ትንቢተ ሚልክያ (Malachi)
እሱ ተከታታይ ጅማሬዎችን ያሳያል – የዓለም መጀመሪያ ፣ የሰው ልጅ እና እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የገባውን ቃል ኪዳን። የመጀመሪያው መጽሐፍ ዘፍጥረት በእግዚአብሔር ዓለም ፍጥረት ተከፈተ። የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ባለመታዘዙ የሰው ልጅ ብዛት ወደ ተለያዩ ብሔሮች እና ቋንቋዎች ሲከፋፈል ፍጹምው ዓለም በክፋት ውስጥ ይወድቃል።
ትንቢተ ሚልክያ (Malachi)
1 ፤ በሚልክያስ እጅ ለእስራኤል የሆነ የእግዚአብሔር ቃል ሸክም ይህ ነው።
2 ፤ ወድጃችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተ ግን። በምን ወደድኸን? ብላችኋል። ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ያዕቆብንም ወደድሁ፥ ዔሳውንም ጠላሁ፤
3 ፤ ተራሮቹንም በረሃ አደረግኋቸው፥ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮች አሳልፌ ሰጠኋቸው።
4 ፤ ኤዶምያስ። እኛ ፈርሰናል፥ ነገር ግን የፈረሰውን መልሰን እንሠራለን ቢል፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነርሱ ይሠራሉ፥ እኔ ግን አፈርሳለሁ፤ በሰዎችም ዘንድ። የበደል ዳርቻና እግዚአብሔር ለዘላለም የተቈጣው ሕዝብ ይባላል።
5 ፤ ዓይኖቻችሁም ያያሉ፥ እናንተም። እግዚአብሔር ከእስራኤል ዳርቻ ወዲያ ታላቅ ይሁን ትላላችሁ።
6 ፤ እናንተ ስሜን የምታቃልሉ ካህናት ሆይ፥ ልጅ አባቱን፥ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፤ እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተም። ስምህን ያቃለልን በምንድር ነው? ብላችኋል።
7 ፤ በመሠዊያዬ ላይ ርኩስ እንጀራ ታቀርባላችሁ። እናንተም። ያረከስንህ በምንድር ነው? ብላችኋል። የእግዚአብሔር ገበታ የተነቀፈ ነው በማለታችሁ ነው።
8 ፤ ዕውር መሥዋዕትንም ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? አንካሳውንና የታመመውን ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? ያንን ለአለቃህ አቅርብ፤ በውኑ በአንተ ደስ ይለዋልን? ወይስ ፊትህን ይቀበላልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
9 ፤ አሁንም ጸጋን ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔርን ለምኑ፤ ይህ ከእጃችሁ የተሰጠ ሲሆን ከቶ ፊታችሁን ይቀበላልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
10 ፤ በመሠዊያዬ ላይ እሳትን በከንቱ እንዳታቃጥሉ ከእናንተ ዘንድ ደጅ የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ! በእናንተ ደስ አይለኝም፥ ቍርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
11 ፤ ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፤ በየስፍራውም ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፥ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
12 ፤ እናንተ ግን። የእግዚአብሔር ገበታ ርኩስ ነው፤ ፍሬውና መብሉም የተናቀ ነው በማለታችሁ አስነቀፋችሁት።
13 ፤ እናንተ። እነሆ፥ ይህ ድካም ነው ብላችሁ ጢቅ አላችሁበት፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ በቅሚያ የያዛችሁትንም አንካሳውንም የታመመውንም አቅርባችኋል፤ እንዲሁ ቍርባንን ታመጣላችሁ፤ በውኑ ከእጃችሁ ይህን ልቀበለውን? ይላል እግዚአብሔር።
14 ፤ እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ስሜም በአሕዛብ ዘንድ የተፈራ ነውና በመንጋው ውስጥ ተባት እያለው ለጌታ ተስሎ ነውረኛውን የሚሠዋ ሸንጋይ ሰው ርጉም ይሁን።
1 ፤ አሁንም እናንተ ካህናት ሆይ፥ ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው።
2 ፤ ለስሜ ክብር ትሰጡ ዘንድ ባትሰሙ፥ በልባችሁም ባታደርጉት፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እርግማን እሰድድባችኋለሁ፥ በረከታችሁንም እረግማታለሁ፤ አሁንም በልባችሁ አላደረጋችሁትምና እኔ ረግሜአታለሁ።
3 ፤ እነሆ፥ ክንዳችሁን እገሥጻለሁ፥ የመሥዋዕታችሁንም ፋንድያ በፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ ከእርሱም ጋር በአንድነት ትወሰዳላችሁ።
4 ፤ ቃል ኪዳኔ ከሌዊ ጋር ይሆን ዘንድ ይህን ትእዛዝ እንደ ሰደድሁላችሁ ታውቃላችሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
5 ፤ ቃል ኪዳኔ ከእርሱ ጋር የሕይወትና የሰላም ቃል ኪዳን ነበረ፤ ይፈራ ዘንድም እነርሱን ሰጠሁት፤ እርሱም ፈራኝ፥ ከስሜም የተነሣ ደነገጠ።
6 ፤ የእውነት ሕግ በአፉ ውስጥ ነበረች፥ በከንፈሩም ውስጥ በደል አልተገኘበትም፤ ከእኔም ጋር በሰላምና በቅንነት ሄደ፥ ብዙ ሰዎችንም ከኃጢአት መለሰ።
7 ፤ ካህኑ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና ከንፈሮቹ እውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባቸዋል፥ ሰዎችም ሕግን ከአፉ ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል።
8 ፤ እናንተ ግን ከመንገዱ ፈቀቅ ብላችኋል፤ በሕግም ብዙ ሰዎችን አሰናክላችኋል፤ የሌዊንም ቃል ኪዳን አስነውራችኋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
9 ፤ ስለዚህ መንገዴን እንዳልጠበቃችሁ፥ በሕግም ለሰው ፊት እንዳዳላችሁ መጠን፥ እኔ ደግሞ በሕዝብ ሁሉ ፊት የተናቃችሁና የተዋረዳችሁ አድርጌአችኋለሁ።
10 ፤ ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን? የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን ለማስነቀፍ እኛ እያንዳንዳችን ወንድማችንን ስለ ምን አታለልን?
11 ፤ እግዚአብሔር የወደደውን መቅደስ ይሁዳ አርክሶአልና፥ የእንግዳውንም አምላክ ልጅ ሚስት አድርጎ አግብቶአልና ይሁዳ አታልሎአል፥ በእስራኤልና በኢየሩሳሌም ውስጥ ርኵሰት ተሠርቶአል።
12 ፤ ይህን ከሚያደርግ ሰው፥ እግዚአብሔር የሚጠራውንና የሚመልሰውን ለሠራዊትም ጌታ ለእግዚአብሔር ቍርባን የሚያቀርበውን ከያዕቆብ ድንኳን ያጠፋል።
13 ፤ ይህንም ደግሞ አድርጋችኋል፤ እግዚአብሔር ቍርባኑን ዳግመኛ እንዳይመለከት፥ ከእጃችሁም በደስታ እንዳይቀበለው መሠዊያውን በእንባና በልቅሶ በኀዘንም ትከድናላችሁ።
14 ፤ እናንተም። ስለ ምንድር ነው? ብላችኋል። ሚስትህ ባልንጀራህና የቃል ኪዳንህ ሚስት ሆና ሳለች እርስዋን አታልለሃታልና እግዚአብሔር በአንተና በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለ ሆነ ነው።
15 ፤ እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ አንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን? እርሱም የሚፈልገው ምንድር ነው? ዘር አይደለምን? ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ፥ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል።
16 ፤ መፋታትን እጠላለሁ፥ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፥ ልብሱንም በግፍ ሥራ የሚከድነውን ሰው እጠላለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ እንዳታታልሉ መንፈሳችሁን ጠብቁ።
17 ፤ እግዚአብሔርን በቃላችሁ አታክታችኋል። እናንተም። ያታከትነው በምንድር ነው? ብላችኋል። ክፉን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ መልካም ነው፥ እርሱም በእነርሱ ደስ ይለዋል፤ ወይስ። የፍርድ አምላክ ወዴት አለ? በማለታችሁ ነው።
1 ፤ እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፤ እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፤ የምትወዱትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
2 ፤ ነገር ግን እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው? እርሱስ በተገለጠ ጊዜ የሚቆም ማን ነው?
3 ፤ እርሱም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፥ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፥ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቍርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ።
4 ፤ እግዚአብሔርም እንደ ዱሮው ዘመንና እንደ ቀደሙት ዓመታት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ቍርባን ደስ ይለዋል።
5 ፤ ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በመተተኞችና በአመንዝሮች፥ በሐሰትም በሚምሉ፥ የምንደኛውን ደመወዝ በሚከለክሉ፥ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን በሚያስጨንቁ፥ የመጻተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
6 ፤ እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ ስለዚህ የጠፋችሁ አይደላችሁም።
7 ፤ ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምር ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፥ እርስዋንም አልጠበቃችሁም። ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተ ግን። የምንመለሰው በምንድር ነው? ብላችኋል።
8 ፤ ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል። እናንተም። የሰረቅንህ በምንድር ነው? ብላችኋል። በአሥራትና በበኵራት ነው።
9 ፤ እናንተ፥ ይህ ሕዝብ ሁሉ፥ እኔን ሰርቃችኋልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ።
10 ፤ በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ፤ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፥ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
11 ፤ ስለ እናንተ ነቀዙን እገሥጻለሁ፥ የምድራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፤ በእርሻችሁም ያለው ወይን ፍሬውን አያረግፍም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
12 ፤ የተድላ ምድር ትሆናላችሁና አሕዛብ ሁሉ ብፁዓን ብለው ይጠሩአችኋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
13 ፤ ቃላችሁ በእኔ ላይ ድፍረት ሆኖአል፥ ይላል እግዚአብሔር። እናንተ ግን። በአንተ ላይ ደፍረን የተናገርነው በምንድር ነው? ብላችኋል።
14 ፤ እናንተም። እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ ትእዛዙንስ በመጠበቅ፥ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ፊት ኀዘንተኞች ሆነን በመሄድ ምን ይረባናል?
15 ፤ አሁንም የሚታበዩትን ሰዎች ብፁዓን ብለን እንጠራቸዋለን፤ ክፉንም የሚሠሩ ጸንተዋል እግዚአብሔርንም ይፈታተናሉ፥ ያመልጣሉም ብላችኋል።
16 ፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም አደመጠ፥ ሰማም፥ እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።
17 ፤ እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የእኔ ገንዘብ ይሆናሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ሰውም የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚምር፥ እንዲሁ እምራቸዋለሁ።
18 ፤ ተመልሳችሁም በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፥ ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል ትለያላችሁ።
1 ፤ እነሆ፥ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፥ ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
2 ፤ ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፥ ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል፤ እናንተም ትወጣላችሁ፥ እንደ ሰባም እምቦሳ ትፈነጫላችሁ።
3 ፤ በምሠራበት ቀን በደለኞች ከእግራችሁ ጫማ በታች አመድ ይሆናሉና እናንተ ትረግጡአቸዋላችሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
4 ፤ ለእስራኤል ሁሉ ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌ በኮሬብ ያዘዝሁትን የባሪያዬን የሙሴን ሕግ አስቡ።
5 ፤ እነሆ፥ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ።
6 ፤ መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል።
Latest News
ilovejesus1.com
My name is Eden Fessehaye and i build ilovejesus1.com website for everyone to have access to the bible and audio bible as well. There is Amharic, Tigrigna and English bible. Also, the English bible can be translated to any languages for everyone to have access to...
Trust in Christ and receive Him as your Savior.
Christ is ready. “Here I am! I stand at the door and knock. If anyone hears my voice and opens the door, I will go in” (Revelation 3:20). Receive him now. “Yet to all who received him, to those who believed in his name, he gave the right to become children of God”...
You must repent and ask God for forgiveness.
“He who conceals his sins does not prosper, but whoever confesses and renounces them finds mercy” (Proverbs 28:13). Forgiveness is promised. “If we confess our sins, he is faithful and just and will forgive us our sins and purify us from all unrighteousness” (1 John...