16 ፤ ኢሳይያስም ሕዝቅያስን። የእግዚአብሔርን ቃል ስማ።
17 ፤ እነሆ፥ በቤትህ ያለው ሁሉ፥ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚፈልስበት ወራት ይመጣል፤ ምንም አይቀርም፥ ይላል እግዚአብሔር።
18 ፤ ከአንተም ከሚወጡት ከምትወልዳቸው ልጆችህ ማርከው ይወስዳሉ፤ በባቢሎንም ንጉሥ ቤት ውስጥ ጃንደረቦች ይሆናሉ አለው።
19 ፤ ሕዝቅያስም ኢሳይያስን። የተናገርኸው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው አለው። ደግሞም። በዘመኔ ሰላምና እውነት የሆነ እንደ ሆነ መልካም አይደለምን? አለ።
20 ፤ የቀረውም የሕዝቅያስ ነገር፥ ጭከናውም ሁሉ፥ ኵሬውንና መስኖውንም እንደ ሠራ፥ ውኃውንም ወደ ከተማይቱ እንዳመጣ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
21 ፤ ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

1 ፤ ምናሴም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ አምስት ዓመት ነገሠ፤ የእናቱ ስም ሐፍሴባ ነበረ።
2 ፤ እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳወጣቸው እንደ አሕዛብ ርኵሰት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።
3 ፤ አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታውን መስገጃዎች መልሶ ሠራ፤ የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው ለበኣል መሠዊያ ሠራ፥ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከለ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ አመለካቸውም።
4 ፤ እግዚአብሔርም። ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ ባለው በእግዚአብሔር ቤት መሠዊያዎችን ሠራ።
5 ፤ በእግዚአብሔርም ቤት በሁለቱ ወለሎች ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ።
6 ፤ ልጁንም በእሳት አሳለፈ፥ ሞራ ገላጭም ሆነ፥ አስማትም አደረገ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም ሰበሰበ፤ ያስቈጣውም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።
7 ፤ እግዚአብሔርም ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን። በዚህ ቤት ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤
8 ፤ ያዘዝኋቸውንም ሁሉ፥ ባሪያዬም ሙሴ ያዘዛቸውን ሕግ ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም ለአባቶቻቸው ከሰጠኋት ምድር የእስራኤልን እግር እንደ ገና አላቅበዘብዝም ባለው ቤት የሠራውን የማምለኪያ ዐፀድን የተቀረጸውን ምስል አቆመ።
9 ፤ ነገር ግን አልሰሙም፤ እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ ምናሴ አሳታቸው።
10 ፤ እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያት እጅ እንዲህ ሲል ተናገረ።
11 ፤ የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ርኵሰት አድርጎአልና፥ ከፊቱም የነበሩ አሞራውያን ከሠሩት ሁሉ ይልቅ ክፉ ሥራ ሠርቶአልና፥ ይሁዳንም ደግሞ በጣዖታቱ አስቶአልና
12 ፤ ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የሚሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ ክፉ ነገርን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ።
13 ፤ የሰማርያንም ገመድ የአክዓብንም ቤት ቱንቢ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ ሰውም ወጭቱን እንዲወለውል ኢየሩሳሌምን ወልውዬ እገለብጣታለሁ።
14 ፤ የርስቴንም ቅሬታ እጥላለሁ፥ በጠላቶቻቸውም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፥ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ምርኮና ብዝበዛ ይሆናሉ፤
15 ፤ አባቶቻቸው ከግብጽ ከወጡ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ሠርተዋልና፥ አስቈጥተውኝማልና።
16 ፤ ደግሞም ምናሴ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ይሠራ ዘንድ ይሁዳን ካሳተበት ኃጢአት ሌላ ከዳር እስከ ዳር ኢየሩሳሌምን እስኪሞላት ድረስ እጅግ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ።
17 ፤ የምናሴም የቀረው ነገርና የሠራው ሥራ ሁሉ፥ ያደረገውም ኃጢአት፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
18 ፤ ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቤቱም አጠገብ ባለው በዖዛ አትክልት ተቀበረ፤ ልጁም አሞጽ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
19 ፤ አሞጽም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዮጥባ ሰው የሐሩስ ልጅ ሜሶላም ነበረች።
20 ፤ አባቱም ምናሴ እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ።
21 ፤ አባቱም በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ፥ አባቱም ያመለካቸውን ጣዖታት አመለከ ሰገደላቸውም።
22 ፤ የአባቶቹንም አምላክ እግዚአብሔርን ተወ፥ በእግዚአብሔርም መንገድ አልሄደም።
23 ፤ የአሞጽም ባሪያዎች አሴሩበት ንጉሡንም በቤቱ ውስጥ ገደሉት፥
24 ፤ የአገሩ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞጽ ላይ ያሴሩበትን ሁሉ ገደሉ፤ የአገሩም ሕዝብ ልጁን ኢዮስያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡት።
25 ፤ የአሞጽም የቀረው ነገርና የሠራው ሥራ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
26 ፤ በዖዛም አትክልት ባለው በመቃብሩ ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

1 ፤ ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ከባሱሮት የሆነ የአዳያ ልጅ ይዲዳ ነበረች።
2 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገርን አደረገ፥ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሁሉ ሄደ፥ ቀኝም ግራም አላለም።
3 ፤ በንጉሡም በኢዮስያስ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት በስምንተኛው ወር ንጉሡ ጸሐፊውን የሜሶላምን ልጅ የኤዜልያስን ልጅ ሳፋንን ወደ እግዚአብሔር ቤት ላከው፥ እንዲህም አለው።
4 ፤ የመቅደሱ በረኞች ከሕዝቡ የሰበሰቡትን ወደ እግዚአብሔር ቤት የገባውን ገንዘብ ይደምር ዘንድ ወደ ካህናቱ አለቃ ወደ ኬልቅያስ ሂድ።
5 ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ላሉት ሠራተኞች አለቆች ይስጡት፤ እነርሱም የተናደውን የእግዚአብሔርን ቤት ለሚጠግኑት ሠራተኞች፥
6 ፤ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች፥ ለድንጋይም ወቃሪዎች፥ መቅደሱንም ለመጠገን እንጨትንና የተወቀረውን ድንጋይ ለሚገዙ ይክፈሉት።
7 ፤ ነገር ግን እነርሱ የታመኑ ነበሩና በእጃቸው ስለ ተሰጠ አይቈጣጠሩአቸውም ነበር።
8 ፤ ካህኑም ኬልቅያስ ጸሐፊውን ሳፋንን፥ የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቻለሁ አለው፤ ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው፥ እርሱም አነበበው።
9 ፤ ጸሐፊውም ሳፋን ወደ ንጉሡ መጣ፥ ለንጉሡም። በመቅደሱ የተገኘውን ገንዘብ ባሪያዎችህ አፈሰሱት፥ በእግዚአብሔርም ቤት ሠራተኞች ላይ ለተሾሙት አለቆች ሰጡት ብሎ አወራለት።
10 ፤ ጸሐፊውም ሳፋን ለንጉሡ። ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው።
11 ፤ ንጉሡም የሕጉን መጽሐፍ ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ።
12 ፤ ንጉሡም ካህኑን ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓክቦርን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን።
13 ፤ አባቶቻችን በእርስዋ የተጻፈውን ሁሉ ይሠሩ ዘንድ የዚህችን መጽሐፍ ቃል ስላልሰሙ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ እኔና ስለ ሕዝቡ ስለ ይሁዳም ሁሉ የዚህችን የተገኘችውን መጽሐፍ ቃል እግዚአብሔርን ጠይቁ ብሎ አዘዛቸው።
14 ፤ እንዲሁም ካህኑ ኬልቅያስና አኪቃም ዓክቦርም ሳፋንና ዓሳያም ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢያቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርስዋም በኢየሩሳሌም በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ከእርስዋም ጋር ተነጋገሩ።
15 ፤ እርስዋም አለቻቸው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት።
16 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የይሁዳ ንጉሥ እንዳነበበው እንደ መጽሐፉ ቃል ሁሉ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ።
17 ፤ በእጃቸው ሥራ ሁሉ ያስቈጡኝ ዘንድ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፥ አይጠፋምም።
18 ፤ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ግን እንዲህ በሉት። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ ሰማኸው ቃል፥ ልብህ ገር ሆኖአልና፥
19 ፤ እነርሱም ለድንቅና ለመርገም እንዲሆኑ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የተናገርሁትን ሰምተህ በእግዚአብሔር ፊት ተዋርደሃልና፥ ልብስህን ቀድደሃልና፥ በፊቴም አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር።
20 ፤ ስለዚህም ደግሞ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፥ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራ ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ዓይኖችህ አያዩም። ይህንም ለንጉሡ አወሩለት።

1 ፤ ንጉሡም ላከ፤ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምንም ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰባቸው።
2 ፤ ንጉሡም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጣ፤ ከእርሱም ጋር የይሁዳ ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ሁሉ፥ ካህናቱና ነቢያቱም፥ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሾቹ ጀምሮ እስከ ታላቆቹ ድረስ ወጡ፤ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ በጆሮአቸው አነበበ።
3 ፤ ንጉሡም በዓምደ ወርቁ አጠገብ ቆሞ እግዚአብሔርን ተከትሎ ይሄድ ዘንድ፥ ትእዛዙንና ምስክሩንም ሥርዓቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ ይጠብቅ ዘንድ፥ በዚሁም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል ያጸና ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ፤ ሕዝቡም ሁሉ ቃል ኪዳን ገቡ።
4 ፤ ንጉሡም የካህናቱን አለቃ ኬልቅያስን በሁለተኛውም መዓርግ ያሉትን ካህናትን በረኞቹንም ለባኣልና ለማምለኪያ ዐፀድ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ የተሠሩትን ዕቃዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር መቅደስ ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው፤ ከኢየሩሳሌምም ውጭ በቄድሮን ሜዳ አቃጠላቸው፥ አመዱንም ወደ ቤቴል ወሰደው።
5 ፤ የይሁዳ ነገሥታትም በይሁዳ ከተሞች በነበሩት በኮረብታው መገጃዎች በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ መስገጃዎች ያጥኑ ዘንድ ያኖሩአቸውን የጣዖቱን ካህናት፥ ለበኣልና ለፀሐይ ለጨረቃና ለከዋክብት ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ያጥኑ የነበሩትንም አስወገደ።
6 ፤ የማምለኪያ ዐፀድንም ጣዖት ከእግዚአብሔር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም ውጭ ወደ ቄድሮን ፈፋ አወጣው፤ በቄድሮንም ፈፋ አጠገብ አቃጠለው፥ አድቅቆም ትቢያ አደረገው፥ ትቢያውንም በሕዝብ መቃብር ላይ ጣለው።
7 ፤ ሴቶቹም ለማምለኪያ ዐፀድ መጋረጃ ይፈትሉባቸው የነበሩትን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያሉትን የሰዶማውያንን ቤቶች አፈረሰ።
8 ፤ ካህናቱንም ሁሉ ከይሁዳ ከተሞች አወጣቸው፤ ከጌባም ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ካህናት ያጥኑበት የነበረውን የኮረብታ መስገጃ ሁሉ ርኩስ አደረገው። በከተማይቱም በር በግራ በኩል በነበረው በከተማይቱ ሹም በኢያሱ በር መግቢያ አጠገብ የነበሩትን የበሮቹን መስገጃዎች አፈረሰ።
9 ፤ የኮረብታው መስገጃዎች ካህናት ግን በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ አይመጡም ነበር፤ ብቻ በወንድሞቻቸው መካከል ቂጣ እንጀራ ይበሉ ነበር።
10 ፤ ማንም ሰው ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን ለሞሎክ በእሳት እንዳያሳልፍ በሄኖም ልጆች ሸለቆ የነበረውን ቶፌትን ርኩስ አደረገው።
11 ፤ የይሁዳም ነገሥታት በእግዚአብሔር ቤት መግቢያ አጠገብ በከተማው አቅራቢያ በነበረው በጃንደረባው በናታንሜሌክ መኖሪያ አጠገብ ለፀሐይ የሰጡትን ፈረሶች አስወገደ፤ የፀሐይንም ሰረገሎች በእሳት አቃጠለ።
12 ፤ የይሁዳም ነገሥታት ያሠሩትን በአካዝ ቤት ሰገነት ላይ የነበሩትን መሠዊያዎች፥ ምናሴም ያሠራውን በእግዚአብሔር ቤት በሁለቱ ወለሎች ላይ የነበሩትን መሠዊያዎች ንጉሡ አስፈረሳቸው፥ አደቀቃቸውም፥ ትቢያቸውንም በቄድሮን ፈፋ ጣለ።
13 ፤ በኢየሩሳሌምም ፊት ለፊት በርኵሰት ተራራ ቀኝ የነበሩትን፥ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለሲዶናውያን ርኵሰት ለአስታሮት ለሞዓብም ርኵሰት ለካሞሽ ለአሞንም ልጆች ርኵሰት ለሚልኮም ያሠራቸውን መስገጃዎች ንጉሡ ርኩስ አደረገ።
14 ፤ ሐውልቶቹንም ሁሉ አደቀቀ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፥ በስፍራቸውም የሙታንን አጥንት ሞላበት።
15 ፤ ደግሞም በቤቴል የነበረውን መሠዊያ፥ እስራኤልንም ያሳተ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ያሠራውን የኮረብታውን መስገጃ፥ ይህን መሠዊያና መስገጃ አፈረሰ፤ ድንጋዮቹንም ሰባበረ፥ አድቅቆም ትቢያ አደረገው፥ የማምለኪያ ዐፀዱንም አቃጠለው።
16 ፤ ኢዮስያስም ዘወር ብሎ በተራራው የነበሩትን መቃብሮች አየ፤ ኢዮርብዓምም በበዓል ጊዜ በመሠዊያ አጠገብ ሲቆም እነዚህን ነገሮች የተነባ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ ልኮ ከመቃብሮቹ አጥንቶቹን አስወጣ፥ በመሠዊያውም ላይ አቃጠላቸው አረከሰውም። ዘወርም ብሎ ወደ ተናገረው ወደ እግዚአብሔር ሰው መቃብር ዓይኖቹን አቅንቶ።
17 ፤ ያ የማየው የመታሰቢያ ምልክት ምንድር ነው? አለ። የዚያችም ከተማ ሰዎች። ከይሁዳ ወጥቶ በቤቴል መሠዊያ ላይ ይህን ያደረግኸውን ነገር የተናገረው የእግዚአብሔር ሰው መቃብር ነው ብለው ነገሩት።
18 ፤ እርሱም። ተዉት፥ ማንም አጥንቱን አያንቀሳቅሰው አለ፤ እነርሱም ከሰማርያ ከወጣው ከነቢዩ አጥንት ጋር አጥንቱን ተዉ።
19 ፤ በሰማሪያም ከተሞች የነበሩትን፥ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ የእስራኤል ነገሥታት የሠሩትን የኮረብታውን መስገጃዎች ኢዮስያስ አስወገዳቸው፥ በቤቴልም እንዳደረገው ነገር ሁሉ እንዲሁ አደረገባቸው።
20 ፤ በዚያም የነበሩትን የኮረብታውን መስገጃዎች ካህናት ሁሉ በመሠዊያዎቹ ላይ ገደላቸው፥ የሰዎቹንም አጥንት በመሠዊያዎቹ ላይ አቃጠለ። ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ።
21 ፤ ንጉሡም ሕዝቡን ሁሉ። በዚህ በቃል ኪዳን መጽሐፍ እንደ ተጻፈው ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ፋሲካ አድርጉ ብሎ አዘዛቸው።
22 ፤ እንደዚህም ያለ ፋሲካ በእስራኤል ላይ ይፈርዱ ከነበሩ ከመሳፍንት ዘመን ጀምሮ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ አልተፈሰከም።
23 ፤ ነገር ግን በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ተፈሰከ።
24 ፤ ደግሞም ካህኑ ኬልቅያስ በእግዚአብሔር ቤት ባገኘው መጽሐፍ የተጻፈውን የሕጉን ቃል ያጸና ዘንድ፥ መናፍስት ጠሪዎቹንና ጠንቋዮቹን ተራፊምንና ጣዖታትንም በይሁዳ አገርና በኢየሩሳሌም የተገኘውን ርኵሰት ሁሉ ኢዮስያስ አስወገደ።
25 ፤ እንደ ሙሴም ሕግ ሁሉ በፍጹም ልቡ በፍጹምም ነፍሱ በፍጹምም ኃይሉ ወደ እግዚአብሔርም የተመለሰ እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ ከእርሱ አስቀድሞ አልነበረም፤ እንደ እርሱም ያለ ንጉሥ ከእርሱ በኋላ አልተነሣም።
26 ፤ ነገር ግን ምናሴ ስላስቈጣው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ከነደደው ከታላቁ ቍጣው ትኵሳት አልተመለሰም።
27 ፤ እግዚአብሔርም። እስራኤልን እንዳራቅሁት ይሁዳን ከፊቴ አርቀዋላሁ፤ ይህችንም የመረጥኋትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና። ስሜ በዚያ ይሆናል ያልሁትን ቤት እጥላለሁ አለ።
28 ፤ የቀረውም የኢዮስያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
29 ፤ በእርሱም ዘመን የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ ከአሦር ንጉሥ ጋር ሊጋጠም ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ወጣ፤ ንጉሡም ኢዮስያስ ከእርሱ ጋር ሊጋጠም ወጣ፤ ፈርዖንም በተገናኘው ጊዜ በመጊዶ ገደለው።
30 ፤ ከሞተም በኋላ ባሪያዎቹ በሰረገላው አድርገው ከመጊዶ ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፥ በመቃብሩም ቀበሩት። የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወሰዱት፥ ቀብተውም በአባቱ ፋንታ አነገሡት።
31 ፤ ኢዮአክስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሦስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ። እናቱም አሚጣል ትባል ነበር፥ እርስዋም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።
32 ፤ አባቶቹም እንዳደረጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
33 ፤ በኢየሩሳሌምም እንዳይነግሥ ፈርዖን ኒካዑ በሐማት ምድር ባለችው በሪብላ አሰረው፤ በምድሩም ላይ መቶ መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ፈሰሴ ጣለበት።
34 ፤ ፈርዖን ኒካዑም የኢዮስያስን ልጅ ኤልያቄምን በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ አነገሠ፥ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠው። ኢዮአክስንም ወስዶ ወደ ግብጽ አፈለሰው፤ በዚያም ሞተ።
35 ፤ ኢዮአቄምም ብሩንና ወርቁን ለፈርዖን ሰጠው፤ እንደ ፈርዖንም ትእዛዝ ገንዘብ ይሰጥ ዘንድ ምድሩን አስገበረ፤ ለፈርዖን ኒካዑም ይሰጥ ዘንድ ከአገሩ ሕዝብ ሁሉ እንደ ግምጋሜው ብርና ወርቅ አስከፈለ።
36 ፤ ኢዮአቄምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ዘቢዳ ትባል ነበር፤ እርስዋም የሩማ ሰው የፈዳያ ልጅ ነበረች።
37 ፤ አባቶቹም እንዳደረጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።

1 ፤ በእርሱም ዘመን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነዖር ወጣ፥ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ተገዛለት፤ ከዚያም በኋላ ዘወር አለና ዐመፀበት።
2 ፤ እግዚአብሔርም የከለዳውያንንና የሶርያውያንን የሞዓባውያንንም የአሞንንም ልጆች አደጋ ጣዮች ሰደደበት፤ በባሪያዎቹ በነቢያት እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ያጠፉት ዘንድ በይሁዳ ላይ ሰደዳቸው።
3 ፤ ምናሴ ስላደረገው ኃጢአት ሁሉ ስላፈሰሰውም ንጹሕ ደም፥ ኢየሩሳሌምንም በንጹሕ ደም ስለሞላ ከፊቱ ያስወግዳቸው ዘንድ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ትእዛዝ በይሁዳ ላይ ሆነ፤
4 ፤ እግዚአብሔርም ይራራ ዘንድ አልወደደም።
5 ፤ የቀረውም የኢዮአቄም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
6 ፤ ኢዮአቄምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ዮአኪን፤ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
7 ፤ የባቢሎንም ንጉሥ ለግብጽ ንጉሥ የነበረውን ሁሉ ከግብጽ ወንዝ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ወስዶ ነበርና የግብጽ ንጉሥ ከዚያ ወዲያ ከአገሩ አልወጣም።
8 ፤ ዮአኪን መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ስምንት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ፤ እናቱም ኔስታ ትባል ነበር፤ እርስዋም የኢየሩሳሌም ሰው የኤልናታን ልጅ ነበረች።
9 ፤ አባቱም እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
10 ፤ በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነዖር ባሪያዎች ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፥ ከተማይቱም ተከበበች።
11 ፤ ባሪያዎቹም በከበቡአት ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናብከደነዖር ወደ ከተማይቱ ወጣ።
12 ፤ የይሁዳም ንጉሥ ዮአኮንና እናቱ፥ ባርያዎቹም፥ አለቆቹም፥ ጃንደረቦቹም ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወጡ፤ የባቢሎንም ንጉሥ በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ያዘው።
13 ፤ የእግዚአብሔርም ቤት መዛግብትን ሁሉ የንጉሡም ቤት መዛግብትን ከዚያ አወጣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን በእግዚአብሔር መቅደስ የሠራውን የወርቁን ዕቃ ሁሉ ሰባበረ።
14 ፤ ኢየሩሳሌምንም ሁሉ፥ አለቆቹንም ሁሉ፥ ጽኑዓን ኃያላኑንም ሁሉ፥ ጠራቢዎቹንም ሁሉ፥ ብረት ሠራተኞቹን ሁሉ አሥር ሺህ ምርኮኞች አፈለሰ፤ ከድሆች ከአገሩ ሕዝብ በቀር ማንም አልቀረም።
15 ፤ ዮአኮንንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ፤ የንጉሡንም እናት፥ የንጉሡንም ሚስቶች፥ ጃንደረቦቹንም፥ የአገሩንም ታላላቆች ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማረከ።
16 ፤ የባቢሎንም ንጉሥ ብርቱዎቹንና ሰልፍ የሚችሉትን ሁሉ፥ ኃያላኑን ሁሉ ሰባት ሺህ ያህል፥ ጠራቢዎችና ብረት ሠራተኞችም አንድ ሺህ፥ ወደ ባቢሎን ማረከ።
17 ፤ የባቢሎንም ንጉሥ የዮአኪንን አጎት ማታንያን በእርሱ ፋንታ አነገሠ፥ ስሙንም ሴዴቅያስ ብሎ ለወጠው።
18 ፤ ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም አሚጣል የተባለች የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።
19 ፤ ኢዮአቄምም እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
20 ፤ ከፊቱ አውጥቶ እስኪጥላቸው ድረስ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ቍጣ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሆኖአልና፤ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።

1 ፤ ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠኝኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፤ በዙሪያዋም ዕርድ ሠሩባት።
2 ፤ ከተማይቱም እስከ ንጉሡ እስከ ሴዴቅያስ እስከ አሥራ አንደኛው ዓመት ድረስ ተከብባ ነበር።
3 ፤ በአራተኛውም ወር በዘጠኝኛው ቀን በከተማይቱ ራብ ጸንቶ ነበርና ለአገሩ ሰዎች እንጀራ ታጣ።
4 ፤ ከተማይቱም ተሰበረች፥ ሰልፈኞችም ሁሉ በሁለት ቅጥር መካከል ባለው በር ወደ ንጉሡ አትክልት በሚወስደው መንገድ በሌሊት ሸሹ፤ ከለዳውያንም በከተማይቱ ዙሪያ ነበሩ፤ በዓረባም መንገድ ሄዱ።
5 ፤ የከለዳውያንም ሠራዊት ንጉሡን ተከታተሉ፥ በኢያሪኮም ሜዳ ያዙት፤ ሠራዊቱም ሁሉ ከእርሱ ተለይተው ተበትነው ነበር።
6 ፤ ንጉሡንም ይዘው የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጡት፤ ፍርድም ፈረዱበት።
7 ፤ የሴዴቅያስንም ልጆች በፊቱ ገደሉአቸው፤ የሴዴቅያስንም ዓይኖች አወጡ፥ በሰንሰለትም አሰሩት፥ ወደ ባቢሎንም ወሰዱት።
8 ፤ በባቢሎንም ንጉሥ በናቡከደነፆር በአሥራ ዘጠኝኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ባሪያ የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።
9 ፤ የእግዚአብሔርንም ቤትና የንጉሡን ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምንም ቤቶች ሁሉ፥ ታላላቆቹን ቤቶች ሁሉ፥ በእሳት አቃጠለ።
10 ፤ ከዘበኞቹም አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት ሁሉ የኢየሩሳሌምን ቅጥር ዙሪያዋን አፈረሱ።
11 ፤ የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን በከተማይቱ ውስጥ የቀረውን ሕዝብ፥ ሸሽተውም ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን፥ የቀሩትንም ሕዝብ አፈለሰ።
12 ፤ የዘበኞቹም አለቃ ከአገሩ ድሆች ወይን ተካዮችና አራሾች እንዲሆኑ አስቀረ።
13 ፤ ከለዳውያንም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የነበሩትን የናስ ዓምዶች፥ በእግዚአብሔርም ቤት የነበሩትን መቀመጫዎችና የናስ ኵሬ ሰባበሩ፥ ናሱንም ወደ ባቢሎን ወሰዱ።
14 ፤ ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹንም መኰስተሪያዎቹንና ጭልፋዎቹንም የሚያገለግሉበትንም የናስ ዕቃ ሁሉ ወሰዱ።
15 ፤ የዘበኞቹም አለቃ ማንደጃዎቹንና መቀመጨዎቹን፥ የወርቁን ዕቃ ሁሉ በወርቅ፥ የብሩንም በብር አድርጎ ወሰደ።
16 ፤ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ቤት የሠራቸውን ሁለቱን ዓምዶች አንዱንም ኵሬ መቀመጫዎቹንም ወሰደ፤ ለእነዚህ ዕቃዎች ሁሉ ናስ ሚዛን አልነበረውም።
17 ፤ የአንዱም ዓምድ ቁመት አሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የናስም ጕልላት ነበረበት፤ የጕልላቱም ርዝመት ሦስት ክንድ ነበረ፥ በጕልላቱም ላይ በዙሪያው የናስ መርበብና ሮማኖች ነበሩ፤ እንዲሁም ደግሞ በሁለተኛው ዓምድ ላይ መርበብ ነበረበት።
18 ፤ የዘበኞቹም አለቃ ታላቁን ካህን ሠራያን ሁለተኛውንም ካህን ሶፎንያስን ሦስቱንም በረኞች ወሰደ።
19 ፤ ከከተማይቱም በሰልፈኞች ላይ ተሾመው ከነበሩት አንዱን ጃንደረባ፥ በከተማይቱም የተገኙትን በንጉሡ ፊት የሚቆሙትን አምስቱን ሰዎች፥ የአገሩንም ሕዝብ የሚያሰልፍ የሠራዊቱን አለቃ ጸሐፊ፥ በከተማይቱም ከተገኙት ከአገሩ ሕዝብ ስድሳ ሰዎች ወሰደ።
20 ፤ የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ወስዶ የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጣቸው።
21 ፤ የባቢሎንም ንጉሥ መታቸው፥ በሐማትም ምድር ባለችው በሪብላ ገደላቸው። እንዲሁ ይሁዳ ከአገሩ ተማረከ።
22 ፤ የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በይሁዳ ምድር በቀረው ሕዝብ ላይ የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን አለቃ አደረገው።
23 ፤ የጭፍሮቹም አለቆች ሁሉ፥ የናታንያ ልጅ እስማኤል፥ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፥ የነጦፋዊውም የተንሑሜት ልጅ ሠራያ፥ የማዕካታዊውም ልጅ ያእዛንያ፥ ሰዎቻቸውም የባቢሎን ንጉሥ ጎዶልያስን እንደ ሾመ በሰሙ ጊዜ ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጡ።
24 ፤ ጎዶልያስም። ከከለዳውያን ሎሌዎች የተነሣ አትፍሩ፥ በአገሩ ተቀመጡ፥ ለባቢሎንም ንጉሥ ተገዙ፥ መልካምም ይሆንላችኋል ብሎ ለእነርሱና ለሰዎቻቸው ማለላቸው።
25 ፤ በሰባተኛው ወር ግን የመንግሥት ዘር የነበረ የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል ከእርሱም ጋር አሥር ሰዎች መጥተው ጎዶልያስንና ከእርሱ ጋር በምጽጳ የነበሩትን አይሁድንና ከለዳውያንን እስኪሞቱ ድረስ መቱአቸው።
26 ፤ ከለዳውያንንም ፈርተው ነበርና ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡ ሁሉ የጭፍሮቹም አለቆች ተነሥተው ወደ ግብጽ መጡ።
27 ፤ እንዲህም ሆነ፤ የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማከረ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያ ሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ዮርማሮዴቅ በነገሠ በአንደኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪንን ከወህኒ አወጣው፤
28 ፤ በፍቅርም ተናገረው፥ ዙፋኑንም ከእርሱ ጋር በባቢሎን ከነበሩት ነገሥታት ዙፋን በላይ አደረገለት።
29 ፤ በወህኒም ውስጥ ለብሶት የነበረውን ልብስ ለወጠለት፤ ዮአኪንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ በፊቱ ሁልጊዜ እንጀራ ይበላ ነበር።
30 ፤ ንጉሡም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ የዘወትር ቀለብ ዕለት ዕለት ይሰጠው ነበር።

Latest News

ilovejesus1.com

My name is Eden Fessehaye and i build ilovejesus1.com website for everyone to have access to the bible and audio bible as well.  There is Amharic, Tigrigna and English bible.  Also, the English bible can be translated to any languages for everyone to have access to...

Trust in Christ and receive Him as your Savior.

Christ is ready. “Here I am! I stand at the door and knock. If anyone hears my voice and opens the door, I will go in” (Revelation 3:20). Receive him now. “Yet to all who received him, to those who believed in his name, he gave the right to become children of God”...

You must repent and ask God for forgiveness.

“He who conceals his sins does not prosper, but whoever confesses and renounces them finds mercy” (Proverbs 28:13).  Forgiveness is promised. “If we confess our sins, he is faithful and just and will forgive us our sins and purify us from all unrighteousness” (1 John...

Jesus Christ died and rose again for our sins.

Jesus Christ died in our place. “But God demonstrates his own love for us in this: While we were still sinners, Christ died for us” (Romans 5:8). He is the way to new life. “Therefore, if anyone is in Christ, he is a new creation; the old has gone, the new has come!”...

Sin separates you from God

Everyone has sinned. “For all have sinned and fall short of the glory of God” (Romans 3:23). Sin brings death. “For the wages of sin is death” (Romans 6:23). “For it is by grace you have been saved, through faith and this not from yourselves, it is the gift of God-not...

Recognize that God loves you

“For God so loved the world that he gave his one and only Son, that whoever believes in him shall not perish but have eternal life” (John 3:16). He has new life for you. “I have come that they may have life, and have it to the full” (John 10:10).

The light of Jesus

Then Jesus again spoke to them, saying, “I am the Light of the world; he who follows Me will not walk in the darkness, but will have the Light of life.” (John 8:12, NASB) While I am in the world, I am the Light of the world.”...

Second Coming of Christ

Revelation 7:14 - “...they are the people who are coming out safely through the terrible tribulation. The blood of the Lamb has washed and made white their robes.” Revelation 19:7 - “They will be Christ's bride and will have...

ilovejesus1.com

My name is Eden Fessehaye and i build ilovejesus1.com website for everyone to have access to the bible and audio bible as well.  There is Amharic, Tigrigna and English bible.  Also, the English bible can be translated to any languages for everyone to have access to...

Trust in Christ and receive Him as your Savior.

Christ is ready. “Here I am! I stand at the door and knock. If anyone hears my voice and opens the door, I will go in” (Revelation 3:20). Receive him now. “Yet to all who received him, to those who believed in his name, he gave the right to become children of God”...

You must repent and ask God for forgiveness.

“He who conceals his sins does not prosper, but whoever confesses and renounces them finds mercy” (Proverbs 28:13).  Forgiveness is promised. “If we confess our sins, he is faithful and just and will forgive us our sins and purify us from all unrighteousness” (1 John...